spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትደራሲ እና እውነት (ምትኩ አዲሱ)

ደራሲ እና እውነት (ምትኩ አዲሱ)

ደራሲ እና እውነት

[ከ December 16, 2023 የቀጠለ]

በክፍል 1፣ የደራሲ ጥሪ ለእውነት መመስከር ነው አልን፤ ሕዝብን ወደ እውነት (ፍትኅ ውበት አብሮነት) መምራት ነው አልን። ለእውነት ያልታዘዘ ደራሲ ጥሪውን የሳተ፣ ግብዝ ነው አልን። ተስፋዬ ገብረአብና መረጃ አልባ ጽሑፎቹን ተመለከትን። በክፍል 2። ተስፋዬ “ወቅቱ ባመጣው አጀንዳ”፦ በደርግ፣ ቀጥሎ በህወሓት ቀጥሎ በኦሮሞ ፖለቲካ ሲሳተፍ፣ ቋሚ አቋሙ ለኤርትራዊነቱ (ለኤርትራ ፖለቲካ) እንዳደላ አየን። በዚህም፣ ከእውነት ጋር መስማማት የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል የተጓዘበትን ስውር ጠመዝማዛ መንገድ ታዘብን (በአንፃሩ፣ አቤ ጉበኛ፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ በአሉ ግርማ፣ ወዘተ፣ ያሳለፉት ፈተና ይታወሰናል)። የተስፋዬ ተሳትፎ ባለ-3 ገቢር ነው፦ በሻብያና በህወሓት ሠርግና ምላሽ ሰሞን ህወሓትን ማግነን፣ የኦሮሞን ፖለቲካ ለህወሓትና ለሻብያ ዓላማ ማመቻቸት። ህወሓት እና ሻብያ በተለያዩ ማግሥት ደግሞ የኦሮሞን ፖለቲካ ህወሓትን ለማዳከሚያ ማዋሉን አየን። 

በቀጣዩ መጨረሻ ክፍል፣ የተስፋዬን እና የኢትዮጵያዉያንን ሚዛን ያጣ ጠርዘኛ ፖለቲካ እንመለከታለን፦ አለመደማመጥ፣ አለመከባበር፣ ብርሃን ባጣ አውላላ ሜዳ ላይ መርመስመስ፤ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል፣ ተበደልኩ እንጂ አልበደልኩም አካሄዳችንን፤ ማመኻኘት እንጂ ኃላፊነት የማይቀበል ባህላችንን።

በተስፋዬ ውስጥ ራሳችንን እናያለን። በተስፋዬ ላይ የምንበሳጨው ስለምንመሳሰለው፣ ማንነታችንን ስለሚያስታውሰን ነው። በሌላ ሥፍራ እንደ ታዘብኩት፣ ማታለል/ማጋነን ለኢትዮጵያዉያን ሁለተኛ ኃይማኖታችን ነው! ፖለቲከኞቻችን ለምን “የበረሃ ስም” መደረብ አስፈለጋቸው? “እውነት” ልንሰማው የምንሻው ነው፤ ከዘረኛነት ጉድጓድ መውጣት ያቃተን ከህወሓት አስቀድሞ የኖርንበት የኖረብን ስለ ሆነ ነው። በእነዚህ ስድሳ ዓመታት፣ ፈርሃ እግዚአብሔርን ጣልን፣ ክብራችንን ጣልን፤ እርስ በርስ መከባበር መቀባበል መቀራረብ ተሳነን። ለጊዜአዊ ሥልጣን እንጂ ከመንደር ያለፈ ራእይ ለማቆናጠጥ የበቃ መሪ ማፍራት አቃተን። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሰው ሞት መጨፈር፣ የሟችን አስከሬን እንደ ግዳይ ማውለብለብ አይታሰብም ነበር፤ ዛሬ መደበኛ ተደርጓል። የምንኲራራበት ኃይማኖታችን የት ገባ?!

