spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትስለ ኢትዮጵያ (በአባይነህ ወልደማርያም)

ስለ ኢትዮጵያ (በአባይነህ ወልደማርያም)

አብይ አህመድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ገደል ለመክተት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደረ ነው :: ነገ ዛሬ ሳይባል የመንግስት ሃላፊነቱን በሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎ ለሚታቀፍ የሽግግር  መንግስት ማስረከብ አለበት :: ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማስቀጠልና ሕዝቡን አሁን ከሚታየው የባሰ እልቂት ለማዳን ሌላ አማራጭ የለም :: በአንድ ወፈፌ አምባገነን ማን አለብኝነትና የጥፋት ውርጅብኝ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ሊፈርስ አይገባም ::

አብይ አህመድ - ኢትዮጵያ

በአባይነህ ወልደማርያም

የሀገራችን ሕዝብ : አእምሮው bየታወከ ፍፁም ጨካኝ አምባገነን የሀገር መሪ ነኝ ባይና :  እሱ ሥር በተኮለኮሉ አሽከሮቹ : ለከት የለሽ የሥልጣንና የዘረፋ ፍላጎት : ሥር የሰደደ ክፋትና  የማያቋርጥ የደም ጥማት የተነሳ : ዛሬም እንደገና በጦርነት እሳት እየተለበለበ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል : ልብ ያቆስላል :: 

ባለፉት አምስት አመታት በተካሄዱት ፍፁም አላስፈላጊ የእርስበርስ ጦርነቶችና የሰላማዊ ዜጎች አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች : በመላው ኢትዮጵያ በከንቱ የፈሰሰው ተሰፍሮ የማያልቅ የምስኪን ሕዝብ ደምና : የወደመው የሀገርና የሕዝብ ንብረት : በዚያም ሂደት የደበዘዘው የአብሮነት እሴት ያነሰ ይመስል ፤ የመንግስት ሥልጣን በያዙ ጥቂት ጨካኝ ግለሰቦችና ቡድኖች እኩይ ዓላማና ማንአለብኝነት የተነሳ : ሀምሳ አመት ሙሉ እፎይታ ያጣው ሕዝባችንና ድሃ ሀገራችን : እንደገና ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ መነከራቸው የግፍ ግፍ ነው :: 

ላለፉት ሠላሳ ሁለት አመታት ካለኃጢያቱ ካላንዳች ተከላካይ ባለማቋረጥ ሲቀጠቀጥ የኖረውንና :  ይብሱንም ባሁኑ አምባገነን የአምስት አመት የሥልጣን ዘመን : በሚልዮኖች ሲፈናቀልና በሺዎች ሲታረድ የኖረውን ፍፁም ድሃ አማራ ኢትዮጵያዊ ወገኑን ለመፍጀት : “የሀገር መከላከያ ሠራዊት” ሲሰለፍ ማየት : ማንኛውም ሰው የሆነ ፍጡር ሊሸከመው ከሚችለው ሃዘን በላይ ነው :: 

የሰው ልጅ ደምና እንባ ወንዝ ሆኖ ቢፈስ : በክፉዎችና በደንቆሮዎች ሥራ ምክንያት : በኢትዮጵያ  ምድር ላይ ካለማቋረጥ እየወረደ ያለው የደምና የእንባ ጎርፍ : ዓለምን ያጥለቀልቅ ነበር :: 

አለመታደል ሆኖ : ላለፉት ሃምሳ አመታት : በኢትዮጵያ የመንግስት ሥልጣን ላይ በተከታታይ የሚቀመጡ ሰዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው : ይህንን ለማሰብና : ለሕዝብ ሰላምና የኑሮ መሻሻል ቅድሚያ ለመስጠት የሚፈልጉም የሚችሉም ሰዎች አይደሉም :: 

ያሁኖቹም መሪዎች : ከመልካምነት ከእውቀትና ከብስለት ፍፁም ነፃ በሆነው የእውር ድንብር የሥልጣንና የዘረፋ ጥማታቸው የተነሳ : ሀገሩን በማያባራ ሁከትና ጦርነት ማጋየትን እንደ ጀብዱ የሚያዩ : የሰይጣን ሥራቸውን ጥቁሩን ነጭ ነው እያሉ ካለምንም ሃፍረት በአደባባይ የሚለፍፉ : በሕዝብ ላይ ካለማቋረጥ የሚያላግጡ አይንአውጦች ናቸው ::

በዚህ በማያባራ የእብዶች ሆያሆዬ : ካለኃጢያቱ በደመከልብ የሚያልቀው ድሃ ሕዝብና : እየወደመ ያለው ሀገር : ለነዚህ በክፋትና በጭካኔ ለታወሩ ሰዎች ምናቸውም አይደለም :: 

ለከትየለሽ በሆነ የሥልጣንና የዘረፋ ፍላጎት ከመታወራቸው ብዛት : ራሳቸው ቤተሰቦቻቸውና  ልጆቻቸው የቆሙበትን መሬት እየደረመሱት መሆናቸውን ማመዛዘን አይችሉም :: 

ትናንት በሕወሃት አልጠግብ ባይነትና ክፋት ምክንያት በተካሄደው እጅግ አሰቃቂ ጦርነት :  እንደቅጠል የረገፈው ከሚልዮን በላይ የሚገመት ድሃ ሕዝብ : ወታደር ሚሊሽያና እጅግ ብዙ  ንፁሃን ዜጎች : ሴቶች ሕፃናትና አረጋውያን ሬሳ የአውሬ ሲሳይ ሆኖ ቀርቷል :: 

በጦርነቱ ሂደት : በትግራይ በጎንደር በወሎ በጎጃም በአፋር በሰሜን ሸዋ : በሰላማዊ ዜጎች ላይ  በሰፊው ለተፈፀመው እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ማንም ተጠያቂ አልሆነም :: 

የሀገሩ ኢኮኖሚ በጦርነትና በአጠቃላይ የአመራር ብልሹነት የተነሳ ገደል ገብቶ : ሕዝቡ ግዙፍ ችግር ላይ ከወደቀ ከርሟል :: በሀገራችን ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ ለመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል  የሚያቅትበት ደረጃ ላይ ተደርሷል :: 

በየክፍለሀገሩ በዘሩና በቋንቋው ምክንያት ብቻ የተጨፈጨፈውና በሚልዮኖች የተፈናቀለውን : ዛሬም ድረስ ካለምንም ምክንያት ዘሩ ብቻ እየተመረጠ የሚባረረውንና የሚገደለውን ሕዝብ  እግዚኦታ የሚሰማ የመንግስት ጆሮ ወይም የፍትህ አካል በጭራሽ የለም :: 

