spot_img
Saturday, April 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትኩሽ እና ሐበሻ (በ ደረጀ ተፈራ / በግል የቀረበ ዳሰሳ)

ኩሽ እና ሐበሻ (በ ደረጀ ተፈራ / በግል የቀረበ ዳሰሳ)

(በ ደረጀ ተፈራ / በግል የቀረበ ዳሰሳ)

  1. መግቢያ፤

በ-August 26, 2023 “አስማረ ብሩህ” የተባሉ ፀሃፊ “የኦህዴድ ብልፅግና ፓርቲ ፀረ-ሴሜቲክ እንቅስቃሴና በግዕዝ ሥልጣኔ ላይ ያለው ቅናት” በሚል ርእስ “ኦህዴዳውያን ሀገር እየመሩ ያሉት በፀረ-ሴሜቲክ ስሜት እና በግዕዝ ሥልጣኔ ቅናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን፣ ሴሜቲክና ኩሺቲክ በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ በመከፋፈል አሁን በእነሱ የአገዛዝ ዘመን ከሴሜቲኩ ወደ ኩሽ ስልጣን ዞሯል የሚል የፓለቲካ አመለካከት እንዳላቸውና “የኩሽ ህዝቦች ትብብር” የሚል ህብረት እስከመመስረት መድረራሳቸውን ገልጸዋል። በታሪክ ሂደት ከግዕዙ ጋር ተያይዞ በሃገራችን ኢትዮጵያ በሥነ መንግስት፣ በሃይማኖት፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በኪነ ጥበብ፣ በኪነ ህንፃ እና በመሳሰሉት የተገኙትን ትሩፋቶች በጋራ ከመጠም ይልቅ በበታችነት በሽታ ተለክፈው፣ በጥላቻና በድንቁርና ተሞልተው የንጹሃን ደም በማፍሰስ፣ ሃገራችንን በማፈራረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም እጃቸው ከ1982 ዓ/ም ከአሶሳው የጅምላ ጭፍጨፋ ጀምሮ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ እና በመሳሰሉት አካባቢዎች በንጹሃን የአማራ ህዝብ ደም የተጨማለቁ እንደ ዲማ ነጎ፣ ሊንጮ ለታ፣ ሌንጮ ባቲና የመሳሰሉ የኦነግ መስራች፣ የድርጅቱ ፖሊሲ ቀራጭ፣ ውሳኔ እና አቅጣጫ ሰጪ ወንጀለኞችን በለውጥ ስም ወደሃገር ውስጥ በማስገባት በኦህዴድ/ ኦነግ መሩ መንግስት የድንበርና ያስታራቂ ኮምሽን፣ የጠ/ሚ አማካሪ ወዘተ እየተደረጉ መሾማቸው ይታወቃል። ከነዚህም ውስጥ የጠ/ሚ አብይ አህመድ ከፍተኛ አማካሪ የነበረውና አሁን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የተሾመው ሙሰኛ ቱጃሩ ሌንጮ ባቲ ይገኛል። ሌንጮ ባቲ በሚቀጥሉት ሦስት ሺ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኦሮሞ (በኩሽ) የሚመራ ይሆናል ማለቱን ከላይ በተገለጸው ፅሁፉ ተመላክቷል። ጸሃፊው አስማረ ብሩህ በርካታ ሚዛን የሚደፉ ሃቆችን ያቀረቡ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተዛማችነት ባለው “ኩሽ” በሚለው አወዛጋቢ ቃል ዙሪያ ያለኝን አንዳንድ የግል ምልከታዎችን ማካፈል እፈልጋለሁ። ወደ ዝርዝር ሃሳቡ ከመግባቴ በፊት አንባቢዎቼ ኩሽ ማነው? መገለጫውስ ምንድን ነው? የቆዳ ቀለም፣ ቋንቋ ወይስ ስልጣኔ ነው? የህዝቡስ መኖሪያ ስፍራ ወዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዲያሰላስሉ እጋብዛለሁ።

