
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ሃምሌ 28 ቀን 2015
በክፍል አንድና ሁለት ለማሳየት እንደተሞከረው፤ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ በኢትዮጵያ ላይ ያወጁት የኢኮኖሚ ጦርነት፤ በሃሰት ትርከት የተሞላና የፖለቲካውን አውድ የራሳቸውን የግል በቀል ለመወጣት የጀመመሩት ዘመቻ እንጂ ለሃገር በመቆርቆር አለመሆኑ አሳይቻለሁ። በዚህ ክፍል ደግሞ የኢኮኖሚውን ጉዳይ እየቋጨሁ፤ ወደ ዶ/ር ዮናስ የተጣመመ የኦሮሙማ ትርከት ላይ በማተኮር፤ እኝህ ሰው፤ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈቱት በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፤ ከእንደ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የሃገር ገዳይ ፕሮጀክት ጋር የተቀናጀ ያልተቀደሰ ጋብቻ መሆኑንም በጭብጥ አሳያለሁ።
የሃሰት ትርከት፤ ባልተገባ መረጃ።
እንኳን PhD ያለው ሰው ይቅርና፤ የሁለተኛ ድረጃ ተማሪዎች እንኳን ለሚጽፉት ጽሁፍ፤ ጭብጥ ያለው መረጃ እንዴት እንደሚያቀርቡ ያውቃሉ። ማንኛውም መረጃ ሲቀርብ ምንጩ ከየት እንደሆነ የመጀመሪያ ምንጭ የሁለተኛ ምንጭ በሚል ያጠቃቀስ ፕሮቶኮል አለው። በስማ በለው የሚቀርብ መረጃ፤ እንደ ተጨባጭና አሳማኝ መረጃ ሆኖ አይቀርብም። ዮናስን በሰማሁና ጽሁፋቸውን ባነበብኩ ቁጥር፤ እኝህ ሰው ኢኮኖሚክስ መማራቸውን እንድጠራጠር ያደርገኛል። ብዙ ነገር ዋሽተውናል፤ ትምህርታቸውንስ ዋሽተውን ይሆን ብሎ መጠየቅም ተገቢ ይሆናል። በበርካታ የዶ/ር ዮናስ ብሩ ጽሁፎች ላይ የምናየው እንደ መረጃ የቀረበው፤ “የመንደር ወሬ” ነው። ለዚህም ነው፤ ዮናስ ሲጽፉ፤ “አራምባና ቆቦ” የሚረግጡት። መረጃቸው መሰረት ስለሌለው ዛሬ ያሉትን ነገ ይሰርዙታል። ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብር እያተሙ” ቤተ መንግሥት ይሰራሉ እንዳላሉን፤ ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ንግድ ገቢ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጫካ ፕሮጀክት እየዋለ ነው ይሉናል። ለዚህም ከግምት በስተቀር የሚያቀርቡት ምንም መረጃ የለም። በየ ዩቲዩብ ላይ የራሳቸውን ድምጽ በመስማት “የሚመረቅኑት” ዮናስ፤ ቆም ብለው እንኳን ምን እያሉ እንደሆነ አያስቡም። የሚሰማቸው ስላጡም ነው፤ “አዳምጡኝ” በሚል የማላዘን ጩኸት በየ ዩቲይብ ያይ እየቀረቡ፤ ውሸታቸውን በመደጋገም እውነት ለማስመሰል የሚሞክሩት።
ዮናስ አልሰሙ እንደሆነ ደግሜ ልንገራቸው። የጫካው ፕሮጀክት እየተሰራ ያለው ሃብታሞች በሚያዋጡት የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ነው። ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትርሩ በፓርላማው ፊት ደጋግመው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦርድ የሚተዳደር እራሱን የቻለ ተቋም ነው። ይህን ካላወቁ፤ በውስጡ ያሉትን ሰዎች አነጋግረው መረጃ ማግኘት ይቻላል። ዮናስ በአንድ አስቂኝ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ የፃፉት ጽሁፋቸው ላይ፤ ስለ አየር መንገዱ የተወራው ውሸት ነው ብሎ ምላሽ የሰጠው የአየር መንገዱ አስተዳደር ነው፡ ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መግለጫ አልሰጡም ይሉናል። ይህ ጉዳይ የሚመለከተው አየር መንገዱን በመሆኑ አየር መንገዱ ምላሽ ሰጥቷል። የዮናስ ቁጣ ግን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእኔ ውሸት ለምን መልስ አልሰጡኝም” የሚል ነው። ዛሬም የሚንጠራሩትና ላንቃቸው እስኪበጠስ የሚጮኹት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት በመሳብና “በቀሌን እይ” ከሚል ድንክዬ አስተሳሰብ ነው።
ዶ/ር ዮናስ፤ የኦሮሞን ሕዝብ ለማስመታታ የሚረጩት “ዮርሙማ መርዝ ነው። ዶ/ር ዮናስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግሥት እንዳለ ይነግሩናል፤ ይቺ ከጽንፈኛው ጃዋር መሐመድ የተሰረቀች እሳቤ ነች። ዮናስ ስለ”ኦርሙማ” ሲጽፉ የሚያቀርቡት መረጃ፤ በስማ በለው የተጠፈነገ በማር የተጠቀለለ መርዝ ነው። ደስ የሚለው ነገር ግን የቁራ ጩኸታቸው በሕዝብ ጆሮ የተነፈገው በመሆኑ፤ በበይነ መረብ ላይ ተበትኖ የሚቀር አመድ ከመሆን አያልፍም። የሳቸው ጩኸት ማረፍያ የሚያገኘው፤ በጽንፈኛው ጎጠኛ ልብ ውስጥ ብቻ ነው።
