spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየትየፋኖ እንቅስቃሴና የአማራ የፍትህ ጥያቄ

የፋኖ እንቅስቃሴና የአማራ የፍትህ ጥያቄ

fano Ethiopia _ ፋኖ
ምስሉ ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ

ሰሎሞን ገብረስላሴ
ሃምሌ 2015

የአብይ መንግስት ከ5 አመት በፊት ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረዉን ተስፋ ማንም የሚያዉቀዉና የተደሰተበት ክስተት ነበር፡፡ ሆኖም እየቆየ ያ ተስፋ ሲጠፋ፤ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነችዉና በፀረ-ወያኔ ትግሉ ከጎናችን የቆመችዉ ፖርቱጋላዊት አና ጎሜሽ እንደጠየቀችዉ “ ያን የመሰለ ተስፋ እንዴት ወደ ኣስፈሪ ቅዠት ይለወጣል?” ያለችዉ ገላጭ ነዉ፡፡ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦች ላይ ጉዳቶች ቢደርሱም፤ በተለይ በኣማራ ማህበረሰብ ላይ የተለየና ከፍተኛ በጥናት የተካሄደ ጉዳት ደርሶበታል- የዘር ማጥፋት፤ በሚሊዮኖች መፈናቀል፤ በሃሰት ትርክት የአገሪቱ ችግር ሁሉ መነሾ ተደርጎ መወራት፤ በቢሊዮኖች ብር የሚቆጠር ንብረት መወረስ፤ ወደ ዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ እንዳይገባ በየጊዜዉ መስተጓጎል፤ ምሁራኑ፤ ነጋዴዎችና አንቂዎች በገፍና በግፍ መታሰርና በወያኔ ጊዜ ከደረሰባቸዉ ሰቆቃ ተጨማሪ ኢሰብአዊ ቶርቸር መፈፀም የመሳሰሉትን ወንጀሎች ይጨምራል፡፡

ይህ ያገሪቱ ሁኔታ ለዉጥ የተባለዉ መክሸፉን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየዉ፤ የመንግስትን ጥፋቶችም በሰላማዊ መንገድ የመታገልን በር የዘጋ ስርአት እንዲፈጠር ሆነዋል፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊነት መመዝገብ ቢችሉም፤ እንቅስቃሴያቸዉ በእጅጉ የተገደበ ነዉ፡፡ ሁለት ፓርቲዎች (እናትና ባልደራስ) ምርጫ ቦርድ የሚያስገድደዉን ጉባዔያቸዉን እንኳን እንዳያደርጉ ታግደዉ፤ ዛሬ ሁኔታዉ ኣላሰራት ቢላት ስልጣን የለቀቀችዉ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ባደረገችዉ ብርቱ ትግል በጣም ዘግይተዉ ማካሄድ ችለዋል፡፡ እንደ ሰላማዊ ሰልፍ ያሉት ህጋዊ ትግሎችን ማካሄድማ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር የኑሮ ዉድነት አባሎችን እንዳስጨነቀና የደመወዝ ማሻሻያ ባይደረግ እንኳን ግብር መክፈል እንዲቆምለት በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሲያስታዉቅ በመንግስት የተከለከለበትን አይተናል፡፡

በዚህ ሁኔታ የዚህን መንግስት ግፎችና በደሎች ለመታገል ከሚጠቀሱ ሃይሎች ሃይማኖቶችና የሃገራዊ የዉይይት ኮሚሽኑ ይጠቀሳሉ፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመንግስትን ጣልቃ ገብነት በሚያረካ ሁኔታ ታግላ ብታስቆምም፤ ሁላችንም እንደምናዉቀዉ ፍዳዋ ገና አላለቀም፤ ለተገደሉና ለታሰሩ ምእመናን ፍትህ አላገኘችም፤ እንዲያዉም እንኳን ያገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ታግላ ልታሸንፍ፤  በአንድነት ፀንታ ለመኖር የሞት የሽረት ትግል እያደረገች ነዉ፡፡ በእስልምና ሃይማኖትም የበርካታ መስጊዶችን መፍረስን ተከትሎ ጠንከር ያለ ተቃዉሞ ቢታይም፤ አገራዊ ችግሮችን የመፍታት ትግሉን የሚችለዉ አይደለም፡፡  በተመሳሳይ ሀገራዊ ኮሚሽኑ ዉይይት ከማስደረግ ያለፈ ስልጣን የለዉም፡፡ በሃገሪቱ አብዛኛዉ ክፍል ጦርነትና ቀዉስ ባለበት የተሳካ ዉይይት ማካሄዱ ቢያጠራጥርም፤ ቢሳካለት እንኳን የዉይይት ጭማቂዉን ለመንግስት (ለኣቢይና ለፓርላማዉ) ነዉ የሚያቀርበዉ፡፡ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ዜጎች የ1 ደቂቃ ፀሎት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነ መንግስት እንዴት ነዉ ያገሪቱን ቁልፍ ችግሮች መፍትሄ ሃሳብ የሚቀበለዉ? ሌላዉ ኣማራጭ ተደርጎ የሚቀርበዉ በምርጫ መንግስትን ለመለወጥ የመታገል አማራጭ ነዉ፡፡ መንግስት ያለፈዉን ምርጫ ያጭበረበረበትን ስልት ራሱም ያመነዉ ስለሆነ፤ አሁን ደግሞ በሙሉ አምባገነንነት ያገሪቱን ሃብት እየተቆጣጠረ ስለሆነ፤ ተአማኒነት ያለዉ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል::

