spot_img
Tuesday, November 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትየባህር በርን በተመለከተ ያመለጡ ዕድሎች

የባህር በርን በተመለከተ ያመለጡ ዕድሎች

advertisement

ከሲሳይ መንግስቴ 

የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ግንኙነት ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ በአንድ መንግስት ስር ሲተዳደሩ የቆዩባቸው ዘመናት በርካታ እንደነበሩም ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ከሩቁ የአክሱም ዘመነ መንግስትን ማንሳት የሚቻል ሲሆን ከቅርብ ጊዜው ታሪካችን ደግሞ የአጼ ኃይለስላሴ አገዛዝን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ኤርትራ የአሁኑን ስሟን ከማግኘቷ በፊት ባህረ ነጋሽ በመባል ትጠራ የነበረ ሲሆን በ1881 ዓ.ም ጣሊያን አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ኤርትራ የሚለው ስያሜ እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡ 

ባህረ ነጋሽን ጣሊያን ከመቆጣጠሩ በፊት ገዥው ራስ አሉላ አባነጋ የነበሩ ሲሆን በዶጋሌና በሰሀጢ ከጣሊያን ወራሪ ወታደሮች ጋር ጦርነት ገጥመው አሸንፈዋቸው የነበረ ቢሆንም ከአጼ ዮሀንስ ፈቃድ ሳያገኙ ከጣሊያን ጋር በመዋጋታቸው ምክንያት በአጼ ዮሀንስ ላይ ቅሬታን ፈጥሮ በመካከላቸው አለመግባባትን አስከትሎ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ በዚህም ምክንያት ጣሊያን ቁጥጥሯን እያጠናከረች መጥታ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ ኤርትራን በቅኝ ግዛት ስር እንድትቆይ ማድረግ ችላለች፡፡ 

ሆኖም የ2ኛው የዓለም ጦርነት በአንድነት ሀይሎች አሸናፊነት ማብቃቱን ተከትሎ ኤርትራ ከጣሊያን አገዛዝ ነጻ ስትወጣ በጊዜው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አጼ ኃይለስላሴ ባደረጉት ያላሳለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ማድረግ ቻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሒደት የፌዴሬሽኑን ግንኙነት በማፍረሳቸው ፌዴሬሽኑ ከአስር አመት በላይ መዝለቅ ሳይችል ቀረ፡፡ በዚህም ምክንያት የኤርትራ ወጣቶች የትጥቅ ትግል ጀምረው ለሰላሳ አመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በ1983 ነጻ ወጣች፡፡

እንግዲህ የመጀመሪያው ዕድል ያመለጠው በንጉሱ የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑ ነው፣ ሁለተኛው ዕድል በ1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ የደርግን መንግስት ከማስወገዱ በፊት በሸአብያ፣ በኦነግና በኢሐአዴግ መካከል ሎንደን ላይ ድርድር እንዲካሄድ አሜሪካ ጥረት ባደረገችበት ወቅት ኤርትራ ነጻ የምትወጣ ከሆነ የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ እንዲሆን አማራጭ ሀሳብ ቀርቦ እንደነበረና የሸአብያ ተወካዮችም ጉዳዩን ሊያጤኑት እንደሚችሉ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም የኢሐአዴጉ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ይኸ ጉዳይ ያለቀለት ስለሆነ አጀንዳ ሊሆን አይገባውም በማለት እንደዘጉት በወቅቱ አሜሪካንን ወክሎ አደራዳሪ የነበረው ኸርማን ኮኸን በቅርቡ ይፋ ማድረጉን ሰምተናል፡፡ 

በዚህ የተሳሳተና ሀላፊነት የጎደለው ውሳኔ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት ተደረገ፡፡ ሦስተኛው በ1992 ዓ.ም ተገኝቶ የነበረው ዕድል ነው፣ ይህም ማለት በ1990 ግንቦት ወር ውስጥ ኤርትራ የኢትዮጵያን ግዛት ወራ ልኣላዊነቷን በመዳፈሯ ምክንያት በ1992 ዓ.ም ጦርነት ተካሂዶ ባድመን ከማስለቀቅ አልፎ ወደ ኤርትራ ግዛት መግባት ተችሎ የነበረ ቢሆንም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በፈጠረው ጫናና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወሰኑት የተሳሳተ ውሳኔ አማካኝነት ጦርነቱ እንዲቆም ተደረገ፡፡ 

ከዛም ወደ ድርድር እንዲገባ ተወስኖ ንግግር ሲጀመር የጠገኘውን ወታደራዊ የበላይነት በመጠቀም የባህር በር ማግኘትን እንደመደራደሪያ አድርገው ማቅረብ ሲገባቸው አሁንም በዝምታ አልፈው ሁለተኛ ታሪካዊ ስህተት ፈጸሙ፡፡ ስህተቱ ይኸ ብቻ ቢሆን መልካም ነበር፣ ከዛም አልፈው በ1928 ዓ.ም የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በግልጽ የሻራቸውን የ1902 እና የ1908 ዓ.ም በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስታት መካከል ተደርገው የነበሩ ስምምነቶችን በማስረጃነት በማቅረብ ኢትዮጵያ እንድትሸነፍና ባድመና አካባቢው ለኤርትራ እንዲወሰን ምክንያት ሆኑ፡፡ 

ከዛም አልፈው ይግባኝ የማይደረግበት ውሳኔ የሚወስን ዓለም አቀፍ ኮሚሽን እንዲቋቋም በመስማማትም ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ይባስ ብለው የኮሚሽኑ ውሳኔ ባድመን ለኤርትራ እንዲሆን አድርጎ ባለበት ሁኔታ ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነልን በማለት የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን በውሸት የአዲስ አበባን ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በማስወጣት እንዲጨፍሩ ማድረግ ቻሉ፡፡ እንግዲህ ታሪካዊ ሁኔታዊችን ወደ ኋላ መለስ ስንል ይህንን እውነታ ነው የምናገኘው፣ ቀጣዩስ ምን መልክ ይኖረው ይሆን የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

_

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here