  • ኩሽ (Kush) ባጭሩ፣

“ኩሽ” ለሚለውን ቃል የሃይማኖት ሰዎች፣ የታሪክ ፀሃፊዎች፣ የቋንቋ ምሁራን እና ፓለቲከኞች በየራሳቸው መንገድ የተለያየ ትርጉምና ፍቺ ሲሰጡት ይታያል። ኩሽ ተብለው የሚጠሩ ህዝቦች መኖሪያ ስፍራቸው፣ የሚናገሩት የቋንቋ ዓይነትና የመሳሰለው እንደ ፀሃፊው የእውቀት ደረጃና የጥናት ውጤት ደረጃ፣ እንደ ግለሰቡ የፓለቲካ ዝንባሌ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ (Biblical History) ስለ ኩሽ የዘር ሃረግ የሚከተለውን ይላል። ኖህ የሚባል አንድ ፃድቅ ሰው ሴም፣ ካም እና ያፌት የሚባሉ ልጆች ወለደ። ካም በተራው ኩሽ፣ ምስር (ምጽራይም)፣ ፉጥ እና ከነዓን የሚባሉ አራት ልጆችን ይወልዳል። ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖህ ልጆች ለኑሮ በሚያመቻቸው ቦታ ቤተሰባቸውን እየያዙ በተለያየ አቅጣጫ በመሰደድ መኖር ጀመሩ። ኩሽ የሚለውን ቃል ፍቺ ስንመለከት የቃሉ ቀጥታ ገጸ ንባቡ (Literally) ከመጽሃፍ ቅዱስ አንጻር አጀማመሩ ከካም (Ham) ልጅ ከሆነው ከኩሽ ዘር መገኘትን እንጂ ከቋንቋ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳልነበረው መረዳት ይቻላል። ሴም፣ ካም እና ያፌት አንድ ላይ ያደጉ፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች የሆኑ የስጋ ወንድማማቾች ስለነበሩ ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩ ስለማደጋቸው የሚያጠራጥር አይደለም። ይሁንና እነዚህ የኖህ ልጆች ለኑሮ በሚያመቻቸው ቦታ ቤተሰባቸውን እየያዙ በየአቅጣጫው በመጓዝ መኖር ጀመሩ፣ ከብዙ ትውልድ በኋላም የባህል፣ የአኗኗር፣ የቋንቋና የመሳሰለው ልዩነት እያሳዩ መጡ።

በመሆኑም በጊዜ ሂደት ኩሽ የሚለው መጠሪያ (ቃል) ከአንድ በላይ ትርጉም እየያዘ መጣ።

  • አንደኛው በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው የዘር ሃረጉ ከኩሽ በደም የሚወለድ ማንኛውም ጥቁር የሰው ዘር የሚገልጽ ሲሆን፣
  • ሁለተኛው ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የቋንቋዎችን ምደባ (Language Classification) ያደረጉት የቅኝ ገዢ መንግስታት ሚሲዮናውያን ኩሽ በማለት ስም የሰጡት የቋንቋ ቤተሰብ ነው።
  • ሶስተኛው የኩሽ ትርጉም ደግሞ የታሪክ ምሁራን በሰሜናዊ ሱዳን በአባይ ሸለቆ የነበረን የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ የሚገልጹበት ነው።

ሚሲዮናውያኑ የአፍሪካ የቋንቋዎችን ምደባ ባደረጉ ጊዜ የፈጸሙት መሰረታዊ የሆነ ስህተት አለ፣ ይኸውም ኩሽ ብለው ለሰየሙት የቋንቋ ቤተሰብ ሌላ አግባብነት ያለውን ስም መስጠት (መጠቀም) ሲችሉ ቀድሞ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ የጋራ መጠሪያነት ያገለግል የነበረውን የመጽሃፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን “ኩሽ” የሚለውን ጥቅል ቃል (Generic Term) ለአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ብቻ ነጥለው መስጠታቸው ነው። በሌላ አነጋገር ለምሳሌ አፍሪካ የሚለው ቃል ለጥቂት ነገዶች (ጎሳዎች) ቋንቋ መጥሪያነት ብቻ ነጥሎ በመስጠት የአፍሪካ ቋንቋ ብሎ እንደመሰየም ነው። Traditional Linguist ተብለው የሚታወቁት እነዚህ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን የሰሩትን ስህተት ሳያርሙ ከእነሱ ቀጥሎ የአፍሪካ ቋንቋዎችን ምደባ የሰሩ የቋንቋ ምሁራን (Linguist) በግዴለሽነት በዛው መቀጠላቸው ችግሩን ይበልጥ አወሳሰበው።

  • ሐበሻ ማነው?

አበሻ (ሐበሻ) የሚለው ቃል ዘርን፣ ጎሳን፣ ነገድን፣ ሃይማኖትን ወይም የትኛውንም ማህበረሰብ በተናጠል የማይወክል፣ ውህድ ማንነት ሲሆን በባህል፣ በኑሮ፣ በባህሪና በአስተሳሰብ (Mindset)የሚገለጽ ነው። ለምሳሌ የአበሻ መድሃኒት፣ የአበሻ ልብስ፣ የአበሻ ዶሮ፣ የአበሻ ጎመን፣ የአበሻ ቃሪያ፣ እንዲሁም ከባህሪና ከስነ ምግባር አንፃር ደግሞ የአበሻ ጀብዱ፣ የአበሻ ኩራት፣ የአበሻ ይሉኝታ፣ የአበሻ ጀግንነት ወዘተ እየተባለ ይገለጻል። ስለዚህ አበሻነት በኢትዮጵያ ምድር በቅሎ ያደገ፣ በሚታይና በሚጨበጥ፣ በኑሮ፣ በባህል፣ በምግብ፣ በልብስ እና በመሳሰሉት የሚገለጽ በመሆኑ ብሔርና ቋንቋ ሳይገድበው የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ መገለጫ መሆን ችሏል።