የሰሜኑ ጦርነት በድርድር መቆሙ ተመራጭነት እንደተጠበቀ ሆኖ : በዚህ ፍፁም አላስፈላጊ :  እጅግ አሰቃቂና አውዳሚ ጦርነት ቀንደኛ ተዋናይ የነበሩትና : ያንን ሁሉ ምስኪን ሕዝብ ያላንዳች  ርህራሄ በገፍ የፈጁትና ያስፈጁት የሕወሃት መሪዎች : ተጠያቂ ሊሆኑ ቀርቶ : ሁለት አመት ሙሉ  ያን ሁሉ ደሃ ወታደር እያስጨረሱ ሲዋጉዋቸውና : በቀን 24 ሰዓት ጥንብ እርኩሳቸዉን እያወጡ  ሲወነጅሏቸው በነበሩት የ”ብልፅግና” መሪዎች : በአደባባይ ጉንጫቸዉ ተገላብጦ ተስሞ ካባ  ተሸልመዋል :: በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እንዳሻቸው እንዲጎማለሉ ተፈቅዶላቸዋል :: 

አሁን በቅርቡ ደግሞ : EFFORT በሚባል ስም የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ለ27 አመት ሙልጭ አርገው የዘረፉበት ግዙፍ የቢዝነስ ተቋም : ሥራውን (ዘረፋውን) እንዲቀጥል በይፋ ተፈቅዶለታል :: 

አብይ አህመድ ይህንን የጉድ ጉድ በፍፁም አይንአውጣነት በይፋ ሲፈፅም : ትናንትና በራሱ አንደበት በተደጋጋሚ : “የሰሜን እዝ በጁንታው በሕወሃት ከጀርባው ተወጋ : በተኛበት ተረሸነ : ሬሳው እንደ ውሻ መሬት ለመሬት ተጎተተ : ሴት ወታደሮች ጡታቸውን ተቆረጡ በሳንጃ ተዘለዘሉ : በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችና መኮንኖች ልብሳቸውን ተገፈው ራቁታቸውን ተባረው ኤርትራ ገቡ: ሌላም ሌላም አሰቃቂ ግፍ ተፈፀመባቸው…” እያለ ሌት ተቀን ሲንተከተክ እንዳልነበር ሁሉ :  የሕወሃት ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረቡ ለግዜው ይቆይ ቢባል እንኳን : ይህን ያህል አይን አውጥቶ

በአደባባይ ሲሸልማችው : ያ ሁሉ ዘግናኝ ግፍ የተፈፀመባቸው ወታደሮችና ወገኖቻቸውስ  ሕዝቡስ ምን ይለኛል ሊል የሚችልበት አእምሮና ህሊና የሚባል ነገር ጨርሶ የሌለው ሰው መሆኑን ሁነኛ ማሳያ ነው ::  

በአንፃሩ ደግሞ በዚያ አውዳሚ ጦርነት ካለ አንዳች የመንግስት የስንቅና ትጥቅ እገዛ : በራሱ አሮጌ መሳርያና : የአብይ መንግስት ማርከህ ታጠቅ ባለው መሰረት : በከፍተኛ መስዋዕትነት እየማረከ : የሕወሃትን እስከአፍንጫው የታጠቀ ጦር በቀዳሚነት የመከተውና : አብይን እና ጋሻ ጃግሬዎቹን  ሕወሃት በይፋ ከደገሰላቸው በአደባባይ መቀፍድድ ያዳነው : በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው  

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል : ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ ትጥቅህን ካልፈታህ ተብሎ : በአብይ መንግስት ይፋ ጦርነት ከታወጀበት ወራት አስቆጥሯል :: በዚህም የተነሳ በሽዋ በጎንደር  በጎጃም በወሎ ሰፊ ውጊያ እየተካሄደና እጅግ ብዙ ሕዝብ እንደገና እያለቀ ነው :: 

ፋኖ የሚባለው የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ተጠሪዎች : ለምን መንግስት ባዘዘው መሰረት ትጥቃችሁን አትፈቱም ሲባሉ የሚሰጡት መልስ ግልፅና ትክክለኛ ነው :: 

– አሁን ባለው የጎጥ ሕገመንግስት የአማራ ክልል በሚባሉት ክፍላተሃገር : ሕዝቡን በጭካኔ የፈጀውና : ዘመን የማይሽረው ወንጀለኛ የሆነው ሕወሃት : ትጥቁን መፍታት ቀርቶ : በየእለቱ እንደገና የሚጠናከርበት መንገድ እየተመቻቸለት እያለ : 

– ከሕወሃት የግፍ አገዛዝ በብዙ የሕይወት መስዋእትነት ወደቀድሞ ይዞታቸው የተመለሱትን የወልቃይትና ራያ መስተዳድሮች እንደገና ለመንጠቅና : ሕዝቡን እንደቀድሞው ለመርገጥ : በአብይ አህመድ ሙሉ ፍቃድ ወደሥልጣን የተመለሰው የሕወሃት ቡድን አሰፍስፎ ጦሩን እየሰበቀ እያለ : 

– የአብይ መንግስት ኦነግ ሸኔ እያለ በሚጠራው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድንና : በነሸመልስ አብዲሳ  በሚታዘዙ እጅግ ጨካኝ ሕገ ወጥ ሚሊሽያዎች : በሌሎችም ግፈኞች ሲካሄድ የቆየውና  አሁንም ያላባራው : በወለጋና በቤኒሻንጉል በመተከል በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች : የአማራ ተወላጆችን ማሳደድና መጨፍጨፍ ባልቆመበት ሁኔታ : 

– አልፎ ተርፎም በአዲስአበባና አካባቢው : የአማራ ተወላጆችንና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን እየመረጡ : ቤታቸውን ላያቸው ላይ በግሬደር እየደረመሱ : በመቶ ሺዎች ማፈናቀልና : ከነሕፃናት ልጆቻቸው ጎዳና ላይ መወርወር በቀጠለበት ሁኔታ ፥ ይህ የግፍ ሥራ አንሶ : የአብይ ሰዎች በመንግስት ሚድያ ላይ በፊት ለፊት ወጥተው : ካለአንዳች ቅንጣት ሰብአዊነትና ሃፍረት:  እነዚህን ዜጎች “ሕጋዊ ድሃ አድርገናቸዋል” እያሉ በሕዝብ መከራ ላይ እየተሳለቁ ባለበት ሁኔታ:  

– የአማራ ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶችን ንብረትና ገንዘብ : ካላንዳች ሕጋዊ ምክንያት ማገድ  በቀጠለበት ሁኔታ :

– የአማራ ተወላጅ የሆኑ የሕብረተሰብ አንቂዎችን : መምህራንን የመንግስት ሰራተኞን  ወጣቶችን : ከመንገድ ላይና ከቤታቸው በግፍ ማፈንና መሰወር መደብደብ ማሰቃየት መግደል  በቀጠለበት ሁኔታ : 

