spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትደራሲ እና እውነት  - ክፍል 2 (ምትኩ አዲሱ)  

ደራሲ እና እውነት  – ክፍል 2 (ምትኩ አዲሱ)  

ደራሲ እና እውነት

ምትኩ አዲሱ

(December 7, 2023  ከታተመው የቀጠለ)

በቀደመው ክፍል፣ ተስፋዬ ገብረአብ ጥሩ ተመራማሪ ነው? የሚል ጥያቄ አንስቼ፤ አንባቢዬ፣ Ethiopianchurch dot org, Books & Reviews ላይ “ስደተኛው እና አምላኩ”ን እንዲመለከት ጠቁሜ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ፣ የዚህኛው ጽሑፍ ረቂቅ የተጠናቀቀው ተስፋዬ በሞተበት ወቅት ስለ ነበረ፣ ሟቹን እና ኀዘን የደረሰባቸውን ለማክበር ሳይታተም ቆይቷል። ሰሞኑን፣ “የአደአው ጥቊር አፈር” መጽሐፍ መታተም፣ ዳግመኛ በተስፋዬ ዙሪያ ግብግብውይይት አስነስቷል። ግብግቡ እንደ ተለመደው፣ ወደ ብርሃን ሳይሆን ወደ ወገንተኛነትና ስሜታዊ መቆራቆስ በማዘንበሉ፣ ምናልባት አማራጭ ቢሆነን ይህን ጽሑፍ አቅርቤአለሁ። ቀጥሎ በምሠነዝራቸው አሳቦች ላይ ወንድማችን ተስፋዬ አፃፋውን መመለስ እንደማይችል በመገንዘብ፣ ትኲረቴን በፃፋቸውና በተናገራቸው መረጃዎች ላይ ብቻ አድርጌአለሁ።

ተስፋዬ፣ በደል ስለ ደረሰባቸው ሁሉ ሳይሆን፣ ለይቶ ለኦሮሞ ሕዝብ መቆርቆሩ፤ ከ “ቡርቃ ትዝታ” በኋላ “ገዳ” ገብረአብ መባሉ፣ ቀብሩ የተወለደበት አደአ ሳይሆን ኤርትራ መደረጉ፣ ከመነሻው ልቡና ጒልበቱ ለሻብያ/ኤርትራዊነቱ መነበሩን ይጠቊማል፤ 4/ የአኖሌን ሐውልት በተመለከተ፦ ተስፋዬ፣ በልምድ እና በእውቀት የሚቀድሙት ብዙዎች እያሉ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ኃላፊ መደረጉ፣ የሰሞኑን ፕሮፓጋንዳ ለማራመድ ዓይነተኛ እድል ፈጥሮለታል። የአኖሌ ሐውልት ተከላ፣ በህወሓት አደራጅነት፣ የክልል ፓርቲ ፖለቲከኞች ውሳኔ መሆኑን ብዙዎች ዘግበዋል። ድርጊቱ እንደ ማንኛውም የአገራችን ፖለቲካ፣ በአካባቢው ሕዝብ ላይ የተጫነ እንጂ የሕዝብን ፈቃድ ያካተተ አልነበረም። ስለ ክልል፣ ስለ ቋንቋ፣ ስለ ትምህርት፣ ወዘተ፣ የተላለፉት ውሳኔዎች፣ ከውጤታቸው እንዳየነው፣ አሣር ዱብ ዕዳዎች ነበሩ። ተስፋዬ፣ ከወቅቱ ፖለቲከኞች ባልተናነሰ ተጠያቂ ነው። 