ሐበሻ የሚባል የተለየ ጎሳ፣ ብሔር፣ ህዝብ ወይም ክልል በኢትዮጵያ ምድር የለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ቋንቋው ግዕዝ የሆነ ሐበሻ የሚባል ነገድ በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር ነበር ሲሉ ይሰማል፣ ሌሎቹ በተለይ ሃገሪቷን በዘር፣ በጎሳና በየምክንያቱ የመከፋፈል ልክፍት ያለባቸው ጠባብ ብሔርተኞች ደግሞ አበሻ የሰሜን ኢትዮጵያ ነዋሪዎችን የሚወክል ነው ይላሉ። እውነቱ ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ይነስም ይብዛ የሴም፣ የኩሽ እና የናይሎቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ጎሳና ነገዶች የሚገኙበት እንጂ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተለየ አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታም በምስራቅ፣ በማዕከላዊና በደቡብ ኢትዮጵያ በርካታ የሴም ቋንቋ ተናጋሪ ነገዶች ይገኛሉ። መላው ኢትዮጵያዊ በጋራ የሚጋራው ከአለባበሱ እና ከአመጋገቡ ጀምሮ በርካታ ተመሳሳይ ባህልና ስነልቦና ያለው ህዝብ ነው። ለምሳሌ የአገው ትውልድ የሚመዘዘው ከንጉስ ዳዊት የልጁ ልጅ ነው። ቀዳማዊ ምኒሊክ የዳዊት የልጅ ልጅ የንጉስ ሰሎሞን ልጅ ነው። ስለዚህ የአገው እና የአማራ ነገስታት የአጎት ልጆች(Cousin) ወይም ወንድማማቾች ናቸው። እንደሚታወቀው ንጉስ ዳዊት የእስራኤል ዘር በመሆኑ ሴማዊ ነው። ስለዚህ የአገው ነገድ የነብዩ የንጉስ ዳዊት ዘር ስለሆነ በቋንቋው የኩሽ ቤተሰብ ቢባልም በደሙ ግን የሴም ዘር ነው። በመሆኑም አማራ እና አገው በታሪክም፣ በባህልም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑ ከአንድ የዘር ግንድ የተገኙ በደም የተሳሰሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው።

ባጠቃላይ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየን መነሻው የትም ይሁን የት ሐበሻነት በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ እንደጨው ሟሙቶና እንደ ቅቤ ቀልጦ በአለባበስ፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር፣ በአስተሰብ፣ በባህሪ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚንጸባረቅ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ጎሳና ነገዶች የሚጋሩት ቋንቋ፣ ብሔር እና ሃይማኖት የማይገድበው ውህድ ማንነት እንጂ በተናጠል የእገሌ ብቻ ነው የሚባል አይደለም። ሐበሻነት የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ ለዘመናት በጋራ በመኖሩ የገነባው የጋራ እሴት ነው። አበሻ የሚለው አገላለጽ የሃገር በቀል የሆነውን እፅዋት፣ እንስሳ፣ ሰውን እና አስተሳሰቡን ጭምር የሚመለከት፣ ኢትዮጵያዊውን ከውጭ ከመጣው ከባዕዱ ለመለየት የሚያገለግል ስለሆነ ሐበሻ ለሃገሩ ነባር (Native) መሆንን ያመለክታል። እንደሚታወቀው በጥንት ጊዜ የነበሩ የሃገራችን ንጉሶች እኔ የኢትዮጵያ ንጉስ ነኝ ይላሉ እንጂ ሃገሬ ሐበሻ ወይም አቢሲኒያ ናት ብለው አያውቁም። ከውጭ መንግስታት ጋር ሲፃፃፉም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት እያሉ ነበር ራሳቸውን ያስተዋውቁ የነበረው። ለምሳሌ በ4ኛው ክ/ዘ የነገሰው ንጉስ ኢዛናም ሆነ ከሺህ ዓመት በኋላ በ14ኛው ክ/ዘ የነገሰው አፄ ዓምደ ጽዮን እራሳቸውን የሚጠሩት እኔ “ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” እያሉ ነበር። ይሁን እንጂ የ60ዎቹ ግራ ዘመም ፓለቲከኞች የሆኑት እነ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፤ ትህነግ እና የመሳሰሉ ህዝቡን በንጉሳዊ መንግስት ላይ ለአመፅ ለማነሳሳት ሐበሻ የሚለውን ቃል ትርጉሙን በማዛባት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅመውበታል። በዚህ ክፉ ስራቸው ህዝቡን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ኢትዮጵያን እንደ አኬል ዳማ የደም መሬት አደረጓት። ይኸው የእነሱ ጦስ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ጭምብል እራሱን ሸፍኖ እየተመላለሰ ቁም ስቅላችንን እያሳየን ይገኛል።

  • የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ (Nile Valley Civilization)

እንደሚታወቀው በአባይ ወንዝ ዳርቻ ከሚገኙት ከኑብያና ከግብፅ እስከ ሜሶፖታሚያ ድረስ የተገነቡ አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ስልጣኔዎች በወንዝ (በውሃ) ዳር የተገነቡ ናቸው። በቅድመ ታሪክ ኑቢያ (Nubia) የሚባለው በሰሜን ሱዳን ውስጥ በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች የሚገኝ አካባቢ (Geographical Region) ሲሆን ከዛሬ 8ሺህ ዓመት ጀምሮ የሚታወቅ መጠሪያ ነው። ኑቢያ ከደቡብ ግብጽ ከሚገኘው ኤሌፋንቲን ተብሎ ከሚጠራው ከአስዋን ግድብ ጀምሮ እስከ ጥቁርና ነጭ የአባይ ወንዝ (Nile River) መገናኛ እስከሆነው ካርቱም ከተማ ድረስ የሚያካልል ነበር። ኩሽ የሚለው መጠሪያ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጸበት ከኖህ ቤተሰብ ታሪክ ጀምሮም ሆነ የኩሽ ስልጣኔን በተመለከተ በድንጋይ እና በፓፒረስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙ መረጃዎች የሚያሳዩት ኩሽ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ከዛሬ 2ሺህ 5መቶ ዓመት አካባቢ እንደሆነ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች በልምድ ኩሽና ኑቢያን እየለዋወጡ ሲጠቀሙባቸው ይታያል።  

የኑብያን በረሃ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ በሚያልፈው በአባይ ወንዝ ዳርቻ በተለይም በአባይ ሸለቆ (Nile Valley) የሰፈሩ ጥንታዊ ማህበረሰቦች ነበሩ። እነዚህ ማህበረሰቦች በግብርና፣ በአደን፣ በአሳ ማጥመድ፣ በከብት ማርባት፣ በሸክላ ስራ፣ በንግድ እና በመሳሰሉት ስራዎች ተሰማርተው ይኖሩ ነበር። እነዚህ ማህበረሰቦች በሂደት ከሰፈራ (Settlement) ወደ አነስተኛ ስልጣኔ በመሸጋገር በአባይ ወንዝ ዳርቻ ከዛሬ 5 ሺህ 5 መቶ ዓመት አካባቢ ከርማ ወይም ኑብ (Kerma/ Pnubs) በተባለ ቦታ የመጀመሪያውን የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ (Civilization) መሰረቱ። ከከርማ ቀጥሎ ናፓታ (Napata)፣ ማኩሪያ (Makuria)፣ አሎዲያ (Alodia)፣ ኑባቲያ (Nobatia) እና የመሳሰሉት የጥቁር ህዝብ መኖሪያ መንደሮችና ስልጣኔዎች በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች እየተስፋፉ ሄዱ። እነዚህ በአባይ ዳርቻ የነበሩ የጥቁር ህዝብ ስልጣኔዎች በግብፅ የፈርዖን ጦር የወደሙት በአካባቢው የበላይ ገዥ ለመሆን በነበረ የጠላትነት ስሜት ነበር። በተለይ በ25ኛው ስርወ መንግሥት ኑቢያውያን ናፓታን ዋና ከተማቸው በማድረግ ከግብጽ እስከ ሶሪያ ድረስ ይገዙ ስለነበር ሳምቲክ 2ኛ (Psamtic II) የተባለ ፈርኦን በ592 ዓ/ዓለም ናፓታ ዳግም ግብጽን መግዛት እንዳትችል አድርጎ በበቀል ከተማዋን ያለ ምህረት እና ያለምልክት ከምድረገጽ አጠፋት። ይሁንና ከሞትና ከምርኮ የተረፉት የናፓታ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ወደ ደቡብ ኑቢያ እርቀው በመሰደድ የሜሮኤ መንግስትን (Meroe’ Kingdoom) በመመስረት ንግስናቸውን ቀጠሉ። ይህ የሜሮኤ መንግስት የኩሳ (ኩሽ) መንግስት እየተባለ በጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ይገለጻል።

