spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትይደርስ ለእህት ዓለሜ

ይደርስ ለእህት ዓለሜ

ከWFP ገፅ የተገኘ ምስል

(ምናባዊ  ደብዳቤ፥ በአያሌው ደጀን)

ምን ተብሎ ነው የሚጀመረው? ከየት ብነሳ ይሆን የውስጤ፣ የነፍስያዬ እና የመንፈሴ ጣር የሚሰማው? የነገር ሁሉ ውል በተንኮለኛ ሸማኔ እንደ ተቋጠረ ቁጢት አልፈታ ያለው ትውልድ እንዴትስ፣ ከወዴትስ ቢጀምር ነው የሀሳቡ መልክ የሚያዘው? እንጃ…….

ብቻ ግን “ይመስገን” የሚል በእምነት የጠነከረ ምላሻችሁን እያሰብሁ ነው ‘የሰማይና የምድሩን ያህል፣ የመከራውንና የመዘንጋቱን ያህል፣ የመገፋትና የመፈተንን ያህል ‘ይህ’ ተብሎ በማይሰፈር የምደር ሲኦል ውስጥ ያላችሁ ወገኖቼ እንዴት ናችሁ?😥 የምለው። እንዴት ናችሁ?

አበወይ እንዴት ነው? የጥይት አረር የሚያሳድደው ወንድም ጋሼስ እንዴት ሁኖ ይሆን? እቴወይስ የሀዘን እና የርሃብ ቸነፈሩን እንዴት ችላው ይሆን? እህታለምስ እንዴት ነሽ? በግራና በቀኝ ተሰልፈው፣ በሰው በላ ፓለቲካዊ ሽኩቻ ልጆቿን አጥታ ከቶ አዘኑን ችላው ይሆን? እንደው ለማናቸው አልቅሳ ይሆን ሀዘኗን የምትወጣው? አይወይስ እንዴት ነው? እያልሁ ያው የህያው ሙት ሁኛለሁ።

ባለፈው “እግዜርን ተስፋ አድርጌ፣ በበጋ በፀሐይ ተጠብሼ ባርስም በዘሩ ወቅት በማሳው ትራክተር ሳይሆን ታንክ ተመናሸበት። አሁን በጤፍ ፋንታ አረም አብቦበታል ማሳው” ብሎኝ ነበር ጋሻዬ። እኔም ባለፈው የደውልሁ ጊዜ  “ጦርነቱ የፈጀውን ፈጀ። አሁን ደግሞ ርሃብ አንጠራውዞ እየፈጀን ነው። ‘ምነው አንድያውን በመድፉ ባለቅን ይሻል ነበር’ የሚያሰኝ ሞት የማማረጥ ጣጣ ወድቆብናል ወንድምዓለም” ያለኝ እያሰብሁ እስካሁን ውስጤ ይታወካል።

ታንኩ ሁላ መሬቱን ሲመነሰሽበት ከረመ። ከብቱም ሀይ ባይ አጥቶ ከየአቅጣጫው በሚተኮስ ጥይት አለቀ። አሁን ደግሞ የተረፉትን እንኳን ሽጠን ነፍሳችንን እንዳናቆይ ድርቁ አድቋቸዋል። ደግሞስ “ነገ የተሻለ ቀን ቢወጣ አንድያችንን ተነቅለንን እንቅር? እንደው ምን ቢቸግር ከበረቱ ጥጃ፣ ከጎታው ዘር እንዳይኖር ይደረጋልን?” አለኝ። “የልጆቹን ወዳጅ ጥጆቹን ሳይነካ እምነቱን ጠብቆ ነው የሞተው ለካ” የተባለው የማይሻር ምሃላውን ለመጠበቅ ርሃብን ተጨባበጠው።