ተስፋዬ፣ እውነትን የሚፈልገው፣ ለሚፈልገው ጉዳይ ድጋፍ እንዲሆነው ነው፦ “የጋዜጠኛ ፖለቲከኛ ነው። የጋዜጠኛ ፖለቲከኛ ድርጊቱን ሳያዛባ ዘግቦ ዳኝነቱን ለአንባቢ እንደ መተው ዘገባውን ጨምሮበትና ቀንሶለት የራሱን አሳብ ማስፈጸም ይሻል። ከአሳቡ ጋር የማይስማማውን አይታገስም፣ ይወርፋል” ብዬ ከላይ በጠቆምኩት ሥፍራ ላይ ጠቅሼ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ከኢሳት እስከ ኢቢሲ እስከ ዘሐበሻ እስከ ርዕዮት እስከ “ኢትዮዎች” … እንደ ጒድ የፈላው የኢንተርኔት “ጋዜጠኛ” የሚያስቀድመው፣ በመረጃ በእውቀት በመልካም ስነ ምግባር የተደገፈ ሚዛናዊነትን፣ እውነትን፣ ሳይሆን፣ ስድብ ማሠማመርን፣ በ “ሰበር ዜና” 

ሽፋን እውነትን ማስካድን፣ ቅልጥ ያለ አንጃ ፖለቲካና የሽብር ንግድን ነው። 

ተስፋዬ፣ በደርግ ዘመን፣ “ሶሻሊስት ካድሬ” መነበሩ፣ በህወሓት/ሻብያ ዘመን ወደ ዘር ፖለቲካ አራማጅነት መዛወሩ ለምን ይሆን? ተብሎ ሲጠየቅ (“ላይፍ” መጽሔት፣ 2006 ዓም)፦ “ስለ ዘር መነጋገር ወቅቱ ያመጣው አጀንዳ ነው” ማለቱን ጠቅሼ ነበር። የእውነት ሚዛኑ፣ ወቅቱ ያመጣው ርእዮተ ዓለም (ዘውድ፣ መደብ፣ ብሄር፣ ዛሬ ደግሞ ብልጽግና) ነው ማለቱ ይመስላል። ተስፋዬ፣ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተሰኙ ተከታታይ ቅጽ መጽሐፎችን በ 1991 ዓም ያሳተመው ህወሓትን ለማግነን መሆኑን አንዘነጋም።

ተስፋዬ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደል ለማጉላት ምንሊክን በዋነኛነት ጠቅሷል። ምንሊክ እንከን የለሽ መሪ አልነበረም። ተስፋዬ፣ ምንሊክን በኦሮሞ ላይ በደረሰ በደል ሲወነጅል፣ ምንሊክ በአማራ፣ በወላይታ፣ ወዘተ፣ ላይ የፈፀመውን ጭከና አሳንሶና ዘንግቶት እንመለከታለን። “ዘመናዊ” በተሰኘ ታሪካችን ከቴዎድሮስ እስከ ዮሐንስ እስከ ተክለሃይማኖት እስከ ምንሊክ እስከ ኢያሱ እስከ ዘውዲቱ እስከ ኃይለሥላሴ እስከ መንግሥቱ እስከ መለስ እስከ ዐቢይ ጭከና ያልታየበት አንድም የታሪክ ቊራጭ የለንም! ምንሊክ ጭከናን በሞኖፖል የያዘ አስመስሎታል። ይባስ፣ “ንጉሥ” ምን ማለት እንደ ሆነ የተረሳው/የተረሳን ይመስላል። በአንፃሩ፣ የቀድሞውን በደል የሚክዱ፣ የሚያሠማምሩና እንደ ነበረ እንዲቀጥል የሚሹ መኖራቸው፣ ዘመናዊ ትምህርት እና ሃይማኖተ አበው ሊያጠራው ያልቻለ የባህላችንን ጭለማ ጎን ይጠቁመናል። ለምንሊክ ጎጃሜ ሆንክ ጎንደሬ፣ ኦሮሞ ሆንክ ትግሬ ሥልጣኑን ከተቀናቀንክ አይታገሥህም፤ ከተባበርከው ይሾምሃል። ቴዎድሮስም፣ ዮሐንስም፣ ኃይለሥላሴም፣ መንግሥቱም፣ መለስም፣ ዐቢይም፣ ትረምፕም፣ ፑቲንም በዚህ ልዩነት የላቸውም።  

ተስፋዬ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የጀርመን፣ የሩስያ፣ የቱርክ መሪዎች በገዛ ወገናቸው እና በሌላው ላይ የፈፀሙት ዘግናኝ በደል የታሰበው አይመስልም። ፍትህን በዘር አቅልሟት ተሠውራበታለች። በእውነት እውነትን ከሚያገናዝብ ደራሲ፣ በጥልቀት ከሚያነብ ተመራማሪ ይኸ ዓይነት ሚዛን ማጣት አይጠበቅም። ነገሮች ሁሌ ከርቀት እንደሚታዩት አይደሉም፤ ሲቀረቡ፣ ውስብስብ ናቸው። ጨርሶ ጭለማ የሆነ መሪ እና ጨርሶ ብርሃን የሆነ ተመሪ የትም የለም!