ምንም እንኳን የሜሮኤ (የኩሳ) ስልጣኔ ከግብጽ የራቀ በመሆኑ ለጊዜው የተረጋጉ ቢመለሱም በሌላ በኩል ደግሞ ለአክሱም ከነበራቸው ቀረቤታ አንጻር የአካባቢውን የንግድ መስመር ለመቆጣጠር ከአክሱም መንግስት ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ ገቡ። በመሆኑም የሜሮኤና የአክሱም መንግስታት ትከሻ ለትከሻ ይለካኩ ጀመር። በወቅቱ የሜሮኤ መንግስት ከአባይ ወንዝ በተጠለፈ ውሃ በመስኖ የእርሻ ልማት በተጨማሪ በብረት ማቅለጥ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) ስራም የተካኑ ነበሩ። ይሁንና በሜሮኤ አካባቢ ይገኝ የነበረ የእርሻ መሬት በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ በመስኖ ይታረስ ስለነበር አፈሩ ለምነቱን በማጣቱ በቂ ምርት መስጠት አቆመ። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው የነበረ ደን ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨፍጭፎ በማለቁ (Deforestation) ምክንያት ህዝቡ ከፍተኛ የእንጨት እጥረት አጋጠመው። ባጠቃላይ የሜሮኤ ኢኮኖሚ ተደራራቢ ችግር ውስጥ ወደቀ፣ መንግስቱም ጥንካሬውን እያጣ ሄደ። ከዚህ በተጨማሪ ከአባይ ወንዝ እስከ ቀይ ባህር ዳርቻ በዑደት ከቦታ ቦታ በመዟዟር ይኖሩ የነበሩ ቤጃ የሚባሉ ከብት አርቢ (Pastoral Nomadic) ማህበረሰቦች በሜሮኤ ከተማ እና በአካባቢው በሚገኙ መንደሮች ላይ ድንገተኛ ወረራ በመፈፀም በተደጋጋሚ ዝርፊያና ጥቃት ይፈጽሙ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ (ኤርትራ) አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የአክሱም መንግስት አካል የነበሩ (Bareya)፣ ሳሊም (Salim)፣ ኩናማ (Kunama) የሚባሉ ማህበረሰቦች ነበሩ (አሉ)። ኢኮኖሚው የተዳከመው የሜሮኤ (የኩሳ) መንግስት ወደ አክሱም ግዛት ውስጥ ጥሶ በመግባት እነዚህን የባርያ፣ የሳሊም እና የኩነማ ማህበረሰቦችን ለመፈንገል ጥቃት ይፈጽምባቸው ጀመር። (ባርያ በወቅቱ የአንድ ማህበረሰብ መጠሪያ ስም ነበር)። እነዚህ ማህበረሰቦች መልዕክተኛ አክሱም ከተማ ድረስ በመላክ የደረሰባቸውን ጥቃት ለመንግስታቸው በማሳወቃቸው በወቅቱ የአክሱም ንጉስ የነበረው ንጉስ ኢዛና ከሜሮኤ መንግስት ጋር የአትባራ (የተከዜ) ወንዝ ወደ ዓባይ ወንዝ በሚቀላቀልበት አካባቢ በ350 ላይ ጦርነት አድርገው በንጉስ ኢዛና የሚመራው የአክሱም ሰራዊት ድል በማድረግ ወደ አክሱም በድል ተመለሰ። ንጉስ ኢዛና ከድል በኋላ አንዱን በአክሱም ሌላውን ደግሞ በሜሮኤ ከተማ ባቆመው በድንጋይ (Tablet) ሃውልት ላይ በግዕዝ፣ በሳባውያን እና በጥንታዊ የግሪክ ቋንቋዎች (TriLingual) በጻፈው የድል ሃውልት ላይ እኔ ንጉሰ ነገስት ኢዛና የኢላ አሚድ ልጅ በሰማይ እና በምድር አምላክ ረዳትነት የኖባ (የኩሳ) ህዝቦች በአመጽ ተነሳስተው የባርያ እና የሶባ (ጥቁር እና ቀይ ህዝቦችን) በግፍ በማጥቃታቸው ጦርነት ገጥሜያቸው አሸነፍኳቸው ይላል። በመቀጠልም በዚሁ የድል ሃውልት ላይ እኔ የኩሳ (የሜሮኤ)፣ የቤጃ፣ የሳባ፣ የኢትዮጵያ ንጉስ ነኝ በማለት በማያሻማ ሁኔታ ንጉሰ ነገስት መሆኑን ገልጿል።

  • ቋንቋ ምደባ እና የህዝብ ፍልሰት፣

እንደሚታወቀው የሰው ልጅ በዓለማችን ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲፈልስ፣ ሲሰደድ፣ ሲሰራጭ ኖሯል። በተለይ በኢትዮጵያ የተደረጉ የህዝብ ፍልሰቶችን እና ስርጭቶችን የተመለከትን እንደሆነ በሦስት አቅጣጫ የተደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን። አንደኛው ከኢትዮጵያ ተነስቶ ድንበር አቋርጦ ወደ ውጭ (ወደ ቀረው ዓለም) የተደረገ ፍልሰት፣ ሁለተኛው ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የተደረገ፣ ሶስተኛው ደግሞ ከአንደኛው የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል የተደረጉ የሃገር ውስጥ ፍልሰቶች እና መስፋፋቶች ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ብቻ ሳትሆን የቋንቋና የባህል መፈጠሪያና መዋሃጃ ጭምርም ናት። በተለያዩ ዘመናት ሰዎች ከኢትዮጵያ ምድር ተነስተው ወደ ቀረው ዓለም በተሰራጩ (በተሰደዱ) ጊዜ ባህልና ቋንቋቸውም አብሯቸው እንደሚሰራጭ ይታወቃል። ከብዙ ዘመናት ቆይታ በኋላ በዳግም ፍልሰት (Back Migration) ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ወይም በንግድና በመሳሰሉት ከህዝቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በተሰደዱበት ቦታ ያዳበሩትን ባህልና ቋንቋ ይዘው በመመለስ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በፈጠሩት መስተጋብር አዲስ ውህድ ማንነት (ሐበሻነትን)አስገኝተዋል።