– በአዲስአበባና በሌሎችም ቦታዎች : የአማራ ተወላጆችንና ሌሎችንም ከመንገድ ላይ እያፈኑ :  ቤተሰቦቻቸው ከአቅም በላይ የሆነ ቤዛ/Ransom ንብረታቸውን ሸጠውም ቢሆን እንዲከፍሉ  ማስገደድ : መክፈል ካልቻሉም

: የታገቱትን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል እየተካሄደ እያለ : 

– ከአማራ “ክልል” ወደ አዲስአበባ የሚመጡ የጭነትና መኪኖችን : በነሽመልስ አብዲሳ ትእዛዝ እያገቱ አዲስአበባ እንዳይገቡ መከልከል : ጭነታቸውን መዝረፍ : የመንገደኛ  አውቶብሶችን እያስቆሙ : ለሕክምና የሚሄዱትን ጭምር አዲስአበባ እንዳይገቡ መከልከል ባልቆመበት ሁኔታ : 

– መንግስት ተብዬው : ይህንን በአማራ ሕዝብ ላይ በየቀኑ በሰፊው የሚካሄድ የግፍ ግፍ :  እንኳን ሊያስቆምና ለሕዝቡ የሕይወት ዋስትና ሊስጥ ቀርቶ : ጨፍጫፊዎቹን በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያባባለና እያገዘ ባለበት ሁኔታ : 

– በአልጠግብ ባይነት የሀገራችንን ሕዝብ በገፍ የፈጁትና ያስፈጁት የሕወሃት መሪዎችና የጦር አዛዦች : በአብይ መንግስት ሲሳሙና ሲሸለሙ : በአንፃሩ እነሱን በጀግንነት የመከቱትና  ሀገራቸውንና የአብይን መንግስት ከመፈራረስ ያዳኑት : እንደነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ ያሉ 

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች : በአብይ አህመድ ትእዛዝ ሕክምና ተከልክለው ሞት ተፈርዶባቸው እያሉ : 

– “የአማራ ክልል መንግስት/የአማራ ብልፅግና” የሚባሉት ህሊና ቢስ ሆድ አደር የአሽከርነት ሱሰኞች : ሠላሳ ሁለት አመት ሙሉ ሕዝባቸውን ሲያስቀጠቅጡና ሲቀጠቅጡ ኖረው : አሁን እንኳንስ የአማራን ሕዝብ ሊታደጉ ቀርቶ : ዛሬም እንደገና ከአዲሶቹ ጌቶቻቸው ሥር  ተኮልኩለው : የአማራን ሕዝብ አስገዳይና ገዳይ ሆነው በተሰለፉበት ሁኔታ : 

– የአማራ ሕዝብ : በምዕራብ በሱዳን የድንበር ተሻጋሪ ወታደሮች : በምስራቅ በሕወሃት : በደቡብ በተለያዩ በኦሮሞና በሌሎች ጎሳዎች ስም በተደራጁ ታጣቂዎች የሚደርስበት ጥቃትና የሕልውና ፈተና ሳይቀረፍና : ምንም ግልፅ የሆነ መተማመኛ ሳይኖረው : 

– መንግስት ለሕዝቡ በሕይወት የመኖር ዋስትና ለመስጠት ባልቻለበትና : በተቃራኒው  ከጨፍጫፊዎቹ ጋር በሚያብርበትና ራሱ የሕዝብ ጨፍጫፊ በሆነበት ሁኔታ : 

– ሕግ ማክበርና ፍትህ የሚባል ነገር : በቀዳሚነት መንግስት ነኝ በሚለው ሕገወጥ ቡድን ተሽቀንጥሮ በተጣለበት ሁኔታ :

ይህ ሁሉ ከላይ የተዘረዘዉ ግፍ ባልቆመበትና : የአማራ ሕዝብ ወደ ፈጣሪው እግዚኦ ከማለት ሌላ  ምንም አይነት ከለላ ባላገኘበት አውድ : በሰላም አርፎ የተቀመጠውና በመንግስት ላይ አንድም ጥይት ተኩሶ የማያውቀው : ይልቁንም ውድ ሕይወቱን እየሰዋ የመንግስት አጋር ሆኖ የከረመው  የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል : ለምንድን ነው ከሌሎች አማራን በጠላትነት ከሚፈርጁና ከሚፈጁ  የታጠቁ ኃይሎች በፊት በግድ ትጥቅህን ፍታ የሚባለው?? 

መንግስት ተብዬው : ትናንት የሀገራችንን ሕዝብ በግፍ ከፈጁት ካስፈጁትና በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ያን ሁሉ ዘግናኝ ወንጀል ከፈፀሙት ሕወሃቶች ጋር : እንዲሁም ኦነግ ሸኔ ከሚባሉት ራሱ አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ሰላማዊ ሕዝብ የሚፈጁ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ለሰላም ድርድር ሲቀመጥ: ለምንድን  ነው አርፎ የተቀመጠውን የፋኖን ሕዝባዊ ኃይል : በአግባቡ ለማነጋገርና በትእግስት ለመወያየት ያልፈለገውና ዘሎ ጦርነት ውስጥ የገባው?? 

ለምንድን ነው ለአማራ ሕዝብ የእባካችሁ አትግደሉን አታሳዱን በገዛ ሀገራችን መድረሻ አታሳጡን : ሌላው ሁሉ ይቅርና በሕይወት የመኖር መብት ይኑረን ጥያቄ : መልስ ለመስጠት ያልቻለው ወይም ያልፈለገው?? 

መልሱ ቀላልና ግልፅ ነው : በተዘዋዋሪም በቀጥታም በመንግስት ሥልጣን ላይ ባሉ ቱባዎችም  በጋሻ ጃግሬዎቻቸውም በንግግርም በተግባርም በየቀኑ እየታየ ነው :: 

አላማቸውና ተግባራቸው : አማራ የሚባለውን መከረኛ ሕዝብ የምንችለውን በየሰበቡ  ፈጅተን : የተቀረውን ሰብረንአንገቱን አስደፍተን : ሁለተኛ ቀና እንዳይል በሁሉም  መስክ አድቅቀን : ታሪኩንና ቅርሱን አውድመን ካልሆነ በስተቀር : በኢትዮጵያ ምድር ላይ  የ”ኦሮሙማ” እና “የኩሽ” የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነትን ለዘለቄታው ማስፈን አንችልም የሚል የሰይጣን ተልእኮ ነው : እቅጩ ይኸው ነው ::  

ይህንን ተልእኮ ለማስፈፀም : በአብይ አህመድና በአሽከሮቹ ክፉ አስተሳሰብ : ለዚህ እርኩስ አላማ አልንበረከክም እምቢኝ አሻፈረኝ እንደሚል የሚታወቀውን የፋኖን ሕዝባዊ ግንባር :  ድምጥማጡን ማጥፋትና : የአማራን ሕዝብ በሙሉ ማሽመድመድ ያስፈልጋል :: 

