spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትፋኖ 4 ኪሎ ሲገባ የምመክረው (ፖሊሲ 1)

ፋኖ 4 ኪሎ ሲገባ የምመክረው (ፖሊሲ 1)

ደሳለኝ ቢራራ
ደሳለኝ ቢራራ

በደሳለኝ ቢራራ

መግቢያ

የሀገራችን ዋና ችግር የብሔር ፖለቲካ እንደሆነ በርካታ ምሁራን እና ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ያነሳሉ። የብሔር ፖለቲካን በህግ ማእቀፍነት ጽኑ መሰረት ሁኖ እሚያገለገለው ደግሞ ህገመንግስቱ እንደሆነ ያስረዳሉ። ህገመንግስቱ ከቁጥጥር ውጭ ለሆነ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ጭምር ከለላ ሁኖ ቆይቷል።  በዚህ የተነሳ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ህገመንግስታዊ ነው ማለት ይቻላል። 

አረመኔያዊ ስልጣን ጥመኞች ይህን ብሔርተኝነት በሀሰት ትርክቶችና የጥላቻ አስተምህሮዎች በመመረዝ አንዱን ብሔር የሌላው ጠላት አድርገው በማቅረብ  በህዝብ ፍጅት ላይ የተመሰረተ ገደብ አልባ ስልጣን ለመያዝ ለበርካታ አስርት አመታት ተጠቅመውበታል። የተዘራው ስሁት አስተምህሮና ጥላቻም አሜከላ ሁኖ በቅሎ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ንጹሀን ዜጎች በብሔራቸው ተመርጠው ከቀያቸው እንዲሳደዱና እንደ በግ ታርደው እንዲበሉ ሁሉ አድርጓል።  ጥላቻ በዚህ ደረጃ ከሞራል ገደብ ያለፉና ሰብአዊ ያልሆኑ ባህሪያትንም እንዲታዩ አድርጓል። 

ይህ አውሬነትና አረመኔነት ከስልጣን ጥመኛ ሴረኞች አልፎ የበርካታ ወጣትና በጥላቻ ያበዱ ጽንፈኞች መገለጫ ሁኗል። የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ከልሂቃኑ አልፎ ቀላል በማይባል መጠን በህዝብ ደረጃ የሚንጸባረቅ ባህሪ እስከመሆን በመድረሱ አሳሳቢ ነው። በህዝቦች መካከል መጠራጠርንና ብሔር ዘለል መስተጋብሮችን ከማቀዝቀዝ አልፎ ሀገርን የመበተንም ተጽእኖ ይኖረዋል። ይህ ወቅታዊው የሀገራችን ህዝብ ነባራዊ ሁኔታ ነው። 

ችግራችን ምንድን ነው?

ብዙሀኑ ልሂቃን እንደሚያቀርቡት ትንተና የሀገራችን ችግር ህገመንግስቱ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ቀላል በሆነ! መፍትሔ ብለው የሚሰጡትን የህገመንግስት መቀየር ሀሳብ መተግበሩ አጭር የውሳኔ ጉዳይ ነውና ቶሎ ለውጥ ማምጣት በተቻለ ነበር። ችግሩ ግን ከህገመንግስቱ ያለፈ እና የገዘፈ በብዙውም የተዋለደ መሆኑ ነው።  በዚህም የተነሳ  የህገመንግስቱ መሻሻል ህገመንግስቱ የፈጠራቸውን ችግሮች አያጠፋቸውም። 

የብሔር ልዩነት እስካለ ድረስ፥ የተፈጠሩት ስሁት ትርክቶች እስከሰረጹ ድረስ፥ ጥላቻው ከደምና አጥንት ድረስ ዘልቆ በተዋሃደበት ደረጃ የህገመንግስት መሻሻል በነዚህ ህዝቦች መካከል የተነሳን መጠላላት ለማስቀረት ፋይዳው አይታየኝም። ህገመንግስቱኮ መፍጠር የሚችለውን ያህል ጥላቻ ከሚገባው በላይ ፈጥሮ አጠናቋል። ሌሎችንም አዋልድ ችግሮች አራብቶልናል። 