በሃገራችን ቁጥራቸው ከ85 ያላነሱ ነገዶች/ ብሔሮች ይገኛሉ። በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሞ ሸለቆና በአካባቢው ሃይቆችና ወንዞች ዳርቻዎች ብቻ ከ40 በላይ ሲሆን ከቋንቋ ብዛት አንፃር ስንመለከት ደግሞ በኢትዮጵያ ከ83 በላይ ቋንቋዎች (Languages) እና ከ200 በላይ ዘዬዎች (Dialects) መኖራቸው ተረጋግጧል። የቋንቋ ምደባ (Languages Classification) ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከቅኝ ግዛት ማስፋፋት ጋር በተያያዘ ወደ አፍሪካ በመጡ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን፣ በቅኝ ግዛቶቹ ሹመኞች፣ በሰላዮቻቸው እና በመሳሰሉት ነበር። ከፍተኛ የቋንቋ ብዝሃነት (High Linguistic Diversity) ባለበበት እና ከ2000 ያላነሰ ቋንቋዎች በሚነገርበት በአፍሪካ አህጉር የቋንቋውን ተናጋሪ ማህበረሰቦችን በያሉበት በማግኘት እና በቂ መረጃ አሰባስበው ስለመስራታቸው ከሞያ ብቃት ጋር በተያያዘ በቅኝ ገዢ ሚሲዮናውያን እና ፓስተሮች  ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዋናነት በመንግስቶቻቸው ህዝቡን በመከፋፈል ለአገዛዝ በሚያመች ሁኔታ የፈጸሙ በመሆኑ የቋንቋ ምደባው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው አያጠያይቅም።

ከላይ እንደተገለጸው ከቅኝ ገዢ መንግስታት ከተላኩ ሚሲዮናውያን እና ፓስተሮች በመቀጠል የአፍሪካ ቋንቋዎችን ምደባ (Language Classification) የተደረገው በ1963 ላይ በአሜሪካዊው የስነ ልሳን ሊቅ በሆነው በፕ/ር ጆሴፍ ግሪንበርግ በተባለ ሰው ነው። ግሪንበርግ አፍሪካን በአካል ያልረገጠ ሲሆን ከእሱ በፊት Friedrich Müller እና Diedrich Westermann የተባሉ ሚሲዮናውያን (Traditional Linguist) የአፍሪካ የቋንቋ ቤተሰብ በማለት አዘጋጅተውት የነበረውን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የራሱን “Mass Comparison Method” ብሎ የሰየመውን የቃላቶችን ዝምድና ማነጻጸሪያ ዘዴ (Tabulation) በመጠቀምና አንዳንድ የስም ለውጦችን በማድረግ ቋንቋዎችን ምደባ አደረገ። ባጠቃላይ ፕ/ር ጆሴፍ ግሪንበርግ በአፍሪካ አህጉር እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚነገሩ ቋንቋዎችን 1) አፍሮ-ኤሽያ (Afro-Asiatic)፣ 2) ናይሎ-ሳህራ (Nilo-Saharan)፣ 3) ኒጀር-ኮንጎ (Niger-Congo) እና 4) ካሆሲያን (Khoisan) የቋንቋ ቤተሰብ በማለት በአራት ትላልቅ (ዓብይ) የቋንቋ ቤተሰቦች መደባቸው። እያንዳንዱ ዓብይ የቋንቋ ቤተሰብ በስሩ ንኡሳን የቋንቋ ቤተሰቦችን ያቀፈ ነው። ለምሳሌ በተራ ቁ 1 ላይ አፍሮ-ኤሽያ (Afro-Asiatic) ተብሎ በሚጠራው ዓብይ የቋንቋ ቤተሰብ ስር ኩሻዊ፣ ሴማዊ፣ ኦማዊ፣ በርበር፣ ቻዳዊ፣ ኮፕት/ Egyptian በማለት ይዘረዝራቸዋል።

