spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ዓለም እቀፍ የአማራ ህብረት
የዓለም እቀፍ የአማራ ህብረት አርማ

የአብይ አህመድ ብርሃኑ ጁላ ሺመልስ አብዲሳና አዳነች አቤቤ ጅምላ እስርና ቀይ ብር በአማራ ምድር

የአብይ አህመድ ወራሪ ሰራዊት የፋኖን ጠንካራ ምት መቋቋም አቅቶት በየአውደ ውጊያው ሽንፈትን በመከናናቡ ሽንፈቱን መቀበል ተስኖት በተለያዩ የአማራ ከተሞች ንጹሃን ወጣቶችን ያለ ርህራሬ እየረሸነ ይገኛል። በዚህ ሳምንት ብቻ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከመቶ በላይ ወጣቶችን ከየቤታቸው እያወጣ የረሸነ ሲሆን በጅምላ የት እንደተቀበሩ በህዝብ ልጆች ሚስጥሩ ሊወጣ ችሏል። እንዲሁም በሰሜን ሸዋ እንሳሮ ለሚ በተባለ ቦታ 23 ወጣቶች እጃቸው የፊጥኝ ታስሮ እንደተረሸኑ የቪዲዮ መረጃው ሳይቀር ለህዝብ ይፋ ሆኗል። በደብረ ታቦር  ከተማ በእብናት ብዙዎችን ከመረሸን አልፎ ሆስፒታሉን በመድፍ በመደብደብ ታካሚወችን፣ ህመምተኞችን ሊጠይቁ የመጡትንና እና ጠባቂ ሰራተኞችን ጨምሮ ብዙ ሰው ሙትና ቁስለኛ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል። ባለፈው ሳምንት በላሊበላ፣ በብቸና፣በአማኑኤል፣ ደምበጫ ብዙ ወጣቶችን የረሸነ መሆኑን ተረድተናል። በፍኖተ ሰላም፣ የጁቤ፣ ደብረብርሃንና ቆቦ በድሮን ብዙ ንጹሐን ሰወች እንደተገደሉ ተረጋግጧል።

ቀደም ሲል በደብረ ኤልስያም ገዳሙን በመውረር ከ550 በላይ መነኮሳትና ፀበልተኞችን ተጨፍጭፈው እንደተገደሉ የሚታወቅ ነው። እንዲሁም በወሎ የአንድ የአስራ ስባት አመት ወጣት ብልት በፍፁም አረመኔዓዊነት መቆረጡ መላው ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነና በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀደምቶቹ አባቶቻቸው ይፈፅሙት ከነበርው አረመኔያዊ ድርጊት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የእነ አብይን ማንነት በግልፅ ለመላው ዓለም ያሳወቀ ክስተት ሆኗል። ይህን አረመኔያዊ ተግባር አምርረን እያወገዝን እንዲህ አይነቱ አስነዋሪ ድርጊት አማራውን ከማሳቀቅ ይልቅ ይበልጥ አምርሮ መታገል እንዳለበት የበለጠ አስረጅ ሆኖሎታል።

ይህ ወራሪ ሰራዊት በአብይ አህመድ፣ ብርሃኑ ጁላ እና ሺመልስ አብዲሳ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የአማራ ወጣቶችን  እየረሸነ ያለባቸውን ከተሞች ዘርዝሮ መጨርስ የማይቻል በመሆኑ እንደ ምሳሌ የሆኑትን ብቻ ለማቅርብ ተገደናል። ከዛሬ 46 አመት በፊት መንግስቱ ኃይለማርያም የኢትዮጵያን በተለይም የአማራው ወጣት ላይ ቀይ ሽብር አውጆ በመቶ ሺህወች የሚቆጠሩ ወጣቶች መረሸኑ ይታወቃል። አብይ አህመድም የፋኖን ኃይል ባዘመተው ወራሪ ሰራዊት መቋቋም ሲያቅተው የአማራውን ወጣት ከየቤቱ በማስወጣት እየረሸነ በጅምላ እየቀበረ ይገኛል።

