ማስተዋል ጠግነው (Mastewale Teginew from London, UK)
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ እኤአ የካቲት 12፣ 2023 በለንደን ተጠርቶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ነው፡፡ የሰልፉም ዓላማ የኢትዮጵያ መንግስት የኦርቶዶክስ ቤ/ክን ሲኖዶስን ለሁለት ለመክፈል እያደረገ ያለውን ጣልቃገብነት መቃወም ነበር፡፡ እኔም እንደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይነቴ በለንደኑ ሰልፍ ላይ በመገኘት ተቃውሞዬን አሰምቻለሁ፡፡
ወደኋላ ሳስበው ግን፣ ጠ/ሚ/ሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ሰሞን የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲጠቀሟቸው ከነበሩ ቃላት በተቃራኒ ቆመው መገኘታቸው ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ ከእነዚህ የአብይ አህመድ የሽንገላ ቃላት መካከል በዚህ ፅሁፍ ሁለቱን ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡
- ‹‹ኦርቶዶክስ ሃገር ናት››
‹‹ኦርቶዶክስ ሀገር ናት›› እያለ ሲያታልለን የኖረው አብይ አህመድ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ፀረ-ኦርቶዶክስ አቋም ሊያራምድ ቻለ›› የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ እስቲ የነገሩን ሂደት ከመነሻው ጀምረን እንየው፡፡
ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ በ2010 (እኤአ በ2018) ወደ ሥልጣን ሲመጣ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ካደረጋቸው ተግባራቶች መካከል አንዱ በአሜሪካ የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሲኖዶስ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለስና እርቀ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነበር፡፡ በዚህ የእርቅ ሂደት ውስጥ ነበር ጠቅላይ ሚ/ር አብይ ‹‹ኦርቶዶክስ ሀገር ናት›› የሚልና የብዙዎችን ድጋፍ ያስገኘለትን ንግግር የተናገረው፡፡
‹‹ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሀገር ናት›› እያለ በአደባባይ ሲሸነግለን የነበረው ጠ/ሚ/ር አብይና የሚመሩት መንግስት ግን ፀረ-ኦርቶዶክስ የሆነ ተግባር ውስጥ መግባት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነበር፡፡ አጀማመሩም የቤተ ክርስትያኗን የአደባባይ በዓላት በማወክ ነበር፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለዘመናት የጥምቀትንና የመስቀል በዓል ሲከበሩባቸው የነበሩ ቦታዎችን በመከልከልና የሃይማኖቱ ተከታዮች በአደባባይ እንዳይዘምሩ በማፈን የመንግስት የፀጥታ አካላት በዓላቱን በየዓመቱ ሲያውኩ ኖረዋል፡፡
የአደባባይ በዓላትን በማወክ የተጀመረው የመንግስት ተግባር ግን ወዲያው ቤተ ክርስትያኗን ለሁለት የመክፈል ሴራ ውስጥ ገባ፡፡ ይሄንንም ሰይጣናዊ ሥራ መጀመሪያ፣ በሐምሌ ወር 2011 (2019) የኦሮሚያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽነር እና በኦርቶዶክስ ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በሆኑት በቄስ በላይ መኮንን በኩል፤ በመቀጠል ደግሞ በጥር ወር 2015 (2023) በእነ አባ ሳዊሮስ በኩል ሞከረው፡፡ የነአባ ሳዊሮስ ተግባር ብዙ ኦርቶዶክሳውያንን መስዋዕትነት አስከፈለ፡፡ እኔ በታሪክ ንባቤም ሆነ በህይወቴ አይቼ በማላቀው ደረጃ ቤ/ክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማቅ (ጥቁር) ለብሳ አየኋት፡፡ እኛም በለንደን ተቃውሞ ሰልፍ የወጣነው ይሄንን የቤ/ክናችንን ሐዘን ለመጋራት ነበር፡፡
የእነ አባ ሳዊሮስን ‹‹መፈንቅለ ሲኖዶስ›› ተግባር ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ የሰጡት ዛቻና ማስፈራሪያ የተሞላበት መግለጫ ግን፣ በጉዳዩ ውስጥ መንግስት በቀጥታ እጁ እንዳለበት የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ቆይተው ግን፣ ከጀርባ ሴራውን ሲጎነጉኑ የነበሩት ጠቅላይ ሚ/ር የህዝቡን ቁጣ ሲያዩ፣ አስታራቂ ሆነው መጡ፡፡
- ‹‹የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሞተር ነው››
ጠ/ሚ/ር አብይ በመጋቢት 2010 (2018) ልክ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ካደረጓቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ጉዞዎች ውስጥ ከጂግጂጋ በመቀጠል የተጓዙት ወደ መቀለ (ትግራይ) ነበር፡፡ መቀለ ላይ ‹‹የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሞተር ነው›› በሚል ያደረጉት ንግግር ከበርካታ የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነትን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
ጠ/ሚ/ር አብይ እንደዚህ በቃላት የሸነገሉትን ህዝብ ግን፣ ለመስደብና በጠላትነት ለመፈረጅ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በመጀመሪያ፣ ህወሓት የሰራቸውን ነገሮች ሁሉ በማጥላላት ጀመሩ፤ በመቀጠል ህወሓት ሲመራቸው የነበሩ እንደ ሜቴክና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክቶችን ‹‹የህወሓት የሙስና ተቋማት›› በማለት ተፈርጀው በመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘጋቢ ፊልም እንዲሰራባቸው ተደረገ፡፡ በመቀጠል የተቋማቱን መሪዎች ኢ/ር ስመኘውንና ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውን ወደ መግደልና ማሰር ገቡ፡፡
ከዚያም፣ ጠ/ሚ/ሩ ህወሓትንና ደጋፊዎቹን ‹‹ጁንታ›› የሚል ስያሜ በመስጠት፣ በመላው ኢትዮጵያ ተበትነው የሚገኙ ትግራዋዮች በሀገራቸው ተሸማቀው እንዲኖሩ አደረጉ፡፡ በስተመጨረሻም፣ መገናኛ መስመሮችን ሁሉ በመዝጋትና ጦር በማዝመት ‹‹አሳውን ለማጥመድ፣ ባህሩን ማድረቅ›› በሚል መርህ፣ የትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት አወጁ፡፡ በቃላት ሽንገላ የተጀመረው የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ የሥልጣን ጉዞ፣ መጨረሻው ውድመትና የህዝብ እልቂት ሆነ፡፡
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