የኦሮሙማ ትርከት፤
ዮናስ አድገኛ መርዛቸው ጭብጥ መረጃ እንዳለው ለማስመሰል፤ በቦርከና ድኅረ ገጽ ላይ፤ “በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያስቀር የአስቸኳይ ጊዜ ማኒፌስቶ” በሚል ርዕስ በፃፉት ጽሁፍ፤ እርስ በእርስ የሚደረግ ጦርነትን የሚያስቀር “ማኒፌስቶ” ሳይሆን ጽሁፋቸው የሚጋብዘው ጦርነትን ነው። በዚህ ጽሁፋቸው፤ ኢንተርሃሙይ በቱትሲዎች ላይ ከረጨው አደገአና መርዝ ባልተናነሰ መልኩ፤ ዮናስ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጦርነት ያወጀ መርዛቸውን ረጭተዋል። ለጽሁፋቸው መረጃ ይሆናል ብለው ከጠቀሱት ኩነት አንዱ እንዲህ ይላል።
“የአማሮ ህዝብ በሶስት በኩል በኦሮሞ የተከበበ በመሆኑ ከሌሎች አጎራባች ብሄሮች ጋር እንዳይገናኝ መንገድ ተዘግቶበታል:: ለመግለጽ በሚያዳግት እና ይህ ነው በማይባል አፈና እና በመከራ ውስጥ ይገኛል:: ከመወረርና ከመጨፍጨፉም አልፎ እንደ አንድ ብሄር ህልውናው አደጋ ላይ ነው:: …” (ሃሰን ሼካ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት 11 ኛ መደበኛ ስብሰባ መጋቢት 2015)” በማለት “መረጃቸውን” ያጋራሉ። በመጀመርያ፤ አንድ የተማረ ሰው እንዲህ ዓይነት “መረጃ” ሲያቀርብ፤ ተናጋሪው፤ ከምን አንፃር ተናገሩ፤ ንግግራቸው የፖለቲካ ዓላማ አለው ወይ፤ ብሎ ይጠይቅና፤ ተናጋሪው ያሉትን እውነተኛነት ከተጨማሪ ምንጭ ያረጋግጣል። የዮናስ መረጃ አቀራረብ፤ በሕግ ዓይን (hearsay; አሉባልታ) ተብሎ ይወሰዳል። እንዲህ ዓይነት ምስክርነት፤ በፍርድ ቤት ተቀባይነት የለውም። ለዚህም ነው “ተማርን” የሚሉ ሰዎች፤ ጽሁፋቸውን በጭብጥ ተመርኩዝወ እንዲያቀርቡ የሚጠበቀው። የዶ/ር ዮናስ ዓላማ ግን፤ በጭብጥ የተመረኮዘ ትንታኔ ማቅረብ ሳይሆን፤ ፋሽስታዊ እሳቤ ያለው ነው። ፋሽስቶች፤ ጽንፈኛ አስተሳሰባቸውን እያጎለበቱ የሚሄዱት፤ በሕዝብ ውስጥ “እኛና” “እነሱ” የሚል ከፋፋይ ሃሳባቸውን መሰረት ለማስያዝ በሚረጩት መርዝ ነው። ዶ/ር ዮናስ እንድንቀበል የፈለጉት፤ የኦሮሞ ሕዝብ አጥቂ ሌላው ተጠቂ መሆኑን ነው። ለዚህም ነው የአማሮ ሕዝብ በኦሮሞ ሕዝብ እየተጨፈጨፈ ነው የሚለውን መርዛቸውን በመርጨት፤ ከአማሮና ከሌላውም ሕዝብ ለእኩይ አላማቸው አጋር ለመፈለግ የሚንፈራገጡት። ነገር ግን፤ የአማሮ ሕዝብ የሚዋሰነው ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከኮንሶ፤ ከጎሞግፋ፤ ከቡርጂ፤ እንዲሁም ከደረሼ ለዩ ወረዳ ጋር መሆኑን አይነግሩንም። በዚህ መልዕክት መተላለፍ የተፈለገው “መረጃ”፤ የኦሮሞ ሕዝብ በአማሮ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም እንጂ፤ ኦነግ ሸኔ በተባለ አማፂ ቡድን፤ እንደሚፈጽም የተገለጸ አይደለም። ኦነግ ሸኔ የተባለው አማፂ ቡድን፤ ኦሮሞን ጭምር የሚገድል ጨካኝ ቡድን እንጂ የኦሮምን ሕዝብ እንደማይወክል ለዶ/ር ዮናስ አይጠፋቸውም። በነገሬ ላይ አማሮ ወረዳ፤ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣታቸውም በፊት ከወኃ እና ከግጦሽ ጋር በተያያዘ፤ በተደጋጋሚ ግጭቶች ይነሱበት እንደነበር አዲስ ማለዳ የተባለው ጋዜጣ ሰኔ 28 ቀን 2015 ባወጣው እትሙ ላይ አስነብቧል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በአማሮ ወረዳ ብቻ ሳይሆን፤ አማሮ ወረዳን በሚጨመርው የኮንሶ ዞን፤ በአማጽያን በሚደርስ ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ መፍትሔ ለመስጠት፤ የፌደራል መንግስቱ የመከላከያን ሰራዊት ማሰማራቱንና፤ አካባቢው በአሁኑ ስዓት በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ መሆኑንና በአማሮ ልዩ ወረዳ፤ አሁን አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ዶ/ር ዮናስ አይነግሩንም። ዮናስና መሰሎቻቸው እንደሚሉን የዐብይ መንግስትና የኦሮሞ ሕዝብ ተቀናጅተው በሌላው ብሔረሰብ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ፤ በአማሮ ወረዳ ለምን መከላከያን ማስገባትና ጥቃት ፈፃሜው የሸኔ አማፂ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ ተፈለገ? ላም ባልዋለበት ኩበት ፍለጋ የሚሄዱት ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ የጥላቻ መርዛቸው በዚህ ብቻ አያቆምም።
የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም።
