spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየት“አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ የመጨረሻው ክፍል

“አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ የመጨረሻው ክፍል

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ታኅሣሥ 21 2016

ከጥቂት ወራት በፊት በዚህ ርዕስ ሥር ሶስት ተከታታይ ጽሁፎችን አቅርቤ ነበር፤ ይህ ደግሞ የመጨረሻው ክፍል ነው። በምእራባውያን የዓመት ቆጠራ ሰሌዳ፤ አዲሱ ዓመት ሊመጣ የቀረው ጊዜ ሁለት ቀን ከመሆኑ አንፃር፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና መራሽ መንግሥትና ይህን መንግሥት በጉልበት ለመጣል ትጥቅ አንግበውና፤ በተለይም የተለያዩ ይማህበራዊ ሚድያ የአየር ሞገድ ተቆጣጥረው በምናባቸው 4 ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት የተቃረቡትን ኃይሎች በግርድፉ ይህ ጽሁፍ “ይገመግማል”። 

የፈረንጆቹ 2023 መባቻ ላይ ቆመን፤ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ሁኔታ በግርድፉ ስናይ፤ ኢትዮጵያ አሁንም በግጭት እየተናጠች፤ ሕዝቡብ በኑሮ ውድነት እና በመልካም አስተዳደር ጉድለት እየተናጠ ቢሆንም፤ ብዙ መልካም ነገሮች እና ተስፋ ሰጪ ክስተቶችም የታዩበት ዓመት ነው። በተለየም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አፍላቂነት በገብታ ለሃገር ተጀምረው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች፤ ብዙ አካባቢዎችን የቀየሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ እድል የፈጠሩና ወጣቶች በራሳቸው የግል ሥራ መተዳደር የሚችሉበትን ሁኔታም ያመቻች ከመሆኑ አንፃር ኢኮኖምያዊና ማህበራው ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው። 

ከዚህ ባለፈም ወደ መገባደድ ላይ ያለው የኮይሻ ግድብ ለአካባቢውና ለሃገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፤ የጎርጎራ፤ ወንጪ፤ የሃላላ ኬላ፤ ጨበራ ጩርጩራ፤ ሥራቸው ተጠናቆ ገቢ ለመሰብሰብ የተዘጋጁበትም ወቅት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የተሰሩት አገር አቋራጭ መንገዶች፤ የአዲስ አበባን የተልያዩ ክፍለ ከተሞች የሚያገናኙ ድልድዮች መገንባትና  መጠናቀቅ እንዲሁም የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት፤ በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በ2023 በከፍተኛ ሁኔታ የተሰሩና እየተሰሩ  ያሉ ከፍተኛ ኢኮኖምያዊ ፋይዳ ያላቸው ድርጊቶች ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ፤ የኅዳሴ ግድብ 4ተኛው የውኃ ሙሌት፤ በአዲስ አበባ በቀን ወደ 280 ሺህ የሚጠጋ እንጀራ የሚያመርት የእንጀራ አምራች ድርጅት ሥራ መጀመር አመርቂና በርቱ የሚያሰኝ የ2023 ክንውኖች ናቸው። በአዲስ አበባም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የገበያ ማዕከላት መከፈት ሌላው ኢኮኖምያዊ ፋይዳ ያለው ክንውን ነው። ይህ ሁሉ የሆነው፤ ሃገራችን የተለያዩ ግጭቶችን እያስተናገደች መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን አስደምሟል።  

ሙስናና፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፤ ኢትዮጵያ ካጋጠናት ከፍተኛ ተግዳሮት መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንን ለመቀየር፤ የመንግሥትን ከፍተኛ ትኩረት ከመሻት ባሻገር፤ በተለይ የተለያዩ የዜና አውታሮችና፤ የሲቪክ ድርጅቶች በጽንት ሊሰሩበት የሚገባ ነው። ሕብረተሰቡም የመልካም አስተዳደር ለውጥ እንዲመጣና ሙስናን ከስር መሰረቱ ለመንቀል የራሱን ሚናና ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ሁሉንም ነገር ከመንግሥት ብቻ በመጠበቅ ብዙ ወደፊት መራመድ አይቻልም። ቴክኖሎጂን በመጠቀም፤ ሙሰኞችን ማጋለጥና የሥራ ኃላፊነታቸውን ለህዝብ አገልጋይነት የማያውሉ ልግምተኛ ሹመኞችን አድባባይ በማውጣት በማጋለጥ ዜጎች የዚግነት ኃላፊነትና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብሎ ይህ ፀሃፍ ያምናል። ሃገር ዜጎቿን ትመስላለሽ እንዲሉ ነውና፤ የነቃና መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዜጋ  በግሉ ወይም ሌሎችን በማስተባበር፤ ሃገርን ወደፊት የሚያራምድ ሥራ ይሥራ።     

በተከታታዮቹ ሶስት መጣጥፎች፤ ይህ ፀሃፍ እንዳስነበብው፤ በአሁኑ ስዓት ለሃገራችን ትልቅ ፈተና የሆነው የኦሮሞና የአማራው ጽንፈኛ ኃይል በመሆኑ፤ ይህን ፈተና ለመወጣት መንግሥት የጀመረውን የሰላም ጥሪ እንዲሁም ሕግ የማስከበር ዘመቻ አጠናክሮ በመቀጠል፤ እነዚህ ኃይሎች ለሃግርና ሕዝዝብ ስጋት እንዳይሆኑ ሊያደርግ ይገባል። እነዚህ ኃይሎች፤ ዓላማቸው የማይገባቸውን ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ተግቶ የሚሰራ በመሆኑ፤ የሚፈልገው በሃገሪቱ ከፍተኛ እልቂት እንዲፈጠርና፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ጭፍጨፋ እየተፈፀመ ነው” በሚል ትርከት መእራባውያንን ጣልቃ ገብነት ለመማጸን፤ በዚህም በምእራባውያን ጀርባ ተንጠልጥሎ ወደ ሥልጣን መምጣት ነው። ኈልቱም ኃይሎች የሚተነፍሱት በውጭ ኃይሎች ሳንባ በመሆኑ፤ መንግሥት ሕዝቡን በማወያየትና የመፍትሔው አካል በማድረግ፤ ጽንፈኛው ኃይል በአደብ የሚገዛበትን መንገድ ሊያበጅ ይገባዋል። እነዚህ ኃይሎች፤ “አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ለማቃጠል” ወደ ኋላ የማይሉ ሽብርተኞች በመሆናቸው፤ የአጭር፤ መካከለኛና፤ የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍ፤ በመላ ሃገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት የጀመረውን ዘመቻና የሰላም ጥሪ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።  