ይሁን እንጂ እንደ Lionel Bender (2000), Harold Fleming (1976), Lyle Campbell (2008) እና የመሳሰሉ የቋንቋ ልሂቃን (Linguists) የፕ/ር ጆሴፍ ግሪንበርግ በጅምላ ንጽጽር ዘዴ (Mass Comparison Method) መሰረት ያዘጋጀው የቋንቋ ምደባ የማይዛመዱ ቋንቋዎች አንድ ላይ ደበላልቆ መያዙን በመጠቆም፣ አመዳደቡ የሃሳብ እና የመዋቅር (Conceptual And Structural) ችግሮች እንዳሉበት ሙያዊ ትችቶችን በመስጠት ማሻሻያ እንዲደረግበት ሂስ አቀረቡ። የጅምላ ንጽጽር ዘዴው በአፍሪካ ቋንቋዎች ምደባ ላይ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የአሜሪካ ነባር (Native) ህዝቦች በሆኑት በቀይ ህንዶች ቋንቋ ምደባ ላይም ተመሳሳይ ህጸጽ ነበረበት።

የጆሴፍ ግሪንበርግ የጅምላ ንጽጽር ዘዴ በአፍሪካ የቋንቋ ምደባ ላይ ያሳየውን ውስንነት አንድ ሁለት ምሳሌዎችን በማንሳት ለማየት እንሞክር። እንደሚታወቀው የኑብያ ስልጣኔ ከጀመረበት በአባይ ወንዝ ዳር በሰሜን ኑብያ ከሚገኘው ከርማ ከሚባለው ጀምሮ ናፓታ፣ ማኩሪያ፣ አሎዲያ፣ ኑባሺያ፣ ዶንጋላን አልፎ እስከ ደቡባዊ ኑብያ እስከ ሆነችው ሜሮኤ ድረስ አሁኑ በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው የቋንቋ ቤተሰብ የተመደበው የኩሽ ቋንቋ በሚባለው ሳይሆን በናይሎ ሳህራ (Nilo-Saharan) የቋንቋ ቤተሰብ ስር ነው። እዚህ ላይ የተጣረሰ ነገር ያለ ይመስላል። በአሁኑ ጊዜ ሃውልቶቹና ቤተ መቅደሱ ፈራርሰው በሚታዩበት በመሬቱ/ በአካባቢው ላይ የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ “ናይሎ-ሳህራ” ነው እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣኔው ግን የኩሽ ስልጣኔ ነው ማለታቸው ግልጽ አይደለም። ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም አሁን በዘመናችን በተለይም በእኛ ሃገር ”የኩሽ” ቋንቋ ተናጋሪ ተብለው የተሰየሙት ህዝቦች ወይም ነገዶች ”በኩሽ” ስም ከመጠራታቸው ውጪ በጥንት ጊዜ ኑብያ ውስጥ በታሪክ የኩሽ ስልጣኔና ህዝብ ተብለው ከሚታወቁት ህዝቦች ጋር በቋንቋ፣ በባህል፣በአምልኮትና በመሳሰለው የሚጋሩት አንዳች ነገር ለመኖሩ የቀረበ ማስረጃ የለም። በሌላ አነጋገር ባሁን ጊዜ በአካባቢው በመኖር ላይ የሚገኙ የኑብያ ህዝቦችን በናይሎ ሳህራ የቋንቋ ቤተሰብ ሲመደቡ፣ ከኑብያ የግዛት ክልል ውጪ የሚገኙ ለኩሽ ስልጣኔ የነበራቸው ታሪካዊ ግንኙነት የሚያሳይ አንዳችም መረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ በሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ ህዝቦች ግን የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ተብለው መመደባቸው ነገሩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል። ሌላው ደግሞ የአገው ህዝብ የዘር ትውልድ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከትውፊት አንጻር ስንመለከት በደሙ ሴማዊ ሆኖ እናገኘዋለን። በአገው ማለትም በላስታ ማህበረሰብ ትውፊት እንደሚነገረው የአገው ትውልድ የሚመዘዘው ከንጉስ ዳዊት የልጁ ልጅ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ምኒሊክ ጋር አብረው እንደመጡ ይነገራል። ቀዳማዊ ምኒሊክ የዳዊት የልጅ ልጅ የንጉስ ሰሎሞን ልጅ በመሆኑ ከአገው አባቶች ጋር የአጎት ልጆች ወይም ወንድማማቾች ናቸው ማለት ነው። እንደሚታወቀው ንጉስ ዳዊት ደግሞ የእስራኤል ዘር ሴማዊ ነው። ስለዚህ የአገው ነገድ የነብዩ የንጉስ ዳዊት ዘር ስለሆነ በቋንቋው የኩሽ ቤተሰብ ቢባልም በደሙ ግን የሴም ዘር ነው።

