spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትበኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ጥቆማዎች 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ጥቆማዎች 

Ethiopian Political Parties _

አደፍርስ በላቸው (PhD) 

ይህ ርዕስ አሁን በአገራችን ኢትዮጵያ ለተከሰቱት መሰረታዊ ችግሮች መንስኤ ከሆኑት አንኳር ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ፣ የችግሩን መጠን ዘርዘር አድርጎ መፈተሽ እና የመፍትሄ አቅጣጫ ማሳየት ወቅታዊ እና ከፍተኛ ትኩረት ሊቸረው ይገባል ብሎ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል። 

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታ እና እንቅስቃሴ ከሌላው አለም አንፃር ሲታይ በጣም አጭር እድሜ ያስቆጠረ መሆኑን እንገነዘባለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ አስተዳደር ስርአት በንጉሳዊ አገዛዝ እና በአካባቢ ጎሳ መሪዎች የአስተዳደር ዘይቤ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ልምድ ነበረው። 

በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአገዛዝ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሚቀነቀኑት መፈክሮች መሃል ዋና ዋናዎቹ “መሬት ላራሹ” እና “ዲሞክራሲ እንደ እንግሊዝ” የሚሉ እንደነበሩ ማስታወስ ይቻላል። ይህም እሳቤ የዘውድ ሥርዓቱ ለአገር አንድነት እና ምልክትነት በአሰባሳቢነት እንዲቆይ ሆኖ የመንግስት የአሠራር ስርአት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቁመው እነሱ ፕሮግራማቸውን ለህዝብ እያስተዋወቁ በሚደረግ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይወሰን የሚል እንደነበር የሩቅ ጊዜ ትዝታ አይደለም። በአጭሩ የነበረው ጥያቄ ስርአታችን የእንግሊዝን (United Kingdom) የፖለቲካ ስርአት አይነት ይሁን የሚል ነበር። ሆኖም የተካሄደው የመንግስት ለውጥ ግብታዊ ሆኖ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የታጀበ ስለነበር እና በወቅቱ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመኖራቸው ብዙ ውዥንብር ተፈጥሮ ነበር። 

በነበረው ሂደት ውስጥ የምስራቁ የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም (ideology) ወደ አገራችን ሰርጎ በመግባት እና ወታደራዊው መንግስትም የሶሻሊስት እሳቤውን ስላመነበት አንዳንድ “ፖለቲካ ድርጅት መሰል” ስብስቦች (እንደ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ እና ሌሎችም) ተቋቁመው ይህንኑ የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም በማቀንቀን ሊንቀሳቀሱ ሞክረው ነበር። ሆኖም የወታደራዊው መንግስርት (ደርግ) በራሱ የሚመራ አንድ ፓርቲ ብቻ ፈቅዶ “የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ)” በሚል ስያሜ እስክ 1983 ዓ.ም ድረስ በሥራ ላይ መቆየት ችሏል። 

በ1983 ዓ.ም በጦርነት በግብታዊነት ወደ ስልጣን የመጣው ህወሀት መሩ የኢህአዴግ ቡድን በአሠራር ከደርግ ለየት ባለ መልኩ የብዝሐ የፖለቲካ ፓርቲ (multi-party system) ስርአት ለማስፈን ሙከራ ቢያደርግም በመጨረሻ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በማፈን እና ባለማሰራት አውራ ፓርቲየሚል መጠሪያ ለራሱ በመስጠት የዴሞክራሲ እና ነፃ ምርጫ አሠራር የግርዶሽ አዙሪት ውስጥ ሊገባ ችሏል። 

በ2010 ዓ.ም በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ሲመራ የነበረው ህወሀት መሩ ኢህአዴግ ከአባል ድርጅቶቹ መሃል ህወሀትን ብቻ ከውስጡ በመቀነስ የተወሰነ ማስተካከያ በማድረግ እና ስሙን ወደ “ብልጽግና ፓርቲ” በመቀየር ዛሬ በምናየው መልኩ የአውራ ፓርቲ መሪነቱን አስቀጥሎ ይገኛል። 

