spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትየባህር በር ተደራሽነት (Access to the Sea) አጀንዳ ጉዳይ ሲፈተሽ!

የባህር በር ተደራሽነት (Access to the Sea) አጀንዳ ጉዳይ ሲፈተሽ!

የባህር በር  _ ሲሳይ መንግስቴ 
ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር )

ከሲሳይ መንግስቴ 

ሰሞኑን በሀገራችን ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ውስጥ የመነጋገሪያ ርእስ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ባለፈው ሳምንት ጠቀላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ ለኢትዮጵያ የባህር በር የመኖር አሰፈላጊነትን አስመልክተው በጽ/ቤታቸው ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት የሰጡት የ45 ደቂቃ ገለጻ አንዱና ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ርእሰ ጉዳዩ ባለፉት ሁለት አመታት በምን መልኩ መታየትና መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት ቤተመንግስት አካባቢ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት በመድረክ ላይ በይፋ ከመገለጹም በላይ በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ተሰጥቶት ሲዘገብ ለመመልከት በቅተናል። 

እውነት ነው ጉዳዩ ቀደም ሲል ለጋዜጠኞችና ጡረተኛ ዲፕሎማቶች በመወያያ ርእስነት ቀርቦ እንደነበርም ሰምተናል፣ ይህንን ሁኔታ ተከትሎ ሀሳቡን በበጎ መልኩ የተመለከቱ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል አሉታዊ አንድምታው ጎልቶ የታያቸው ወግኖች እንዳሉም ከንግግሮቻቸው እየሰማን እና ከጽሁፎቻቸውም እያነበብን ነው። ጉዳዩን በአሉታዊ መልኩ የተመለከቱት ወገኖች አጉልተው ሊያሳዩ የሚሞክሩት በኤርትራ መንግስትና ሕዝብ ላይ ሊያሳድረው የሚችለውን ሰጋትና እሱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የግንኙነት መሻክር ነው።

እናም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የ 45 ደቂቃ ገለጻ (Lecture) በጥሞና በተከታተሉት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከል የዚህ አይነት ስሜትና ጥርጣሬ ለምን ሊፈጠር ቻለ? አጀንዳውስ ቢሆን አዲስና አይነኬ መሆን ይገባዋልን? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ይመስለኛል፣ ምክንያቱም ላለፉት 32 አመታት ውሾን ያነሳ ውሾ የተባለ ይመስል ዝም ተብሎ የቆየን ጉዳይ አሁን ላይ በድንገት ተነስቶ ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ ማቅርብ ለምንስ አስፈለገ? ወቅቱስ ለዚህ የተመቸ ነውን? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳልና ነው። 

ይህም የሆነበት ምክንያት ባለፉት ሶስት አመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስንታመስ ቆይተን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀው በሀዘን ድባብ ውስጥ ባለንበት፣ በትሪሊዮን የሚገመት ሀብትና ንብረት በወደመበትና የሰላም አየር ባልሰፈነበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አሁንም ጭምር በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመስን ባለንበት ሁኔታ ሌላ ወደ ተጨማሪ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል አጀንዳ ይዞ መምጣትና መድረክ ፈጥሮ የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ማድረግ ተገቢና ወቅታዊ ነውን? የሚለው ጥያቄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአጠቃላይና ይህን ርእሰ ጉዳይ በንቃት ለሚከታተሉ ወገኖቸ በተለይ በእጅጉ ስለሚያሳስብ ጭምር ነው። 