ተስፋዬ “ያመንኩበትን እጽፋለሁ …ጥሪዬን እከተላለሁ” ማለቱ፣ ሌሎች ትዝብቶችን ያጭራል። ተስፋዬ የደራሲነት ጥሪ የለውም ለማለት የሚደፍር የለም። መፃሕፍት መፃፍ፣ ብቻ የሚያስቀር ተግባር ነውና፣ ጥሪ ያላቸውም እንኳ እስካልተጉ አይፀኑም። ተስፋዬ፣ ለንባብ ያበቃቸው መጽሐፍት ስለ ጥሪው ህያው ምስክር ናቸው። የፃፋቸው ያመንኩበትን ነው ብሏልና፣ ኋላ እንደምጠቅሰው፣ እምነቱ ለእውነት የተገዛ እምነት ነበር ለማለት ግን ያዳግታል። በመጀመሪያ፣ ስሙን ያገነኑ መፃሕፍት ታትመው የተሠራጩት የወቅቱን የዘር ፖለቲካ ትኲሳት ተከትለው ነው። ቴዲ አፍሮ፣ “ቀነኒሳ አንበሳ” ሲል፣ መለስ “ሸባብ ሰላም” ሲሉ፣ ዐቢይ “ኢትዮጵያን ወደ ጥንት ታላቅነቷ እንመልሳታለን” ሲሉ፣ እንደ ተስፋዬ የወቅቱን የስሜት ማእበል በነፃ መጋለባቸው ነው። ትኲሳቱ ሲበርድ፣ ሥራውም አብሮ መቀዛቀዙ አልቀረም። ይልቊን ተስፋዬ፣ የሥርዓቱ ተጠቃሚና አራማጅ እንደ ነበር አንርሳ። ቢቢሲ አማርኛ፣ (ሜይ 17/2019)፦ ሥራዎችህን የማይወድዱ አንባቢዎች ምክንያታቸው ምንድነው? ብሎ ለጠየቀው፣ የተስፋዬ ምላሽ፣ ወደ ተነሳሁበት ጒዳይ መሸጋገሪያ ይሆነኛል። የተስፋዬ ምላሽ፦ 

“በአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ያልተለመዱ ገፀባህርያት [በመጽሐፌ] ውስጥ አሉ። በአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የተለመደው ጫላ ወይንም ጫልቱ የሚል ስም ለቤት ሠራተኛና ለዘበኛ ሲሰጥ ነው፤ ኦሮሞ ስም ያለው ዋና [ዐቢይ] ገፀባህሪ ሆኖ አያውቅም። ከመነሻው በዚህ የተከፉ ሰዎች አሉ። የደነገጡ ሰዎች አሉ። የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የሆኑ ልብወለዶችን ሰብስበህ ተመልከታቸው። ከፊያሜታ በስተቀር [የበዓሉ ግርማ ኦሮማይ ረዥም ልብወለድ ገፀባህሪ] በጠቅላላ አማራ ናቸው። ወይንም የአማርኛ ስም ያላቸው ናቸው። ይህ ነው የተለመደው። ፀሐፊው ከኦሮሞም ይሁን ከትግራይም ይሁን በተለምዶ የአማርኛ ስም ነው ለገፀባህርያቱ የሚሰጠው። ይህ የእኔ አጀማማር ወጣ ያለ ስለ ነበር ከመነሻው ሰዎች እንዳልወደዱት አይቻለሁ፤” የሚል ነበር።

