spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትሽምግልና (በሥምረት አያሌው ታምሩ)

ሽምግልና (በሥምረት አያሌው ታምሩ)

ሽምግልና
ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ

በሥምረት አያሌው ታምሩ (semretayalew@gmail)
ታህሳሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.

በህዝብና በመንግሥት ፣ በጌታና በሎሌ፣ በባልና በሚስት፣በወላጅና በልጅ፣ በጓደኛሞችና፣በጎረቤታሞች… ወዘተ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች እንዲበርዱና ሰላማዊ ግንኙነቶች እንዲ[እንዲፈጠሩ] ከሚደረጉባቸው ነባር ማህበራዊ ዕሴቶቻችችን መካከል አንዱና ዋነኛው የሽምግልና ባህላችን መሆኑ ይታወቃል። ይኽ ባህል የተጣላን በማስታረቅ ብቻ ሳይሆን ደምን በማድረቅና የቆየ ቂምም እንዲሽር በማድረግ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የኖረ አኩሪ ባህላች ነው።

ሽምግልና፤ በዳይና ተበዳይ በትክክል የሚለዩበት አልፎ ተርፎም የተበደለው የሚካስበት የበደለው የሚቀጣበት አሰራር አለው። ሽምግልና ከሁሉ አስቀድሞ  የግራ ቀኙን ልባዊ ፍላጎትና ፈቃደኝነት ይሻል።በይበልጥም ደግሞ የሽምግልናውን ማህበረሰባዊ ዋጋና ተቀባይነት ማክበርን ይጠይቃል።

በሸማግሌነት የሚሠየሙ ስዎች ደግሞ፥ ከሁሉ አስቀድሞ የተስጣቸውን ኃላፊነት ያለአንዳች ተጽዕኖና ማዳላት ለመወጣት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት ደግሞ ከአንድ ለሽምግልና ደረጃ እንደ ደረሰ ሰው ከእነሱ የሚጠበቀውን በእውቀት፣በልምድ፣በጥበብና በማስተዋል የተደገፈ ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል። 

ውታደራዊው መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ አካባቢ ጎጃምን ለማረጋጋት ብሎ ለሽምግልና ከላካቸው የአካባቢው ተወላጄች መሀል አለቃ አያሌው ታምሩ ይገኙነበረ። በዚያ ሽምግልና ላይ የፈጸሙት አስደናቂ ተግባር በህይወት ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ሰፍሯል።

ሀ/ የወታደራዊው መንግሥት መልእክትና የጐጃም ጉዞ

ኢትዮጵያን ለአስራ ሰባት ዓመታት የገዛው ወታደራዊ መንግሥት፤ በዘመኑ መጀመሪያ አካባቢ ከገጠሙት ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው በጐጃም ክፍለ ሀገር ተነስቶ የነበረው የህዝብ አመጽ ነው፡፡ የአመጹ መንስኤ መሬታችንንና መሣሪያችን አይወረስም የሚል ሲሆን፡፡ የወታደራዊውን መንግሥት ሹማምንትን አመራርም አንቀበልም የሚል እምቢተኝነት ነበረበት፡፡

ይህን አመጽ በጉልበት ለመቋቋም መሞከት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የተገነዘበው መንግሥት፤ ሰላማዊ መፍትሔ ለመስጠት ወሰነ፡፡ ይኸውም ከተለያዩ ጐጃም ንዑሳን ክልልሎች የተወጣጡ ‘አገሬው ሊሰማቸው ይችላል‘ ፣‘ የህዝቡን ሥነ ልቡና’ ያውቃሉ ተብሎ የተመረጡ የክፍለ ሃገሩ ተወላጅ ሽማግሌዎችን መላክ ነበረ፡፡ በዚሁ መሠረት ከተመረጡት የጐጃም ተወላጆች መካከል አባቴ አንዱ ነበረ፡፡ 

ሽማግሌዎቹ ከጉዟቸው ቀደም ብሎ በቤተ መንግሥት ገለጻና መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበረ፡፡ የገለጻውና የመመሪያው ዋነኛ ጭብጥ መንግሥት የህዝብን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ለህዝቡ ማስረዳትና ህዝቡም ተረጋግቶና ጊዜ ሰጥቶ ራሱን የለወጡ ተጠቃሚ እንዲያደርግ መምክር ነበረ፡፡ 

አባቴ ይህ ተልዕኮ ሲሰጠው  “እኔ ለዚህ ተልዕኮ አልመጥንም፡፡ ሌላ ሰው ብትልኩ ይሻላል፡፡”በማለት ራሱን ለማግለል ሞክሮ ነበረ፡፡ ይህንንም ያደረገው ፤የተሰጠው መልእክት ተፈጻሚ ስለመሆኑ መተማመኛ ስላልነበረው ነው፡፡ ነገርግን “ህዝቡ እኛ ከምንነግረው እናንተ የምትነግሩትን ያምናል፡፡ ይሰማል፡፡ በህዝቡና በመንግሥት መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት ለማስቀረት ከእናንተ የተሻለ ሽማግሌ አናገኝም” ስለተባለና በህዝብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ በመስጋት መልእክቱን ለማድረስ  ሄደ፡፡ ህዝቡ እንዲሰበሰብ እየተደረገ በተዘጋጁ የተለያዩ መድረኮች ላይ ያደረጋቸው ንግግሮች ሲጠቃለሉ የሚከተለው መልእክት ነበራቸው፡፡

