spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትበኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት ያስነሳው አቧራ ሲፈተሸ!

በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት ያስነሳው አቧራ ሲፈተሸ!

በሲሳይ መንግስቴ

መግቢያ

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድና በሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ መካከል ከወደብና ባህር አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለመጭዎቹ 50 አመታት ለንግድና ለጦር ሰፈርነት እንድትጠቀምበትና በምትኩም ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ኪራይ በገንዘብም ሆነ በአይነት ልትከፍል እንዲሁም ከኪራዩ ታሳቢ የሚሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ከሌላ አትራፊ የንግድ ድርጅት ድርሻ እንዲኖራት ለማድረግና ከኢትዮጵያ መንግስት እንደ ሀገርም እውቅና ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ 

ይህንን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ፕሬዚዳንት ወዲያውኑ ተቃውሟቸውን በመግለጻቸው ምክንያት አንዳንድ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች ሁኔታው እንደሚያሳስባቸው መግለጽ ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድና የአረብ ሊግ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አገራት የተፈጠረውን ውጥረት በሰላማዊ መንገድና በንግግር እንዲይይዙት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፣ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ሀሳብ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ 

ይህም ከፊሉ መንግስት የወሰደውን አቋም በመደገፍ ኢትዮጵያ ለህልውናዋ ስትል የወደብ አገልግሎትና የባህር በር ለማግኘት ያደረገችው ስምምነት ስለሆነ ተገቢ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ዕውቅና ውጭ የተደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ውግዘት እያስከተለባት ነው፣ በዚህም ሳቢያ ተጎጅ ትሆናለች የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ የክርክራቸውን ሀሳብ ሲያጠናክሩም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከዲፕሎማሲው ዓለም እየተገለለች ነው፣ የዓለም አቀፍንም ሆነ አህጉራዊ ህጎችን በመጣስ የተደረገ ስለሆነ ችግር አለበት በማለት በደምሳሳው ስሜታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ጽሁፍ በአጭሩም ቢሆን ለመዳሰስ የሚሞከረው ክርክሮቹ ተገቢ ናቸውን? የሚለውን ሀሳብ በመፈተሸ በማስረጃ አስደግፎ ዕውነትን መግለጽ ነው፡፡ 

የመግባቢያ ሰነዱ ይዘት ምን ይመስላል?

በሁለቱ ወገኖች የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ይዘት ሲፈተሽ በዋነኛነት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን የሚሸፍን ሆኖ እናገኘዋለን፣ ይህም ማለት አንደኛው ኢትዮጵያ የበርበራን ወደብ ለቀጣዮቹ 50 አመታት በሊዝ ውል ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ላይ የደረሱ መሆናቸውን የሚገለጽ ሲሆን ሁለተኛው ከበርበራ ወደብ ጋር በተያያዘ 20 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን የባህር አካባቢ ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት (የባህር ሀይል) የሚሰፍርበት ቦታ እንዲኖራት የሚፈቅድ ነው፡፡ በምትኩ ደግሞ ኢትዮጵያ ለወደቡ ከምትከፍለው የ50 አመት ሊዝ ዋጋ ላይ የሚታሰብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ከሌላ መንግስታዊ የልማት ድርጅት ድርሻ እንዲኖራት ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ የሶማሌላንድ ልኣላዊ ሀገር እንድትሆን ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷን ይገልጻል፡፡ 

ይህንንም እውነታ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ ላይ የመግባቢያ ሰነዱን በፈረሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በማያሻማ መልኩ ገልጸውታል፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ የመንግስትም ሆነ የፓርቲ ባለስልጣናትና በመንግስት የሚደገፉ የመገናኛ ብዙሀንና የዩቱብ ተንታኞች ይዘቱን በማዛባት ኢትዮጵያ በቀይ ባሀር ወደብና የባህር ሀይል መስፈሪያ ቦታ አገኘት በማለት በሰበር ዜና መልክ ሲገልጹት ሰምተናል፡፡ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ቀን የመንግስት ኮምኒኬሽን ባወጣው መግለጫ የባህር በርና ወደብ የተገኘው በቀይ ባህር ዳርቻ ሳይሆን በኤደን ባህረ ሰላጤ መሆኑን ገልጧል፣ይህም የተሳሳተ አገላለጽና የተጋነነ አቀራረብ አሁን ላይ እያየን ያለውን ውዝግብ አስነሳ፡፡