ተስፋዬ እውነት የኦሮሞን ሕዝብ በገፀባህርያት ደረጃ ከዘበኛነት ወደ ዋነኛነት አሻግሯል? “ጫልቱ እንደ ሄለን” ን እንመለከታለን (የስደተኛው ማስታወሻ፣ ም. 7፣ ገጽ 66-100)። ለመሆኑ፣ ወላጅ ስም የሚያወጣው በምን ምክንያት ነው? የዛሬ ትውልድ (ውጭ የፈሰሰውን ጨምሮ)፣ ስሙን “ሄኒ” “ቤኒ” “ጆኒ” “ጄሪ” የሚለው ለምንድነው? ከባሌ እስከ አዲሳባ፣ ከሞያሌ እስከ ጎንደር በፌስቡክ የምናነብባቸው ስሞች ስለ ስም አወጣጥ ምን ይነግሩናል? 

“ገዳ” የተሰኘው ኤርትራዊው ተስፋዬ፣ በአማርኛ በፃፈው መጽሐፍ ውስጥ፣ ሄለን የተሰኘችዋ ጫልቱ፣ ከተማ ገብታ እንመለከታለን። አዲሳባ የመጣችው፣ ባላገር ያጣችውን አማራጭ ፍለጋ ነው። የወደደችውን ሰው በፈለገችው ሰዓት ለማግባት አለመቻሏ፤ የትምህርት እና የሥራ እድል ማጣቷ፤ ባህሏ ስላደረሰባት ጭቆና እና አዲሳባ ታላቅ እህት ስላላት ጭምር ነው። ይኸ የጫልቱ ብቻ ሳይሆን የጒራጌ፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ሁሉ ታሪክ ነው። 

ከሰባ አምስት ዓመት በፊት፣ ሌላኛዋ ጫልቱ (ጫልቱ ግፋወሰን) ስሟን መቀየር ሳያሻት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ሠንዳፋ ጨርሳ፣ አዲሳባ እቴጌ መነን እና አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ተከታትላለች። ከውጭ አገር ተመልሳ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሆነች። ቀጥላ ዶክትሬቷን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ተቀብላ እዚያው እስከ እለተ ሞቷ (1987 ዓም) በተመራማሪነት ስትሠራ ቆየች። የኢትዮጵያ የኖረ ችግር ዘር ሳይሆን፣ የአገር መሪዎች ዜጋን አማራጭ መንሳትና ብርሃን ያልገባው ባህል እንደ ሆነ እንመለከታለን። የትምህርትና የሥራ እድል በተስፋፋ መጠን ተገድዶ ጋብቻና፣ በገዛ ቋንቋ፣ ኃይማኖትና ባህል ማፈር እየቀረ መጥቷል። በአንፃሩ፣ የ66ቱ ሶሻሊስት አብዮት ካስገኛቸው “ድሎች” መሓል በባህልና በቋንቋ አለማፈር ዋነኛው ነው። ተስፋዬ በጫልቱ አሳብቦ ያነሳቸው ጉዳዮች፣ ከላይ እንዳመለከትኩት፣ ለ ብሶት ፖለቲካ እንዲያመቹ አስቦበት ነው።

ኦሮሞን ከዘበኛነት ወደ ዋነኛ ገፀባህርይ ያሻገረው እውን ተስፋዬ ነው? በ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ከገፀባህርያቱ ዋነኞቹ ሰብለ ወንጌል እና በዛብህ፣ ፊታውራሪ መሸሻ ናቸው። በፊታውራሪ እና በአካባቢው ኗሪ ላይ ትልቅ ተጽእኖ የነበራቸው ደግሞ፣ መነኲሴው አባ ተክለ ሃይማኖት የጒድሩ ኦሮሞ ናቸው። አባ፣ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆን አልነበረባቸውም? የኦርቶዶክስ እምነት መነሻው አይሁድ ነው፤ አገራችን የገባው፣ ከቢዛንቲን ቱርክ፣ በሶርያ በእስክንድሪያ ግብፅ አድርጎ ነው። ተስፋዬ፣ ጭራሽ የአማራ ኃይማኖት አድርጎታል! ለጫልቱ እሬቻን መድቦላታል! እሬቻ እንደ ዮጋ እንደ ሌሎች ባህላዊ ተፈጥሮአዊ በዓሎችና እምነቶች ኦሮሞ ህንድ ጃፓን ካልሆንክ አይልም። የፈለገ ይሳታፋል፣ ያልፈለገ አይሳተፍም። አባ ተክለ ሃይማኖት፣ በምንኲስና ሳይሆን በኦሮሞ ስማቸው መጠራት ነበረባቸው? ተስፋዬ በፃፋቸው መጽሐፍት ውስጥ ዋነኛ ገፀባህርያቱን ለምን ትግራዋይ ሳያደርጋቸው ቀረ? ለምን በትግርኛ አልፃፈም? ለሚዛናዊነት ሲባል፣ እነዚህ ተጓዳኝ ጥያቄዎች አብረው መታየት ይኖርባቸዋል።

