
ብሩህ አስማረ
ከ2005ቱ ብሄራዊ ምርጫ ማግስት በመላ ሀገሪቱ በአመፅ ስትታመስ ለነበረችው ኢትዮጵያ፣ በ2010 የመጣው የፖለቲካ ለውጥ ትልቅ ተስፋን የሰነቀ ነበር፡፡ ጠ/ሚ አብይ በተመረጡ ማግስት ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች (ለምሳሌ- ጂግጂጋ፣ መቀለ፣ ጎንደር፣ አምቦ) በመሄድ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አሰባስበው ነበር፡፡ ከሀገር ውጭም ወደ ኤርትራ በመሻገር የኖቤል የሰላም ሽልማት የሆኑበትን የ20 ዓመታት የውጥረት ዘመናትን አስወግደው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላምን ማስፈን ችለው ነበር፡፡
የፖለቲካ ለውጡ ከመጣ ብዙም ሳይቆይ ግን ጠ/ሚሩ ህወሓትን የሚያንቋሽሹ ንግግሮች ማንፀባረቅ ጀመሩ፡፡ በሙስና ሰበብም የህወሓትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መያዝ፣ ማዋረድና ማሰር ጀመሩ፡፡ በመቀጠል የታዋቂ ሰዎችና የንፁሐን ዜጎች ግድያዎች መከሰት ጀመረ፡፡ በዚህም የህዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ስመኘው በቀለ፣ የሀገር መከላከያ ኤታማዦር ሹም ሌ/ጄ ሰዓረ መኮንን፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ የኦሮምኛ ዘፈኖች አቀንቃኝ ሃጫሉ ሁንዴሳ ተገደሉ፡፡
በመቀጠል በህዳር 2012 (እ.ኤ.አ 2020)፣ ወደ አንድ ሚሊዮን ዜጎችን የጨረሰው የትግራዩ ጦርነት ተከሰተ፡፡ በዚህም ጦርነት የኤርትራና የአማራ ሃይሎች ከፌዴራል መከላከያ ጋር አብሮ በመሰለፍ የትግራይ ህዝብ ላይ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ፈፀሙ፡፡
ወደ ኢኮኖሚው ስንሻገር፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ በእጥፍ የወረደበት፤ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡና የዜጎች የዕለተለት ኑሮ ላይ ለውጥ ማምጣት ለሚችሉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ፋንታ፣ የሀገሪቱን ሀብት በመናፈሻና ቤተ መንግስት ሥራ ላይ አባከነው፡፡ በዚህም፣ መንግስት የሀገር ውስጥ ብድሩ በከፍተኛ መጠን ጨመረ፡፡ በዚህም፣ የሸቀጦች ዋጋ በከፍጠኛ መጠን ያሻቀበበትና የዜጎች ድህነት በከፍተኛ መጠን የጨመረበት ክስተት ተፈጠረ፡፡
ከሰላምና ፀጥታ አኳያ ደግሞ፣ ቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ላይ ያሉት ታጣቂዎች በስፋት መንቀሳቀስ የጀመሩበትና የዜጎች በሰላም የመኖርና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት በእጅጉ የተገደበበት፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በዓለም ቀዳሚ የሆንበት ክስተት ተፈጠረ፡፡
በሰብአዊ መብት አያያዝና በሚዲያ ነፃነት ዙሪያ የአብይ አህመድ መንግስት ያሳየው ደካማ አፈፃፃምም የማይዘነጋ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አክቲቪስቶች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይያዛሉ፣ ጋዜጠኞች የሚዲያ መሳሪያዎቻቸው ይዘረፋሉ፣ እነሱም በዘፈቀደ ይታሰራሉ፤ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ወራትን በእስር ቤት ያሳልፋሉ፡፡
በተቋማት ነፃነት ዙሪያም የአብይ አህመድ መንግስት የኋልዮሽ ተጉዟል፡፡ መንግስት በፍ/ቤቶችና በምርጫ ቦርድ ሥራዎች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ባሳደረው ጫና የተነሳ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕ/ት እና ምክትል /ፕ/ት እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ሊቀ መንበር ከሥልጣን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ የብሄራዊ ባንክ ገዥውም እንዲነሳ ተደርጓል፡፡
በዲፕሎማሲ ረገድም፣ የኢትዮጵያ ተሰሚነት በእጅጉ የቀነሰበትና መንግስት የተለያዩ ማዕቀቦች የተጣሉበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ – የብድርና እርዳታ መከልከል፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአሜሪካ የአገዋ ዕድል መሰረዝ ተከስቷል፡፡
ባጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በአብይ አህመድ አመራር ላለፉት አምስት ዓመታት በሰላምና ፀጥታ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝና በሚዲያ ነፃነት፣ በተቋማት ነፃነት፣ በኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ መስክ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት ወቅት ነው፡፡
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