ይኸው ነው ያሁኑ ጦርነት ብቸኛ አላማ : ሌላው የአብይ መንጋዎች ልፍለፋ : መሬት ጠብ የማይል ከንቱ መቀላመድና : በግልፅ በአይን የሚታየውን እውነት መካድ : ወይም እንደ ሰጎኗ ጭንቅላትን አሸዋ ውስጥ መቅበር ነው :: 

ሰላማዊና ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ወገኖቻችንን ጨምሮ : ማናቸውም የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችና  ዜጎች : ይህንን ሀገር አውዳሚ አላማ በፍፁም አይጋሩም :: የሁሉም ሕዝብና ዜጋ ፍላጎት :  ከወገኑ ጋር በሰላም በእኩልነት መኖርና ኑሮውን በሕብረት ማሻሻል ነው ::

እነዚህ ክፉዎችና ጨካኞች : እንኳንስ አርባ ሚልዮን አማራ ቀርቶ : ስድስት ሚልዮን ትግራዋይ እንደ ሕዝብ ካበረና እምቢ ካለ : በምንም አይነት ማሸነፍ እንደማይቻል : ትናንት እነሱ ራሳቸው ከዋሉበት አውድ መማር የማይችሉ ደካሞች ናቸው :: 

የዚህ ሁሉ እብደት ውጤቱ : አብይ አህመድና አሽከሮቹ ባቀጣጠሉት እሳት : ራሳቸውንና ሀገራችንን ማጋየት ብቻ ነው :: 

ይህንን ፍፁም የለየለት Genocidal ዓላማና ተግባር ለመመከትና : ኢትዮጵያን ከሀገራዊ ውድመት ለማዳን : ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን : ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር በሚችለው አቅምና መስክ መታገል ይጠበቅበታል :: 

ከኦሮሞ ወገኖቻችን መሀል : በነአብይ አህመድ በነሽመልስ አብዲሳና በመሰሎቻቸው ቅጥፈት :  ከንቱ ዲስኩርና ቅዠት የተታለሉና : በአማራም ሆነ በሌሎች ብሄረሰቦች መገፋት እንጠቀማለን ብለው የሚያስቡ ወገኖች ካሉ ፤ ሕውሃትን የሙጥኝ እንዲል ተወናብዶና ተገዶ : ግፍና መከራ ብቻ ካተረፈው ከትግራይ ሕዝብ መማር ይችላሉ : ያም አልበቃ ካለ : ይህንን (https://www.ethiopianreporter.com/117142/) ጥርት ያለ መልእክት አጢነው ራሳቸውን እንደገና መመርመር ይኖርባቸዋል ::  

ለሁሉም የሀገራችን ዜጎች ፍትህና ርትእ የሚሹና : ለዚህም የሚታገሉ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በርካታ ናቸው : ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብም ከዚህ የተለየ ፍላጎት የለውም :: 

በአብይ አህመድ የአምስት አመት የሥልጣን ዘመን : በሰላምና በምቾት የሚኖር አንድም የሀገራችን ክፍል ወይም ብሄረሰብ የለም : ኦሮሞ ወገኖቻችንን ጨምሮ ሁሉም ፍዳውን እያየ ነው ::  

ይህንን መከረኛ ሕዝብና ሀገር ለመታደግ ምንም ሌላ ምርጫ በማጣቸው ምክንያት :  ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው እየተዋደቁ ያሉትን : የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑትን የፋኖ አርበኞችንና : ሌሎችም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህና ርትእ የሚታገሉ ወገኖችን :  በሚቻለው መንገድ ሁሉ መደገፍ : ባለን አቅም ሁሉ ደጀን መሆን : የዚህን እብድ ሰውዬ እርኩስ  አላማና ሰይጣናዊ ተግባር : ባለን አቅም ሁሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ማጋለጥና መሞገት :  አማራጭ የሌለው ጉዳይ የሆነበት ግዜ ላይ ነው ያለነው :: 

የሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት : የአብይ አህመድ መንግስት ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ በመላው የአማራ ሕዝብ ላይ በግልፅ እያካሄደ ያለውን Genocidal ጭፍጨፋ : በ”አስቸኳይ ግዜ አዋጅ” ስም እንዲያፀድቅ በታዘዘበት ግዜ : ቀደም ሲል የአብይ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የሕዝብ እንደራሴ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር : “ፓለቲካዊ ችግር በጠመንጃ ሊፈታ አይችልም : የችግሩ ምንጭ የ”ብልፅግና” መንግስት የፓለቲካዊ አመራር ውድቀት ነው : ይህ መንግስት እንኳን የአማራን ሕዝብ የማያባራ መፈናቀልና መገደል ሊያስቆም : ለችግሩ የተዛቡ አመለካከቶችን በማራመድ እያባባሰው ነው : የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአስቸኳይ ጦርነቱን አቁሞ

ወደ ካምፑ መመለስ አለበት : በአማራ ሕዝብና በ”ብልፅግና” ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት በማይጠገን ሁኔታ ስለተበጠሰ : ሁሉንም የአማራ ኃይሎች የሚያካትት ጊዜያዊ አስተዳደር ሊቋቋም ይገባል..” ብለው በጥብቅ አሳስበዋል :: 

የአቶ ገዱ አስተያየት ለግዜው መሸጋገሪያ ሃሳብ ቢሆንም : ዘላቂ ሀገራዊ መፍትሄ አይሆንም :: 

አሁን እየተካሄደ ባለው የዘር ፍጅት ምክንያት : የአማራን ሕዝብ ከነዚህ አረመኔዎች  ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ሳለ : በውስጡ ያዘለው ሀገራዊ አጀንዳና  መዳረሻ አለ : ይኸውም ኢትዮጵያን እንደሀገር ከመበታተንና ሕዝቡንም ከመተላለቅ  ማዳን ነው :: 

ይህ አደጋ ግምታዊ ነገር ሳይሆን : አፍጦ የመጣና የአብይ አህመድ እብደት ባንድ ወይም  በሌላ መልኩ ካልተወገደ በእርግጥ የሚሆን ነገር ነው :: 

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል : ራሱንና የአማራን ሕዝብ : አልፎም የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአብይ አህመድ : ብርሃኑ ጁላ : ሽመልስ አብዲሳ : አበባው ታደሰ… ወዘተ የሚባሉ አረመኔዎች ጭፍጨፋ ለመከላከል በታላቅ ጀግንነት እየተፋለመ ነው :: 

በዚህ እንደገና ሳይፈለግ በግድ ሕዝባችን ላይ በተጣለ የጦርነት ፍዳ : የአብይ ጦር ገሚሱ ይዋጋል ገሚሱ የገዛ ወገኔን አልገድልም ብሎ ይከዳል : ሌላው ደግሞ ሰላማዊውን ሕዝብ በአረመኔያዊ ጭካኔ ይጨፈጭፋል :: 

