spot_img
Tuesday, October 3, 2023
Homeነፃ አስተያየት“ግብስብስ” (በራየ ብዕሩ  ከደጃች ውቤ ሰፈር) 

“ግብስብስ” (በራየ ብዕሩ  ከደጃች ውቤ ሰፈር) 

advertisement
የዮኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጭፈራ ላይ ( ፎቶው ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ ምርጥ ቲዮብ)

በራየ ብዕሩ  ከደጃች ውቤ ሰፈር

የማህበረሰብ ምህንድስና ጠበብት የሆነው ፈረንሳዊው ኤሚል ዳርካይም (on suicide)  በተሰኘው የምርምር መድብሉ ላይ በጥልቅ የተመራመረው ነገር ቢኖር ግለሰብ እና  ማህበረሰብ በሚለው ርዕስ ሥር የማህበራዊ ትስስር መላላት እንዴት ግለሰብን ብሎም  ማህበረሰብን የመበጣጠስ እና የመበታተን አቅሙ ሃያል እንደሆነ በጥልቅ አሳይቷል።  ሰው በግሉ ወይንም ማህበረሰብ በጋራ ለከፍተኛ ቀውስ ይጋለጣል፤ ይሄ የዳርካይም  ንግግር በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆንብን፤ የህብረተሰብ  ትስሰር ሃያል የሆነባቸው አገራት ውስጥ ግለሰብ የራሱ ተነሳሽነት ብሎም የህብረተሰብን  የጋራ በጎ ብልጽግናን ይከተላሉ፤ እራሳቸውንም ሆነ ህብረተሰብን የሚጎዳ ነገር አያደርጉም፤  ይህንንም ዳርከይም ሚዛናዊ የህይወት ምርኩዝ ይለዋል። እንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ህየወቱን የሚያጠፋ በጣም ጥቂት ነው፤ ለእንደዚህ አይነቱ ከንቱ ጥፋት የሚጋለጡ ግለሰቦች የሚኖሩበት ማህበረሰብ ሁልጊዜም ቢሆን ምንም የጠበቀ የማህበረሰብ ትስስር የሌላቸው ሚዛናዊ የህይወት ምርኩዝ የተሰበረባቸው ናቸው ይላል። 

እዚህ ላይ የኢትዮጵያዊያንን የጎረቤትን ቡና ጠጡን ጥሪ ልብ ይሏል፤ ምን ያህል  የማህበረሰብ ማስተሳሰሪያ ገመድ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ህብረተሰብ ቡና ጠጡን  በሚመስል በጣም ትንሽ ነገር ግን የዘለቄታ የህወት መስተጋብር ያላቸውን በጎ እና ጠንካራ  የጋራ ትስስር በማህበረሰቡ ውስጥ ይፈጥራሉ ፤ ብሎም በማህብርረሰቡ ውስጥ ያሉትን  ግለሰቦች በራዕይ ያገናኛሉ ፤ ይሄም በዕለት ተዕለት ኑሮእቸው ይገለጣል። ቡና በመጠራራት፤ በዓላትን በጋራ የማክበር መንፈስ፤ ሐዘንን በጋራ የማጽጽናት ፤ በጎን በጋራ የመመኘትን ፤  ብሎም የጋራ የሆነውን “ጎጆ” አገርን የመጠበቅ ጅግንናን ይጋራሉ ። ይሄም በቀላሉ  የማይታይ በቁም ነጋር ላይ የተመሰረተ ትልቅ ነገር እነደሆነ ማህበረሰቡ በሚሰጠው ከበሬታ፤  ግለሰቦችም በማህበረሰቡ ውስጥ የከበረ ቦታ በማግኘት ከበሬታ የሚቸረው ሥራ እንዲሰሩ  ይገፋቸዋል። ይሄንን በሌላ አንጻር ስንመለከተው ግለሰቦች ብቸኛ እና ግለኛ ከመሆን  የሚመጣ መላ ቅጡ የጠፋበት ምስቅልቅል የሆነ የስብዕና አረንቋ ውስጥ እንዳይዘፈቁ  ይረዳቸዋል። ስለ ስብዕና ልዕልናም በእጅጉ ይጨነቃሉ ፤ የዚህ ማህበራዊ ማዕቀፍ የሌላቸው  ግለሰቦች ግን ለሌሎች ቀርቶ ለራሳቸውም ግድ ስለማይኖራቸው በቀላሉ ይወታቸውን ይቀጥፋሉ ፤ ሌሎችንም ይቀጥፋሉ፣ ያስቀጥፋሉ፣ የህግ እና የስብዕና ደርዝን ይዘላሉ።   