እንደዚሁም ወገናችንን አንወጋም ብለው የተቃወሙ በመከላከያ ውስጥ ያሉ አማራወችም እየተለዩ እንደተረሸኑ ለመረዳት ችለናል። ከርሸናው የተረፉትን በጅምላ ወደ እስር ቤት እየወረወራቸው ይገኛል። አዳነች አቤቤና ሺመልስ አብዲሳም ይህን የጅምላ እስር በአዲስ አበባ በተለያዩ የኦሮሚያና የአማራ ከተሞች በሰፊው እያካሄዱ ይገኛሉ። በሺህወች የሚቆጠሩ አማሮች በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ። የፓርላማ አባላት፣ የምክር ቤት አባላት፣ ፓለቲከኞች፣ ጋዘጤኞች፣ ማህበራዊ አንቂወች፣ ዶክተሮች፣ ተማሪዎች፣ በሰራዊቱና በፓሊስ ውስጥ ያሉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ አማራወች ታስረው እንደሚገኙ ተዘግቧል።

ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ይህን አብይ አህመድና ግብረ አበሮቹ በአማራው ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ወረራ፣ ግድያ። ሽብር እና የጅምላ እስር አጥብቆ ይቃወማል፣ ያወግዛልም። እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በሙሉ እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህን ድርጊት እንዲያወግዙ ጥሪ እያቀረብን ይህን ወንጀል እየፈፀሙ ያሉት ለፍርድ እንዲቀርቡ በሚደረገው ጥረት በትብብር እንድንሰራ በድጋሜ ጥሪ እናቀርባለን። የንፁሀን ደም ከንቱ ሆኖ እንደማይቀርም በፅኑ እናምናለን። 

አማራውም ሆነ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ገዳይና አፋኝ የአብይ አህመድ ስርዓት ነፃ መውጣት የሚችሉት ይህንን አስከፊ ኃይል አምርሮ በመታገል የስርዓት ለውጥ በማምጣት ብቻ ነው። ይህንን እውነታም አብዛኛው ኢትዮጵያውያን እየተረዱት የመጡ  በመሆኑ ትግሉን ለማጎልበት ይረዳሉ ያልናቸውን የሚከተሉትን ጥሪዎች እንቀርባለን።