የፋኖ ሕዝባዊ ኃይል የውጊያ አቅም እሱ ከጠበቀው በላይ ሲያይልበትና መከላከያ ውስጥም መሸብረክ ሲፈጠር : የራሱ እብደት አንሶ : የኦሮሞን ወጣቶች በሰፊው እየመለመለ : ትናንት  የኦሮሞ ደም ደማችን ነው ብሎ ከጎናቸው ተሰልፎ በታገለው ፋኖ እና : በወገናቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ለማዝመትና : የባሰ የሕዝብ ለሕዝብ እልቂት ለማቀጣጠል በይፋ እየጣረ ነው :: 

የፈሪነት የደንቆሮነት እና እጅግ ሥር የሰደደ ክፉነት መጨረሻው ይህ ነው :: 

በዚህ እጅግ አሳዛኝ : ሕዝብና ሀገር አውዳሚ የሆነ ወቅት : ኦሮሞ ወገኖቻችንና ሌሎችም  ብሄረሰቦች : “የአማራ ደም የኛም ደም ነው” ብለው : ሀገራቸውንና እና ሕዝባቸውን ከነዚህ አረመኔዎች ለማዳን አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩ ይጠበቃል :: 

በአማራ ሕዝብ ላይ በሰፊው እየተካሄደ ካለው ጭፍጨፋ ባሻገር : አዲስአበባን በግድ መሰልቀጥ : የጉራጌን ሕዝብ አዋክቦ ወደ ኦሮሚያመጨፍለቅ : የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያብር አስር ቦታ ሰነጣጥቆ የነሱ አሽከር ማድረግ : የአፋርና የሶማሌን ክፍለሀገሮች መደፍጠጥ : የ”ኦሮሚያ”ን ወሰን በሁሉም አቅጣጫ በግድ ማስፋፋት : በሚሊተሪና  ሴኩሪቲ ተቋማት : በመንግስት መስሪያ ቤቶች በባንኮችና : በሁሉም የኢኮኖሚና 

የመንግስት ፖሊሲ አውታር በሆኑ ቁልፍ የአመራር ቦታዎች ላይ : ባለሙያዎቹን እያባረሩ  ችሎታ ባይኖራቸውም ለአብይ ቡድን ታማኝ በሆኑ ባለግዜዎች መተካትና ተቋማቱን  መቆጣጠር ፤ የኦሮሙማየበላይ ፈላጭ ቆራጭነትን ማረጋገጫ እቅዶችና በተግባር ለማዋል እየተሞከሩ ያሉ ኩነቶች ናቸው :: 

አብይ አህመድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ገደል ለመክተት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደረ ነው: በመጀመሪያው የሥልጣን አመቱ ፍፁም አፈቅቤ ሆኖ ቀርቦ : አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እሱ ራሱ  በማያምንበት ስብከት አታሏል :: 

ባለፈው አራት አመት ግን ሀገር አጥፊ አጀንዳው ነጥሮ ወጥቷል :: በታውከ አእምሮ የሚነዳ እጅግ  አደገኛ ሰው መሆኑና: አይን ያወጣ ውሸታም አታላይ ዘባራቂ እጅግ ክፉ ሰው መሆኑ ገሃድ ወጥቷል:: 

ሰብአዊነት እውነት ቅንነት ደግነት ሀዘኔታ ሃፍረት ፀፀት ማስተዋል ብስለት ከስህተት መማር ከሚባሉት መሰረታዊ የሰው ልጅ እሴቶች : ከአንዳቸውም ጋር በጭራሽ አይተዋወቅም :: 

“በእርግጠኝነት ልንገራችሁ : በድጋሚ ላለረጋግጥላችሁ” ወዘተ እያለ : ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተደጋጋሚ ከገባዉ ቃል ውስጥ : በአፍጢሙ ያልደፋውና በተቃራኒው ያልሄደበት አንድም ሃገራዊ  ጉዳይ የለም :: ከቅጥፈቱ ብዛት አንዱ ውሽት ሌላውን ጠልፎ እየጣለ የኮሜዲያኖች መቀለጃ ከሆነ ከርሟል :: 

የለየለት Narcissistic Psychopath ከመሆኑ ብዛት : አምስት አመት ሙሉ ባለማቋረጥ  እየተካሄደ ባለው የሺዎች ንፁሃን ድሃ ዜጎችና ሕፃናት የማያባራ አሰቃቂ እልቂት : እንኳን እንደሰው ፍጡር ሊያዝንና እንደ መንግስት መሪ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ቀርቶ : ፓርላማ ውስጥ ተቀምጦ “እኔ የመንደር ጠባቂ ፓሊስ አይደለሁም : ገና ብዙ ሰው ይሞታል : አሜሪካም ሰው  ይገደላል…” ወዘተ እያለ : በሀገርና በንፁሃን ዜጎች እልቂት ላይ በይፋ ያላግጣል :: 

በመላው ሀገር ከአምስት ሚልዮን በላይ ድሃ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በግፍ ከቀያቸው ተፈናቅለዉ : በየግዜያዊ መጠለያውና በየጫካው እየተሰቃዩና እየተንቀጠቀጡ እያሉ : እነሱን መልሶ ማቋቋም ቀርቶ : ይባስ ብሎ : በአዲስአበባ ዙርያ ዘራቸው እየተመረጠ የዜግነት መብታቸው የተገፈፈ  ከመቶ ሺህ በላይ ቤተሰቦችን : በአማካይ አምስት መቶ ሺህ ዜጎችን : በአረመኔያዊ ጭካኔ መኖሪያ ቤታቸውን ላያቸው ላይ በግሬደር አስደርምሶ : ከነሕፃናት ልጆቻቸው መንገድ ላይ  ወርውሮ : በብዙ ቢልዮን ዶላር ወጪ አዲስ ከተማና ቤተመንግስት ያስገነባል :: 

ይህ ሁሉ ሕዝብ እንደዚህ እየተሰቃየ : የተቀረውም በየቀኑ እየናረ በሚሄደው የኑሮ ውድነት ክፉኛ እየተቸገረ ባለበት ወቅት : ለትርፍ ቤተመንግስት ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣት ተገቢ ነው ወይ ተብሎ በሕዝብ እንደራሴዎች ሲጠየቅ : አያገባችሁም ገና ምን አይታችሁ : ለዚህ የቅንጦት ስራ እንዲያውም አምስት መቶ ቢልዮን ብር ነው የማፈሰው ብሎ እብደቱን በአደባባይ ያጋልጣል ::

ይህ ሁሉ ጉድ አልበቃው ብሎ : በሀገሪቱ ፓርላማ ውስጥ አይኑን አፍጥጦ “አዲስአበባ ዉስጥ ብዙ  ኦሮሞ ጠል የሆኑ ሰዎች አሉ” እያለ : የኢትዮጵያዊ አብሮነት አክሊል የሆነው የአዲስአበባ ሕዝብ  ላይ እልቂት ይጋብዛል :: የሀገር መሪ ነኝ የሚል ሰው ቀርቶ : ማንም ትንሽ ማሰብ የሚችል የሰው  ፍጡር : እንዲህ ያለ ፀያፍና እጅግ አደገኛ ነገር እንኳን ፓርላማ ውስጥ የትም ቦታ አይናገርም :: 

