spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየትበተቀመረለት መንገድ እየፈራረሰ ያለው ኢሳት የሕዝብ ሚዲያ

በተቀመረለት መንገድ እየፈራረሰ ያለው ኢሳት የሕዝብ ሚዲያ

ESAT Logo
የኢሳት አርማ

 

በቃሉ አንተነህ

 ከ2013 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከግንቦት ሰባት እጅ ወደ ሕዝብ ንብረትነት በተለየ ሕግ የተሸጋገረው ኢሳት የሕዝብ ሚድያ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅታዊ አወቃቀር ተዋቅሮ ከመስከረም 2014 ዓም ጀምሮ በአዲስ አመራር እንዲደራጅ ተደርጎ ህዝባዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ 

በተለይም በ2014 ዓ.ም በሀገሪቱ አንድነት ላይ የተቃጣውን የወያኔ ጥቃት ተቃውሞ ጌራን፣ ኢዮብን እና አማኑኤልን የመሳሰሉ ብስል ጋዜጠኞችን ወደ ጦር ግንባር በመላክና ህዝብን በማስተባበር ለመልሶ ማጥቃቱ ከመንግስትም ሚድያ በላይ ተገቢውን የሚድያ ተጋድሎ ያደረገ እና ይህንንም በህዝብ ያስመሰከረ ሚድያ እንደነበር ሕብረተሰቡም ሆነ መንግስት የሚያረጋግጠው የቅርብ ጊዜ እውነታ ነበር፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የሕዝብ ንብረት እና ይህ ውድመት ያስከተለውን ረሃብ እርዛት እና ስደት እንዲሁም ጉስቁልና ለመግታት ከመንግስት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በበለጠ ሁኔታ ከእለት ጉርስ ጀምሮ እስከ ልብስ እና መጠለያ ድረስ ለተቸገረው ሕብረተሰብ ለማድረስ በአይበገሬዋ ጋዜጠኛ መታሰብያ ቀጸላ እና ሴት አጋሮችዋ የተመራው ጊዜ የማይሽረው ድጋፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንጊዜም የማይረሳ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ጠንካራ ተግባር በሚከናወንበት ወቅት የኢሳትን ታሪካዊ ሂደት ለመቀልበስ የሚታገሉ ደጋፊ መሰል የቦርድ አባላት አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ዋናው ማስረጃ ሆኖ የሚታወቀው በ2014 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከአሜሪካ በሚተላለፈው በተወዳጁ ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ እነዚሁ ሰዎች ያደረጉት የጥቃት ዘመቻ አንዱ መገለጫ ነበር፡፡

የየዕለት የመንግስትን ድክመቶች እያሸተተ ሲያጋልጥ የነበረውን ይህንን በእነ መሳይ መኮንን የሚመራ ጠንካራ ልምድ እና እውቀት ያለውን ቡድን ለይቶ ለማጥፋት የተደረገው ከፍተኛ ዘመቻ ተሳክቶ እነሱን ለዘመናት ከሚታወቁበት ሚድያ ላይ በመንቀል በእነሱ ስም ከሕዝብ የተሰበሰበውን ከሶስት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ቅርጥፍ አድርጎ ለመብላት ተችሎዋል፡፡

በዶር አዚዝ የሚመራው የውጭው ቦርድ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሀገር ውስጥ ባስቀመጠው ከዕውቀትም ሆነ ከልምድ ነፃ በሆነው ራስ ወዳድ በኢሳት የቦርድ ሊቀመንበር ዶር እሸቱ መረጃ አቅራቢነት የሀገር ውስጥ የቦርድ አባላትን ሙሉ ለሙሉ ከአባልነት ካስወገደ በሁዋላ ሚድያውን ከህዝባዊነት ወደቀደመው ግንቦት ሰባት ንብረትነት ለመመለስ የሚያስፈልገው ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀቀ፡፡ 

ለዚህ አፈፃፀም እንዲረዳ በግንቦት ሰባት ዋና ፀሃፊ በአንዳርጋቸው ፅጌ እና በግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር አበበ ቦጋለ የሚመራ አንድ ኮሚቴ በስውር በማደራጀት የአንዳርጋቸው ጉዳይ አስፈፃሚ እና የሀገር ውስጥ ምስጢር ተካፋዩ በነበረው በቦርዱ ሊቀመንበር መረጃ አቀባይነት ኢሳትን መሰርሰር ጀመሩ፡፡ 