የክርክሮቹ (ውዝግቦቹ) አግባብነት ሲፈተሸ

የመንግስት ባለስልጣናት፣ የብልጽግና ደጋፊ የማህበራዊ ሚዲያ ተንታኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ በጭፍኑ ደግፈው ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው እንዲሁም ቋሚ ስምምነት እንደተፈረመ አድርገው በመቁጠር ሀሳባቸውን ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስምምነቱን የሚቃወሙ ኢትዮጵያዊያንን ባንዳ እስከማለት ደርሰዋል፣ እነዚህ ወገኖች ሀሳባቸውን የሚያቀርቡት የስምምነት ሰነዱን ትክክለኛ ይዘት በመረዳትና ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በአግባቡ ተገንዝበው ሳይሆን እንዲሁ በጭፍን ድጋፍና ባልተጨበጠ ህልም ላይ ተመስርተው እንደሆነ ከክርክር አቀራረባቸው ስሜታዊነትና ወገንተኛነት መረዳት ይቻላል፡፡ 

በተቃራኒው ይህንን የመግባቢያ ስምምነት የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ ይኸ ስምምነት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በአግባቡ ከመመዘን ይልቅ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ብቻ በማጉላት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ፓርቲያቸው ብልጽግናን ለማውገዝ ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ አስገራሚው ነገር እነዚህ ወገኖች ምናልባትም ከሶማሊያ ፌዴራል መንግስት በላይ ለጉዳዩ ትልቅ ቦታ ሰጥተው ሲዘግቡና ትንሹንም ትልቁንም የተቃውሞ መግለጫ በማንሳት በማጋነን ጭምር የኢትዮጵያን መንግስት ለማውገዝ ሲጠቀሙበት መመልከታችን ነው፡፡ 

በዚህ ረገድ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድና የአረብ ሊግ እንዲሁም ግብጽ፣አሜሪካ፣ ቻይና፣ ቱርክና የመሳሰሉት አገራት ጉዳዩ ያሳስበናል በማለት ያወጡትን የተለሳለሰ መግለጫና አንዳንድ የኬኒያ የፓርላማ አባላት የሰጡትን ጠንከር ያለ አስተያየት መሰረት በማድረግ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጠቅላላው ኢትዮጵያን እንደተቃወመና እንዳስጠነቀቀ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደተገለለች አድርገው ሲያቀርቡ ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ስምምነቱ የጨረቃ ወደብ ስለሆነ የሚያስገኘው ጥቅም የለም እስከማለትም ደርሰዋል፣ 

እነዚህ ወገኖች የተቃውሟቸው መነሻ ብልጽግናን መጥላታቸው ይመስለኛል፡፡ ለዚህም እንደጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግለን የሚችለው ቀደም ሲል በኢሕአዴግ ይመራ የነበረው የኢፌዴሪ መንግስት የሚሰራውን የልማት ስራ ከመደገፍ ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ አሉታዊ ጎኑን በማጉላት ላይ ጊዜያቸውን ያጠፉ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ አሁንም ከዛ ስህተት ተምረን የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ይዘት በአግባቡ በመፈተሸና ያስነሳውን ተቃውሞና ያስገኘውን ድጋፍ በጥንቃቄ በመፈተሸ ሚዛናዊ ሀሳብ ከማቅረብ ይልቅ በጭፍኑ በመቃወምና በማውገዝ ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ማቅረብን የሙጥኝ ብለው እናገኛቸዋለን፡፡

የስምምነቱ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ደጋፊዎች መዘንጋት የሌለባቸው ነገር ቢኖር ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ የሚወስዷቸው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አቋሞች በተለይም በሌላ አገር ላይ ስጋትን የሚፈጥር ከሆነ ከተወሰኑ አካላት ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም በሒደት መልክ መያዙ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሰረት የሶማሌላንድ ወቅታዊ ሁኔታን ከሞንቴቪዶ ስምምነት አንጻር በመመልከት የስምምነቱን ህጋዊነት/ህገወጥነት መፈተሸ ተገቢ ነው፡፡ የሞንቴቪዶ ስምምነት እ.እ.አ በ26/12/1933 የተፈረመ ሲሆን ስራ ላይ የዋለው ደግሞ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ከ26/12/1934 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ 