≈∞≈

ወደ “ጫልቱ እንደ ሄለን” እንመለስ። ተስፋዬ ጫልቱን ዋነኛ ገፀባህርይ ማድረጉ፣ ስለ ሰብዓዊ መብቷ ገዶት ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። ጉዳዩ ሰብዓዊ መብት ቢሆን ኖሮ ከኤርትራ ድንበር መውጣት ባላስፈለገው! ለጊዜው ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ፦ የጫልቱ አክስት ወ/ሮ ሙሉመቤት፣ “በአማርኛሽና በንቅሳትሽ አሰቃዩሽ አይደለም?” ትላታለች (ገጽ 85)። እውነቱ ግን፣ ጫልቱ ብቻ ሳትሆን፣ በአማርኛና በንቅሳትማ ከተማ የገባ ሁላ ተሠቃይቷል (ማሠቃየት ባላገርን ማንጓጠጥ ከሆነ!) ጒራጌም፣ ትግሬም፣ ወለየም፣ ከምባታም በአማርኛው ተሠቃይቷል። አማራስ በኦሮምኛው አልተሠቃየም? እንግሊዝኛ ሲሰባብር ኢትዮጵያዊ አልተሠቃየም? ሁለተኛ፣ “በኢትዮጵያ አቆጣጠር” ላለማለት፣ ተስፋዬ “በግዕዝ 

አቆጣጠር” ይለናል (ገጽ 99)፤ ኤርትራን ላለማግለል ይመስላል!

ከፖለቲካ ፍጆታው በተጨማሪ፣ በ “ጫልቱ እንደ ሄለን”፣ ተስፋዬ የኦሮሞ ታሪክ እና ባህል እውቀቱን ለማስመስከር እንዳሰበ ያስታውቃል። ሠላሳ አራት ገጽ ከፈጀ ድርሰት ውስጥ (ከገጽ 66-100)፣ 60 በመቶ ያህሉ (20 ገጾች)፣ ከቊቤ ኦሮምኛ፣ ወደ ግእዝ የተተረጎሙ አባባሎችና ምሳሌዎችን ያካተተ ነው። ተስፋዬ ግን ምሳሌዎቹን መናገርና መተርጎም ቀርቶ ቀላሉን ኦሮምኛ እንደማይችል በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሮ፣ ወደ ፊት ለመግባቢያ ያህል ኦሮምኛ ለመማር እቅድ እንዳለው ገልጾ ነበር። 

በቊንጅናዋ እና በዝናዋ ወደር ያልተገኘላት ይቺ ጫልቱ፣ በ25 ዓመት እድሜዋ ሞተች ይለናል። በ14 ዓመት እድሜ፣ ታዋቂ ፈረስ ጋላቢ ነበረች። ማንም የማይደፍረውን “ጒራቻ” የተሰኘ ፈረስ ሎሻውን የሚይዝ ከጫልቱ ወዲያ አልነበረም። ተስፋዬ የጫልቱን ዝርያ እና ያደገችበትን አካባቢዎች (ሆራ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ወዘተ እያለ) በኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ለመሙላት ሲቻኮል፣ ራሱን እና ቢሾፍቱ ኗሪዎችን በተለይም ኤርትራውያን ቤተ ሰዎቹን እስከ መኖራቸው ረስቶአቸው እንመለከታለን። እውነታው ግን፣ በኢትዮጵያ ቀርቶ በዓለም ዙሪያ ተስፋዬ የሚያውጀው ዓይነት የሕዝቦች አሠፋፈር ታይቶ አያውቅም! በሌላ አነጋገር፣ የመጠን ጉዳይ እንጂ፣ በደምና በባህል፣ በኃይማኖትና በቋንቋ ያልተቀላቀለ ሕዝብ የትም የለም። ጫልቱን ሲያደንቃት ይልቅ፣ ሳያስበው፣ ስብእናዋን አጋንኖ እንመለከታለን፦

