spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትየንሰሀ ጥሪ፤ እንዴት በሶስት ትውልድ እልቂቱ ይብቃ?  ሰኞ ጥዋት ከደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ...

የንሰሀ ጥሪ፤ እንዴት በሶስት ትውልድ እልቂቱ ይብቃ?  ሰኞ ጥዋት ከደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ጋር

ያሬድ ኃይለመስቀል

Yaredhm.yhm@gmail.com 

ህዳር 10 ቀን 2016 ዓመተ ምህረት የልጆቻችን ኢትዮጵያ ወንድሜ ከፍአልኝ ኃይሉ ቀጠሮ አስይዞልኝ እኔ ያሬድ ኃይለመስቀል ደጃዝማች ወልደሰማዕትን ለማግኘትና ለመማር ወደ ቤታቸው ሄድኩኝ።  ደጃዝማች ወልደሰማያት በጣም የማደንቃቸው ትልቅ የኢትዮጵያ ቤተ መጽሐፍ ናቸው።

ምናልባትም እግዚአብሔር ረጅም እድሜ የሰጣቸው ስለ ኢትዮጵያ፤ ስለ ንጉሳቸው እና ኢትዮጵያን በደማቸው ስላቆዮ አርበኞች እውነቱን እንዲመሰክሩ መሰለኝ።  ለዓመታት ተተርኮ የማይልልቅ እውነትና ታሪክ እሳቸው ጋ አለና ረጂም እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው እመኛለሁ።

ይህ ጽሁፍ ከሳቸው የተማርኩትን ታሪክ እኔ በገባኝ መጠን በራሴ ድምጽና ቅላጼ ነው የጻፍኩትና ሀይል ቃልና ስህተት ከተገኘበት የኔው ስህተት መሆኑን ተረዱልኝ።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ህዳር 14 የዛሬ 49 ዓመት ስልሳ አርበኞች በደርግ ወታደሮች የተረሸኑበት ቀን ነው።  ከሁለት ወራትም በኋላም የየካቲት የደም አብዮት 50 ዓመት ይሆነዋል። 

ይሆንን የሀምሳ አመት የጭካኔና  የመጨራረስ ጉዞ እንዴት ማስቆም ይቻላል የሚለውን ለማንሳትና ለመማር ነበር የሄድኩት።

እኔ በአብዮቱ ግዜ ሳድግ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ አስተዳደር “በዝባዥ፡ ጨቋኝ፡ ፊውዳል፡ ደም መጣጭ”  እየተባለ ሲሰደብ እየሰማሁ ነው ያደኩት። 

አድጌ ተምሬና አንብቤ ስረዳ ደም መጣጮቹ እና አቆርቋጆቹ ከዛ በኋላ የመጡት ወታደሮችና ጥራዝ ነጠቅ ምሁራን እንደሆኑ ተረዳሁ። 

እኔ ውሸት እንደሆነ ባውቅም ቁጭ ብዬ ከደጃዝማች ወልደሰማያት ሳዳምጥ ደግሞ መረጃዎችንም አገኘሁ። ሌላውም እንደ እኔ ያስጠኑንን ስድብና ጥላቻ ገለል አድርገን  እውነቱን መፈለግ ከጀመርን መከራችን ሊያበቃ ይችላል ብዬ አምናለሁ። “እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” መጽሐፍ ቅዱስ ይል የለ. 

የደጃዝማች እድሜ እና የአእምሮ ንቃት 

ደጃዝማች በ1917 ዓመተ ምህረት ነው የተወለዱት። በዘጠና ዘጠኝ አመታቸው ላይ ቢሆኑም የዛሬ ሰባ እና ሰማንያ አመታት የሆነውን ነገር፣ ስም፣ ቀን፣ ታሪክ፣ እና ያነበቡትን መጽሐፍ ገጽ ሳይቀር ገለጥ ገለጥ አድርገው መረጃ ያቀርባሉ። 

ለሚያቅርቡት ታሪክ ደግሞ መረጃ ለማሳየት ብድግ ብለው መጽሐፍ ያነሱና ገጹን ገልጥ ገለጥ አድርገው እስቲ ይህንን አንብበው ይላሉ። በዚህ እድሜ እንዲህ ዓይነት የማስታወስና የማንበብ ችሎታ ማግኘት የሚገርም ብቻ ሳይሆን ተአምርም ይመስላል።

ደጃዝማች ወልደሰማያት ቤት ወደ አምስት ተኩል ገደማ ገባን።  ደጃዝማች ወልደሰማያት የዘጠና ዘጠኝ አመት እድሜ አይመስሉም። እንደ ቢሮ የሚጠቀሙበት ክፍል በደርጃ ከፍ ብሎ የተሰራ መግቢያ አለው። ይህንን እንዴት እንደሚወጡ በአእምሮዬ ሳሰላስል ከፍያለው እሳቸው በሩጫ ነው የሚወጡት ብሎኝ ገባን። ስንገባ ስለ እርሻ ጉዳይ የሚያስተምሩዋቸው ሁለት ወጣቶች ነበሩ።  እነሱ ተሰናብተው ሲወጡ አንደኛው ወጣት ስለ ፍራፍሬ እንዲማር ደሞዝ ሊከፍሉት የቀጠሩት መሆኑን ነገሩን። ወደ ዝርዝሩ ባንገባም እሱ ተምሮ ካዛ ይሄንን እንዲያስተም መሰለኝ።