ከላይ ባጭሩ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው በኢትዮጵያ የብዝሐ ፓርቲ ስርአት ልምድ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ሲታይ እድሜው እና ልምዱ እጅግ አጭር (ከ30 አመት ያልበለጠ) ሆኖ እናገኛዋለን። 

የ 30 አመት ጊዜውም ቢሆን ህብረተሰቡ የዴሞክራሲ ስርአትን ተለማምዶ፣ ልዩ ልዩ ፍላጎቶቹን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዳይጠይቅ እና ውጤት እንዳይገኝ፣ ስልጣን ላይ የወጣው ፓርቲ ኃይልን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመቁጠር “በደማችን ያገኘነውን ስልጣን በወረቀት መቀማት አይቻልም” እስከ ማለት ደርሶ ነበር። ይህም ያልተገባ አቋም ችግርን በጠመንጃ አፈሙዝ የመፍታት አማራጭ አዋጪ ባህላዊ አሠራር እስኪመስል ድረስ እስከዛሬም ድረስ ከ “ጦረኝነት አዙሪት” ልንወጣ አልቻልንም። 

ዛሬም በአገራችን ኢትዮጵያ አንዣቦ የሚገኘው መጠነ ሰፊ አስተዳደራዊ ድክመት እና ግጭት በዚህ ሰው ሰራሽ የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት(vicious circle) የተወሳሰበ በመሆኑ፣ የሚከሰቱ የተፈጥሮ ችግሮችን ተቋቁሞ አገራዊ ልማት እና እድገት ላይ ማተኮር አልተቻለም።

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የተመሰረቱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉልህ ድክመቶችን ዘርዝሮ ማየቱ፣ ጎልተው የሚወጡ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ በፓርቲዎች መካከል ለሚደረግ ትብብርም ይሁን አንድነት ጠቃሚ መራጃ ሊሰጥ ይችላል። 

በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አመለካከት መሰረት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉት ፓርቲዎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚከተሉት ችግሮች ሰለባ ናቸው። 

1ኛ ፟> የመንግስት ሥልጣን የያዘው/የሚይዘው ፓርቲ የመንግስት መዋቅርን፣ ሀብትን እና ሠራተኞችን ለግል የፓርቲ ሥራ የመጠቀም ችግር፣ 

ይህ ችግር በመኖሩ ምክንያት የፓርቲ እና የመንግስት ሥራ መደበላለቅን እና መደራረብን አስከትሎ፣ በተለያየ ደረጃ ላይ የተመደቡ ሀላፊዎች እና ሙያተኞች በሥራ ብዛት ወይም በስብሰባ መደበኛ ሥራቸው ላይ ስለማይገኙ ህብረተሰቡ የተለያየ አገልግሎት በወቅቱ ማግኘት አልቻለም፣ እጅግ የበዛ የስብሰባ ጋጋታ ይካሄዳል! አገልግሎት ቢገኝም በብዙ የቀጠሮ ምልልስ የሚከወን ነው። ቀጠሮም በግብታዊ ክስተቶች ምክንያት ይሰረዛል። ከፍተኛ የህዝብ አገልግሎት መዛነፍ ይስተዋላል። እጅግ ብዙ ምሬት ይስተጋባል። ኮራፕሽን ተንሰራፍቷል። 