እነኚህ ከላይ የዘረዘርናቸው የማህበረሰብ ማዕቀፍ ሰጠፉ የህግ እና የስብዕና ደርዝ በህብረተሰብም ላይም ይጠፋል። ይህም ማንም ለማንም አይጨነቅም፤ የጋራ የሚለው  ዕምነት ይሸረሸራል ፤ በህብረተስ ውስጥ እየኖሩ ብቸኛ ይሆናሉ፤ አገር ውስጥ ሆነው  ባይተዋር ይሆናሉ፤ የአብሮነት ፤ የአገርነት ፤ የአገር ልጅነት ስሜት ይበናል፤ ወንድም ፤ እህት ፤ ጎረቤት ፤ መንደር ፤ ቀዬ ትርጉም ያጣሉ፤ ወጥ ሥርዓት አይኖርም፤ ዕውቀት ትርጉም ያጣል፤  ብልጠት የዕውቀትን ቦታ ተቆናጦ ይቀመጣል፤ ጥፋት የመንጋ ሥርዓት ይሆናል፥ፍርዱም የመንጋ ይሆናል። ትናንትና የጨዋነት ምግባር መለኪያ የነበረው መስፈርት ይወድቅና በሌላ  ይተካል። ከእደዚህ አይነት ምስቅልቅል ውስጥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስተር ያሉት  አይነት ምግባር ማማው ላይ ይቀመጣል፤ “እናንተ የሰራችሁትን እየጻፉ ነው እነሱ ምሁር  የሚባሉት እነሱ ጥሩ ጫማ እንኳን የላቸውም ”… እዚህ ላይ ልንገነዘብ የሚገባን ዛሬ  ህብረተሰባችን የደረሰበት የህይወት ምስቅልቅል እንዲሁ የተከሰተ አይደለም የህብረተሰብ  የአስተሳሰብ እና የአሰራር ውጤት ነው። በተለይ ይሄ ሁሉ ግብስብስ በተለያዩ የዕምነት ቋጠሮዎች እና ድባቦች ባይያዙ እና ባይሸፈኑ ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባል አገርም ሆነ ኢትዮጵያዊ የሚባል ህዝብ አይኖርም ነበር። የሚባል ቦታም ሆነ ህብረተሰብ ህይወት አልባ  ቦታ በሆነ ነበር፤ የቀረው ዓለምም እንደ ዙ አይነት እይታ ባየን ነበር።  

 ከዚህ እንዴት ነው የምንወጣው? ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገ ለሚኖረ ው የኛው ልጆች ትውልድ ? ነገ ምንድን ነው? ዛሬ የኢትዮጵያዊያን ሥነ ልቦና ምን ይመስላል? አገሩን በጋራ  ገምዶ ያለውን የእምነት ገመዶች ውስጥ አንዱን ስንቃኝ ፤ በአንድ የሃይማኖት መምህር ፊት የምናየውን እንደዚህ ለቁጥር ያሚያዳግት የሰይጣን መዓት ከየት የመጣ ነው ብለን  እንድጠይቅ ያደርገናል ፤ ሰይጣንን ዛሬ ነው እንዴ ኢትዮጵያ የምታውቀው? ለቁጥር  የሚያታክት የህብረተሰባችን ክፍል በአደባባይ በሰይጣን ስም ሲውዘፈዘፍ የምናየው ለምንድን ነው? የእግዚአብሔርን መኖር አማኝ ነኝ፤ ጥያቄዬ ግን እውነት ኢትዮጵያችን  ከላይ እስከ ታች የሰይጣን መናኸሪያ ሆናለች? ዛሬ ኢትዮጵያ አምስት ሺህ ዘመን  ያስቆጠረች አገር በማይመስል መልኩ ከዛም አልፎ አስቂኝ በሚመስል ትርኢት ፈውስ  ታገኛለህ እየተባለ ስብዕናን በሚያዋርድ መልኩ ፊቱ በጫማ እየተመታ የሚወድቅበት አገር  መሆኗን ማየት ከየት የመጣ ነው? ይሄ ብቻውን አንዱ የማህበራዊ ህይወት ሠንሠለት  መበጣጠስ አንዱ መገለጫው ነው። ኸረ ዕውቀት ከወዴት አለህ? ማስተዋልስ እንዴት ደረስክ ያሰኛል።  