ሕግና ስርዓት የሚከበርበት መንግስት ቢኖር ኖሮ : አብይ አህመድ ሕዝብን በሕዝብ ላይ  በማነሳሳት ተከሶ ዘብጥያ መውረድ ነበረበት :: እንዲህ ያሉ ተጠያቂነት የሌለባቸው የጥላቻ  ዲስኩሮች ናቸው ሕዝብ እያጫረሱ ሀገራችንን ገደል እየከተቱ ያሉት ::  

በተቃራኒው : ጥላቻ ይቅር ሰብአዊ መብትና ሕግ ይከበር ሕዝብ በከንቱ አይሰቃይ አይገደል የሚሉ  ሰላማዊ ዜጎች : በስፋት ይሳደዳሉ ይታፈናሉ ይቀጠቀጣሉ ይገደላሉ :: በፓርላማ የሕዝብ  እንደራሴዎችን ጨምሮ : በአብይ መንግስት ላይ በእውነት ላይ የተመሰረተ ትችት የሚያቀርቡ  ዜጎች : ከያሉበት እየተለቀሙ በየማጎርያው ይሰቃያሉ :: 

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች : በመታወቂያ ወረቀታቸው  ወይም በስማቸው አማራ መሆናቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው : ከየመንገዱ እየታፈሱ ራቅ  ወዳሉ ማጎሪያዎች (concentration camps) እየተጋዙና እየታመቁ : በረሃብና በተስቦ በሽታ  አበሳቸውን እያዩ ነው : አንዳንዶቹም እየሞቱ ነው ::  

የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከዳር አስተባብረው : ታላቁን የአድዋ ድል የመሩት የኤፄ ምኒልክ  መታሰቢያ ሐውልትና አደባባይ ዙርያ : አመታዊውን የአድዋ ድል በአል ለማክበር የተሰበሰቡ  ዜጎችን : እየቀጠቀጡ ማባረር ሳይበቃቸው : በአቅራቢያው የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቤተክርስትያን ውስጥ ድረስ ተከትለው ገብተው : በቲርጋዝና በጥይት ደብድበዋቸዋል :: 

ለ”ኦሮሙማ” አዲስአበባን የመሰልቀጥ እኩይ አላማ ሲባል : በፍፁም ሕገወጥነት ካለቦታቸው  አዲስአበባ ውስጥ በብዛት የተሰማሩት የ”ኦሮሚያ” ፖሊሶች : በበዓላት ቀን የኢትዮጵያ ባንዲራ  ጥለቱ ላይ ያለበት ነጠላ ሽሚዝ ወይም ቲሸርት የለበሱ ዜጎችን : በአደባባይ እያስወለቁ  ባንዲራውን እየቀደዱ ሲጥሉና ሰዉን ሲደበድቡ ማየት የተለመደ ሆኗል :: 

የምስጋና በአል በሆነው በቅርቡ በተከበረው የእሬቻ በአል ላይ : የሽመልስ አብዲሳ ኮልኮሌዎች በብዛት ሆነው : በአዲስአበባ በአዳማ በቢሾፍቱ…ወዘተ የምትኖሩ አማሮች : ፋኖን ካላወገዛችሁ በናንተ ላይ ይብሳል : አዲስአበባ የኦሮሞ ነው” እያሉ በአደባባይ እየጮሁ የጄኖሳይድ ደወል ሲያሰሙ ነበር ::  

ይህ የፍጅት ጥሪ የመነጨው ከአብይና ከሽመልስ ጎራ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ : በዚህ ቀውጢ ሰአት እንዲህ ያለ እጅግ አደገኛ ነገር በይፋ በአደባባይ ሲለፈፍ : መንግስት ተብዬዎቹ ለይስሙላ እንኳን ይህ ልክ አይደለም ብለው አንዲት መስመር ለመናገርና : ሕዝቡን ትንሽም ቢሆን ከሽብር ለማረጋጋት አለመፈለጋቸው ነው ::  

ሩዋንዳ ውስጥ ከሶስት ወራት ባልበለጠ ግዜ ውስጥ : አንድ ሚልዮን ሕዝብ በገጀራ የተጨፈጨፈበት የጄኖሳይድ ደወል የተደወለው ልክ በዚህ ሁኔታ ነው ::  

በሀጫሉ ሁንዴሳ መገደል ሰበብ : ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የሻሸመኔ ከተማ ሲቃጠል : ንፁሃን አማርኛ ተናጋሪዎችና ሌሎችም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ከየቤታቸው እየተጎተቱ  ሚስትና ልጆቻቸው ፊት እንደበግ ሲታረዱ ፤ የከተማው ከንቲባ ገዳዮቹን ለማስቆም አቅቶት  እርዳታ ለመጠየቅ ለአለቃው ለሽመልስ አብዲሳ ቢደውል : “አርፈህ ተኛ” የሚል ትእዛዝ  እንደተሰጠው በይፋ መመስከሩ የትናንት ክስተት ነው ::  

ሽመልስ አብዲሳ ለዚህ ወንጀል እንኳን ተጠያቂ ሊሆን ቀርቶ : የአዲሳባን ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ  ከገፋ በኋላ የሚንደላቀቅበት ቤተመንግስት “ፊንፊኔ” ውስጥ ለማስገንባት ሽር ጉድ እያለ ነው :: 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን : ከሩዋንዳው እልቂት  አመጣጥና አካሄድ ተምረው : በዚህ ወር ባወጡት ዝርዝር ሪፖርት : ኢትዮጵያ ውስጥ  ያለው ሰፊ የሰብአዊ መብት ቀውስና : እየተባባሰ ያለው ዘር ተኮር ጦርነት : ወደ  ጄኖሳይድ እያመራ ነው ብለው በማያሻማ ቋንቋ በጥብቅ አሳስበዋል :: 

ባሁኑ ሰዓት : የአብይ አህመድ ጦር በበርካታ የአማራ “ክልል” አካባቢዎች መብራት  ስልክና ኢንተርኔት አጥፍቶ : ታዛቢ በሌለበት የፋኖን ሕዝባዊ ኃይል ለማሸነፍ እየሞከረና : ሰላማዊውን ሕዝብ በከባድ መሳርያ በድሮንና በአየር ኃይል : በየከተማውና በየማሳው  ላይ እየፈጀ ነው :: 

ሀገሩ በከፍተኛ የጦርነት እሳት : በሰላማዊ ዜጎች ፍጅትና በአጠቃላይ ሁከት ክፉኛ እየተለበለበ ባለበት በዚህ እጅግ አስፈሪ ሰአት : አብይ አህመድ “ ግዜው ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትና : ውጭ ሀገር ልጅ ማሳደግ ስለማይመች ሀገራቸው አምጥተው  የሚያሳድጉበት ግዜ ነው…” እያለ : የሕፃን አይሉት የእብድ ነገር ይዘላብዳል :: 

