spot_img
Saturday, September 30, 2023
Homeነፃ አስተያየትለሁላችንም የእኩል እናት እና ቤት የሆነች ኢትዮጵያ ነው የምታስፈልገን!!

ለሁላችንም የእኩል እናት እና ቤት የሆነች ኢትዮጵያ ነው የምታስፈልገን!!

advertisement

Ethiopia for all of us

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን.)

እንደ መንደርደሪያ

ከሰሞኑን ለአንድ የቢሮ የመስክ ሥራ የሶማሊ ክልል መስተዳድር ዋና ከተማ በሆነችው ጅግጅጋ ነው ያለሁት። ታዲያ አንድ ምሽት ላይ ከመሃል ከተማው ወደ አረፍኩበት ሆቴል እንዲወስደኝ ከተሳፈርኩበት የባጃጅ አሸከርካሪ ጋር የትውውቅ ሰላምታ አደረገን ነበር። በነገራችን ላይ ከተማ ውስጥ ለመንቀሳቀስ አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀመው ባጃጅና “Force” የሚባል ከባጃጅ ከፍ የሚል የታክሲ አገልግሎት በሚሰጥ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ነው። እናም ከዚህ የባጃጅ አሽከርካሪ ወጣት ጋር ከትውውቃችንና የሰላምታ ጥቂት የቃላት ልውውጣችን የባጃጁ ባለቤትና ሹፌር የሆነ ወጣት ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጣ፤ ትግራዋይ እንደሆነ ተረዳሁኝ።

ባለፉት የሁለት ዓመት የእርስ በርስ አሰቃቂ ጦርነት በብዙ ዋጋ የከፈለችውን ትግራይን በአእምሮዬ እያመላለስኩ፤ የባጃጁን ሹፌር ወደ ጅግጅጋ መቼና እንዴት እንደመጣ ጠየኩት። ወጣቱ የትግሪኛ ቅላጼ በተጫነው አማርኛ ወደ ጅግጅጋ እንዴት እንደመጣና ስለ ቆይታው እንዲህ አወጋኝ፤

“… ከትግራይ መጥቼ አዲስ አበባ፣ ቃሊቲ ሰፈር ለ5 ዓመት ባጃጅ ላይ ነበር የሠራሁት። ባለፈው ጊዜ ከተማ ውስጥ ባጃጅ አትሠሩም ብለው ሲከልክሉን ባጃጄን ሽጬ እዚህ ሶማሊ ክልል፣ ጅግጅጋ መጣሁ። እዚህ ከትግራይ የመጡ ሁለት ጓደኞች አሉኝ። እናም እዚህ ና ከእኛ ጋር ትሠራለህ ሲሉኝ መጣሁ። ወደዚህ ከመጣሁ ገና ሁለት ወሬ ነው። ግን ዋአይ ለሥራም ለኑሮም ከአዲስ አበባ ይልቅ ጅግጅጋ ትሻላለች። የኑሮ ውድነቱ ቢከብድም ወንድሜ ጅግጅጋ ለኑሮ ጥሩ ናት አለኝ…።” በፈገግታ በታጀበ ድምፀት።

መቼ ይሆን ለሁላችንም እኩል እናትና ቤት የሆነች የኢትዮጵያን በተግባር እውን የምናደርገው?!

ከዚህ ትግራዋይ የባጃጅ ሹፌር ጋር ያደረግነውን የሐሳብ ልውውጥ እያወጣሁና እያወረድኩ… መቼ ይሆን ያለ ምንም ሰቀቀንና ሥጋት ሁሉም ኢትዮጵያ በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ መኖርና መሥራት የሚችልበት ሙሉ ነጻነት የሚኖረው?! አልኩ… ይሄ የባጃጅ አሽከርካሪ ከተወለደባት ምድር ትግራይ ይልቅ አዲስ አበባ ትሻለኛለች ብሎ ሸገር ላይ ከተመ። አዲስ እንደፈለገው ሳትሆንለት ስትቀር ደግሞ “ምን ዕዳ አለብኝ?!” ኢትዮጵያዊ አይደለሁ እንዴ ብሎ ከአዲስ አበባ ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዞ ሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ላይ ኑሮውን መሠረተ።

