spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትፖለቲካ ‹Dirty Game› የሚሆነው መቼ ነው?

ፖለቲካ ‹Dirty Game› የሚሆነው መቼ ነው?

ፖለቲካ  _ ወርቅነህ ገነት
ወርቅነህ ገነት

ወርቅነህ ገነት

በመጀመሪያ ከፅንሰ ሀሳቡ በመነሳት ‹ፖለቲካ ምንድን ነው?› የሚለውን ማየቱ ግንዛቢያችንን የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ‹ፖለቲካ ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ በተለያየ መልኩ የሚበየን ፅንሰ ሀሳብ ነው። ከዚህ አንፃር በአንድ በኩል ፖለቲካ ማለት ‹የአስተዳደር ጥበብ ነው፤ ማን ምን ይገባዋል? መቼ? እና በምን መልኩ? ተብሎ የሚበየንበት አስዳደራዊ ጥበብ ነው> የሚል አለ። በሌላ በኩል ደግሞ  ፖለቲካ ‹dirty game ነው፤ ፖለቲካ ኮረንቲ ነው› ማለት የተለመደ ሆኗል። ከዚህ አኳያ በትክክል ‹ፖለቲካ ምንድን ነው?› የሚለውን ስናይ ፖለቲካ ማለት ሌሎች ጉዳዮችን በሙሉ ተፅዕኖ ውስጥ አድርጎ የሚቆጣጠር ልዕለ-ድርጊት ነው፡፡ <Politics is a master science that controls all other affairs> እንዲል ፈላስፋው አሪስቶትል! ስለዚህ ፖለቲካ ማለት የአስተዳደር ጥበብ ሲሆን ፖለቲከኞችና መሪዎች የህብረተሰብን ጥቅል ፍላጎት (aggregate interest of the society) እንደ ፖለቲካዊ-ኃይማኖት በመያዝ በመርህና በህግ የሚያስተዳድሩበት ሂደት ነው። 

ከዚህ አንፃር ፖለቲከኛ ማን ነው? ማነውስ ፖለቲከኛ መሆን ያለበት? የሚለውን ስናይ ፖለቲከኛ ማለት የህብረተሰብን አኗኗር በአወንታዊ መልኩ መቅረፅ የሚችሉ እሳቤዎችን በማመንጨት መምራት የሚችል ሰው ማለት ነው። ከዚህ አንፃር ፖለቲከኛ ማለት ፈላስፋ ማለት ይሆናል፤ የሚፈላሰፈው ግን “ማን ፈጠረን?” ምናምን እያለ ሳይሆን ‹ለሀገሬ ብሎም ለዓለም ምን አይነት የፖለቲካ ርዕዮትና የኢኮኖሚ ፖለሲ ያስፈልጋታል› በሚል አኳኋን ነው። ስለሆነም ፖለቲከኛ ፈላስፋ የሚሆነው ዜጎችን ከችግርና መከራ ወደ ምቾታዊ የአኗኗር ሥርዓት ለማሻገር በሚያደርገው የሀሳብ ማመንጨት ሂደት ነው። ለዚህም ነው ፈላስፋው Plato ‹Philosophers should be kings and kings should be political-economic philosophers› ሲል የገለፀው። ስለዚህ ፖለቲከኛ ማለት በህዝብ የሚገለገል ሳይሆን ተሻጋሪ ሀሳብ በማመንጨት ሀገርና ህዝብን የሚያገለግል ማለት ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ፖለቲካ መፈላሰፍ በሚችሉ በፖለቲከኞች ተዘወረች ማለት ነው፤ በውጤቱም ፖለቲካ ከ‹dirty gameነት› ወጥታ የአስተዳደር ጥበብ ትሆናለች ማለት ነው።

ለመሆኑ ግን ፖለቲካ “Dirty game” የሚሆነው መቼ ነው? ፖለቲካ የአስተዳዳር ጥበብ የሚሆነውስ መቼ እና እንዴት ነው? የሚለውን ማየቱ የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ በመሠረቱ ፖለቲካ አዳዲስ እሳቤ በሚያመነጩ ፖለቲካዊ ፈላስፎች መመራት ይኖርበታል ። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ ግን ማሰብ የሚከብዳቸውና ትምህርት-ጠሎች ፖለቲካውን መጫወት ከጀምሩ  ፖለቲካ “Dirty game› ይሆናል። ለዚህም ነው ‹When the idiots try to play it, politics will become a dirty game› ሲል ፈላስፋው Plato የገለፀው። ስለሆነም ፖለቲካ የአስተዳደር ጥበብ ይሆን ዘንድ መዘወር ያለበት በፖለቲካዊ ፈላስፎች እንጅ በፖለቲካ መኃይማን መሆን የለበትም። ከዚህ አንፃር በህብረተሰብ ዘንድ ጥቂት ሰዎች መፈላሰፍንና አዳዳስ አወንታዊ ርዕዮት ማመንጨትን ሲወዱ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ግን ማሰብ-ጭንቄ የሆነበትና ከአዕምሮው ይልቅ ሎሎች የንዑሰ-ሰብ ተግባር የሚከውኑ አካላቶቹን የሚጠቀም ነው።