ቶማስ ጃፈርሰን፤ አንድ ሰው መዋሸት ከጀመረ፤ ደግሞ ለመዋሸት አይፈራም ይለናል። በሃገራችንም “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” የሚል ብሂል አለ። እድሜ ጠገብ የሆነን ሰው በአደባባይ ውሸታም ማለት ቢከብድም፤ በሃሰት ትርከት ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት፤ ደም ለማቃባት ተግቶ የሚሰራን ሰው ለማጋለጥ፤ እውነቱን ፍንትው አድርጎ ከማሳየት ሌላ አማራጭ የለም።
ጽንፈኛ ኃይሎች የሚረጩትን መርዝ መሰረት የሚያሲዙት፤ የሃሰት ዜና በማሰራጨት፤ ጭብጥን በማጣመም፤ በሕዝብ ውስጥ የተጠቂነት ስሜት በመፍጠርና “እኛና “እነሱ” በሚል ከፋፋይ እሳቤ ተጠቂነት የሚሰማው ሕዝብ ተስፋ ቆርጦ በስራቸው እንዲሰባሰብ ማድረግ ነው። መሶሎኒና ሂትለር ያደረጉትም ይህንኑ ነው። ሂትለር ጀርመኖች በአይሁዶች ላይ የነበራቸውን ጥርጣሬ በማስፋት ነው ከጀርመኖች ድጋፍ ማስበሰብ የቻለው። በአንደኛ የዓለም ጦርነት የጀርመን ወታደር የነበረው ሂትለር፤ ለጀርመን በጦርነት መሸነፍ ምክንያቶቹ አይሁዶችና ኮምኒስቶች ናቸው የሚለውን ሰበብ ለራሱ እኩይ ዓላማ ተጠቀመበት። ከእኛ በላይ ለጀርመን ተቁርቋሪ የለም በሚል ስሜት፤ ጀርመንን መልሼ ጠንካራ አደርጋለሁ በሚል ፕሮፖጋንዳ፤ ሂትለር የ1932 (እ.አ.አ) የፓርላማ ምርጫ አሸነፈ። ሂትለር የጀርመንን ሕዝብ ብሔራዊ ስሜት በመኮርኮር፤ በአይሁድና በኮምኒስቶች ላይ የነበረውን ጥላቻ ተጠቅሞ፤ የፖለቲካ ሥልጣን መቆናጠጥ ችሏል። የኢትዮጵያ ጽንፈኛ ሃይሎችም፤ ከሂትለር የፖለቲካ ደብተር ላይ የሰረቋትን እሳቤ በመጠቀም፤ ትላንት ኦሮሞ ጠል በሆኑ ጽንፈኞች ሲራገብ የነበረውን እኩይ አመለካከት፤ “ኦሮሙማ” ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ነው በሚል የሃሰት ትርከት፤ ጦራቸውን ሥለው፤ በኦሮሞ ሕዝብ ደረት ላይ አነጣጥረዋል። ለዚህም እኩይ አላማቸው፤ የሌላውን ኢትዮጵያዊ ቀልብ ለመሳብና ብሔራዊ ስሜት ለመኮርኮር ሃሰተኛ ዜና እየፈበረኩ የሴራ ፖለቲካቸውን ያጮኹታል። የጥቂት ሰዎችን እኩይ እና ጽንፈኛ አመለካከት፤ እንደ አንድ ብሔር እሳቤ መላኪያ አድርገውም በየድኅረ ገጹና ዩ ቲይብ ላይ፤ የጦርነት መለከታቸውን ይነፋሉ።
የዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ ስለ “ኦሮሙማ” የፃፉት አደንቋሪና አሳሳች ጽሁፍ የዚህ እቅድ አንዱ ገጽ ነው። ዮናስ ከ11 ዓመታት በፊት በፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ “Promoting and Developing Oromummaa” በሚል ርዕስ የተፃፈውን ጽንፍ የረገጠ ጽሁፍ መነሻ በማድረግ ነው ዛሬ “ኦሮሞ መጣብህ” “አትነሳም ወይ” በብሔርና በሃይማኖት ተደራጅተህ “ጥቃቱን ተከላከል” የሚለውን ዲስክራቸውን የለቀቁት። በዚህ ጽሁፋቸው ፕሮፌስር አሰፋ የሚናገሩት፤ ኦሮሞን ስለማስተባበርና፤ “በቅኝ ገዥዎች” የኦሮሞ ሕብ ጠፋብት የሚሉትን ቋንቋ፤ ባሕልና እሳቤ እንደገና ስለማደስ ነው። ይህ ጽሁፍ፤ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ “ኦሮሞ የማድረግ” ዝንባሌ ያለው ጽሁፍ አድርጎ ማቅረብ፤ ከዛም አልፎ፤ ይህ እሳቤ በመላው የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርጎ መስበክ፤ ምሁራዊ ሸፍጥ ብቻ ሳይሆን፤ ሆን ብሎ የታቀደ የክፋት መንገድ ለመሆኑ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሁሉ ይገነዘበዋል ብዬ አምናለሁ። ፕሮፌሰር አሰፋ የፃፉት የራሳቸውን ሃሳብ እንጂ የኦሮሞን ሕዝብ የሚወክል ጽሁፍ እንዳልሆነ ማንም ፊደል የቆጠረና ትንሽ ማስተዋል የተቸረው ሰው የሚገነዘበው ነው። በየትኛውም መመዘኛ፤ ለአሰፋ እሳቤ ተጠያቂም መሆን ያለባቸው አሰፋ እንጂ መላው የኦሮሞ ሕዝብ ሊሆን አይችልም።
የዶ/ር ዮናስ ጽሁፍ፤ ሃሳቡ፤ የኦሮሞ ጽንፈኞች የአማራውን ሕዝብ ለመወንጀል ከሚጽፉት የሃሰት ትርክት የተለየ አይደለም፤ የኦሮሞን ጽንፈኛ ትርከት ወደ ጽንፈኛ አማራ ትርከት ገለበጡት እንጂ። የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ይሉሃል ይህ ነው። የኦሮሞ ጽንፈኛ በአማራ ተገዛን፤ ቁንቋችን፤ ባሕላችን፤ በአማራ ቁንቋ በአማራ ባህል ተተካ ሲል፤ የእንደ ዮናስ ዓይነት የአማራ ጽንፈኛ ደግሞ ቋንቋችን በኦሮምኛ ተተካ፤ ባሕላችን ኦሮሙማ ሊሆን ነው እያለ የቁራ ጩኸቱን ይጮሃል። ዮናስ፤ የአንድን ሰው ጽሁፍ እንደ መላው የኦሮሞ ሕዝብ እሳቤ አድርገው ማቅረባቸው፤ እኝህ ሰው በቀላቸውን ከግብ ለማድረስ፤ ሕዝብን ደም ለማቃባት የሄዱበትን አደገኛና አሳሳች መንገድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ነው። አዲስ እስታንደረድ በተባለው ጋዜጣ ግርማ ጉተማ የተባለ የኦሮሞ ጽንፈኛ ለዶ/ር ዮናስ የሰጠው ምላሽ፤ እነዚህ ጽንፍ የረገጡ ሁለት ሰዎች፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። አሁንም ለኢትዮጵያ የእግር ውስጥ እሳት የሆነው የእነዚህ የጥቂት ሁለት ዋልታ ረገጥ ጽንፈኞች ትርክቶች ናቸው።