ብዙም ሳንቆይ ወደ ቁምነገሩ ገቡ። አንተ ማነህ? ለምን መጣህ? ምን ፈለክ አላሉኝም። እድሜህ ስንት ነው አሉኝ ነገርኳቸው ወድያው በፈጣን አእምሮዋቸው አብዮቱ ሲፈነዳ ልጅ ነበርክ ማለት ነው አሉኝ።  ይህ ያሉበት ምክንያት ሳሰላስል የተረዳሁት “የዛ የኮሚኒስት ትውልድ” አባል እንዳልሆንኩ ለማረጋገጥ መሆኑ ገባኝ።  ምናልባትም የዛ ትውልድ አባል ብሆን ኖሮ ትምህርቱንም በዛው መጠን ያስተካክሉት ነበር ብዬ ገመትኩ።

ከዛ ጨዋታውን ጀመሩ። ሁለተኛ መጽሐፋቸውን እየጻፉ ነበርና ኮምፒዩተራቸው እንደተከፈት ጭውውቱን በጥያቄ ጀመሩት። 

ለምንድነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገደል፣ ሲታረድ፣ ሲፈናቀልና ሲሳደድ ዝም የሚባለው ብለው ጠየቁን? ትውልዱ እንደቅጠል ሲረግፍ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ እንዴት ጠፋ?  ድሮ ሰው በጩቤ ከተወጋ እንኳን መንደሩም ሀገሩ ይሸበራል። አሁን ግን ሰው እንደ ቅጠል ሲረግፍ ለምን ብሎ እንኳን የሚጠይቅ የለም? ሞት እንደ ተራ ዜና ነው የሚታየው አሉን።

ይህንን ሲሉ ሀሳቤ በርካታ ቦታዎችን ያስስ ነበር። እኔ ራሴ በምካፈልባቸው “የምሁራን ስብስብ” ውስጥ ሳይቀር እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚያነሳ ሰው እንደ ችግር ነው የሚታየው። የሚገድሉት ሳይሆን ስለሚሞቱት ሰዎች የሚቆረቆሩት ናቸው የሚብጠለጠሉት። 

ይህ ባህል እንዴት በዚህ ሀገር መጣ ብለን ከጠየቅን?  የዛሬ 49 ዓመት እራሳቸውን ደርግ ብለው የጠሩት ወታደሮችና ተራማጅ ነን ያሉ “ምሁራን” ያለ ፍርድ 60 አዛውንቶችንና አርበኞችን በጅምላ ረሽኑ።   እነዚህ አዛውንቶችና አርበኞች ብዙዎቹም በጡረታ ላይ የነበሩ እድሜያቸው የገፋና ተኩሰው ሸፍተው ያጠቁናል የሚባሉ አልነበሩም። ከጥቂቱ በስተቀር ጣልያንን የተዋጉና ሀገርን በአርበኝነት ያገለገሉ ነበሩ። ይሁንና በድላችኋል፣ ያላግባብ በልጽጋችኋል ተብለው ሲከሰሱ ስማቸውን ለማጽጻት በፈቃደኝነት እራሳቸውን ወደ እስር ቤት ያስገቡ ነበሩ። በነጻ ፍርድ ቤት ተከራከረው ስማቸውን ለማጽዳት ከተፈረዳባቸውም ቅጣታቸው ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ አዛውንቶች ነበሩ።  

ይሁንና ለፍርድ ሳይቀርቡ በወታደሮቹ የድምጽ ብልጫ ታህሳስ 14 1967 በግፍ ረሸኑዋቸው። ይህንና ይህንን የንጹሀን ደም መፍሰስ ያወገዘ “ተራማጅ” ነኝ የሚል አልታየም። 

እንዲያውም አንድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ተማሪዎች መሀበር አባል የነበረ ዘመዴ ጋር ይሄንን ስናነሳ የዛን ዘመን አብዮተኞች “ለአድኃሪያን ቀብር ለቅሶ እንውጣ ነው ወይ የምትሉት?” ብለው ተሳለቁብን ያለኝ ትዝ አለኝ። 

ይህም ፍትሀዊ ያልሆነ ግድያ “አብዮታዊ እርምጃ” የሚባል ስም ተሰጥቶት ተቀባይነት እንዲያገኝ “ምሁራኑ” ተባበሩ።  እንዲያውም “ቆራጡ መንጌ” የሚል ሹመት ሰጥተው የእድገት በህብረት ዘማቾች በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆነ።

ትልቁ የአብዮተኞች ስህተት በህግ ሳይሆን በአብዮታዊ እርምጃ በአድኃሪያንና ፊውዳል ብለው የሚሰድቧቸውን አባቶቻቸውን ለመደምሰስ ሲስማሙ ነው። የነሱ “ቆራጡ መንጌ” በፊውዳሎች  ላይ ብቻ አፋፍሞ የሚቆም መስሏቸው ነበር። 

ደርግ በጡረተኛ በአርበኞች ላይ አጁን ሲያሟሽ በዚያ የሚቆም የመሰለው ፊደል የቆጠረ ግን አርቆ የማያይ ነበር።

ወድያው ወጣቱን እየሰበሰበ በየቀበሌው በአብዮት ጠባቂዎች “አብዮታዊ እርምጃ” መውሰድን ደርግና መኢሶኖች፣ ኢጫትቶች፣ ወዝሊጎች፣ ሰደዶች እና ማሌሪዶች ፈቀዱ። ይሄንን ወንጀል የተከበረ “ቀይ ሽብር” የሚል የዳቦ ስም አወጡለት። የሩስያኖችንም የቦልሼቪክና ሜንሼቪክ ትርክትና ይህ የማይቀር የታሪክ ሀቅ እንደሆነ ተተነተነ።

