
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ ሃምሌ 11 ቀ 2015 ዓ ም
“መነጽር ይገዛል ሞኝ የጨዋ ልጅ
ሁሉን የሚያሳየው መሰንበት ነው እንጂ”።
መሰንበት ደጉ ከሚለው የአቶ ሳሙኤል ፈረንጅ የግጥም መድብል የፊት ሽፋን ላይ የተወሰደ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ፈተናና ችግር አልፋለች፤ ዛሬም ከባድ የሚባል ፈታን ገጥሟታል። ችግሩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ሕጋዊ መፍትሔ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሔ እየተፈለገ በመሆኑ ነው። ልክ እንዳሁኑ ችግር፤ አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግርና ፈተናዋ ከውስጥ የመነጨ እንጂ፤ ብዙዊች እንድሚሰብኩን ከውጪ የመጣ አይደለም። ቤተክርስቲያኗ ለረጅም ጊዜ የፖለቲካ መጠቀምያ ሆና ለነገስታት አገልግላለች። የወታደራዊው መንግሥት፤ ቤተክርስቲያንን ከመንግስት እስከለየበት ጊዜ ድረስም፤ በመንግስታዊ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና የማድረግ አቅም እንደነበራት የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። የሕወሃት መራሹ መንግሥት በግንቦት 1983 ሥልጣን ሲይዝ፤ ፓትርያርክ በመሾም ጭምር በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደ ነበርና የቤተ ከርስቲያኒቱን አመራር ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ እንደተጠቀመበት የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሕወሃት መራሹ መንግሥት በቤተክርስቲያኒቱ ሥራ ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከፈላ ከ25 ዓመታት በላይ በውዝግብ ቆይታለች። በዘልማድ ለሶስት ተከፈለ እንበል እንጂ በተለይ በሰሜን አሜሪካ ለአምስት የተከፈለ ነበር። ከነዚህም ውስጥ በዋሽንግተንና አካባቢው የሚገኘው፤ የትግራይ ተወላጆች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና የኦሮሞ ተወላጆች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይገኛሉ።
ሕወሃት ስልጣን ሲይዝ፤ የቤተክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ ከሃገር አሳዶ፤ እራሱ የፈለገውን ፓትርያሪክ ባመሾሙ፤ አብዛኛው በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተከታይ፤ “ስደተኛው ሲኖዶስ” የሚል ሥያሜ የተሰጠው በብፁእ አባ መርቆርዮስ የሚመራውን ሲኖዶስ በመከተል፤ የተለያዩ ቤተክርስቲያናትን አቋቋመ። በአባ ጳውሎስ የሚመራው በሃገር ውስጥ የነበረው ሲኖዶስ ደግሞ፤ በተለያዩ ውጭ ሃገራት ያለውን መዋቅር ተጠቅሞ ሃገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናትን አስፋፋ። ከሁለቱም ገለልተኛ የሆኑ ደግሞ አቋም ያልወሰዱ ቤተ ክርስቲያናትም ተመሰረቱ። ከነዚህም የሚታውቀው አንዱ፤ በአባ መላኩ (አሁን አባ ፋኑኤል) የሚመራው፤ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነበር። በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶችም፤ ከሁለቱም ያልወገኑ ካህናት፤ የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን በማቋቈም፤ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምዕመኑን ውጥረት ውስጥ ከተውት እንደነበር እናስታውሳለን። በተለይ ውጭ “ስደተኛው” ተብሎ በሚታወቀው