spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ በሳል አመራር ትዘረጋለች

ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ በሳል አመራር ትዘረጋለች

 

Ethiopia _ failed leadership
ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ

ደረጀ ተክሌ ወልደማርያም
ከአዲስ አበባ

በኢትዮጵያ በዘመናዊው ታሪክዋ ሶስት ስርዓቶችን ማስተናገድዋ ይታወቃል፡፡እነሱም ባላባታዊ ወይም ፊውዳሊዝም የተሰኘውና የራሱን ህገመንግስት በ1923 ዓ.ም የቀረፀ በሁዋላም የተሻሻለ ሕገመንግስት ያስተናገደ ሥርዓት ነበር፡፡ 

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ንጉሠ ነገስቱ ከፍተኛውን የሥልጣን አካል የሚቆጣጠርበት እና ከሰማይ በታች ያለው የኢትዮጵያ ምድር ከያዘው ሕዝብና ንብረት ጋር የንጉሠነገሥቱ ነው በሚል ቅኝት የሚታወቅ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ ንጉሡ ያላመነበት ውሳኔ የማይፈፀምበት ከንጉሡ በሁዋላም ቢሆን ከተወላጆቹ መካከል በተቀመጠው የአነጋገስ ስርዓት የሚካሄድበት ሂደት ነበር፡፡ የፓርቲ አደረጃጀትንም በተመለከተ በንጉሠ ነገስቱ ዘመን ሀገሪቱ ፓርቲ አልባ ነበረች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ልምዱ በሌላት ሀገር በዚያ ስርዓት ውስጥ የፓርቲ አመራር ባይጠበቅም ፓርቲ ለማደራጀት ለሚሞክሩ ሁሉ መንገዱ ክፍት አልነበረም፡፡ 

ከፊውዳሊዝም መገለጫዎች መካከል ማንኛውም ሰው ጌታ ሲኖረው ማንኛውም ጌታ ደግሞ መሬት አለው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው ጌታውን በታማኝነት እንዲያገለግል እንደሚጠበቅበት ሁሉ ጌታውም ተከታዩን ከሌላ አቅጣጫ ከሚመጣ ጥቃት የመጠበቅ ሃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ይህ የኑሮ ዘይቤ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተቀባይነት ነበረው ፡፡ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ያልተመጣጠነ የሀብት ክፍፍልም እንዲሁ አንዱ የፊውዳሊዝም መገለጫ ነበር፡፡ በእነዚህና በሌሎች መገለጫዎቹ ሀገራችን በትክክል ለረጅም ዘመናት የስርዓቱ ተከታይ እንደነበረች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ 

የባላባታዊውን ሥርዓት አስወግዶ ወደሥልጣን የመጣው ወታደራዊው መንግስት ሀገሪቱን በኮሚኒዝም ሥርዓት አደራጅቶ ለመምራት ከምስራቁ ዓለም ጋር ወዳጅነት የመሰረተ ሲሆን ዘግይቶም ቢሆን የራሱን ሕገመንግስት በማርቀቅ የኮሚኒዝምን ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ጥረት አድርጎዋል፡፡ 

በወታደራዊው መንግስት ዘመን ሀገራችን በአንድ ፓርቲ ዕዝ ስር ነበረች፡፡ በማንኛውም የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ሀገር ውስጥ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት የሚጠበቅ ቢሆንም ተቃዋሚ ፓርቲ ለማዋቀር ጥረት ያደረጉ ሁሉ ተጠቃለው በገዢው ፓርቲ ስር እንዲሆኑ አለበለዚያም እንዲወገዱ የተደረገበት ወቅት ነበር፡፡ በመሆኑም የኮሚኒዝም ሥርዓት ተከታይ ሀገር መገለጫ ከሆኑት መርሆዎች መካከል የግል ማምረጫ ተቁዋማትን መውረስ ፣ መሬትን ከባለመሬቶች ላይ