ሳቋ ከቱሉ ዲምቱ ተራራ ተጋጭቶ፣ ብልቢሎ ጫካ ላይ ይበተናል። የአድአ ሊበን ሰማይ ላይ ይንሳፈፋል፤ ዳካ አራራ ላይ ይደርሳል። ጠጉሯ ጥቁር፣ እንደ ጉራቻ ጭራ ይዘናፈላል። ጥርሶቿ እንደ አረፋ ያንፀባርቃሉ። ጫልቱ የብልቢሎ ጫካ ንስር ትመስላለች። ከአገጯ የጀመረ ንቅሳቷ እስከ ደረቷ ወርዶ ቀይ ህንዶችን አስመስሎአታል። ቀይ ስለሆነች ንቅሳቷ በጣም ደምቆ ውበቷን ሰገነት ሰቅሎታል። በርግጥም ደረቷን ነፍታ የቆፍቱን ኮረብታዎች ስትጋልብባቸው ለሚመለከት ጫልቱ ዝንተአለም በህይወት የምትኖር የቱሉ ጭቋላ ልዕልት ትመስል ነበር። (ገጽ 69) 

ከላይ በተጠቀሰው ክፍል፣ ተስፋዬ ሳያቅደው ኢትዮጵያውያን ስለ ቊንጅና ያለንን ዕውር ዘረኛ ነውረኛ አመለካከት አንፀባርቋል፦ ከቢዛንቲን እስክንድርያ የወረስነውን የኢየሱስን የማርያምን የመላእክትን ፈረንጃዊ ንጣት ልብ እንበል። ኢየሱስ እና ማርያም አይሁድ ናቸውና በመልክ ከአውሮጳ ይልቅ ለእኛ ይቀርባሉ። መላእክት ሥጋ ለባሽ አይደሉም! የሆሊውድ ፊልም ተፅዕኖም ቀላል አይደለም። ቆንጆ ሴት፣ ቀይ (ህንድ) ፈረንጅ መምሰል አለባት፤ ጠጉሯ ሉጫ፤ አፍንጫዋ ሰልካካ! ወንድ ሲቀላ “እንደ ሴት” ያምራል። ሴቶች ለመቅላት ይቀባባሉ፤ አንዳንዶች ሲቀባቡ፣ በስነ ልቡናቸው መኮሰስ ላይ ጨምረው የቆዳ ህመም ይሸምታሉ። ባጭሩ፣ ጠቆር ጠየም ያሉ ይናቃሉ። ውበትን በነጭ/ቀይ እንጂ በጥቊር ውስጥ እንዳናይ ታውረናል። ምድራችን ግን ምንሊክን፣ መንግሥቱ ኃይለማርያምን፣ አማር አክዌን፣ ሼኽ ኾጀሌን ጨምሮ የጥቋቊሮች የጠያይሞች እና የቀይ ዳማዎች ብዙሓን ምድር ነች! ሀዲስ አለማየሁ፣ በአንፃሩ፣ ጒዱ ካሳ ትምህርቱን እንደ ጨረሰ፣ ባላባት ወላጆቹ፣ አፈረ ጠላቱ የተሰኘች እግር አጣቢ አገልጋይ፣ እንደ ምሳር እንደ ጊደር እንደ ሸለሙት ተርከዋል። 

ጒዱ ካሳም፣ ወላጆቹ ያሰቡለትን የባላባት ልጅ ማግባት ትቶ “ከጥቊረቷ በቀር በቊጥር መልክና በደም ግባት ውብ ናቸው ከሚባሉት ሴቶች የምትወዳደረዋን” እንቆጳዝዮን ብሎ ሰይሞ እንዳገባት፤ በዚህ ምርጫው ዘመዶቹ እንዳገለሉት ተርከዋል። እንቆጳ “ከፍጥረቷ መልከ ቀና፣ የወተት አረፋ የመሰለ ጥርስዋ … ጥቃቅን ውብ አይኖችዋ ከሁለት ጒትቻዎች ገባ ብለው በጨለማ እንደ ተቀመጡ አልማዞች ሲያበሩ፣ እዚህ ግድም የሰው ፊት መኖሩን ከመገመት በቀር አጣርቶ ለማየት የሚያስቸግር ነበር” (ፍቅር እስከ መቃብር፣ ገጽ 330-331፣ 1996 ዓም)። የተስፋዬም የሀዲስም ትረካ ዘመኑ የዘውድ አገዛዝ ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል! 

