spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ

የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ

ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ

ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ (ዶ/ር)

አጠቃላይ መግቢያ

ኢትዮጵያ ሀገራችን በአለም ላይ ይገኙ ከነበሩት ቀደምት ስልጣኔዎች ውስጥ አንዷና ዋነኛ ተጠቃሽ እንደነበረች ይታወቃል፣ ሕዝቦቿም ቀጣይነት ያለው የመንግስት ስርአትን የመሰረቱት ከሽህ አመታት በፊት እንደሆነም ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚህ ረገድ የአክሱም ስልጣኔ በቀዳሚነት ይነሳል፣ የአክሱም ስልጣኔ ሲነሳ ደግሞ የአገው፣ የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች የላቀ ሚና ጎልቶ ይነሳል፡፡ ለዚህም ነው ተሻለ ጥበቡ የተባለ ጽሀፊ እነዚህን ሕዝቦች ማለትም አገው፣ አማራና ትግሬን የአክሱም ስልጣኔ ሶስቱ መሰረቶች ሲል የሚጠራቸው።

በዚህም ምክንያት የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ትስስር ከጥንት ጀምሮ እየጠበቀና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተወሳሰበ በመሄድ ሀገር በጋራ ከመመስረትና ከመገንባት አልፎ ከቅርበታቸው የተነሳ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብራቸው ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ ሀገር በመመስረትም ሆነ መንግስትን በማቋቋም ረገድ በሁለቱም ሕዝቦች የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የተቀናቃኝነትና የተፎካካሪነት ሁኔታ የነበረና አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም በአብዛኛው ግን አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደነበም አይዘነጋም፡፡ 

የሀገርን ዳር ድንበር ከወራሪ ሀይላት በመከላከል ረገድም ይሁን የሕዝቦችን ነጻነት አስከብሮ ለማቆየት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የሁለቱም ሕዝቦችና ልሂቃን አሻራ ከፍተኛ መሆኑ የሚጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዛም አልፎ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመልካም ጉርብትና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ማህብራዊ ግንኙነት ፈጥረው አብረው የኖሩና አብረው የሰሩ ሕዝቦች መሆናቸው ሲታሰብም በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል የሻከረ ግንኙነት ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ 

ለምን ቢባል ሁለቱም ሕዝቦች በጋብቻ ተሳስረው ተዋልደው በቀላሉ ላይለያዩ ተዛምደዋል፣ አብዛኛዎቹ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የክርስትና እና የእስልምና ሀይማኖቶች ተከታዮች መሆናቸውም ግንኙነታቸውን ይበልጥ ጠንካራና በቀላሉ እንዳይበላሽ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከዛም ባሻገር ባህላዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነታቸው ከማንም በላይ የጠበቀና በጋራ መጠቃቀምና መከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሲታይ የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ታሪካዊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ 

የቀደመውን ሁኔታ ትተን ባለፉት 40 አመታት በመተጋገዝና መስዋእትነት ታጅቦ የነበረውን ግንኙታቸውን እንኳ ብንመለከት አሁን ላይ የአማራ ሕዝብ መሪ ድርጅት ነኝ የሚለው የአማራ ብልጽግና አውራሽ የሆነው ኢሕዴን/ብአዴን ሲመሰረት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሊያታግል በሚችል መልኩ ተዋቅሮ የነበረ ቢሆንም በዋነኛነት ይንቀሳቀስ የነበረው በዋግ ኽምራ እና በአማራ ሕዝቦች መኖሪ በተለይም በሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ስለነበረ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የትግል አጋርነት እየጠነከረ እንዲሄድ ማድረጉ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ሲመሰረት በትግራይ መሬት ውስጥ ሆኖ የህወሀትንና የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ አግኝቷል። 