በተለይም በአማራ ክልል ጽንፈኛው ኃይል፤ ከፈረንጆቹ ሃምሌ 2023 ጀምሮ የተቀናጀ የትጥቅና የኢኮኖም ጦርነት ከፍቷል። የትጥቅ ትግሉ የሚመራው፤ በሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ሲሆን፤ የኢኮኖሚ ጦርነቱ የተመራው በዶ/ር ዮናስ ብሩ በኩል ነበር። የሻለቃ ዳዊትና የዶ/ር ዮናስ ያልተቀደሰና ያለአቻ ጋብቻ፤ ፍፁም የተዝረከረከ በመሆኑና የሕዝብ መሰረት የሌለው በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን፤ የተከበሩት ሻለቃ ዳዊትና ዶ/ር ዮናስ የፃፏቸውን ጽሁፎች በማጣቀስ ይህ ፀሃፍ ከዚህ በፊት ሞግቷል። ባለፉት ሶስት ጽሁፎች በተለይ ዶ/ር ዮናስ እንዴትና ለምን “አብይን አትንኩ” ከሚለው ካምፕ “ኦሮሙማን” እናጥፋ ወደሚለው ዋልታ ረገጠ እሳቤ ለምን እንደተሻገሩም መረጃ በማጣቀስ፤ እኝህ ሰው፤ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት “ያወጁት” ለሃገርና ለሕዝብ በማሰብ ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፤ እኝህን ሰው ወደ ተባረሩበት የዓለም ባንክ የሥራ ገበታ እንዲመለሱ አልሞከሩም ከሚል ንዴትና ቂም መሆኑንም ራሳቸው ከፃፏቸው ጽሁፎች በመነሳት፤ በሰፊው አቅርብያለሁ። ዶ/ር ዮናስ፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፀእኖ ለመፍጠር ብዙ ቢሞክሩም፤ ምንም አልተሳካላቸውም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ሁኔታ ላይ መሆኑን የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያስታውቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ስዓት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ካሉት ሃገራት በኢኮኖም እድገቷ የቀዳሚነት ቦታውን ይዛለች። በጣም የሚገርመው ደግሞ የእነ ዶ/ር ዮናስ፤ ነዓምን ዘለቀና ሌሎች ፀረ ዲሞክራሲ ኃይሎች ሕልምና ምኞት፤ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ወደ ሃገሩ ገንዘብ እንዳይልክ የማድረግ ዘመቻ ቢሆንም፤ እስካሁን ባለው መረጃ፤ ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ እስካሁን በ.04% ጨምሯል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ላይ የታወጀው የኢኮኖሚ ጦርነት የከሸፈ ጦርነት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

 በአማራ ክልል የትጥቅ ትግሉን ለመጀመር ዝግጅት የተጀመረው ኢትዮጵያ ከሕወሃት መራሹ አማፂ ቡድን ጋር ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው። ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል፤ በፈረንጆቹ ታኅሳስ 7 2023 ባሰፈረው ዘገባ እንዲህ ሲል አስነብቧል።  የፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አስረስ ማረ ዳምጤየህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው በመግባት ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ስቃይ እየፈጸሙ በነበረበት ወቅት ነው ይህ አደረጃጀት [ፋኖ] ነሐሴ 6/2013 .. የተፈጠረው።” ይላል (ድምቀት የተጨመረ)።  ከዚህ የምንረዳው፤ እስካሁን ድረስ እራሱን “ፋኖ” ብሎ በሚጠራው ኃይልና በደጋፊዎቹ “ፋኖ” የትጥቅ ትግል የጀመረው መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት በመምከሩ ነው የሚለው ትርከት ሃሰት መሆኑን ይህ የጊዜ ሰሌዳ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።   

በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው፤ ክለውጡ ጀምሮ፤ የግል ፍላጎታቸውን ከግብ ለማድረስ ተንቀሳቅሰው፤ ፍላጎታቸው ከግብ ሳይደርስ በመቅረቱ፤ በአሁኑ መንግሥት ላይ ቂም ቋጥረው ሲንቀሳቀሱ ለነበሩት ለእነ ሻለቃ ዳዊት ዓይነት ሰዎች፤ ከሕወሃት ጋር የተደረገው ጦርነት፤ ኢትዮጵያን ማጥቃት እንችላለን፤ በአቋራጭም ሥልጣን ለመያዝ እንችላለን ከሚል የቅዠት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃገር ለማዳን በሚሰራበት ጊዜ፤ እነ ሻለቃ ዳዊት በመለመሏቸው የአስተሳሰብ ድኩማን አማካኝነት ሰራዊቱን ከጀርባ የሚወጋ ኃይል በድብቅ ሲያደራጁ የነበረው። ሻለቃ ዳዊት፤ ለኢትዮጵያ የሚበጅ “ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቻለሁ” በሚል ዕቡይ መንፈስ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ፤ ሃሳቤ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ያገኛል የሚል ሕልም ነበራቸው። ይህ “ፍኖተ ካርታ” ውድቅ ሲደረግ ግን፤ ዳዊት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ዘመቻቸውን ጀመሩ። ዓላማዬን ከግብ ያደርስልኛል ብለው ያመኑት ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጥላቻ መንዛትና፤ በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መካክለ ግጭት መፍጠርን ነው። ለዚህም ነው፤ “Time for Machate”, “State Terrorism in Ethiopia”, “A call for reevaluating US Forign Policy”, እንዲሁም “Ethiopia: A Country on the Brinks” በሚል ርእስና ሌሎችም በፃፏቸው ጽሁፎች “ኦሮሞ መጣብህ” የሚል አንድምታ ያለው የሃሰት ትርክታቸውን የሚያሰራጩትና ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት ነው። 

ዳዊት፤ የለውጡን መንግሥት ማጠልሸት የጀመሩት፤ ገና ለውጡ መሬት እረግጦ ጥፍሩ መሬቱን ቆንጥጦ ባልያዛበት ወቅት ነበር። በተለይም ጃዋር መሃመድ ከተባለ ድንክዬ የፖለቲካ ነጋዴ ጋር ዶ/ር ዐብይ በመመሳጠር፤ ኦሮሞ ተኮር መንግሥት ሊያቆቁም እንደሆነ ሳይታክቱ ሻለቃ ዳዊት ሰብከዋል። ጃዋርና ዶ/ር ዐብይ የተለያየ ዓላማና ግብ እንዳላቸው ፍንትው ብሎ በታየበት ጊዜ እንኳን፤ ዳዊት ለሰሩት ከፍተኛ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ይቅርታ ለመጠየቅ እንኳን ድፍረት አልነበራቸውም። ሻለቃ ዳዊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ የጠለሸ ታሪክ ያላቸውና አሁንም በዚህ የሞት አፋፍ እድሜ ላይ ሆነው፤ እርስ በእርስ እንድንባላ የሚደግሱልን መሆናቸው እጅግ ያሳፍራል። እኝህ ሰው ለክህደት አዲስ አይደሉም፤ “Red Tears” በሚለው መጽሐፋቸው፤ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ዘራፊና ጨፍጫፊ አድርገው በመሳል፤ ለሻዕብያ የፕርፖጋንዳ ክንፍ ከፍተኛ ውለታ ሰርተዋል። ሻዕብያ “የወቅቱ የኢርትራ አስተዳዳሪ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ደርግ የፈፀመውን ግፍ እማኝነታቸውን ተናዘዙ” በሚል መጽሐፉን ለፕሮፖጋንዳ ከመጠቀሙም በላይ፤ በኤርትራ ለነበሩ በሻዕብያ ለተማረኩ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ስቃይና ሞት አንዱ ምክንያት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ የክህደት ባሕሪያቸውም ነው፤ እኝህ ሰው የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባ ለማስወጋት፤ ከወያኔ ጋር በውግያ ላይ ሆነን፤ ጽንፈኛውን ኃይል ሲያስታጥቁና ለጦርነት ሲያዘጋጁ የነበሩት። ሻለቃው የሰሩት የተሳሳተ ሥሌት ግን የዶ/ር ዐብይን ትዕግስትና፤ የግጭት የፖለቲካ ባሕላችንን ለመቀየር የሚያደርጉትን ሙከራ እንደ ደካማነት በማየታቸው ነው። 

የአማራ ሕዝብና ሌላውም ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት ምንም አጠያያቂ አይደለም። ማንም ግን ጥያቄውን ሊያቀብ የሚገባው በሰላምና ሕጋዊ መድረኮችን በመጠቀም ብቻ ሊሆን ሲገባው፤ ነፍጥ አንስቶ “ጥያቄ አስመልሳለሁ” የሚል ማንኛውም ኃይል በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። በአማራው ሕዝባችን ላይ የሕወሃት መራሹ መንግሥትና ከለውጡም በኋላ የኦሮሞ ጽንፈኞች ከፍተኛ ጥቃት ፈጽመውበታል። ከለውጡ በኋላም በኦሮሞ ጽንፈኞች በአማራው ሕዝባችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለማስቆም፤ መንግሥት በወቅቱ በነበረው አቅም ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበትም፤ በኦሮምያ ክልል ባለው የአመራር ግድፈትና በጽንፍ በተሰለፉ የክልሉ ባለሥልጣናት ተንኮል ብዙ ውጤታማ ሳይሆን መቆየቱ አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን ማንም አርቆ ማሰብ የሚችል ሰው፤ ይህንን የኦሮሞ ጽንፈኛ ኃይል የሚዋጋን የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባው መውጋት አማራጭ መፍትሔ ነው ብሎ ሊያስብ አይችልም። እንደ ሻለቃ ዳዊት ዓይነት ሰዎች ለማንም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እኝህ ሰው ለብዙ ሴቶች፤ ኅጻናትና አዛውንቶች ከፍተኛ ሞት ምክንያት የሆኑ ሰው ናቸው። አሁንም ሃገር ውስጥ ትርምስ በመፍጠርና “ዘር ማጥፋት” እየተፈፀመ ነው በሚል ትርክት በፈረንጆቹ ታዝለው ውደ ቤተ መንግሥት የመግባት ቅዠት ውስጥ በመሆናቸው ነው ዛሬም የጥፋት በትራቸውን ያነሱት። እኝህ ሰው ግን እንደፈለጉ ቢንፈራገጡ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ዛሬም የሚሰሩት ሥራ ‘ጣቱን የሚጠባ ኅጻን የማይሰራውን ሥራ ነው’። በቅርቡ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፤ ምኞትን መከላከል አይቻልም። ምንም እንኳን የጽንፈኛው የፕሮፖጋንዳ ማሽን፤ ጽንፈኛው ኃይል የሕዝብ መሰረት አለው ብሎ ቢለፍፍም፤ ሃቁ ግን፤ ይህ ኃይል ከሕዝብ የተነጠለ፤ ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብለው አጥቶ በየጥሻው የሚንከራተት የሽፍታ ቡድን ሆኗል። 

የአማራ ጽንፈኛና የአማራ ሕዝብ ለየቅል ናቸው።

በየብሔር/ብሔረሰቡ ምንም ፈሪሃ እግዚአብሔርም ይሁን ስብእና የሚባል ነገር የሌለው ዋልታ ረገጥ ጽንፈኛ ቡድን አለ። ይህ ጽንፈኛ ቡድን የሚወጣበትን ብሔረስብ እወክላለሁ እያለ ቢደሰኩርም፤ የሚሰራው ሥራ ግን የወጣበትን ብሔረስብ የሚጎዳ ጨካኝና ነውረኛ መሆኑን ነው የሚያሳብቀው። ከሕወሃት ጋር በተደረገው ጦርነት፤ በሕወሃት መንጋና መንጋውን ተከትሎ በመጣ የትግራይ ወጣትና አዛውንት በአማራ ክልል ከፍተኛ በደል መፈፀሙን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። የትግራይ ሰራዊት ከአማራ ክልል ተቀጥቅጦ ከወጣ በኋላና ትግራይ ውስጥ ከመሸገ በኋላ ግን፤ ከትግራይ ክልል እየሸሸ ወደ አማራ ክልል ተሰዶ የመጣውን ትግራዋይ፤ የአማራ ሕዝብ በሚገርምና በሚያስደምም ሁኔታ አቅፎ ተቀብሎ፤ መጠለያ፤ ምግብና አልባሳት ሰጥቶ አኑሮታል። ይህ አለምን ያስደመመ ጨዋነት እና ትልቅነት ከጽንፈኛው ቡድን ነውረኛ ድርጊት ጋር ሲነፃጸር የሰማይና የምድርን ያክል ልዩነት አለው። ጽንፈኛው በሃሳብ ከእሱ የተለዩትን እንደ አቶ ግርማ የሺጥላ ዓይነት የሕዝብ ልጆችን በጠራራ ፀሃይ ገድሏል። የባሕር ዳር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩትን “የሰላም ዲፕሎማት” ተብለው የሚታወቁትን” አቶ ቤንጃሚን ወንዴን፤ የሽዋ ሮቢት ከንቲባን አቶ ውብሸት አያሌውን፤ የባሕር ዳር ፖሊስ መምርያ ሹም የነበሩትን ኮማንደር ዋጋው ታረቀኝ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በአደባባይ ገድሏል። በጣም የሚያሳዝነው፤ በዚህ የግድያ ሂደት፤ በፖለቲካ ውስጥ ምንም ድርሻ የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት አጥፍቷል። ይህ የፈሪ ቡድን፤ የፈሪ በትሩን ሲሰነዝር ሰላማዊ ሰዎችንም ገድሏል። ከአቶ ግርማ የሺጥላ ጋር የነበሩ ከአምስት በላይ ሰዎች ሹፊራቸውን ጨምሮ ይህ የጥፋት ቡድን ገድሏል። የአቶ ግርማ ታዳጊ ወጣት ልጃቸውና ባለቤታቸው በነበሩበት መኪና ውስጥ ነው፤ የዚህ የአረመኔ ቡድን የጥይት እሩምታውን የለቀቀው። የሽዋ ሮቢት ከተማ ከንቲባ፤ የመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቦምብ ተጥሎ ነው የተገደሉት። ከዚህ በተጨማሪ በባሕር ዳር ከተማ በተደጋጋሚ በጽንፈኛው ኃይል በተወረወረ ቦምብ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተጎድተዋል፤ ተገለዋልም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምንሰማው፤ ይህ እነ ሻለቃ ዳዊት ያደራጁት ኃይል፤ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቦምብ እየጣለ ይገኛል።

