spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትሰላም ሳይኖር “ሰላም ነው” አትበሉን ! (ዳዊት ዓለሙ )

ሰላም ሳይኖር “ሰላም ነው” አትበሉን ! (ዳዊት ዓለሙ )

Kulubi _ Metehara
ከቁልቢ ገብርኤል በዓል አክብረው ሲመለሱ በኦሮሚያ ክልል በመተሃራ ከተማ በተጣቂዎች የተገደሉ ወገኖቻችን፡፡ (ፎቶ ፡ ከኢኤምኤስ ቪዲዮ የተወሰደ)

ዳዊት ዓለሙ 

‘ሰላምን ስለፈልግን ብቻ ሰላም አይሆንም’ የሚል አባባል አለ። ሃሳቡ ሲብራራ ሰላምን አጥብቀን ስለፈልግን ብቻ ወይም በምኞት ብቻ ሰላም ማግኘት አይቻልም። አንዳንዴ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ጦርነት ግድ የሚልበት ጊዜ አለና። ስለዚህ ሰላም በፈላጊው እና በአስፋኙ (በሚያረጋግጠው) ህብረት ተግባራዊ የሚሆን ነው። ማለትም ህዝብ ሰላምን አፈልጋለሁ ካለ፡ በስልጣን ላይ ያለው አካል ይሄን ተግባራዊ የሚያደርግበትን መንገድ ይወጥናል። ተግባራዊም ያደርጋል።

በዚህ ሰላምን በማጽናት ወቅት ደግሞ ዜጎች ማደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ፡ ትብብር እና ትእግስት የመሳሰሉ ግዴታዎችን ማሳወቅ የመንግስት ድርሻ ነው። በአንጻሩ በጦርነት እና ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ያለን ሃገር የሚምራ መንግስት፡ በቂ ግንዛቤ የሌላቸውን ዜጎቹን ባለማሳወቁ ወይም በማሳሳት የእሳት ራት ቢያደርግ ከተጠያቂነት አያመልጥም።

መንደርደሪያ

በታህሳስ ወር ከሚከበሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የመልዓኩ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል ነው፡፡ ይሄን ታላቅ በዓል ለማክበር ደግሞ አቅም ያላቸው፣ ስእለት ያለባቸው እና ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ሰዎች ድሬዳዋ በሚገኘው ቁልቢ ደብረኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመገኘት ያከብራሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የብልጽግና መንግስት መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ወደ ስፍራው በሚደረገው የየብስ ጉዞ ላይ በሚፈጠሩ የእገታ አለፍ ሲልም ህይወትን የሚያሳጡ ችግሮች ምክንያት ምእመናን አገር አቋርጠው መሄድን አይደፍሩም፡፡ 

ብዙዎች እንደሚሉት ደግሞ በዚህ ሰዓት አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ አጎራባች ከተሞች መሄድ ህይወትን አደጋ ላይ መጣል ነው፡፡ ደፍረው የሚጓዙ ህይወታቸው ባይጠፋ እንኳ ፡ ሊታገቱ ይችላሉ። ምናልባት ከመገደል ይልቅ መታገት ይሻላል የሚል ሰው አይጠፋ ይሆናል፡፡ እውነታው ግን የታገቱ ሰዎች እንኳን በህይወት የመቆየት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ የሰሞኑን አንድ አሳዛኝ ታሪክ ላጋራችሁ፡፡

ካህኑ በናዝሬት እካባቢ የሚያገሉ አረጋዊ አባት ናቸው፡፡ ስማቸውን ለካህኑም ሆነ ለደብራቸው አገልጋዮች ደህንነት ሲባል ከመግለጽ ልቆጠብ፤ እኚህ ካህን ወደሚያገለግሉበት ደብር ለሃዋርያዊ ተልእኮ ሲመላለሱ፡ በአንድ አጋጣሚ በኦነግ ታጣቂዎች እጅ ይወድቁና ይታገታሉ። ከእገታው ነፃ እንዲለቀቁ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር እንዲያመጡ ለቤተሰባቸው ይነገራል፡፡ ወዳጅ ዘመድ፣ ጎረቤት እንዲሁም ይሄን ዜና የሰሙ በሙሉ ገንዘብ በማዋጣት ለአጋቾቹ ይላካል፡፡ ሆኖም አረጋዊው ካህን ሳይለቀቁ ከ15 ቀናት በላይ ሆናቸው። ቤተሰቡ በመንታ ልብ ሆኖ ይጠባበቃቸዋል። አርፈዋል እንዳይባል የሰሙት ማረጋገጫ የለም። አሉም እንዳይባል ወደቤታቸ አልመጡም። ምናልባትም እኚህ አባት በህይወት ይኖራሉ ብሎ ማሰብ እንደሚከብድ ከአጋቾቹ የቀደመ ተግባር በመነሳት ጥርጣሬያቸውን የሚያስቀምጡ አሉ፡፡

ቁልቢ የሄዱ ምእመናን ምን ገጠማቸው?

