spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትታሪክን እያጠፉ ፥ ታሪክ ጠባቂ መምሰል 

ታሪክን እያጠፉ ፥ ታሪክ ጠባቂ መምሰል 

አድዋ ዜሮ ዜሮ
የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት (ከማህበራዊ ሚዲያ የተወሰደ)

(ዳዊት አለሙ)

የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው የፕሮጀክቱ ሃላፊ መናገራቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። እግር ጥሎት ፒያሳ፡ ዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ ሰሞኑ የተገኘ ሰውም ይሄን ይመለከታል።

ሙዚየሙ ከሚገኝበት ቅጥር ግቢ በተጭማሪ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ የሚወስደው ወይም ከዚያ የሚነሳው መንገድ ጭምር እየተስተካከል ይገኛል።

ባለፈው አመት ይጠናቀቃል የተባለው እና 4.6 ቢሊዮን ብር ያስወጣል የተባለው (ምን ያህል ተጨማሪ ወጪ እንዳስወጣ ባይታወቅም) ሙዚየም ማለቂያው ላይ እየደረሰ ነው።

በነገራችን ላይ የዚህ ሙዚየም ስያሜ ፡ አድዋ ዜሮ ዜሮ የሚለ መጠሪያ ቀናነት ተጎደለው (ድሉን የሚያኮስስ) ይመስለኛል። የጀግኖች አባቶቻችን የድል ምልክት የሚያስታውሰንን አድዋን ፡ ካልጠፋ ስም ለምን ‘ዜሮ ዜሮ’’ ብሎ መሰየም እንዳስፈለገ አይገባኝም። ደባ ያለብት ሆኖ ይመስለኛል፡ በውስጠ ታዋቂ ስሙን የማሳነስ ፡ የማደብዘዝ አይነት አካሄድ … ለማንኛውም ጊዜ ይፈታዋል።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን ይሄን ሙዚየም ለመስራት የጠፉት ሌሎች ቅርሶችና፡ በአካባቢው በስራ ተሰማርተው የነበሩ ወገኖች ስራ አጥ መሆናቸው እና እንደከተማ/ እንደሃገር እየታየ ያለው አላስፈላጊ የቀለም ቅብ … ሙዚየሙ የሚገባውን ትኩረት እንዳይሰጠው፡ መንግስት ሊያሳምን የሚሞክረውን “ሃገር ግንባታ ውጥን” ስራ ህዝቡ በጥርጣሬ እንዲመለክተው ማድረጉ ነው።

መቼም መልካም መልካሙ የመንግስት ሚዲያዎች ስለሚያዳምቁ ፡ እኛ ደግሞ እንከኑን ፡ የታየውን ክፍተት በማሳየት ለወደፊት መሰል ስራዎች እንዳይደገሙ ወዲህም ደግሞ ለታሪክ ለማስቀመጥ በመጠኑ ችግሮቹን ነቅሰን በማውጣት እናሳይ በሚል ይሄን ከትበናል ፥ መልካም ንባብ።

የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ውጥን ይፋ ሲደረግ አብዛኞቻችን ደስ ብሎን እንደነበር በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በህዝቡ ዘንድ ቅሬታዎች መነሳት የጀምሩት ግን ግንባታው አጋማሹ ላይ ሲደርስ የተወሰዱት ያለተገቡ ርምጃዎች መሆናቸው ማሳሰብ ያስፈልጋል።

በርካቶችን ስራ-አጥ ማደረጉ

እንደሚታወቀው ያራዶቹ መንደር ፒያሳ ለብዙዎቹ የገቢ ማግኛ፡ ሁሉም ባቅሙ ሰርቶ ወደቤቱ ገንዘብ ይዞ የሚገባባት የአዲስ አበባ እንብርት ነች (ነበረች ልበል መሰልኝ) ። ለማሳያ ያህል አሁን በተገነባው የአድዋ ሙዚየም ዙሪያ በርካታ ንግዶች ይካሄዱበት ነበር። 

የመነጽር ፡ የሰአት ፡ የስጦታ እቃ፡ የሞባይል መሽጫና መጠገኛ፡ የሴቶች የመዋቢያ እቃዎች መሽጫ፡ የተለያዩ መጻህፍት በተጣጣኝ ዋጋ የሚገበዩባቸው እንዲሁም ለአመታት ጫማ በማሳመር የሚተዳደሩ ዜጎች ያሉበት ስፍራ ነበር። አሁን ላይ እነዚህ ወገኖቻችን ከዚህ ስፍራ ስለተነሱ በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም። 

