

(ዳዊት ዓለሙ)
በደራሲ እና ገጣሚ በረከት በላይነህ በእይታ ላይ የሚገኘው ቴአትር “እያዩ ፈንገስ – ቧለቲካ” ቴአትር ከነገ ሃሙስ ጥር 2 /2016 ዓ.ም ጀምሮ ከመድረክ እንዲወርድ በፀጥታ አካላት ትእዛዝ መተላለፉ ታውቋል።
የአንድ ሰው ቴአትር የሆነው እና በተዋናይ ግሩም ዘነበ ድንቅ ትወና ከሁለት ወራት በላይ በአለም ሲኒማ መድረክ እየታየ የሚኘው ቴአትሩ፡ የመንግስት የፀጥታ አካላት ለዓለም ሲኒማ የስራ ኃላፊዎች ባስተላለፉት ትእዛዝ ነው ከነገ ጀምሮ ለህዝብ እንዳይታይ መከልከሉን ከአዘጋጆቹ ማረጋገጡን የፊልም ባለሞያው ያሬድ ሹመቴ ያስታወቀው።
ቴአትር ቤቱም የደረሰውን የክልከላ ትዕዛዝ ለአዘጋጆች በማሳወቅ ውሉን ማቋረጡም ታውቋል። ሆኖም አዘጋጆቹ ሆኑ ሲኒማ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ያሉት ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የአንድ ሰው የሙሉ ጊዜ ቴአትር እያዩ ፈንገስ ከዚህ ቀደም “ፌስታሌን” እና “አጀንዳዬን” ለመድረክ ያበቃው መጋቢት 2006 ዓ.ም ነበር። አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ቴአትሩ ዘንድሮ ከእረፍት በኋላ “ቧለቲካ” በሚል ርእስ መታየት ጀምሮ ነበር።
ይሄ ቁጥር ሶስት እያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” ከጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር ሀሙስ እና እሁድ ይታይ ነበር። በሁለት ወር ከ16 ቀን ቆይታው 20 ጊዜ መድረክ ላይ ታይቷል።
የሙሉ ጊዜ ቴአትር ከመሆኑ በፊት በራስ ሆቴል ይዘጋጅ በነበረው ‘ጦቢያ ፖይቲክ ጃዝ’’ እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ከ25 ጊዜ በላይ ከ20 – 30 ደቂቃ ተቀንጭቦ ለእይታ በቅቷል።
ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን በቀልድ እያዋዛ የሚተቸው እያዩ ፈንገስ 1, 2 እና 3 የመታገዱ ምሥጢር ምናልባትም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስለሚተች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
__
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com
Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ





