
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ነሐሴ 6፣ 2023
ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በብዙ አፍሪካ አገሮች የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት፣ የህዝቦች ኑሮ መዘበራረቅና ዓላማ-ቢስ መሆን፣ እንዲያም ሲል በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ አሳቦ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ማድረግና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ወደ ርስ በርስ መተላለቅ እንዲያመራ መንገዱን ማዘጋጀት፣ በተራ አነጋገር ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከአምባገነናዊ አስተዳደር መስፈንና ከዲሞክራሲ አለመኖር ጋር ሲያያዝ ይታያል። አንዳንዶች እንዲያውም እንደዚህ ዐይነቱን ዓላማ-ቢስ የህብረተሰብ ጉዞ የአፍሪካ መሪዎች ወይም የጥቁር ህዝብ ችግር አድርገው የሚመለከቱ አሉ።
በእርግጥ ለአንድ አገር ስርዓት ባለው መልክ መተዳደርና፣ ህብረተሰቡም በዕቅድና በዓላማ እንዲመራ ከተፈለገ በዚያ የሰፈነው አገዛዝ ህብረተሰቡን በማደራጀት ረገድ የሚጫወተው ሚና አለ። ጥያቄው ግን አንድ ህብረተሰብ ዓላማ ባለው መልክ እንዳይደራጅና ቆንጆ ቆንጆ ስራዎችን እንዳይሰራ የሚያግዱት ነገሮች ምን ምን ናቸው? በስነ-ስርዓት እንዲደራጅስ ከተፈለገ መሪዎችም ሆነ ህብረተሰቡ መከተል የሚገባቸው ኖርሞች፣ ፍልስፍና፣ ሞራልና ስነ-ምግባር አሉ ወይ? ምንስ ይመስላሉ ? ወይስ አንድ ህዝብ እየተዋከበና ርስ በርሱ እየተፋጠጠ መኖሩ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው ወይ ? አንድ ህብረተሰብስ በምን መልክ ነው መታየት ያለበት? በሌላ አነጋገር፣ ለመብላትና ለመጠጣት ብቻ የሚኖርበት ? ወይስ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ ጥበባዊና ኢኮኖሚዊ፣ እንዲሁም ሌሎችም ነገሮች ተደራጅተው ህብረተሰቡ እንደሰውነታችን በብዙ ነርቮች ተሳስሮ፣ ልክ እንደደም ዝውውር ሳያቋርጥ፣ በተለይም ኢኮኖሚው አንድኛው መስክ ከሌላው ጋር በመያያዝ ውስጠ-ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ የሚጓዝበት መድረክ ነው ወይ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በአሁኑ ዘመን የግሎባል ካፒታሊዝም አይሎ መውጣትና፣ የብዙ ህብረተሰቦችን ህይወት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያመሩ ማስገደድና ማዘበራረቅ፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ፈራቸውን እየሳቱና በቀላሉ የማይመለሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል። በተለይም የየመንግስታቱ መኪና በከፍተኛ ደረጃ ሚሊታራይዝድ መሆንና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጦር ስልት ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ በዚህም ላይ የስለላው ድርጅት መጠናከርና ህዝብን አላላውስም ማለት፣ ብዙ የአፍሪካ መንግስታት አንድ መንግስት ለአገሩና ለህዝቡ ምን መስራት እንዳለበት እንዳይገነዘቡና አትኩሮአቸውንም በሀገር ግንባታ ላይ እንዳያደርጉ አግዷቸዋል ማለት ይቻላል። የየመንግስታቱትም ሚና ህብረተሰቡን ከማደራጀት፣ ህብረ-ብሄርን ከመገንባት፣ በሳይንስና በቲክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ ራስን ወደ ማጠናከሪያና ሀብት ዘራፊነት ተለውጧል። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና አገዛዞች የህዝቦቻቸው ተጠሪዎች ሳይሆኑ፣ በውጭ ኃይሎች የሚታዘዙና፣ በተለይም ጦርነትንና ህዝባዊ ሀብትን ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው።
ከዚህ ስንነሳ በፍጹም ልናልፈው የማንችለው ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኖ ይገኛል።ይኸውም ብዙ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ከሞላ ጎደል ስርዓት ባለው መልክ ተደራጅተው ሲጓዙና፣ የብዙ ሚሊያርድን ህዝቦች ዕድል ወሳኝ መሆን ሲችሉ፣ እንደኛ ያለውንስ ህዝብ ስነ-ስርዓት ያለው አደረጃጀት ለምን ተሳነው? ስነ-ስርዓትስ ባለው መልክ ለመደራጀት የሚጎድሉን ነገሮች ምንድናቸው? ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ህብረተሰብአዊ ? ወይስ የፖለቲካ ፍልስፍና እጦትና መሪዎች የሚመሩበት አንዳች ፍልስፍና አለመኖር ?