ስለዚህ የሀገሪቱ ችግር ከህገመንግስቱ የበለጠ ነው። በመሆኑም ህገመንግስቱ ቢሻሻልም ችግሩ ይኖራል። በዋናነት ችግሩ ብሔር ነው። የብሔር ልዩነት መኖር ከተፈቀደለት ወደ ጽንፈኝነት መሄዱ ተፈጥሯዊ እድገቱ ነው። ብሔርን እንደ መደብ ማንነትም፥ እንደ ዘር ማንነትም፥ እንደ ባህል ማንነትም፥ እንደ ማህበራዊ-ፖለቲካ ማንነትም እንደ ኢኮኖሚ ማህበረሰብም ሊጠቀመው ይችላል። በሁሉም ሁኔታዎች ከአቻዎቹ ጋር ፉክክር፥ ውድድርና ተቃርኖ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው። ጥቅሜን አስከብራለሁ ወይም በላጭ እሆንበታለሁ በሚለው አሰላለፍ የሚፈልገውን አስተሳሰብ ሊያራምድ ይችላል። ጽንፈኝነቱ የሚፈጠረው በዚህ ሁኔታ ነው። “ብሔር” በሚባል ማንነት ንኡስ ሀገር መሆን የሚችል ማህበራዊ ስነልቦናና ውቅር ባይኖር ኖሮ ግን በሀገራችን ውስጥ ዜግነት መስፈን ይችላል። ሰው እንሆናለን። የአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ችግራችን ብሔር ነው። ብሔርን ደግሞ በቀላሉ ማጥፋት ይቻላል። 

በርካታ ሀገራት በተለያየ ዘመን ላጋጠማቸው የህልውና ፈተና እንደ ችግሮቻቸው አይነትና ባህሪ ተገቢውን የመፍትሔ እርምጃ በመውሰድ ህዝባቸውን ከመጥፋትና ሀገራቸውን ከመፍረስ ታድገዋል። በዚህ ደረጋ ግዙፍ ችግሮችን እልባት ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ጊዜ ከዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች አኳያ ብዙ እንከን የሚነሳባቸውና መንግስታቱንም አንባገነናዊ ባህሪ የሚያላብሱ ናቸው። ሆኖም ግን ችግሮቹ ሊያስከትሉት ከሚችለው ጥፋት ጋር ተመዛዝኖ እንጅ ምርጫ መወሰድ ያለበት ሁሉም ችግሮች አልጋ በአልጋ የሆነ መፍትሔ እንደማይኖራቸው ግንዛቤ መያዝ አለበት። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት የቻይና ብሔራዊ ስጋት የህዝብ ቁጥር መጨመር ነበር። በምንም ሁኔታ ህዝቡም መመገብና ስራ ሰጥቶ ማስተዳደር የማይቻልበት ደረጃ ከተደረሰ ወደ ውሱን ሀብቶችን መሻማትና እልቂት ውስጥ ነው የሚገባው። በመሆኑም የወሊድ መጠን ላይ ቁርጥ ያለ ገደብ በመጣል ነው የህዝቡን መጠን መቆጣጠር የተቻለው። ልጅ ደጋግመው መውለድ የሚፈልጉ ቤተሰቦችን በህግ መገደብ ግን የዜጎችን መብት መግፈፍ ወይም የመንግስት አምባገነንነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለዚህ ነው ህዝብን ለጥፋት ከሚዳርግ መብት ይልቅ አምባገነንነት ጠቃሚ የሚሆነው። 

በሀገራችን ኢትዮጵያም በትውልድ ላይ የሚሰራ የፖሊሲ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር ከደምና ከአጥንቱ ጥላቻ የተዋሀደውን ትውልድ በህግና በሞራል መሳሪያዎች መያዝ በማይቻልበት ደረጃ ደርሷል። የብሔር ልዩነት እና የእርስ በእርስ ጥላቻው በየጊዜው እየሰፋ እና እየተወሳሰበ ነው የሚሄደው። ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከተለያዩ አደረጃጀቶች አልፎ የህዝቡ ባህሪ ሁኗል። ከዚህ በኋላ በብሔር መደራጀት በህግ ቢከለከልም፥ የብሔር ፓርቲዎች ቢበተኑም፥ ከህዝቡ የሰረጸውን አመለካከትና ጥላቻ መበተን አይቻልም። የብሔር ጥላቻ የየዕለት ህይወትና የመስተጋብር ደንብ ተደርጎ ነው የሚለመደው። በአጭሩ ጥላቻ ባህል ይሆናል። 