የፌደራል መንግሥቱ ከሕወሃት ጋር በጦርነት ውስጥ ገብቶ በነበረበት ጊዜ፤ በነሐሴ 2013 (August 2021) እራሱን በፋኖ ስም ፍኖተ ሰላም ውስጥ ያደራጀው ሻለቃ ዳዊት መራሹ የነፍሰ ገዳይ ቡድን፤ የፌደራል መንግስቱን በጉልበት ከሥልጣን አወርዳለሁ በሚል ትዕቢት ነበር፤ በርካታ ፀረ ሕዝብና አደገኛ እርምጃዎችን ይወስድ የነበረው። በወቅቱ፤ ከሕወሃት ጋር የነበረውን ጦርነት ለመቋጨት በነበረው አጣዳፊ ጉዳይ ምክንያት ለዚህ የነፍሰ ገዳይ ቡድን ብዙ ትኩርት አልተሰጠውም ነበር። ለዚህም ነው አቶ ግርማ የሺጥላ፤ “የሚቀድም ጉዳይ ስለነበረን፤ ከጀርባ እየወጉን በዝምታ ያለፍናቸው ከጅብ ጋር ጎን ለጎን እየተራመድን ነበር” ያሉት። የአማራ ክልል መንግሥትና የፌደራል መንግሥቱ፤ እራሱን በትጥቅ ባደራጀው የአማራ ፅንፈኛ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፤ ችግሩን በሽማግሌ ለመፍታት ተደጋጋሚ ሙከራ እንዳደረገ፤ በርካታ ቪድዮዎች ተለቀዋል። ሆኖም የዚህ ጽንፈኛ ኃይል ፕሮፖጋንዲስቶች፤ “ጦረኛው መንግሥት” ብለው በመንግሥት ላይ ሊሳለቁ ሲሞክሩ ማየት ሕዝብን ለማደናገር የማይተኙ መሆናቸውን ያሳብቃል።

የሽምግልና ሂደቱ ፍርሃት የመሰለው ጽንፈኛ ኃይል ግን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲገዘገዝ በኖረው የሻለቃ ዳዊት እና በሃገር ውስጥ በመለመሏቸው ግብረ አበሮች፤ አይዟችሁ እየተባሉ፤ ስለተበረታቱ የጥፋት መንገዱን ቀጠሉበት። በተለይም፤ የፌደራል መንግሥቱ የየክልል ልዩ ኃይሉን በተለያዩ የሃገሪቱና የየክልሉ የጸጥታ መዋቀር ውስጥ ለማካተት በማቀድ በወሰደው እርምጃ፡ በተለይ በውጭ የሚኖረው ጽንፈኛ ኃይል፤ “የኦሮሞ መንግሥት፤ የአማራን ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታታ የሸረበው ሴራ ነው” በሚል የሃሰት ፕሮፖጋንዳ፤ አልተሳካም እንጂ፤ የአማራ ልዩ ኃይልን ከነትጥቁ በማስኮብለል፤ ከጽንፈኛው ኃይል ጋር እንዲቀላቀል፤ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል። በእነዚህ የእናት ጡት ነካሾች የሃሰት ትርከት፤ በተጀመረ ግጭት፤ በሕዝብ ላይ ጉዳት በመድረሱ፤ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት እርምጃ መውሰድ ሲጀምር፤ ትላንት “ኢትዮጵያ” እያለ ሲደሰኩር የነበረ ጽንፈኛ ሁሉ ጭምብሉ ወልቆ፤ የጎጡ ብብት ውስጥ ተሸጉጦ፤ “በአማራ ክልል ውስጥ እንዴት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል” ማለት ጀመረ። ትላንት ኦሮምያ፤ ሲዳማ፤ ቤኒሻንጉል፤ ጋምቤላ፤ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ መንግሥት ሕግ ያስከብር፤ መንግሥት ሕግ ለማስከበር አቅም የለውም ደካማ ነው፤ እያለ ሲወተውት የነበረ ሁሉ፤ አማራ ክልል ያ ሁሉ ባለሥልጣን በጽንፈኛው ተገድሎ፤ ጽንፈኛው ኬላ እያበጀ ሕዝብን ያለ አግባብ ሲዘርፍና፤ የፌደራል መንግስቱን በጉልበት ከሥልጣን እናወርዳለን የሚል እንጭጭ እና ጨካኝ ቡድን ክልሉን ሲያተራምስ፤ እንዳላየ በማለፈ፤ ከወያኔ የፖለቲካ ደብተር ላይ የወሰዷትን “ጄኖሳይድ” የሚል ቃል  “የአማራ ጄኖሳይድ” የሚል ትርከታቸውን በየቻሉት ማህበራዊ ሚድያ ላይ ያሰራጩ ጀመር።

እነ  ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስም፤ የማይዋጉበትን ጦርነት ለኩሰው፤ ገንዘብ ወደ መሰብሰብ ዘመቻቸው ቀና ደፋ ማለትን ተያያዙት። ችግር ባለበት ክልል ሁሉ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከተደረገ፤ ግድያና የቦምብ ፍንዳታ በበረከተበት የአማራ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ የማይደረግበት ምክንያት ምንድን እንደሆነ ሊነግሩን አልሞከሩም። እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው ሰላም አይደለም። በሃገር ውስጥ ሰላም ለማስፈን  ከተፈለገ የፌደራል መንግስቱን በጉልበቴ ከሥልጣን አወርዳለሁ ያለ ቡድን በዝምታ መታለፍ እንደሌለበትም ሳያውቁ ቀርተው አይደለም። ትላንት በተለያዩ ጽሁፎቻቸው፤ መንግሥት ደካማ ነው ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን አልተወጣም ይሉን የነበሩ ጨለምተኞች፤ በአማራ ሕዝብ ስም ለመነገድ ታጥቀው መነሳት ብቻ ሳይሆን፤ የአማራን ሕዝብ ከወንድሙ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለማጋደል የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ግን አልተሳካም። የአማራ ክልል ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው። ትላንት በጦርነት የደቀቀ ኢኮኖሚው እንዲንሰራራ ነው የሚፈልገው። እነ ሻለቃ ዳዊት የሚፈልጉት ገን ኢትዮጵያ ውስጥ የደም መሬት ነው። “አንድን ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” አዋጪ ነው ብለው በማመን፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ተገትው የሚሰሩት።

