spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትአሁናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁነትና በአማራ ላይ እየደረስ ላለው ቀውስ መውጫ መንገድ ጥያቄ...

አሁናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁነትና በአማራ ላይ እየደረስ ላለው ቀውስ መውጫ መንገድ ጥያቄ አንድ፡ የሀገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታና የቀውሱን ስረ-ምንጭ እንዴት ያዩታል ?

Ethiopia-Politics -Amhara

ወርቅነህ ጌትነት 

እንግዲህ ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት የሀገረ-መንግስትነት ታሪክ ያላት ሀገር ነች። በዚህም የሀገረ-መንግስት ታሪኳ ውስጥ ከ3ሺህ ዘመናት በላይ በዘውዳዊ ሥርዓት የተዳደረች፣ ቀጥሎም ከ1967 -1983 በወታደራዊ ሥርዓት የተመራች እና ከድህረ 1984 እስከ አሁን ደግሞ በብሔር ተኮር የፖለቲካ አውድ ውስጥ የምትገኝ ሀገር ነች። ምንም እንኳን የዚህ የረጅም ዘመናት የታሪክ ባለቤት ብትሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ግን በሀገረ-መንግስቷ አመሠራረት ላይና አሁን እየተከተለችው ባለው የፖለቲካ ሥርዓትና ብሔራዊ ምልክቶቿ ላይ መግባባት የለም። በዚህም ምክናየት ተቃርኖ፣ግጭትና ጦርነት የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት መገለጫ እስኪመስሉ ድረስ በየጊዜው የሚከሰቱ ቀውሶች ሆነውብናል። ስለሆንም ፍትሕና ዘላቂ ሠላም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሠማይ ስር የሚፈለጉ ግን ደግሞ እውን ለማድረግ አስቸጋሪ የሆኑ ኩነቶች ሆነዋል።

ይሄ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የፖለቲካ ኃይሎቻችን የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት ግንባታ ተቃርኖ በተሞላበት መልኩ ከመረዳታቸው የሚመነጭ ነው። በዚህም መሠረት ሶስት አንኳር የፖለቲካ ኃይሎችንና በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስት አመሠራረት ላይ ያላቸውን ተቃርኖ እና የሀይል አመሠላለፍ እንመልከት።

1. የመጀመሪያው አረዳድ፣ ኢትዮጵያ የተመሠረተችውበተስፋፊነትና ጨቋኝነት (Expansion-Oppression) ነው የሚል አረዳድ ነው፡-በዚህኛው የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት አረዳድ ውስጥ ትህነግን(የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር) የመሠሉ የፖለቲካ ኃይሎችን እናገኛለን። በትህነግ ፖለቲካዊ አረዳድ መሠረት የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ “ተስፋፊነት” ተመስርታ ከአማራ ውጭ የሆነውን ማህበረሰብና ባህል እንደጨቆነች አድርገው የሚተርኩት ነው። በዚህም ውስጥ አማርኛ ቋንቋ እና አርንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ሰንደቃላማ እንደመጨቆኛ መሣሪያነት ጥቅም ላይ እንደዋሉ ይተርካሉ። ሆኖም ግን አማርኛ የኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ቋንቋ ሆኖ በድጋሜ የተወሰነው እና ከአርማው በስተቀር የዛሬው አርንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ሰንደቃላማ ብሔራዊ አርማ የተደረው ከትግራይ ማህፀን በወጡት በአፄ ዮሐንስ 4ኛ መሆኑን መናገር አይፈልጉም። ከዚህ ይልቀሰ ከአፄ ዮሐንስ በኃላ ከነገሱት ከአፄ ምኒልክ ጋር አያይዘው መተረክ ይፈልጋሉ። በዚህም የተሳሳተ አተራረካቸው የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ሥርዓት መሪነትን በአንድ በኩል ከአፄ ዮሐንስ 4ኛ  በኋላ፣ አማራ ከእነሱ እጅ ነጥቆ የወሰደባቸው ሲያስመስሉት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያን አጣነው የሚሉትን ለማስመለስ አማራ ላይ ቀሚያደርጉት የተሳሳተ ተረክ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ቀውስ ከትቶታል።