በተለይም በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት በአማራ ሕዝብ ህልውና ላይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል-የአለመቀጠል ሁኔታ ላይ የደቀነው አደጋ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ ይህንን ችግር ወደ ጎን በማለት ወይም አቅልሎ በመመልከት ሌላ ጦርነት ሊያስከትልና የኢትዮጵያን ሕዝብም ሊከፋፍል የሚችል አጅንዳን አምጥቶ መደቀን አንድም የሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር መሞክር፣ አሊያም የለየለት እብደት ነው የሚሆነው ከሚል ስሜት የሚመጣ ይመስለኛል። በሌላ አነጋገር የውስጥ ፖለቲካዊ ችግራችንን በአግባቡ ሳንፈታና ጦርነቱ ያሰከተለውንና እያሰከተለ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ሳናካክስና ሳናስቅር ሌላ ፍጥጫ ውስጥ የሚያስገባ ብሎም ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችል ጉዳይ አምጥቶ መደንጎር አደገኛ እንደሆነ ይታመናል።

በአጠቃላይ ሲታይ ወቅቱ ይህንን ስሱ (Sensitive) አጀንዳ አንስቶ መወያያ ማድረግ ያስችላል ወይ? በአሁኑ ወቅትስ ይህ አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባልን? የሚሉት ጥያቄዎች ተገቢነት እንደተጠበቁ ሆነው ጉዳዩ የብዙሀኑን ትኩረት በሚስብ መልኩ ለውይይት መቅረቡና የመነጋገሪያ አጅንዳ መሆን መቻሉ ግን ያን ያህል ክፋት አለው ብዬ አላምንም። እንዳውም አጀንዳው እጅግ የዘገዬና ለፖለቲካ ትክክለኛነት ሲባል ወደ ጎን ተብሎ የቆየ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ለምን ቢባል ባለፉት 30 አመታት የትህነግ-ኢሕአዴግ አመራር ይህችን አገር ካሳጣት መሰረታዊ ጥቅሞች መካከል የባህር በር እንዳይኖራት ማድረጉ አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል። 

እውነታው እንደዛ ከሆነ ለምን ይሆን ከአንዳንድ ወገኖች ጠንከር ያለ የተቃውሞ ሀሳብ የሚቀርበውና ጥርጣሬን ለመጫር የሚሞከረው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፣ በእኔ እይታ አንዳንዶቹ አሁን ያለው የሀገራችን ችግርና እያሰከተለው ያለው ከፍተኛ የሆነ ጉዳት በእጅጉ አሳስቧችው ሲሆን ሌሎቹ ግን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አስተዳደራቸውን ለማሳጣት ስለሚጥቅማቸው መሆኑን ከአቀራርባቸው መረዳት ይቻላል። ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንደሚባለው የዚህ አይነት የሰሉ ትችቶችንም ሆነ ሊያስከትል የሚችለውን ፍጥጫ ተሰግቶ ለአገር ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ ጥያቄን አንስቶ በማህበረሰቡ ዘንድ የመነጋግር አጀንዳ እንዲሆን አለማድረግና ዘላቂ መፍትሄ አለመሻት ሌላ ጥፋት ነው የሚሆነው። 

እርግጥ ነው በዚህ ወቅት ይህን ርእሰ ጉዳይ በዋና አጀንዳነት አቅርቦ መነጋገሪያ ማድረግ ሊፈጥር የሚችለውን ችግር ማገናዝብ መቻል ከአንድ ሀላፊነት ከሚሰማው ፖለቲካኛም ሆነ ዜጋ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ለምን ቢባል አሁን ላይ የዚህ ኣይነት ስሱ (Sensitive) የሆነን ጉዳይ በከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት ደረጃ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ በራሱ አንድም በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ይቆጠራል፣ ሁለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ በአጠቃላይና ልሂቃኑን ደግሞ በተለይ ለመከፋፈል በር ይከፍታል የሚለው ስጋት ውሀ ያነሳልና ነው። በሌላ አነጋገር መላ ሰውነቷ በእሾህ የተወጋባት ዝንጀሮ በየትኛው የሰውነትሽ ክፍል ላይ ያለውን እሾህ እናውጣልሽ ሲሏት ፊት መቀመጫየን አለች እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ውስጥ ነው የምትገኘው፣ ይህም ማለት የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው የሰላም መታጣት፣ እጅግ አስከፊ የሆነው የኑሮ ውድነት፣ በግልጽ የሚታየው የተካረረ ብሔረተኝነት ሀገር ለማፍረስ የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱና ይህንን አስከፊና አገርንና ሕዝብን አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል አደገኛ ሁኔታን ሊቀለብስ የሚያስችል የመፍትሄ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ አጀንዳው ለውይይት መቅረቡ በአዎንታዊ መልኩ ከመታየት ይልቅ በአሉታ መታየቱ የሚያስገርም ጉዳይ አይሆንም።