ሲኖዶስ ውስጥ፤ የፖለቲከኞች አሻራ ፈጦ የታየበትና፤ በየቤተ ክርስቲያኑ “ኮሚቴ” ውስጥ የነበሩ ፖለቲከኞች፤ ዓላማቸውን ለማያስፈጽሙና ለማይደግፉ ካህናትና ቄሳውስት፤ ደሞዝ እስከ መከልከል የደረሱበት አሳፋሪ ኩነት እንደነበረም ይህ ጸሃፍ ያስታውሳል። በተለይ ክሁለቱም ሲኖዶስች እራሳቸውን ያገለሉ ቤተ ክርስቲያኖች፤ በቅዱስ ፓትርያሪኩ አባ መርቆርዮስ (ነፍሳቸውን ይማር) የሚመራው ሲኖዶስ ሥር እንዲሆኑ ይደረግባቸው የነበረ ግፊት እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ፤ የክርስትናን መርሆ የጣሰ ነበር። አባ መላኩን ለማዋረድና ለመጫን የተሄደበት መንገድም ስደተኛው ሲኖዶድስ ላይ የነበረውን የፖለቲከኞች የእጅ ጥምዘዛ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነበር። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም. ይህ ፀሃፍ፤ በጊዜው ይሰራበት በነበረ የሕብረት ሬድዮ አማካኝነት ከአባ መላኩ ጋር ቃለ ምልልስ የማድረግ እድልና ክብር አግኝቷል። በዛ ቃለ ምልልስም፤ በቤተክርስቲያኑ አባቶች መካከል የነበረው ልዩነትና ግጭት ፍንትው ተደርጎ የታየበት ነው። ይህንንም ተከትሎ’ በወቅቱ ይህ ፀሃፍ፤ ከሕብረት ሬድዮ ጋር በመሆን፤ ብፁአን አባቶች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ያደረገው ጥረት፤ በእነ አባ ይስሃቅ፤ አባ ዜና ማርቆስና ሌሎች አባቶች እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል። በሰሜን አሜሪካ ለትግራይና ለኦሮሞ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም መመስረት ዋናው ምክንያት የፖለቲከኞች እጅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነከሩ ብቻ ሳይሆን፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም እጃቸውን ከፖለቲካ ማንሳት ስላልፈቀዱ ነው።
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም፤ ይህ ፀሃፍ ያዘጋጀው በነበረ ልዩ ሬድዮ በተባለ ጣብያ፤ ከአባቱ ከአቶ ሳሙኤል ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮት ያደጉ ብቻ ሳይሆኑ፤ በልጅነታቸው በድቁና ያገለገሉ ነበሩ። በ1993 ዓ.ም ስለ ቤተክርስቲያኗ ከዚህ ፀሃፍ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ በቶሮንቶ ካናዳ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሰረት ጥረት ከሚያደርጉት ሰዎች አንዱ ነበሩ። በወቅቱ ከተናገሩት ውስጥ አሁንም በዚህ ፀሃፍ አእምሮ ውስጥ የሚደውል አንድ ነገር አለ። አቶ “ድሮ ድሮ፤ እኛ ስንጣላ፤ ገስፀው የሚያስታርቁን አባቶች ነበሩ፤ አባቶች ሲጣሉ ግን የሚገስጽና የሚያስታርቃቸው ማን ነው?” የሚለው የአቶ ሳሙኤል ጥያቄ አሁንም ወቅቱን የሚመጥን ጥያቄ ነው። አዎ፤ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ገሳጭና ተቆጪ እንዲሁም አስታራቂ በማጣታቸው ክፍፍሉና ውዝፍቡ ከ25 ዓመታት በላይ ፈጀ። ይህ ውዝግብ የተቋጨው፤ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ነበር። ያም ሆኖ ግን አባቶች እጃቸውን ከፖለቲካው ላይ ያላነሱ በመሆናቸውና፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር፤ ችግሯን በሕግ ሂደት ለመፍታት ቁርጠኝነት ስለጎደለው፤ ይኽው ዛሬም ቤተክርስቲያኒቱ ከውዝግብ አልዳነችም።