በዚህ የሀገረ-መንግስት አረዳዳቸውም የትህነግን ተስፋፊነትና ጨፍላቂነት እንደ ስህተት አይቆጥሩትም። በተለይም በወልቃይትና ራያ አማራዎች ላይ ያደረሱትን ተስፋፊነትና ጨፍላቂነት እንደ ጥፋት አይቆጥሩትም። ሥለሆነም ይሄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሌላ ቀውስ የሚጨምር ሁነት ሆኗል።

2. ሁለተኛው የሀገረመንግስት አረዳድ ደግሞ የቅኝ ተገዥነት (Colonial Thesis) አረዳድ ነው።

በዚህኛው አረዳድ ውስጥ ደግሞ ዋልታ-ረገጥ የሆነውን የኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) አረዳድና አስተሳሰብ እናገኛለን። በኦነግ የፖለቲካ እሳቤ መሠረት ኢትዮጵያ “ከ150 ዓመት የዘለለ ታሪክ የሌላት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቅኝ ገዥነት” የተመሠረተች አድርጎ የሚተርክ ነው። ሆኖም ግን ይሄን የተሳሳተ ተረክ ሲያቀርቡ በኦሮሞ ባህላዊ አስተዳደር በገዳ ወታደራዊ ሥርዓት የኦሮሞ መስፋፋት ጊዜ ነባሯን ኢትዮጵያ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው እንዴት እንዳፈራረሷትና እንዳወደሟት ማውራት አይፈልጉም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን ብቻ ተጎጅ አድርገው ያቀርባሉ።

የሆነው ሆኖ ግን ታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች እነ ዶናልድ ሌቪን፣ ሌዊስ ክራፕፍ፣  አባ ባህርይ እና የራሳቸው የኦሮሞ ተወላጆች ይልማ ደሬሳ እና ፕ/ር መሐመድ ሀሰን በጻፉት መሠረት ከ1520 እስከ 1840ዎቹ ድረስ በገዳ ሥርዓት የተመራው የኦሮሞ መስፋፋት ከደቡባዊ ኢትዮጵያ ቦረና ተነስቶ የሀገራችንን ምዕራብ፣ ማዕከላዊና ምስራቅ ክፍል እንዳትለቀለቋት መናገር አይፈልጉም።  በዚህ የተሳሳተና የነጥሎ ተጠቂነት አረዳዳቸውም ኢትዮጵያን በራሳቸው መልክ ብቻ መገንባት (Making Oromuma Core and others periphery) ይሄ ካልሆነ ግን ተገንጥሎ ሀገር መሆንን የፖለቲካ ፕሮግራማቸው አድርገውታል።

3. ሶስተኛው የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሀገረመንግስት አረዳድ ደግሞ የፈራረሰችዋን የኢትዮጵያ ሀገረመንግስት መልሶ የመገንባት (Reunification or re-establishment of Ethiopia) አረዳድ ነው።

በዚህኛው አረዳድ ውስጥ የኢትዮጵያዊ ሀገርተኝነት (Civic-nationalism) አቀንቃኞችን ነው የምናገኛው። የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሀገረ-መንገስት ግንባታ አረዳድም በዚህኛው ስር የሚመደብ ነው። የአንብሮው (The source of the thesis) ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገረ-ግዛት በሶስት ምክናየቶች ፈራርሶ ነበር። ሥለሆነም በኋላ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እስከ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የነበሩ ነገሥታት ያደረገት በተለዩ ምክንያቶች የፈረሰውን የኢትዮጵያ ሀገረ-ግዛት እንደገና በሀገረ-መንግስትነት መገንባት ነው የሚል ነው። 