ሀዲስ ለተስፋዬ፦ ጥቊርም ቆንጆ እኮ ነው የሚል ተግሣጽ እንደ ሠነዘሩ ግልጽ ነው። ተስፋዬ የቀሰቀሰውን የማንነት ብሶት በግራ መጋባት ተክቶ፦ “ሄለንነቷ እንዲህ በንኖ ከጠፋ፤ ወደ ጫልቱነትም መመለስ ካልቻለች ማንን ነው የምትሆነው? ወይም ምንድነው የምትሆነው?” ይለናል (ገጽ 99)። የግራ መጋባቱና የተምታታ ማንነቱ  ፈጣሪ ተስፋዬ እንደ ሆነ አንርሳ! ሀዲስ በአንፃሩ፣ የኖረ፣ ዛሬም ያለ፣ የፆታ፣ የቀለም እና የዘር መድልዎን በሥር ነቀል ሰብዓዊነት አክሽፈውት እንመለከታለን። ኦሮሞ በኦሮሞ ላይ (በጫልቱ)፣ አማራ በአማራ ላይ (በአፈረ ጠላት)፣ አንዱ በሌላው ላይ በደል ማድረሱ እውነት ነው። ሁሉም አገር፣ ሁሉም ቤት እሳት አለ ማለታቸው ነው። ቊምነገሩ ዞሮ ዞሮ፣ ስለ ሰብዓዊነት ማ ተቆጨ? ከጠባብ አመለካከት ማ ተላቀቀ? ማ መፍትሔ አስገኘ? ነው። ተስፋዬ፣ ፈረንጅ መምሰልን እያደነቀ፣ ጫልቱ፣ ሄለን መባሏ ለምን እንዳስከፋው ማወቅ ይቸግራል። የፌስቡክ ትውልድ የፈረንጅ ስም እንደ ከረሜላ ሲሻማ እያየን እኮ ነው!

ተስፋዬ፣ ሀ/ የጫልቱ ንቅሳት ውበቷ ነው ያለንን ዘንግቶ፣ ፈንጠር ብሎ ንቅሳቷ ስቃይዋ እንደ ሆነ ሊያሳምነን ሞክሯል (ገጽ 85)። ንቅሳት (ጥርስን ጨምሮ) በአገራችን፣ ውበት እና ኃይማኖት ያልሆነበት ዘመን የለም። ንቅሳት የጥንት ባህል ነው፤ በፈርዖን ልጆች ዘንድ ይታወቃል። ንቅሳት ዛሬ በነጮች ዘንድ እጅግ መስፋፋቱ ለምንድነው? ለስቃይ ነው? አይደለም፣ ለውበት፣ በንጣታቸው በመቀየም፣ ለትሥሥር፣ ግለ ታሪክን ለመዘከር ነው፤ ለ/ ተስፋዬ ንቅሳትን፣ ከኦሮሞ ስቃይ እና ከአማርኛ ቋንቋ ጋር አያይዞታል! ጥላሁን ገሠሠ፦ አልጠፋልህ ብሎኝ የልቤ ውስጥ እሳት | ጥርሴ እንዲያምር ብዬ ተወጋሁ ንቅሳት፤ ወይም፣ አሻም ያማተቤ፣ አሻም ያደመቶ | አሻም ያኒቂሴ አሻም ያኩለቶ፣ ሲለን። በውበቷ የሰከረ ሌላኛው፦ ንቅሳትሽማ መቊጠሪያ የሚመስለው | ያን ውበትሽን አስበለጠው ከሰው፤ ሲል፦ ውበት እንጂ ዘር አሠቃየኝ ማለታቸው አይደለም። በ “መቊጠሪያ” ጽሞናን፣ ትውስታን፣ ጸሎትና ኃይማኖትን ማጣቀሱ ነው። 