ይህንንም ከግብ ለማድረስ፤ ጽንፈኛው ኃይል፤ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ ለሚፈልጉ፤ ለእንደ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ዓይነት ከሃዲዎች መሳሪያ በመሆን፤ አማራውን ይገላል፤ የአማራን ሕዝብ ልማት ያደናቅፋል፤ የአማራን ሕዝብ ሰላም ይነሳል። ምስኪኑ የአማራ ወጣት፤ እነ ዳዊት በደገሱለት የሞት ቱቦ ውስጥ ይገባል። በእሱ ሥም ይነገዳል፤ ገንዘብ ይሰበሰባል። ጽንፈኛው ኃይል እራሱ  ረግጦ የሚገዛት ኢትዮጵያ እውን ካልሆነች በቀር፤ በሃገር ውስጥ ሰላም እንዲኖር አይፈልግም። በዚህ ቅዠት ውስጥ ያሉት ኃይሎች፤ ምንም አቅም የላቸውም፤ አቅማቸው የሚቆጣጠሩት የማኅበራዊ ሚድያ ላይ መፎከር፤ መዋሸት፤ ሌላውን ማሸማቀቅና ደጋፊዎቻችውን “የተስፋ ዳቦ” መመገብ ነው። የእነዚህ ኃይሎች አቅምና ጡንቻ ምላሳቸው ላይ ብቻ መሆኑን መሬት ላይ ያለው እውነታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
                 

በተለይም ኦሮሞውን ከአማራው ጋር በማጋጨት፤ ሕዝቡን በደም ለማቃባትና፤ ከደም መሬት የሚነክሩትን የደም ጨርቅ በአውሮፓና በአሜሪካ በማውለብለብ፤ የነጭ ጌቶቻችውን ጫማ ስመው ወደ ሥልጣን እንመጣለን ብለው ሌት ተቀን ይቃዣሉ። ምንም ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው በአማራ ኅፃናት ሕይወት ቁማር የሚጫወቱ አረመኔዎች ናቸው። ወንድሞቻቸውን ገድለው በአደባባይ የሚፎክሩ እነዚህ አረመኔዎች የአማራን ሕዝብ ፍፁም አይመጥኑም፡ ግን በሥሙ ግን ይነግዳሉ። በበረት ስባሪው፤ ጽንፈኛ ቡድን፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ነጭ ሽብር፤ በሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ፊታውራሪነትና፤ በዶ/ር ዮናስ ብሩ ሹም ባሻነት የሚመራ፤ የቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ስብስብ ለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ፤ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሰበቁት የኢኮኖሚ ጦርነት፤ እንደ ጉም እየተነነ መሄዱን እየመሰከርን ነው። በአማራ ክልል ላይ ያለው፤ የጽንፈኞች የነጭ ሽብርም፤ የመንግሥት ሹመኞችን ጨለማን ተገን አድርጎ ከመግደል ባለፈ የፈየደው ነገር የለም። የእነዚህ ኃይሎች ጩኸት እያደነቆረን ያለው በማህበራዊ ሚድያዎች ፉከራና ሽለላ ነው። እራሳቸውን “የአማራ ድምጽ” ነን እያሉ በሚጠሩ፤ እውቀት አልቦ ቱልቱላዎችና (የዶ/ር ዮናስን ቃል ለመጠቀም) ቱቱ ቡቱቱዎች፤ እንኳን ለአማራ ድምጽ ሊሆኑ ይቅርና፤ የአማራ ሕዝብ የውስጥ እግር እሳት ከሆኑ ውለው አድረዋል። እነዚህ በእውቀት ጠኔ የተመቱ የእውቀት ረሃብተኞች፤ እራሳቸውን አግዝፈው ይመልከቱ እንጂ፤ ማንም ከቁብ አይቆጥራቸውም። በምናባቸው የሚያዩት ብዙ የአማራን ክልል ምድር የተቆጣጠረ ኃይል አለ። ምድር ላይ ግን ያረጀ መሳሪያ ከሚያወዛውዝ፤ አዛውንትን፤ ሴቶችንና ኅጻናትን እያስፈራራ፤ ገመድ ወጥሮ “ቀረጥ የሚቀርጥ” የሰፈር ወመኔ ባለፈ፤ ከመከላከያ ጋር ሊወዳደር የሚችል አቅም ያለው የለም። ይህ የወመኔ ጥርቅም፤ አደብ እንዲገዛና፤ የሕዝቡን ሰላም እንዳያውክ፤ ጥሪ እየተደረገለት ነው። የዚህ የወመኔ ቡድንና፤ ዋሽንግተን ተቀምጠው የሚሸቅጡበት ጨካኞች ግንኙነታቸው በጥቅም የተሳሰረ ነው። ወመኔው፤ ተደብቆ ሰው እየገደለ ክልሉን ሰላም ይነሳል፤ የደም ነጋዴው ደግሞ በስሙ ገንዘብ ይሰበስብበታል። 