 እንደ አገር እና ህብረተሰብ የነገ እጣችን ምንድን ነው? እራሳችንን ለመመገብ እንኳን  የበቃን አይደለንም ፤ እንደዛም ሆነን መጀመሪያ የሚያስጨንቀን አገራዊ ጉዳይ አይደለም ፤ ሥርዓት፣ ህግ እና የግብረገብ ልዕልና የሌለው ግለሰብም ይሁን ማህበረሰብ እጣ ፈንታው  የጭለማ ላይ ጉዞ ነው የሚሆነው። እንደ ኢትዮጵያ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት በሆነበት አገር ውስጥ ሲሆን ደሞ ችግሩን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል። በተበጣጠሰ የማህበረሰብ ሠንሠለት ውስጥ አዱኛን ለማፈስ በሚሽቀዳደሙ ጥቂት የህይወት  ጉንዳኖች የብዙሃኑ ቤት የሆነው አገር የሚባለውን ነገር ኩይሳ ያደርገዋል። መዓት እና ምስቅልቅል የሚሆነውም ይሄው ነው። ከሰማይ እንደ መና ዱብ የሚል ነገር አይደለም  የእኛው የእጅ ሥራ ውጤት ነው። የዳበረ የነጠረ የማህበረሰብ ትስስር ይላል ዳርካይም  ግለሰቦች ባልረባ ሃሳብ እንዳይባክኑ ያደርጋቸዋል ማህበረሰብን የማገልገል ሃላፊነት እንዳለባቸው የገነዘባሉ፤ በሚያጋጥማቸው የዕለት ተዕለት ችግርም ብዙዎች አይንገላቱም ፤ ከዛ የበለጠ የአገር ራዕይ አለ ብለው ለዛ መስዋዕትነት ይከፍላሉ ፤ ቢደክመኝ የሚረዳኝ፤ ቢደክመን የሚረዳን አለን ብለው በማሰብ እራስን ብቻ አልፎም ጎሳን ብቻ አምልኮ ከመሞት  ይወጡ እና የሰውን ልጅ ወደሚለው ከፍተኛ የአስተሳሰብ ቅድስና እራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤  በዚህም እንኳን የሰው ልጅ ቀርቶ ሳርም ቅጠሉም ይጠቀማል ብለው ያምናሉ፤ የስብዕና  ከፍተኛ ማማ ላይ ይቀመጣሉ፤ መለኪያቸው የሰው ልጅ ብቻ ይሆናል። 

 የብዙሃን እናት የሆነችውን ኢትዮጵያን ከጎሳ በተለቀሙ ጥቂት የድግስ አንጋቾችን  ሰብስቦ በንዋይ ናላቸውን በማዞር አገር በዚህ አይነት መልኩ እናስቀጥላለል ብሎ ማመን  የዋህነት ሳይሆን ድንቁርና ነው። ዘመናዊ ድንቁርና ፤ ይልቁንም ዳርካይም እንደ ድህነት ያለ  እራስን ለመግዛት የሚያስችል ትምህርት የሚሰጥ ት/ቤት ከቶውንም አይገኝም ይላል፤ በአገራችን አብዛኞቹ ስልጣን ላይ የተንፈራጠጡትን ስንመለከት ከዚሁ ከድህነት አቧራ  ላይ የተነሱ መሆናቸው እንኳን ይልቁንም ለመጡበት ማህበረሰብ እንኳን በጎውን ሌት  ተቀን እንዲያስቡ እና እንዲሰሩ ባደረጋቸው ነበር፤ ከእነሱ ስልጣን ዘመን መራዘም ይልቅ የህብረተሰብ የአሁን እና የወደፊት እንግልት ብሎም ምስቅልቅል ህይወት መስተካከል  ይበልጣል የሚል ሃሳብ ባዳበሩ ነበር።  