አማርኛ ከቋንቋነት አልፎ እንደ ችግር መታሰቡ ግር ይላል። እንደ ሌላው ሁሉ ቋንቋ፣ መግባቢያና ድልድይ ነው። ኦሮሞው አማርኛ ማወቊ (አማራው ኦሮምኛ ማወቊ)፣ ኑሮን ለማሳካት ብቻ ሳይሆን፣ አሳቡን በማጋራት ውስጥ ስብእናውን ለማጽናት፣ ለጎረቤቱና ለራሱ ሰላምና መተማመንን ለመፍጠር ነው። ተስፋዬ፣ ግማሽ አዲሳባ አማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪ ሆኖ እያለ፦ አማርኛ ለመማር ኦሮምኛ አለመናገር ነው ይለናል፤ ጫልቱ ኦሮምኛ ብቻ የሚናገሩ ዘመዶቿን በአማርኛ እንጂ አላናግራቸው አለች ይለናል። የአገራችን አብዛኛው ሕዝብ በሁለት ሦስት አራት ቋንቋ እንደሚናገር ሊያዘናጋን ይሻል።    

የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በቋንቋቸውና በባህላቸው ኲራት እንዳይሰማቸው ተደርጎ እንደ ነበረ አይካድም። ትምህርት ቤት ለመመዝገብ፣ ሥራ ለመቀጠር ስማቸውን መቀየር የተገደዱ ጥቂት ግለ ሰቦችን አውቃለሁ። ለመሆኑ፣ የዘመኑ ወጣት፣ በህግ ስሙ ላይ የተቀነፈ መጠሪያ ስም ማኖሩ ለምን ይሆን? ተስፋዬም እንደ ጠቀሰው፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሰሚነትና (አንዳንዴም ያልተገባ) ተጽእኖ እንደ ነበራት ግልጽ ነው። በአንፃሩ፣ ኦርቶዶክስ አማራ ሆነው ያልተጠቀሙ ሥፍር ቊጥር የላቸውም። አማርኛ መማር፣ እንግሊዝኛ ኦሮምኛ እንደ መማር፣ ኑሮን ለማሸነፍና እቅድን ለማስፈጸም ከረዳ ማንም ይማረዋል። ካለመማር፣ መማር ይሻላል። እውቀት ጠልነት፣ የኢትዮጵያ ምሑራን መለያ ከሆነ ሦስተኛ ትውልድ ይዘናል። ለዓላማው ሲል አማርኛን፣ ኦሮምኛን፣ ወዘተ፣ ጃፓኑም፣ ቻይናውም፣ ሰይጣኑም ይማረዋል። “ቋንቋን በቋንቋ” በተሰኘው ጽሑፌ (2010 ዓም)፦ አገራችን ወደ ፊት በሚኖራት ፈጣን የኢኮኖሚና የባህል እድገት ጎዳና ላይ ኦሮምኛን አለመማር አማራጭ የለውም ብዬ ነበር። መስጠትና መቀበል መከባበር በሌለበት ጦርነት እንጂ የትኛውም ዓይነት እድገት አይኖርም! ሰላም ያውርድ እንጂ የወደፊቱ አገራዊ እድገታችን ቋንቋዎችን ከማወቅ ጋር የተያያዘ ይሆናል። ተስፋዬ ግን የኢትዮጵያን ግራ መጋባት ውስብስብነቱን የተገነዘበ አይመስልም። 

የኢትዮጵያ ዐቢይ ችግር የኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፤ በዋነኛነት የአሳብ ድህነት ነው። ምንጩም፦ እግዚአብሔርን አለመፍራት፣ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን መካድ፣ በህግ አለመተዳደር፣ ሥልጣን የጠማቸው፣ ብቃት የሌላቸው፣ ድንገት ብቅ የሚሉ ጠበኛ መሪዎች፣ የቀደመውን ሽረው፣ ለውጥ አስመስለው አገርን መለማመጃ ማድረጋቸው ነው። የድህነት መገለጫዎቹ፦ አማራጭ የማይታገስ፣ የማያፈናፍን ርእዮተ ዓለም (ማርክሲስት ሌኒኒዝም፣ የጎሳ ፌዴራሊዝም)፣ የማይጨበጥ ተስፋ (ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ እንመልሳታለን ወይም “ሜክ ኢትዮጵያ ግሬት አጌን”) እና የመሳሰሉት ናቸው። የጫልቱ ታሪክ በዘውድ አገዛዙ ዘመን ነውና፣ በተስፋዬ እይታ፣ የስድሳ ስድስቱ ሶሻሊስት አብዮት ከናንካቴው አልፈነዳም፤ ከንጉሣዊው አገዛዝ በኋላ፣ የደርግ ዘመን ማብቂያና የህወሓት ጎሳ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ምሥረታ ጋ አምጥቶ ይጥለናል። 

