spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትሥልጡን ባህሪበኢትዮጵያ ውስጥ እየጠፋ ነውን?

ሥልጡን ባህሪበኢትዮጵያ ውስጥ እየጠፋ ነውን?

Teshome Abebe - Ethiopia news
ከተሾመ አበበ

ከተሾመ አበበ
መስከረም 5 2016  ዓ. ም .      

ትርጉም በአበበ ኃብተሥላሴ ጥር 19 2016 ዓ. ም.

ይህ ጽሑፍ ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰበና ከዚህ በፊት ከነበረ የአመራር ተመክሮና ልምድ ላይ መሰረት ያደረገ ነው። በመሆኑም ጽሑፉ በመስኩ እንደ ሰለጠነ ባለሙያተኛ ሳይሆን ለሥልጡን ባህሪ አረዳድ መጠነኛ አስተዋጽዎ ለማድረግ በማሰብ የቀረበ ነው። በመሆኑም ምንም ዓይነት የፍቺና የማብራርያ ስህተት ካለ የራሴ (የፀሐፊው) ነው። 

ሥልጡን ባህሪ በኢትዮጵያ የሞት አደጋ ውስጥ ሲሆን ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉ የነቃ አእምሮ ያላቸው ግለሰቦች ደግሞ የግለሰብ ጨዋነት እየጎለበተ እንደሆነ ይታያቸዋል። ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ነው? 

በመሰረቱ ሥልጡን ባህሪ ግልጽ በሆነ ጨዋነትና ትሁት ባህሪ ወይም ንግግር ሊገለጽ ይችላል። ሰፋ ባለ አረዳድ በሥልጡን ባህሪ ላይ ያለ ግንዛቤ ምክንያትን፣ የአሰራር ዘዴን፣ ግብን ወይም ዓላማን መከተል እንደሚገባ ያመላክታል። ከዚህ አረዳድ በመነሳት መገንዘብ የሚቻለው ሥልጡን ባህሪ ቁርጠኛ/ተስፈኛ ነው ምክንያቱም የሕዝብ ደህንነትን የመጠበቅ መርህ በተቻለ መጠን በአግባቡ እንዲቀጥል የሚተገበር ነው። የመገናኛ ብዙሃን በናኙበ ዓለማዊ ሁኔታ ማንኛውም የተሰነዘረ ሃሳብ በስፋትና በብዛት መንሸራሸሩን ከቶውኑ መቆጣጠር አይቻልም። ማንም ግለስብ የተነፈሳት ነገርና ያለበት መንገድ ሳይቀር በተለየ አቀራረብ ማለትም በጣም ተጋኖ፣ በጣም የሚያበሳጭ ሆኖ፣ በጣም አኗቋሪ ሆኖና ሲብስም በጣም አስፈሪ ወይም አስደንጋጭ ሆኖ ለሕዝብ እይታና ጆሮ በደቂቃ ውስጥ ይደርሳል። በዚህ ሁኔታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሃላፊነታቸውን ችላ ብለው በማናለብኝነት የሚጠቀሟቸው አገላለጾች መስመር ያልፉና የተቀረው ማህበረሰብ ሞራልን ሆነ ሥነ-ምግባርን ከመጤፍ እንዳይቆጥር በማድረግ ሥልጡን ባህሪ በዘላቂነትና በዋልጌነት እንዲተካ ብሎም ስድነት እንዲሰፍን በር ይከፍታሉ።

እኔ እዚህ ላይ ስለ ሥልጡን ባህሪ ስፅፍ ስለ ጨዋነት እያወራሁ አይደለም። ጨዋነት ከማህበረሰቡ የሥነ-ምግባር ሕግጋት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ሥልጡን ባህሪ ግን “የሕብረተሰብን የጋራ ወግ አክባሪ ነው”። ሥልጡን ባህሪ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርገው የዲሞክራሲ ግቦች እውን እንዲሆኑ የሚደረግ ጥረትን የሚያካትት ጭምር በመሆኑ ነው። የንቃት ደረጃ፣ የፈጠራ ችሎታና ማህበረሰብ ለሥልጡን ባህሪ የመሰረት ድንጋይ መሆናቸውን በዚህ መስክ ላይ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው ግለሰቦች በሚገባ ልብ የሚሏቸው ናቸው። ለምሳሌ ሂንክሌይ (እ.አ.አ 2000) ሥልጡን ባህሪ ቀና አመለካከት፣ ጨዋነት፣ ለሌላው አሳቢ መሆን፣ በመልካም አስተዳደግ መታነጽና አክባሪ መሆን የሚባሉ አምስት ባህሪያት እንዳሉት ይገልጻል። 

የሥልጡን ባህሪ ድንቅነት

ብዙ ጊዜ ሥልጡን ባህሪ የጨዋነትን ሞገስ የተላበሰ ባህሪ ተደርጎ ይወሰዳል ብሎም ይህ ጊዜ የማይሽረው ባህሪው የሰለጠኑ ሕብረተሰቦችን ወግም ይደግፋል ይንከባከባል። ሥልጡን ባህሪ የሕብረተሰብ ደንቦችና ተግባራትን በማካተት እኛ በሕብረተሰብ ውስጥ ከሌሎች ጋር የሚኖረን መስተጋብር እንዲሰምር፣ አክባሪ እንድንሆን፣ ቀና አመለካከት እንዲኖረንና እንደራሳችን ለሌላው እንድንጨነቅ ይመራናል። ሥልጡን ባህሪ ሌላውን እንደራስ በማየትና በእርስ በርስ መከባበር ላይ መሰረት ያደረገ ነው። ሥልጡን ባህሪ ሁሉም ግለሰቦች ከማንነታቸው፣ ከሚከተሉት ዕምነትና ማህበረሰባዊ ቦታ (ማዕረግ) ውጪ ሰው በመሆናቸው ብቻ ለሚኖራቸው ዋጋና ክብር ዕውቅና ይሰጣል። ይህን የመሰለ የሥልጡን ባህሪ መሰረታዊ እውነታ ነው ዜጎች የሚለያያቸው ጉዳይ ቢኖር እንኳ አንድነታቸውን ለሚጠብቅ የሰከነ ውይይት ተገዢ ሆነው መገኘታቸው የዛ ሕብረተሰብ ጥንካሬ እንደሆነ እውቅና የሚሰጠው። ይህ ጽሑፍ የሥልጡን ባህሪን መሰረታዊ ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ ባህሪያትንና ጥቅምን ይፈትሻል ብሎም አንድ ሕብረተሰብ ሥልጡን ባህሪን ሲያጣ የሚደርስበትን አስከፊ ሁኔታ ይመረምራል። በማስከተልም ከሥልጡን ባህሪ ውጪ የሆነ አመራር በመኖሩ ምክንያት በሕብረተሰብ ውስጥ በስፋት የሚታዩ ችግሮችን ይገመግማል።