ከነዚህ የኢትዮጵያን ሀገረ-ግዛት ያፈረሱ ሁነቶች  ውስጥ ዋነኛው በገዳ ወታደራዊ አደረጃጀት የተመራው የኦሮሞ መስፋፋት ነው። በታሪክ ጸሐፍት እንደተሰነደው ከ1522 ከገዳ ሜልባህ ጀምሮ እስከ አፄ ቴዎድሮስ መምጣት ድረስ በተደረገው የኦሮሞ ገዳ ወረራ የኢትዮጵያ ሀገረ-ግዛት እየፈራረሰ ከ22 ብሔርሰቦች በላይ በሞጋሳ ሥርዓት (Assimilating of Non-Oromos) እንዲወርሙ ወይም እንዲዋጡ ተደርገዋል። በዚህ የሞጋሳ ሥርዓት ከወረሙ (Assimilate) ከተደረጉ ህዝቦች መካከልም አማራ፣ሀድያ፣ዛይ፣ዋጅራት፣ክስታኔ፣ጉራጌና ሌሎችም ይገኙበታል። በዚህም ምክንያት ከገዳ ወረራው በኃላ የተዋጡ ብሔርሰቦች ይኖሩበት የነበረው ቦታ ወደ ኦሮሞ የጎሳ ስያሜዎች ተቀይሯል። ስለሆነም ይሄ የፈረሰውን የኢትዮጵያ ሀገረ-ግዛት መልሶ የመገንባት ሂደት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በኦሮሞ ገዳ ወታደራዊ ወረራ የፈራረሰችውን ኢትዮጵያ የመገንባት ሂደት እንጅ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ሆኑ ሌሎች ነገሥታቶች በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ ተስፋፊነትንም ሆነ ቅኝ ግዛትን አላማ አድርገው አልጫኑም የሚል ነው።

ጥያቄ  ሁለት፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ኃይሎችን አሰላላፍ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ አንፃር እንዴት ያዩታል?

እንግዲህ የኢትዮጵያን የፓለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ካየነው በዚህ ከላይ ባየናቸው “የተስፋፊ-ጨቋኝነት”፣ ቅኝ ተገዥነት እና የፈራረሰውን የኢትዮጵያ ሀገረ-ግዛት መለሶ በመገንባት አረዳድ ላይ ተመስርተው የወደ-ፊቷን የኢትዮጵያ ሁኔታ በየፖለቲካ ፖሮግራማቸው የሚስሉ ናቸው። የተጨቋኝነት አረዳድ ያላቸው እንደ ትህነግ አይነት የፖለቲካ ኃይሎች አማራውን እንደ ተስፋፊና ጨቋኝ በመቁጠር በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ሥርዓት ለማንበር አማራው “ማህበራዊ እረፍት” ማግኜት የለበትም የሚሉ ናቸው። ኢትዮጵያን እና ነገሥታቶቿን እንደ ቅኝ ገዥ የሚቆጥሩት የኦነግና ኦነጋዊ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ “ነፃ ወጥተው” የራሳቸውን ሀገር ለመመሥረት የሚኳትኑ ናቸው። ይሄን ለማስፈፀምም ህዝባቸውን ከአማራ ጋር ያተሳሰሩትን ድንበር ተሻጋራ ማንነቶች መበጠስና በአካባቢያቸው የሚኖሩ አማራዎችንና ኢትዮጵያዊ እሳቤ ያለቸው የእነሱ ሰዎችችን ጭምር በማፈናቀልና በመግደል የተጠመዱ ናቸው። እንግዲህ አነዚህ ትህነግና ኦነግ የተባሉ ጽንፈኛ ቡድኖች ከእነ እሳቢያቸው እና የተሳሳተ ትርክታቸው ጥምረት ፈጥረው ነው በ1984 ዓም መንግስት በመመሥረትና ትርክታቸውን የኢፌደሪ ህገመንግስት አድርገው በማውጣት አማራው ላይ እስካሁን ድረስ የማያቋርት ቀውስ እያደረሱበት የሚገኙት።

ጥያቄ ሶስት፡ ከነዚህ የትህነግና የኦነጋዊ እሳቤ ካላቸዉ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ አንፃር በአማራ ላይ የተከሰተዉን ቀዉስ እንዴት ያዩታል?