በፖለቲካዊ ፍልስፍና እይታ መሠረት ደግሞ ፈላስፎች እንስሳዊ ባህርያችው የሆነውን መብላት፣ መጠጣት፣ ወሲብ ማድረግ እና መደባደብን ሰዋዊ ባህሪ በሆነው ‹በማሰብና ወደ ልዕለ-ሰብነት በማደግ ዝንባሌ ያሸንፉታል› የሚል ነው። ስለዚህ ለመብልና መጠጥ ወይም ለወሲብ ብለው በህዝባቸው አይገለገሉም፤ ህዝባቸውን ያገለግላሉ እንጅ። በአንፃርሩ ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ከሰዋዊ ባህሪው ይልቅ እንስሳዊ ባህሪው የሚጎላበት ስለሆነ በቁጥር ጥቂት በሆኑት ፖለቲካዊ ፈላስፎች መመራት አለበት። በዚህ መኃል ግን የመንግስት ስልጣን፣ ማሰብ ጭንቄው በሆነውና የህበረተሰብን ጥቅል ፍላጎት (aggregate interest) መያዝ በማይችሉ የፖለቲካ መኃይማን እጅ ከገባ ፖለቲካ “Dirty game” ይሆናል።

ስለሆነም ፖለቲካን “Dirty game” የሚያደርጉት ተራማጅ እሳቤና ትምህርት-ጠል የሆኑ የፖለቲካ መኃይማን የመንግስትን ስልጣን ሲይዙ ነው። እነዚህ ሰዎች ፖለቲከኛ የሆኑ የሚመስላቸው ነገር ግን ፖለቲካን ያልተረዱ እና ምናልባትም “ስሙ ከብዶት ሞተ” እንደሚባለው የፖለቲከኛነትን ሸክም መሸከም የማይችሉ ሰዎች ናቸው። እነዚህ የተራማጅ እሳቤ-ጠል ሰዎች ፖለቲካን በተጫወቱ ጊዜ ፖለቲካ ማለት <ኮረንቲ ነው፤ መገዳደል ነው፤ሴራ ብቻ ነው> ተብሎ በህዝብ ዘንድ መጥፎ የሆነ ነገር እንዲሰርፅ ይሆናል። ከዚህም አልፎ ብሩህ አምሮ ያላቸው አሳቢያን ወጣቶች ፖለቲካን በሳይንስ መንገድ አጥንተው ፖለቲከኛ ከመሆን ይልቅ ወደ ሌላ ዘርፎች በመግባት ፖለቲካችን በፖለቲካ መኃይማን እንዲመራ ይገደዳል። እነዚህ የፖለቲካ መኃይማን በሚሰሩት ነገር ነው በብዙ  ታዳጊ ሀገራት ፖለቲካ ችግር ሲፈጥር እንጅ መፍትሔ ሲያመጣ የማይታየው።

ሥለዚህ ፖለቲካ የአስተዳደር ጥበብ ሆኖ የሀገርና ህዝብን ችግር ይፈታ ዘንድ ፖለቲካችን ማሰብን በማይፈሩና እንስሳዊ ፀባያቸውን በሰዋዊ ባህሪያቸው በተቆጣጠሩ ፖለቲካዊ ፈላስፎች መመራት አለበት። እሳቤና ትምህር ጠሉ የፖለቲካ ስልጥንን ሊቆናጠጥ አይገባም። ይሄ ሳይሆን ከቀረ ግን ግጭትና ችግር የሀገራት መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡ ምክናየቱም ግጭቶችና ችግሮች ምንጫቸው ፖለቲካዊ መኃይምነት ነውና! 