ወያኔ የሰሜን እዝን በመምታት የሰሜኑን ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይህም በብልፅግናና በወያኔ መካከል የስልጣን ፉክክር ሲካረር ቆይቶ የመጨረሻዉ ምእራፍ ነበር፡፡ በጦርነቱ የትግራይ፤የኣማራና የኣፋር ህዝቦች በእጅጉ ተጎድተዋል፡፡ ከጦርነቱ በሆዋላ ወያኔና ኦሮሞ ብልፅግና ልዩ ወዳጅነት ፈጥረዉ የፕሪቶርያ ስምምነት ተፈራርመዉ ቢያንስ የጥይት ድምፅ ቢጠፋም፤ በሆዋላ እንደታየዉ በኣማራ ክልል ህዝቦች ላይ በጋራ ማሴር ቀጥለዋል፡፡ የመጀመሪያዉ ሴራ የኣማራ ክልል ልዩ ሃይልና ፋኖ ትጥቃቸዉን እንዲያወርዱ በሸፍጥ የሄዱበት መንገድ ነዉ፡፡ “በሁሉም ክልሎች የሚደረግ ነዉ” በሚል ቅጥፈት ኣማራ ክልል ላይ ብቻ ፌዴራል መንግስቱ በኣማራ ህዝብ ላይ እስካሁን ያላቆመ ጦርነት ከፈተ፡፡ እንዲሁም ብልፅግናና ህወሃት ያደረጉትን የጀርባ ስምምነት ለመፈፀም፤ ባንድ በኩል በፕሪቶርያ ስምምነቱ መሰረት ትጥቅ ያልፈቱ እስከ አፍንጫዉ የታጠቁ የወያኔ ብዙ ዲቪዥኖች ወደ ወልቃይት/ጠለምት/ራያ እየተጠጉ፤   በሌላ በኩል የመከላከያ ሃይል ከአማራ ክልል አመራር እዉቅና ዉጭ ስዉር መዋቅሮችን በነዚህ ቦታዎች እየመሰረተ ያለበት ሸፍጥ ይፋ ሆኖአል፡፡ በነዚህ ሸፍጦች አስገዳጅነት አማራ ፋኖም ራሱንና የክልሉን ህዝብ ለመታደግ የመከላከል ዉጊያ በከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ጥቂት የፌዴራል ፓርላማ አባላት መንግስት በኣማራ ክልል የሚያደርገዉን ጦርነት አቁሞ ወደ ዉይይት እንዲመጣ ቢጠየቅም እስካሁን አሻፈረኝ ብሎ የኣማራ ክልል አርሶ ኣደር በማዳበሪያ እጦት እየቀጣ የእርሻ ጊዜዉን በማስተጓጎል በጦርነቱ ገፍቶበታል፡፡ የዚህ ሸፍጥ ኣንዱና ትልቁ አደጋ በአማራ ክልል ዉስጥ በሚከተሉት አመታት ረሃብ ሊከሰት የሚችልበት ሰፊ እድል መኖሩ ነዉ፡፡

ስለዚህ የፋኖ ፍትሃዊ የመከላከል ትግል መደገፍ አለበት፡፡ ግፉንና በደሉን በሰላማዊ መንገድ ማስቆም እንደማይቻል ከላይ አሳይተናል፡፡ በግፍ ወያኔ ከህገመንግስቱ በፊት ቀድሞ የወሰዳቸዉ የኣማራ ክልልን በመሰረቱ ክፍለ አገሮች የነበሩት ወልቃይት፤ ጠለምትና ራያን እንደገና ለመዉሰድ ከኦሮሞ ብልፅግና ጋር እንደሚያሴር ከላይ አይተናል፡፡ የነዚህ ግዛቶች ንዋሪዎች ያሳዩትን የኣማራ ማንነትና መጀመሪያ የተወሰዱበትም በጉልበት እንደሆነ በማመን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በኣማራና በትግራይ ህዝቦች በተከታታይ በማድረግ ችግሩን በቋሚነት መፍታት ይቻላል፡፡ 

