spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትደራሲ እና እውነት  (በምትኩ አዲሱ )

ደራሲ እና እውነት  (በምትኩ አዲሱ )

ምትኩ አዲሱ 

የደራሲ ተቀዳሚ ጥሪ ለእውነት መመስከር ነው፤ ለእውነት ለመመስከር፣ በውስጠኛ አሳቡ እውነተኛ መሆን  ይኖርበታል። ለራሱ እውነተኛ ሳይሆን ለሌላው እውነተኛ ልሁን ቢል ግብዝ ነው። ደራሲ ከእውነት ወዲያ  ሕይወት፣ ወገን፣ አገር የለውም። የሚበልጥበት፣ መወደድና መደነቅ ሳይሆን፣ ጭለማን መግለጥ፣ ብርሃን  መፈንጠቅ ነው። 

ጥሩ ደራሲ፣ ጥልቅ አንባቢ ነው፤ ተመራማሪ ነው፤ አዝናኝ አስተማሪም ነው። የደራሲ ምግባሩ፣ የኖሩ  አስተሳሰቦችን በአዲስ መልክ በመጠረዝ የአመለካከት ለውጥ ማቀዳጀት ነው፤ ስብእናን ማበልጸግ፣ የአብሮነትን ብልኃት መጠቆም ነው።  

ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ብዙ መፃሕፍት ታትመዋል። በቴክኖሎጂ እገዛ የተለያዩ ጽሑፎች ተነብበዋል።  ከገባንበት ማኅበራዊ ማጥ ፈቅ ሊያደርጉን ሊያወጡን ግን አልቻሉም። የጸሐፍት ቋንቋና ዘዬ እርስ በርስ እንጂ  ከብዙሓኑ ሕዝብ መረዳት እጅጉን ተራርቋል። ይኸ፣ ጥያቄ ሊፈጥርብን ይገባል።  

ደራሲ፣ መሪም ነው። የአገር እና የሕዝብ መሪ ነው፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። ከአውሮጳ፦ ጆይስ፣ ፑሽኪን፣  ሼክስፒር እና ገርተ። ከላቲን አሜሪካ፦ ቦርኤስ፣ ፓዝ እና ማርኬዝ። ከአፍሪካ፦ ‘ንጉጊ (በ “ቅኝ ገዥ”  ቋንቋ ከማሰብ ይልቅ በስዋሂሊ ማለቱ)፣ አቼቤ (በ “ቅኝ ገዥ” ቋንቋ ቅኝ ግዛትና ዘረኛነትን መዋጋቱ)፣ እና ጸጋዬ ገብረ መድህን (በእንግሊዝኛ ጀምሮ ወደ ዲቃላ አገር-በቀሉ ፊደል መዞሩ)። ከመካከለኛው ምሥራቅ፦ ግብጻዊው ማህፉዝ (በፈረንሳይ መነፅር የዐረቡን መቃኘቱ)፤ ዓሊ ኤስበር (አዶኒስ)፣ ቅኝ ገዥውን በገዛ ልሳኑ  ዐረባዊ ማድረጉ፤ እና ዳርዊሽ (ስደተኛ በቋንቋው ስብእናውን ማስከበሩ)። ከእስያ፦ ራቢንድራናት ተጎር  (የጥንት ህንድኛ ስነ ጽሑፍና ፍልስፍናን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ማጎናጸፉ)፤ወዘተ። እነዚህ ሁሉ፣ ቋንቋና  ባህላቸውን በማዳበር፤ ለዓለም ኅብረተ ሰብ እና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ አበርክተዋል።  

ከአንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ትውልድ በኋላ፣ የስንቶች የዘመኑ ጸሐፍት ሥራዎች በሕዝብ ዘንድ ይታወሱ ይሆን?  አንድ ነገር አንርሳ፣ ከእውነት ጋር ያልተጣመሩ ሁሉ፣ ወቅቱ ሲፈራርቅባቸው እንደ ቅጠል ይረግፋሉ! ዝና  እና ትርፍ ያስቀደሙ ሁሉ፣ ወደ መረሣት ያዘግማሉ። የሀዲስ “ፍቅር እስከ መቃብር” ከ 1958 ዓም ጀምሮ  እየተነበበ ነው (ዩቱብን ሳይጨምር፣ በ1996 ዓም 9ኝኛው ህትመት ላይ ደርሷል)። የበአሉ ግርማ “ከአድማስ  ባሻገር”፤ የስብሃት ገብረ እግዚአብሔር “ያዲሳባ ተረቶች”። የጸጋዬ ቅኔዎችና ቴአትሮች (“ወንድ ብቻውን 