ወደቀደመው ጉዳያችን ስንመለስ፣ በቁልቢ የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓሉ ለማክበር ከአዲስ አበባ፣ አቃቂ ቃሊቲ ተነስተው ወደ ድሬዳዋ ያቀኑ ወገኖች ገና ከአዲስ አበባ ሲወጡ ነበር እንቅፋት የገጠማቸው፡፡ ታጣቂዎቹ ተጓዦቹን በማስቆም ሰላሳ ሺህ የሚጠጋ ገንዘብ እና 10 ሞባይል ከነጠቁ በኋላ ይለቋቸውና ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ 

በዓሉን እክበረው ሲመጡ በተመሳሳይ መኪናቸው ላይ የተኩስ እሩምታ በመክፈት እንዲያቆሙ ያዟቸዋል። ታዲያ ከእነዚህ ተጓዦች በፊት ወደ አርባ ምንጭ የሚጓዝ መኪናም ታግቶ ኖሮ እዚያው ይገናኛሉ፡፡ 

አጋቾቹ ከኋላ ወደመጣው የአዲስ አበባ መኪና ፊታቸውን ሲያዞሩ፡ የአርባምንጭ ተሳፋሪዎችን የያዘው ሾፌር በፍጥነት እየነዳ ያመልጣል። ከኋላ እየተከተሉ እና ጥይት እየተኮሱ ለማስቆም ቢሞክሩም አሽከርካሪው ፍጥነቱን በመጨመር ተሳፋሪዎቹን ከእነዚህ አውሬዎች መታደግ ችሏል፡፡ ርግጥ ነው ከኋላ ወንበር የነበረ እንደ ተጓዥ አራት ቦታ ተመትቶ ህይወቱ አልፏል፤ 8 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሆኖም ሹፌሩ በወሰደው ፈጣን ርምጃ ሊደርስ የሚችለውን አስከፊ ጉዳት መቀነስ ችሏል፡፡

አጋቾቹ የአዲስ አበባ ተጓዦች ላይ ባካሄዱት የተኩስ እሩምታ አራት ሰዎችን ገድለው፣ አንዲት በድንጋጤ የወደቀች ሴትን (ሞታለች በማለት) እዚያው ጥለውና መኪናውን በማቃጠል የቀሩትን ሰዎች በመያዝ ወደ ጭካ ይገባሉ፡፡ ከመኪናው ቃጠሎ በተአምር የተረፈችው የዚች እህት ቤተሰቦች በሰጡት እማኝነት ነው ጥቃቱን ለማወቅ የተቻለ፡፡ ህይወታቸው ከመኪናው ጋር የተቃጠለው ወገኖች ማንነታቸውን ለመለየት ስላስቸገረ በአካባቢው ግብአተ መሪታቸው ለፈጸም ችሏል።  እስካሁን ባለው መረጃ የታገቱት ሰዎች ምን እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

በድሬዳዋ የሚከበረውን የቁልቢ ቅ/ገብርኤል ዓመታዊ በዓል አስመልክቶ አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ መኖሩን ከከተማዋ ከንቲባ ጀምሮ በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ ከንቲባው አቶ ከድር ጁሃርም ምእመኑን ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ እያሉ ሲቀበሉ ታይተዋል፡፡ የበዓሉን ፍጻሜ ተከትሎም ‘በሰላም መጠናቀቁን’ ከንቲባው ገልጸው ነበር፡፡ 

ምንም እንኳን በዓሉ በድሬዳዋ በሰላም ቢፈጸምም፣ ከላይ እንደተገለጸው ወደ አርባምንጭ ከተመለሱት 55 መንገደኞች ውስጥ እንድ ሰው ተገድሎ፣ 8 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ተመልሰዋል፡፡ በተመሳሳይ ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ከነበሩት 18 ምእመናን ውስጥ 4 ሰዎች ተገድለው አንዲት እህት ተርፋ፣ የቀሩት ታግተው ተወስደዋል፡፡ ታዲያ ከበዓሉ በፊት ሲነገር እንደነበረው ‘አስተማማኝ ሰላም አለ’ የተባለው ድሬዳዋ ላይ ብቻ ነው ? በተቀረው የሃገሪቱ ክፍል ሰላም ሳይኖር ግብዣ ማደረግስ ተገቢ ነው? ለጠፋ የሰው ልጆች ህይወት ተጠያቂው አጋቹ ብቻ ሊሆን ይችላልን?