የሥልጡን ባህሪ መስፈርቶች 

ለሥልጡን ባህሪ የመጀመሪያው አስፈላጊ ጉዳይ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ መቻል ሲሆን፣ ውይይት በሚደረግበት ወቅት ግለሰቦች ለመከባበር፣ ለመደማመጥና የተለየ ሃሳብን ለመስማት ፈቃደኛ የሆነ ሥነ-ልቡና እንዲኖራቸው ሥልጡን ባህሪ ይጠይቃል። ሥልጡን ባህሪ ግለስቦች ከእርስ በርስ ክስ ነፃ እንዲሆኑና በተቃራኒው ለውይይት በቀረበ ፍሬ ሃሳብ ላይ በሚሰነዘሩ ሃሳቦች ዙሪያ ላይ እንዲያተኩሩ ግድ ይላል። ሁለተኛው ትዕግሥትን መላበስ ነው። በሥልጡን ባህሪ የታነጸ ሕብረተሰብ ልዩነትን የሚቀበልና የተለዩ ሃሳቦች በሚሰነዘሩበት ወቅት መታገስ የሚችል ነው። በተጨማሪም የተለያዩ አመለካከቶች፣ እይታዎችና ሃሳቦች የሰው ልጅ እንዲቀጥል የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን የሚያዳብሩ መሆናቸውንና ሰዎች ተከባብረው በሰላም አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያመቻቹ መሆናቸውን ይረዳል። ሦስተኛው ለሌላው እንደራስ መጨነቅ ነው። በሥልጡን ባህሪ መታነጽ ማለት ለሌውም በእኩል መጨነቅ፣ ስሜታቸወን ለመረዳት አልፎ መሄድና አመለከከታቸውንም ለመረዳት መጣር ማለት ነው። ይህን የመሰለ ለሌላው የመጨነቅ ባህሪ ልዩነትን ለማሰወገድ ለሚደረግ ውይይት እንደ ድልድይ የሚያገለግል ሲሆን መተሳሰብና ትብብር እንዲሰፍን የሚረዳ ነው። ስለዚህ የሥልጡን ባህሪን ምንነት በሚገባ ከመረዳት አንፃር ጨዋነት፣ ትዕግሥትና ቀና ልቡና የሥልጡን ባህሪ መገለጫዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። 

የሥልጡን ባህሪ እሴቶች ምንድን ናቸው?

ሥልጡን ባህሪ ለግለሰቦችም ሆነ ለመላው ሕብረተሰብ ጥቅም ከፍ ያለ ግምት ያለው መሆኑ ሊነገር አይገባውም። ሥልጡን ባህሪን  የሚተገብሩ ግለሰቦች ከሌሎች ጋር በመከባበር ላይ የተመሰረተና አዎንታዊ መስተጋብር እንዲሰፍን በማድረግ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖራቸው፣ የአዕምሮ ደህንነታቸውን መጠበቅና ግጭትም እንዲቀንስ ይረዳል;። ሥልጡን ባህሪ ለሌላው በእኩል መቆርቆር፣ በጥሞና መደማመጥ ብሎም የተለየ ሃሳብን የማስተናገድ ብቃት፣ የራስን አቅም ለመገንባትና ከሕብረተሰብ ጋር የሚያግባባ ችሎታ ለማዳበር ይረዳል።

በሕብረተሰብ ውስጥ ተግባብቶ፣ ተስማምቶና ተከባብሮ አብሮ የሚኖር ማህበረሰብ ለመፍጠር ሥልጡን ባህሪ ያስፈልጋል። ጠንካራ ግንኙነት ያለው ሕብተረሰብ እንዲፈጠር፣ ሕብረተሰቡ እንዲተባበርና ልዩነቱን በሰላም እንዲፈታ አስተዋፅዎ ያደርጋል። በዚህ መንገድ የታነጸ ሕብረተሰብ የዲሞክራሲ መርሆዎች እንዲተገበሩ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሰው ልጅ መብትና እኩልነት እንዲከበሩ ብሎም የተረጋጋ ሕብረተሰብ እንዲፈጠርና የጋራ ልማት እውን እንዲሆን የማስቻል ከፍተኛ ዕድል ይኖረዋል።

በአጠቃላይ ሥልጡን ባህሪ የተሻለ ጤናማና አቃፊ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው፤ እግረ መንገዱንም ግለሰቦች የተሻሻለ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖራቸው ብሎም ግለሰባዊ አቅማቸውንና ብቃታቸውን ለማዳበርም ይረዳል። በመሰረቱ ሥልጡን ባህሪ በሰፈነባቸው ሁሉም ሕብረተስቦች ውስጥ የሚከተሉትን ልብ ማለት ይቻላል።

 1. የሕብረተሰብ ውህደት፡ ሥልጡን ማህበረሰብ በተግባቢነቱና በግጭት አልባነቱ ይታወቃል። በመሆኑም ሰዎች እርስ በርሳቸው በመከባበርና በቀና አመለካከት የሚተያዩ ከሆነ ውጥረቶች ወደ ግጭት ወይም ጠላትነት የመቀየራቸው ዕድል የጠበበ ይሆናል።
 2. ውጤታማ ተግባቦት፡ ሥልጡን ባህሪ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ፣ ተግባቦታችን እንዲጎነብትና በልዩነቶች ላይ እንድንደራደር ያለንን አቅም ከፍ ለማድረግ ያግዛል። ለሥልጡን ባህሪ በሚገዛ ሕብረተሰብ ውስጥ ዕድገትንና ፈጠራን በሚያዳብር መልኩ ችግሮች ገንቢ በሆነ መንገድ ይፈታሉ።
 3. አመኔታና ሕብረት፡ አመኔታ የጠንካራ ማህበረሰቦች መሰረት ነው። ሥልጡን ባህሪ በግለሰቦችና በተቋማት መካከል አመኔታ ይገነባል ይህ ደግሞ የተሻለ አንድነትና መተባበር እንዲኖር ያግዛል።

የሥልጡን ባህሪ አለመኖር የሚፈጥረው አንድምታ ምንድን ነው?