ሌሎቹ አምስት የኮሚኒስት ድርጅቶች የመኢሶን መሪዎች በዶ/ር ኃይሌ ፊዳና እንዳርጋቸው አሰግድ: የሰደድ መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ተካ ቱሉና መንግስቱ ገመቹ፣ የማሌሪድ መሪ ዶ/ር ዲማ ነገዎ አሁን የኦነግ መሪ፣ የወዝሊግ መሪ ዶ/ር ሰናይ ልኬ፣ የኢጭአት መሪ ባሮ ቱምሳ “ለአናርኪስቶች” ማለትም ለኢህአፓዎች ፍትህና ፍርድ ቤት አያስፈልግም ብለው ቀይ ሽብርን ደገፉ። እነዚህም ተራማጆች ግድያ በአናርኪስት ላይ የሚቆም መስሏቸው ነበር። ከዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ አንዳርጋቸው አሰግድ እና ኮ/ል መንግስቱ በቀር ለወሬ ነጋሪ የቀረ የለም። ሁሉም የዘሩትን አጨዱ።

ይሁንና ሁሉም ተራማጅ ነኝ ያለው ትውልድ እነ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ያለፍርድ  የመግደል መብት ለደርግ አሳልፎ በመስጠቱ ይህ ግድያ የሀገሪቷ ያልተጻፈ ህገመንግስት ሆነ። እንግሊዞች የተጻፈ ህገመንግስት የላቸውም። ባለፈው በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነ ፍርድ እንደ ህግ ሆኖ ይጠቀሳል። 

ይህ ተራማጁ ለደርግ የሰጠው መብት ለሀምሳ ዓመታት የሀገሪቷ ያልተጻፈ ህገ መንግስት ሆነ። ሀገሪቷንም የደም መሬት አደረጋት። ባለፉት ሀምሳ ዓመት ወስጥ ደም ሳይፈስበት የዋለ ቀን የለም። 

ንሰሀ

ለዚህ ነው ይህ ነገር የት ተጀመረ? እንዴትስ ተጀመረ? እንዴት ይሄንን ያለ ፍርድ የመግደል ባህል እናስቁመው ብለን መጠየቅ ያለብን።  እኛም  ለተሳተፍንባቸው፣ ስላበረታታናቸው ግድያዎች መጸጸትና ንሰሀ መግባት ያለብን። 

ቀጥለው “ድሮ እኮ ሰው ከገደለ ወዲያው ይያዛል ያለበለዚያም ቀድሞ ይሸፍታል” አሉን። አሁን ሰውን ያለ ፍርድ ገሎ የሚኖርበት ሀገር ነው።  ሀብት ንብረት የነበረው ሰው ሁሉ ተፈናቅሎ በየመኪናው ተራ ሲለምን ነው የሚታየው።  ለምን ብሎ የሚጠይቅ በዚህ ትውልድ እንዴት ጠፋ?  

ህዝባቸው እንዲህ ሲሆን መሪዎች ለስልጣናቸውና ለምቾታቸው ብለው ለምን ብለው እንኳን አይጠይቁም። እነሱም አንድ ቀን እኛስ እንደ ቀደሙት ያለ ፍርድ እንሞት ይሆን ብለው አያስቡም። ሰው ያልዘራውን ያጭዳልን??

ይሄ ሁሉ ጭካኔ  ለምን መጣ ብላችሁ ከጠየቃችሁ ይሄንን ሁሉ መዓት ያመጡት የተማርን ነን ያሉ ናቸው።  “የኢህአፓ አንድ ፕሮፌሰር እኔጋ መጥቶ ነበር።  እኔም ምን አልኩት መሰላችሁ? በፖለቲካ ከምታገለግሉት በላይ እናንተ ኢህአፓዎች፣ መኢሶኖችና ደርጎች ተባብራችሁ በሩስያ እንደተደረገው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ብትጠይቁና። “እኛም እግዚአብሔር የለህም ብለን ገዳይም ሟችም ሆነናልና ይቅር በለን” ብትሉ ይህንን ልታስቆሙ ትችላላችሁ። የኢትዮጵያንም ህዝብ ይቅርታ ብትጠይቁ መከራው ያበቃል ይሆናል አልኩት።

እግዚአብሔር በኦሪት ዘጸአት ም20 ቁ 5_6 “እኔ የሚጠሉኝን ሁሉ እቀጣለሁ፣ ዘራቸውን ሁሉ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ እቀጣለሁ። ለሚወዱኝ ትእዛዜን ለሚጠብቁ ሁሉ ግን እስከ ሺ ትውልድ ድረስ ዘላለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ” ይላል። አሁን ንሰሀ ብንገባ በሶስት ትውልድ መከራው ይቆምልን ነበር አሉኝ።  

የሶስት ትውልድ እልቂት

የመጀመሪያው የነ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ትውልድ ተረሸነ፣ ሽማግሌ የተባለ ሁሉ፣ አርበኛ ሁሉ “አድሀሪ፣ በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ ፊውዳል፣ ደም መጣጭ” እየተባለ እየተሰደበ በመላው ኢትዮጵያ በልጆቹ ተገደለ፣ ተዘለፈ፣ ታስሮም እንደ ልጅ ተገረፈ”። 

ከዛ ቀጥሎ የመጣው አብዮታዊ ትውልድ እርስ በርሱና በታጠቁ ወታደሮች በየቦታው ተጨፈጨፈ፣ ተገረፈ፣ ሰቆቃ ተቀበለ። 

በኤርትራ፣ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በባሌ፣ በሀረር፣ በወለጋ እና በየቦታው ጋራና ሽንተረር እርስ በእርሱ እንደ አውሬ እየተዳደነ ተጨራረሰ። 

ደርግም ተብለው ተማምለው የተሰባሰቡት እነ አጥናፉ አባተም ባሰቧሰቧቸው ሀምሳ አለቃዎችና ተራ ወታደሮች ተገደሉ ። የፈረንጅ ትምህርት ተምረው ግድያን ለደርጎቹ ያሰለጠኑትም እነ ዶ/ር ሰናይ ልኬ እና እነ ዶ/ር ሀይሌ ፊዳም ባሰለጠኗቸው ተናካሽ ውሾች ተበሉ። 