እንግዲህ የኦነግና የትህነግ የትብብር የፖለቲካ አሠላለፍና አሁናዊ የአማራ ህዝብ ቀውስን እንዴት እንደወለደው እንይ፡፡ በ1960ዎቹ  የጀመረው የተጨቋኝነትና ቅኝ ተገዥነት ተረክ አድጎ በ1984 መንግስት መስርቶ በኋላም ትርክትቱን በኢፈዴሪ ህገ-መንግስትነት አዘጋጅቶ ሀገሪቱን መግዛት እና “ተስፋፊና ጨቋኝ” ብሎ የፈረጀውን የአማራ ህዝብ ማፈናቀልና መግደል ተያያዘው።  ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የነፃ አውጪ ነን ባዮች የትህነግና ኦነግ ሚኒፈስቶ ህገመንግስት ሆኖ መሠራቱ ነበር። ይሄ እውነታም የህገመንግስቱ መግቢያ ላይ “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት ለማረም” በማለት አማራው ላይ አደጋ የቀሰረ ኃይለ-ቃል እናገኛለን። በዚህም ቀውስ ምክንያት የአማራ ህዝብ ከዛኔው እስከ ዛሬ ድረስ እየተፈናቀለና እየተገደለም ቢሆን በኢትዮጵያ የፖለተካ ሰማይ ስር አካታች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ እየታገለ ይገኛል።

በተለይም በሐምሌ 2008 ጀምሮ አማራ ባደረገው ህዝባዊ ንቅናቄ  ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን የትርክቱ አውራ የሆነችውን ትህነግን ከማዕከላዊ መንገስት አዲስ አበባ ወደ መቀሌ መሸኜት ችሏል። ከዚያም በውጤቱ የያኔው ኢህአዴግ ከግንባርነት ወጥቶ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባካተተ መልኩ ወደ ብልፅግና ፖርቲነት ተቀየረ። በዚህ ጊዜ አማራ በህዝባዊ ንቅናቄ ያነሳቸው ጥያቄዎች በብልፅግና መሩ መንግስት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ነበረው። ሆኖም ግን ከብልፅግና መሩ መንግስት በነቢብም ሆነ በገቢር ያገኜው መልስ ተቃራነውን ነበር። በዚህም ምክንያት የአማራ ህዝብ ነገው እንዳያጓጓው የተደረገ ህዝብ ሆነ።

የ2010 ለውጡን ተከትሎም በዛኔው የአማራ ክልል ምክርቤት የፌደራሉ ህገመንግስት ይሻሻል ዘንድ ፀደቀ። አማራን ወክሎ በተቃዋሚ ፖርቲነት በተመዘገበው አብን በኩልም የኢፌደሪ ህገ-መንግስት መከለስ እንዳለበት ለጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ቢቀርብም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኩል የተሰጠው ምላሽ ግን “ለአንድ ክልል ብለን ህገመንግስት አናሻሽልም፤” የሚል ነበር።  የ2010ሩ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣ ዘንድ የታገለው የአማራ ህዝብ በኋላም የብልፅግና ፖርቲ ይወለድ ዘንድ ታላቅ አበርክቶ አድርጎ እያለ በምላሹ አማራ እንደ ህዝብ የተረፈው ግን መፈናቀልና መገደል ነው። 