አንድ ሕብረተሰብ ሥልጡን ባህሪውን ሲያጣ የሚከተሉት አስከፊና ጎጂ ነገሮች ይከሰታሉ። 

 1. ጠርዝ ረገጣ፡ የሥልጡን ባህሪ ጉድለት ግለሰቦችና ቡድኖች የተለያዩ ሃሳቦችን ውጤታማ በሆነ ውይይት ለመፍታት ከመሞክር ይልቅ የእኔ በሚሉት ሃሳብ ዙሪያ ብቻ እንዲታጠሩ በማድረግ እርስ በርስ እንዲገፋፉ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በሕብረተሰቡ ውስጥ መከፋፈልን ያባብሳል። 
 2. የሕብረተስቡ ትስስር ይላላል፡ ትሕትና የጎደለውና የማይከባበር ሕብረተሰብ ውስጥ ማህበራዊ ግንኘት እየላላ ይሄዳል ይህም ሰዎች በተናጠል በየጎጥ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ማህበረሰቡን በአንድነት ያቆራኙ የተለያዩ የጋራ እሴቶችን ይዳክማል።
 3. የተቋማት መሽመድመድ፡  በሥልጡን ባህሪ የማይገዛ ተቋም ባለበት ሕብረተስብ ውስጥ ትብብርና አመኔታ የመሸርሸር፣  ተቋማት የመሽመድመድና ውጤተ-ቢስ የመሆን አደጋ ያጋጥማቸዋል። 
 4. የዲሞክራሲ መሸርሸር፡ ዲሞክራሲ በሚገባ በሰፈነበት ሁኔታ ሥልጡን የክርክር ወጎችና ትህትና የተመላባት የልዩነት አያያዝ ተሞክሮዎች እንደ ቤት ምሰሶ  ይታያሉ። ሥልጡን ባህሪ በሌለበት ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ይዳከማሉ ብሎም የዲሞክራሲ መሰረቶች ከፍተኛ ተግዳሮት ይጋረጥባቸዋል።

ሥልጡን ባህሪ ከከበሬታ፣ ለሌላው በእኩል ከመጨነቅና ከበጎ ወይም ከቀና አመለካከት የሚመነጭ ሲሆን ለሚያድግና በሕብር ለሚኖር ሕብረተሰብ የመሰረተ ድንጋይ ነው። የሰከነ ውይይት፣ አንድነትና መተማመን እንዲዳብር ያግዛል። በተቃራኒው ሥልጡን ባህሪ የጎደለው ሕብረተሰብ ለጠረዝ ረገጣ ይጋለጣል፣ ውሁድ ሕብረተሰብን ይንዳል ብሎም የዲሞክራሲ ባህሎችን ይሸረሽራል።  ከዚህም የተነሳ የማህበረሰቦችንና የመንግሥታትን ደህንነት ለማስጠበቅ ሥልጡን ባህሪን መንከባከብና ማበረታታት ያስፈልጋል።

ሥልጡን ባህሪ የጎደለው አመራር የሚፈጥራቸው ችግሮችና መዘዞቹ

አመራር ሕበረተሰብን የመቅረጽ ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው። መሪዎች ከሥልጡን ባህሪ ውጪ ሲሆኑ ወይም ይህ ባህሪ ሲጎድላቸው ይህ በመላው ሕብረተሰብ ውስጥ ይዛመታል። ሥልጡን ባህሪ የጎደለው አመራር በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥራቸው አንድምታቸው ቀላል ያልሆኑ መዘዞችን እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።  

 1. የሥልጡን ባህሪ መጓደልን መደበኛ ወግ ማድረግ፡ መሪዎች እንደ ምሳሌ የሚወሰዱ የሕዝብ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን የሚያሳዩት ባህሪ በሚከተላቸው ሕዝብ ሊኮረጅ ይችላል። መሪዎች ከሥልጡን ባህሪ ውጪ በሚሆኑበት ወቅት ይህን የመሰለ አጉል ባህሪ እንደ ትክክል ይወሰድና አብዛኛውን የሕብረሰብ ክፍል ሊበክል ይችላል። ይህ ነገሮችን የተለመዱ አድርጎ የመውሰድ ልምድ እጅግ መሰረታዊ የሚባሉትን በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ መከባበርንና ቀና አስተሳሰብን ይሸረሽራል።
 2. ጠርዝ ረገጣና መከፋፈል፡ ሥልጡን ባህሪ የሚጎድላቸው መሪዎች በጣም ተንኳሽ አባባሎችን በመጠቀምና “እኛና እነሱ” የሚል እሳቤን በማራገብ ጠርዝ ረገጣን ያበረታታሉ። ይህ ደግሞ በሕብረተሰብ ውስጥ መከፋፈልን ያባብሳል ብሎም ውጤታማ ውይይትና ትብብርን ያደናቅፋል።   
 3. አመኔታንና በራስ መተማመንን ማዳከም፡ ተአማኒነት የውጤታማ አመራር መሰረት ነው። መሪዎች ሥልጡን ባህሪ ሲጎድላቸው በተቋማትና በባለሥልጣናት ላይ ያለ እምነት ይመነምናል። ይህን የመሰለ የእምነት መሸርሸር ደግሞ በሕብረሰሰቡ ውስጥ ውዥንብር በመፍጠር በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለ የግዴታና ውዴታ ውል ትርጉም እንዲያጣ ያደርጋል።
 4. የዲሞክራሲ እሴቶችን ማዳከም፡ ሥልጡን ባህሪ የሚጎድላቸው መሪዎች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የዲሞክራሲ ባህሎችንና ይህንን የሚያስጠብቁ ተቋማትን ሊያዳከሙ ይችላሉ የዲሞክራሲ መሰረቶችንም ይንዳሉ። ይህን የመሰለ አጉል ልምድ አምባገነነት እንዲነግስና የሕግ የበላይነት ችላ እንዲባል በር ይከፍታል።  
 5. የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መሸርሸር፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሥልጡን ባህሪ የማይገዛ አመራር መኖር በአገራት መካከል የሚኖር ግንኙነትን ውጥረት ውስጥ ይከታል ብሎም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ይገድባል። ዲፕሎማሲ ውጤታማ በሚሆን ውይይት ላይ የሚተማመን በመሆኑ ይህ በጎደለበት ሁኔታ ግጭትና አለመረጋጋት የመስፈን ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል። 