ይህ በኢሳት ነፃ እንቅስቃሴ ላይ ቀስቱን የቀሰረ የኢህአፓ ቡድን ለሶስት ወራት ያህል ስንኩል ተግባሩን በምስጢር ሲያከናውን ከቆየ በሁዋላ ኢሳት የነበረውን ድርጅታዊ መዋቅርና የተደራጀበትን መርህና የረጅም ጊዜ ዓላማ በመናድ ፕሮፌሽናል ሚድያ በመሆን ለህዝብ ሲያገለግል የነበረውን ኢሳትን በመውረስ ህዝባዊውን ሚድያ የግል ፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀምያ አድርገው ተቆጣጠሩት፡፡

እኒህ የግንቦት ሰባት አባላት ይህንን ሲያደርጉ የጋራ ዓላማ ይኑራቸው እንጂ ኢሳትን ከናዱ በሁዋላ የተለያየ ጥቅማ ጥቅም  በሶስት ከፍሎ ሳያጋጫቸው አልቀረም፡፡ 

አንደኛው ቡድን የሚመራው በአንዳርጋቸው ሲሆን ይህም ሚድያው ቀኑን ሙሉ ሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጥሎ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ብቻ በአንዳርጋቸው ራዕይ ፍላጎትና አቅጣጫ ሲያውጅ እንዲውል የመፈለግ እና የአንዳርጋቸውን ስሜት ብቻ እንዲያቀነቅን የሚያዘጋጅ ሲሆን 

ሁለተኛው ክፍልና በቦርዱ ሊቀመንበር በእሸቱ በቀለ የሚመራው ቡድን ደግሞ ፍቅረ ንዋይ ያደረበት እና ይህንኑም ለማግኘት መሰሎቹን አሰባስቦ ከግሎባል አሊያንስ ጋር የሚቀናጅ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በማደራጀት እና ሀገር ውስጥ ያለውን ጥቃቅን ጉዳይ በዚሁ ሚድያ በማስጮህ ከውጭ በርዳታ ስም ከሚላከው መና ድርሻውን ለማፈስ በቂ ዝግጅት ያደረገ ነበር፡፡

ሶስተኛውን ቡድን የሚመራው የግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር በአቶ አበበ ቦጋለ ሲሆን ይህ ሰው የኢሳትን ስራ አስኪያጅነት ቦታ እስኪቆናጠጥ ድረስ በሌላ ጉዳይ ሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከወንበሩ በሁዋላ ግን አንዳርጋቸውን በወዳጅነት በማቆየት ሊቀመንበር እሸቱን በውርደት አሰናብቶ ከመንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ስራውን ለማከናወን በነበረው ዕቅድ መሰረት ቦርዱንም ሆነ ሰራተኞቹን ሳያሳውቅ ከብሮድካስት እና ከኮሚኒኬሽን ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባ የተቀመጠ እና ብቸኛ የሚድያ ስርጭት መመርያ የተቀበለ ሰው ነበር፡፡

እዚህ ላይ አንድ ዋና ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡

ጥያቄው አሁን ወንበሩን የተቆናጠጠው የግንቦት ሰባት ምክትል ሰብሳቢ አቶ አበበ ለምን ከመንግስት ጋር አብሮ መስራትን ፈለገው?? በነገራችን ላይ ዋናው ሰብሳቢስ ከማን ጋር እየሰራ ነው?? ኢሳት ምስጢራዊ በሆነ መንገድ የመንግስት ጉዳይ አስፈፃሚ ከሆነ ለዚህ ተግባሩ የኢሳት አመራር ምን ይከፈለዋል፡፡ ለዚህ መልስ ለማግኘት ጉዳዩ ወደ አሜሪካ ይወስደናል፡፡ 

የዛሬው የኢሳት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ይህንን ወንበር ከመመኘቱ ወራቶች በፊት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጭ ያሰባሰበውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የዳያስፖራ መዋጮ ይዞ ለኢንቨስትመንት ጉዳይ ለም መሬት ሲያፈላልግ ቆይቶዋል፡፡ ከፍተኛውን መዋጮ ካዋጡት መካከል በመጨረሻ ዕድሜያቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ግብርና መሰል ፕሮጀክት አደራጅተው ይህንን የመንግስት ሙሰኛ ባለሥልጣን በሚያሳዩት ዶላር እያባበሉ ቀሪ ዘመናቸውን በተድላ እና በደስታ ለማጠናቀቅ ያሰቡ አዛውንት የቀድሞ ኢሳት ደጋፊዎችና ግንቦቶች ይገኙበታል፡፡ 