ቤተክርስቲያኒቱን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም መሳሪያ ለማድረግ ሌት ተቀን የሚባዝኑ ኃይሎች፤ እንደ መዥገር ተጣብቀውባት፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ሲመሯቸውም በትዝብት እያየን ነው። ምእመኑ ቆም ብሎ በማሰብ፤ የአባቶችን ስሕተት ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ፤ ፖለቲከኛውና የማህበረሰብ አንቂ የተባለው የማህበረሰብ አደንዛዥ በሚቀድለት ቦይ እንደ ውኃ ይፈሳል። “ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሴራ ተተብትቧል” የሚለውን የደም ነጋዴ ተቀብሎ እንደ ገደል ማሚቱ ከማስተጋባት ውጭ፤ ለምን፤ እንዴት ብሎ እንኳን አይጠይቅም። ሃይማኖትን ተጠቅመው የብሔር ግጭት ለማስነሳት ተግተው የሚሰሩ የዩቲዩብ ሳንቲም ለቃሚዎችን ወሬ ከመቀባብለ ይልቅ የችግሩ ምንጭ ምንድነው ብሎ ለመጠየቅ እንኳን ድፍረት አጥቷል። ብፁእ ፓትርያሪኩ፤ “በትግራይ በአለም ታይቶ የማይታውቅ በደል ተፈጽሟል” ብለው በአደባባይ ሲናገሩና፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ ትጠይቃለች ሲሉ፤ በምን ምክንያት ብሎ አይጠይቅም። የትግራይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቡድን፤ የሕወሃትን የጥፋት ሰራዊት መርቆና ባርኮ ሲልክ ዓይናቸውን የጨፈኑ አባቶች፤ ሕወሃት የሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሲፈጽም የተባበሩ አባቶች፤’ የሕወሃትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በቤተ ክርስቲያን የደበቁ አባቶች፤ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት፤ የሕወሃትን ዕብሪተኛ አመራር ለመገሰጽ ወኔያቸው የተሰለበ የትግራይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፤ የትግራይንም ሆነ የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው፤ ዛሬ እነሱ ከበላይ ሆነው፤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጄኖሳይድ ፈጽማለች” ብለው በአደባባይ ሲከሱና እናቶችን እንዲህ ዓይነት መፈክር አሲዘው አደባባይ ሲያስወጡ፤ ዝምታን የመረጠው ሲኖዶስ “የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” በማለት እጁን ፖለቲካ ውስጥ ያስገባን የሲኖዶስ አመራር ደፍሮ ለምን ብሎ ለመጠየቀ ያልደፈረ ምዕመን፤ የቤተ ክርስቲያኗ መሰረታዊ ችግር ከአባቶች አለመግባባትና ደካማ አመራራ መሆኑን ለመቀበል የማይፈልግ ምዕመን ነው። በሽታው ሳይታወቅ የሚዋጥ መድሃኒት በሽተኛውን በክፉ ሁኔታ እንደሚጎዳ፤ ከሲኖዶድሱ መማር እንችላለን።
ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሕግን ብቻ በመጠቀም መብቷን ማስከበር ሲገባት፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመረጡት፤ በትንሹም በትልቁም ወጀብ በመፍጠር፤ በሃገር ውስጥ ውጥረት መፍጠርን ነው። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ፤ ሲኖዶሱ፤ የሕግ ክፍል እንዳለው ቢነግረንም፤ ሕጋዊ እርምጃ ሲወስድ ያየነው፤ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በመግለጫ ጋጋታ ውጥረት ከመፍጠርና ምዕመናንን አላስፈላጊ በሆነ ነውጥ እንዲሳተፉ ከማድረግ፤ ሕግን የተከተለ እርምጃ መውሰድ ቢቻል፤ አሁን የምናያቸው ውዝግቦች ባልተፈጠሩ ነበር። በቅርቡ የኦሮምያ ክልልን አስመልክቶ በተነሳው ውዝግብ፤ በመግለጫ ጋጋታ ሕዝብን ከማጨናነቅና ከመንግስትም ጋር አላስፈላጊ አታካራ ውስጥ ከመግባት ይልቅ፤ ከሲኖዶሱ ያፈነገጡት የኦሮም አባቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ዛሬም