ስለዚህ ሥልጡን ባህሪ የጎደለው አመራር ለሕብረተሰቡ እንደ መሰረት ሆነው ያያያዙ ዋልታዎችን በእጅጉ የሚጎዱ አሉታዊ ውጤቶችን ያስከትላል። የሥልጡን ባህሪ ጉድለትን እንደ ትክክለኛ ወግ እንዲወሰድ ያደርጋል፣ ጠርዝ ረገጣን ያበረታታል፣ አመኔታን ይሸረሽራል፣ ዲሞክራሲ ካለም ይታፈናል ብሎም ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ይረበሻል። ይህንን የመሰለ እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ ደግሞ ዜጎች፣ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች ሁሉም ሳያሰልሱ የሥልጡን ባህሪ እሴቶች እንዲጎለብቱና እንዲለመዱ መጣር ይኖርባቸዋል። [ምክንያቱም] ሁሉም ዜጋ ይከተለው ዘንድ እንደ ምሳሌ መሆን የሚችል አመራር በሌለበት በሥልጡን ባህሪ የታነፀ ሕብረተሰብ ማግኘት አይችልም። 

ይህንን አጭር ጽሑፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጡን ባህሪ ጠፍቷል ወይ? በሚል ጀምሬያለሁ። እየታዩ ያሉትን ምፀታዊ ባህሪዎች ታሳቢ በማድረግ መልዕክቴን መቋጨት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል። ሆኖም ግን የሕብረተሰብ ሥርዓትን በተመለከተ ምንም አቋም ቢያዝ እንኳ የሥልጡን ባህሪን አዎንታዊ መለያዎች በምክንያትነት በመውሰድ ጨዋነት ከጎደለው ስድ ባህሪ እንደሚሻል መደምደም ይቻላል። የግለሰብን ሥልጡን ባህሪ አክባሪነት የምናወድስበት ምክንያት ሥልጡን ባህሪ ከሚጎድላቸው የሚለየን ስለሆነ ነው። ሆኖም ግን የሥልጡን ባህሪ ጉድለት አንዳንዴ ሲወደስ የሚሰማው በዚህ አጉል ልምድ ለተበከለው ወገን ጊዜያዊ ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ ነው። በመጨረሻም የሰው ልጅ ለሥልጡን ባህሪ ተገዢ ወይም ስድ፣ እውነተኛ ወይም ቀጣፊ መሆን የሚችለው በሕብረተሰብ ባህሪ፣ ወግና ባህል ላይ ተመስርቶ መሆኑን ልብ ማለት ይጠቅማል።

የጽሑፉ ተርጓሚ ጸሐፊው ስለሥልጡን ባህሪ ምንነት፣ በአንድ አገር ያለ ሕብረተሰብ የተደላደለ ኑሮ እንዲኖር ያለውን አዎንታዊና በመጓደሉ የሚደርሱ አሉታዊ ውጤቶችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሞክረውን ጥረት ከምጣኔ ኃብት ልማት አረዳድ አንፃር በማየት እንደሚከተለው ለማዳበር ይሞክራል። 

የየትኛውም አገር ሕዝብ ስለአገራዊ ልማት ሲያስብ መጀመሪያ ዜጋው በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲችልና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት እንዳይስተጓጎል ሁኔታዎችን ማመቻቸት እጅግ በጣም ወሳኝ እንደሆነ ሊነገር የሚገባው ጉዳይ እንዳልሆነ  ይታወቃል። ሆኖም ግን በአንዳንድ አገራት የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ከሕግ በላይና ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ሕዝብን እየበደሉ፣ እያስራቡ፣ እየገደሉና የአገር ኃብት እየዘረፉ በሥልጣን ላይ በመዝለቅ ቀጥለዋል። ከዚህ በተለየ መልኩ የአንዳንድ አገራት መሪዎች ደግሞ የአገራቸው ኋላ ቀርነት፣ የሕዝባቸው ድህነትና መሃይምነት እያንገበገባቸው ይህንን ለመቀየር ራዕይ ሰንቀው ምጣኔ ኃብታዊ ልማትን እውን በማድረግ ኋላቀር ሕብረተሰባቸውን በአጭር ጊዜ በመቀየር የወደፊት ትውልድን ኑሮ ጭምር ብሩህ እንዲሆን ማድረግ እንደቻሉ ከተመክሯቸው መገንዘብ ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የፊተኞቹ ዓይነት ሳይሆን የሁዋላኞቹ ዓይነት አመራሮች እንዲኖሩትና ኋላቀር አገሩ፣ ድህነቱና መሃይምነቱ እንዲቀየር የሚፈልግ መሆን አለመሆኑ የሚጠየቅ ጉዳይ እንዳልሆነ ለመረዳት ጠቢብ መሆን የማይፈልገው መሬት ላይ ያለው አገራዊ ሁኔታ ግልጽ ያደረገው በመሆኑ ነው።