በዚህ ሂደት ውስጥ ሁሉም የመንግስት አካላት ከህግ አውጪው ጀምሮ በተዋረድ እስከታችህ ድረስ በአንድ ፓርቲ ዲሲፕሊን የተጠረነፉ ስለሆነ እና ብዝሀ ሃሳብን ማስተናገድ ባለመቻሉ፣ ያሉትም መንግስታዊ ተቋማት በፓርቲ ፍላጎት አግልግሎት ላይ ስለሚውሉ፣ በተለይ ደግሞ ፓርቲዎች በጎሣ ማንነቶች ለይ በመመስረታቸው ምክንያት የአንድ ጎሣ አባላት የአድራጊና ፈጣሪነት እና ጠቅላይነት ስልጣንተንሰራፍቷል የሚል ስሜት እና ጥርጣሬ እንዲሁም አቤቱታዎች በሌሎች ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል። በእነዚህ እና መሰል ተግዳሮቶች ምክንያት በሁሉም አካላት ተቀባይነት ያገኙ የመንግስታዊ ተቋማት አደረጃጀት መፍጠር እና የዴሞክራሲያዊ አሠራር ባህል መገንባት አልተቻለም።  

በኢትዮጵያ የድህነት እና የመሃይምነት ስፋት እና ጥልቀት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ህዝቡ በመንግስት ለሚደርስበት አስተዳደራዊም ሆነ የልማት እጦት ችግር፣ ከግላዊ እና መለኮታዊ እሳቤ ጋር በማያያዝ ከራሱ በስተቀር ማንንም ተጠያቂ ሳያደርግ “ከፈጣሪ በታች መንግስትን የማመን” እና የመቀበል ከፍተኛ ዝንባሌ ያሳያል። 80% የኢትዮጵያ ህዝብ በሚኖርበት የገጠሩ አካባቢ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለገበሬው ለማዳረስ፣ መንግስት እነዚህን ግብአቶች እንደ “መያዣ” ስለሚጠቅምባቸው ገበሬው በገዢው ፓርቲ ተጠርንፎ እና በምርጫ ወቅት ድምፁን ስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ እንዲሰጥ ይገደዳል በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ይስተዋላል። “መራጭ ህዝብ ከመንግስት ጭሰኝነት ሳይወጣ ለውጥ አይመጣ” የሚለው አባባልም ከዚህ እውነታ የመነጨ ነው። 

ይህ አሰራር ስልጣን ላይ በወጣው ፓርቲ እና በተፎካካሪዎቹ መካከል እንዲሁም ህዝቡን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚታየውን ከፍተኛ ቅራኔ እና አለመተማመን የፈጠረ በመሆኑ ከዚህ አዙሪት መውጣት ለነገ የማይባል ተግባር ነው። 

2ኛ > በአንዳንድ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የፖለቲካ ጥያቄን እና የሰብአዊ መብትን ጉዳይ ደበላልቆ፣ ወይም የወንጀል ድርጊት ችግርን ከፖለቲካ አጀንዳ ጋር አዳምሮ ሲሠራ በሰፊው ይስተዋላል። 

በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግስትም ሆነ በአለም አቀፍ ድንጋጌዎች በአጽንኦት የተደነገገውን የዜጎችን የሰብአዊ መብት መከበርን፣ ማለትም ሃሳብን በነፃ የመግለጽን፣ በየትኛውም የአገራችን አካባቢ ተዘዋውሮ መሥራትን እና መኖርን፣ እንዲሁም ሀብት ንብረት የማፍራትን መብት በሚፃረር መልኩ ህገወጥ ድርጊት ሲሰበክ እና ሲፈጸም ይታያል። ዜጎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ማፈናቀል፣ መግደል፣ ንብረት መዝረፍ፣ ፖለቲካ ጥያቄ ሳይሆን ደረቅ ወንጀል መሆኑ ተዘንግቷል! በሚያሳዝን እና በሚያስተዛዝብ ሁኔታ አንዳንድ ፓርቲዎች ይህን ድርጊት በመኮነን 

እና ደጋፊዎቻቸውን በተገቢው መንገድ ማስተማር ሲገባቸው ሁኔታውን በዝምታ ወይም “የተለያዩ ግጭቶች እንዲቆሙ መንግስት የፖለቲካውን ምህዳር ማስፋት እና ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ አለበት” የሚል የምስጠት መግለጫ በማውጣት፣ በተዘዋዋሪ የተፈጠረውን የወንጀል ድርጊት እና የሰብአዊ መብት ጥሰትን በፖለቲካ ሰበብ ለመሸፋፈን እና ለመደገፍ ሲሞክሩ ይታያል። ይህ ድርጊት ከፍተኛ መጠራጠርን እና አለመተማመንን የፈጠረ