ክዚህ ውጭ በየማህበራዊ ሚዲያው ተደጋግሞ አሰልቺ በሆነ አኳኋን ጭምር የሚቀርበው የሴራ ትንተናም (Speculation or Conspiracy) ሆነ ያልተገባ ፈንጠዝያ ለማንም የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን የሚከፋፍልና ለጠላትም አሳልፎ የሚስጥ ነው የሚሆነው። አጀንዳው ከተንሳ አይቀር ግን ወደብን ጨምሮ የባህር በር ማግኘት ይቻል ዘንድ በአማራጭነት በቀረቡት ሁኔታዎች ላይ መወያየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል። ይህም ማለት መሬት ወይም ሀገሪቱ ካሏትና በአትራፊነታቸው ከሚታወቁ ኩባንያዎች ውስጥ አገራት መርጠው ድርሻ እንዲወስዱ በማድረግ ይህንን ሀሳብ ማሳካት ይቻላልን በሚለው ላይ መነጋገሩ ተግቢ ነው። 

ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ የእሰካሁኑ ንትርክም በሉት ትችት እነዚህን አማራጭ ሀሳቦች በትክክል ሲያነሳቸው አልተመለከትሁም፣ እነዚህ አማራጭ ሀሳቦች የሚያስገኙት ጥቅምና ጉዳትም በተገቢው ሲዳሰስ አላየሁም። በነገራችን ላይ ወደብ ማግኘትና የባህር በር ባለቤት መሆን እጅግ የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል፣ ወደብን በግዥ መልክ ወይም በረዥም ጊዜ ኪራይ (Lease) ማግኘት ይቻል ይሆናል፣ የባህር በር ባለቤትነት መብትን ግን ወደብን ለማግኘት በሚያስችሉት አማራጮች ማሳካት አይቻልም። 

በዛ ላይ የራስህ የሆነ የባህር በር ሲኖርህ የደህንነትህ ሁኔታ የተረጋገጠ ይሆናል (ጠንካራ የባህር ሀይል ይኖርሀል፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር የትብብርና ጥምረት ግንኙነት ትፈጥርበታለህ፣ ልኣላዊነትህን በአስተማማኝ ሁኔታ ትጠብቅበታለህ ውዘተ)፣ በባህሩ ወይም እንደሁኔታው በውቅያኖሱ ላይም ሆነ ውስጥ የመጠቀም መብትና ነጻነት ይኖርሀል፣ በአሳና በሌሎች የባህር ሀብቶችም ላይ የሚኖርህ የባለቤትነት ድርሻ ከፍ ያለ ይሆናል ወዘተ። 

በአጠቃላይ ሲታይ ይህንን ጉዳይ ማየት ያለብን ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አስተዳደራቸውን ብሎም የብልጽግና ፓርቲን በምንመልከትበት መንጽር ሳይሆን ጉዳዩ ለሀገር በሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት ልክ መሆን ይገባዋል። በሌላ አነጋገር ወደብን ጨምሮ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በአጀንዳነት ተነስቶ የመወያያ ርእስ መሆኑ በራሱ ቸግር ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይመስለኝም፣ ይልቁንም አሁን ላይ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከመፍታት ጎን ለጎን ይህንንም ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ በማቅረብ ዘላቂ መፍትሄ መሻቱ ተግቢ ይሆናል።       

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here