እንግዲህ ከዚህ የሕዝብ ፍላጎትና መሬት ላይ ካለ ሃቅ በመነሳት ነው ኋላ ቀርነትን፣ ድህነትንና መሃይምነትን በማስወገድ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተቋም ደረጀ እንዲጠበቁ፣ የአመራረት ዘይቤ እንዲዘምን፣ ዜጋው ጤናው የተጠበቀና ዕውቀት የዘለቀው እንዲሆን፣ ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ፀጋዎችን መንከባከብ እንዲቻልና የወደፊት ትውልድንም ሕይወት በአስተማማኝ ብሩህ ለማድረግ የሚፈለግ ከሆነ በመሪዎችና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ውስጥ በግልጽ የሚታዩና ከላይ የተገለጹ ከሥልጡን ባህሪያት ጋር የሚጣረሱ ፀረ-አገርና ፀረ-ልማት የሆኑ አጓጉል ባህሪያት ሊታረሙ የግድ ነው የሚያሰኘው። እንደሚታወቀው ከዛሬ ሃምሳ አመታት በፊት በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ውስጥ ይታይ የነበረ የሥነ-ሥርዓትና የሞራል ከፍታ እጅግ በሚያስደነግጥ ደረጃ እንደዘቀጠ በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህ በነበረው ሕብረተሰብ ውስጥ ተቀባይነት ባገኘ የግብረ-ገብ ትምህርት፣ ሥነ-ሥርዓትና ሞራል ተሞርዶ የተገነባ ወግ፣ ባህልና ልምድን የተላበሰ ሕብረተሰብ በሥርዓተ-አልበኝነት፣ በራስ ወዳድነት፣ በሥልጣን መባለግ በመሳሰሉ የሙስና መገለጫዎች ተተብትቦ ሊያዝ የቻለው ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛ አመራር ባለመኖሩ ነው። በተለይ ላለፉት ሰላሳ አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪዎች ሥልጡን ባህሪ በእጅጉ የጎደላቸው በመሆኑ ፍትሃዊ መሆን የማይችልና ፀረ-ልማት የሆነ የጎሳ ፖለቲካ የሁሉ ነገር መዘወሪያ በማድረጋቸው ምንም እንኳን ስለዕድገትና ልማት ሳይታክቱ ቢያወሩም ሰራናቸው የሚሏቸው ማናቸውም ሥራዎች መሬት ላይ ወርደው የአብዛኛውን በድህነት የተያዘ ዜጋ ሁኔታ እንዲባባስ እንጂ እንዲሻሻል ማድረግ አልቻሉም። 

ከላይ እንደተገለጸው የሥልጡን ባህሪ ጉድለት በስፋት የሚታይባቸው ገዢዎች የመንግሥት ሥልጣንን ለረዥም አመታት በመቆጣጠራቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ሄዷል። በአጠቃላይ ለሥልጡን ባህሪ የሚገዙ መሪዎችም ሆነ ሕዝብ ያለበት አገርና ሥልጡን ባህሪ የጎደለው አመራርና ሕብረተሰብ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ ማለት ይገባል። ሥልጡን ባህሪ በሰረጸባቸውና ከዚህ በተቃራኒ በቆሙ አገራት መካከል የሚታየው የሕብረተሰብ ኑሮና ሁኔታ ማለትም ያለው ድህነት፣ መሃይምነት፣ አቅመ-ቢስነት፣ የግጭት መኖርና ልዩነት አፈታት፣ የዲሞክራሲ ባህልና የሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳይ በስፋት የሚለያዩ ናቸው። በአጠቃላይ የሥልጡን ባህሪ እጦት ብሎም የሕበረተሰብ መሰረት የሚባሉ እሴቶች፣ ወጎችና ልምዶችን ችላ ማለትና እነዚህን ጠብቆ አለመሄድ የሚየስከትሏቸው አሉታዊ ውጤቶችን ከሌሎች አገራትም ከኢትዮጵያም ተሞክሮ መረዳት ይገባል። 

ስለዚህ ለረዥም አመታት መሪዎች ቢቀያየሩምና በተለይ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ በድህነት፣ በመሃይምነትና በኋላ ቀርነት ተጠፍንጎ የተያዘው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የነበሩ ችግሮቹ እየተባባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አለመታየታቸው ለወደፊት አገርንና ሕዝብን ለማስተዳደር ሃላፊነት የሚወሰደው ስብስብ ምን ዓይነት መሆን ይገባዋል የሚል ጥያቄ እንዲጠየቅ የግድ ይላሉ። ቀጣይነት ባለውና በምጣኔ ኃብት ልማት አረዳድ ደግሞ ይህ እጅግ በጣም መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ለአንድ አገር መልማትም ሆነ መውደም የአመራር ሚና ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ለአመታት የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡ የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብን ምን እንደዳረጉት የሚታወቅ ሲሆን በሌሎች አገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቻው በእጅጉ የሚለያቸው ዜጋቸው እንደ አንድ ሕብረተሰብ ተግባብቶና ተስማምቶ መኖሩን ያጎለበቱ፣ በሰላም ወጥቶ መግባቱን ያረጋገጡ፣ ሥራ ለዜጎቻቻው መፍጠር የቻሉና አገራዊ ልማትን ያበረታቱ፣ የአመራረት ዘይቤን ያሻሻሉ፣ የዜጋውን ድህነት በእጅጉ የቀነሱና አገርን ከኋላቀርነት አውጥተው አቅም ያዳበሩ መሪዎች ያሏቸው አገራት በውጤት የታየና ለሌሎች እንደምሳሌ የተወሰደ ለውጥ ማሳየት እንደቻሉ ከተመክሯቸው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ለሥልጡን ባህሪ የሚገዙና በተቃራኒው የቆሙ መሪዎች ያሉባቸው አገራት አጠቃላይ ሁኔታ በጣም የተለያዩ  የሆኑት ተአምር ተፈጥሮ ወይም የማይታወቅ ምሥጢር ኖሮ ሳይሆን ከሕብረተስብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ተግባብቶና እመኔታ ፈጥሮ የሚተጋ አመራር በመኖር ባለመኖሩ የሚወሰን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።  