የማህበረሰብ የጋራ ውል የሆነው ህገ መንግስት በጋራ ፍላጎት የሚቀመር የራስን ፍላጎት ከማስፈር ባሻገር የሌሎችን ለመገንዘብ የሚተጋ የእሳቤ ቀመር በመያዝ የግለስብን  ብሎም የማህበረሰብን መብት እና ፍላጎት ፍጽም በሆነ ሰብዓዊ መንገድ የሚያስተናግድ  ሰነድ ካልሆነ በስተቀር ትናንት እኛ እንዲህ ስለሆንን ዛሬ እንዲህ መጻፍ አለበት እነንቶኔ  እንዲህ ነበሩ ተብሎ በጥቂቶች ተጽፎ ለእናንተም ጭምር ነው የሚለው አይነት ሰነድ  መከራን በቆይታ የሚያሳድር እንጂ የትም አያደርስም። አሁን ባለንበት በሃያ አንደኛው  ክፍለ ዘመን የምጣኔ ሃብት ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ምጣኔ በረቀቀበት ዘመን ዘመኑን  የማይመጥን ንግግር በፖለቲካ ደቂቃን በአደባባይ ሲነገር ስንሰማ አቤቱ የፈጣሪ ያለህ  ያሰኛል። ዛሬ በአሜሪካን ጥቁሮች ላይ የሚወርደውን የዘረኝነት በትር በዓለም ጥግ ላይ  ያሉ ስለሰው ልጅ የላቀ እሳቤ ያለው የሰው ልጅ በሙሉ ሲቃወም ስናይ እኛ  ኢትዮጵያዊያኖች ግን አገራችን ውስጥ የአንድነቱ ጽድቅ እንኳን ቀርቶብን አስከፊ እና  አጸያፊ አዳፋ እና የከረፋ የሆነውን የጎጠኝነትን ሸማ እንደልብስ ለብሰን ከእንስሳ ባነሰ  አስተሳሰብ በአድባባይ ዳንኪራ እየወረድንበት እንገኛለን። በጋራ እየተራቡ በተናጥል  እንዴት መፍትሄ ይፈለጋል? በሃያ አንደኛው ክፈለ ዘመን እንዴት አንዱ በአንዱ ላይ ብልጥ  ሊሆን ይችላል ፤ እረሃብተኝነት የቆየ የጋራ ችግራችን ነው እሱን መጀመሪያ ማድረግ ግድ  ይላል የሰው ልጅ እና ረሃቡ ፥ ኢትዮጵያ እና ረሃቧ ፤ ሰው መሆናችን እና ረሃባችን  ካላስተሳሰረን አስር ሚሊዮን ጊዜ ወረቀት ላይ የሚጻፍ ጽሁፍ ሊያስተሳስረን አይችልም ይሄ  ሞኝነት ነው። ሳይበሉ በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ የእንቶኔ ዘር ነኝ የእከሌ ጎሳ ነኝ ማለት አይበጅም። ኢትዮጵያ ወዴት ነው የምትሄደው? ማነውስ የሚመራት ፥ የወደፊት እጣዋስ ምንድን ነው? ማነውስ ወደላቀው ሃሳብ የሚወስዳት? በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ  በአንድ ሰው እና በአንድ ጎጥ ላይ የተመሰረተ ፍላጎት ከቶውንም አገርን ወደ ፊት ሊያራምድ እና ህዝብን ላጋራ ተጠቃሚነት ሊያበቃ አይችልም። የጋራ የሆኑትን የተመረጡ በጎ የቅድስና ሃሳቦችን የሚያሰባስብ ባለ ራዕዩ ማን ይሆን…  

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,732FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here