ነገር ግን በሰሩት መጠን ያገኙት የነበረ ገቢ ግን መቋረጡን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በነገራችን ላይ አንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲነግድ የነበረ እና በርካታ ደንበኞችን ያፈራን ሰው ከአንድ ቦታ ማንሳት ከስራው እንደማፈናቀል፥ አለፍ ሲልም ከዜሮ እንዲነሳ ማደረግ ነው። ለዚያ ነው ከላይ እንዳነሳሁት ፕሮጀክቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካታ ዜጎችን ለስራ አጥነት ዳርጓል ያልኩት።

ትራንስፖርት ተጥቃሚዎችን ያጉላላ

አድዋ ሙዚየም የተሰራበት ከዚህ ቀደም ሼህ አሊ አላሙዲ ለልማት ተረክበው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ ያላዋሉት ስፍራ ነው፡፡ በኋላ ላይ በቀድሞው ከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደር ከባለሃብቱ የተወሰደው። ይሄ ፕሮጀክት ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞም ፒያሳ አካባቢ ያሉ ወጣቶች ተደራጅተው የመኪና ማቆሚያ (parking) አገልግሎት ይሰጡ ነበር። በወቅቱ የአዲስ አበባን ወጣት ለመደለል የተደረግች ማባበያ ነበር የሚሉ አሉ።

የሆነው ሆኖ በዚህ ሙዚየም ዙሪያ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ታክሲዎች(mid taxi / በተለምዶ mini bus) መነሻ እና መድረሻዎች ነበሩ። 

ለምሳሌ ከሳሪስ/ሚክሲኮ/ቦሌ – ፒያሳ ፥ ከፒያሳ – 22 / መገናኛ ፥ አዲሱ ገበያ/ ሱሉልታ/ ቀጨኔ እንዲሁም ከአስኮ/ ኮልፌ/ አጣና ተራ/ – ፒያሳ የሚደረጉ ጉዞዎች መነሻቸው/መድረሻቸው ይሄ አካባቢ ነበር። አሁን እነዚህ የታክሲ ተራዎች አንዳንዶቹ የቀድሞ አትክልት ተራ አካባቢ ፥ ሌሎቹ የድሮው ማስታወቂ ሚንስቴር እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በላይ የሚገኘው የቴሌ መ/ቤት ሆኗል። 

በዚህ ምክንያት ለምሳሌ ከደቡብ -ቦሌ/ሳሪስ መስመር የሚመጡ ሰዎች ወደ ሰሜን- አዲሱ ገበያ ለመሄድ ከመሃሙድ ሙዚቃ ቤት እስከ ቴሌ ሰሜን ቅርንጫፍ በእግራቸው መሄድ ይጠበቅባቸዋል። በአንጻሩ ከአዲሱ ገበያ ወደ 22/መገናኛ መሄድ የሚፈልጉ ሰዎች በእግራቸው ከቅ/ጊዮርጊስ አደባባይ እስከ ኤሌክትሪክ ህንጻ መጓዝ ይገባቸዋል። 

ችግሩ ሰዎች በእግራቸው ለምን ተጓዙ ለማለት ሳይሆን ፥ ይሄን ያህል ርቀት እንዲጓዙ ማድረግ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ከግምት አለማስገባት አይደለምን ? ለማለት ነው። ምክንያቱም በዚያ በተቆፋፈር ፡ ብዙ ጉድጓዶች ባሉበትና በርካታ አደባባዮችን መሻገር ለእነዚህ ወገኖች አዳፋች ነው።

ለነገሩ የብልጽግና መንግስት ለዜጎች ቁብ የሚሰጠው ቢሆን ከተፈናቃዮች አንስቶ እስከ ህይወታቸው አደጋ ላይ የወደቀ ሰዎችን አስተማማኝ ደህንነት መስጠት ያልቻለ ፥ ህግን ማስፈን ያቃተው /ያልፈለገ መሆኑን በተደጋጋሚ ያስመሰከረ ነው።

ታሪክ አያጠፉ ፥ የታሪክ ጠበቃ መምሰል

በተደጋጋሚ እንደሚባለው፡ በተግባርም እንደተገለጠው የብልጽግና መንግስት ለሚዲያ ፍጆታ እንደሚለው ታሪክ የሚያሳስበው፡ ቅርሶችን የሚጥብቅና ሀገር ለማጽናት እሰራለሁ እንደሚለው ሳይሆን ፥ ቅርሶችን የሚያጠፋ ፣ ታሪክን የሚሽር እና ሃገርን ለስጋት የሚዳርግ መሆኑን በሚገባ አስመስክሯል።

ታሪካዊ እና መንፈሳዊ በአላትን ከማስተጓጎል አንስቶ ፡ ያለ እኔ በጎ ፍቃድ በአል ማክበር አይቻልም እስከማለት የደረሰ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኝ መንግስት ነው።

ከዚህ የአድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ጋር ተያይዞም ይሄ ቅርስና ታሪክን የማጥፋት ስራውን ተያይዞታል። በከተማችን በዘመኑ ሰማይ ጠቀስ የነበረውን የፒያሳ አድባር የሆነው የአራዳ ህንፃን ግራና ቀኝ በማፍረስ የተጀመረ አካሄድ ፡ ቀጥሎ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩትን የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ህንጻና የቴሌ ህንጻዎችን በማፈረስ ታሪክ የማጥፋት ስራውን አጧጡፎታል።

ከዚህ ቀደም ከለገሃር/ስታዲየም እስከ ፒያሳ ያለውን አውራ ጎዳና የማስፋፊያ ፕሮጀክት በሚል ሽፋን በአዲስ አበባ የሚገኙትን እድሜ ጠገቦቹን የአንበሳ ፋርማሲ እና ‘ሰይጣን ቤት’ (በኋላ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት የተባለውን) የማፍረስ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ህዝቡ ባሰማው ተቋውሞ ቴአትር ቤቱ ከፊልሉ ሲፈርስ፡ አንበሳ መድሃኒትን ለጊዜው መታደግ ተችሏል። እኔ ያልኩት ካልሆአ የሚለው አገዛዙ አንድ ቀን ጠዋት ስንነሳ አፍርሶ ሊያሳየን ይችላል።

የከተማዋን ውበት ማደብዘዝ 

በመንግስት ሹመኞች “አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እናደርጋታለን” የሚለው አነጋገር አሁንም ድረስ በተደጋጋሚ ይገለፃል። በእውነት እንደሚሉት ቢያደርጉ ደስ ባለን ፥ ለስራቸውም ተባባሪ በሆንን ነበር። ሆኖም ስራቸው ከሚናገሩት በተቃራኒ እንደሆን በብዙ መንገድ አረጋግጠውልናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ እኮ የአዲስ አበባ ውበቷ እድሜ ጠገቦቹ ህንጻዎቿ ፡ ከተማዋን ለዚህ ያበቁ ነዋሪዎቿ ፡ ታሪካዊ ቅርሶቿ … ናቸው። ታዲያ ቀደምት ነዋሪዎቿን አፈናቅሎ የሚፈልጉትን ማስፈር ፡ ታሪኳን አያጠፉ የታሪክ ተቆርቋሪ መምሰል ብዙም አያስኬድም። 

ይባስ ብሎ አሁን በሚሰራው የአድዋ ሙዚየም ዙሪያ ያሉ የንግድ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግራጫ የመቀባት ስራ ላይ ተጠምደዋል። እንደሚታወሰው ከአንድ አመት በፊት የከተማዋን ህንጻዎች ግራጫ የመቀባት እንቅስቃሴ መጀምሩን ተከትሎ ፡ የኪን ህንፃ ባለሞያዎች ትችታቸውን አቅርበው ነበር። እንደምክንያት የቀረበው ደግሞ ግራጫ ቀለም የድባቴ፡ የጨለምተኛ እና ሃዘን የተጫነው ስሜት የከተማው ነዋሪ ላይ መፍጠር ነው ሲሉ ተደምጥው ነበር። 

ይሄን ተከትሎ ተጀምሮ የነብረው ህንጻዎችን ግራጫ የማደረግ ስራ ለጊዜው ጋብ ብሎ ነበር። ነገር ግን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከላይ እንደተገለጸው ግትር በመሆኑ፡ ጊዜ ጠብቆ አላማውን ተግባራዊ ማድረጉን ተያይዞታል። ጸሃፊው ባደረገው ምልከታ የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ዙሪያ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግድ ሱቆች ኣና ሌሎች ህንጻዎች ግራጫ ተቀብተዋል።

እርግጥ የሙዚየሙ የውጪ ቀለም ወርቃማ ቀለም ነው። ምናልባት ዙሪያውን የከብቡትን ህንጻዎች ግራጫ የተደረጉት የአድዋውን ሙዚየም ለማጉላት ይሆን? ይሄን ያስባለኝ የአራዳ ህንጻና በአካባቢው ያሉት ህንጻዎች የፈረሱት ሙዚየሙን እንዳያደበዝዙት ነው የሚሉ ጭምጭምታዎች በከተማው ይሰሙ ስለነበረ ነው።

ለማንኛውም እንደሚሉን የቅርስ፣ የታሪክና የሃገር ተቆርቋሪዎች ከሆኑ ሳያፈርሱ መስራትን በተግባር ማሳየት አለባቸው። የሌሎች ሃገሮች ታሪክ የሚያስተምረንም ያለውን ጥብቆ ከአዲሱ ጋር ማስማት አሊያም አዲስ አካባቢ አዲስ ከተማ መስራት እንጂ የነበረውን እያጠፉ አዲስ መገንባት ያልተለመደ ፡ ጤናማም ያልሆነ ተግባር ነው።

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here