ክስተት ነው። ችግሩ ካልታረመ በስተቀር ስለ ፖለቲካ መነጋገራችንን ትተን በሌላ አሁን ከሚታየው የበለጠ እጅግ ከፍተኛ አጠቃላይ ምስቅልቅል ውስጥ የሚከተን ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሯል። 

3ኛ > ፖለቲካን በብሔረሰብ ማንነት (ጎሣ) ላይ መሰረት የማድረግ ዝንባሌ ሌሎች ሁለንተናዊ እና አገራዊ የጋራ ችግሮች(ጥያቄዎች) እንዲረሱ ወይም በቂ ትኩረት እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። 

የዚህ ወቅት የፖለቲካ ትግል፣ አጠቃላይ አገራዊ እሳቤን አንድነትን በሚመለከት፣ ከንጉሡም ሆነ ከደርግ ጊዜ ያነሰ ሆኖ በአካባቢ ማንነት ላይ ብቻ እንዲያጠነጥን ሲሰራ ይታያል። ይህም ለፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት የተወዳዳሪነት ፖሊሲን በጥልቀት የመቅረጽም ሆነ የማስረጽ ሥራን ሳይጠይቅ ማህበረሰቡን “ሆድ የማስባስ ፖለቲካ” ውስጥ ብቻ ዘፍቆ እሱን እያሰበ እንዲውል እንዲያድር አድርገውታል። ይህ አሰራር በተለይ በህወሀት በሚመራው ኢህአዴግ መንግስት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ አንዱን ህዝብ ከሌላው የማራራቅ እና በጠላትነት እንዲፈራረጁ በተለየ ስልት ሲሰራበት ቆይቷል። የቄሮ እና የፋኖን መናበብ በመመልከት “እሳት እና ጭድ እንዴት አንድ ላይ ሊመጡ ቻሉ? ይህ የሚያሳየው እኛ ሥራችንን በበቂ አለመሥራታችንን ነው” የሚለው የአቶ ጌታቸው ረዳ ያደባባይ ንግግር የቅርብ ጊዜ ማስረጃ ነው። ዛሬም ስልጣን ላይ ያለው የ “ብልጽግና” መሩ መንግስ ከትላንቱ የተሻለ መንገድ ሲከተል አይታይም። እንዲያዊም ይባስ ተብሎ በአንዳንድ የክልል መሪዎች ልዩነቱን በሚያሰፋ እና ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ያደባባይ ንግግር ሲደረግ ይደመጣል። 

4ኛ > በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋሙ ፓርቲዎች የአንድን አካባቢ ማህብረሰብ የተለየ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በጥልቀት እና በቅርበት የማየት እና የማስተናገድ ውስንነት መታየት ሌላው ተግዳሮት ነው፣ 

የአገር አቀፍ ፓርቲዎች የእይታ አድማሳቸው በሁሉም ክልል ለሚኖረው ህብረተሰብ በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እና የጋራ ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ በሚጠቁሙ ዚዴዎች እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብት አጠባበቅን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ነው። በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን፣ ለምሳሌ “ወደ ክልል ልደግ፣ ማንነቴ ይከበር፣ በቋንቋየ ልሥራ፣ እራሴን በራሴ ላስተዳድር፣ እና መሰል ጥያቄዎችን” አገር አቀፍ ፓርቲዎች ሲያቀነቅኑ አይታይም። ምክንያቱም ፓርቲዎቹ የቆሙበትን መርህ እና ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ እና ከመሰረታዊ የፖለቲካዊ ርእዮተ አለማቸው አንፃር ተቃርኖ ስለሚፈጥርባቸው፣ የማንነት ጥያቄዎችን የፓርቲው መታገያ አጀንዳዎች ሊያደርጓቸው አይችሉም። ስለሆነም ይህ አቋማቸው ልዩ ልዩ አካባቢያዊ ጥያቄ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አያስገኝላቸውም። 