ለማንኛውም እዚህ ላይ አጽንኦት መስጠት የሚያስፈልገው ነገር፣ ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው ሲጓዙ በቅድሚያ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ከመንግስት ሃላፊዎች ሳይሆን፤ ከአስተማማኝ የመረጃ ምንጮች ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

የላሊበላ እና የጎንደር ጉዞስ…

የፊታችን ታህሳስ 29 በታሪካዊቷ ቅድስት ከተማ የሚከበረው የቅዱስ ላሊበላ እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዲሁም በጎንደር ከተማ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ አቅም ያላቸው ምእመናን በአውሮፕላን እንጂ፣ በተሽከርካሪ ባያደርጉ ከወዲሁ እናሳስባከን። 

ይሄን ማሳሰቢያ የምንሰጠውም፣ የሃገርን ኢኮኖሚ ከመጉዳት አሊያም የገዳማቱንም ሆኑ የከተማዎቹን ገቢ ለማቀነስ ከማሰብ ሳይሆን ተጓዦች ያልተገባ መስዋእትነት እንዳይከፍሉ ሃላፊነት ከሚሰማው ዜጋ በመነጨ ቀና አስተያየት ነው፡፡

የጎንደር ከተማ ሃላፊዎችም የጥምቀት በዓል ጥሪን ከወዲሁ እያሰተላለፉ ይገኛሉ። ሆኖም የቁልቢውን ጉዞ የተመለከተ ምእመን በመኪና የሚደረገውን ጉዞ እንደማይሞክረው ይገመታል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማም፤ በቁልቢው ሆነ ከዚያ በፊት በተደረጉት ጉዞዎች ሰዎች ህይወታቸው እየተነጠቁ እና እየታገቱ ስለሆነ ከጉዟቸው በፊት እንዲያስቡበት ለማስታወስ ነው፡፡

በተጨማሪም የፀጥታ አካላትም ካለፈው ነገር ትምህርት ወስደው የዜጎችን የደህንነት አደጋ እንዲቀንሱ ለማሳሰብ ነው። ባልተጨበጠ ሰላም ዜጎችን መማገድ ተገቢ አይደከም። ሃላፊነት የሚጎደለው ተግባርም ጭምር ነው።

የአማራ አካባቢ አሁን ላይ በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንደመሆኑ፡ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማደረግ እንደሚገባ ለበዓሉ ታዳሚዎች ማስታወስ ይገባል። የመንግስት ባለስልጣናት እንደሆኑ ከሰው ህይወት ይልቅ ለሚዲያ ፍጆታ የሚደረግ ግርግር ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው። የእነሱን መረጃ እውነት ነው ብሎ ጉዞ ማደረግ ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ 

መደምደሚያ

በጽሁፉ መግቢያ እንደተገለጸው በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢ ያለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሰዎች ህይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ ሰርቶ መብላት በማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ የዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ተጥሷል፡፡ ፍርድ ተጓድሏል ፣ ድሃ ተበድሏል፡፡ የሃገር ኢኮኖሚም ተንኮታኩቷል፡፡ የጸጥታ ችግር በመላው ሃገሪቱ በመኖሩ የተነሳ ከሃገር ውስጥ ሆነ ከሃገር ውጪ ያሉ ጎብኚዎች እግራቸውን እንዲሰበስቡ እየተገደዱ ነው። በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጥሪ የተደረሀላቸው “ሁለተኞቹ ትውልድ ኢትዮጵያውያን” እንደዚህ ቀደሙ ለጥሪው ምላሽይሰጡ ይሆን? ባለሃብቶ (ኢንቨስተሮች) ኢትዮጵያ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ፈርተዋል፤ አይፈልጉም፡፡ 

የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ ዜጎች በረሃብ አለጋ እንዲገረፉ፣ በማንኛውም ሰዓት ህይወታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ፣ ከተወለዱበት፣ ካደጉበት፣ ወግ ማዕረግ ካዩበት ቦታ እንዲፈናቀሉ ተገደዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ በርካታ ቤተሰቦችን ለጎዳና ዳርጓል፤ የቀሩትንም እየፈተናቸው ይገኛል፡፡ 

መፍትሄው ግልጽ እና አጭር ነው፡፡ መንግስት ስለዜጎቹ ግድ ሊለው፤ አስተማማኝ የደህነንት ከባቢን ሊጠር፣ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን፣ አለመግባባትን ከጠብ መንጃ ይልቅ በንግግር ሊፈታ ይገባል። ካልቻለም በሰላም እና በምርጫ አማካይነት ስልጣኑን ለማስረከብ ፈቃደኛ ይሁን፡፡

የአልማዝን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም !!!

ሰላም ለኢትዮጵያችን    

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here