እህታለም ባለፈው “ህፃን ልጄ ሊሞትብኝ ነው። የደረቀ ጡቴን ሲጠባ ልቤን ይስበኛል። ያመኛል። እያዞረኝም ነው” ስትይ ለአንድ ባለ ካሜራ የነገርሽውን እናንተ በማታውቁት፣ እኛ ዩቲዩብ በምንለው ተለቆ አየሁት። አዘንሁ አልልሽም። ያ የማውቀው ወተት እየተቀዳ የሚጠጣበት ማጀትሽ ተራቁቶ ሳይ አዘንሁ ሳይሆን መፈጠሬን ጠላሁ ነው ማለት ያሰኜኝ። ቸርነትሽን፣ ፍቅርሽን፣ ድፍን መንገደኛውን “አፈር ስሆን” ብሎ ያጎረሰ ርህራሄሽን አውቀዋለሁና ሳይገባሽ ለሆነው ሁሉ ባለ እዳነት ነው የተሰማኝ።

“አፈር ስሆን” ያለ የፍቅር ስብዕናሽን እንዴት አይኔ እያየ በርሃብና በመከራ አፈር ስትሆኝ እያየሁ “አዘንሁ” ልበልሽ እታበባዬ? ምንም ማድረግ ያለ መቻል ሲኦል ውስጥ ነኝ። ፀፀትና ጥፋተኝነት እንደ እሳት ነፍሴን በዝምታ እያቃጠላት ነው። 

እንዴት “ኧረ የወገን ያለህ፣ የመንግስት ያለህ፣ ከቶ ሰው አይደለንምን፣ የነፍስ መግቢያ እንሆናችኋለን ነፍሳችንን አትርፉልን” የሚል ተማፅኖሽን፣ ጣርሽን ሰምቼ ምንም ማድረግ አለመቻል ግን እንዴት ያለ ቅጣት ነው? ‘ምነው ባልፈጠርስ፣ አቤት የእዳዬ ሸክም ክብደቱ’ እላለሁ ለእኔው። አትዘኝብኝ😥

ይሄንን ለመናችሁን የሚሰማ የመንግስት ባለስልጣን በቴሌቪዥን ብቅ ይልና፣ በእናንተ መከራ የለሰለሰ ምቾቱ ፊቱ ላይ እያንጠባረቀ “በርሃብ የሞተም፣ የተጎዳም የለም። ቢኖር ኑሮ በስልኩ ቀርፆ ‘ተራብሁ’ ይል ነበር” ብሎ ይዘባበትባችኋል። አቤት ይሄን መስማት ደግሞ እንዴት የባሰ እንደሚያም። ከርሃቡ በላይ የመንግስት አሽሙር ይገድላል። ባትሰሙት በተሻለ እህትወይ።

አሁን ባለፈው እዚህ አዲስ አበባ አንዲት ደሳሳ ቤት ቡና ልጠጣ ጓደኞቼ ጋር ተቀምጬ ነበር። ለመለመን በሚሰቀቅ ስብዕናቸው እጃቸውን ለምፅዋት የሚዘረጉ ወገኖቼን ብዛትና መጎሳቆል፣ የሰው ፊት እሳቱ የሚያደርጋቸውን ማየት አሰቃቂ ነው። 

ብዙዎቹ ለጋ ህፃናት ናቸው። እነዚህ ህፃናት በደጉ ጊዜ ቢሆን ጧት ቂጣ በወተት ቁርሳቸውን በልተው፣ አቀበት ቁልቁለቱን እየተፍለቀለቁ፣ እየተሯሯጡ ደብተራቸውን አንግበው ትምህርት ቤት የሚሄዱ ነበሩ። ፊደል በሚቆጥሩበት፣ በሀገራቸው ባንዲራ ፊት ቁመው በሚዘምሩበት አንደበት “አባባዬ ዳቦ ግዛልኝ” እያሉ የአዲስ አበባን ህዝብ ፊት ይማፀናሉ። ላያገኙ ስንቱን በቁልምጫ ሲጠይቁ ይውላሉ መሰለሽ።

ያገራቸው ባለስልጣን ግን “ውሸት ነው አልተራቡም” ይላቸዋል። ይክዳቸዋል። ደጋግሞ ይገድላቸዋል። የማሽላው፣ የጤፉ፣ የወተቱ፣ የቅቤው ባለቤት ሁነው ለአገሬው በልቶ ማደር የነበራቸውን ሚና በጦርነት የነጠቃቸው መንግስታቸው ግን ዳግሞ ርሃባቸውን ክዶ ይቀጣቸዋል። 