ለትግራይ ክልል አባቶች አስተማሪ በሆነና ሌላውም ክልል በዚህ ጉዳይ ላይ ትምህርት በወሰደ ነበር። ሆኖም፤ እጁን በፖለቲካ የነከረው የሲኖዶስ አመራርና፤ ሲኖዶሱን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የፈለጉ ኃይሎች ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት የሄዱበት መንገድ አሳፋሪና የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፈ ነው። ከኦሮሞ የክርስትና አባቶች ጋር በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት፤ ችግሩን ለመፍታት ያ ሁሉ ወጀብ የሚያስፈልገው አልነበረም። ከሕግ አኳያ፤ እነዚያ አባቶች፤ የራሳቸው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማቋቋም ሙሉ ሕጋዊ መብት አላቸው። የላቸውም የሚል ካለ ሕግ ጠቅሶ ይሟገት። ሕጉ የማይፈቅድላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብለው በዚህ ስም ቤተክርስቲያን ማቋቋም ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ሥልጣንና መብት ያላት ስሙ ላይ ብቻ ነው እንጂ አጠቃላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ላይ አይደለም። የኦሮሞ የቤተክርስቲያን አባቶች ከሲኖዶሱ ጋር የተጋጩት በጥቅም ነው። ይህ በአባቶች መካከል የተፈጠረ ግጭት እንጂ፤ የዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ጣልቃ የገባበት ችግር አይደለም። ይህንን የሲኖዶሱ አባቶች በሚገባ ያውቃሉ። ዶ/ር ዐብይ ጣልቃ የገቡት ለማስታረቅ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ሲኖዶሱ፤ ከትግራይ አባቶች ጋር በተፈጠረው ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበው። በርግጥ ጽንፈኛው ኃይል በሃሰት እንደሚሰብከው፤ ዶ/ር ዐብይ ኦርቶዶክስ ክርስቲያንን የመክፈል ዓላማ ካላቸው፤ ለምንድ ነው ሲኖዶሱ አሁን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስታራቂነት ሚና እንዲጫወቱ የሚጠራቸው?
የቤተክርስቲያኒቱ የኦሮሞ አባቶች፤ ከሲኖዶሱ ሕገ ደንብ ውጭ ሲያፈነግጡ፤ ሲኖዶሱ ማድረግ የነበረበት፤ 1፣ እነዚህ አባቶች በየትኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርሲያን ውስጥ እንዳይገቡ። 2. የቤተ ክርስቲያኑን ገንዘብና በእጃቸው የሚገኘውን ማንኛውንም የሲኖዶሱን ንብረት እንዲያስረክቡ። 3. ካፈነገጡበት ጊዜ ጀምሮ፤ የነበራቸው ደሞዝም ሆነ ማንኛውም ጥቅማ ጥቅም እንዲቋረጥ ማድረግና፤ በፍርድ ቤት እገዳ እንዲጣልባቸው ማድረግ ነበር። ይህ ፍርድ ቤትን የተከተለ ሕጋው እርምጃ የተወሰደው ግን የሰው ሕይወት ከጠፋና በፖለቲካ የተነከረው የአባቶች እጅ፤ ብዙ ውዝግብ ካስነሳ በኋላ ነው።
ዛሬም ሲኖዶሱ መከተል ያለበት ይህንኑ ነው። ምንም እንኳ ምዕመናኑን ላያስደስት ቢችልም መሪር እውነቱ መነገር አለበት። የትግራይ አባቶች የራሳቸውን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማቋቋም ሕጋው መብት አላቸው፤ ጳጳሳትንም የመሾም ሕጋዊ መብት አላቸው። ሕገ መንግሥቱም ይፈቅድላቸዋል። ሕጋዊ የማይሆነው ግን “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” የሚለውን ሥያሜ መጠቀም ነው። ሲኖዶሱ ወደ አላስፈላጊ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ከሚገባና፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ከመጋበዝ ይልቅ፤ 1. በትግራይ ሃገረ ስብከት ያሉ ቤተክርስቲያኖችንና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ንብረትን መረከብ። 