በሌላ በኩል እነዚህ ማንነት እና አካባቢ ተኮር ጥያቄዎች ዲሞክራሲ ከሰፈነ፣ የግለሰብ ሰብአዊ እና የዜግነት መብት ከተከበረ በራሳቸው ጊዜ መልስ ያገኛሉ የሚሉ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፣ ሌሎች የህብረተሰብ ሳይንስ ተንታኝ ምሁራን ደግሞ እነዚህን የአካባቢ ልዩ ጥያቄዎች ለመመለስ በማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም አስፈላጊ አይደለም ይላሉ። ጥያቄዎቹ በልዩ ልዩ የማህበራዊ አደረጃጀቶች (civic organizations)  አማካይነት የፓርቲ ወገንተኝነት ሳይጠይቅ ህዝቡን ሁሉ አስተባብሮ መጠየቅ እና ማስፈጸም ይቻላል የሚል አመለካከት አላቸው። ትክክለኛው መንገድም ይህ ነው ብለው ይከራከራሉ። 

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በተግባር መሬት ላይ እየታየ ያለው ልምድ የሚያሳየው በየአካባቢው “በማንነት ፖለቲካ” ላይ ፓርቲ መስርቶ የስልጣን ተጋሪነትን የማረጋገጥ ሥራ ነው። ይህም ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ የህዝብን ጥቅም የሚያስጠብቁ ፓርቲዎችን አቋም የሚያዳክም እና ለ“ከፋፍለህ ግዛው” መርህ ተጋላጭ ያደርጋል። 

አጠቃላይ ፖለቲካውም በርእዮተ አለም እሳቤ እጦት እንዲቀጭጭ እና የተለያዩ አገራዊ እና ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ የፖሊሲ አማራጮችን ለህዝብ ምርጫ አቅርቦ ለመወዳደር አዳጋች አድርጎታል። 

5ኛ > የልዩ ልዩ ፓርቲ መሪዎች የመሪነት ክብር/ጥማት (personal ego) ሊታለፍ የማይቻል ትልቅ ችገር ሆኖ ይታያል። “እኔ ካልመራሁት ይህ ፓርቲ ህይወት አይኖረውም” ወይም ደግም “እነ እንትና” ከኔ ጋር ሲነፃጸሩ በብዙ መልኩ ያነሱ ሆነው በነሱ እንዴት እመራልሁ ብሎ የመሸሽ/ የመገንጠል ሂደት ይታያል። በኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ “በኪሱ አንዳንድ ዘውድ ይዞ ይዞራል” የሚለው አባባል ከዚህ የመነጨ ይመስላል። ብዙ ፓርቲዎች እዚህ ግባ የሚባል የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፖሊሲ ልዩነት ሳይኖራቸው፣ በመሪዎች መገፋፋት ምክንያት ተጣምረው ወይም ተዋህደው መሥራት ባለመቻላቸው፣ ከፍተኛ በውድድር የማሸነፍ እድል

ሲያመልጣቸው ተስተውሏል። የብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ማሸነፉ በዚህ ምክንያት ነው ብሎ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያስባል። 