ይህንኑ ደካማ ትርከታቸውን ለማጠናከር፤ ዶ/ር ዮናስ እንደ መረጃ የተጠቀሙት ሌላው ጽሁፍ፤ የጃዋር መሐመድን ጽሁፍ ነው። እኝህ ሰው፤ ጃዋር መሐመድን የአሰተሳሰብ ድኩማን መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹና ሲያብጠለጠሉ እንዳልነበር፤ የዚህን የሃሳብ ድንክዬ ጽሁፍ ማጣቀሳቸው፤ ዮናስ ምን ያክል ጭንቅ ውስጥ እንደገቡ የሚያሳይ ነው። ዮናስ ጃዋርን ሲጠቅሱ እንዲህ ይሉናል፤ “ታዋቂው የኦሮሞ ማህበረስብ አንቂ ጃዋር መሃመድ ባወጣው ባለ 76 ገጽ ጽሁፍ ችግሩ የመጣው የኦሮሞ ብልጽግና የኦሮሞን ማንነትና ባህል በሌሎች አካባቢዎች ለመጫን ባለው ፍላጎት ነው ብሏል።” ጃዋር መሐመድ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት “አሁን የኦሮምያን የአየር ሞገድ ተቆጣጥረነዋል፤ አሁን ደግሞ፤ የሚቀረን አሮምያን ከነፍጠኛ ማጽዳት ነው” ሲለን እንዳልነበር፤ ለበርካታ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ሞትና ስቃይ ምክንያት የሆነን የኦሮሞ ጽንፈኛ፤ ዛሬም ሸኔ የተባለውን ጨካኝ ቡድን የሚደግፍ ሰው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ችግር የኦሮሞን ብልጽግና ሲኮንን ማየትና የዚህን ሰው ሃሳብ፤ እንደ አንድ ጭብጥ መጋራት፤ ከአንድ “ምሁር” የማይጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ዶር/ ዮናስ የደረሱበትን የበቀል ምሬት በግልጽ የሚያሳብቅ ነው።
ኦሮሙማ ማለት ኦሮሞነት ማለት ነው፤ ኦሮሞነት ከአማራነት ወይም ከሌላ ማንነት የተለየ አይደለም። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ አንድ ቋንቋ፤ አንድ ባሕል፤ ወይም የአንድ ብሔር ብቻ ተጽእኖ ይኖራል ብሎ ማሰብ ሃገር ውስጥ ካለው ጭብጥ ጋር የሚጋጭ ነው። ዛሬ አማራነትንም ሆነ ኦሮሞነት በሲዳማ፤ በአፋር፤ በቤኒሻንጉል፤ በሶማሊያ፤ ወዘተ፤ ክልሎች መጫን አይቻልም፤ እያንዳንዱ ብሔር/ብሔረሰብ እራሱን እያስተዳደረ ያለበት የፖለቲካ አውድ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው። በፌደራል መንግስቱና በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ የኦሮሞ የተረኝነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ለመኖራቸው፤ ምንም ጥያቄ የለውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ ፀሃፍ በርካታ መጣጥፎችን አቅርቧል። ከዚህም አልፎ የኦሮሞ ጽንፈኞች ያለውን የፖለቲካ አጋጣሚ ተጠቅመው የራሳቸውን የፖለቲካ እሳቤ በሌሎች ላይ ለመጫን ሲንፈራገጡም ይታያል። ይህ ማለት ግን መንግሥት ፖሊሲ አርቅቆ፤ ከተቀረው የኦሮሞ ሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ የኦሮሞን የበላይነት በሃገር ውስጥ ለማስፈን ይሰራል የሚለው ትርከት፤ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ እንዲገለል የሚነረ የሃሰት ትርከት ነው። አሁን ያለው መንግሥት፤ ልክ እንደ አማርኛ፤ ኦሮምኛን በሕዝብ ላይ ለመጫን ያወጣው ፖሊሲ የለም። የኦሮሞ ባሕልንም ሆነ ማንነት በሌላው ላይ ለመጫን መንግስት እንደ መንግሥት ሰርቷል የሚባልበት አንድ ጭብጥ የለም። ዛሬም በሕግ የወጣው አማርኛ የፌደራሉ የመሥርያ ቁንቋ እንዲሆን ነው። ዐብይ አሕመድ በኦሮሞ ጽንፈኞች የተጠሉበትና (ነፍጠኛ) የሚል ታርጋ የተለጠፈላቸውና ከፍተኛ ውግዘት የደረሰባቸው፤ የኢትዮጵያን ታሪክ አጉልተውና አድምቀው በማሳየታቸው ነው። የኦሮሞ ጽንፈኞች፤ የኢትዮጵያ ጀግኖችን ሃውልት ሲያፈርሱ እኮ እሳቸው፤ የጀግኖቻችንን ሃውልት በቤተ መንግስት ውስጥ የተከሉ ናቸው። ንጉስ ምኒሊክን የሚጠላ ጽንፈኛ ኦሮሞ እየተቃጠለ ነው፤ ዳግማዊ ምኒሊክ ከነ ግርማ ሞገሳቸው፤ በቤተ መንግሥት ውስጥ ተቀርፀው የተቀመጡት፤ ቤተ መንግሥታቸው የሚጎበኘውና ታሪካቸው ደምቆና ጎልቶ የተፃፈው። የትኛው የኢትዮጵያ መሪ ነው ይህን ያደረግው?