 1. ወራሪው የአብይ አህመድ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ከአማራ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጣ በአገርም በውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ግፊት እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
 2. በአገዛዙ ታፍነው የታሰሩት የአማራ ምሁራን መምህርት መስከረም አበራ፣ ዶር ወንድወሰን፣ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ ፓለቲከኛ ስንታየሁ ቸኮል፣ የሲቪክ ማህበራት አመራሮች፣ ዶር መሰረት ቀለምወርቅ፣ ዶር ማዕረጉ፣ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ አባይ ዘውዱ፣ ዳዊት በጋሻው፣ በቃሉ አላምረው፣ ወይዘሮ መነን ኃይሌ (የብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ባለቤት)፣ የምክር ቤት አባላት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሃንስ ቧያሌው፣ ዶር ካሳ ተሻገር፣ እንዲሁም  አቶ ታዴዎስ ታንቱ እና ስማቸው ያልተጠቀሱ አማራ በመሆናቸው ብቻ በማሰቃያ ቦታወች ታጉረው በእስር እየማቀቁና የተለያየ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው፣ ለተላላፊ በሽታ እንዲጋለጡ የተደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ አማራወች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሁሉም ግፊት እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
 3. ሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶች በተለይም በዚህ ስርዓት ግፍ እየደረሰባችሁ ያላችሁ የጉራጌ፣ ወላይታ፣ ጋምቤላ፣ ጉጂ፣ ሶማሊያ፣ አፋር፣ ጋሞ፣ ሲዳማ እንዲሁም ሌሎች ነገዶች የአማራውን ህዝብ የህልውና እና የስርዓት ለውጥ ትግል አሁን ከሚያደርጉት በላይ እንዲደግፉና ትግሉን የራሳቸው  አድርገው እንዲቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን። 
 4. የኦሮሞ ህዝብ፦ አብይ አህመድና ግብረ አበሮቹ በስምህ እየነገዱ ወንድምህና ጎረቤትህ ከሆነው በሃይማኖት ከሚመስልህ ተዋልዶና ተጋብቶ አብሮህ ተስማምቶ ከሚኖረው ከአማራው ጋር ለትውልድ የሚተላለፍ ደም እያቃቡህ ስለሆነ በቃችሁ አቁሙ በስማችን አትነግዱ ልጆቻችን አማራውን ለማጥፋት አንልክም ማለት ትችል ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።
 5. የትግራይ ህዝብ፦ ህወሓት የሚባል ስብስብ አማራው ጠላትህ ነው ብሎ በመስበክ የትግራይን ልጆች በአማራው ላይ እንዲዘምቱ ካደረገ ወደ 47 አመት ሆኖታል። በእነዚህ ግማሽ ምዕተ ዓመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማሮች ሲገደሉ በስተመጨረሻው ደግሞ በቅርቡ በተደረገው ጦርነት ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ወጣቶች ባላስፈላጊ ጦርነት እንዲያልቁ ይሄው ድርጅት ምክንያት ሆኗል። ህወሓት ከአማራው ጋር ለዳግም ጦርነት ህዝብን እያነሳሳች በመሆኑ በቃ ልጆቼን አልሰጥም ብለህ ከወንድምህ የአማራ ህዝብ ጋር ብትቆምና ለስርዓት ለውጥ ብትታገል እውነተኛ ዕርቅ በአማራና በትግሬው መካከል ለማስፋን በእጅጉ ስለሚረዳ፤ ሳትዘገይ ለስርዓት ለውጥ ትግል እንድትነሳ ጥሪ እናቀርባለን።
 6. በአብይ አህመድና ብርሃኑ ጁላ ትዕዛዝ አማራ ክልል በመግባት ህዝብን እየጨፈጨፋችሁ ያላችሁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዘር ማጥፋት ወንጀል እየተሳተፋችሁ መሆኑን ተገንዝባችሁ፣ ተጠያቂነታችሁ በህይወት እስካላችሁ ድረስ የማታመልጡበት መሆኑን በመረዳት አፈሙዛችሁን ህዝብን ለመፍጀት ትዕዛዝ ወደሰጡት በማዞር የስርዓት ለውጥ ትግሉን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን።ይህንን ለምታደርጉና ላደረጋችሁ ሁሉ ከፍተኛ አክብሮት አለን።
 7. ፈረሰ የተባለው የኦሮሚያ ልዪ ኃይል ምን ሲደረግ አማራ ክልል ገባ? አማራው ተወረረ እንጅ ማንንም አልወረረም። ታዲያ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የአማራን ህዝብ ለመውረር እንዴት አባይን ተሻግሮ አማራውን ወረረ? ይህን ፍፁም አይን ያወጣ ወረራ የኦሮሞ ልዩ ኃይል ተቃውሞ ወደመጣበት እንዲመለስ ጥሪ እናቀባለን።
 8. የትግራይ የጦር ጄነራሎችና መስመራዊ መኮንኖች፣ አማራው ላይ እየተደረገ ያልውን ፋሽስታዊ ወረራ እየመሩ መሆኑን ተረድተናል። ለ47 አመት በአማራው ላይ ያደረሳችሁት በደል ተዘርዝሮ የማያልቅ ኁልቆ መሳፍርት ግፍ ይበቃችኋልና ለራሳችሁ፣ ለህዝባችሁ እንዲሁም ለልጆቻችሁ ስትሉ አቁሙ። አማራው እንደሆነ ከተገፉት ጎን የሚቆመውን ፈጣሪውን ተማምኖ የጀመረውን ከግቡ ሳያደርስ ላይቆም ተነስቷል። ህዝብ እንዳይተላለቅ አሁኑኑ ከአብይ ጋር ተባብራችሁ አማራው ላይ የጀመራችሁትን ሽረባና ወረራ እንድታቆሙ ጥሪ እናቀርባለን።