በኢትዮጵያ ሁኔታ የነበሩ ችግሮች ማለትም ድህነት፣ መሃይምነት፣ ረሃብ፣ ሥራ-አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የግጭቶች መበራከት፣ ጦርነት፣ የሰላምና የደህነት እጦት የመሳሰሉት መሻሻል ሳይሆን እየባሰባቸው መቀጠል የቻሉት አመራር ካለው አገርን በወግ የማስተዳደር ፍላጎትና ችሎታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሆኖ ይገኛል። አንድ አመራር ለሥልጡን ባህሪ ተገዢ መሆን አለመሆኑ ማለትም ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና መፍትሄ ለመስጠት የሚተጋ መሆን አለመሆኑ፣ የሕዝብ ድምጽ የሚሰማ ወይም አምባገነን መሆኑ፣ የአገር ኋላ ቀርነትን ለመቀየር የሚያስችል የልማት ራዕይ ያለው መሆን አለመሆኑ፣ በዚህም መሰረት ዜጋውን በአንድነት ማነሳሳት ወይም በጎጥ ተከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲናቆር ማድረጉ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላም እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር መሻት አለመሻቱ ሁሉም ተነባብረው ለአገርና ሕዝብ የሚበጅ ልማት እውን ማድረግ መቻል ወይም አለመቻልን ይወስናሉ። ምክንያቱም በመሰረታዊነት እነዚህ ሁሉ የሚወሰኑት ያለው አመራር  ለአገራዊ ልማት ወይም ለግል ወይም ለቡድን አጀንዳ ቅድሚያ የሚሰጥ ሆኖ ሲገኝ ነው። በተጨማሪ ለአገር ጥቅም የሚሰጡ ምጣኔ ኃብታዊ እቅዶችን ቅድሚያ መስጠት አለመስጠት፣ ሕዝብ እንደ ዜጋ ብሎም ኢትዮጵያም እንደ ኋላቀር አገር መገላገል የምትፈልገውን ድህነትና መሃይምነት ለማስወገድ መጣር አለመጣር፣ የጤና ጥበቃና የትምህርት ዕድል ማዳረስ አለማዳረስ፣ ኋላቀር አመራረትን ማሻሻል አለማሻሻል የመሳሰሉ አንገብጋቢ ችግሮች ተገቢው ትኩረት የሚሰጣቸው ወይም የሚነፈጋቸው ለአገርና ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ወይም ከዚህ ላነሰ አጀንዳ ቅድሚያ የሚሰጥ አመራር ሲኖር ነው። ይህንንም ተከትሎ ነው በአንድ አገር ውስጥ የመንግሥት ሥልጣን በጨበጠ አመራርና በሕዝብ መካከል ከፍተኛ መተማመን አለመተማመን፣ መከባበር መናናቅ፣ መተባበር ወይም መቃረን ብሎም ልማት ወይም ውድመት ሊከሰት የሚችለው።

እንደተባለው ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት፣ ለዲሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር በመርህ ደረጃ የሚተጋ አመራር መኖር ማለት ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛና እንደምሳሌ የሚወሰድ ስለሚሆን በዚህ ሥር የሚተዳደረው ሕብረተሰብም መሪውን የተከተለ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ስለሚሆነ ይህን የመሰለ የአመራርና የሕዝብ ስምረት አገርንና ሕዝብን መለወጥ የሚያስችል ይሆናል። ይህን የመሰለ ስምረት ደግሞ እጅግ አታካች፣ ፈታኝ፣ እልህ አስጨራሽና ውድ የሆነ ምጣኔ ኃብታዊ ልማትን እውን ማድረግን በእጅጉ ያቀላል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በ2010 ላይ ወደ ሥልጣን እንደመጣና ከዚያም በኋላ የተናገራቸው ንግግሮች የኢትዮጵያ ሕዝብን ልብ የነኩ በመሆናቸው አገዛዙ ለትገብራቸው የሚተጋ ቢሆን በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ ድጋፍ ፈጥሮ ስለነበር እንደ አገር የሚፈለገውን ሰላም፣ ዕድገትና ልማት በእርግጠኝነት እውን ማድረግ የሚያስችል እንደነበረ ልብ ማለት ያስፈልጋል። 

እዚህ ጋ ከላይ እንደታየው ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛ አመራር ሚና ምን ሊሆን እንዲምችል ለማሳየት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ሕዝብን ልብ የበላበት ንግግርን ተከትሎ የታየው የሕዝብ ድጋፍ አገራዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ነበረው። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ሰው እንደጠበቀው ቀና አስተሳሰብ ያለው፣ የተለየ ሃሳብ ዕርግማን ሳይሆን ‘በረከት’ እንዲኖረው የሚጥር፣ በአንደበቱ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ከልቡ ቢሆንና ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚሰራ፣  ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን በመቀበል ለሰላም መስፈንና ለዜጋ ደህንነት ያለአድልዎ የሚተጋ፣ ለቅንጡዎች መዝናኛ የሚሆኑ ፓርኮችና ለራሱ መኖሪያ ቤተመንግሥት ግንባታ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብን እያስጨነቀ ያለ ረሃብን ለማስታገስና ለዳቦ እጦት አቅርቦት ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንና ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምንጭ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ለተያዘ የተረኝነት አጀንዳ ሲባል ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ ሥርዓት ለመተካት ፍቃደኛ ቢሆን በጊዜው የነበረው የሕዝብ ድጋፍ እጅግ በጣም ከፍተኛ አገራዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል እንደነበር በቁጭት ማንሳት ይቻላል። ምክንያቱም በነበር የቀረ ስለሆነ። 

ይህን ማለት ያስቻለው በአመራርና በሕዝብ መካክለል ያለ መግባባትና መተማመን የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች እንክብካቤ በተቋም ደረጃ እንዲጠበቅ ለማስቻል ይህንንም ተከትሎ አገራዊ ልማት እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽዎ እንዳለው ከተለያዩ አገራት ተሞክሮ መረዳት በመቻሉ ነው። በዚህ ላይ መሰረት አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥፎ አስተዳድርን ተከትለው የሚሰተዋሉና ሥር በሰደደ ሙስና የሚገለጹ ማለትም በሥልጣን መባለግና ዓይን ያወጣ ሌብነት፣ የሕግ የበላይነትን አለማስከበር፣ ተረኝነትና አድሏዊነት ብሎም የሥነ-ሥርዓትና የሞራል መላሸቅ ኢትዮጵያን አንደ አገርና ከመቶ ሚልየን በላይ የሆነ ሕዝቧን ወደ ማይወጣበት አዘቅጥ እየወሰዷት በመሆኑ ለመፍትሔው መስራት የዜግነት ግዴታ ይሆናል። በመሆኑም በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውለታ ያለበት ምሁር፣ የፖለቲካ ተዋናይ ነኝ ባይ፣ የማህበረሰብ አንቂ፣ የብዙሃን መገናኛ ላይ የተሰማራ ሙያተኛና ጋዜጠኛ ሁሉ የሥልጡን ባህሪ ጉድለት የሚያስከትለውን አሉታዊ አንድምታ ለሕዝብ ማስረዳትና ግንዛቤ በስፋት እንዲፈጠር መጣር ብሎም ወደፊት ወደ ሥልጣን የሚመጣ ማናቸውም ኃይል ይህንን በሚገባ የተገነዘበ እንዲሆን ማስቻል ተገቢነት የሚያንሰው ተግባር ይሆናል።  