ከድህረ ለውጡ ጀምሮ ከምክትል ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “ከእንግዲህ አማራ አንገቱን አይደፋም፤” እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ኢትዮጵያን የዜጎች ደኅንነት የሰፈነባት ሀገር እናደርጋታለን፤” የሚል ቃል ኪዳን መሠል ንግግር ቢደረግም በዜጎች ላይ በተለም በአማራ ህዝብ ላይ መፈናቀል፣ መገደልና ጦርነት አልተቋረጠም። በዚህም ምክንያት በለውጥ ኃይሉ ቃል ተገብተው የነበሩ ጉዳዬች አምስት ዓመት ሙሉ ቢጠበቁም ከመሳካት ይልቅ ወደ መክሽፍ እያመሩ ይመስላል። 

በዚህም ምክንያት የአማራ ህዝብ ጥያቄ ከአዳራሽ ወጥቶ ወደ ጎዳና ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ቀጥሎም ወደ አርሶ አደሮች የጅራፍ ሰልፍና በመጨረሻም ወደ ጠመንጃ ተኮር ትግል እየተቀየረ መጣ። ስለዚህ ጠቅለል አድርገን ካየነው ከለውጡ በኋላ ከብልፅግና ፖርቲ መሩ መንግስት፣ የአማራ ህዝብ ይጠብቃቸው የነበሩ የህገመንግስት ማሻሻያ፣ የማንነትትና ወሰን ጥያቄ፣  በተዛባ ትርክት ምክንያት ከክልሉ ውጭ የሚኖር አማራን ያገለለ መንግስታዊ አሰራርና የእኩል የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ጥያቄዎች የሚመለሱበት መልኩ ከመመቻቸት ይልቅ የተገላቢጦሹ እየሆነ ነገው አስፈሪ እየሆነ መጣ።

በተለይም የፌደራሉ መንግስት በሚመራው የብልፅግና መንግስትና በትህነግ ተቃርኖ ምክንያት  በተካሄደው ጦርነት አማራ በወቅቱ ከነበሩት 14 ዞኖች 7ቱ ተወረውበት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሶበታል። በውጤቱም የወደመውን መልሶ ለመገንባት 292 ቢሊዬን ብር እንደሚያስፈልግ ተጠንቶ ቢቀርብም በፌደራል መንግስት በኩል የድጎማ በጀት ወጥቶለት መልሶ ከመገንባት ይልቅ ችላ ተባለ። 

ከዚያም ሲያልፍ የትህነግና የፌደራሉ መንግሥት ጦርነት በፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት ቢቋጭም የአማራ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ወልቃይትና ራያ ጥያቄዎች ፖለቲካዊና ህጋዊ መልስ ሣያገኙ ‹የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ፌደራል የፀጥታ ኃይ ይቀየሩ› በሚል የአማራ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ ሳያደርግ የአማራ ልዩ ኋይል ትጥቅ እንዲፈታ ተወሰነበት። ይሄም በእስካሁኑ የብልፅግና መሩ መንግስት የመከዳት ስሜት ውስጥ የገባው የአማራ ህዝብ ይበልጥ ነገው አስፈራው። ከዚያም ሲያልፍ “ጽንፈኛ ኃይሎችን” ትጥቅ ለማስፈታት በሚል በፌደራሉና በክልሉ መንግስት በተደረገ ዘመቻ  የአማራ ክልል ወደ ጦርነት ቀጠናነት እየተቀየረ መጣ።

መንግስት ጽንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች ለመቆጣጠር አማራ ክልል ዘመቻ እያደርግሁ ነው በሚልበት የተለያየ ጊዜ፣ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚደረግ ጉዞ የአማራ ክልል ተጓዦች ተመርጠው ‹ወደ አዲስ አበባ አትገቡም› መባል የተለመደ እየሆነ መጣ። ከዚህም ሲከፋ ተጓዦችም ሆነ ሹፌሮች በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ታጣቂዎች እየታገቱ ሚሊየን ብር ይጠየቃሉ፤ይገደላሉ።  ይሄ ሲሆን ግን የሀገሪቱ የደኅንነት መስሪያ ቤትም ሆነ የፀጥታ ኃይል በባንክ በኩል የአጋቾች የሚላከውን የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ወንጀሉን ማስቆም አልቻለም። ከዚህ በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም በነበረው የግብርና ግብዓት አቅርቦት የአማራ አርሶ አደሮች በቂ ግብዓት ካለማግኜታቸውም ባሻገር በየአካባቢው በሚገኙ የመንግሥት ቢሮዎች ሲጠይቁ “የጅራፍ ማጮህ ፖለቲካ” ተብሎ ስላቅ ደረሰባቸው። 