በዚህ ስምምነት አንቀጽ 1 መሰረት የአንድን አገር ቁመና ለመመዘን ተቀባይነት ያላቸው መስፈርቶች ተብለው የተቀመጡት በቋሚነት የሚኖር ሕዝብ፣ ዳር ድንበሩ የታወቀ ግዛት፣ የመንግስት መኖርና ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት የመፍጠር አቅም የሚሉት ናቸው፡፡ ይህም ማለት አገር ለመባል በሌላ አገር ወይም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና ማግኘት የግድ እንዳልሆነ ከላይ ከተዘረዘሩት መስፈርቶች መረዳት እንችላለን፡፡ በሌላ አነጋገር በዚሁ የቃል ኪዳን ሰነድ አንቀጽ 3 ላይ የአንድ አገር መኖር ከሌሎች አገራት ዕውቅና መስጠት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ በማያሻማ አኳኋን ገልጾት እናገኘዋለን፡፡ 

ይኸው አንቀጽ ሁኔታውን ዘርዘር አድርጎ ሲያስቀምጥ አንዲት አገር ከሌሎች አገራት ዕውቅና ከማግኘቷ በፊት አንድነቷንና ነጻነቷን የማስከበር ብሎም ይጠቅመኛል ብላ ያመነችበትን አደረጃጀት የመፍጠርና ህግ የማውጣት መብት እንዳላትም ያስቀምጣል፡፡ ሌላው በዚህ ስምምነት ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ አንቀጽ 7 ሲሆን ዕውቅና በግልጽ ወይም በዝምታ ሊሰጥ እንደሚችል ማስቀመጡ ነው፡፡ በዝምታ በሚሆንበት ጊዜ ግን እያዳንዱ ድርጊት አዲሱን ሀገር ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ የሚደረግ መሆኑን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡ 

ከዛም ባሻገር በዚሁ ቃል ኪዳን አንቀጽ 11 ላይ የተቀመጠውን ዝርዝር ሁኔታ ስንመለከት በጦር መሳሪያ በተደገፈ ሀይል ወይም በዲፕሎማቲክ ማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ጫና አሊያም በማንኛውም አይነት አስገዳጅ እርምጃ የተደገፈ ስምምነት ከተደረገ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያስቀምጣል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን አስገዳጅ ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ የኢትዮ-ሶማሌላንድ የወደብና የባህር በር አጠቃቀምን አስመልክተው ያደረጉትን የመግባቢያ ስምምነት ስንመረምረው የሶማሌላንድ መሪዎች ወደውና ፈቅደው ያደረጉት ስምምነት ሲሆን በምትኩም ከኢትዮጵያ የሊዝ ኪራይ የሚያገኙበት መሆኑን አረጋግጠው የገቡበት ስምምነት መሆኑን እንመለከታለን፡፡ 

በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ ላይ የሀይል እርምጃም ሆነ ሌላ አይነት ስጋት የሚፈጥር ጫና አሳድራ የገባችበት ስምምነት ሳይሆን የጋራ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል በድርድርና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመግባባያ ሰነድ ስለተፈራረሙ ህገወጥ ነው ሊያስብል የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና መስጠቷ የሚጠቅማት መሆኑን ካረጋገጠች በግልጽም ሆነ በተግባር ዕውቅና ለመስጠት መወሰኗ ወንጀል አይደለም፡፡ 

ይህ ማለት ግን ምንም እንኳ ሶማሌላንድ ላለፉት 32 አመታት ቀደም ሲል የነበረው የሶማሊያ መንግስት መፍረሱን ተከትሎ ራሷን በራሷ ስታስተዳድር የቆየች ሲሆን የፌዴራል መንግስት ከተቋቋመ በኋላም ቢሆን የፌዴራል መንግስቱ አካል ሆና ያልቆየች ብትሆንም የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት አሁንም ድረስ እንደራሱ አካል አድርጎ ስለሚቆጥራትና ህጋዊ በሆነ መልኩ የተለያዩ ባለመሆናቸው በድርጊቱ መከፋቱ አይቀርም፡፡ 

ይህንንም መከፋት ደግሞ ከቻለ በሀይል ካልሆነለት ደግሞ በፖለቲካና በዲፕሎማሲያው ዓለም የቻለውን ያህል በመጮህና በማስጮህ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥረት ማድረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት አሁን ላይ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም ይህንኑ እውነታ ያመለክታልና ያን ያህል የማይጠበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ አስገራሚ የሚሆነው ነገር የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ለጉዳዩ ከሚገባው በላይ ትኩረት ሰጥተው የማሽቃበጣቸው ጉዳይ ነው፡፡     

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. አንባቢ ወይም የአፍሪቃ ቀንድ የፓለቲካ ትኩሳትን የሚከታተል ሰው መጠየቅ ያለበት ከ 30 ዓመት በላይ ከዋናው ሶማሊያ ተቆርሳ ራሷን በሰላም የምታስተዳድረው ሱማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው የባህር በር ስምምነት ሳቢያ ከአረቡ እስከ ነጩ ለምን አሽካካ በማለት ነው። ጉዳዪ ግልጽ ነው። የኢትዮጵያን መበልጸግና ብሎም ማደግ ሌላው ዓለም አይፈልገውም። ሁልጊዜ የእነርሱ አገልጋይና ተመጽዋች ሆነን እንድንኖር ነው የሚፈልጉት። ይህ ዝም ብዬ በጥላቻ የማወራው ሳይሆን ሲፈተሽ ካለፈና ከአሁን የአረብና የነጩ ዓለም የተንኮል መድበል ውስጥ ተፈልጎ የሚገኝ ነው። ይሁን እንጂ አሁን በሃርጌሳና በአዲስ አበባ ያለው ሽርጉድ ፍሬ አልባ እንደሚሆን መገመት ከባድ አይሆንም። በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣልና! ለዚህም መረጃ የሚሆነን ከኤርትራ ጋር የብልጽግናው መንግስት የነበረው የጫጉላ ቤት ሆያ ሆየ አሁን በጥላቻና በመጠራጠር መተካቱ ነው። ድሮም ቢሆን ሻብያ ለወያኔ ካለው ጥላቻ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ከሚል እንጂ ሻብያ የኢትዮጵያን ብልጽግናና ሰላም ተመኝቶ አያውቅም። ኢትዮጵያ ቅኝ አድርጋን ነበር የሚሉት እነዚህ የፓለቲካ ሙቶችና ደጋፊዎቻቸው ከ 30 ዓመት የመገዳደል ፓለቲካ በህዋላ እንሆ ዛሬ አፍሪቃዊቱን ሰሜን ኮሪያን መስርተዋል። በምድሪቱ ከስደት ተርፈው ለሚኖሩት ይመቻቸው። የሚያሳዝነው እግሬ አውጭኝ እያሉ በየዓለማቱ ሁሉ ተበታትነው በየደረሱበት ሁሉ እየተከፋፈሉ ሲፈነካከቱና ያስጠለሏቸውን ሃገሮች ንብረትና ሃብት ሲያወድሙ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ነው። በቅርቡ በአውስትራሊያ የሆነውን አንባቢ ልብ ሊል ይገባል።