ይሁን እንጂ ወዲያ ቢባል ወዲህ ከግብርና ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሊሰማሩበት ያሰቡት መሬት ለዋናው ከተማ በሚቀርብ ቦታ ላይ ለማግኘት ባለመቸቻሉ ሌላ ዘዴ እንዲቀይሱ አስገደዳቸው፡፡ ስለዚህም የመንግስት ባለሥልጣናት በህዝብ ላይ በየቀኑ የሚፈፅሙትን በደል የሚዘግበውን እና የህዝብ እንባ ለማድረቅ ከሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር የሚተናነቀውን ኢሳትን ከሕዝብ ንብረትነት በመንጠቅ ለመንግስት በስጦታ መልክ ማቅረቡ የተመኙትን መሬት በተመኙበት ወልቂጤ አካባቢ እንደሚያገኙ ያረጋግጣሉ፡፡ የስራ አስፈፃሚውም ተረኛ ተወላጅነት ተጨማሪ ዕሴት እንደሚኖረው በማመን ከመንግስት ጋር ያለውን ቁርኝት አጠናከሩት፡፡ በአዚዝ የሚመራው ቡድንም የስራ አስፈፃሚውን አበል እና መኖርያ ወጭ በመሸፈን የወልቂጤውን ፕሮጀክት ማፋጠን ጀመረ፡፡  

እዚህ ላይ ግን አንድ እንቅፋት እንደሚኖር በቡድኑ ታመነበት፡፡ ይህም በኢሳት ጠንካራ ስነልቦና የተገነቡት እነዚያ የኢሳት ሰራተኞች ለዚህ እኩይ ዓላማ ይሰለፋሉ ወይ የሚለው ነበር፡፡ መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ሆነ፡፡ አይሰለፉም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ይጠየፉታል የሚል፡፡ 

በአዲሱ ቡድን የመሬት ስጦታው እንዲሳለጥ በኢሳት በኩል መወሰድ ከሚገባቸው ዋና ዋና እርምጃዎች መካከል በጠንካራ ሃያሲነታቸው የሚታወቁትን ሁለት ፕሮግራሞች ከአየር ላይ ማውረድ ነበር፡፡ ከእነዚህም ፕሮግራሞች አንደኛው በጠንካራዋ ሴት በመቲ /መታሰቢያ/ የሚመራው እኛስ የሚሰኘው እና በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚቀርበው በመንግስት ድክመቶች ላይ ያነጣጠረ ውይይት እና ሁለተኛው ደግሞ በስለሺ የሚመራው በፕሮግራም ኃላፊው በደረጀ ይመር እና በአማኑዔል መንግስቱ የሚንቀሳቀሰው የመንግስትን ችግሮች በመልቀም ከነመፍትሔው የሚያቀርበው እጅግ ተመራጭ የሆነ ፕሮግራም ነበር፡

ይህ አሳፋሪ እርምጃ ሲወሰድ የመጀመርያው ዱላ ያረፈባቸው ፕሮግራም መሪዎች ስራቸውን እንዲለቁ በመገደዳቸው ያሳደጉትን ሚድያ ለግንባታ መሬት ፈላጊው ግንቦት ሰባት እየለቀቁ ወጡ፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ለቁራሽ መሬት እና ብር ሳይሆን ለህሊናቸው ያደሩ ቁጥራቸው ከ14 የማያንስ ነባር የኢሳት ሚድያ ሰራተኞች ስራቸውን ለቀቁ፡፡ የዛሬው ኢሳት ከነመሳይ እስከ እስከ እነጌራ ድረስ ያሉትን በጋዜጠኝነት ጥርሳቸውን የነቀሉ ነባር ጋዜጠኞችን በማሳደድ የህዝብን ሚድያ በጥቅማቸው በለወጡ ተረኞች ተተኩ፡፡ በረቀቁት የቱጃሩ አዚዝ እጆች የሚመራው አዲሱ የአበበ አስተዳደር መንግስትን ለማገልገል መውተርተሩን ተያያዘው፡፡

ኢሳት የግለሰቦች አጅ መንሻ እንዲሆን ተፈረደበት 

ደህና እንሰንብት   

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here