መፍትሔው

በብሔር ልዩነት ምክንያት ለመጣብን ችግር መፍትሔው ብሔርን ማጥፋት ነው። ብሔርን ማጥፋት የሚቻለው ህዝቡን በሚያቀላቅልና በሚያዋህድ ስልት ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁነኛው ዘዴ የጋብቻ ፖሊሲ ማርቀቅ ነው። 

የጋብቻ ፖሊሲ

የጋብቻ ፖሊሲው በተመሳሳይ ብሔር ላይ ጋብቻ እንዳይደረግ የሚከለክልና ተጋቢዎች ከተለያየ ብሔር እንዲሆኑ የሚያስገድድ መሆን ይችላል። ከሚያስገድዱ ህጎች በፊት ደግሞ ከተለያዬ ብሔር መጋባትን የሚያበረታቱ ስነስርአቶች፥ ክንዋኔዎችና እውቅናዎች በስፋት ልምምድ እንዲደረግባቸው ማመቻቸት ይቻላል። ሳቢ ሁኔታን መፍጠር ቀላል ነው። በዚህ መንገድ ለሚጋቡ ጥንዶች በተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶች ቅድሚያ የሚሰጡበትንና አንጻራዊ መብቶቻቸው የተሻለ የሚጠበቁበትን አሰራር በሲስተም መዘርጋት ይቻላል። ለምሳሌ በጤና አገልግሎት ዘርፍ የሚያገኙትን ጥቅም ከሌላው የተሻለ ማድረግ፤ በትምህርትና ሌሎችም አገልግሎቶች ከነጻ ተጠቃሚነት እስከ ዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚነት ድረስ መብት እንዲኖራቸው በማድረግ ከተለያየ ብሔር የሚጋቡ ሰዎችን ፍላጎት ሳቢና አበረታች መንስኤዎችን ማመቻቸት ይቻላል። በማህበረሰቡ ውስጥም ክብርና ሙገሳ እንዲሰጣቸው የሚያደርጉ የሰርግ ክንዋኔዎችን ማመቻቸት ይቻላል። 

በዚህ ሁኔታ በአንድ ትውልድ ወይንም በሰላሳ አመት ውስጥ ብሔር የሚባልን ነገር ሙሉ በሙሉ ከሀገራችን ማጥፋት ይቻላል። ሰው ሳይሞት፥ ዘር ሳይጨፈጨፍ፥ ክፉ ዜና ሳይሰማ፥ ስደትና እልቂት ረሀብ ሳይከሰት፥ ምንም ጦርነት ሳይገባ ብሔር ይጠፋል። ከተለያየ ብሔር የተጋቡ ወላጆች ያለው ልጅ ኢትዮጵያዊ ብቻ ማንነት ይኖረዋል። ዜጋ ብቻ ይሆናል። ከማንም አቻ ዜጋው አያንስም፤ አይበልጥምም።   

አዲሱ ትውልድ ብሔር አይኖረውም። የየትኛውም ብሔር ታሪካዊ በደል ወይም ልዩ ጥቅም ተወቃሽም ሆነ ባለቤት አይሆንም። የሀገራችን አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ገጽታዎች የሁሉም ዜጎች እኩል የታሪክ አካል ይሆናሉ። “የአንተ አያት የኔን አያት በድሎታል” ብሎ ብሶት የሚሰማው ዜጋ አይኖርም። ሁሉም ከሁሉም የተዳቀለ በመሆኑ የልማቱም የጥፋቱም፥ የኩራቱም የሀፍረቱም እኩል ባለቤት ይሆናል። የኢትዮጵያን ታሪክ አሉታዊውንም ሆነ አወንታዊውን ሁሉም እኩል ባለቤት ይሆኑበታል እንጅ “ይህ የእኛ ታሪክ፡ ያ ደግሞ የእናንተ ታሪክ” የሚሉት ምንም ነገር አይኖርም።

አዲሱ ትውልድ ዘር ቆጥሮ ይሄ የኔ ነው የሚለው ታሪክም ሆነ መሬት አይኖርም። በዜግነት የሚገባውን ጥቅምና የሚከበርለትን መብት ብቻ በህግ የሚያስከብር ነው የሚሆነው።  