ጃንሆይ በሀረር አካዳሚ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በህንድና በእስራኤል ያሰለጠኗቸው ወታደሮች ንጉሰ ነገስታቸውንና አለቆቻቸውን አዋርደው እንደገደሉት ሁሉ እነሱም በራሳቸው ወታደሮች ተገድለው እሬሳቸው ተጎተተ። 

ጃንሆይ ያዋረዱዋቸውን ወታደሮች “እነዚህ ወታደሮች መለዮአቸው መከበሪያቸው ሳይሆን የውርደት ምንጭ ይሁን፣ ቅዳሜ ቢደሰቱ እሁድ መርዷችሁ ይሁን፣  እስራት፣ ሞት ፣ውርደት ስንቃቸው ይሁን…. ሁሉም በወለደው ልጅ ይዋረድ፣ ሰላም ፍቅር ይጥፋ፣ባለስልጣኖቹም የሚተራረዱ የሚጋደሉ ይሁኑ፣ ያለ እውቀት ተናጋሪ ይብዛባት… ” ብለው ሰኔ 16 ቀን 1968 ረግመዋል ብለው  የቅርብ ተንከባካቢያቸው የነበሩት ጽፈዋል። 

ይህ እርግማን ይስራ አይስራ አያከራክርም። ይሁንና የኢትዮጵያ ሰራዊት ህይወት ከተጠቀሰው እርግማን የተለየ አይደለም።

እሳቸው ይርገሙም አይርገሙም እንደዛ የሚኮራበት የነበረው የወታደራዊ ሞያና ኮፍያው ተዋርዶ መሬት ላይ ተነጥፎ መለመኛ ሆኖ ታየ። 

ይህ ኮፍያ በኮርያ እሬሳ እንኳን አላስማርክ ብሎ የጥቁርን ህዝብ ያኮራና የአሜሪካኖቹን ጀነራሎች ያስደመመና ታሪክ እንዲጽፉለት ያስገደደ ሰራዊት ዛሬ በሺዎች እየተማረከ አፈር ለብሶ ጫማውን አውልቆ በዮቲዮብ ሲናዘዝ የሚታይ ሆነ።

ያኔ ማንም ሰው ወታደር አይሆንም ነበር፣ ከየ ትምህርት ቤቱ ቁመናቸው ያማረ፣ አይምሮ ብቃታቸው የተረጋገጠ ወጣቶች እየተመረጡ ነበር ወታደር አካዳሚ የሚገቡት። ልጃገረዶች ሊያገቡዋቸው የሚመኙዋቸው እናት አባት በደስታ መርቀው የሚድሩላቸው የተወደዱ ነበሩ። 

ጃንሆን እየለመኑ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ህንድና እስራኤል እየላኩ አስተምረው ባለ ሞያ ያደጓቸው ነበሩ። ታድያ እነዚህ ወታደሮች አለቆቻቸውንና ያስተማራቸውን ንጉሰ ነገስት አዋርደው፣ ሰድበው ቀብረው እላያቸው ላይ ቁጭ አሉ።  

ንጉስና አርበኛ በመግደል ፋይሉ ተዘግቶ ቢሆን ጥሩ ነበር። እነዚህ ወታደሮችም በራሳቸው ወታደሮች ተገለው እሬሳቸው ተጎተተ። 

ከዛም ቀጥሎ ይሄንን ሰራዊት አዋርደው ለማኝ ያደረጉትም እነሱም ተዋርደው ተረሽነው እሬሳቸው ታየ። እንደ እርግማኑም ሁሉም በልጁ የሚቀጣ ሆነ። ሁሉም እራሱን የመጨረሻ አያደረገ እያሰበ ነው ግፍ የሚፈጽመው። ይሁንና እሱም በልጁ የሚዋረድ ሆነ። አሁንም ይብቃን ስላላልን ይሄው ነው የሚቀጥለው። 

ያሁኑ ትውልድ ደግሞ በብሄር ጣኦት ይዞ እናቶችን፣ ድሆችን፣ ቄሶችና ሼኮቹን በየጎጇቸው እያደነ የሚገድል ሆነ። እርስ በርሱም እየተጫረስ ነው።

አሁን አራተኛውን ትውልድ መግደል ጀመረዋል። ያልተወለዱ ህጻናት ከእናታቸው ማህጸን ሳይቀሩ አውጥተው  መታረድ ተጀምሯል። ባለፈው በግድያ መፍትሄ እናመጣለን ያሉ ባለስልጣኖች ሁሉ በከፈቱት መንገድ ጠፉ። የሚገርመው ለምን ብለው አይጠይቁም። ምክንያቱም ለሁሉም የደነደነ የፈራኦንን ልብ ሰጥቷቸዋልና። እኔስ ልጆቼስ በዚህ መንገድ እጠፋ ይሆን ብሎ የሚጠይቁ ባለስልጣናት አልታዩም።

ታድያ ይህ የአራት ትውልድ ቅጣት በፊታችን እየተከናወነ ለማየት ጋረደብን?  ለምን ሆነ ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ እንዴት ጠፋ?  ምንስ ብናደረግን ነው የኛ መከራ የሚያባራው ብለን መጠየቅ ተሳነን? ምንስ ብናደርግ ነው ይሄንን ማስቆም የምንችለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋልና እባካችሁ ብለን እንጠይቅ