ራስን በመስተዋት ማየት፤
ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ “ኢትዮጽያን ና የአፍሪካን ቀንድ ለማዳን የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና ወሳኝ ሚና” በሚለው ጽሁፋቸው፤ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፃፉት ጽሁፍና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግለጽ የተጠቀሟቸው እሳቤዎች፤ በሙሉ የዮናስ ብሩን ባህሪ የሚያሳዩ በመሆናቸው፤ ዶ/ር ዮናስ እራሳቸውን በመስተዋት እያዩ የፃፉት ለመሆኑ፤ ጥያቄ የለኝም። ዶ/ር ዐብይ ከልጅነታቸው ጀምረው ለሕዝብ የቆሙና ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው በትጥቅ ትግል አውድ ሚና የነበራቸው ናቸው። ዶ/ር ዮናስና መሰሎቻቸው የብሔራዊ ውትድርናን ሸሽተው ወድ ጅቡቲ ሲያቀኑ፤ ዐብይ ግን ወደ ትግል ሜዳ ነው የገቡት። ዐብይ ለሃገራቸው ከአንዴም ሶስት ጊዜ በጦር ሜዳ ዘምተው ተዋግተዋል። ግንባራቸውን ሳያጥፉ፤ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ከውስጥ በመሩት ትግል፤ ለወያኔ ከሥልጣን መነሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ዛሬም ሕይወታቸውን አስይዘው፤ ለመሞት ቁርጠኛ ሆነው፤ ለሃገራቸው የሚቻላቸውን እያደረጉ ነው። እኝህ ሰው፤ ራስ ወዳድ ሳይሆኑ ሃገር ወዳድ መሆናቸውን ደግመው ደጋግመው አስመስክረዋል። እነ ለማ መገርሳ ኦሮሞነትን እናስቀድም ሲሉ፤ ዐብይ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም አለብን ብለው ከቁርጥ ቀን ወዳጃቸው ከለማ መገርሳ ጋር ተለያይተዋል። ልጆችና ሚስታቸውን ለስደት ዳርገው እሳቸው የሞትን ጽዋ ለመጋት፤ ለሃገር በጽናት ቆመዋል። በሕዝብ መካከል ሰላም፤ ፍቅር፤ መተሳሰብ፤ እርቅ እንዲኖር ሰብከዋል፤ አሁንም እያስተማሩ ነው። በአንፃሩ፤ እንደ ዮናስ ያሉ ጽንፈኞች፤ ተሰደደ ተገፋ እያሉ ሙሾ ለሚያወርዱለት ሕዝብ አንድ ጠርሙስ የሚጠጣ ወኃ አቀብለው የማያውቁናቸው። እንደ ዮናስ ብሩ ዓይነት አዲስ መጥ “የብዕር ታጋዮች” በፍርሃታቸው ተሸብበው፤ የኢትዮጵያዊነት ጭንብላቸውን አጥልቀው፤ በምቾት ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ተግተው እየሰሩ ነው። እኝህ ውትድርና ላለመሄድ በፍርሃት ሸሽተው ከሃገራቸው ተሰደው፤ ዛሬ በሃገር ላይ ጦርነት ሲያውጁና “ጀግና፤ ጀግና” ሲጫወቱ ማየት፤ ገራሚ ብቻ ሳይሆን፤ “ጅብ ያማያውቁት ሃገር ሄዱ፤ ቁርበት አንጥፉልኝ” ይላል የሚለውን ተረት ያስታውሰኛል።
ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ለመምሰል መፍጋት፤
“አንዳንድ ሰዎች፤ ጥቅጥቅ ባለ የሚገርም ጨለማ ውስጥ ስለሚኖሩ ብርሃን ለማየት ሲሉ ያነዱሃል” ይላል ደራሲው Kamand Kojouri. ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ የበቀል ስሜታቸው ከወረወራቸው ጨለማ ለመውጣት፤ በተጫረው የጽንፈኞች፤ እሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ፤ ከጽንፈኛው የበለጠ ጽንፈኛ ሆኖ ለመታየትና አድናቂ ለማፍራት፤ የኦሮሞን ሕዝብ ሁሉ እሳት ውስጥ ለመጨመር ይዳክራሉ። ዶ/ር ዮናስ ኦሮሙማ ስለሚባለው ጽንሰ ሃሳብ የቃረሟትን ቁንጽል ሃሳብ ወስደው፤ ‘የኦሮሞ መንግሥት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ፤ በሞጋሳ ስልተ ስርዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ኦሮሞነትን ለመጫን ተግቶ እየሰራ ነው” ይሉናል። እኝህ ሰው “ዕውቀታቸውን” በቅዱስ ጽዋ ብርሌ እንደተቀመጠ እንቁ ነገር አድርገው ቢያቀርቡልንም፤ በዙ በፃፉና ባወሩ ቁጥር፤ ብዙ ነገር የማያውቁና፤ ምንም ዓይነት ግንዛቤ እንደሌላቸው ነው የተረዳሁት። ለመሆኑ ኦሮሙማ ምንድነው? ቀድም ብዬ እንደገለጽኩት ኦሮሙማ ኦርሞነት ነው፤ ልክ እንደ አማራነት፤ ሲዳማነት ወዘተ የአንደ ማህበረሰብ መገለጫ ነው። የኦሮሙማ ጽንሰ ሃሳብ፤ በኦሮሞ ብሔርተኞች ሲቀነቀን ዓመታት ተቆጥረዋል። እሳቤውም “አማራ ማንነታችንን አጥፍቷል፤ ቁንቋንችንን አጥፍቶ አማርኛን በግድ ጭኖብናል፤ ባሕላችንን፤ እንዲሁም አጠቃላይ የኦሮሞ ማንነታችንን አጥፍቶብናል፤ ስለዚህ፤ የኦሮሞን ማንነት ማስመለስ አለብን’ የሚል ነው። ዛሬ እያንዳንዱ ብሄር/ብሄረሰብ፤ ማንነቴ ተረግጧል፤ ቋንቋዬን፤ ባሕሌንና ማንነቴን አሳድጋለሁ፤ በሚልበት ወቅት፤ ኦሮሞው የኦሮሞን ቋንቋ፤ ባሕልና ማንነት ማሳድግ፤ ለጽንፈኛው ለምን ሥጋት ሆኖ ታየ?