“…መንግሥት መብታችሁንና ጥቅማችሁን ለማክበርና ለማስከበር ፈቃደኛነት ያለው መሆኑን እንድንገልጽላችሁ ነው የላከን፡፡ ይህ የመንግሥት ቃል እውነት ወይም ሀሰት ስለመሆኑ ማረጋገጫው የሚገኘው ወደ ፊት በተግባር በሚገለጡ አሠራሮች ይሆናል፡፡ እኛ መልእክት ለማድረስ ነው የመጣነው፡፡ በተገባው ቃል መሠረት መፈጸሙን መከታተል ደግሞ የእናንተ ፋንታ ነው፡፡ መብታችሁን፣ ክብራችሁንና ጥቅማችሁን የሚጠብቅ ከሆነ ከመንግሥት ምንም የሚያጣላችሁ ነገር እንደሌለ አምናለሁ፡፡ የአገሬ የጐጃም ህዝብ! ርስትህን፣ ሃይማኖትህንና ክብርህን ወዳድ እንደሆንክ አውቃለሁ፡፡ የነፍስ ወከፍ መሣሪያህም መብትና ክብርህን የሚደፍር ሲመጣ ለመከላከያ የምትይዘው እንጂ ሌላ ክፉ ሀሳብ የሌለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥትም የህዝብን መብትና ክብር እጠብቃለሁ አከብራለሁ ሲል ርስትህን ሃይማኖትህንና ክብርህን ማለትም እነዚህን ሁሉ የምታስከብርበትን መሣሪያህን ጭምር ሳይነካ  ቃሉን ይጠብቃል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ቃሉን እንደሚያከብር አምናለሁ፡፡ እናንተም የተገባላችሁ ቃል ከተከበረ ሌላ የምትሹት ነገር ይኖራል ብዬ አለጠረጥርም፡፡ ከተገባላችሁ ቃል ውጪ ሆኖ በርስታችሁ፣ በሃይማኖታችሁና በክብራችሁ ላይ ለሚመጣ ነገር ግን ወሳኝ እናንተው ራሳችሁ ናችሁ፡፡…” በማለት አስተማረ፡፡ 

የአገር ሽማግሌዎቹ በተዘዋወሩበት ቦታ ሁሉ የሚሠሩትንና የሚናገሩትን እንዲቆጣጠሩ የተላኩ የፖለቲካ ሹማምንት አብረው የነበሩ ቢሆንም በአባቴ አንደበትና እንቅስቃሴ ማዘዝ አልቻሉም፡፡ 

ከጉዞ መልስ ስለሁኔታው በደረሳቸው ዘገባ የተበሳጩት የደርጉ ሊቀመንበር ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ምክትላቸው ኰሎኔል አጥናፉ አባተ አባቴን ወደ ቤተ መንግሥት አስጠሩት፡፡ 

“ህዝብ እንዲያረጋጉ ቢላኩ እንዴት የባሰ ጦርነት ቀስቅሰው ይመጣሉ?” ኰሎኔል አጥናፉ  ጠየቁት፡፡

“የምን ጦርነት? እኛ ከተመለስን የተነሳ ጦርነት አለ እንዴ?” በማለት ጠየቀ አባቴ፡፡

“ምን ሲያስተምሩና ሲናገሩ ሰንብተው እንደመጡ ሰምተናል፡፡” ኰሎኔል መንግሥቱ ነበሩ፡፡ ንዴት እየተናነቃቸው ተናገሩ፡፡

“እኔ ቅድሙንም አትላኩኝ ለእናንተ መልእክት አልመጥንም ብዬአለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከላካችሁኝ ውጪ የተናገርኩት ነገር የለም፡፡ ‘ህዝቡን የምታውቁት እናንተ ናችሁ፡፡ ህዝቡን አረጋግታችሁ ኑ አላችሁን፡፡’  ህዝቡ ከርስቱ፣ ከሃይማኖቱና ከክብሩ ሌላ የሚፈልገው ነገር የለም፡፡ ‘መንግሥት እነዚህን አይነካብህም እርጋ’ ብዬ አስተማርኩኝ፡፡ መንግሥት ይመጣል መንግሥት ይሄዳል፡፡ ቁምነገሩና ዋናው ህዝብ ነው፡፡ ህዝብን መዋሸት አያዋጣም፡፡ እና ሌላ ምን እንዳስተምር ትጠብቁ ነበር? ” የሚል መልስ ሰጣቸው፡፡

ሥምረት አያሌው ታምሩ፣ አባቴና እምነቱ፣ 2ዐዐ7 ዓ.ም.

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here