የስድሳ ስድስቱ አብዮት፦ በገዛ ባህልና ቋንቋ አለማፈርን፤ የሥራን ክቡርነት በማጽናት፣ በሽመና፣ በአፈር ገፊነት፣ በፋቂነት መኲራትን እንዳቀዳጀ አልታሰበውም። አብዮቱ፣ በታወሩ ግትር የሥልጣን ጥመኞች፣ ዘርን ባማከሉ “ነፃ አውጭዎች” መታመሡ፤ አርሶና አርብቶ አደሩን፣ ባብዛኛው የኦሮሞን ሕዝብ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጡን ከምንም የቆጠረው አይመስልም። 

ተስፋዬ፣ ይህን የሚያክል ጒልህ ስህተት እንዴት ሊፈጽም ቻለ? ምክንያቱ ሁለት ነው፦ መጀመሪያ፣ በውስጠኛ አሳቡ ለእውነት ስላልተገዛ! ለእውነት መመስከር እና ፕሮፓጋንዳ አብረው አይሄዱማ! ሁለተኛ፣ የማህበረ ሰብን ሕይወት በ(ራሱ)መጽሐፍ ገፆች ብቻ ስለ ወሰነው፤ በአንጃ ፖለቲካ ዐይን ብቻ ስለ ቃኘው። አብዛኛው ሕዝብ ማንበብ መፃፍ እንደማይችል፣ የተፃፈውን ገዝቶ ለማንበብ አቅም እንደሌለው፣ ማንበብ ለሚችለው በአቅሙ መጥኖ የሚጽፍለት ደራሲ መታጣቱን አላካተተም። ደጋግሜ፣ ተስፋዬ ውስብስቡን አቀለለው ያልኩት ለዚህ ነው። በሙዚቃ፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብስ ዓለም? በኦርቶዶክስ፣ በእስልምና፣ በካቶሊክ፣ በፕሮቴስታንት፣ በተፈጥሮ ባህላዊ ኃይማኖትስ? በኢኮኖሚና 

በፖለቲካው ምህዳርስ? ይህንን እጅግ ሰፊውን ክፍል አላካተተም! ለምሳሌ፣ የኦሮሞን ሕዝብ የዘመናት በደል በማስወገድ፣ ኃይሌ ፊዳ፣ ደበላ ዲንሳ፣ ዘገየ አስፋው፣ ወዘተ፣ ያበረከቱትን ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ላንጠቅስ እንችልም። ከስፖርቱ፣ አበበ ቢቂላን፣ ደራርቱ ቱሉን፣ ማሞ ወልዴን፣ ጥሩነሽ ዲባባን፣ ወዘተ። ደግሞ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ አበበ ባልቻ፣ ሃይማኖት አለሙ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ወዘተ። ተስፋዬ ስላነሳው እንጂ ይኸ ቊምነገር ሆኖ አይደለም! በሌላ አነጋገር፣ ተስፋዬ ብዙሓኑ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ወላይታ መኃይም በሆነባት ምድር፣ በጣት የሚቆጠሩ ከተሜዎች መጽሐፍ በሚያነቡባት፣ ከሚያነብቡ መሓል ብዙዎች መጽሐፍ መግዣ በሌላቸው ምድርና ዘመን፣ ለትረካው ያመቸውን ያንደኛውን በደል አጋንኖ ያቀርብልናል። 