ኢሕዴን ከምስረታው ማግስት ጀምሮ ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባም የህወሀት ሁለንተናዊ ድጋፍ አልተለየውም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሒደትም የህወሀትና የኢሕዴን መሪዎች የአስተሳሰብ አንድነት እየፈጠሩ በመምጣታቸው እና የትጥቅ ትግሉንም አቀናጅተው ማስቀጠል እንዳለባቸው እያመኑ ሲመጡ ሁለቱም ድርጅቶች ወደ አንድ መጥተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) መስርተው በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ይመራ የነበረውን የደርግ መንግስት በማስወገድ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ 

የደርግ-ኢሠፓ ስርአት ከተወገደ በኋላም ከእነችግሩም ቢሆን በሀገሪቱ አንጻራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር፣ ህግና ስርኣትን በማስከበርና አንጻራዊ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በማስመዝገብ ረገድም የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ማህበራዊ ልማት እንዲመጣ በማድረግ ረገድም ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳቸው ለሌላኛቸው መድህን እስከመሆን ደርሰው እንደነበር በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ትተን በ1993 ዓ.ም ህወሀት ለሁለት በተሰነጠቀበት ወቅት ሀገሪቱ አስከፊ የሆነ ችግር ውስጥ እንደምትገባ በመገንዘብ የብአዴን አመራር ከተቻለ ህወሀቶች ወደ አንድ እንዲመጡ ካልሆነ ደግሞ የሀሳብ ልዩነታቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በዚሁ አለመግባባት ሳቢያ ሀገር ችግር ውስጥ እንዳትወድቅ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ 

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በወልቃይት-ጠገዴ፣ በጠለምት እና በራያ አካባቢዎች የተነሳው የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በአግባቡ ባለመስተናገዱና ለረዥም ጊዜም ሲጓተት በመቆየቱ ምክንያት የሁለቱም ክልሎች መሪ ድርጅቶች የሆኑት ህወሀትና ብአዴን የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ተጠቅመው ችግሩ ሳይባባስና አሁን ወደ ደረሰበት አስከፊ ደረጃ ሳይደርስ ታሪካዊና ማህበራዊ ትስስርን፣ ባህልና ቋንቋን እንዲሁም የሕዝቦቹን እውነተኛ ፍላጎት መሰረት በማድረግ መፍታት ሲችሉ በቸልተኝነትና የትም አይደርስም በሚል ስሜት ሲጓተት በመቆየቱ ሳቢያ ከሌሎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ጋር ተዳብሎ ለግጭት በር መክፈቱ ይታወቃል፡፡ 

ይህም ሁኔታ በፖለቲካ ድርጅቶቹ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ ሲሄድ በአንዳንድ አክራሪ ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች አማካኝነት በተደረገው አላስፈላጊ ቅስቀሳ ሳቢያ የግንኙነቱ መሻከር ወደ ሕዝቡ እየሰፋ መጥቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለቱ ሕዝቦች በጥርጣሬ አይን እስከመተያየት የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በለውጡ ዋዜማ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማሰናከል ጥረት ሲያደርጉ የተደረሰባቸው እና የወልቃይት-ጠገዴ፣ የጠለምትና የራያን ሕዝብ ጥያቄ ለማዳፈን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ የህወሀት አባላትና ደጋፊዎች ከጎንደር እና ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች አንዲወጡ መደረጉና ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከአዲስ አበባ በደሴ- ወልዲያ አድርጎ ወደ መቀሌ የሚወስደው መንገድ የተዘጋበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 

ይህን ተከትሎ የትግራይ የጸጥታ ሀይሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች በአጠቃላይና የማንነት ጥያቄ ባነሱ ሕዝቦች ላይ በተለይ ይፈጥሩት የነበረው ወከባም አሳሳቢ ሆነ፣  ይህም ሁኔታ በሁለቱ ክልሎች ልሂቃን ብቻ ሳይሆን በሕዝቦቹም መካከል ጥርጣሬን መፍጠር ችሏል፣ ከዛም አልፎ የፌዴራል መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር ተግባር ተግባርን ተከትሎ የአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎች በጦርነቱ መሳተፋቸው በቋፍ ላይ የነበረውን ግንኙነት በእጅጉ አበላሽቶታል፣ ይህን ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ ተገቢም አስፈላጊም ሆኖ ስላገኘሁት ይህን የመነሻ ሀሳብ አቅርቤያለሁ፡፡