በቀደመው ዘመን የዚህን ወገናችንን የኑሮ ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ዛሬ ግን ይህን የአብሮነት ታሪካችንን በነበር እናስታውሰው ዘንድ ተገደናል። በእኛ ዘመን ያለንበትን አስፈሪ እውነታ ስንታዘብ (በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን- አባቶች፣ እናቶች፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና ሕፃናት የሰቆቃ ድምፅ በጆሮዬ እያቃጨለና የመከራ ሕይወታቸው ፊቴ ላይ ድቅን ብሎ እየታየኝ- የትናትናው የአብሮነት ታሪካችን፤ በኢትዮጵያዊነት ፍቅርና አንድነት መንፈስ የተሳሰርንበት ውሉ እንዲህ መላላቱ፣ መሳሳቱ አስተከዘኝ።

ለነገሩማ ተግባራዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የወደቀም ቢሆንም ቅሉ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ግን ከላይ ባነሳሁት ገጠመኜ በተንደረደርኩበት ሐሳብ ጋር በተያያዘ እንዲህ የሚል ድንጋጌ/አንቀጽ አለው።

ማንኛውም ሰው በማንኛውም ስፍራ በሰብአዊነቱ እውቅና የማግኘት መብት አለው፤ (አንቀጽ 24 ቁ. 3) በሌላ ስፍራም፤ “ማንኛውም ኢትዮጵያ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመንቀሳቀስ፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት እንዳለው፤” ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ የዛሬዋ ኢትዮጵያችን እውነታ ግን ከዚህ በጣሙን የተለየ ከሆነ ሰነባብቷል። እናም ያለፉትን ዓመታት የእናት ኢትዮጵያን ስቃይዋን፣ የሕዝቦቿን ሰቀቀንና መከራ ቆም ብለን ማሰላሰል ያስፈልገናል።

“… ከክልላችን ውጡልን፣ ይህ አለን የምትሉት ሀብትና ንብረት ሁሉ በእኛ መሬት ላይ ያፈራችሁት ሀብት ነውና ሰባራ ሳንቲም ከክልላችን ይዛችሁ መውጣት አትችሉም፤ ይህና ያ ሕዝብማ እንዲህ አድርጎናል… እናንተና እኛ እኮ…” በሚል ተአማኒነቱ ባልተረጋገጠ የቂም በቀል ታሪክና የብሔር/የዘውግ/የጎሳ ፖለቲካ ነጋዴዎች/Ethnic Enterpreuner የጥላቻ ትርክት በግፍ የተገደሉ፣ በጅምላ የተጨፈጨፉ፣ በአንድ ጀምበር ሀብት ንብረታቸው ለእሳት የተዳረገባቸው፣ ሀገሬ/ወገኔ ብለው ከኖሩበት ቀዬ በግፍ የተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የግፉአን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን የሰቆቃ ድምፅ፣ መከራና ሰቆቃቸውን ማሰላሰል ያዝኩኝ።

በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ይህን ጽሐፍ እየከተብኩበት ባለሁበት ካፌ በረንዳ ላይ ከአገረ ሶሪያ በእርስ በርስ ጦርነት ጦስ ተፈናቅለው- ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ ሀገራችን የመጡ ሁለት ሶሪያውያን እናቶች መንገድ አቋርጠው በካፌው በረንዳ ላይ ወደተቀመጥን ተስተናጋጆች ሲመጡ ታዩኝ።

አንደኛዋ እናት በግምት የ6 ዓመት ዕድሜ ያላትን ሕፃን ልጇን ጭምር የሚሸጡ ዕቃዎችን አስይዛ በካፌው የሚስተናገዱ ሰዎች እንዲገዟቸው አንጀትን በሚያንሰፈስፍ ሁኔታ ተስተናጋጆችን በዓይናቸው ይለማመጣሉ። ሌላኛዋ ሶርያዊት እናት ደግሞ በእቅፍዋ ያለችውን ጸሐይ ያዛላቸውን ሁለት ሕጻናትን በእቅፏና በእጇ ይዛ ወዲህና ወዲህ እያለች ለልመና እጇን እየዘረጋች ነው። የጽሐፌ መነሻ ሐሳብና ይህ ግጥጥሞሽ ገረመኝ።

እናም እኛስ ብንሆን ፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንና ቁርቁሳችንን ገደብ ካላደርግንበት አሁን በተያያዝነው የእልኽና የመጠፋፋት መንገድ የነገ ዕጣ ፈንታችን እንደ እነዚህ ሶሪውያን ስደተኞች ላለመሆናችን ምን ዋስትና ይኖረናል?!