የአማራ ፋኖን ሕዝባዊ ኃይል እና የአማራን ሕዝብ እጨፈልቃለሁ ብሎ የከፈተው የእብሪት ጦርነት  መልሶ ሲለበልበው : የሕዝቡን ቀልብ ለማስቀየስ የሚችል መስሎት : “ውሃ የባህር በር ቀይ ባህር ወዘተ” የሚል አሁን ባለንበት እጅግ ከፍተኛ ሀገራዊ ሁከትና እልቂት ወቅት ትርጉም የለሽ የሆነ  ዝባዝንኬ ያወራል :: የመንግስትን ሥልጣን በሙሉ ጠቅልሎ በእጁ አስገብቶ : ይህን ሁሉ  የማያቋርጥ የሕዝብ ፍጅትና ስቃይ በቀጥታ በግለሰብ ደረጃ እየመራ : በጎን ደግሞ ሃይማኖተኛ ነኝ  እያለ ይቀባጥራል : የእግዜርን የአላህን ስም በሐኬት በከንቱ ሲጠራ ይውላል ::

አብይ አህመድ በአንድ በኩል የገዛ ሕዝቡን በ”ሀገር መከላከያ” ሠራዊት በመጨፍጨፍ :  በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ የተንደላቀቀ ቤተመንግስት በማስገንባት ሌት ተቀን  በተጠመደበት በዚህ የሀገራችን የጭንቅ ሰአት : በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት  በድርቅ በጦርነትና በመፈናቀል ምክንያት 36 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን በረሃብ እየተሰቃዩ  ይገኛሉ : በተቀረውም ሀገር ድህነት እየተባባሰ ነው : በከተማ የሚኖሩ ደሞዝተኞች በቂ  ምግብ በልተው ለማደር እጅግ ተቸግረዋል :: በገንዘብ ሚኒስትሩ ሪፖርት መሰረት :  በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በትግራይ በአማራና በአፋር የደረሰውን ውድመት መልሶ  ለማቋቋም ከ28 ቢልዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል :: 

የአብይ አህመድ የ”ብልፅግና” መንግስት : በሁሉም መለኪያ ፍፁም የተበላሸ ሀገር አውዳሚ  መንግስት መሆኑ ጥርት ብሎ እየታየ ነው :: በሀገሪቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች በሙሉ ፤ በሕዝብ ሰላምና መረጋጋት : በኢኮኖሚ ማኔጅመንት : በሕግና ፍትህ : በሕዝብ አስተዳደር : በውጭ ፓሊሲና ዲፕሎማሲ : በሁሉም መስክ ሙሉ በሙሉ ውዳቂ ነው :: 

ጠቅላይሚኒስትር ነኝ ባዩ : በራሱም ሆነ በሌሎች ምክር ለመሻሻልና ስህተቱን ለማረም የሚያስችለው መሰረታዊ የአእምሮ ብቃትም ሆነ : ለሕዝብና ለሀገር የሚያስብ ልብ  በጭራሽ የሌለው CERTIFIED PSYCHOPATH ነው ::  

አብይ አህመድ : ነገ ዛሬ ሳይባል የመንግስት ሃላፊነቱን : በሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎ  ለሚታቀፍ የሽግግር መንግስት ማስረከብ አለበት :: ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማስቀጠልና ሕዝቡን አሁን ከሚታየው የባሰ እልቂት ለማዳን ምንም ሌላ አማራጭ የለም :: 

በአንድ ወፈፌ አምባገነን ማን አለብኝነትና የጥፋት ውርጅብኝ : ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ሊፈርስ አይገባም :: 

ኢትዮጵያዊነት ምን ግዜም አሸናፊ ነው :: ለማሸነፍ ግን : በመሰረታዊ ኢትዮጵያዊ አብሮነትና  እኩልነት : በሕዝብ ሰላም እና የኑሮ መሻሻል ላይ የሚያተኩር : ጥርት ያለ ሀገራዊ እይታና  የማይታጠፍ ፅናት ያስፈልጋል :: 

ኢትዮጵያ : ማንም መደዴ ባለግዜ መሬት ጠብ በማይል አደንቋሪ ፖለቲካ እያፈረሰ እንደገና የሚያቦካት ሀገር መሆኗ : ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲያበቃና ዳግም እንዳይመለስ : በሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎ በሚወለድ ፅኑ መሠረት ላይ መቆም አለባት :: 

ሀገራችን ዝንተአለም የጦርነት አውድማ : ድሃና የፈረንጅ እርጥባን ለማኝ የሆነችው : ምንም ሀገር  በቀል ሀብት ስለሌላት ወይም የሰነፍ ሕዝብ ሀገር ስለሆነች አይደለም :: ታሪኳም ቢሆን እንደሁሉም  የአለም ሀገሮች ልማትም ጥፋትም ያለበት ነው :: ልማቱም ጥፋቱም ደግሞ የሁሉም ማህበረሰብ ድርሻ አለበት :: በኢትዮጵያ የሩቅም የቅርብም ታሪክ : አልሚ ብቻ ወይም አጥፊ ብቻ የሆነ ማህበረሰብ በጭራሽ ኖሮ አያውቅም ::

ኢትዮጵያ የማያቋርጥ የድህነትና የጦርነት አውድማ የሆነችው : በየወቅቱ የሚነሱ ባለግዜዎች : መጥፎውን እያረሙ መልካሙን እያለመለሙ : ኢትዮጵያዊ አብሮነት እና የሕዝብ ኑሮ መሻሻል ላይ ከማተኮር ይልቅ : ለራሳቸው የማያዛልቅ ሥልጣን እና ዘረፋ  እንዲመቻቸው : ሕዝብን በአሰስ ገሰሱ ማናቆርን ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው :: 

ባለፉት ሀምሳ አመታት : በተለይም በወያኔ/ኢህአዲግ ዘመን : ለጥቂቶች የስልጣንና የዘረፋ ፍላጎት  መሳርያነት ሲባል : ሀገሪቱ እንደ ሁሉም አገር ወጣ ገባ በሆነ የታሪክ ሂደት የተዋቀረችበትን ትርክት  ፤ እውነቱንና መልካም ጎኑን ሆን ብሎ በመደበቅ ወይም በመካድ : መጥፎውን በማጋነንና  በፍፁም ሐሰት በአንድ ብሄረሰብ ላይ በመለጠፍ : የሐሰት ትርክት በመጨመር : በሌላው  ሕብረተሰብ መንፈስ ውስጥ እጅግ የተለጠጠ የተበዳይነት የቂምና የጥላቻ መርዝ በመዝራት :  አንድ ሙሉ ትውልድ ለማያባራ ሁከት አዘጋጅተው : ሀገርና ሕዝብ ፍዳቸውን እያዩ ነው ::  