  • ማጠቃለያ፣

የኩሽ ስልጣኔ እና የኩሽ ቋንቋ የተለያዩ ናቸው። የኩሽ ስልጣኔ ሲባል በኑብያ ውስጥ በአባይ ዳርቻ የነበረውን ጥንታዊ የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ ለማለት እንጂ በወቅቱ ህዝቡ ይናገረው የነበረው ቋንቋ አሁን በሃገራችን “የኩሽ  ቋንቋ” ተብሎ ከሚገለፀው ጋር አንድ ነው ለማለት ዓይደለም። በቅድመ ታሪክ በኩሽ ህዝብ ተብለው በሚጠሩት ማህበረሰቦች የነበራቸው ባህል፣ ልማድ፣ የአምልኮ ስርዓት፣ የቤተመቅደስና የቤተመንግስት ህንጻ የአሰራር ጥበባቸው፣ የንጉሶች የመቃብር ሃውልቶች አሰራር፣ የአምላኮቻቸው መጠሪያ ስሞች አሁን የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ተብለው በሚጠሩት ህዝቦች ዘንድ አንዱም አይገኝም። የጥንቱ የኩሽ ቋንቋ (ቋንቋዎች) ምን ዓይነት እንደነበር(ሩ) አይታወቅም። በድንጋይ ላይም ሆነ በፓፒረስ ላይ የኩሽ ነገስታት ስለራሳቸው ነገድና ጎሳ፣ በግዛታቸው ስለ ነበሩ ማህበረሰቦች ብዛትና ዓይነት ወይም ይናገሩት የነበረውን ቋንቋ በተመለከተ ያስቀመጡት ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘም። የኩሽ ቋንቋ (የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ) መባል የተጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሃገራችን እና አህጉራችን በመጡ ሚሲዮናውያን (“ነጭ ደብተራዎች”) ነው። ሚሲዮናውያኑ የፈለጉትን ሌላ ገላጭ የሆነ ስም መጠቀም (መስጠት) ሲችሉ በምንቸገረኝነት ከጥንት ጀምሮ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ በጋራ መጠሪያነት ያገለግል የነበረውን “ኩሽ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል (Generic Term) ለአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ብቻ ነጥለው መስጠታቸው የቃሉን ትርጉምና ታሪካዊ አመጣጡን በማዛባት በብዙ ሰዎች ዘንድ ኩሽ በሚለው ቃል አጠቃቀም ላይ መደናገርን ፈጠረ።

የመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለፀው ኩሽ እና በታሪክ የኩሽ ስልጣኔ የሚባሉት የተለያዩ መሆናቸውን “ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ዶ/ር ግርማ አውግቸው በሰፊው አብራርተው ስለጻፉት መፅሃፉን ማንበብ የተሻለ ይሆናል። ከሞላ ጎደል በመጽሃፉ ላይ የሚከተሉት ፍሬ ሃሳቦች ይገኛሉ፡ በዘመናችን ኩሽ እየተባሉ የሚገለጹትን የቋንቋ ቤተሰቦችም ሆኑ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሕዝቦች ጥንት በቅድመ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ጀምሮ በነበረው ኩሽ በሚባለው አገር (ስልጣኔ) ከሚኖሩ ነገዶች ወይም ሕዝቦች በቀጥታ የወረዱ ናቸው ማለት አይደለም። በዘመናችን ኩሽ የሚባሉት ህዝቦች በስማቸው ከመመሳሰል ውጭ “ከጥንቱ የኩሽ ስልጣኔ” ጋር ግንኙነት የላቸውም። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ ኩሽ ተብሎ የተገለፀው የካም ልጅ (የኖህ የልጅ ልጅ) እና አሁን በሥነ ልሳን ጥናት ኩሽ የሚባለው የቋንቋ ቤተሰብ ከስማችው መመሳሰል በስተቀር የታሪክ ግንኙነት የላቸውም። —//—

እውነት መዳኛችን ነው!

ደረጀ ተፈራ

ለተጨማሪ ንባብ፣

“ኩሽ፣ ሴም፣ ኑቢያ፣ አበሻ እና ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ – ዘ ሐበሸ – ድህረ ገጽ ላይ  በ JULY 7, 2021 ያቀረብኩትን ጽሁፍ መመልከት ይችላል።

ምንጭ፣

“ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ” (ዶ/ር ግርማ አውግቸው )
“በረራ – ቀዳሚት አዲስ አበባ (1400 – 1887). .” ዶ/ር ሃብታሙ መንግስቴ ተገኝ – 2020
“The Origin Of Amharic” (Girma Awgichew Demeke)
“The Ethiopian Borderlands” (Richard Pankhurst)

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. አቶ ደረጀ ተፈራ ስለ ኩሽ እና አበሻ አመጣጥ እና ትርጓሜ መረጃዎችን በመንተራስ በዘመናችን ህዝብን ለፖለቲካ ስልጣን ሲሉ በዘር ለመከፋፈል የተለየ ትርጓሜ ለሚሰጡ መልስ እና በጭፍን ለሚከተሏቸው መንጋ የማንቂያ ጥናታዊ ፅሁፍ ነው ። አቶ ደረጀ እናመሰግናለን !!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here