ሥለሆነም ጠቅለል አድርገን ስናየው ከላይ በተዘረዘሩት አባባሽ ምክንያቶች የአማራ ህዝብ ትግል ከአዳራሽ ስብሰባ ወጥቶ ወደ ጎዳና ላይ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ከዚያም ወደ አርሶ አደርች የጅራፍ ሰልፍ፣ በመጨረሻም ወደ ጠመንጃ ተኮር ህዝባዊ ትግል ተሸጋገረ። 

ጥያቄ አራት፡ ስለዚህ ልዩነትን በጦርንት መፍታት ወይስ በፖለቲካ ድርድር መፈታት ነው ዘላቂነት ያለው? ከዚህ አንፃር የሌሎች ሀገራት ተሞክሮስ ምን ይመስላል?

ጦርነት አውዳሚ ነው፤ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ በአማራ ክልል በተለይ እና በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያሉ ቀውሶችን ለመፍታት ከነ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊዘርላኔድና ህንድ ብዝህ-ባህልንና የህዝባቸውን መሰረታዊ ጥያቄ የመለሱበትን መንገድ መከተል የተሻለ ያደርገዋል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ከጠመንጃ ይልቅ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግርና ድርድርን ቅድሚ በመሥጠቱ የዜጎቻቸውን ጥያቄ መልሠው የተረጋጋ ፖለቲካና ሠላቂ ሠላምን ማስፈን ችለዋል።

ስለሆነም በአማራ ክልልም ሆነ በኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካና ዘላቂ ሰላም እውን ይሆን ዘንድ የመጀመሪያው ኃላፊነት የሚጠበቀው ከመንግስት ነው። ስለዚህ በዚህ የአርሶ አደሮች የሰብል መሠብሠቢያ ወቅት መንግሥት ‹ትጥቅ ለማስፈታት› በሚል ወደ አማራ ክልል የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ በማቆም ከተፋላሚ ኋይሎች ጋር ያለውን  ጉዳዩ  ወደ ውይይትና ምክክር የማምጣት ኃላፊነት አለበት።  በአጠቃላይ መንግሥት የአማራ ህዝብ የጠየቃቸውን መሠረታዊ ጥቄዎች ማለትም የተዛባ ትርክት ክለሳ፣ የህገመንግስት ማሻሻያ፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እና ከክልሉ ውጭ ያሉ አማራዎች የፖለቲካ እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከተመለሱ አሁን የተከሰተው ግጭትና ቀውስ ወደ ተረጋጋ ፖለቲካና ዘላቂ ሠላም ይቀየራል።

አመሰግናለሁ፡፡

ወርቅነህ ገነት

የፖለቲካል ሳይንስና አለም-አቀፍ ጥናት መምህር

Email: wogeyih@gmail.com 

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkenaበነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን በቦርከና የቢዝነስ ዳይሬክተሪ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ ቦርከናን ይደግፉ፡፡
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

2 COMMENTS

  1. ወቅቱን ያገናዘበና የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ከነመፍትሔዎቻቸው ከሥር መሠረቱ ያብራራ ቃለመጠይቅ ነው። እናመሰግናለን 🙏

  2. Great article! I only want to add one suggestion. For a dialogue to succeed PP needs to be obliged to replace its leadership starting from the PM. The same people who created all the mess shouldn’t be part of the solution. May be TPLF also need to replace its leadership too.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here