አዲሱ ትውልድ ከተለያየ ብሔር ወላጆች የተገኘ ስለሚሆን ከወላጆቹ ዘረመል መራራቅ የሚያገኘው በርካታ ጥቅም አለ። በሽታ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ይሆናል፤ የአእምሮ እድገቱና የሰውነት ጥንካሬው ፈጣንና ብርቱ ይሆናል። ማህበራዊ ህይወቱና ተግባቦቱም የተሻለ ይሆናል። ይህ በዘረመል ውህደቱ የሚገኝ ሳይንስ ደጋግሞ ያረጋገጠው ጥቅም ነው። 

ተግዳሮቶች

ይህ አዲስ ትውልድ እንዳይፈጠር የሚያደርጉት በርካታ እንቅፋቶች ይኖራሉ። ዋናዎቹ እራሳችን አሁን ያለነው በራሳችን ቋት ልክ የምናስበው የየብሔሩ ጠባቦች እና ጽንፈኞች ነን። 

በመጀመሪያ ዘራችን እንዳይቀላቀል እና እራሱን ችሎ እንዲቀጥል የምንፈልግ እብሪተኞች፥ የእኛ ዘር ከሌላው ይበልጣል ብለን የምናስብ፤ በዚህ ሀሳባችን እኛም ያልተጠቀምን ልጆቻችንም እንዳይጠቀሙ የምንከለክል የራሳችን ጠላቶች እንኖራለን። ፖሊሲውን ተቃውመንም እንነሳለን። የመንግስት ቁርጥ አቋም መሆኑ ሲታወቅ ግን በጊዜያዊነት ተነስቶ የሚበርድ የተቃውሞ ማእበል ነው የሚሆነው። ፖሊሲው የሚተገበረው በአንድ ትውልድ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ህዝቡ እንዲቀየጥ በሚያደርግ መልኩ እንደ ባህል የጋብቻ ልማድ በሚሆንበት ደረጃ ነው። ስለዚህ የጋብቻ ፖሊሲው በሂደት ይለመዳል። 

ሁለተኛው ፈተና፡ አዲሱ ትውልድ የማንኛውን ብሔር ባህልና ማንነት ይዞ ይቀጥላል? የትኛውን ቋንቋ ይናገራል? የትኛውን ምግብ ይበላል? የትኛውን ልብስ ይለብሳል? ወዘተ እያልን በራሳችን ያልፈጸምነውን በልጆቻችን ላይ እንዲደረግ የምንፈልገው ስግብግብ ግለኝነት እና ቅናት ነው።  ይህ የእራስን ማንነትና መገለጫ የማውረስ ግብግብ ሊፈጠር የሚችለው የሚመጣውን ትውልድ ማንነት ባለማወቅ ነው። አዲሱ ትውልድ አሁን ካለነው የትኛውም ዘውግ ጋር አይመሳሰልም። ፈጽሞ የራሱ የሆነ ቅይጥ ማንነት ነው የሚኖረው። የመረጠውንና የሚመቸውን በፍላጎቱ የሚበላ። የሚለብስ። የሚናገር ነው የሚሆነው። “ቆጮ ካልበላህ ልጄ አይደለህም!” ብለን አናስፈራራውም ወይም “እንጀራ የነፍጠኛ ነው አትብላ!” ብንለው አይሰማንም። 

አዲሱ ትውልድ የራሱን ምርጫዎች በወቅቱ ከሚኖሩት ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር አመዛዝኖ እጣ ፋንታውን የሚወስነው እራሱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ቋንቋም ሊመርጥ ይችላል። የእኛ ትውልድ ግን በማያገባው ጉዳይ ወሳኝ አካል የመሆን ዝንባሌ ስላለው መሰናክል ከመሆን ወደ ኋላ አይልም። 

ሶስተኛው፡ “አሀዳዊነት! አሀዳዊነት!” የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች መሰማታቸው አይቀርም። ይህም አሀዳዊነትን እንደ ስድብ ከመለማመድ የመጣ እንጅ ምንነቱን እና የዚህን ፖሊሲ አላማ በውል ተረድቶ በተሻለ አማራጭ ለመሞገት አይደለም። ለጩኸቱ ግን የአሀዳዊነቱን ሂደትና በጎነት ማስረዳት ተገቢ ነው። አሀዳዊነቱ በእርግጥም ተፈላጊና ህዝብ አድን የሆነ ሀገር የሚታደግና የሚያሳድግ የማንነት ግንባታ ነው። ሆኖም ግን አዲስ በሚፈጠር ማንነት ነው አሀዳዊነቱ እንጅ አሁን ካሉት ብሔሮች ውስጥ አንዱን መርጦ ቀሪዎቹን ሁሉ እሱን እንዲሆኑ የሚገደዱበት አሀዳዊነት አይደለም። እንደዛ አይነት አሀዳዊነትማ ፋሽዝም ነው። ይህ ፖሊሲ የሚያፈራው ፍጹም በሆነ ውህደት አንድ የሚሆን ማህበረሰብን ነው። 