ከላይ ስለሥልጡን ባህሪ በተገለጸው መሰረት አንድ ሕብረተሰብ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰከነና አመንክዮ በሚገዛው መንገድ ለመወያየት፣ ለመደማመጥና የተለየ ሃሳብን ለመስማት ፍቃደኝነት የማያሳይ ከሆነ ለሕብረተሰቡ የሚጠቅም ሥራ ለመስራት አያስችልም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ለአመታት የነበሩ መሪዎች ሥልጡን ባህሪን መርሃቸው አድርገው የተከተሉ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያ የጦርነትና የግጭት ምድጃ እንድትሆንና በረሃብ፣ በድህነትና በዕዳ ስሟ የሚነሳ ሆኖ እንዲቀጥል አድርገዋል። በመሆኑም እነዚህ ከሥልጡን ባህሪ ጋር የተጣሉ መሪዎች የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነው ድህነት፣ መሃይምነት፣ ረሃብና ጦርነት እየቀነሱ ሳይሆን እየተባበሱ መሄዳቸውን፣ ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ የዜጋው ደህንነት ለከፍተኛ ችግር መዳረጉንገ፣ የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋቱን፣ ዜጎች መፈናቀላቸውን ብሎም ለልማት መዋል ይገባው የነበረ የአገር ኃብት እየባከነ መቀጠሉን ማስቀረት አልተቻለም። ለሥልጡን ባህል የሚገዛ አመራር ባለመኖሩ ሁሉንም በእኩል የሚዳኝ ሕግን ማስከበር ስላላስቻለና በተያዘው የጎሳ ፖለቲካ መሰረት የመንግሥት ባለሥልጣናት ፍትሃዊ ሳይሆን አድሏዊ በመሆናቸው ከሕግ በላይ ሆነው ከፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሰላም ኃይላት ጋር ተባባሪ መሆን በመምረጣቸው መሰረታዊ የዜጋውን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ አልተቻለም። 

በመሆኑም በዚህ በተፈጥሮው ፍትሃዊ መሆን በማይችል የጎሳ ፖለቲካ መሰረት በተረኝነት ለተያዘ ዓይን ያወጣና በሌላው ኪሳራ የአንድ ሕብረተስብ ክፍልን ጥቅምና ፍላጎት አስጠብቃለሁ ባይ የኦሮሙማ አጀንዳ ሲባል አገር በግጭትና በጦርነት እንድትታመስ በመሆኗ የምርት እጥረት እንዲፈጠር፣ እንደልብ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር እንዳይቻል፣ የምርት ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነት እንዲከሰት በማድረግ የአብዛኛው ዜጋ ሕይወት ለከፍተኛ ችግር የተዳረገ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር መሳደብ ይሆናል። የአገርንና የሕብረተሰብን ኋላቀርነት መቀየር የሚቻለው ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ ምጣኔ ኃብታዊ ልማት እውን ማድረግ ሲቻል ሲሆን ይህ ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛ ማለትም የአገሩ ኋላቀርነት የሚቆጨው፣ ለአገርና ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት የቆመ፣ ሕግ የሚያከብርና የሚያስከብር፣ በሥልጣን የማይባልግ፣ ልዩነቶችን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የሚችል፣ ቀና አመለካከት ያለው፣ የአመራረት ዘይቤ እንዲዘመን የሚጥር፣ ለሚያስተዳድረው ሕዝብ በእኩል የሚጨነቅ፣ ለፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል የሚተጋ፣ የልማት ራዕይ የሰነቀ፣ ለትግበራውም ሕዝብን ማስተባበር የሚችልና የመንግሥት አስተዳደርን ለዚሁ አላማ መዘወር የሚችል ብቃት ያለው አመራር ሲኖር ነው። ምክንያቱም ዕውቀት የዘለቀው፣ የፈጠራ ችሎታው የዳበረና የኑሮ ደረጃው የተደላደለ ሕብረተሰብ መፍጠር ማለት ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛና ለምሳሌ አሁን በኢትዮጵያ የዕለት ተዕለት ዜና የሆኑ አስከፊና የጨለማ ዘመን ወንጀሎች፣ በሥልጣን መባለግ፣ ሙስና፣ ተረኝነትና አድሏዊነትን መሸከም ሳይሆን ጭራሽ የማይታሰብ የሚያደርግና አስተዳዳሪውን የሚያሽቆጠቁጥ እንጂ የባሰ አታምጣ ባይነት ተረት ተረት የሚሆኑበት ይሆናል ማለት ነው። ለዚህም ነው መልካም አስተዳደርና ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ ያላቸው፣ ተመጋጋቢና አንዱ አንዱን የማጎልበት ባህሪ ያለው ነው የሚባለው። 

