spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትበኢትዮጵያ ከለውጥ ሃይሉ በበለጠ የለውጥ አደናቃፊ እየሆነ ያለው የልሂቃን ያልተገባ መቆራቆስ ነው! 

በኢትዮጵያ ከለውጥ ሃይሉ በበለጠ የለውጥ አደናቃፊ እየሆነ ያለው የልሂቃን ያልተገባ መቆራቆስ ነው! 

From CNN

 አበጋዝ ወንድሙ 

ዶክተር መረራ ጉዲና ብዙ ጊዜ የአማራ ፣ የኦሮሞና የትግራይ ልሂቃን የሚጋጩ ህልሞቻቸውን ተወያይተው ካላስታረቁ መዘዙ ሃገር ሊበትን ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለው ይገልጻል። መረራ ለምን እነዚህን ሶስት የብሄረሰብ ልሂቆች ብቻ እንደመረጠ ሙሉ በሙሉ ባልረዳም ፣ የነዚህ ሶስት ብሄረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ ልሂቆች የርስ በርስ መቆራቆስ ግን፣ ሃገር ሊበትን ወይንም ሊያጠፋ ወደሚችል ጎዳና ሊውስድ እንደሚችል ያለፈው ዓመት በሀገራችን የሚታየው ችግር ግልጽ ያደረገውና እኔም የምቀበለው ነው። 

የአብይ ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ወኔ አግኝቶና ውስጣዊ ትግል አካሂዶ የበላይነትን ለመቀዳጀት የረዳው ፣ ወደ ስልጣን ማማ ከመምጣቱ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ፣በልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች የተካሄዱ፣ ከድምጻችን ይሰማ፣እስከ ኮንሶ፣ኦሮሚያና አማራ ክልል ተደጋፋፊነት ማጎልበት በጀመሩና፣ ኢህአዴግን ከመሰረቱ ባንገዳገዱ ህዝባዊ ትግሎች መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ። 

ይሄም ቢሆን ግን፣የለማ ቡድን ተብሎ የሚታወቀው ስብስብ ፣ይሄንን ህዝባዊ ትግል እንደምርኩዝ ተጠቅሞና ቁርጠኝነትን ተላብሶ፣ በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነቱን ለማግኘት ባይንቀሳቀስና፣ ባያሳካ ኖሮ በሀገራችን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የታየው ለውጥ ዕውን እንደማይሆንም በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  

በአብይ የሚመራው የኢህአዴግ አስተዳደር በሀገራችን እንዲመሰረት ከምንመኘው የዴሞክራሲ ስርዓት አንጻር  ውስንነቶች ቢኖሩትም ግን ፣በወቅቱ የድርጅቱን የበላይነት መቀዳጀቱና እሱንም ተከትሎ የወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች፣ሀገራችንን ከመበታተን አደጋ የታደገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ለሚያስፈልጋት መሰረታዊ ለውጥ ለሚደረገው ረጅም ትግል አመቺ ሁኔታ መፍጠሩም ጭምር ትልቅ ሃገራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል። 

ከዚህ በሀገራችን ከተከሰተው ለየት ካለ የለውጥ ሂደት ማለትም፣በራሱ በኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ የመጣ ለውጥ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ እንግዲህ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አስራ አምስት ወር የተካሄደውና አሁንም በመካሄድ ላይ ያለው የስርዓት ለውጥ ሳይሆን አስተዳደራዊ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል ። 

ይሄ ማለትም አሁን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የህወሃት የበላይነት በኦዴፓ የበላይነት የተተካበትና አንዳንድ መዋቅራዊ መሻሻሎች የሚካሄድበት፣ ህወሃት የበላይ በነበረበት ወቅት ይደፈጠጡ የነበሩ አንዳንድ ህገ መንግሳታዊ መብቶች፣ የኢህአዴግን ድርጅታዊ መዋቅር በመጠቀም ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት የሚደረግበት ወቅት መሆኑን መገንዘብ፣ ያልሆነ ተስፋ ከመሰነቅ ይታደገናል። 