በመውሰድ ለአርሶ አደሩ ማከፋፈል ፣ የፋይናንስ ተቁዋማትን በመንግስት ቁጥጥር ስር የማድረግ ተግባር በኢትዮጵያ ተከናውኖዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኮሚኒዝም ስርዓት ውስጥ ከሚጠበቁ ዋና ዋና መርሆዎች መካከል የወዝአደሩ አምባገነንነት አለመታየቱ ወይም አለመፈቀዱ ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን የኮሚኒዝም ስርዓት አራማጅ ከነበሩ ሀገራት ጎን ለማሰለፍ የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚው አቅም አያስደፍርም ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በዘመኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሚኒዝም መገለጫ ሆኖ የሚታወቀው የግለሰብን ሀብት መገደብና የብዙሃንን ጥሪት ማዳበር ቢሆንም እሱም ቢሆን ሌኒን ባስነበበን መንገድ አልተካሄደም፡፡ ከኮሚኒዝም በትክክል የወረስነው ወኔውንና በዓላቱን ሲሆን መጨበጫው ሳይታወቅ ነበር ሥርዓቱ የከሰመው፡፡ 

በሶስተኛ ደረጃ የሚታወቀው ሥርዓት ደግሞ ወታደራዊውን መንግስት በተካው ኢህአዴግ የተደራጀውና ብሔርን መሰረት ያደረገው የፌደራሊዝም ሥርዓት ነበር፡፡ ሥርዓቱ በህግ እንዲደገፍ ለማድረግ ኢህአዴግ አርቅቆ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ያደረገው የፌደራል ሕመንግስት እና በየብሔረሰባቸው የተደራጁ ክልሎች ያረቀቅዋቸው ህገመንግስቶች ይህንኑ የብሔር ፌደራሊዝም ሥርዓት የሚያረጋግጡ ነበሩ፡፡ 

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ዓለማችን የኮሚኒዝምን መሸርሸር እያረጋገጠች የመጣችበት ዘመን በመሆኑ ሥርዓቱ በአንድ የገዢ ፓርቲ ሥርዓት ስር የሚመራበት ዘመን ሳይሆን የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓትን የሚያሰፍን ወቅት ላይ መድረሳችን እሙን ቢሆንም ፓርቲ የማደራጀት ተግባርን መፍቀድና የመድበለ ፓርቲ ሃሳቦችን ተቀብሎ ማንሸራሸር ተለያይተው ኖረዋል፡፡ 

በመጀመርያ ደረጃ የፌደራሊዝም ስርዓት ማለት በማንኛውም የመስተደዳድር እርከን ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን መጎናፀፍ ማለት ነው፡፡ ከዚህም ጋር የብዙሃኑን መብት ማረጋገጥና የአናሳውን መብት ማስጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡ 

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ሁኔታ በክልሎች የተለየ ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ እና ክልላዊ ሕገመንግስት ከማደራጀት ውጭ የሚታዩ ብዙ ጉድለቶች ነበሩ አሁንም አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 

1ኛ. ሀገሪቱ ከሶስት አሰርተ ዓመታት በሁዋላም እንኩዋን ቢሆን እስከ ዝቅተኛው የመስተዳድር እርከን ድረስ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን አላጎናፀፈችም ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ክልሎች አሃዳዊ መሰል የአስተዳደር ቅርፅ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ 

2ኛ. የሀገሪቱ ህጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚባልለትን የፌደራሉን መንግስት ሕገመንግስት የሚቃረኑ የክልል ሕገመንግስታት ፀድቀው በስራ ላይ ውለዋል፡፡ 

3ኛ. በፌደራሉ መንግስት ብቻ መዋቀር የሚገባው የመከላከያ ሰራዊት ልዩ ኃይል በሚባል ሕገወጥ አባባል ተደራጅቶ ክልሎች ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ገንብተዋል፡፡ በውግያም ተካፍለዋል፡፡

4ኛ. እንዲሁ በተጨማሪ በፌደራል መንግስቱ መዋቅር ውስጥ ብቻ የሚኖረው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከስሙ በስተቀር ክልሎች ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ የውጭ ግንኙነት ሲያከናውኑ ማየት የተለመደ ሆኖዋል፡፡ 