በአስተዳደርና በስም አጠራር በደል አልደረሰም አልልም። የሚዘገንን ብዙ ጭካኔ፣ ብዙ በደል ተፈጽሟል። በደልን በእውቀት ብርሃንና ከዘመኑ አስተሳሰብ አኳያ እንጂ በበደል ማካካስ ወደ ኋላ ከሚጎትትና ዛሬን ከሚያባክን በቀር ፋይዳ የለውም። ፋይዳ የለውም ማለት፣ ታሪክ ይረሳ ማለት አይደለም! ስህተትን ላለመድገም ግን፣ ከነመራራነቱ ታሪክን አበክሮ ከማወቅ ውጭ አማራጭ የለም! 

ከተማ ገብቶ የከተማ ስም መያዝ፣ አካባቢ ቀይሮ፣ ተቀባይነት ለማግኘት ከአካባቢው ጋር መዋሃድ፣ የሰዎች ሁሉ ራስን የማኖሪያ ስልት ነው። ዐረብ አገር ሲሄዱ እስላም ስም፤ አሜሪካ የፈረንጅ ስም፤ አዲሳባ የሚያዋጣውን ስምና ባህርይ መላበስ በኦሮሞ ብቻ ላይ የተከሰተ ነው መባሉ፣ በዘመኑ ከነበረው፣ ዛሬም ካለው እውነታ ይልቅ የተስፋዬን ያልጠራ አሳብ ይገልጠዋል። ከላይ እንደ ጠቆምኩት፣ ተስፋዬ እንዳቀለለው ሳይሆን ነገሩ የተወሳሰበ ነው። ኢትዮጵያ የቅልቅል ሕዝብና ባህል አገር ነች፤ ንጹሕ አማራ፣ ንጹሕ ኦሮሞ፣ ትግራዋይ፣ ወላይታ፤ ንጹሕ ጀርመን፣ ዐረብ፣ ወዘተ፣ ብሎ የለም። ንጹሕ ኦሮሞ አማራ ትግራዋይ ቢኖር ኖሮ፣ ህወሓት የጎሳ ፌዴራሊዝምን ባካለለበት በሳምንቱ አገራችን በፈራረሰች ነበር! 