ትላንት እግዚአብሔር የለም ብለን በአዳባባይ ታበይን ፈጣሪን ዘለፍነው። ሀይማኖች “የጭቁን ህዝብ ማደንዘዣ ነው፡ ብለው በዚህች በተቀደሰች ምድር ሰበኩ ምሁራን ያለ ንሰሀ ሳልገቡ ሹልክ ብለው ዛሬ መጽሀፍ ሰባኪ የሆኑና ኑራሯቸውን ያደላደሉ አሉ። በእርግጥ ሰውን እንደማታለን ፈጣሪን ማታለል ይቻላልንና 

ደርግ ጥብቅ ሚስጥር ብሎ ለካድሬዎቹ ባሰራጨው ጽሁፍ ኃይማኖት የጭቁኑ ህዝብ ጠላት ነው ብሎ ክርስትናንና እስልምናን እንዴት ማጥፋት እንዳለበት ለካድሬዎቹ መመሪያ በጽሁፍ በትኖ ነበር። የሚገርመው ነገር ደግሞ የትኞቹ ቤተ እምነቶች ለጭቁኑ ህዝብ ሲባል ወደ ሙዝየምነት መቀየር እንዳለባቸው።  የትኞቹ የግዕዝ መጽሐፎች ደግሞ ተሰብስበው መጥፋት እንዳለባቸው ሁሉ ዝርዝር ጽፎ ነበር። አብዮተኞቹ እግዚአብሔር ያውቁ የነበሩ መሆናቸውንና ውስጥ አዋቂዎች መሆናቸውን ይህ የሚስጥር ትዕዛዝ ያሳያል።

በአጠቃላይ የዛ አብዮተኛ ትውልድ መሪዎች ብዙዎቸ ዳዊት ደግመው ዲያቆን ነበሩ፣ቁራን ቀርተው ፊደል የቆጠሩ ነበር። አንዳንዶቹም በሚሲዮናውያን በወለጋ ፊደል የቆጠሩና መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የሚዞሩ የነበሩ። አባቶቻቸውም የፕሮቴስታንት እምነት ሰባኪዎች የነበሩ ናቸው። 

እንደ አሁኑ ትውልድ ሳያውቁ ስህተት ሰሩ አይባልም።  ታድያ ምን ነካቸው ካልን ከሞስኮ የመጣ ክፉ መንፈስ በራሳቸው ላይ አርፎ እግዚአብሔር የለም ብለው ተሳደቡ፣ ታበዩ፣ እናት አባቶችን፣ ጳጳሳትን አንቀው ገደሉ እነሱም የዘሩትን አጨዱ። ታድያ ይህ ንሰሀ አያስፈልገውምን?

የጸጸትና የንሰሀ አስፈላጊነት 

አዳም የሰራው ጥፋት እኮ “አትብላ” የተባለውን ፍሬ ስለበላ ነው ለ5500 ዓመት የተቀጣው።  እኛ እግዚአብሔር የለም ብለን፣ ተሳድበን ንጉስ ገለን፣ ጳጳስ በሲባጎ አንቀን ገለን። በአረአያ ስላሴ የተፈጠረውን ወጣትና አዛውን ጨርሰን ዛሬ እንኳን ተሳስተን ነበር እንዴት ማለት ተሳነን?  

የፈራኦንን ልብ አደነድነዋለው እንዳለው እኛም ልባችን ደንድኖ ይሆን? እንደ ሩሲያኖች እንኳን እንዴት በሰራነው ስህተት መጸጸት አቃተን? ተማሪዎቹ በአርበኞቹ ግድያ የሚቆም መስሏቸው ነበር። ወታደሮቹ ደግሞ በተማሪዎቹ ግድያ የሚቆም መስላቸው ነበር። ከዛም በኋላ የመጡት አማጽያኖች በወታደሮቹ ሞት የሚቆም መስሏቸው ነበር። 

ይህንን ሳናደርግ ሳንጸጸትና ይቀርታ ሳንጠይቅ መፍትሄ አናገኝም።  በዚህ ሳምንት የዛሬ 49 ዓመት ኢትዮጵያን ከጣልያንና ከእንግሊዝ መንጋጋ ነጻ አውጥተው ባለ ወደብ  ሀገር አድርገው የሰጡንን በጅምላ ያለ ፍርድ ፈጀን። ለዚህ ሀገር የስልጣኔ በር ለመክፈት ትምህርት ቤት ከፍተው ወታደር አሰልጥነው የብርሀን መንገድ ያሳዩትን ንጉሰ ነገስት ገድለው በላያቸው ላይ ቁጭ አሉ። ጳጳሱን በሲባጎ አንቆ አሰቃይቶ መግደል መለማመጃ ያደረገ  ትውልድ መጣ።

ንሰሀ ያስፈልገናል የምለው ኢትዮጵያ ልዩ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ የኃይማኖት ሀገር ናት። እኛ ከሁሉም እንለያለን።  እኛ አሁን ከኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች ማለትም ከግሪክ፣ ከህንድ፣ ከአርመን፣ ከሩስያ ሳይቀር እንለያለን።  እነሱ ከአረማዊነት ነው ወደ ክርስትና የመጡት። አንዳንዶቹም ነብያትን ሳይቀር አንገታቸው እየቆረጡ ነው ክርስትናን የተቀበሉት።  የኛ ክርስትና ግን በሰላም ነው የመጣው።  

