
ማስተዋል ጠግነው
ከሎንዶን ፣ እንግሊዝ
በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ይገኛል፡፡ መንግስትታት ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሏቸው፡፡ ምንም እንኳን አምባገነን መንግስታት ነፃነትና የዲሞክራሲ መብቶች ላይ አፋኝ ቢሆኑም፣ ሰላምና ፀጥታ ላይ፣ እንዲሁም የዜጎች ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሐብት የማፍራት መብቶችን በማስከበር ረገድ ግን ጠንካራ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ የዲሞክራሲ መብቶች ላይ በሚያደርገው አፈና ቢተችም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ግን አምጥቷል፤ ዜጎች በፈለጉት ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና በሰላም የመኖር መብታቸውንም አስከብሮ ነበር፡፡ በዲፕሎማሲና በምስራቅ አፍሪካ የነበረው ተሰሚነትም ትልቅ ነበር፡፡
በአብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ግን ከእነዚህ ውስጥ አንዱንም አላሳካም፡፡ በአብይ አህመድ ያልተገራ የግል ፍላጎትና መርህ አልባ ባህሪ የተነሳ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ማለትም ከሱዳን፣ ከኬንያና ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል፤ በአፍሪካ ያላት ተሰሚነትም ወርዷል፡፡
የአብይ አህመድ መንግስት የሀገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታም ማስከበር አልቻለም፡፡ ዜጎች በሰላም የመኖር መብታቸውን ተነፍገዋል፤ ሰላማዊ ሰዎችን ከታጣቂዎች ጥቃት መከላከል አልቻለም፡፡ የመንግስት የፀጥታ አካላት እንደፈለጉ ሰላማዊ ዜጎችን ያስራሉ፣ ይሰውራሉ፣ ያግታሉ፣ ይገድላሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ በቅርቡ የወጣው አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በሰላም ዕጦት የተነሳ በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ የሆነ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ፡፡
ሙስና ላይ የሚሰማው ነገርም በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ስልጣናቸውን በመጠቀም በምግብና በግንባታ ምርቶች ላይ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ይፈፅማሉ፤ የውጭ ምንዛሬዎችን ያሸሻሉ፡፡ ዛሬ ተቋማዊ መልክ የያዘው ሙስና፣ ውስኪ በሽጉጥ ካልከፈትን የሚሉ ሰዎችን ፈጥሯል፡፡ ኢኮኖሚያዊ የዋጋ ግሽበቱ በየዓመቱ በ38% እየጨመረ ነው፡፡ አብይ አህመድ በ2010 ወደ ሥልጣን ሲመጣ 5,000 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ፣ ዛሬ ከ6 ዓመት በኋላ በ3 እጥፍ ጨምሮ 15,000 ብር ገብቷል፡፡
መንግስት፣ ብዙ ሰው የሚቀጥሩና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶችን ከማስፈፀም ይልቅ፣ የሀገሪቱን ሀብት እምብዛም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በሌላቸው ፓርኮች ግንባታ ላይ አባክኖታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፓርላማው ዕውቅናና ከመንግስት የፋይናንስ ሥርዓት ውጭ በሆነ መንገድ በ850 ቢሊየን ብር (ወይም በ15 ቢሊየን ዶላር) አዲስ ቤተመንግስትን የካተተ ‹‹የጫካ ፕሮጀክት›› ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ ባለው ተራራ ላይ እየተገነባ ነው፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን በሌላ አዋጪ በሆኑ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ቢውል 3 የህዳሴ ግድቦችን ወይም 20 ሆስፒታሎችንና በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ በመልሶ ግንባታ ላይ ይዋል እንኳ ከተባለ በአንድ ቢሊየን ዶላሩ ብቻ በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልል የወደሙ ሁሉንም ት/ቤቶችን መልሶ መገንባት ይችላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ሀብት በእንደዚህ ዓይነት ቅንጡ ፕሮጅክቶች ላይ እያባከኑ ያሉት ከ6 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ባሉበት፣ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት 28 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የዕለት እርዳታ ጠባቂ በሆኑበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ አጥተው ሰልፍ በሚወጡበት፣ ክልሎች ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት ወርሃዊ ደምወዝ ባጡበት፣ የሀገሪቱ የውጭ ብድር ዕዳ 28 ቢሊየን ዶላር በደረሰበት ወቅት ነው፡፡ ይሄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግል ፍላጎታቸው እንጂ ለዜጎች ደህንነትና ችግር ደንታ የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ተግባራት ኢትዮጵያ የአብይ አህመድ የግል ንብረት ሆናለች፡፡
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