ይህንን የጥፋት አዙሪት ለመግታት : በሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎ ፤ የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል መሰረታዊ ጥይቄዎች በሰፊ ትእግስት በሚገባ በማዳመጥ : በእርቅ መንፈስ : በማስተዋል በሐቅ በእውቀት : ምርቱንና ግርዱን በጋራ በመለየት : በሕዝባችን ዘላቂ ጥቅምና የኑሮ መሻሻል : በእኩልነትና የአብሮነት እሴቶች ላይ በሚያተኩርና : የሚያስፈልገውን ግዜ (ጥቂት አመታት) ወስዶ በሚደራደር ጉባኤ ወደ ጋራ ስምምነት (Grand Bargain) መድረስ ይቻላል :: 

ኢትዮጵያ ውብ ባህልና ቋንቋ ያላችው የብዙ ድንቅ ብሄረሰቦች ሀገር መሆኗ የሚያነጋግር ነገር  አይደለም : በረጅሙ የሀገራችን የታሪክ ጉዞ ሕዝቡ በተለያየ ግዜና በተለያየ ምክንያት  በየአቅጣጫው እየፈለሰ እየተጋመደ መኖሩም የሚያከራክር አይደለም ::  

የዛሬ 49 አመት በ1967 ዓ.ም የታወጀው የመሬት ላራሹ አዋጅና : ከዚያም በኋላ የተደረጉት  ለውጦች : ከነግዙፍ ግድፈቶቻቸው : ቢያንስ በሀገራችን ውስጥ በባላባት መጨቆንን  ማስቀረታቸውና : የብሄረሰቦችን ክብር ባህልና ቋንቋ ከፍ ማድረጋቸው እሙን ነው :: በዚህ ሂደት  ግን ሆን ተብሎ አንድ ትውልድ ሙሉ የተዘራው : በሐሰት ትርክት ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ቂም :  ሀገራችንን ገደል እየከተተ ነው :: 

ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርት እንዲማሩ እንዲተዳደሩና እንዲዳኙ : ባህላቸውን እንዲያዳብሩ : በየአካባቢያቸው የአስተዳደር እርከኖች ራስገዝ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው :: ይህንንም ለዘለቄታው ለማሳካት: ባለፉት ሠላሳ ሁለት አመታት የተኬደበትን ጉዞ ምርቱንና ግርዱን በቅንነት በመመዘን : በሰፊ ብሔራዊ ውይይት : ጥልቅ ጥናትና በሕዝብ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ : የተሻሻለ የፌዴራል ሥርአት አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ፤ ኢትዮጵያችን ውስጥ ማናቸውም ዜጋ : የትም ይወለድ የትም ይደግ : ከየትኛውም ብሄረሰብ ይውጣ : በሕጋዊ መንገድ ከያዘውና ግብር ከሚከፍልበት የግል ይዞታው ውጪበማናቸውም የኢትዮጵያ መሬት ላይ : ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ መብትና : ሌላውን ዜጋ አግላይና ገፊ የሆነ ክልልሊኖረው አይገባም ::

የሁሉም ክፍለሀገሮች እና ብሄረሰቦች ውብ ባህልና ቋንቋ ማበብ : የተመጣጠነ የኢኮኖሚ እድገትና ተጠቃሚነት : በቀዳሚነት በዘር ላይ የተቀረቀረ አናቋሪና አጋዳይ ሕገመንግስት እና : በዘር ላይ ብቻ የተመሰረተ የ”ክልል” አጥር አያሻውም :: ዘር ከፖለቲካ መዋቅሩ ተወግዶ : የማመጣጠኑ ተግባር በኢኮኖሚ በትምህርት በባህልና ቋንቋ እድገት ፖሊሲዎች እንዲያውም በተሻለ ሊተገበር ይችላል ::  ስኬታማ የሆኑ ሕብረብሄራዊ ሀገሮች ያደረጉት ይህንን ነው :: እኛ ሀገር የሰፈነው የዘረኝነት መርዝ በዚያ መልኩ ካልታረመ : መንገዱ ቁልቁለት ብቻ ነው ::  

ሕብረብሄራዊ አብሮነትና እድገት በምኞትና በዲስኩር አይመጣም :: ዘፈኑ የፍቅር ኑሮው በዘር አጥርይሳካል ብሎ ማመን : ያንኑ ቂጣ መላልሰው እየጋገሩ ጣእሙ ይቀየራል ብሎ እንደማመን ያለ “እብደት” ነው :: 

ካሁን ወዲህ በኢትዮጵያ የመንግስት ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ አካል : በኢትዮጵያዊ አብሮነት እና  በሁሉም ብሄረሰቦችና ዜጎች እኩልነት : በሕዝብ ኑሮ መሻሻል : በሰላምና በሕግ የበላይነት ላይ  የሚያተኩር መሆን እለበት :: 

ባለፉት ሃምሳ አመታት ሕዝባችንን ካለማቋረጥ ሲያወናብድና ሲያሰቃይ የኖረውን :  የማንም እንኩቶ በየግዜው እየተነሳ የሚለፍፈውን : ሕዝቡን በሰበብ አስባብ የሚከፋፍል የሚያናቁርና የሚያደኸይ እኩይ ቡትቶ ፖለቲካን በቁርጠኝነት በቃ! በቃ! ለማለት ግዜው አሁን ነው :: 

ሀገራችን ኢትዮጵያ : እንደ ሶማልያ ሶርያና የመን ሀገረ መንግስቷ ፈርሶ : 125 ሚልዮን ሕዝብ ሀገርና መንግስት የለሽ ሆኖ በሚልዮኖች የሚሰደድበት : የተቀረውም የማያባራ የእርስበርስ እልቂትና ስርዓት አልበኝነት (Anarchy) ውስጥ የሚገባበት አደጋ በግልፅ እየታየ ነው :: 

ይህንን አደጋ ለመቀልበስ : ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ : ከልብ መቆርቆርና ባለው አቅም ሀገሩን ለማዳን መታገል : ተደራጅተው የሚታገሉትን እውነተኛ የሕዝብ ወገኖች በጥንቃቄ እየለየ መደገፍ ይጠበቅበታል ::  

እንደዚሁም : የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ኃይል ላይ በግድ የጫነውን አላስፈላጊ ጦርነትና : በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን ፍጅት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲያቆም ከፍተኛ ድምፅ ማሰማት : ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ለሚያሳትፍ  ሀገር አቀፍ የምክክር ሸንጎና ለሽግግር መንግስት የሚደረገውን ጥሪ መደገፍና ማገዝ  እጅግ አስፈላጊ ነው :: 

ከልክ በላይ መታገስ ውጤቱ ሀገር የለሽ መሆን ነው :: 

———- // ———-

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here