የመነሻ ሀሳቡ ዋና ዓላማ 

የአማራና የትግራይን ሕዝቦች ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ወደ ቀደመው ሁኔታ በመመለስ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሕዝብ ለሕዝብ ግኝኙነቱ እንዲሻሻል በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡

የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ወደ ቀደመ ሀኔታው ለመመለስ መሰራት ያለባቸው ተግባራት

በመጀመሪያ የዚህን ተነሳሽነት አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ለሁለቱም ክልል ገዥ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ማስረዳትና አዎንታዊ ምላሻቸውን ማግኘት ያስፈልጋል፣ ከዛም ከሁለቱም ሕዝቦች መካከል ለዚህ ስራ ቀና ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያላቸውን ታዋቂ ሰዎች በመለየት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት መምከርና በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ተግባራት በጋራ መለየት መቻል፡፡ ከዛም በአፋጣኝ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡ 

ይህን ሁኔታ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሀሳቡን የሚደግፉ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የተሳካላቸው እና በሁለቱም ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በአንድ ላይ ተገናኝተው በአላማው አስፈላጊነት ላይ እንዲመክሩ በማድረግ ወደ ቀጣዩ የማግባባት ስራ መሸጋገር አስቀድሞ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመቀጠልም በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርግ ስራ በመስራት በተቀናጀ መልኩ የሚጀመረው የማግባባት ስራ መሰናክል እንዳይገጥመው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡   

በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሊወሰዱ የሚገባቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች

 1. በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በወልቃይት፣ በጠለምትና በራያ አካባቢዎች ከሚገኘው መደበኛ ፖሊስና ሚሊሻ በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ሰላምና ጸጥታ እንዲያስጠብቁ የተወሰነውን ውሳኔ በማክበር መንቀሳቀስ፣ ለዚህም የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ሙሉ ተባባሪ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚደርግ ስራ መስራት፡፡ ከዛም አልፎ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ስሜትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ፡፡
 2. በየትኛውም የአዋሳኝ አካባቢዎች ሁለቱንም ክልሎች የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ክፍት ሆነው አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ማድረግና በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ የፍተሻ ኬላዎች/ጣቢያዎች በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር የሚደረግባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
 3. በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ (የገበያ) እና ባህላዊ ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፣ ቀደም ሲል ተፈጥረው የነበሩትን አለመግባባቶች በየምክንያቱ እያነሱ ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲሻክር ከሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችና ቅስቀሳዎች ለመቆጠብ ጥረት ማድረግ፡፡
 4. ሁለቱንም ሕዝቦች ወይም የህግ አስከባሪና የጸጥታ አካላት ወደ ግጭት ሊወስዱ የሚችሉ ትንኮሳዎችን ማስቆም መቻል፣ ይህም ማለት ሁለቱም ክልሎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀኖቻቸው አማካኝነት የሚደርጉትን የጥላቻ ንግግር፣ ያልተገባ ቅስቀሳና በተግባር ሊገለጹ የሚችሉ የማነሳሳት ስራዎችን በግልጽ በማውገዝ ሕዝቡ እንዳይቀበላቸው ለማድረግ የተቀናጀ ስራ መስራት፡፡
 5. ተራ የስርቆትና የውንብድና ተግባራትን የሚፈጽሙ፣ ዘረፋ የሚያካሂዱና ሌሎችን ደረቅ ወንጀሎችን ፈጽመው ከአንደኛው ክልል ወደ ሌላኛው ክልል ገብተው ለመደበቅ ወይም መጠለያ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በህግ መሰረት ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ በጋራ በመስራት የአዋሳኝ አካባቢዎች የወንጀለኞች መደበቂያ እንዳይሆኑ ማድረግ፣
 6. ህገ ወጥ ንግድን፣ ኮንትሮ ባንድንና ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለማስቆም የሚደረጉ የተናጠል ጥረቶችን በተቀናጀ መልኩ ለማስኬድ የሚያስችል ስምምነት ላይ በመድረስ እነዚህን ህገ ወጥ ድርጊቶች ለመከላከል ይቻል ዘንድ በጋራ ለመንቀሳቀስ ጥረት ማድረግ፣
 7. የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ሀይሎች እንቅስቃሴ፣ ስልጠናም ሆነ የተኩስ ልምምድ የሌላኛውን ክልል ሕዝብና አስተዳደር የማይረብሽ/የማያውክ እንዲሆን የሚያደርጉ እርምጃዎችን መውሰድ፡፡
 8. ከላይ የተጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለማከናወን ይቻል ዘንድ በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የጥምር ኮሚቴዎችን በማቋቋም በአፋጣኝ የተቀናጀ ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይሆንም፡፡ እነዚህም ጥምር ኮሚቴዎች በዋነኛነት በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚቋቋሙ ሆነው ከአካባቢዎቹ የአስተዳደር አካላት፣ ከመደበኛ ፖሊስ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከሴቶች ማህበራት የተውጣቱ እንዲሆኑ ማድረግ፣
 9. ይህንን ተግባርና ሀላፊነት በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ ይቻል ዘንድ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ ስብሰባዎችን እንዲያካሂዱ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በቀጣይነት ማሻሻልና ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንዲመለስ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለምሳሌ በራያ-አዘቦና ራያ አላማጣ፣ በእንዳ መሆኒ (ማይጨው ዙሪያ) እና በራያ-ወፍላ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩትን ወንድም ሕዝቦች፣ በሽራሮና በሰቲት ሁመራ ወረዳዎች መካከል የሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ቅድሚያ ሊስጠው የሚገባው ተግባር ነው፡፡
 10.  የሚቋቋሙት የጥምር ኮሚቴዎች በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከሚሰፍረው የመከላከያ ሰራዊት/ፌዴራል ፖሊስ አመራሮች ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር የአካባቢዎቹ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፣ በማናቸውም ሁኔታ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር በሚፈጠሩ መድረኮች ላይ የመከላከያ/የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች በታዛቢነት እንዲገኙ በማድረግ ሒደቱን እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ 
 11. በመጨረሻም የወልቃይት-ጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ አካባቢ ሕዝብ የራሱን እድል ራሱ እንዲወስን ዕውቅና ከመስጠት ጀምሮ ውጤቱን በጸጋ ለመቀብል ዝግጁ ሆኖ መገኘት መቻል ተገቢ ነው፡፡

በሒደቱ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች 

የፌዴራል መንግስት ህግ ለማስከበር በትግራይ ላይ የወስደውን እርምጃ ተከትሎ የአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ግንባር ቀደም ተባባሪ ሆነው በመቆየታቸውና ቀደም ሲል ጀምሮ የአማራ ማንነት ጥያቄ አንስተው በወቅቱ ምላሽ ሳያገኙ ቆይተው የነበሩትን የወልቃይት-ጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ አካባቢዎችን በቁጥጥራቸው ስር ማዋላቸው በትግራይ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ላይ የፈጠረው ቅሬታ መኖሩ እና የትግራይ የጸጥታ ሀይሎች የአማራ ክልልን በወረሩበት ወቅት በመገናኛ ብዙሀን በመታገዝ ጭምር በአማራ ልሂቃን ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን በማለት መነሳታቸው ብቻ ሳይሆን በወረራው ወቅትም በአማራ ሕዝብና አካባቢዎች ላይ የፈጸሙት ግፍና በደል በቀላሉ እንዳይግባቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።  