2. አዲሱን የትግራይን የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክርስቲያን የተቀላቀለ ማንኛውም አባት፤ የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትግራይ ሃገረ ስብከት ውስጥ ምንም ቦታ እንደማይኖረው መወሰን፤ ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ቤተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ እግድ ማውጣትና ማናቸውንም ጥቅማ ጥቅም ድሞዝን ጨምሮ ማቋረጥ። 3. አሁን በሲኖዶሱ ስር ያሉ ግን ከሲኖዶሱ ላፈነገጡ አባቶችም ሆነ፤ ሲኖዶሱ የትግራይ ሃገረ ስብከትን ሙሉ ለሙሉ እስኪረከብ ባጀት አለመመደብ። 4. ማንኛውም የዓለም የኦርቶዶክስ ዓብያተ ክርስቲያናት አዲስ ከተቋቋመው ቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረውና አገዝም እንዳይሰጥ ማሳሰብ። ሊወስዳቸው ከሚገባ አጣዳፊና ወሳኝ እርምጃዎች ውስጥ ጥቂቱ መሆን ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 ቁጥር 1 እንዲህ ይላል። “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት አለው። ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡” ይላል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መብቷን ልታስከብር የምትችለው የሃገሪቱን ሕግ በመከተል ብቻ ሊሆን ይገባዋል። የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር የትግራይን የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክርስቲያንን የጵጵስና ሹመት የማስቆም ምንም ሕጋዊ ሥልጣን የለውም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፖለቲከኞችን ወደ ኃይማኖት በመጋበዝ ጣልቃ ገብነትን አያበረታቱ፤ እነሱም ከፖለቲካው ላይ እጃቸውን ያንሱ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር፤ የሌሎችን የሃይማኖት ፍላጎት ሲያከብርና የራሱን መብት በሕግ ሲያስከብር፤ ውዝግቦች ይቀራሉ፤ በሃገራችንም አላስፈላጊ ነውጦች ይቀንሳሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማንም ግፊትና በወጀብ ልትፈርስ አትችልም። ጥንካሬዋ ከእግዚአብሄር ጥበቃና በውስጧ ካሉ ምዕመናን ጥንካሬ የሚመነጭ እንጂ፤ ከውጪ ሃይሎች አለመሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል። የኃይማኖት አባቶች መስራት ያለባቸው ለሰማያዊ ጥቅም እንጂ ለምድራዊ ሊሆን አይገባውም። አባቶች በመሃላቸው ያለውን አለመግባባት በቅንነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመፍታት አቅም ሊያዳብሩ ይገባል። እንኳን በመሃላቸው ለሚፈጠር አለመግባባት ለሃገር የሚተርፍ የእርቅ አውድ መፍጠር ይኖርባቸዋል። ሕዝቡ ከእነሱ ብዙ ነገር ይጠብቃል። አባቴ እንዳለው፤ እኛ ስንጣላ አባቶች ያስታርቃሉ፤ አባቶች ሲጣሉ ግን ማን ይገስፃል ማንስ ያስታርቃል? ለዚህ መልሱ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ነው ያለው። እንደ ፖለቲከኞች ለምድራዊ ጥቅም ሳይሆን፤ እንደ መንፈሳዊ አባትነታቸው፤ ለሰማያዊው ጥቅም ተግተው ከሰሩ፤ እጃቸውን ከፖለቲካው ላይ ካነሱና፤ ለፖለቲከኞች መጠቅመያ ላለመሆን እራሳቸውን ከጠበቁ፤ መልሱን አጠገባቸው ያገኙታል ብዬ አምናለሁ።
ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