የፋኖን የመከላከል ትግል ስንደግፍ ታሳቢ የሚሆኑ ነገሮችን አካትተን ነዉ- በኣማራ ህዝብ ላይ የደረሰዉ በደል በመጠንና በትኩረት የአንበሳዉን ድርሻ ቢይዝም፤ አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች እየደረሰባቸዉ ያለ ጉዳት በመሆኑ የፋኖ ትግል ኢትዮጵያዊ መሰረት መያዝና ሌሎች ግፍን ለመታገል ለተነሱ ኢትዮጵያዉያን አጋዥ መሆንና ህጋዊ ትግል ከሚያደርጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም የትግል ትስስርና ኣጋርነትን ማሳየት አለበት፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ኢትዮጵያዉያንን የሚያስቀይምና በታሪክና በስትራቴጂ ድጋፍ የሌላቸዉ ሃሳቦችን ከሚራምዱ ጥቂት አማሮች ትርክት ትግሉ ራሱን ማፅዳት አለበት፡፡  የፋኖ ትግል ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ትግል ጋር ተዳምሮ የአቢይ መንግስትን ወደ ጠረጴዛ ዉይይት እንዲመጣ ለማስገደድ መርዳት አለበት፡፡  የፋኖ ድርጅቶች በዚህ ዉይይት አማራ ወኪሎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያዉያንንም ሊወክሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ የዚህ ዉይይት ተቀዳሚ አላማዉ የብልፅግና መንግስት አገሪቱን ለመምራት፤ ህግን የማስከበር አቅም ወይም ፍላጎት እንደሌለዉ ስለታየ፤ ያገሪቱም ኢኮኖሚ እየዘቀጠ በመሄዱ የሽግግር መንግስትን አስፈላጊነት እንዲቀበል ማስገደድ ወይም ማሳመን ነዉ፡፡  

የሽግግር መንግስቱን የሚመሰርቱት አብዛኞቹ የመንግስት አካል የሆኑ መስሪያ ቤቶች ወኪሎች ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ መመዘኛዉ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ ማሳየታቸዉና በለዉጡ ተስፋ የተጣለባቸዉ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ከነዚህም ወኪሎች መካከል የምርጫ ቦርድ፤ የህዝብ እንባ ጠባቂ ድርጅት፤ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የሲቪክ ድርጅቶች የጋራ ህብረት፤ የሃይማኖቶች የጋራ መድረክ፤ የኢትዮጵያ ኣትሌቲክ ፌዴሬሽን፤ የፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲቱት የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡ የመንግስት ተቋሞችን ወኪሎች በሽግግር መንግስቱ ማካተት ምናልባት መንግስት በጠረጴዛዉ ዉይይት የሽግግር ሃሳብን እንዲቀበል ይረዳ ይሆናል፡፡

የሽግግር መንግስቱ ስራዎች የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚሽን መሰየምና ሂደቱን ወደ ፍፃሜ ማድረስ፤ ያገሪቱን ፀጥታና የህዝቡን ደህንነት መጠበቅና የእርቅና የፍትህ ዉይይቶችን ማስጀመርና የኑሮ ዉድነነትን ማስተካካያ ርምጃ መዉሰድ ናቸዉ፡፡

ይህ ዜጎችን በማፈንና መዳረሻቸዉን በማጥፋት የሚባዝን መንግስት ሲያስፈልግም በርካታ ብር የሚጠይቁ ጠላፊዎችን ሊያስቆም ያልቻለና የተባበረ  የማፍያ ባህሪ ያለዉ፤ ኦሮሙማን በማራመድ የህብረተሰቡን አንድነት የናደ የጎሳ ፋሽስት የኦሮሞ ብልፅግና መንግስት በስልጣን በቀጠለ ልክ ኢትዮጵያዊነት እየተዳከመ ስለሚሄድ ባስቸኳይ ከስልጣን መወገዱ ለኣገሪቱ መቀጠል ዋስትና ነዉ፡፡

የፋኖ ድርጅቶች ዛሬ በትግላቸዉ የአማራ ክልል መንግስትን ወደ ድርድር ሊያመጡ የሚችሉበት አቅም ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ ሲፈጠር ፋኖ ለዉይይትና ለድርድር ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር የሚባለዉ ከክልሉ ሳይሆን ከፌዴራል መንግስት ጋር ነዉ የምደራደረዉ ያለዉን ፋኖ ማለት የለበትም፡፡ አጋጣሚዉን በመጠቀም የእዝ ሰንሰለቱንና ዉህደቱን ለማፋጠን ስለሚረዳዉ ፋኖ ከክልሉ መንግስት ጋር መነጋገርን መስማማት አለበት፡፡ እንደ ቅድመ ሁኔታም ፋኖ ተደራዳሪዎችን በነፃ ለመምረጥ እንዲችል የፋኖ መሪዎች በነፃነት ሊሰበሰቡ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ሲደረግ ፋኖ መንግስትን ሙሉ በሙሉ አምኖ በመዘናጋት መሆን የለበትም፡፡