 9. የአብይን የወረራ ትዕዛዝ ተቀብላችሁ ህዝባችሁን በመውጋት ያላችሁ የአማራ አድማ ብተና ፓሊሶችና የሚሊሺያ አባላት፦ ቦታ በማሳየት መረጃ በመስጠት የምታገለግሉ አማራወች በሺምግልና ስም ፋኖን እያሰጠቃችሁ ያላችሁ ሽማግሌወችና አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ፍፁም ነውርና ይቅር የማይባል ድርጊት አየፈፀማችሁ በመሆኑ በአስቸኳይ ከዚህ አስነዋሪ ተግባራችሁ እንድትታቀቡ ጥሪ እናቀርባለን። ባታቆሙ ግን የከፋ ነገር የሚመጣው በእናንት ሲሆን ልጆቻችሁና ትውልዳችሁ በሙሉ የባንዳ ዘር እየተባለ ሲሸማቀቅ እንደሚኖር ልትረዱት ይገባል።
 10. የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የሁሉም አፍሪካውያን  ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፦ አብይ አህመድ በአማራው ላይ እያደረገ ለሚገኘው መጠነ ሰፊ ወረራ የዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ ወራሪውን ሰራዊት ወደ አማራ ክልል በማጓጓዝ  ላይ መሰመራቱን እናወግዛለን፣  ይህን ህገ ወጥ ተግባርም በአስቸኳይ እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን። ይህ ህገ ወጥ ድርጊት የማይቆም ከሆነ የአምራ ህዝብ ሰራዊት ጭነው ወደ አማራ ክልል ከሚገቡ አውሮፕላኖች እና ወራሪዎች ራሱን ለመከላከል ሙሉ መብት እንዳለው መታወቅ ይኖርበታል።
 11.  የአማራው የቁርጥ ቀን የሆናችሁ የፋኖ አደረጃጀቶች እየከፈላችሁ ያለውን የህይወት መስዋዕትነት እጅግ የምናከብረውና ትውልድ ሊመካበት የሚችል አኩሪ ጀብዱ እየፈፀማችሁ መሆኑን እንገነዘባለን። የአማራ የህልውና ብሎም ኢትዮጵያ ከዚህ አፋኝ፣ ዘረኛና አፓርታይዳዊ ስርዓት በአጭር ጊዜ እንድትላቀቅ ይረዳ ዘንድ መሬት ላይ ትግሉን እየመራችሁ ባላችሁት የፋኖ አወቃቀሮች መካክል ከአሁኑ የበለጠ መተባበርና መናበብን እንደሚጠይቅ ተረድታችሁ የተጠናከረ  የጋራ አደረጃጀት እንድትፈጥሩ ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን። መሰሪው አብይ አህመድ በየጊዜው በተናጠል ለይቶ ለማነጋገር የሚያደርገውን ጥረት ሁሉ በማምከን የጋራ የሆነውን የአማራውን የህልውና ትግል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን።
 12. በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን አማራው ተገዶ የገባበትን የህልውናና የስርዓት ለውጥ ትግል  እየመሩ ከሚገኙት ጎን በመቆም በገንዘብ በሃሳብና በተለያዩ ስራወች በሰፊው ተሳትፎ እንድታደርጉ እና እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርባለን።
 13. ዓብይ አህመድና ግብረ አበሮቹ በአማራው ህዝብ ላይ በወለጋ፣ በመተከል፣ በደራ፣ አጣየ የፈፀሙትን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል በአጠቃላይ በአማራው ክልል ባደረሰው ወረራ፣ ሽብርና፣ ጅምላ እስር በፍትህ አደባባይ እንዲቀርቡ ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሙያዊ ትብብር  በማድረግና መረጃ በመሰብሰብ እንድትተጉ ጥሪ እናቀርባለን።

በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት አውጆ ንፁሃንን እየፈጀ ያለ ስብስብ ስልጣኑን ለማቆየት እንዲችል ድርድር ብሎ ለማደናገር ቢሞክር ሰሚ ሊኖረው ፈፅሞ አይገባም። የአማራው የህልውና ትግል ብሎም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከዚህ ዘረኛና አፓርታይዳዊ አገዛዝ ነፃ የሚሆኑት በድርድር ሳይሆን ሁሉን አቀፍ በሆነ የስርዓት ለውጥ መሆኑን በመገንዘብ ይህን አላማ እውን ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አሰተዋዖ ማበርከት ይኖርበታል። አስከፊውን ስርዓት ታግሎ ለመጣል እና የተሻለ ስርዓት ለማምጣት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከአማራው የህልውናና የነፃነት ትግል ጋር መቆም ያለባቸው ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው! 

ፍትሕ ለአማራ ህዝብ፣ ፍትሕ ለንጹሐን እና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ!

ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ፀንታ ለዘላለም ትኖራለች!

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here