ዮናስ፤ “ስጋታችንን ለመጨመር” ሲፈልጉ፤ ኦሮሙማን ማስፋፋት የተፈለገው፤ የሞጋሳን የአስተዳደር ዘይቤ በመጠቀም ነው ይሉናል። ለመሆኑ እኝህ ሰው ሞጋሳ ምን እንደሆነ ያውቃሉ? ሞጋሳ ማለት ጉዲፈቻነት ማለት ነው። ጉዲፈቻነት፤ ለአንድ ሰው ሲሆን፤ ሞጋሳ ደግሞ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ጉዲፈቻ ማድረግ ነው። አሌሳንደር ትሪዩልዚ እና ተሰማ ታዓ “የወለጋ የታሪክ ሰነዶች፤- ከ1880ዎቹ እስከ 1920ዎቹ (እ.አ.አ) በሚለው መጽሃፋቸው፤ የቦረና ሰዎች፤ በጦርነት ከሚማርኳቸውን ሰዎች ጋር በጋብቻ እንደሚተሳሰሩና ከዛም አልፈው በሞጋሳ (adoption) ቤተሰብ እንደሚያረጓቸው ይነግሩናል። ዶ/ር ሚልኬስ ሚዴጋ “Oromumma(ኦሮሙማ): Comprehensive Understanding of Oromoness” በሚለው ጃንዋሪ 17 2021 ባሳተሙት ጽሁፋቸው በሞጋሳ ጉዲፈቻ የሚሆኑ ሰዎች፤ በኦሮሞ ቤተሰብ የሚታቀፉት በፍላጎታቸው ብቻ መሆኑን ይነግሩናል። ታድያ እነ ዮናስ ብሩ “አያ ጅቦ መጣ” የሚለው የቅጥፈት ትርከታቸው ከምን የመነጨ ነው። የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ቁንቋ፤ ባሕልና ማንነት ማደግ፤ ለምንድነው በአማራ ሕዝብ ለሚነግደው ጽንፈኛ ሥጋት የሆነው?
አርኪዮሎጂስቱ ዶ/ር ገመቹ መገርሳ፤ “ጥሩ ኦሮሞ ያልሆነ ኦሮሞ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አይችልም” ይላሉ። ኦሮሞነት፤ አማራነት፤ ተግራዋይነት፤ ወላይታነት ወዘተ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ናቸው። አማራነት ለኢትዮጵያ ሥጋት እንዳልሆነ ሁሉ፤ ኦሮሞነት ለኢትዮጵያ ሥጋት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ዛሬ በየትኛውም ብሔር/ብሔረሰብ ላይ፤ ኦሮሞነትን ለመጫን የሚደረግ ጥረት የለም። ቀደም ሲል ከነበረው ስርዓት ዛሬ የሚለየው፤ እያንዳንዱ ክልል የራሱን ቋንቋ በትምህርት ፍኖተ ካርታው ውስጥ አካቷል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ ብቻ በግድ (በፖሊሲ ተቀርጾ) አትማርም፤ በትውልድ ክልልህ ቋንቋም የመማር ግዴታ አለብህ። ይህ ያስኮረፋቸው ጽንፈኞች ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ ጽንፈኞች ብቻ ናቸው። ከጽንፈኛው በላይ ጽንፈኛ ለመሆን የሚዳዳቸው የተከበሩ ዶ/ር ዮናስ፤ የኦሮሞ ሕዝብ የክርስትናን እና የእስልምናን ሃይማኖቶች ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን ያለምንም ሃፍረት ይነግሩናል። አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ፤ ክርስትናንም እስልምናንም የተቀበለ ሕዝብ መሆኑን ለዮናስ ዓይነት ሰው ጠፍቷቸው ነው?
ከዛም አልፎ፤ ዮናስ፤ መንግሥት አማራን ትጥቅ እያስፈታ ነው የሚለውን የሃሰት ትርከት ሊሸጡልን ይፈልጋሉ። ምንም እንኳን መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን እንደ አዲስ እያዋቀረ እንጂ ትጥቅ እያስፈታ እንዳልሆነ ቢታወቅም፤ በአማራ ክልል “ትጥቅ ማስፈታቱ” ልክ እንዳልሆነም ይነግሩናል። በጣም የሚገርመው ግን ክብርት ርዕዮት አለሙ፤ በሚያዘጋጁት “ምንጊዜም ሚድያ” ላይ በኅዳር 2022 እኔና ዶ/ር ዮናስ ባደረግነው ውይይት፤ ዶ/ር ዮናስ ሕወሃት ትጥቅ ከፈታ “የሁሉም የክልል ልዩ ኃይሎች” ትጥቅ መፍታት አለባቸው ብለው ሲሞግቱ ነበር። ዛሬ ግን ከጽንፈኛው ጋር የፖለቲካ ዝሙት ፈጽመው “አልጋ ለመጋራት” ሲተጉ ማየት፤ የእኝህ ሰው የበቀል ስሜት ምን ያክል ቁልቁል እንዳወረዳቸው ያሳብቃል።
አላዋቂ ሳሚ — ይለቀልቃል።
የተከበሩ ዶ/ር ዮናስ ብዙውን ነገር፤ ያለዕውቀት እንደሚናገሩ በቅርቡ፤ ራሳቸውን “የኦሮሞ” ተወካይ ያደረጉ ማንም ግን ወክሉኝ ያላላቸው የኦሮሞ ጽንፈኞች፤ የኦሮሞን ኮምኒቲን ወክለናል ብለው ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር ጋር ከጥቂት ቀናት በፊት ስብሰባ አድርገው ነበር። እነዚህ ጽንፈኞች፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ምን ያክል እንዳሳዘናቸው ለማይክ ሃመር መግለፃቸው ተዘግብዋል። ይህ የሚያሳየን፤ የዮናስ “ኦሮሞ ሁሉ ተባብሮ እየሰራ ነው” የሚለውን የሃሰት ትርከት ውድቅ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ጽንፈኛ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ነው። ምናልባት ዶ/ር ዮናስ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ “አዲስ በመሆናቸው” ብዙውን ነገር የሚጽፉት በጭብጥ በተመሰረተ እሳቤ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል። የኦሮሞ ሕዝብ እንደ አንድ ሊያስብ ይቅርና፤ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች እንኳን እንድ እንድ የማሰብ አቅም አላዳበሩም። ኦሮሙማ እየተባለ የሚጮኽበት መሰርት የለሽ የጽንፈኞች ትርከት የሚያመላክተው፤ ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት የደም ባሕር በሃገራችን ለመፍጠርና፤ በነጮች ቡራኬ ወደ ሥልጣን መምጣት ነው። ይህ “አንድን ሰው ለመግደል፤ ኅንፃውን የማቃጠል” እሳቤ አዋቂ በሚመስሉ፤ ግን ፖለቲካውን በቅጡ ባልተረዱ፤ በጭፍን ጥላቻና በቂም በተቋጠረ እሳቤ የሚቀነቀን አደገኛ የፖለቲካ መስመር ነው።
“ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” እንዲሉ፤ ዶ/ር ዮናስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሃይማኖት ጉዳይ ለመንከርና፤ ጽንፈኛውን ለማስደሰት የሄዱበት መንገድ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው። ሲሆን፤ እንዲህ ዓይነት ዕድሜ ጠገብ ሰዎች፤ ሰላምና እርቅ እንዲፈጠር ተግተው ይሰራሉ እንጂ፤ አገር እንድተተራመስ በሃሰት የተቀመመ ቤንዚን እሳቱ ላይ መጨመር አልነበረባቸውም። ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር የማንም ሴራ አይደለም። ይህ የቤተክርስቲያኗ አባቶች፤ የእርስ በእርስ አለመግባባት የፈጠረው ችግርና ችግሩን በሰላምና ሕግን በተከተለ መንገድ ለመፍታት ዘገምተኝነት መታየቱ ነው። በተለይ ላለፉት 30 ዓመታት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አጥር ላይ ተንጠልጥለው የራሳቸውን የፖለቲካና የዘረኝነት ዓላማ ለማሳካት ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ብዙ ሞክረዋል። ለዚህም ነው ዛሬ፤ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ብቻ እንኳን፤ ሁለት የቅድስተ ማርያም፤ ሁለት የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያናት ያለን። ትላንት የቀድሞው ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ሲመጡ ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩና፤ ድንጋይ ካልወረወራችሁ እያሉ ሌላውን ሲረግሙና በየሬድዮው እየወጡ ሲሳደቡ የነበሩ ጽንፈኞች፤ ዛሬ የቅድስት ቤተክርስቲያኗ ተቆርቋሪ መስለው ለመታየት ሲሞክሩ፤ ጉዳዩን በጥልቅ የምናውቅ ሰዎች ተገርመናል።
ዛሬ የጽንፈኛው አፈቀላጤ የሆነው መሳይ መኮንን ከጥቂት ዓመታት በፊት፤“የጎጃምና የጎንደር ካህናት፤ አዲስ አበባ ከሚገኘው ሲኖዶስ እራሱን መገንጠሉን መግለጫ አወጣ” ብሎ በደስታ ጮቤ እየረገጠ “ሰበር ዜና” ብሎ እንዳልዘገበና ስለነዚህ አባቶች “ጀግንነት” አውድሶ እንዳላወራ፤ ብፁእ ፓትርያሪኩ አባ ማትያስን፤ የሕወሃት የፖለቲካ ሹመኛ ናቸው ብሎ እንዳልተሳለቀ፤ ዛሬ “ቤተክርስቲያን በአብይ አሕመድ ሴራ ተከፈለች” ብሎ ሲዘግብ ትንሽ እንኳን ማፈር የሚባል ነገር አይታይበትም።
ብዙው ሰው መቀበል የማይፈልገው፡ በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ከፍተኛ ያለመግባባት እንዳለና ያንን አለመግባባት ለመፍታት ብዙ ጥረት እንዳልነበረ ነው። የቀድሞው አባ መላኩ (የአሁኑ አባ ፋኑኤል) ከዋሽንግተን ዲሲ የቅዱስ ገብርኤል እራሳቸውን ያገለሉት፤ “ዘርዎ ምንድነው” ተብለው ስለተጠየቁ መሆኑን የሚዘነጋ የዲሲና አካባቢው ነዋሪ የኦርቶዶክስ ምእመን ይኖር ይሆን? ይህን የዘረኝነት በሽታ የጠሉ ሰዎች አይደሉምን ከአባ ፋኑኤል ጋር ሆነው ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ያቋቋሙት? ይህ የትላንት ታሪክ፤ ዛሬ ተሰንግቶ ነው? ለመሆኑ ዶ/ር ዮናስ ኦሮሙማ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እይሰራ ነው ሲሉ ምን ጭብጥ ላይ ተመርኩዘው ነው። አባ ሳዊሮስ የተባሉት አባት፤ ከ 10 ዓመት በፊት ከቤተ ክርስቲያን አባቶችና በተለይም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር የነበራቸውን ችግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች አያውቁምን? ከ11 ዓመታት ገደማ በፊት፤ አባ ጻዊሮስ በሚመሩት የጉጂ ቦረና ሃገረ ስበክት ውስጥ የተፈጠረው ውዝግብ ለብዙዎች አዲስ ነውን? https://newawdemi.wordpress.com/2012/07/08/%E1%8B%A8%E1%8C%89%E1%8C%82- ይህንን ሊንክ ተከትሎ በወቅቱ ይወጡ የነበረውን መግለጫዎች ለሚያነብ፤ የቤተክርስቲያናችን ችግር የቆየና የጥቅም ግጭት መሆኑን ለመረዳት አይቸገርም።