ከላይ እንዳልኩት፣ የተስፋዬ የደራሲነት ጥሪው አያከራክረንም። ሆኖም፣ ለጥሪው እንዳልተገዛ እንታዘባለን፤ ጥረቱ ብርሃን ከሚፈነጥቅ ይልቅ፣ ድንግዝግዝና ውዥንብርን አበራክቷል። በዚህ ዘመን ለእውነት የተገዙ ስንት ደራሲያንን፣ ስንት የኪነ ጥበብ መሪዎችን መጥቀስ እንችላለን? በአገር ጒዳይ፣ ብርሃን በማጣት፣ በጭለማ የምንርመሰመስ ለምንድነው? ጸሐፍት የመሪነት ጥሪና ኃላፊነታቸውን ችላ ብለው፣ አደባባዩን ላልተገባቸው መቧቸሪያ እንዳደረጉት ይመስለኛል።

≈∞≈

ተስፋዬ ገብረአብ፣ ታኅሣሥ 15/2014 ዓም ናይሮቢ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንዳለ በ 53 ዓመት እድሜው በሞት ተለይቶናል። አራት ቅርስ ትቶልን እንዳለፈ ይመስለኛል፦ 1/ ለበጎ ይሁን ለክፉ፣ የብዕርን (የአስተሳሰብን) ኃይል። በአንደበታችን የምንለዋወጣቸው ቃላት በድርጊት የመተርጎማቸውን ፍጥነት፦ “የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል፣ ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል። ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ” እንዲል ብሉይ (ምሳሌ 18:20-21)፤ “አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው … በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን” እንዲል ሀዲስ (ያዕቆብ 3:5-9)፤ 2/ የሕይወትን አጭርነት፤ ድንገት ኃይል ከድቶ አንደበት በድን ስትሆን፦ “ኮማ” ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞ “ኮማ ውስጥ” የምትል ባለ-10 ገጽ በጅምር የቀረች ረቂቅ፤ (መለስ ዜናዊ ቤልጀም ሆስፒታል በጅምር የቀረ “የአፍሪካ ልማት” የጥናት ሠነድ ትተው አልፈዋል)። ያንኑ ያንኑ ስናወራ ሦስት ትውልድ እንዳባከንን ልብ እንበል! 3/ ተስፋዬ የስደትን ኑሮ አስከፊነት ማየቱና ማሳየቱ። በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ፣ በጦር፣ በጥላቻ፣ በእጦት፣ በክልል ፖለቲካ የመሰደድን መራራነት። ተስፋዬ፣ “ቋሚ መኖሪያህ የት ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፦ “ቋሚ ያልሆነ ሰው ምን ቋሚ መኖሪያ ያስፈልገዋል ብለህ ነው? እስክትሞት ድረስ ዝም ብለህ መኖር ነው (ሳቅ)። ከ 50 ዓመት በኋላ ምን ቋሚ መኖሪያ ያስፈልጋል። አሁን ያለሁበት ስድስት ወር እቆያለሁ (ስቶክሆልም)፤ ከዚያ በኋላ አሜሪካ እሄዳለሁ፤ እንደዚህ ስትል 60 ይገባል፤ በዚያው እድሜዬ አለቀ ማለት ነው። ለእኔ መኖር መጻፍ ብቻ ነው። ስለ ቋሚ መኖሪያ አስቤ አላውቅም” ይለናል። ተስፋ ባጣ አመላለሱ (እንደ ብዙዎቻችን እድሜ ከሃምሳ ከስድሳ ሲያልፍ “እድሜ አለቀ” እንላለን!)። ብርቱ ለመምሰል ቢሞክርም፣ እንደ ማንም ተረጋግቶ መኖር እንደሚሻና ራሱ በሚያውቃቸው ምክንያቶች ኑሮ 

እንዳልተሳካለት እንመለከታለን። (ቢቢሲ አማርኛ፤ ነሐሴ 19/2019)። ከዚህ እንማር ይሆን?