የመፍትሄ ጥቆማዎች 

ሀ > ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለወደፊቱ የሰዎችን መሰረታዊ ሰብአዊ መብትን ማክበር፣ ማስከበር፣ ለደጋፊዎቹ ማስተማር፣ ጥሰት ተፈጽሞ ሲገኝ ከምንም የፖለቲካ ጥያቄ ጋር ባለማገናኘት ወይም ሰበብ ባለማፍጠር በግልጽ ማውገዝ፣ መንግስት የዜጎችን መብት እንዲያስከብር እና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ ማቅረብ። ይህ ሳይሆን እስካሁን እንደሚታየው በሽፍንፍን ወንጀልን ከፖለቲካ ጋር አዳምሮ ለማለፍ ወይም የችግሩ ፈጣሪዎችን ለማቀፍ የሚሞከር ከሆነ፣ ይህ አቋም ለፓርቲው የወደፊት ተቀባይነትም ሆነ የጎንዮሽ ትስስርን ለመፍጠር ፍጹም አዳጋች ያደርገዋል። የህዝብን የርስ በርስ ግንኙነት በመሸርሸር አጠቃላይ አገራዊ ቀውስ ይፈጥራል። በመጨረሻም ከውጭ ጠላት በስተቀር ማንም የውስጥ ተጠቃሚ ነጥሮ አይወጣም። ይህ እጅግ መሰረታዊ የሆነ መታለፍ የሌለበት ቀይ መስመር መሆኑን መረዳት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህን ቀይ መስመር በሚያልፉ ፓርቲዎች ላይ ሌሎቹ ፓርቲዎች የጋራ አቋም በመውሰድ ከህግ አስከባሪው ኃይል ጋር ተባብረው ህግ እንዲከበር ማድረግ ተገቢ ነው። 

ለ > የመንግስት መዋቅሮች እና ሠራተኞች የፓርቲ ሥራን ከመንግስት ሥራ ጋር ደበላልቀው እንዳይሰሩ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርግ የጋራ ፕላትፎርም/መድረክ ማደራጀት (ያለ ተጨማሪ ወጪ በፓርቲዎች አደረጃጀት መስመር ብቻ ሊከወን ይችላል)። 

ሐ > በመንግስት ለውጥ ወቅት በፓርቲ የሚመደቡ የሥራ መደቦች እስከምን ደረጃ ድረስ መሆን እንዳለበቸው በጋራ መወሰን እና ከዛ ውጭ ያሉ የቴክኒክ ሠራተኞች (technocrats) ሁል ጊዜ በቋሚ ሠራተኞች በችሎታ (merit) የሚሞሉ መሆናቸውን መቀበል፣ በአፈጻጸም መተግበር። የመንግስት ለውጥ ሲደረግ እና ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ የመንግስት ሠራተኞች መደበኛ ሥራቸው የማይነካ መሆኑን በሁሉም ፓርቲዎች ማኒፌስቶ ማረጋገጥ። ይህ ከሆነ የመንግስት መዋቅር እና ሠራተኞች ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩል የማገልገል አሠራር እና ልምድ ይፈጥራል። 

መ > ማንኛውም ፓርቲ ከላይ በመፍትሔ አቅጣጫ ተራ ቁጥር አንድ የተጠቀሰውን መርህ ሳይጥስ በፈለገው ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የመደራጀት እና የመታገል መብት እንዳለው ይታመናል። ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ ባለው የምርጫ ህግ መሰረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ(ጥምረት) ተወዳድሮ ስልጣን ለመያዝ ካሰበ፣ ግራ እና ቀኝ የተወጣጠረውን የተቃርኖ የፖለቲካ አካሄድ አርግቦ የልሂቃን መቀራረብ (elite bargaining) እና የፕሮግራም መጣጣም ፈጥሮ በጋራ መሥራት ውጤት አልባ ከሆነው ከዜሮ ድምር ጨዋታ (zero-sum game)  የሚያወጣ ይሆናል። 