ፋኖ በድርድሩ ሊያነሳቸዉ ከሚገቡ ጥያቄዎች የሚከተሉት ዋነኛ ይመስላሉ፡፡

  • የመከላከያ ሃይል ሙሉ በሙሉ በአማራ ክልል የሚያደርገዉን የዉድመት ጦርነት አቁሞ ከክልሉ መዉጣት
  • የመከላከያ አመራር በወልቃይት፤ ጠለምትና ራያ ከክልሉ አመራር እዉቅና ዉጭ ከህዝብና የበታች አስተዳደሮች ጋር የሚያደርገዉን ተፅእኖ የመፍጠር ዉይይት ባስቸኳይ ማቆም
  • የፌዴራል መንግስትና የክልሉ መንግስት ላንዴና ለመጨረሻ ወልቃይት፤ጠለምትና ራያ የአማራ ርስቶች መሆናቸዉን በይፋ እንዲቀበልና ከኣጎራባች የትግራይ ህዝቦች ጋር ህዝብ ለህዝብ ዉይይት እንዲጀመር መንግስት እንቅፋት እንዳይሆን
  • በክልሉ ከ 12 ሽህ በላይ የታሰሩ ሁሉም ፋኖዎችና የፖለቲካ እስረኞች በቶሎ እንዲፈቱ፤ እንዲሁም በአማራነታቸዉ ብቻ በክልሉና ከክልሉ ዉጭ የታገቱ የሰራዊት ኣባላት ባስቸኳይ እንዲፈቱ
  • ለኣማራ ገበሬዎች ያለባቸዉን የማዳበሪያ ችግር ባስቸኳይ በመፍታት የመዝሪያ ወቅቱ ወዳለፈበት እርሻቸዉ እንዲመለሱ ማድረግ
  • ለኦሮሞ ብልፅግና ተላላኪ በመሆን በኣማራ ህዝብ ላይ በደል ያደረሱ፤ ከሃላፊነታቸዉ በላይ ሄደዉ ሰቆቃ ያደረሱ የአማራ ብልፅግና የፀጥታና የኣሰተዳደር ሃላፊዎች እንዲጠየቁ
  • የብልፅግና መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ በተለየ የሚያደርገዉን ማሳደድ አቁሞ፤ በሃሰት የወንጀል ክስ ያጎራቸዉንና ቶርቸር ያደረጋቸዉን በአዲስ አበባ የሚገኙ  ከ50 በላይ የፖለቲካ እስረⶉች ባስቸኳይ እንዲፈታ
  • ብልፅግና የኢትዮጵያን ችግሮች በተለይ የኣማራን ህዝብ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ እያባባሰና እያወሳሰበ ስለሆነ፤ የመፍትሄዉ አካል ለመሆንም ፍላጎት ስለሌለዉ ባስቸኳይ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበትን መንገድ ህዝባችን እንዲመክርና ተግባራዊ እንዲያደርግ
  • ባገሪቱ ኣአስተማማኝ የሽግግር ስርአት ተዘርግቶ፤ በኣማራዉ ላይ የሚደረገዉ ጭፍጨፋ አቁሞ፤ እዉነተኛና መላዉን ህዝባችንን የሚወክል የመከላከያና የፖሊስ ሃይል እስቲዋቀር ድረስ ፋኖ እንደመዋቅር እንዲቀጥል

የሚሉት ለድርደር ቀርበዉ መልስ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የኣማራ ህዝብ ብሶት መጠን ያለፈ በመሆኑ ምክንያት ዛሬ ብዙ ኣማሮች የሚያምኑት የፖለቲካ ስልጣን አማራዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ካልያዘ በስተቀር በኣማራዉ ላይ የሚደረገዉ ግፍ ማቆምያ አይኖረዉም የሚል ነዉ፡፡ ይህ ብሶት የወለደዉ እምነትን ለመገንዘብ መቻል ይኖርብናል፡፡ ሆኖም አገሪቱ ከቀዉስ ወደ ቀዉስ እንዳትንከባለልና የኣማራዉም ብሶት ኢትዮጵያዊ መሰረት ስላለዉ መልክ ባለዉ መንገድ በኣካታች የሽግግር መንገድ መሄድ የጦርነቱን ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ ለሰላምና ዴሞክራሲያዊነት መሰረት ይሆናል፡፡

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here