ስለሆነም አንድ ሀገር ፈላስፋ ፖለቲከኛ ከሌላት ኢኮኖሚዋ ይከስራል፣ማህበራዊ ጉዳዮቿም ይጎሳቆላሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል የፖለቲከል ሳይንስ አባት ተብሎ የሚጠቀሰው አሪስቶትል ” Politics is a master science that can control all other affairs” ብሎ የገለፀው። ከዚህ ላይ ፖለቲካ እንዴት ሌሎች ነገሮችን እንደሚቆጣጠር እንይ። በአንድ ሀገር ላይ የፖለቲካ ሥርዓት መክሸፍ ካለ ኢኮኖሚያዊ ክስረት ያመጣል። ኢኮኖሚያዊ ክስረት ደግሞ ማህበራዊ ዝቅጠትን ያስከትላል። Political system failure causes economic loss and economic loss results social-decay. 

ለምሳሌ፡- ይሄን ከእኛ ሀገር አንድ ሁነት ጠቅሰን እንየው! በፖለቲካ ሥርዓት መክሸፍ ምክናየት የትህነግ እና የፌደራሉ መንግስት ተቃርኖ ገፍቶ ሄዶ ወደ ወታደራዊ ፍልሚያ በተቀየረ ጊዜ በትግራይ ክልል የሚገኜው ግዙፉ ሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማምረት አቆመ። በዚህም ምክናየት የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት በገቢያው ላይ ተከሰተ። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ክስረት ምክናየት ግንባታዎች ሲስተጓጎሉና ሲቆሙ በግንባታው ዘርፍ የነበረው ሰፊው የሰው ኃይል ከስራ ውጭ ሆነ። በውጤቱም ይሄ ከስራ ውጭ የሆነ የሰው ኃይል ወደ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ምናልባትም ወደ ዝርፊያና ስርቆት ያመራል። ዝርፊያና ሥርቆት ማህበራዊ ዝቅጠት መሆኑን ልብ ይሏል። ሥለሆነም የፖለቲካ መክሸፍ ኢኮኖሚያዊ ክስረትን ሲያስከትል ኢኮኖሚያዊ ክስረት ደግሞ ማህበራዊ ዝቅጠትን(social decay) ያመጣል።

ስለዚህ ፖለተካችን ከ<Dirty gameነት> ወደ አስተዳዳር ጥብበነት ይቀየር ዘንድ መፍትሔዎችን ማፍለቅ አለብን፡፡ ስለሆነም ፖለቲካችን የአስተዳድር ጥበብ ይሆን ዘንድ አዳዲስ እሳቤ ማፍለቅ በሚችሉ የፖለቲካ ጠቢባን (Political Philosophers) መመራት ይኖርበታል። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር አንድ ሰው ፖለቲካል ሳይንስ ስለተማረ ብቻ ፖለቲከኛ ለመሆን ብቁ ነው ማለት አይቻልም። ብዙዎቹ የፖለቲካ መኃይማን በቴሌቪዥን ብቅ እያሉ “የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪ አለኝ” ሲሉ እየሰማን ነው። አንድ ሰው ፖለቲካል ሳይንስ መማሩ ፖለቲካን በተሻለ ሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ይረዳው ይሆናል እንጅ መማሩ ብቻውን ፈላስፋዊ ፖለቲከኛ አያደርገውም። በመሠረቱ በስም አጠራርም ቢሆኝ አንድ ፖለቲካል ሳይንስን የተማረ ሰው ፖለቲካል ሳይንቲስት እንጅ ፖለቲከኛ ተብሎ አይጠራም።

ስለዚህ መፈትሔ የሚሆነው በተፈጥሮ ብቃታቸው የእሳቤ-ልዕልና ላይ ያሉ ታዳጊዎችን ከታች ክፍል ጀምሮ ወደ ዝንባሊያቸው አስገብትን በማሰልጠን የመፈላሰፊያ ምቹ መደላድል ፈጥረን ጠቢባን ፖለቲከኞችን ማፍራት እንችላለን። ያኔ ስራው በሰሪዎች እጅ ስለሚሆን ፖለቲካችን ከ”Dirty gameነት” ወጥቶ ሀገራችንን እና ዓለምን የተሻለ የሚያደርግ የአስተዳደር ጥበብ ይሆናል። ስለዚሆነም ፖለቲካ የአስተዳደር ጥበብ ነው፡፡ የአስተዳዳር ጥበብ  የሚሆነው ግን በፖለቲካዊ ፈላስፎችና በአሳቢያን ሲመራ ነው። 

ወርቅነህ ገነት በባህር ዳር ዮኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም-አቀፍ ጥናት መምህር ነው፡፡ ለሚኖረዎት ጥያቄና አስተያየት ስልክ፡ 09 10 43 19 20     Email: wogeyih@gmail.com

_

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here