የዚህ የነጭ ሽብር ዋና አቀናባሪ፤ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ መሆናቸው ማንንም አያስደነግጥም። እኝህ ሰው በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ሲነግዱ የነበሩ፤ በውስጣቸው ሃፍረት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ፈሪና ጨካኝ ሰው ናቸው። እኝህ የሲአየኤ የጡት ልጅ፤ እሳቸው አባል የነበሩበትን የወታደራዊ መንግሥት ፈንቅለው፤ የሃገሪቱ “ገዥ” ለመሆን በነበራቸው ቅዠት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለጠኔ የዳረጉ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ሬከርድ እንደሚያሳየው፤ በ1981 (እ.አ.አ) ጠኔ በኢትዮጵያ ተከስቶ እያለ፤ እኝህ ሰው ይመሩት የነበረው የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮምሽን፤ የዚህን ጠኔ አጣዳፊነት ዜና ለተባበሩት መንግሥታት ያቀረቡት ዘግይተው ብቻ ሳይሆን፤ የረሃብተኛውን ሰው ቁጥርና የሚያስፈልገውን የምግብ ዕርዳታ መጠን በግማሽ አሳንሰው ነበር። ይህ የሆነበት በአጋጣሚ አልነበረም፤ ይህ የሆነው፤ ረሃብን ለፖለቲካ ለመጠቀም በሲአይኤ ታቅዶና ተጠንቶ የቀረበ ዓላማ ነበር። ዓፄ ኃይለሥላሴን ከሥልጣን እንዲነሱ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት የወሎ ረኃብ እንደሆነ፤ ለምዕራባውያኑ  ግልጽ ነው። ለዚህም ነው፤ በ1981 (እ.አ.አ) የተከሰተው ጠኔ ለሶስት ዓመታት እርዳታ ሳይገባ፤ ሕዝባችን በጠኔ እንዲቆላ የተደረገው። እኝህ ሰው የአመራር ብቃት ያልነበራቸው ንዝህላል ብቻ ሳይሆኑ፤ ሕሊናቸውን ለጥቅም የሸጡ፤ ሕዝባቸውን በርሃብ ያስፈጁና የፈጁ፤ በወንጀል መጠየቅ የሚገባቸው ሰው ናቸው። ትላንት፤ በሚሊዮን የሚቆጠረውን የአማራን እና የትግራይ ሕዝብ በጠኔ እንዲፈጅ ዋና ተዋናይ የነበሩ ሰው፤ ዛሬ ለአማራ ሕዝብ “ነፃነት” በሚል ሸፍጥ በአማራ ክልል የጦርነት እሳት እንዲወርድ ቀና ደፋ ማለታቸው ገራሚ ብቻ ሳይሆን፤ ውሻን ወደ እርሻ እንደመላክ ዓይነት ዘግናኝ እሳቤ ነው።

እኝህ ሰው ወታደርም፤ አመራርም ዲፕሎፕትም ሆነው በከፍተኛ ኃላፊነት የሰሩ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የመከላከያ ሰራዊቱ፤ ከሻዕቢያ ጋር ያደረገውን ትንቅንቅና የከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት በናቀና ባዋረደ መልኩ፤ ሻለቃ ዳዊት የሻዕብያውን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን “የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት” እንዲሆኑ የተማጸኑ ሰው ናቸው። ይህንን አሳዛኝና ተንበርካኪ ባህሪ፤ “የነፃ ወታደሮች ንቅናቄ” በሚል ስም በተቋቋመው ቡድን ውስጥ፤ ከሻለቃ ዳዊት ጋር አብረው ሲሰሩ የነበሩት ሻለቃ ስለሺ “አንድነት በአንድነት” በሚለው መጽሃፋቸው በስፊው ጽፈውታል። በነገራችን ላይ “የነፃ ወታደሮች ንቅናቄ” የተባለው ቡድን፤ ሻለቃ ዳዊት ከደርግ ከመክዳታቸው በፊት ቦስተን ውስጥ የተቋቋመ፤ በኋላ ግን በሲ አይ ኤ ትከሻ ላይ ተንጠልጠለው፤ ሻለቃ ዳዊት የጠለፉት ድርጅት መሆኑንና እኝህ ሰው የወታደሮቹን ትግል እንዴት እንዳኮላሹት “ከበደ በለው” የተባሉ ሰው “ለመሆኑ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ማነው?” በሚል ርዕስ ከስድስት ዓመታት በፊት በፃፉት ጽሁፍ አስነብበውናል። (ማንበብ ለምትፈልጉ፡ http://assimba.org/Articles/Shaleka-dawit-malew20170618.pdf ). እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ ሻለቃ ዳዊት ለራሳቸው የግል ጥቅም ከመታተር ውጭ፤ ሲሰሯቸው የነበሩት ሁሉ ሕዝብን ለአደጋ ያጋለጠና አፍራሽ መሆኑን ነው። ምናልባትም በኤርትራ ውስጥ አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ ለሰሩት ሥራ ፀፀት በሚመስል መልኩ “ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያንን ለማቀራረብ” የሰሩት ሥራ በብጎ ቢታሰብም፤ ከበስተጀርባው ምን እንደተጠመደ ግን ለማወቅ እራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል።  

የአማራ ወያኔ፤ የፀረ ኢትዮጵያ እቅድ፤

==============================

ከ15 ዓመታት ገደማ በፊት፤ (ነፍሳቸውን ይማርና) ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕወኃት በሕዝብ ላይ በሚፈፅመው በደል፤ የትግራይን ሕዝብ ተጠያቂ ለማድረግ በፃፉት ጽሁፍ፤ አቡጊዳ በተባለ ድኅረ ገጽ ላይ ለእሳቸው በሰጠሁት መልስ፤ ሕወኃት በሚፈጽመው ግፍ፤ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው በተለየ ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት እንደሌለና፤ ከሕወሃት ጋር ጡት ተጣብቶ፤ ኢትዮጵያን እየመዘበረና፤ ወያኔ የሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ በሕዝብ ላይ በደል የሚፈጽም፤ የአማራ፤ የኦሮሞና’ የደቡብ ሕዝብ “ወያኔዎችም” በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ ያሉትን ግፍና በደል ተጠያቂ አለማድረግ ተገቢ አይደለም የሚል መልስ ሰጥቻቸው ነበር። ዛሬ የአማራው ወያኔ፤ ዓላማውን በመሪው በሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በኩል ግልጽ አድርጎታል:: ዳዊት አማራው የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ፤ ሌላው ደግሞ የእንጀራ ልጅ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ነግረውናል። ሙሉውን ማዳመጥ ለሚፈልጉ፡ https://www.youtube.com/watch?v=k6ldn3gXt24