በአብይ የሚመራውና የለማ ቡድን ተብሎ የሚታወቀው ስብስብ ህዝባዊ ትግሉን ተንተርሰው በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት ተቀዳጁ ማለት ግን፣ ህዝባዊውን አጀንዳ የራሳቸው አድርገው ለስኬቱ ይሰራሉ ማለት እንዳልሆነ ፣ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም አሻጋሪዎቻችን’ እነሱ እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ይሄ ስራ የምልዓተ ህዝቡና የኔ ብሎ የሚቀበላቸውና የሚደግፋቸው ድርጅቶች ተግባር መሆኑን መገንዘብ የግድ ነው።  

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ምናልባትም አብይ፣ የለማ ቡድን የሚባለውን ስብስብ በመጠቀም፣ በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ከርክሞ የጠቅላይ ምኒስተሩን ስልጣን ከያዘ በዃላ በተረጋጋ መንገድ እቅዱን እንዳያሳካ እንቅፋት አየሆኑ ያሉት፣ በዋናነት ጽንፍ በያዙ በነዚህ ሶስት የልሂቃን ስብስቦች ቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚያደርሱበት ወከባ ነው ብሎ መደምደምም የሚቻል ይመስለኛል። 

በጥቅሉ እንዲህ ማለት ቢቻልም ግን ሶስቱም የልሂቃን ስብስቦች የፈጠሩዋቸውና አሁንም ድረስ ያሉ ተግዳሮቶች መገለጫቸው የተለያየ ነው።  

ህወሃት እንደ ድርጅትና በውስጡ ያሉ ልሂቃን፣ ባልጠበቁትና ባላሰቡበት ወቅት በኢህአዴግ ውስጥ የነበራቸው የበላይነት በመነጠቁ ፣ በ እውር ድንብር ወደ መቀሌ አፈግፍገው ፣ ያለ የሌለ አቅማቸውን በመጠቀም በጅምር ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲታትሩ ይታያል። በ 27 ዓመት የበላይነት ዘመን በመላ ሀገሪቱ በዘረጉት መረብ የጥቅም ተጋሪዎች የነበሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማንቀሳቀስ ፣አዲሱ የአብይ አስተዳደር በሁለት እግሩ ለመቆም የሚያደርገውን ጥረት ከጅምሩ እስካሁን ለማደናቀፍ እየጣሩ ይገኛሉ።

የአብይን አስተዳደር የሚደግፉ የትግራይ ልሂቃን መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑም ደግሞ የሚታወቅ ነው። በዋናነት ግን አብዛኛው ከህወሃት ድርጅታዊ መዋቅር ውጭ ያለው የትግራይ ልሂቅ፣ ህወሃት በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን የበላይነት በማጣቱና ፣ ከሱም ጋር ተያይዞ የመጡ የህግ ተጠያቂነቶችን ብሄረሰቡ ላይ የሚደረግ የተለየ ጥቃት ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመድረሱ፣ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ለማጠልሸት፣ ብሎም በትግራይ ህዝብ ዘንድ አግኝቶት የነበረውን ድጋፍ ባብዛኛው እንዲያጣ ለማድረግ አሁንም ድረስ ቅስቀሳውን አላቋረጠም ። አንዳንዱ ጭራሽ አቅሉን ስቶ በፌደራል መንግስቱ ደረጃ የፈለግነውንና ይገባናል የምንለውን ሚና ከተነፈግን ትግራይን እናስገነጥላለን እስከማለት የደረሰም አለ ። 

በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ለመከርከም የብአዴንና የኦህዴድ ተደጋጋፊነት ወሳኝ የነበረ ቢሆንም፣ በአመራር ደረጃ የበላይነቱን የተቀዳጀው የኦህዴድ ቡድን በመሆኑ፣ ብአዴን ውስጥ ያሉ መካከለኛና ዝቅተኛ ካድሬዎች የሚመጥነን ስልጣን አላገኘንም ወይንም ተገፋን የሚል ቅሬታ ሊኖር መቻሉ የሚጠበቅ ነው። 

ሆኖም በክልሉ አዲስ በተቀነቀነውና በተደራጀው ብሄርተኛ ቡድን ፣ ለውጡ ያመጣውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ለቀጣይ ትግል ከመዘጋጀት ይልቅ ፣ ከከዚህ ቀደሙ ሁኔታ እንዳልተለየ፣ ብአዴንም ከህወሃት ተላላኪነት ባለ’ተረኛ’ ነኝ ከሚል ኦህዴድ ተላላኪነት እንዳልወጣ፣ የህወሃት ከስልጣን መገፋትም ለክልሉ ህዝብ የረባ ነገር አላስገኘም የሚል ስዕል በመሳል፣ ለውጡን አስመልክቶ ያደናቃፊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። 

ከዚህም አልፎ ግን ለውጡን በዋነኛነት ያመጣነው አኛ ነን ከሚለው ትርክትና የለውጡ ትሩፋት ዋና ተቋዳሽ መሆን ይገባናል ከሚለው ግብዝነት በላይ ፣በጥቅሉ ሲታይ የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ጽንፈኞች የሚኩራሩበት ዋናው ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥርና የቆዳ፣ ብሎም ሀብት የያዝነው እኛ በመሆናችን ያድራጊ ፈጣሪ ሚናና ሹመኝነትም ባብዛኛው የኛ መሆን አለበት የሚለው ነው።  

አንድ ወጥ ወይንም አንድ ብሄር ብቻ ያለበት ሀገር ቢሆን ምናልባት የቁጥር ብዛት ይሄን ሊያጎናጽፍ ይችላል ሊባል ቢችልም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ህብረ ብሄር ሃገራት ግን፣ ፍትሃዊ ከሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አንጻር፣ ይሄ የቁጥር ስሌት የብዙሃንን አምባገነናዊነት ለመጫን ከመፍጨርጨር ውጭ ሌላ ትርጉም አይኖረውም። 

ይሄ አይነት አካሄድ እስከ 80 ብሄረሰቦች ባሉባት ሀገራችን ቀርቶ ፣በሁለቱ ክልሎችና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ የብዙሃኑን ውሳኔ ወይንም ጥቅም ለማስከበር በሚል፣ በክልሎቹ ውስጥ የሚኖሩትን አናሳ ብሄረሰቦች ለሁለተኛ ደረጃ ዜጋነት እንደዳረገ፣ ብዙ መቶ ሺዎችን ለገፍ ግድያና ስደት እንዳበቃ፣ ባለፉት አመታት የተገነዘብነው ችግር ነው። 

የብዙሃን አምባገነንነት የሚለውን ሃሳብ በጥልቀት ከመረመሩት ውስጥ ለኒ ጉንየር የተባሉ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁርና ፕሮፌሰር፣ ‘የብዙሃን አምባገነንነት’ በሚለው ጽሁፋቸው በግርድፉ የሚከተለውን ይላሉ። አንድ ወጥ  ባልሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲን ከአብላጫ ድምጽ ብቻ ካገናኘነው ፣ በውስጡ ያዘለውን ራስን በራስ  ማስተዳደርን ፣ ፍትሃዊነትን ፣ ሰጥቶ መቀበልንና ድርድርን ፣ በዚህም አልፎ የሚደረስ ስምምነትን የሚዘነጋና  አምባገነናዊም ስለሚሆን፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጽንሰ ሃሳብን የሚጻረር ይሆናል።  