እውነታው የአባቶች ችግር ሆኖ ሳለ፤ ለምን የመንግሥት ችግር ተደርጎ ተወሰደ? ብዙዎች በተሳሳተ እሳቤ፤ ቤተክርስቲያን ውስጥ ችግር ሲፈጠር “መንግሥት ሕግ ማስከበር አለበት” ሲሉ ይደመጣሉ። የቤተክርስቲያን ደንብ ተጣሰ ማለት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ተጣሰ ማለት አይደለም። መንግሥት ጣልቃ ሊገባ የሚችለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሲጣስ ብቻ ነው። ዶ/ር ዮናስ ይህንን በቅጡ እንደማይረዱ ከሚጽፏቸው ጽሁፎች መረዳት ይቻላል። የዶ/ር ዮናስ የዕውቀት ጉድለት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። እኝህ ሰው ከ40 ዓመታት በላይ አሜሪካ ውስጥ እነደኖሩ ቢነግሩንም፤ የፌደራል መንግሥት መዋቅራዊ አሰራር እንዴት እንደሆነ የማያውቁ መሆናቸውን በሚናገሩትና በሚጽፉት መረዳት ይቻላል። በአንድ ወቅት ሃርሜላ አረጋዊ ቃለ መጠይቅ ስታደርግላቸው፤ “ዐብይ ሽመልስን ማንሳት ቢፈልግ ይችላል” ሲሉ አዳምጬ ለእሳቸው አዘንኩ። የፌደራል መንግሥት አሰራር እንዴት እንደሆነም ስለማያውቁ ነው፤ በሸገር ከተማም፤ በጉራጌም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለተፈጠረ ችግር ጣታቸውን ዐብይ ላይ የሚጠቁሙት። ከዓምስት ዓመታት ገደማ በፊት ይህ ፀሃፍ “የመንግሥት ሥልጣን ከምን ድረስ ነው” በሚል መጣጥፍ፤ የፌደራል መንግሥቱንና የክልል መስተዳድድሮችን ሥልጣንና የሥልጣን ገደባቸውን በሚገባ አብራርቶ ጽፏል። ብዙዎች፤ በተሳሳተ ግምት ዶ/ር ዐብይ ፍፁም ሥልጣን (absolute power) ያላቸው አድርገው ይገምታሉ። ሥልጣናቸው ግን በሕግ የተገደበ ነው። በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጭ የፈለጉትን ማድረግ አይችሉም። የብዙዎቻችን ችግር፤ የለመድነው ሃገራችን በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ስትገዛ ነው። አሁን ያለንበት ጊዜ ግን ፍፁም የተለየ ነው። ጽንፈኛው ቡድን፤ ዐብይ ፈላጭ ቆራጭ እንደሆኑ ሊነግረን ቢሞክርም ሃቁ ግን ከዚህ የተለየ ነው።
የፌደራል መዋቅር፤ እያንዳንዱ ክልልና አካባቢ የራሱ የሥራ ድርሻ አለው። የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ የማይገባበት ብዙ ጉዳዮች አሉ። ዐብይ ሽመልስን አልመረጡም፤ ሽመልስን የማንሳት ምንም ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም። ባይደን የየትኛውንም የአሜሪካ ግዛት አስተዳዳሪ (governor) ማንሳት እንደማይችል ሁሉ ዶ/ር ዐብይም አይችሉም። አንድ ጥሩ ምሳሌ ለስጥ። በቅርቡ ሜሪላንድ ሞንትጎምሪ ካውንቲ ውስጥ የተፈጠረውን የግብረ ሰዶማውያንን የሚደግፍ የትምህርት ፖሊሲ እንደምሳሌ ብንወስድ፤ ይህ ፖሊሲ ካውንቲው ያወጣው ፖሊሲ ነው፤ ባይደን ቀርቶ የሜሪላንድ አስተዳድሪ በፈቃዱ መለወጥ አይችልም። በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የካውንቲው ነዋሪዎች ተቃውሞ የገለፁት በካውንቲው ውስጥ እንጂ ዋይት ሃውስ ሄደው አይደለም። የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ የሚመለከተው የፌዴሬሽንን ምክር ቤት ነው፤ የወልቂጤ ሕዝብ የወኃ ጥያቄ የሚመለከተው የወልቂጤ ከተማን አስተዳደር ገፍቶም ከሄደ የክልሉን መስተዳደር ነው። የሽገር ከተማ ጉዳይ የከተማውን አስተዳደር ገፍቶም ሲሄድ የኦሮምያ ክልልን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጭ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የየክልሉን መስተዳድር ሥራ ሊሰሩ አይችሉም። እራስን በራስ ማስተዳደር የሚለው መርህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብነት ሊተገበር አይችልም። እንደ ዶ/ር ዮናስ ያሉ ሰዎች እንዲህ ዓይነት የማያውቁትን ጉዳይ አንስተው ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ከሚተጉ፤ የቤት ሥራቸውን ሰርተው ለሃገር ጠቃሚ ነገር ቢሰሩ ይመከራል። በነገሬ ላይ ዶ/ር ዮናስና ጽንፈኛ አጋሮቻቸው፤ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወደ ሃገሩ ገንዘብ እንዳይልክ ለማሳደም ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው ቢሰሩም፤ ወደ ሃገር የሚላከው ገንዘብ በ 4.1% ጨምሯል። የአማራ፤ የኦሮሞና፤ የትግሬ ጽንፈኞች፤ ኢትዮጵያ ላይ ምእራባውያን ማዕቀብ እንዲጥሉ ቢወተውቱም፤ የተጣሉ ማዕቀቦች እየተነሱና ለኢትዮጵያም አዳዲስ እድሎች እየመጡ ነው። በቅርቡ የእንግሊዝ መንግሥት የሰጠው ከቀረጥ ነፃ የንግድ እድል አንዱ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከሰብዓዊ መብት ረገጣ ዝርዝር ውስጥ አውጥቷል፤ ከዛም አልፎ፤ የአለም የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ የ 3ቢልዮን ዶላር እገዛ እንዲደረግ ባለፈው ወር ወስኗል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የጽንፈኛው የቁራ ጩኸት ሳይሆን፤ የኢትዮያን እድል የሚወስነው፤ መሬት ላይ የሚሰራው ሥራ መሆኑን ነው። እነ ዮናስ፤ በሚያውቁትም በማያውቁትም ጉዳይ፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት በሃገራችን ቀውስ ለመፍጠር እየተጉ ያሉበት መርዛም ፖለቲካቸው፤ እየከሸፈ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ነው። (ይቀጥላል)
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