ከዛም አልፎ ከራያ፣ ከጠለምትና ከወልቃይት-ጠገዴ ነዋሪዎች የሚነሱ የአማራ ማንነት ጥያቄዎችን በተመለከተም ከሁለቱም ወገኖች የውይይቱ አጀንዳ አካል እንዳይሆኑ የመፈለግ፣ በተለይም የትግራይ ፖለቲከኞችና ልሂቃን እነዚህ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ካልተመልሱ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ አይደለንም ሊሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከአማራ እና ከትግራይ ሕዝቦች ይህንን የማግባባት ስራ በገለልተኝነት ስሜት ውስጥ ሆነው ለማካሄድ የሚችሉ ጠንካራና ገለልተኛ ሰዎችን ለማግኘትና የሁለቱንም ክልሎች አመራሮችን ይሁንታ ለማረጋገጥ የተወሰነ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ዋናው ችግር ይሆናል፡፡

መወሰድ የሚገባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች

በትግራይ ክልል ላይ የተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ በትግራይ ሀይሎች ላይ ያስከተለው ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ ቢኖርም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል በዚህኛው ስራ ላይ አሉታዊ ጥላ ሊያጠላበት የሚችል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ይህንን እውነታ በመገንዘብ ከፖለቲካው በላይ የሁለቱን ሕዝቦች ሽህ አመታትን ያስቆጠረውን ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ለማሻሻል ሲባል የሚሰራው የማግባባት ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የማስገንዘብ ስራ በመስራት ይሁንታቸውን ፈጥነው እንዲሰጡ የማግባባት ስራዎችን መስራት ይጠይቃል፡፡ 

በእርግጥ ይኸ የማግባባትና የማሳመን ስራ ቀላል ግምት የሚሰጠው ሊሆን አይችልም፣ ሆኖም ይህንን ተጋፍጦ ከማለፍ ውጭ ሌላ ምርጫ ስለማይኖር ገፍቶ በመሄድ ለማሳመን ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በአዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በወልቃይት-ጠገዴ፣ በጠለምትና በራያ አካባቢ ሕዝቦች አማካኝነት የሚነሱ የአማራ ማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸው በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መነሻ መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምና መልካም ግንነኙነት ሊፈጠር የሚችለውም የእነዚህን አካባቢ ሕዝቦች ወቅታዊ ችግር መረዳት ሲቻልና ለጥያቄያቸውም ህጋዊ በሆነ መልኩ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥ መሆኑም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ 

በአጠቃላይም ይህንን ዐብይ ጉዳይ በሀላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት ይዘው የሚንቀሳቀሱ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ከሁለቱም ሕዝቦች ልሂቃንና ፖለቲከኞች መካከል ፈልጎ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም እነዚህን ሰዎች በአዲስ አበባና አካባቢዋም ሆነ በክልሎቹ ውስጥ ከሚኖሩ ገለልተኛ ወገኖች መካከል ፈልጎ በማግኘት የጉዳዩን አስፈላጊነት በማስረዳት ማሰማስራት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡    

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን በቦርከና የቢዝነስ ዳይሬክተሪ ላይ ለማውጣት
እዚህ ይጫኑ፡፡ ቦርከናን ይደግፉ፡፡

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

3 COMMENTS

 1. It’s a good move for peace between people
  Corrections ,
  1, you can’t call it Hgi maskeber if it is why do the Amhara forces leave then?
  2,Amhara region was created by the constitution it should divide in to 4 regions, then wollo ,gonder asking border disputes with Tigray.
  3, you never say a single word about the displaced people from the regions very sad .
  4,you mentioned the Amhara people suffering by TDF but you didn’t mention the Tigray suffering by Amhara fano
  4,does the Amhara government answer the Agew, kimant questions?
  5, raya and welkait can recognize as Amhara but it can be under Tigray Administration like Agew and kimant,
  If you are not asking for land easiy and simple
  6,First Amhara doesn’t accept the constitution can’t claim land at all
  7, Oromo has a claim about finfine do you accept it?

 2. መቼም ይኸንን የብልጽግና ካድሬ የሚሰማም ይኖራል? ደሞ ተሰው ፊት ሲቀርብ ትንሽ አያፍር፡፡ አብይን ወክሎ አዲሳ አበባ ለአጨብጫቢ ፓርላማነት ተወዳድሮም አልሆነለትም፡፡

 3. It is not our urgent problem. Our urgent problem is to get rid of the Abiy regime. The Tigrean people must be able to solve their own problems.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here