እኝህ እድሜ ጠገብ ሰው ግን በሃሳብ የቀነጨሩ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያን የደም ባሕር ለማድረግ ተግተው ሲሰሩ ቆይተዋል። አልተሳካላቸውም፤ እንጂ ጊዜው “የቆንጨራ” ነው በሚለው ከ4 ዓመታት በፊት በፃፉት አገር አጥፊ ጽሁፍ፤ ጦርነትን ቀስቀሰው ደም ሊያፋስሡ ሞክረዋል፤ አድማጫ በማጣታቸው አልተሳካም። አሁን ደግሞ የአማራ ወጣቶችን በተሳሳተ እሳቤ እየቀሰቀሱ ወደ ጦርነት አስገብተው፤ ለብዙ ደሃ ገበሬ ልጆች ሞት ምክንያት ሆነዋል። እኝህ ሰው በሃምሌ 20፣ 2015 እራሳቸው ባቋቋሙት የአማራ ሚድያ በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ፤ ዓላማቸውን 4 ኪሎ ለመግባትና አማራን ማዕከል ያደረገ መንግሥት ለመገንባት መሆኑን ነግረውናል። እንደሳቸው እምነት፤ ሌላው ኢትዮጵያ ምድር የተፈጠረው ሕዝብ፤ አማራን ለማገልገል የተፈጠረ እንጂ፤ ለሃገር ግንባታው ምንም አስተዋጽኦ የለውም፤ በኢትዮጵያ እድል ላይ የመወሰን መብትም የለውም። እኝህ የሃሳብ ጮርቃ የሆኑ ሰው፤ “ኢትዮጵያን የገነባው አማራ ነው” “ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ አማራ ነው” ኢትዮጵያን Define ያደረገው አማራ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፤ የአክሱም ሥርወ መንግሥትን፤ በምናባቸው ጎንደር ወይም ባሕር ዳር ተክለውታል። ይህንን ተረት ተረት “እየሰበኩ ነው” ወጣቱን ወደ ማገዶ የሚልኩት። በቀይ ሽብር ወቅት፤ የዳዊት ወልደጊዮርጊስ ጓደኛና የሥራ ባልደረባየነበሩት፤ መላኩ ተፈራ የተባለ ጨካኝ፤ የጎንደርን ወጣቶች በአደባባይ ሲሰቅልና ሲረሽን፤ የአማራ እናቶች እንዲህ ብለው ነበር። 

“መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም፤

የዛሬን ተውልኝ ሁለተኛ አልወልድም።”  

ዳዊትም ልክ እንደ ጓደኛቸው፤ ይህ ጥቁር ታሪክ እንዲድገም ተግተው እየሰሩ ነው። የአማራን ወጣት ወደ ሞት እየገፉ፤ ለበርካታ ወጣቶች ሞት ምክንያት ሆነዋል። ነገም ይህ እሮሮ እንዳይደገም፤ የጦርነት ታምቡር የሚመቱ ሰዎች አደብ ሊገዙ ይገባል። ይህ ፀሃፍ በተደጋጋሚ እንደጠቀሰው፤ በአማራ ሥም የሚነግደው ጽንፈኛ ቡድን፤ ዋና ፍላጎቱ፤ ኢትዮጵያ በአማራ ብቻ እንድትገዛ ነው። ዳዊት ወልደጊዮርጊስና እሳቸውን መሰል ጽንፍ የረገጡ የአማራ ልሂቃን፤ “አማራ ኢትዮጵያ ነው፤ ኢትዮጵያ አማራ ነው” ሲሉ በአደባባይ እየሰማን ነው። ቀድመው ስለሕብረ ብሔራዊነት ቢሰብኩንም፤ ይህ ጭምብላቸው አሁን ተገልጧል። በእነሱ እምነት ኢትዮጵያዊነት በእነሱ ቡራኬና ምርቃት የሚገኝ “ፀጋ” ነው። እነዚህ ነውረኞች፤ ዛሬ ያ የለበሱት የኢትዮጵያዊነት ጭንብል ወልቆ፤ ከ65% በላይ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ረግጠን ካልገዛን ሃገር በሰላም ልትኖር አትችልም እያሉን ነው። ዳዊት የመቃብር አፋፍ ላይ ቆመው፤ በምናባቸው 4 ኪሎን እያዩ ነው፤ 4 ኪሎን “የአማራ ማዕከል” ለማድረግ ያላቸውን ምኞት ነግረውናል። ልክ የትግሬው ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ልጠቅምህ ነው ነፃ ላወጣህ ነው ብሎ ሰብኮ፤ ተጠቃሚዎች የሆኑት የትግራይ ወያኔ መሪዎች እንደነበሩት ሁሉ፤ ዛሬም በሻለቃ ዳዊት የሚመራው የአማራ ወያኔ በአማራ ሕዝብ ይነግድ እንጂ፤ ሥልጣን ላይ እንኳን ቢወጣ ለአማራው ሕዝብ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ትላንት የአማራን ሕዝብ በጠኔ የፈጀ አረመኔ፤ ዛሬ 4 ኪሎ ለመግባት ባለው ምኞት፤ ዋሽንግተን ተደብቆ፤ በአማራ ክልል ቀውስ በመፍጠር፤ የአማራን ወጣት ወደ እሳት እየማገደ ያለ በሃገር ላይ ጦርነት የቀሰቀሰን አረመኔ፤ ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅም ምንም ሥራ ሰርቶ የማያውቅ ሰው፤ አሁን የሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ለአማራ ሕዝብ፤ የሚጠቅም ሥራ ይሰራል ብሎ መጠበቅ፤ ጅልነት ነው። እኝህ ሰው በምናባቸው ወደ የሚያዩት 4 ኪሎ የሚገቡበት አቅም ይቅርና፤ ከኢትዮጵያ ድንበር 4 ኪሎ ሜትር በድፍረት ሊቆሙ የሚችሉበት ወኔ እንደሌላቸው በድፍረት መናገር ይቻላል። እኝህ መርዘኛ ሰው፤ በሜረጩት “የተረት ተረት ፕሮፖጋንዳ” የአማራን ሕዝብ ከሌላው ወንድም ሕዝብ ጋር በማቃቃር በሃገር አደጋ ከመጋበዝ ውጭ የሚፈይዱት ምንም ነገር የለም። በቀደሙት ጽሁፎቼ እኝህ ሰው ከሻዕብያ ጋር በመተባበር በሰሩት ሸፍጥ ለብዙ ብርቅዬ ጄነራሎች ሞት ምክንያት መሆናቸውንና፤ እሳቸው ከሃገር ከወጡ በኋላ እንደነ ተስፋዬ ዲንቃና፤ ኃይሉ ይመኑ ዓይነት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮሎኔል መንግሥቱ ለማስገደል ለኮለኔሉ የፃፉትን ደብዳቤ፤ ወያኔ አደባባይ አውጥቶት አንብበናል። እኝህ ሰው፤ ሥልጣን ለማግኘት፤ ሕዝብን ማፋጀት አዋጪ መንገድ ነው ብለው ነው ዛሬ የማራ ክልል በጦርነት የሚታመሰው። ከእኝህ ሰው ጋር መተባበር የሃገር ክህደት፤ በሕዝብ ላይ የሚሰራ ሸፍጥ ነው። “አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” አዋጪ እንዳልሆነ፤ ከሱዳን፤ ሊብያ፤ የመንና፤ ሶርያ፤ ትምህርት እንውሰድ። 

መፍትሔው ምንድ ነው?