ተስፋዬ ቀጥሎ፣ “የሚናፍቀኝ አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ቢሾፍቱ ሐይቅ፣ ሆራ፣ የአድዓ መልክዓ ምድር፣ ባቦ ጋያና ቦሩ የተባሉ በልጅነት የሮጥኩባቸው መስኮች፣ ሐይቆች፣ እነ በልበላ ወንዝ፣ እነዚህን ድጋሚ ማየት ይናፍቀኛል፣” (ስም አጠራሩን ልብ ይሏል)። የአፄ ኃይለሥላሴ ቢሾፍቱን ደብረዘይት፣ አዳማን ናዝሬት ማሰኘት፣ “ዘእምነገደ ይሁዳ” ንጉሥ ምን ማለት እንደ ሆነ ካልተረሳን በቀር አይደንቅም። ኃይለሥላሴም እኮ ኦሮሞ ናቸው! ከተሞች ደግሞ ከአንድ በላይ መጠሪያ ማግኘታቸው የተለመደ ነው፦ ንውዮርክ (ቢግ አፕል፣ ኤምፓየር ስቴት፣ ወዘተ)፤ ለንደን (ቢግ ስሞክ፣ ኮክኒ ታዎን፣ ወዘተ)፤ ጆሃንስበርግ (ኤጎሊ፣ ጆበርግ)፤ አዲሳባ (ፊንፊኔ፣ ሸገር)። በ “ያልተመለሰው ባቡር” (1988 ዓም)፣ ተስፋዬ፣ ቢሾፍቱን፣ ደብረዘይትም ይላታል። በራሱ መጽሐፍ ውስጥ ኦሮሞ እንኳን ዋነኛ ገፀባህርይ ሊሆን፣ በቅጡም አልተወከለም!) 4/ ምድር ላይ የሚታየውን ክፍፍል እና ጥላቻ፤ ሰማይ ቤት ካለው ፍቅር ጋር አነፃፅሯል፦ “ወደ ሰማይ ስትሄድ ግን እዚህ ያልኖርከውን ፍቅር ነው የምትኖረው” (ቢቢሲ አማርኛ፣ ታህሳስ 28/2021)። ተስፋዬ ወደዚህ ድምዳሜ እንዴት እና መቸ እንደ ደረሰ ማወቅ ይቸግራል። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፦ በተስፋዬ መጽሐፎች ውስጥ በብዙ መልኩ በተደጋጋሚ፣ ጸሎት እና እግዚአብሔር ተጠቅሰዋል፤ “ወደ ኃይማኖት ያዘነበለ ታናሽ ወንድም” ነበረው፤ ጴንጤዎች “እግዚአብሔር ተናገረኝ” የሚሉት ነገር ሁሌ እንዳስገረመው ነው። ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ይዛው የሄደች እህት ነበረች። በ“የደራሲው ማስታወሻ”፦ “ሆላንድ ከገባሁ በኋላ ግን በተለይ በበጋው ወራት የሳምንቱ ማብቂያ ላይ በራሴ መንገድ ጸሎት ማድረስ ጀመርኩ። በምዕራብ ዞይስ መውጫ ከወንዙ ዳርቻ አንዲት ሰው ሠራሽ ኮረብታ አለች። አልፎ አልፎ ወደ ኮረብታዋ ሄጄ ጫፉ ላይ ቁጭ በማለት ጸሎት … የፈጠረኝ አንድ እውቀት ያለው ሃያል አምላክ መኖሩን አምናለሁ” ይለናል (ገጽ 359)፣ ወዘተ። 

ተስፋዬ፣ ስለ መከፋፈል፣ ስለ ጥላቻ፣ ስለ ፍቅር፣ በኋለኛው ዘመኑ ብዙ እንዳሰበበት ግልጽ ነው። ወደ ፍፃሜ ሲቀረብ የተድበሰበሱ፣ በእልኽ የተሄዱ የልብ አሳቦችና የኅሊና ቊስሎች እንደ ክዋክብት ብሩህ ሆነው ብቅ ይላሉ። እሺ ላለ፣ ለንስሃና ለምህረት ያበቃሉ (“ህሊና እንደ አምላክ”፣ የስደተኛው ማስታወሻ፤ ም.34)። 

በጽሑፍ ከተወልን ውጭ ስለ ተስፋዬ የማናውቀው፣ እግዚአብሔር ብቻ በምሕረቱ የሚያውቀው ብዙ ነገር አለ። እርስ በርስ ፍቅርን ግን ለሰማይ አገር አናቆየው፤ ዘመናችን ሳትቆረጥ እዚሁ ቶሎ ቶሎ እንቀባበለው።

© 2023 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here