ተስፋዬ ተቻኲሎ ስለ ራሱ መስካሪ ባይሆን ይሻለው ነበር፤ እንዲህ ይለናል፦ “የኦሮሞ ወጣቶች በቄሮ ቃሬ አማካኝነት ተነሥተው ሀገሩን ሲያጥለቀልቊት የቡርቃ ወንዝ ከተደበቀበት ወጣ ብዬ እንደ ተሳካለት ሰው ራሴን ቆጥሬያለሁ። የኦሮሞ ወጣቶችም እኔን እንደ ሰሙኝ መጽሐፌን እንዳነበቡ ማወቄ የበለጠ ሞራል ሰጥቶኛል” ይለናል (ቢቢሲ አማርኛ 2019)። ተስፋዬ ጨርሶ አስተዋጽዖ አልኖረውም ባልልም፣ ነገሩ ግን እርሱ ካሰበው በላይ ውስብስብ ነው። ለቄሮ አነሳስ አንደኛው ምክንያት፣ የህወሓት ጒልበተኛ ፖሊሲ ነው። ህወሓት ያፈቀደውን አድርጎ፣ በፖሊስ ኃይል/በኮማንድ ፖስት ተቃውሞን ማስቆም እንደሚችል ስለ መሰለው ነው። በኦሮሞ ክልሎች፣ አማርኛ ቋንቋ ከአማራ “ቅኝ” ነፃ ከመውጣት ጋር በመያያዙ፣ አብዛኛው ቄሮ የተስፋዬን ቀርቶ የትምህርት ቤት መጻሕፍቱን እንዳያነብብ፣ በፌዴራል መንግሥት ሥራ እንዳይይዝ ታግቶ ነበር። ማንበብ ከሚችሉ አማርኛ ተናጋሪዎችም እንኳ፣ ገዝተው ለማንበብ የማይችሉት ይበዛሉ። ሌላኛው ምክንያት፣ በሥልጣን ትግሉ ውስጥ ይሆኑኛል ብሎ ያሠለፋቸው ኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ ህወሓትን ስለ ከዱት ነው። ከሌሎችም ክልሎች ወጣቱ እንዳመፀ አንርሳ!

የተስፋዬ መጽሐፍት የወቅቱን ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባታቸው፣ እንደሚያደንቃቸው እንደ በአሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን እና ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ሥራዎች፣ ሥራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ እንደማይሆኑ መረሳት የለበትም! “የቡርቃ ዝምታ” የታተመው ከሃያ ሦስት ዓመት በፊት የዘር ፖለቲካ በተጋጋለበት ወቅት በ1992 ዓም ነው። የተስፋዬን መጽሐፍ ያደመቀለት፣ በቅድሚያ በዘርና በቋንቋ መሠረት ላይ የታነፀው ገዥው ፓርቲ፣ ፊደል የቆጠረውና ታሪኩን አጥርቶ ያላወቀው፣ ግራ የተጋባው ከተሜው ነው። ከተሜው ሁሌም ብቻውን ብዙሓኑን እንደሚወክል ያስባል! ከመለስ ዜናዊ ጒብዝና አንደኛው፣ ከተሜው ስለ ራሱ ያለው አስተሳሰብ ፋይዳ ቢስ፣ በቀላሉ መታረም እንደሚችል ማወቃቸውና፣ ይልቅ ገጠሬው እንዳይነሳባቸው በመሬት ሥሪት፣ በመስሎ አዳሪ፣ በአፈ-ሙዝና በጆንያ ማዳበሪያ ቀፍድደው መያዝ መቻላቸው፣ በየአምስት ዓመቱ ለይስሙላ ምርጫ ማብቃታቸው ነው። 

ኮሜድያን እሸቱ መለሰ፣ ቅርብ ጊዜ በአንድ ዝግጅቱ ላይ ከአዲሳባ ወጣ ብላ ወደምትገኝ ገጠር ከተማ ተጒዞ፣ ደህና ኑሮ ከሚኖር ከአንድ ገበሬ ጋር ይጨዋወት ነበር። ያዲሳባ “ታዋቂዎች”ን ፎቶ ለገበሬው እያሳየው፣ ይኸ ማነው? ይኸስ? ይኸስ? ይለዋል። ስድስት ሚሊዮን ከተሜ የተለቀቀበትን ፌስቡክ፣ ፌስቡክ ምንድነው? ይለዋል። ገበሬው፣ የተጠቀሱትን “ታዋቂዎች” ማወቅ ቊምነገር መደረጉ አስገርሞት፣ ሳቅ እያለ፣ አንዳቸውንም ለይቶ እንደማያውቃቸው ይነግረዋል። በሌላ አነጋገር፦ ራሳችንን እና ሌሎችን የምናይበት ዐይን እንከን አያጣውም ብሎ ማሰብ ትሕትና ነው። ሳይንቁ፣ ሌሎችን እና አመለካከታቸውን ማስተናገድ ብርሃንን ማስተናገድ ነው። ስብእናችን እውነትን በመጠማታችን ይለመልማል።   

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  
እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ 
@zborkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here