ሃገራችን ያለባትን ፈተና እንደመዘርዘር ያክል  መፍትሔው ቀላል አይደለም፤ ጦርነት ግን በምንም መልኩ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሃገራችን ከግጭት አዙሪት እንድትወጣ ከፈለግን ሁላችንም የተጀመረውን ሥልጣን በስላም የማሸጋገር ሂደት ማጠናከርና ማስቀጠል አለብን። ለዚህም የምክክር ኮሚሽኑ የራሱን ሚና ይጫወታል የሚል የዚህ ፀሃፍ ተስፋ ነው። ሌላው ደግሞ ተቋማትን የመጠቀመ ልምድ ማዳበር ነው። በመንግሥት በኩል የሚፈፀሙ በደሎችን ለማስቆም፤ ፍርድ ቤቶችን፤ ኢስመኮን፤ እንዲሁም የእምባ ጠባቂ ተቋማትን መጠቀም ይኖርብናል። ከብዙ ሰዎች ጋር ባደረኩት ውይይት፤ እነዚህ ተቋማት አይሰሩም የሚል እምነት አለ። መች ፈተሽናቸው እና ነው አይሰሩም ብለን የምንደመድመው? ተቋማቱ ካልሰሩ ደግሞ እንዲሰሩ ማድረግ የዜጎች ኃላፊነት ነው። የዲሞክራሲ ግንባታ ሥራ ይጠይቃል። ሁሌም እንደሚባለው መንግሥት በተፈጥሮው ስድ ነው። ያንን ስድነት ሊገቱ የሚችሉት ግን የነቁ ዜጎች በሚያደርጉት ትግል ነው። በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ ሕዝብን ማስተማርና ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ በምእራባውያን ሃገራት የምንኖር ኢትዮጵያውያን አንድ መረዳት ያለብን ነገር፤ እያንዳንዱ ሃገር የዲሞክራሲ ሂደቱ እየተጠናከረ የመጣው ዜጎች በሚያደርጉት ትግልና በሚከፍሉት መስዋእትነት ነው። ሌሎች የገነቡት ሃገር ላይ ተቀምጠን፤ እነዚህን ሃገራት ስናወድስ፤ የሃገራችንን ስርዓተ መንግሥት ማን እንዲገነባልን ነው የምንጠብቀው? ምሁሮቻችን፤ ስህተት እያሸተቱ፤ የሚሰሩትን ሥራዎች ለማጣጣል ተግተው ከሚሰሩና በምእራባውያን ምክር ቤቶች ደጅ ከመጥናት ይልቅ፤ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ያተኩሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጥሩ ጅማሮዎች አሉ፤ እውነት ለመናገር፤ በቅንነት ከተመለከተን፤ ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ አሁን ዓይነት ሰርቶ የሚያሰራ መሪ ኖሯት አያውቅም። ዐብይ ከነችግራቸው፤ ኢትዮጵያን ያሰቀደሙ፤ ለ30 ዓመታት የተሸረሸረውን የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት እየገነቡ ያሉ፤ ድንቅ መሪ ናቸው። 

ማንም ሰው ፍፁም የለም። የሚሰሩ ሥራዎችን እየደገፍን፤ ስህተቶችን እያረምን ጥፋቶችን እያወገዝንና እየሞገትን የጎደለውን እንሙላ። ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስደምሙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ዓይናችንን እንጨፍን ካላልን በስተቀር ይህ ዓለም የመሰከረው ሃቅ ነው። የምንቆመው፤ ለፓርቲ ወይም ለመሪ መሆን የለበትም፤ የምንቆመውና ትኩረታችንም  ለሃገር ብቻ መሆን አለበት። እያንዳንዳችን መገፋፋትን ካቆምን፤ የምንሰብከውን የጥላቻ መርዝ ከተውን፤ አንዳችን ሌላችንን በእኩለነትና በመከባበር ከተመለከትን፤ ለመጪው ትውልድ የምናስረክባት ኢትዮጵያ ዛሬ እንደምናወድሳቸው ሃገራት ተወዳሽ ትሆናለች። ይህ የእኛ የቤት ሥራ ነው። መፍትሔው ከዋሽንግተን፤ ሞስኮ፤ ቤልጂንግም፤ ሆነ ብራስልስ ሊሆን አይችልም። 

ቸር ይግጠመን። መልካም 2024 ይሁን።
ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ቸሩ እግዚአብሔር ይጠብቅ።

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ” እንደሚሉት ያለ ነው ይህ ጽሑፍ። ከዳንኤል ክብረት/ጋንኤል ክስረት የተሰጠህን ጽሑፍ ነው የለጠፍከው። ይህን የፈጠራ እና በሴራ የተለወሰ ትርክት መንግሥት እስፖንሰር ያደረገው እንደሆነ ግልጽ ነው። 1981 አጼው ነበሩ አልክ። ከሞቱ ከ7 አመታት በኋላ መሆኑ ነው። የፋኖ ትግል መሪ የለውም እያለ መንግሥት ሲለፍፍ የነበረውን ረስተህ ሻለቃ ዳዊት መሪ ናቸው አልክ። ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብለው የሌለው ታጋይ ነው ብለህ ካድክ ውስጥህ ስንቅና ትጥቅ የሌለው መከላከያ እንጂ ፋኖ አለመሆኑን እያወቀ። ፋኖን ጽንፈኛ አልክ ጆሮህ ራሱ አብይ አህመድ ያለውን ፋኖ ሀገሩ ከተነካችበት ዝም የማይል እንጂ አብይ አህመድ ስለጠራው የማይዋጋ መሆኑን ሲናገር እየሰማ። አንድ ድርጅት የሚከፍለውን የ33 ሚሊየን ዩሮ ብድር መክፈል ያቃታት ሀገር በኢኮኖሚ ከምስራቅ አፍሪካ 1ኛ ናት ትላለህ። ፋብሪካ የሰራ ይመስል መዝናኛ ሰራ ብለህ አብይ አህመድን ታወድሳለህ። ፋኖ በሀምሌ ወር ጦርነት ጀመረ አልክ ልብህ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ መንግሥት ያወጀውን ጦርነት እያወቀ። ከ570 መነኮሳት በላይ የገደለው መንግሥት ግንቦት ወር መሆኑን ጠፍቶህ ሳይሆን ሴራ ጉንጎና ላይ ስለሆንክ ነው። የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አይበተንም ተብሎ የአማራ ልዩ ሀይል እንዲበተን መደረጉ ጦርነት መሆኑን እንኳን አንተ ማሙሽ እና ሚጡም ያውቁታል። አማራ በክልሉ ሙሉ ሆ ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ፈሪ ብሎ የዘበተበት ማን እንደሆነ እያወቅህ ሰላም እንጂ ጦርነት አያስፈልግም ትላለህ። ተረኛው አማራን በድሮን እየጨረሰ ፋኖን ጽንፈኛ ትላለህ። የሆንክ ቡትቶ ነገር ነህ አቦ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here