እኛ ከአረመኔት ሳይሆን ከኃይማኖት ነው የመጣነው።  እስልምናም እዚህ ሀገር ነው የተፈጠረው።  ለምሳሌ የኛ እስልምና ከክርስትና ነው የመጣው።  ክርስቲያኑ ነው እስላም የሆነው።  ክርስቲያኑ ደግሞ ከኦሪቱን አጣምሮ ነው የተቀየረው። ኦሪቱ ደግሞ ከአብርሀም ከመልከጸዴ ነው የመጣው። ለዚህ ነው ክርስትናም እስልምናም ኦሪትም  ኃይማኖት በዚህ ሀገር ነው የተጀመረ የምለው።  እኛ የካህኑ የመልከጸዴቅ ልጅ ልጆች ነን። እኛ ካህኖች ነበርን። የመልከ ጸዴቅ የልጅ ልጅ የኢትዮጵ ልጆች ነን። ኢትዮጵ ነው ኢትዮጵያ የሆነው። ኢትዮጵያውያን ለኃይማኖታቸው ታማኝ ናቸው። እስልምናውም በሰላም በፍቅር ነው እዚህ የተቀበለነው እንጂ በጦር አይደለም። ለዚህ ነው እኛ ልዩ ነን የምለው አሉኝ። 

ለምሳሌ ቆረሾች (ሳውዲዎች) የነብዩ መሀመድን ተከታዮች ሲያሳድዱ የነብዩ ቤተሰቦች ወደ ሰላም ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ያሉት።  በዛን ዘመን የነበሩት ንጉሥ አጼ አርማሕ ነበሩ። ይመስላኛል ከ576፟ እስክ 620 ድረስ የገዙት።  ቁጥሩን መጽሐፍ ላይ ፈልጌ እነግርሀልሁ።  ይሁንና አጼ አርማሕ በሰላም ተቀብለው አቆይተው እምነቱም በነጻነት እንዲሰበክ አድርገው ከዛም ነብዩ መሀመድ በመጨረሻ ከተረጋጉ በኋላ ለአጼ አርማሕ ደብዳቤ ጽፈው እንደውም የነብዩን ሁለተኛ ሚስት የሆነችውን የአቡሻከርን ልጅ ኢምሐቢባን አጭተው አራት መቶ ወቄት ወርቅ ሸልመው ነው ለነብዩ መሀመድ የላኩት። ለዚህም ነብዩ መሀመድ ይህቺን ሀገር የመረቋት፤ አትንኳት ያሉት።

ኢትዮጵያ ከሌላው ክርስቲያንም እስላምም ይለያል የምለው በፍቅር ስለተጀመረ ነው። ሌሎቹ እኮ ፈጣሪን የተቀበሉት በሰይፍ ያለበለዚያም ነቢያት የክርስቶሰን መልዕክተኞች አንገታቸው ከቆረጡ በኋላ ነው። የክርስቶስ ደቀመዝሙር የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ለሮማውያን የክርስቶስን አዳኝነት ስለሰበከ በ64 ዓመተ ምህረት ላይ በሮማው ንጉስ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ነው የተገደለው።  

ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያዊ በብሉይ ስርአት መሰረት ጃንደረባ እግዚአብሔር ለማምለክ ወደ እየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ነው ክርስቶስን ተቀብሎ ተጠምቆ ክርስቲያን የሆነው። በፍቅር በልብ እንጂ በሰይፍ ወይንም ነቢያት አንገታቸውን እየሰጡ አይደለም ክርስትናም እስልምናም ወደዚህ ሀገር የመጣው።

የመጀመሪያውንም “አላሁ ክበር!” ብሎ እስላምን ለአለም ያወጀው ኢትዮጵያዊው ቢላል ነው።  ነብዩ መሀመድን ያሳደገችው ሞግዚት ኢትዮጵያዊ ናት። ኢትዮጵያ እስላምና ክርስቲያን ተጋብተው አብረው የሚኖሩባት ሀገር ነበረች። ይህም በፍቅር ስለሆነ ነው።  ኢትዮጵያ ከመልከጸዴቅ ጀመሮ እስከ አሁን ድረስ ያለው እምነት ሁሉ ኃይማኖት በሰላም ስለመጣ ነው።  

ለምሳሌ የቅማንት እምነት በአብዛኛው ህዝበ ልቦና ነው፣ ይህ ደግሞ ህግ በሙሴ ከመጻፉ በፊት ከአዳም እስከ ሙሴ ያለ ነው።  ከዛ ሙሴ ነፍስ አጥፍቶ ሲሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ነው የመጣው።  ኦሪት ዘጸአት 2 ፡ 15-22 ጀምሮ ይሄንን ይመሰክራል

15 ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ።……አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ አሉ። ልጆቹንም። እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች። በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። 

እዚህ ላይ ታድያ ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኘው የሚል ጥያቄ ይነሳል። መልሱም ዮቶር የምንለው ኢትዮጵያዊ መሆኑንና የሙሴ ሚስትም ሲፓራ የኛው የኢትዮጵያ ትውልድ መሆንዋን እንዴት አወቃችሁ ብላችሁ ለምትጠይቁ ። መልሱም በመጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምስክረነቱን እናገኛለን።

ኦሪት ዘኍልቍ ምዕራፍ 12 ቁ1 _15

1፡ ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ። ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ። እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ። እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።”

ይህ ሙሴ በኢትዮጵያ እንደኖረ ብቻ ሳይሆን ዘረኝነትን እንደማይወድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ፈጣሪ እንደተገለጸለት መረጃ አለ። ለምሳሌ ኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 6 ያለው እንዲህ ይመሰክራል።

1፣ ሙሴም የዮቶርን የአማቱን የምድያምን ካህን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም። ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ። እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ። ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ።  እርሱም። እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። ደግሞም። እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ።

ይህንን ጥቅስ  በየሐዋርያት ሥራ 7፣33 ተደግሞ ተጽፎም እናገኘዋለን። 

“ጌታም። የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ።”