    የ2024 የገመና ሪፓርት እንደሚያመለክተው የአሜሪካው ዶላንድ ትራፕ ከተመረጠ ዓለም ሁሉ የመከራ ባህር ትሆናለች ይላል። ጭላንጭሉ የአሜሪካ ዲሞክራሲም አፈር አባቱ እንደሚገባ አስረግጦ ያስጠነቅቃል። እውነት በአሜሪካ እንደሌለች የሚያሳየው ለሰማይ ቤት አድረናል የሚሉ ይህን የደምና የጥላቻ ሰው መደገፋቸው ነው። በአሜሪካ እውነት ቀደም ሲል ተንጋዳ ከሆነ ከትራፕ ምርጫ በህዋላ ምድር ላይ ትጎተታለች። ይህ በዚህ እንዳለ የኢራንና የፓኪስታን በሚሳኤል መደባደብ፤ የሃማስና የእስራኤል ፍትጊያ፤ የየመን ተተናኳሾችና የህዝቡላ እሳት ውርወራ ከዪክሬንና ራሺያ ግጭት ጋር ተዳብሎ ዓለምን እንደሚንጣት ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። የአዲስ አበባውና የሃርጌሳው ስምምነት ያስነሳውም አቧራ ከዚሁ ከዓለም የፓለቲካ አሰላለፍ ጋር የተቆራኘ ነው። የመቋዲሾው መንግስት ለኢትዪጵያ ጦርነት ዝግጅ ነን ሲል ከካይሮና ከአስመራ ጋር መክሮ ነው። ግን ጦርነት ቢነሳ አንድም አትራፊ አይኖርም። የእብድ ገላጋዪች እሳትና ጭድ እያቀበሉን ከመተላለቅ ሌላ። ስለ ጦርነት አስከፊነትና ከንቱነት ማወቅ የፈለገ ሰው Conquest to nowhere by Anthony B. Herbert ማንበብ ማለፊያ ግንዛቤን ይሰጣል። ስለ ሱማሊያ ያለፈ ሃበሳና ገመና ደግሞ Call Me American by Abdi Nor Iftin መጽሃፍ ፈልጎ ማንበብ ነው። ግፍ የማይለየው የአፍሪቃ ቀንድ ጅቡቲ ላይ ከሃገራቸው እርቀው ስለ ሰፈሩት ሃገሮች የዓረብ ሊግ ጭጭ ሲል ገና ኢትዮጵያ በሱማሊያ በኩል የባህር ወደብ ታገኛለች ሲባል አካኪ ዘራፍ ያስባላቸው የጥቁር ህዝቦችን ልዕልና እና ጥንካሬ በጭራሽ ስለማይፈልጉት ነው እንጂ ለሱማሊያ አንድነት አስበው አይደለም። ማን ሆነና አልሸባብን የሚያስታጥቀውና በንዋይ የሚረዳው?
    በማጠቃለያው ኢትዮጵያ በዘር፤ በቋንቋ፤ በሃይማኖትና በክልል ዙሪያ ያሉ የፓለቲካ ሽኩቻዎችን በመተው በመስማማት በአንድነት የውጭና የውስጥ ጠላትን መመከት እስካልቻሉ ድረስ የሃበሻዋ ምድር ከሱዳን በከፋ መልኩ ማጥ ውስጥ ትገባለች። የብሄር ነጻ አውጭዎች ባርነት አራማጆችና መከራ አዝናቢዎች መሆናቸውን ህዝባችን ሊረዳ ይገባል። ከእርስ በእርስ የጦርነት አባዜ ካልተላቀቅን የምድሪቱ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በዘሩም ሆነ በቋንቋው ወይም በሃይማኖቱ ነግጄ አተርፋለሁ ያለውም ቢሆን እየከሰረ ተያይዞ ዋይታ እንደሚሆን ልናውቅ ይገባል። በምድር ላይ እሳት ለኩሼና አስለኩሼ ሃገር ጥዬ እወጣለሁ ብሎ የሚያስብም ካለ አሁን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራሊያ በስደተኛ ላይ ያለውን ጥላቻና ፍራቻ ያልተገነዘበ ብቻ ነው። የእንግሊዝ መንግስት ደጃፉ ላይ የደረሱ ስደተኞች ወደ ረዋንዳ ለመላክ ማሰቡ አንድ የበቃኝ ምልክት ነው። ገና ብዙ ነገር ይከተላል። ስለሆነም ሃገርን ሰላም አድርጎ ተረጋግቶ ከዘመድ አዝማድ ጋር የተገኘውን ተካፍሎ መኖር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የሃርጌሳውንና የአዲስ አበባውን የወደብ ስምምነትና ሌሎችንም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚያስረዳን ጊዜ እንጂ የእኔም ሆነ የሌሎች የፈጠራ ዜና አይሆንም። ጠብቀን እንይ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here