spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ሥላሴ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት በጎንደር...

ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ሥላሴ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት በጎንደር ድል እራት ላይ ህዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም በለንደን ከተማ ያደረጉት ንግግር

ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ሥላሴ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት በጎንደር ድል እራት ላይ ንግግር ሲያደርጉ

ውድ እንግዶች፤

ቅርብ የሆነ ፍቅር ስላለን ውድ ወንድሞቸ ብዬ ልጥራችሁ፤ እግዚአብሔርም ይህን ይወደዋል፡፡ ዛሬ እዚህ የተሰበሰብነው ስለነጻነት ባለን የጋራ ጽኑ እምነትና ለኢትዮጵያና ለነጻነቷም ባለን የሃሳብ አንድነትና ፍቅር ነው፡፡ 

ታላቋ ብሪታኒያንና ከእሷ ጋር በጋራ ልማት ትስርስር ውስጥ ያሉትን ሀገሮችም እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ታላቁን ንጉሠነገሥት፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን፤ አያቴን፤ የአገራቸውን የኢትዮጵያን ነጻነት ከጣልያን እጅ እንዲያገኙ በመታገል እረድተዋቸዋልና፡፡ ይህም ድል፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አለም ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ይህ የ82ተኛው አመት የጎንደር ድል በዓል ጨፍጫፊና በዳይ ለነበሩት የአክሲስ ሃይሎች የመጀመሪያውን ሽንፈታቸውን ያበሰረ ስለሆነ ነው፡፡ ደግሞም፤ ጣልያን በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ወረራ፤ የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ያስጀመረ መሆኑን እናስታውስ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በ1932 ዓ.ም የአለም ሃይሎች እርዳታ ማድረግ እስኪጀምሩልንና በ1934 ዓ.ም ደግሞ ተባብረውን ድል እስክናመጣ ድረስ በጣልያን እጅ ከባድ ግፍና ፍጅት ደርሶብናል፡፡

የአለም ህዝብ የኢትዮጵያን በጣልያን እጅ መሰቃዬት ባልተገነዘበባቸው አመታት ውስጥ፤ አያቴን፤ አጼ ኃይለሥላሴን በጣም ሀዘን ላይ ጥሏቸው ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ የጎንደር ድል የተገኘው፤ ጃፓን ፕርል ሀርበርን በጦር አውሮፕላኖች በደበደበች ከሁለት ሳምንታት በኋላ በመሆኑ፤ ያንን አስከፊ ሀዘን ላንዳፍታ እንኳን ያህል እንድንረሳና እንድንጽናና እረድቶናል፡፡ ግርማዊነታቸውም ከድል በኋላ ኢትዮጵያ ተመልሰው፤ በሀገራቸው ውስጥ የዲሞክራሲ አሰራር እንዲጀመር በማሰብ፤ በህዝብ የሚመረጥ ፓርላማ እንዲቋቋም አደረጉ፡፡ እንደ ታላቋ ብሪታንያም ያለ የህጋዊ ዘውድ አስተዳደር ለማምጣት በማሰብ ላይ ነበሩ፡፡

ይህ አያቴ የጀመሩት የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሙከራ ገና ሳይጠነክርና በ1965 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ህገመንግስት እያዘጋጁ በነበሩበት ወቅት፤ ደርግ በአቋራጭ ስልጣን ይዞ የአያቴን አላማም ሆነ ህይወታቸውን ቀጨው፡፡ የአያቴን ብዙ ቤተሰብም አስሮ አሰቃዬ፡፡ ገደለም፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያንም ተጨፈጨፉ፡፡ 

በዚህ ቀን ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ ለተሰዉ የኢትዮጵያ አርበኞችና ከታላቋ ብሪታኒያ፤ ከኬንያና ከአውስትራሊያ ለሀገራችን ነጻነት ሲዋጉ ለተገደሉ፤ ስማቸውም ባልተጻፉባቸው የመቃብር ጉድጓዶች ውስጥ በዘላለማዊ እረፍት ላይ ለሚገኙ ለእኒያ የውጭ ዜጎች ጥልቅ ሀዘናችንን እንገልጻለን፡፡ ግን አሁን እኛ ኢትዮጵያኖች በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን? የሚያሳዝነው ነገር፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከደርግ ግዜ ጀምሮ፤ማለትም ካለፉት 50 አመታት ገደማ ጀምሮ፤ ከደርግም በኋላ በመጡት የኮሙኒስትና የአምባገነን መሪዎች፤ ሀገሪቱ በመታመስ ላይ ትገኛለች፡፡ ጃንሆይ ያቀዱትም የዲሞክራሲያዊ አሰራር ተስፋ ጠፍቶ፤ በሀገሪቱ ውስጥ አንድነት መንምኖ እናያለን፡፡

ይህ የ82ተኛው የጎንደር ድል በዓል ለምንድነው ትልቅ ነገር ነው የምንለው? በዚህ ሳምንት፤ እድሜ ለጃንሆይ ለንጉሥ ቻርለስ ሶስተኛ ይሁንና፤ ለአዲሱም የንግሥና ግዜአቸው የአምላክ እረደኤት እንዲጨመርበት እዬጸለይን፤ ለኢትዮጵያ ነጻነት ለወደቁት መታሰቢያ እንዲሆን፤ ከብረት የተቀረጸ የጎንደር ድል ቅርስ አዘጋጅተን በዊንድሶር ቤተመንግሥት ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ ተገኝተን አበርክተናል፡፡ ይህ መቸም አብይ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የታላቋን ብሪታኒያ ዘላለማዊ ወንድማማችነት የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ፤ ሁለቱም ሀገሮች በቀይባህር ዳርቻና በስዊዝ ካናል አካባቢ ያላቸውን የጋራ ጥቅምና ሃላፊነት መወጣት የሚችሉበትን መንገድ የሚያበሰር ነው፡፡

በዚህ ሳምንት አያቴ በግዞታቸው ግዜ ይኖሩበት የነበረውን ቤት፤ ፌየርፊልድ ሀውስ፤ በባዝስ ከተማ መጎብኘቴ፤ ያኔ አያቴ ምን ያህል ሀገራቸውን ከጠላት ነጻ ለማውጣት ሲያስቡና ሲያሰላስሉ የነበሩት በዚህ ቦታና አካባቢ በመኖር እንደሆነ ወደኋላ ተመልሸ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ዛሬ ደግሞ የ ለንደን ከተማ ነጻነት ን የክብር ሽልማት የአምላክ ፈቃድ ሆኖ በመቀበሌ ደስታዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በታሪክ አንጻር ሲያዩ ቀላሎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የታላቋ ብሪታኒያንና የኢትዮጵያን ክብርና መቀራረብ የሚያበስሩ፤ በሁለቱ ሀገሮች ያለውንም ታሪካዊ የዘውድ ቅርስ እንዲሁም ወንድማማችነት በሰፊው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ 

አሁን የምናገረው በትዝታ ላይ ብቻ ተመርኩዠ ሳይሆን፤ ዛሬ ከምንግዜውም በላይ፤ በተለይም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ካሳለፍነው ግዜ በበለጠ፤ ሁለቱ ሀገሮች፤ የበጎ ሀሳብ አንድነትና የህዝቦቻቸውን ክብር የሚያስከብሩበትን መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው በሚገባ ስለምገነዘብ ነው፡፡ 

እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት በጦርነትና በትርምስምስ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ትርምስምስና የሰላም እጦት፤ አያቴ ከዙፋናቸው በሃይል ተወግደው ከተገደሉ በኋላ የጀመረና ያላቋረጠ ነው፡፡ ያሁኑ ጦርነት ከዚህ በፊት ካሳለፍናቸው ሁሉ በጣም የከፋና የላቀ ነው፡፡ 

በመላው አለም ውስጥ ከሚካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ በሰው ሞትና ቁስለት ቁጥር የሚበልጠው በዩክሪዬን ወይም በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አንድና ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ ከ1.6 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ፤ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ወይም ንብረታቸው በጦርነት ምክንያት ወድሟል፡፡ ስለሆነም በዩክሪዬንም ሆነ በእስራኤል በሚካሄዱት ጦርነቶች ስለሚሞቱት ሰዎች የምናዘነውና ስለህይዎት ትርጉም የምንተክዘው፤ በሀገራችን ውስጥ እጅግ በከፋ ሁኔታ ስለሚገደሉት ሰዎች በሚገባ ከማወቅና ከመገንዘብ አኳያ ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት ለነጻነታቸው፤ ለህይዎታቸውና ለማንነታቸው እዬተዋደቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት በዚህ የቀውጥ ግዜ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብና በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ጫና እዬተደረገበት ላለው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስትያን የሞራልና የሀሳብ ድጋፍ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የአሁኑ ጦርነት፤ በተባበሩት የአለም መንግስታት የህግ ትርጉም መሰረት “የዘር ማጥፋት” ጦርነት መባል የሚቻል ቢሆንም፤ የኢንተርኔት መስመር በመንግስት እንዲቋረጥ ተደርጎ፤ ጦርነቱን የምእራባዊያን ሀገሮች የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች እንዳይቀርጹትና የአለም ህዝቦችም ፍጅቱን እንዳይገነዘቡት እዬተደረገ ነው፡፡ እናንተ እዚህ የተገኛችሁት ሁሉ ይህን የተደበቀ ጦርነት እንድትገነዘቡትና በተቻላችሁም ሁሉ እንድትረዱን እጠይቃችኋለሁ፡፡

በመጨረሻም በዛሬው ምሽት እዚህ መገኘታችሁ፤ ለልዕልት ሳባና ለእኔ ወደር የሌለው ድጋፍ ነው፡፡ ይህንንም እራት እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ዝግጅት የዘውዱ ምክርቤት የሚያደርገውን ጥረት ሁሉ ለህዝብ የሚያሳውቅበትና የገንዘብም ድጋፍ የሚያገኝበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ 

በድጋሜ ለሁላችሁም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡ 

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን በቦርከና የቢዝነስ ዳይሬክተሪ ላይ ለማውጣት 
እዚህ ይጫኑ፡፡ ቦርከናን ይደግፉ፡፡

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here