ይህ ነበር ይህ ተዓምር በኢትዮጵያ መፈጠሩን ከማመለከቱ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ከሙሴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡና እግዚብሔር ፊት ሲቆሙ ፈጣሪ ባለበት ቦታ ሁሉ መሬቷም የተቀደሰች ናትና ሙሴ እንደታዘዘው ጫማቸውን ያወልቃሉ። ይህንን የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚፈጽሙ ሌሎች ቤተክርስቲያን የሉም።  

ከኢትዮጵያውያን የሙሴን ህግ ሁላችንም ስንቀበል አብዛኛው ኦሪት ወይንም እብራውያን/ ጁዳይዝም የሚባለውን እምነት ተከታይ ነበርን። ከዛ ደግሞ ክርስቶስ ሲመጣ ይሁዳዊ የነበረው ቅርሱን፣ ቤተመቅደሱን፣ ታቦቱን፣ እንደ ሙሴ ጫማ ማውለቁን ይዘን ነው ክርስቶስን  የተቀበለነው። ከዛም ወደ እስልምና የተቀየረው እግዚአብሔርን የሚያውቅ እንጂ አረማውያንነት አልነበረውም።  የሌላው አለም ክርስቲያኖች ሁሉ ከአረመኔነት ወይንም በግድ ስለመጡ እኛ ያለን ታቦት፣ ጥምቀት፣ መቅደስ፣ ትውፊት እና ባለ 81 መጽሐፍ ቅዱስ አይደሉም።

ለምን እና እንዴት ኢትዮጵያ ብቻ 81 መጽሐፍ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ አላት? ፕሮቴስታንቱ 66 ካቶሊኩ ደግሞ 72 ሲሆን እኛ ብቻ ነን 81 እንዴት ኖረን ብሎ የሚጠይቅ የለም?  ለምን ብለን እንጠይቃለን? 

ብንጠይቅ የኛ ነገር ብዙ ሚስጥር እንዳለው እንረዳለን። ለምን መጽሐፈ ሄኖክ በኛ ሀገር ብቻ ተገኘ? ሄኖክ እኮ የአዳም 7ተኛ የልጅ ልጅ ነው? እንዴት ይህ ከአዳም 7ኛ ትውልድ የጻፈው መጽሐፍ በኛ ሀገር ብቻ ተገኘ ብለን መጠየቅ አቃተን? ምን ጋረደብን?  ለምን ፈጣሪ ከእስራኤል ነጥቆ ታቦቱን ለኛ ሰጠን?  አጼ ዳዊት ደግሞ አባይን እገድባለሁ ብለው አስፈራርተው ከኦቶማን ግብጽ ግማደ መስቀሉን ለምን ወደዚህ አመጡ?

ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ልዩ ሀገር ነች የምንለው። ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ሀገር ናት የኃይማኖት ሀገር ናት ብለን የምንለው። 

በፈርንጅ ትምህርት የተለከፈው ደግሞ “እግዚአብሔር የለም” ብለው ንጉሱን ገድለው ጳጳሱን አቡነ ቴዌፍሎስ ደግሞ እንጦጦ ባለው  የራስ ካሳ ቤት ወስደው በገመድ አንቆ አሰቃይቶ መግደልን እየተለማመዱ ገደሉዋቸው። አቡነ ቴዎፍሎስ በግፍ ሲገደሉ የ69 አመት ሽማግሌ ነበሩ። አብዮቱም 5 ዓመቱ ሆኖ ተረጋግታል። እንዴት በሀምሌ 1971 ዓመተ ምህረት እንዲህ ዓይነት ግፍ የሚፈጽም ባለጌና ጨካኝ ትውልድ በዚህ ምድር ላይ እንዴት ተፈጠረ? 

ከጳጳሱ ጋር በገመድ አንቆ መግደልን የተለማመዱባቸው 33  ለሀገራቸው ብዙ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።  እነ ጸሐፊ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ወልደኪዳን ናቸው፣ ክቡር ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም፣ ክቡር ደጃዝማች ሐረጎት አባይ  ነበሩ። ከዛም ቦሀላ ተወስደው የተገደሉ እነ ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ የፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ወራዊት ጠቅላይ አዛዥ የነበሩትና በደርግ ነው የተገደሉት። 

የጳጳሱም አጽም በድብቅ ከተቀብሩበት በ1982 ዓመት ወጥቶ ነው ወደ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተዛውሮ በድጋሜ ተቀበሩ።

የመከራው መንሳኤ

ይህንን ሁሉ መከራ በኢትዮጵያ ላይ ያመጡት ተማርን ያሉ ናቸው። ሶስቱ ሥላሴዎች አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስን የሉም ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ በሶስት ኮሚኒስቶች በማርክስ በኤንግልስና በሌኒን እንዲያምን እንዲያመልክ አደረጉ። 

በየአብዮት አደባባይ እየወጣ ከማርክስ ከኤንግልስና ከሌኒን ፎቶ ፊት እየቆመ እነዚህን የማያውቃቸውን የጀርመኖችና ሩሲያን ፈላስፎች ሲመርቅ፣ ፈጣሪንና እምነትን ደግሞ ሲረግም እየዋለ እንዲመለስ ተገደደ።  

በዚህም መንፈስ ንጉሱን፣ ጳጳሱን፣ ቄሱን፣ ሼኩን አዋርደው ፈጣሪን የካደ ትውልድ እንፈጥራለን አሉ። እነሱም መቅሰፍት በሚመስል ጥፋት እርስ በእርሳቸው ተጨራረሱ።

የጳጳስና የንጉሰ ነገስት ግድያ ብቻ ሳይሆን የዛሬ 49 ዓመት ኢትዮጵያን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነጻነት ያቆሙትን ህዳር 14 ቀን 1967 አመት ረሸኑ። 