እህትወይ እኔ ይህን እያየሁና እያወቀሁ ምንም ላደርግ ላልቻልሁት እዘኝልኝ😪…. “ተማርልን። አንተ እንኳ ለቁም ነገር በቅተህ ችግራችንን ብትፈታልን” ብላችሁ በጨለማ እየዳከራችሁ ወደ ብርሃን ተራራ ያወጣችሁኝ፣ ህይወታችሁን እንደ ሻማ እያቀለጣችሁ ወደ እውቀት ብርሃን የሸኛችሁኝ እኔ አደራዬን በላሁ እናትዓለሜ። አቤት አደራን መብላት፣ ሲፈለጉ አለመድረስ፣ ተስፋን ማጠውለግ ህመሙ! መጥኔ።

እዚሁ ቁጭ ባልሁበት ቡና መሸጫ ቤት በረንዳ አበባ ቄሱ መጡ።  የቀደሱበትን፣ ያቆረቡበትን፣ እግዜርን ያመሰገኑበትን ደብር ጥለው አዲስ አበባ መጡ። የሚለመኑት እሳቸው ይሄን ሀጢያተኛ ህዝብና መንግስት ቁራሽ ዳቦ እየለመኑት ነው። ስጋ ወደሙን ፈትተው ሰማያዊው መና የሚያቀበሉት ቄስ ይሄው ጦርነት፣ ድርቅና ርሃብ ተባብረው ሞትን ሽሽት፣ ቁራሽ ፍለጋ እንዲፈልሱ አደረጓቸው።  አምላክ ለፈተና የላከብን ይሆኑ ይሆን? መቼም ለእንዲህ አይነቱ ፈተናስ ወድቀናል።

የነተበ የክህነት አርማ የሆነው ጥምጣማቸው አናታቸው ላይ አለ። አይ አባቴ ይሄ ህዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔር አለው መስሏቸው እኮ ነው። ይቅር ይበሉን። “ልጆቼ ስለ ወላዲቱ፣ ስለ መድሃኒተዓለም ቁራሽ ተዘከሩኝ” ይላሉ። የሚሰጥ የለም። ሁሉም በሀፍረት ይሁን በቸልታ እንጃ ብቻ አንገቱን ደፍቶ ያሳልፋቸዋል። 

እኔ ግን ይጦረኛል ያሉትን የበላ ጦርነት፣ መቁንናቸውን ያመከነ ድርቅ፣ መራባቸውን የካደ መንግስት፣ ውለታቸውን የበላ ህዝብ ፊት ቁመው መልስ ያጡት ካህን ከሃጢያታችን እየፈቱን ይሄዱ ይሆን እላለሁ። በእንዲህ ያለው የስቃይ ችንካር ከመሰቃየት የባሰ አለ ይሆን? የሚል እረፍት የሚነሳ አቅመቢስነት የወለደው ፍርሃት ይንጠኛል። ተስፋችሁን የበላ ትውልድ አካል መሆኔ ያሳፍረኛል። ጥፋቴ ርቃኑን ይታየኛል። የምደበቅበት ጥፍር አጣሁ😪

እናትዓለሜ “ተመስገን” የምትይው አምላክ ይሄን ሁሉ እያዬ ይሆን? የሚል ጥያቄ ላነሳብሽ እልና የእኔ መጠራጠርን የሚያመክን እምነትሽ “አምላክ እንደ ሰው አይደለም”  ትዝ ይለኛል። በሰው ላይ ተስፋ የማድረግ ነገር እዚህ የመከራ አዙሪት በነገሰበት አገር እንዳልሽው አይሆንም። ግን የሰው መልኩ ሰው ነውና “ተለመኑኝ” የሚል ልመናሽ የማንን ልብ ያራራ ይሆን? ምናልባት የአምላክሽን? እንጃ ብቻ…..  እዝጎ ነው መቼም የሚባለው!

እህትዓለሜ እኔስ ቀኑ ይራራላችሁ እንጅ በሌላው ተስፋ እያጣሁ ነው–በእኔ በእራሴ ሳይቀር። የመንግስትን ነገር ተይው አይነሳ። “ቢቸገር ጨው ብድር” እንዳልሽው ነው። ብቻ እምነታችሁ ይርዳችሁ😥
_

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here