ነው እሚያለቅስ፣” “ሀሁ ፐፑ” ወዘተ፣) እስከ ዛሬ አልነጠፉም፤ እንባና ሳቅ በሕይወት እስካሉ ይቀጥላሉ።  የመቀጠላቸው ምሥጢሩ ምንድነው? ምሥጢሩ፣ ከእውነት ከፍትኅ እና ከሰብዓዊነት ጋር ስለ ተቆራኙ ነው።

≈∞≈ 

ደራሲ፣ በውስጠኛ አሳቡ ለእውነት ያደረ መሆን አለበት ብለናል። ተስፋዬ ገብረአብን እንደ ምሳሌ እናንሳ።  ተስፋዬ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ደራሲያን ጋር ራሴን አልደምርም ከማለቱ ሌላ፣ በአወዛጋቢነቱ ይታወቃል  (ኢትዮፎረም፣ የካቲት 19/2001 ዓም፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ጁላይ 19/2019)። ውዝግብ ማስነሳት በራሱ  ስህተት ባይሆንም፤ ለማወዛገብ ብሎ ማወዛገብ ግን፣ ብርሃን ከመፈንጠቅና በልማድ የተቀበልናቸውን ከመጠየቅ  ይልቅ ወደ ኋላ ይመልሰናል፤ እድገታችንን ያጨናግፋል። 

ተስፋዬ ጥሩ ተመራማሪ ነው? ከ “የስደተኛው ማስታወሻ” (2006 ዓም፣ ም.33 እና 34))፣ “ፍቅር በለጠ”  እና “ህሊና እንደ አምላክ”ን ስገመግም እንደ ገለጽኩት (Ethiopianchurch dot org, Books &  Reviews፣ 2014/2006 ዓም)፣ ተስፋዬ ከሚፈልጋቸው መረጃዎች ውጭ ለምንጩ እና ለዐውዱ ታማኝ  እንዳልሆነ ጠቅሼ ነበር። ለምሳሌ፦ 1/ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው ብሎ የጠቀሰው ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ  የለም (ገጽ 355)። ከዊሊያም ኪንግ (ገጽ 360)፣ ከሶመርሴት ሞም (ገጽ 362)፣ እና ከዶስቶዬቪስኪ (ገጽ  364) ሲዋስ፣ ትርጒማቸውን ለይምሰል ቀያይሮ ምንጩን ሠውሮ ነው፤ 2/ የዐይነ ስውሩ አዝማሪ የገቢሳ  ሙለታ የኦሮምኛ ዘፈን የአማርኛ ትርጕም (ገጽ 182) ተስፋዬን አፋን ኦሮሞ እንደማያውቅ ገልጦበታል፤ 3/  ቢሾፍቱ ተወልዶ አፋን ኦሮሞ ሳይማር ማደጉ ለኦሮሞ ሕዝብና ባህል ፍቅርና አክብሮት ነበረው ለማለት  ያዳግታል። የሚወድ፣ የወዳጁን ቋንቋ ይማረዋል! የትግራይ፣ የኤርትራ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ የኦሮሞ  ወጣት አማርኛ እንዳይማር፣ አማራን በጨቋኝነት ፈርጀው ቋንቋውን እንዳስጠሉት እናስታውስ! አማርኛ ብቻ  ትግርኛ ብቻ ተናጋሪዎች፣ በአንፃሩ፣ ኦሮምኛ ቢማሩ፣ የተሻለ መግባባትና መከባበር አይገኝም ማለት የቋንቋን  ኃይል አለመገንዘብ ነው። 

ይቀጥላል … 

© 2022 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን በቦርከና የቢዝነስ ዳይሬክተሪ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here