አሁንም ድረስ ለሰራነው ስህተት ንሰሀ አልገባ ብለን መተላለቁ ቀጥሏል። የተማሩትና በውጪ የኖሩት የፈረንጆቹ መጠቀሚያ ሆነው የደሀውን ልጅ አስፈጁ። 

ለዚህ ነው በህይወት ያሉ የደርግ፣የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የህወሀት፣ ያኦነግ እና የዛ ዘመን ወጣቶች የነበሩትን ሁሉ ለሀምሳ ዓመት እየዘነበ ያለውን መከራ ለማስቆም በሰሩት ይጸጸቱ፣ ለሰሩት ስህተት ንሰሀ ይግቡ የምለው። 

የሶስት ትውልድ ደም በከንቱ ፈሷል አራተኛው ትውልድ በመሀጸንም እያለ እየሞተ ነው። ንሰሀ ብንገባ ግን አሁን ባለው ሶስተኛው ትውልድ በቃ ይለን ይሆናል። 

ይህንን ደግሞ ሁሉንም አሳምነው ሁሉም ንሰሀ እንዲገባ አድርገው እንደ ሩስያ ንሰሀ ብንገባ ፈጣሪ ይቀር ይለናል።  የዛሬ ሶስት ወር የካቲት ሲመጣ የደም ማፍሰሱና የመገዳደሉ አባዜ  የተጀመረበት ሀምሳ ዓመት ይሆነዋል የንሰሀና የይቅርታ ግዜ ማድረግ አለብን።  ይሄንንም መንግስትም የሀይማኖት መሪዎችም የተማረውል እግዚአብሔር የለም ብሎ በጨቅላ አይምሮ የታበየውም ንሰሀ መግባት ያለበት።

ህዳር 14 ለኢትዮጵያ ነጻነት የተዋደቁ እንደነ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ እና እንደ ራስ መስፍን ስለሺ ያሉ የተረሸኑበት 49 ዓመት ሳይታወስ አልፏል።  ንሰሀ ቀርቶ መሞታቸውን አስታውሶ ሻማ ያበራና ያሰበም የለም።

ወደፊት እውነቱን የሚረዳ ትውልድ ሲመጣ ለነዚህ አርበኞች ሀውልት ማቆሙ አይቀርም። ኢትዮጵያ ላይ ጀግናና አርበኛ መፈጠር ካለበት እንደ የካቲት 12 በግፍ የተጨፈጨፉ አርበኞችን እያሰብን በነጻነት ላቆዩን ጀግኖችን በየአመቱ ማሰብና  ሀውልት ማቆም አለብን።
 

ይህንን ሳናደርግና ሳንጸጸት ትውልድም ጀግናም አናወጣም።  እነ አጥናፉ አባተ ድምጽ ቆጥረው አስረሽነው ጀግና የሚሆኑ መስሏቸው ነበር። እነ ሀይሌ ፊዳ እነ ብርሀነ መስቀል ረዳ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ ተጠርተው ወጥተው ከተረሽኑበት እስር ቤት ገብተው ተቀጥቅጠው፣ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸው አለቁ። 

ደርጉን እንኮኮ ብለው ያቆዩ ጀነራሎች ሳይቀሩ በራሳቸው ወታደሮች እየተገደሉ በአዳባባይ እሬሳቸው ተጎተተ። ከዛም በኋላ እግዚአብሔር የለም ብለው ቤተ እምነቱን እነ ዋልድባ ገዳምን ሲያምሱ የነበሩት በየ ጋራው በጥይት ተደብድበው ሞቱ። አሁንም ይህ የሚቆም አይመስልም።

ከዛ በኋላ የመጡት ሁሉ ጀግና እሆናለሁ ታሪክ እተዋለሁ ያሉ ሁሉ የጥይት እራት ነው የሆኑት። የኢህአፓ መሪዎች ከጥቂት ወሬ ነጋሪዎች በቀር በግፍ ነው የተጨረሱት። የመኢሶኖችም እንዲሁ። ደርግን ግድያ ያስጠኑት እነ ሀይሌ ፊዳ እነ ሰናይ ልኬም እንደዚሁ በጥይት ነው ታሪካቸው የተደመደመው። ግድያውን ያካሄዱትና ድምጽ የቆጠሩትም እነ ኮለኔል አጥናፉ አባተም በሰሩት ስህተት ንስሀ መግባት እድል ሳያገኙ በጓዶቻቸው ተገለው የተቀበሩት።

የንጹሀን ደምን ያፈሰሰ ሁሉ ባፈሰሰው ደም ተጠያቂ መሆኑ አይቀርምና አሁን የ50ኛውን ዓመት የግድያ ዘመን ስናስብ ከዚህ አዙሪት መውጫው ንሰሀ ብቻ ነው።  ለዚህ ነው በዛ ዘመን የነበሩና ግድያ የኢትዮጵያ ህዝብ የብልጽግና በር ነው ብለው ያሰቡና ግድያን የሰበኩ ንሰሀ መግባት ያለባቸው።  ብዙዎቹ የአብዮትና የግድያ አቀንቃኞች አሁን በስልሳዎቹ መጨረሻና በሰባዎቹም እድሜ ላይ ያሉ ናቸው።  በዚህ አለም ንሰሀ ካልገቡ በማርክስ፤ በኤንግልስ እና በሌኒን ስም ወደ ገነትና ዘላለማዊ ህይወት አይገቡም።

አሁንም በስልጣን ላይ ያሉት እጣ ፈንታቸው እንደ አጼ ኃይለስላሴ እንደ ደርግ እና እንደ ህወሀት ባለስልጣናት እንዳይሆን የሚዘሩት እንደሚያጭዱ መልካም ዘር መዝራት ያለባቸው። 

ያሬድ ኃይለመስቀል

Yaredhm.yhm@gmail.com 

__በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here