ሠ > በአሁኑ ወቅት በህጋዊነት ተመዝግበው የሚገኙት ፓርቲዎች አሁን ባለው ሁኔታ (status quo)  ከቀጠሉ፣ በተለይ እንደ ኦነግ እና ኦፌኮ ሰፊ መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች የክልላዊ አጀንዳቸውን ስስ ወይም ልል በማድረግ በሰብአዊ እና በዜግነት መብት ላይ ያላቸውን ድክመት አሻሽለው ከሌሎች ሰፊ መሰረት ካላቸው አገራዊ ፓርቲዎች ጋር ተጣምረው/ተዋህደው ካልሰሩ እና ለውድድር ካልቀረቡ በተናጠል “ብልጽግና” የሚባለውን ግዙፍ አገር አቀፍ ፓርቲ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ያዳግታቸዋል። በአካባቢያቸው በምርጫ የበላይነት የማግኘት አጋጣሚ ቢፈጠርም እንኳን፣ ለአገራዊ ስልጣን በሚያበቃ ደረጃ እና የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጣ በሚስያስችል አቋም የፓርላማ ወንበር ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል የሚል አመለካከት አለ። 

ረ > በዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እሳቤ መሰረት፣ ካሁን ቀደም የብልጽግና ፓርቲን ለመገዳደር “የፌደራሊስቶች ጥምረት”  በሚል በህወሀት የተሞከረው እና ዛሬም በአንዳንድ ክፍሎች የሚቀነቀነው አካሄድ በተግባር ቢታይ መሬት ላይ ያለው የፖለቲካው ምህዳር “በተመሳሳይ አጀንዳ” በብልጽግና የተያዘ ስለሆነ የተለየ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። የፌደራሊስቶች ስብስብ ስልት እና ግብ ስልጣን ላይ ያለውን ኃይል አሰላለፍ በተዘዋዋሪ ለመድገም የሚሞክር አይነት አካሄድ ነው። እዚህ ላይ ግንዛቤ መወሰድ ያለበት “ብልጽግና” ስሙ ነው እንጂ አሠራሩ ከትላንቱ ኢህአዴግ ብዙም ያልተለየ ነው። ብልጽግና በአደረጃጀት ፖሊሲው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ

የፓርቲው አባል መሆን ይችላል ቢልም፣ በተግባር ግን ኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ነው ይሉታል። በሌላ አገላለጽ ልዩ ልዩ “የብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ አስተዳደሮች” በአባልነት ታቅፈው ከነሙሉ መንግስታዊ መዋቅራቸው፣ የአካባቢውን ሃብት እና የሰው ኃይል ተጠቅመው የመሰረቱት ግዙፍ ፓርቲ ነው። የመንግስትን ሀብት እና ንብረት ለፓርቲ አገልግሎት መጠቀምን የምርጫ ህጉ ባይፈቅድም፣ በተግባር ግን በአምስት አመቱ የዝግጅት ጊዜም ይሁን በምርጫ ወቅት በቀጥታ ስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ ጥቅም ሲሰጥ ይስተዋላል። ይህ አሠራር ካልተስተካከለ ነፃ እና ፍትሃዊ የፖለቲካ ምህዳር እና መወዳደሪያ ሜዳ ስለማይኖር አሁን ለሚናየው አይነት ቀውስ አባባሽ ሁኔታን ይፈጥራል። 