5ኛ. በአብዛኛው እንደምንታዘበው የብዙሃኑ መብት ሲከበር የአናሳው መብት ይረሳል፡፡ ወይም አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ይገደዳል፡፡ 

ከዚህም በላይ ሕዝብን ያቀራርባል ተብሎ የሚታሰበው ይህ ስርዓት በመሪዎች ስህተት ብቻ በብሔረሰቦች መካከል የመቀራረብ ሳይሆን የመለያየት ብሎም የመጠላላት መንፈስ በማዳበሩ የኢትዮጵያን ፌደራሊዝም ልዩ መታወቅያው እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ኢትየጵያ የፌደራሊዝም ሥርዓትን በትክክል ተቀብላ አስተናግዳለች ወይም እያስተናገደች ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ 

በእኔ አመለካከት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፊውዳሊዝም ነበር ኮሚኒዝምና ፌደራሊዝም ግን አልነበሩም ብዬ ለመከራከር እችላለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የኮሚኒዝምንና የፌዴራሊዝምን ሥርዓት ሳይንሱም ሆነ ነባራዊው ሁኔታ በማይፈቅደው መንገድ በመተርጎሙ ነው፡፡ ሌላው ለፌደራሊዝም መስረፅ እንቅፋት የሆነው ደግሞ የገዢ ፓርቲው ተግባር ከመንግስት ተግባር ጋር መጣረሱ ነው፡፡ በአንድ ፓርቲ መርሃ ግብር የተሳሰሩ የፓርቲ አባላት በመረጣቸው ህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በቡድን በተሰባሰቡበት የፓርቲ መርሃ ግብር እየተመሩ ሀገሪቱንና ሕዝቡን ይመራሉ ፡፡ አባላቶቻቸው አስተዳደር ሲያዛቡ እና በሙስና ሲዘፈቁ ሥርዓቱ ከሕዝብ ይልቅ ለፓርቲው አባላት ስለሚያደላ ወደ ሌላ ስልጣን ማዛወሩ እንደ መፍትሔ ይታያል፡፡ ሕብረተሰቡ የመረጠውን እንደራሴ ውክልናው ካልጠቀመው መልሶ የማውረድ ሥርዓት አልተበጀለትም ቢሞክርም አይፈቀድለትም፡፡ አብዛኛዎቹ ባለሥልጣናት በተዋፅኦዋቸው ምክንያት ብቻ የቤተመንግስት ቅምጥል ሆነው እንበለ ዕውቀት ከመራጩ ሕብረተሰብ ፈቃድ ውጭ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ሥልጣን እየተዘዋወሩ እድሜያቸውን ይገፋሉ፡፡ 

በመሆኑም ይህ ሁኔታ ተባብሶ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን በመፍጠር ፖለቲካዊ ቁመናዋ በሙሉ በመጥላትና በመውደድ ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም ማለት ፖለቲከኛው በሙሉ እንደሃይማኖት ሰባኪ ጠርዝ ይዞ የሚወደውን ከአምላክ እኩል የሚጠላውን ደግሞ ከሰይጣን እኩል አድርጎ መፈረጁን ተያይዞታል፡፡ የዘመኑ ፖለቲከኛ መሃል መንገድ ርቆታል፡፡ ከሚጠላው አካል አንዳችም ቁም ነገር መኖሩን ይረሳና ከሚወደው ደግሞ አንዳችም ስህተት መኖሩን አይቀበልም፡፡ ስርዓቱ ምሁራንና ፖለቲከኞችን ለሁለት ከፍሎ ሕገመንግስቱ ይቀየር እና ሕገመንግስቱን ማን ነክቶት የሚል ሁለት ዋነኛ ጎራ ፈጥሮዋል፡፡ ሁለቱም ስጋታቸውን የሚገልፁበት መንገድ አላቸው፡