እንደሚታወቀው በአንድ ወቅት በእርስ በርስ ጦርነት ከፈራረሱት የመንና ሶሪያ በልጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሀገር ውስጥ መፈናቀል/Internal Displacement የአንደኝነት ረድፍ የያዝንበት ታሪካችን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት/UN – IOM National Displacement Report 12- እ.አ.አ. በመጋቢት ወር 2022 ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 2.75 ሚሊዮን መድረሱን አመላክቶ ነበር። አንባቢዎቼ ይህ ሪፖርት የትግራይ ክልልን እንደማያካትት ልብ ይሏል።

እንግዲህ ይህ ሪፖርት የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ሰቆቃ የሚያሳይ መሬት ላይ በተጨባጭ ያለ ሐቅ ነው። ዛሬም በመፈናቀል ሥጋት ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ቁጥር ጥቂት አይደለም። ግና መቼ ይሆን ከላይ በገጠመኜ ለማንሳት እንደ ሞከርኩት ከሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ እንደመጣው የባጃጅ ሹፌር ሁሉ፤ በዚህ ዘመን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ቦታና አካባቢ የመኖር፤ የመንቀሳቀስና ሀብት የማፍራት መብቱ እንዲከበር ከቃል ያለፈ ተግባር ማየት የምንችለው?!

መቼ ነው ለሁሉም በእኩልነት እናትና ቤት የሆነች ኢትዮጵያን ዕውን የምናደርገው?! ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በማንነታቸውና በቋንቋቸው የተነሳ የሚደርስባቸው ግፍ፣ ግድያና መፈናቀል ዛሬም በአንድ ድምፅ- በቃ! እረ በቃ! ሊባል ይገባዋል።

እንደ መውጫና መደምደሚያ

ጠረፋማ የሚባሉ እንደ ሶማሌና ጋምቤላ ያሉ ክልሎች ከአጎራባች ሀገራት የሚጋሯቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ከታሪክ እስከ ባህል፤ ከቋንቋ እስከ ጎሳ ዝምድና፤ ከንግድ ትስስር እስከ የጋራ ማንነትና ሥነ-ልቦና ድረስ በብዙ ነገር የተጋመደና የተሰባጠረ ሕዝብ ነው ያለባቸው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ከሌላው አጎራባቹ ሶማሊያ ሕዝብ ጋር በብዙ ነገር ላይለያይ የተሳሰረ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን በሶማሊ ክልል ከሀገራችን ኢትዮጵያ ከአራቱም ማእዘን የመጡ የተለያዩ ሕዝቦች በሰላም ይኖራሉ።

እንደውም ጅግጅጋ ምድር ላይ “የሐበሻ ሰፈር” የሚባል ሁሉ አለ። በዚህ ሰፈር ውስጥ በአብዛኛው ወይም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ሕዝቦች ናቸው የሚኖሩበት (ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግራዋዩ፣ ወላይታው፣ ሐረሪው ወዘተ.)። ታሪኩ፣ ሃይማኖቱ፣ ባህሉ፣ ንግዱ፣ የማኅበራዊ ኑሮውና ሥነ-ልቦናዊ መስተጋብሩ … ወዘተ ላይለያይ አስተሳስሮታል።

እናስ መቼ ነው ለሁሉም በእኩልነት እናትና ቤት የሆነች ኢትዮጵያን ዕውን የምናደርገው?! ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በማንነታቸውና በቋንቋቸው የተነሳ የሚደርስባቸው ግፍ፣ ግድያና መፈናቀል ማብቂያው መቼ ይሆን…?! ዛሬም ይህ የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ግፍና ሰቆቃ በአንድ ድምፅ- በቃ! እረ በቃ! ሊባል ይገባዋል።

እናም ዛሬም ነገም የምንመኛት ኢትዮጵያ- ለዜጎቿ/ለሁላችንም የእኩል እናት እና ቤት የሆነች አገር መሆን ይኖርባታል!!

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,707FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here