በቁጥርም ሆነ በቆዳ ስፋት ትላልቆቹ ብሄረሰቦች በሀገር ግንባታም ሆነ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ሃላፊነት የጎላ እንደሚሆን አጠያያቂ ባይሆንም፣ ይሄንን መሰረት በማድረግ ከሌሎች በቁጥር ከሚያንሱ ብሄረሰብ አባላት እኩል ዕድል አንጂ፣ የበለጠ ተጠቃሚነት ወይንም ተሿሚነት ይገባናል ማለት ግን ፣ በመሰረቱ ኢ- ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ፣ የጋራ ቤታችን በጽኑ መሰረት እንዳይገነባ ትልቅ እንቅፋት ከመሆን ባሻገርም፣ ያልተረጋጋና ሁሌም በቅራኔ የሚናጥ ሀገር ያደርገናል። 

የነዚህ ሁለት ክልሎች ልሂቃን ይሄንን የበለጠ ይገባናል የሚል አካሄድ አክርረው መቀጠል ከፈለጉ፣ እርምጃቸው ለተቀረው የሀገራችን ህዝብ ስጋት ስለሚሆንና መሃከላዊ መንግስቱን በመገዳደር ሀገር ሊበትን ወደሚችል አቅጣጫ ሊወስደን ስለሚችል ፣ ያለቅጥ የተለጠጠውን ክልል ለአስተዳደር ምቹ በሆነ መንገድ በማስተካከል ችግሩን መቅረፍ የግድ የሚልበት ጊዜ ሊመጣም ይችላል። 

የዴሞክራሲ ስርዓትና የሀገር ግንባታን በሚመለከት ከህዝብ ቁጥርና ከቆዳ ስፋት የሚመነጭ እብጠትንና ይዞት የሚመጣውን ችግር፣ በአንድ ወቅት መሐመድ አሊ የተባለው የቀድሞ የፓርላማ አባል ‘ኦሮሞና አማራ -ከትግል አጋርነት ባሻገር ‘ በሚል በጻፈው ጽሁፍ ያሰፈረውን ብጠቅስ፣ ማለት የምፈልገውን በቅጡ ስለሚያብራራ እነሆ።

“ በልማዳዊ አነጋገር ቤት ሊቆም የሚችለው ምሰሶና ዋልታን አማክሎ ነው።በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኦሮሞና  አማራ የአንድነታችን ምሰሶና ዋልታ ናቸው ቢባል ስህተት አይሆንም።ይሁንና ምሰሶና ዋልታ ብቻቸውን ቤት ሊሆኑ  እንደማይችሉ ሊሰመርበት ይገባል።አንድን ቤት ህልው የሚያደርጉት ምሰሶና ዋልታን አማክለው የሚቆሙት ባላና  ወጋግራ ጭምር ናቸው። ቤቱ እንደቤት ሊቆም የሚችለው በአግባቡ ሲማገርና ሲከደን መሆኑን በተለይ አስተዋዩ  ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቀዋል።”  

የአብይ አስተዳደር ከራሱ ከሚመነጩ ድክመቶች በተጨማሪ የነዚህ ልሂቃን አካሄድ ታክሎበት፣ የዛሬ ዓመት አግኝቶት የነበረውን ቅቡልነት በተወሰነ ደረጃ እንደሸረሸረበት ግልጽ ነው። ቅቡልነት እየቀነሰ ሲሄድ ለውጡን ወደፊት ለማራመድ ይችግራል ብቻ ሳይሆን፣ዳግም ወደ ጨለማ ይዞን ሊነጉድ ስለሚችል፣ ሀገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ፣እነዚህ የልሂቃን ቡድኖች ከያዙት አደናቃፊ አካሄድ ተቆጥበው ፣ ድጋፍ ሲያሳፈልግ ደግፈው፣ ነቀፌታም ሲያስፈልግ እንዲሁ ገንቢ በሆነ መንገድ እየነቀፉ ቢጓዙ የዛሬ ዓመት ተኩል ግድም በሀገራችን የፈነጠቀው ተስፋ እየዳበረ ፣ መጪው ጊዜያችን የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here