የብሔርን ፖለቲካ የሚጠሉት የሥርዓቱ መሰረት ቁዋንቁዋ በመሆኑ ሕዝብን አለያይቶ ሀገርን ያፈርሳል የሚል ምክንያት ይሰጣሉ ፡፡ የብሔርን ፖለቲካ የሚደግፉት ደግሞ የተለያዩ የየብሔረሰቡ መገለጫዎች የሚከበሩት በዚህ ስርዓት ብቻ በመሆኑ ሥርዓቱ ከተወገደ በተመሳሳይ ሁኔታ ሀገሪቱ ትፈርሳለች ይላሉ፡፡ የሁለቱም ጥርጣሬ የተለጠጠ ቢሆንም እንኩዋን እውነትነት አለው፡፡ ጥርጣሬው የመጣው ከፍርሃት ነው፡፡ 

ፍርሃት ያደረበት አካል ፍርሃቱ የሚወገድለት የሚያስፈራው አካል ሲወገድ እንደሆነ ብቻ አድርጎ ያምናል፡፡ አስፈሪው አካል ሳይወገድ ፍርሃት እንዲወገድ ማድረግ የሚችለው ብቃት ያለው አመራር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በበሳል አመራር የሁለቱም ፍርሃት ይወገዳል፡፡ ዓለም የተቀየረችው በግለሰቦች በሳል አመራር እንጂ በኢዝም መኖርና አለመኖር አይደለም፡፡ 

አመራሩ የሁሉንም ስጋት ሊቀርፍ የሚችለው የመሪነት ብቃቱን ሁሉም ሊቀበሉት በሚችል መንገድ ሲያደራጀው ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነፃ አመራር፣ ጠንካራ ሕዝባዊ ተቁዋማት መገንባት ይኖርበታል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ ወገንተኝነትን ባልተከተለ፣ ተዓማኒነት በሚኖረው መልኩ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ተመርኩዞ ሕዝቡን ማገልገል ግዴታው ይሆናል፡፡ 

ይህ ከባድ ይመስለኛል በበሳል አመራር ግን ይቻላል ፡፡ ፓርቲ ካልነበረበት ስርዓት የአንድ ፓርቲ ስርዓት መሸጋገርያችን ሆኖ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ግና አስተሳሰባችን አሁንም የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ላይ እንደቆመ ነው ያለው፡፡ አሁንም እኔ የምለው ብቻ ላይ ነን ወይንም ሌላኛውን ማጣጣል ላይ አተኩረናል፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራኑ ለዴሞክራሲ ቅርብ አይደለንም፡ ከተማሩት እና ከሚመሩት ይበልጥ ባላገሩ ሕዝባችን ተቻችሎ የመኖር እና የመሰማማት ብቃት አለው፡፡ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የብዙሃን ፓርቲ ግንባታ ለሀገራችን ያመጣው ቁም ነገር ብዙም አይታይም፡፡ በህዝብ አርቆ አስተዋይነት የተገቱ ብዙ ደም አፋሳሽ አፍ እልፊቶች ከፖለቲከኞች ይሰማሉ፡፡ 

ዴሞክራሲ አብሮ ማደግ ይፈልጋል፡፡ ቢያንስ በቤተሰብ ደረጃ እንኩዋን በውስጡ ማለፍ ይፈልጋል፡ ፖለቲከኞቻችን ለዚህ አልታደሉም፡፡ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት የሚኮራባቸው ዓመታት አልነበሩም፡ በመሆኑም እንደእኔ እምነት ዲሞክራሲን በመንግስትም ሆነ በህዝብ ከሞላ ጎደል እንድንገለገልበት ከተፈለገ በሳል አመራር መገንባት የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡ በሳል አመራር ጥርጣሬዎችን ያስወግዳል፡፡ ልዩነቶችን ያጠባል፡፡ ዕውቀትን በነፃነት ያስተረጉማል፡፡ 

የዚያ ሰው ይበለን
ደረጀ ተክሌ ወልደማርያም ከአዲስ አበባ

 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here