ማጠቃለያ 

ከላይ በተገለጸው መሰረት ሰፊ መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች ካሁን በፊት እንደተለመደው የጋራ ጠላትን ለማሸነፍበጊዜያዊነት የሚደረግ ጥምረትን አስቀርተው፣ ዘለቄታ ያለው የጋራ አጀንዳ ፈጥረው ሌላ አገራዊ እና በሁሉም ዘርፍ መገዳደር የሚችል ታላቅ ጥምረት/ስብስብ ወይም ውህድ ፓርቲ ካልፈጠሩ በስተቀር በተበታተነ ተወዳዳሪነት እዚህም እዛም በማሸነፍ ከፍተኛው የስልጣን ማማ ላይ መድረስ እጅግ አዳጋች ይሆናል። በጎንዮሽ መተጋገል እና ተቃርኖ እስካሁን የመጣንበት የፖለቲካ ልምድ ሊያስተምረን ከቻለ ምናልባት አገኘናቸው ከምንላቸው የፖለቲካ አዎንታዊ ውጤቶች ይልቅ የተከሰቱት ስህተቶች እና በህዝቡ ላይ የደረሰው ሰቆቃ (የደጋፊዎች ሞት፣ እንግልት፣ ተደጋጋሚ እስር፣ የኑሮ መመሰቃቀል፣ ወዘተ) ጎልቶ የወጣበት ክስተት ነበር። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ወገን ሊያስተሳስሩ እና የፓርቲ ቁጥርንም ሊመጥኑ የሚችሉ እጅግ ትልልቅ አጀንዳዎች አሉ። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች “የግል የመሪነት ጥማትን” ለህዝብ ጥቅም ሲባል በጀግንነት ወደጎን በመተው ደጋፊዎቻቸውን በማሳመን እና ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስ ወደ ተመጠኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት እና ውህደት ሽግግር እንዲደረግ ዛሬ ነገ ሳይባል በፍጥነት መወሰን እና መከወን እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። ይህ ክስተት ቢያንስ ለሚቀጥለው ምርጫ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ያስችላል፣ ሲቀጥልም ለዘለቄታውም የመንግስት ጫና አላሰራም ብሎ ቢያስቸግር እንኳን በተባበረ ሰላማዊ ትግግል አስገድዶ መድረኩን ማስከፈት ይቻላል! 

ስልጣን ላይ ያለውም የብልጽግና ፓርቲም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግስት ሥራ አፈጻጸም ፍትህ እና ርትዕ አስፍኖ፣ ህጋዊ አሠራር ካላረጋገጠ እና የሰዎች መብት ረገጣ ካላስቆመ፣ አሁን በአገራችን የሚታየው የፀጥታ መደፍረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችል በመሆኑ፣ ይህም የሰላም እጦት እና የልማት ሥራ መቆምን አስከትሎ ወደ አልተፈለገ አገራዊ አጠቃላይ ቀውስ ማምራትን ስለሚያስከትል፣ በግዙፍ ፓርቲነት እና በመንግስት የጸጥታ ኃይል ብቻ መቆጣጠር እና ማስቆም የማይቻል መሆኑን መረዳት ብልህነት ይሆናል። ስለዚህ የሚታየውን ችግር ሁሉንም ወገን በሚያቅፍ የአሳታፊነት መስመር መፍታት መቻል አለበት። 

በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል የአገራዊ ቅንጅትን መፍጠር ሳይቻል ቀርቶ በተናጠል በሚደረግ የትጥቅ ትግል ብቻ ለውጥ እናመጣለን ብሎ ብዙ መግፋት ውጤት የሚያመጣ አይሆንም። ቢያመጣም እንኳን ፍትህ እና እኩልነትን ሊያሰፍን አይቻለውም። ካሁን በፊት እንደታየው ብዙ የሰው ህይወት፣ ሃብት እና ንብረት እንዲሁም አገራዊ መዳከም ስለሚፈጥር ከውጭ ጠላቶች በስተቀር የትኛውም የአገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ብሔረሰብ ወይም ቡድን እንዲሁም ግለሰብ ተጠቃሚ አይሆንም። የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በትጥቅ ትግል የሚመጣ ለውጥ መብት እና ነጻነትን እንዲሁም እኩልነትን ያላብሳል ብሎ አያምንም። ቢያንስ አሸናፊው ክፍል ብዙ መስዋእትነት ስለሚከፍል በፍርድ ለራሱ ማድላቱ፣ ሀብትም ያለ አግባብ ልያዝ ማለቱ አይቀርም፡፡ እስከዛሬም ያየነው ተግባራዊ ልምድ ይህንኑ መዛነፍ ነው። ስለሆነም የተባበረ ሰላማዊ ትግል አመርቂ ውጤት ያስገኛል። 

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር! 
አደፍርስ በላቸው (PhD) 

በቀረበው ጽሁፍ አስተያየት ለመስጠት በ ኢሚል አድራሻ :- adefrisb@hotmail.com መላክ ይቻላል።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here