ለአንድ ህብረተሰብ በስነ-ስርዓት መደራጀትን አስመልክቶ ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮም ሆነ ከዚያም በፊት ህግና ስርዓት አስፈላጊ መሆናቸውን በብዙ ምርምር የተደረሰበትና በኢምፔሪካል ደረጃም የተረጋገጠ ነው። ይሁንና ግን በተለይም ፍልስፍናን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝና፣ አንድም ህብረተሰብ ሚዛናዊ በሆነ መልክና በስነ-ስርዓት የማደራጀትን አስፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ውይይት የተካሄደበት ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የተነሱና ብዙም ምርምር የተካሄደባቸው የፖለቲካ ፍልስፍናዎች፣ ህብረተሰብን በአንድ ስርዓት ባለው መልክ ማደራጀት፣ በግሪኩ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ላይ ተመርኩዞ ነው። እዚህ ላይ ሌላው የሚነሳው ጥያቄ፣ የተለያዩ የግሪክ ፈላስፋዎች አትኩሯቸውን ለምን በፍልስፍና ላይ፣ በተለይም በፖለቲካ ፍልስፍና ላይ አደረጉ ? የሚለው ከባድ ጥያቄ መመለስ ያለበት ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ለህይወቱ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያና ራሱንም ለመከላከል መሳሪያዎች ቢያስፈልጉትም፣ ከዚህ ዘልቆ በመሄድ የማሰብ ኃይሉን በማዳበርና ራሱንም በማደራጀት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም መሆን እንደሚችል የታወቀ ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ጉዳዮች በየጊዜው ሊሻሻሉና በቁጥር እየጨመረ ከሚሄደው ህዝብ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉት የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ሚናነት በግልጽ ከተቀመጡና፣ በነዚህ ላይ ከፍተኛ ርብርቦሽ ከተደረገ ብቻ ነው።፡ይሁንና አንድ ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር፣ አዳዲስ መሳሪዎችን በመፍጠር ከዝቅተኛ ህብረተሰብ ወደ ከፍተኛ እንዳይሸጋገር፣ ከቁም ነገር ስራ ይልቅ በሆነ ባልሆነው ነገር በመያዝ ወይም በጦርነት በመጠመድ ዝብርቅርቅ ኑሮ እንዲኖርና፣ በዚያው እንዲገፋበት የሚያደርጉትና፣ ይህ ዐይነቱም ኑሮ እንደ ባህልና እንደ ልማድ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ይህንን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመራመሩት የግሪክ ፈላስፎች የሰው ልጅ ከእንስሳ የተለየ ከሆነና፣ ራሱንም ማደራጀትና በሰላም መኖር የሚችል ከሆነ ለምንድን ነው ወደ ጦርነት የሚያመራው? ለምንድን ነው የተዘበራረቀ ኑሮ የሚኖረው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ነበረባቸው።
ሙሉውን በ ፒ ዲ ኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