አራተኛው፡ “ሰዎች ያፈቀሩትን እንጅ በህግ የተወሰነላቸውን ሰው ማግባት አይገባቸውም” የሚል የመብት ተሟገች ክንፍ ነው። ለዚህ ኃይል አስቀድሜ መልስ ሰጥቸዋለሁ። ከአጥፊ ዲሞክራሲ፡ አልሚ አምባገነን ይሻላል። ብሔርተኝነትና የብሔር ልዩነት የሁላችንም የህልውና አደጋ ስለሆነ የተወሰደ መፍትሔ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። የብሔር ልዩነትንና ጽንፈኝነትን ከሚያስቀጥል የመብት ዝክንትል ይልቅ የህዝብ ውህደትን ፈጥሮ እኩል የሀገር ባለቤት የሚሆን አንድ ህዝብ መፍጠር ይበጃል። 

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

4 COMMENTS

 1. Dear admin,

  You should be ashamed of yourself to publish this kind of nazi-like totalitarian pamphlet. This is extremely detrimental to the Amhara struggle, please remove it and apologize!

  • You must have just come out of a cave in Gojjam. Ever heard of freedom of speech? It’s you who are more detrimental to the nation’s well-being than author of this article. What do you mean spilling Fanno secrets about the way it plans to govern from A Rat Kilo? You really expect Borkena to remove an article just because you did not like it, and apologize to you? O man you are so full of yourself. You are so like Fanno!

 2. ፋኖ 4 ኪሎ የሚገባው መች እንደ ሆነ ይፋ ማድረግ አለበት። አለዚያ የሚሸሸው በምን አውቆ ይሸሻል? ወጥቶ የሚቀበለው በምን አውቆ ወጥቶ ይቀበላል? ታላቁ መነኩሴ እስክንድር እና ባለብሩ ሻለቃ ከሠራዊቱ ይቀድማሉ ወይስ ለደህንነታቸው ሲባል ይዘገያሉ?
  ለመሆኑ በስድስት ኪሎ፣ በቦሌ ወይስ በመርካቶ ነው? ቢቻል ቢቻል ከሥራ ቀን ይልቅ በእረፍት ቀን ቢሆን ይመረጣል። ትልቁ ስጋታችን የቤተ መንግሥቱ ደጅ ሳይፀዳ ከች እንዳትሉና እንዳታሳፍሩን ነው። እንደኔ እንደኔ አንድ አመት መታገስ ብትችሉ፣ ጫካ ሃውስ ሊጠናቀቅ ስለ ሆነ ኋላ እቃ ከማጓጓዝ እንድናለን። በርቱልን።

 3. ፋኖ 4 ኪሎ የሚገባው መች እንደ ሆነ ይፋ ማድረግ አለበት። አለዚያ የሚሸሸው በምን አውቆ ይሸሻል? ወጥቶ የሚቀበለው በምን አውቆ ወጥቶ ይቀበላል? ታላቁ መነኩሴ እስክንድር እና ባለብሩ ሻለቃ ከሠራዊቱ ይቀድማሉ ወይስ ለደህንነታቸው ሲባል ይዘገያሉ?
  ለመሆኑ በስድስት ኪሎ፣ በቦሌ ወይስ በመርካቶ ነው? ቢቻል ቢቻል ከሥራ ቀን ይልቅ በእረፍት ቀን ቢሆን ይመረጣል። ትልቁ ስጋታችን የቤተ መንግሥቱ ደጅ ሳይፀዳ ከች እንዳትሉና እንዳታሳፍሩን ነው። እንደኔ እንደኔ አንድ አመት መታገስ ብትችሉ፣ ጫካ ሃውስ ሊጠናቀቅ ስለ ሆነ ኋላ እቃ ከማጓጓዝ እንድናለን። በርቱልን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here