ሌላው የሥልጡን ባህሪ መገለጫ ትዕግሥት ሲሆን ለዚህ የተገዛ አመራርና ሕብረተሰብ ሲኖር በውስጡ ያሉ ልዩነቶችን የሚቀበልና ለመስማትና መፍትሔ ለመስጠት የሚጥር ይሆናል። ይህን ማድረግ የቻለ ሕብረተሰብ በውስጡ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች፣ እይታዎችና ሃሳቦችን በተገቢው መንገድ በማስተናገድ ለአገራዊ ልማት አዎንታዊ ውጤት እንዲያመጡ፣ ዕውቀት እንዲሰርጽ፣ ፈጠራ አንዲዳብርና የአመራራት ዘይቤዎች እንዲሻሻሉ ለማድረግ ስለሚረዱ የተለያዩ ሃስቦች የሚኖራቸውን ጠቀሜታ ማጣጣም ያስችላል። ይህ ሁኔታ ሲሟላ ብሎም ለዚህ የሚተጋ አመራር መኖር ሲችል ነው “ልዩነቶች በረከት” መሆን የሚችሉት። እንግዲህ በዚህ ሁኔታ የሚመራና የሚተዳደር ሕብረተሰብ ያሉበትን ልዩነቶች ገንቢ በሆነና አመርቂ ውጤት ሊያመጣ በሚችል መንገድ መፍታት ስለሚያስችለው፣ ተባብሮ፣ ተከባብሮና በአንድነት ለአገራዊ ልማት እንዲነሳሳና አቅሙን የሚሰልቡና ጥገኛ የሚያደርጉትን ድህነትን፣ መሃይምነትን፣ ኋላ ቀርነትንና ቂመኝነትን አስወግዶ በጋራ ለመበልጸግ የተሽለ ዕድል ይኖረዋል። ለዚህም ነው ለሥልጡን ባህል የተገዛ፣ የአገር ፍቅር ያለውና የልማት ራዕይ ያነገበ አመራር አገርን መለወጥ ከሚችል ምጣኔ ኃብታዊ ልማት ወይም ቀጣይነት ያለው ልማት ጋር ድርና ማግ ናቸው የሚባለው። ስለዚህ በአንድ አገር የመልካም አስተዳደር መኖርና ልማት የሚመጋገቡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሕዝብና አገር ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚጣረስ አስተዳደርና ልማት ደግሞ በተቃራኒው አገራዊ ውድመትን ብሎም የሕብረተሰቡ የሰቆቃ ኑሮን የሚያባብሱ መሆናቸው ከተለያዩ አገራት ተሞክሮ መገንዘብ በመቻሉ ነው ለአንድ አገር መልማት ወይም መውደም አመራር ወሳኝ ነው ያሰኘው። 

በተጨማሪ የሥልጡን ባህሪ መገለጫ መከባበርና ሌላውን እንደራስ የማየት ማለትም ዜጎች በማንነታቸው፣ ካላቸው እምነት ወይም ማህበራዊ ሥፍራ (ማዕረግ) ውጪ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊከበሩ እንደሚገባቸው የተቀበለና ለዚህም የሚገዛ መሆኑ ነው። ይህም ከላይ እንደተገለጸው በሕብረተሰብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ አንድነቱን ጠብቆ፣ የነበረውን መስተጋብር ጠብቆ፣ በመከባበር፣ ለሌላው ወገኑ እንደራስ በመጨነቅ፣ በሰከነና በምክንያት ላይ በተመሰረተ ውይይት ልዩነቶችን ለመፍታት የሚችል መሆኑ ነው። ስለዚህ ፍትሃዊ መሆን ሳይሆን አድሏዊነት፣ ለሌላውም እንደራስ መጨነቅ ሳይሆን እኛ ትልቅ ስለሆንን በሌላው ኪሳራ ሁሉም ነገር ኬኛ ማለት፣ ከዚህ በፊት እንዲህ አድርገኸኛልና አሁን በተራዬ እኔም ያሻኝን አድርግሃለሁ ማለትና ሌላውን እንደ ጠላት በመፈረጅ ለማጥፋት መጣር የነበሩ ቁርሾዎችን ማከም ሳይሆን ከዚህ በፊት እንደነበረው ችግሮችን ለወደፊት ትውልድ ማስተላለፍ በሌላ ጥፋትና ኪስራ አንዱን መጥቀም እንጂ ሁሉንም አትራፊ አያደርግም። በመሆኑም “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ብሎ በጎጥና ለጎጥ ከማሰብ ተላቆ አንድነትና መሰባሰብ የሚኖረውን ኃይል ተገንዝቦ የነበሩ ችግሮች እንዳይቀጥሉ የጋራ ጠላት በሆኑት ድህነት፣ መሃይምነትና ኋላቀርነት ላይ ለመረባረብ በሰከነ ውይይት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መትጋት አርቆ አሳቢና ብልህነት ነው። አለበለዚያ አንሶና ጠቦ በጎሳ ፖለቲካ ሳቢያ አድሏዊ ሆን ቆምኩለት የሚባል ሕብረተሰብ ክፍልን ጥቅም አስጠብቃለሁ ማለት ለሃይለኞቹና ለባለፀጋ አገራቱ አጋፋሪ በመሆን ባለዕዳ ሆኖ መኖር እንጂ እራስን ችሎ፣ ተከብሮና በእኩል ታይቶ መኖርን ማሰብ በመርፌ ቀዳዳ ዝኆን ለማሾለክ መሞከር በመሆኑ ከምጣኔ ኃብታዊ ልማትና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ግንዛቤ አንፃር የዕውቀትም የብልህነትም ድህነትን የሚያሳይ እንጂ ሁሉንም አትራፊ የሚያደርግ መጠበብን የሚያሳይ አይሆንም። 

ይህን የመሰለ ግንዛቤ ሲኖር ነው የሕብረተሰብ ቁርኝት በተሻለ የተግባባና የተከባበረ ሆኖ እንዲቀጥል፣ ዜጋው እንደ አንድ አገር ሕዝብ በአንድነት እንዲተም፣ ቢያንስ አንድ ትውልድ የሚከፈል መስዋዕት ከፍሎ እጅግ በጣም ወስብስብ፣ ፈታኝ፣ እልህ አስጨራሽና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ምጣኔ ኃብታዊ ልማትን እውን በማድረግ የሕዝብንም የአገርንም አቅም ማጎልበትና ማዳበር የሚቻለው። ምክንያቱም ይህን የመሰለ ቀጣይነት ያለው፣ የአብዛኛውን ሕዝብ ኑሮ መለወጥ የሚችልና የአገርንም አቅም በማዳበር ከጥገኝነት ጫና ማላቀቅ የሚቻለው ይህን የመሰለ የልማት ራዕይ የሰነቀ አመራር ሲኖር ነው። በተጨማሪም ሕግ የሚያከብርና የሚያስከብር፣ ፍትሃዊና ለፍትህ የሚተጋ፣ ልዩነቶች በሰከነ ውይይት የሚፈታ፣ የሕዝብንና የአገርን ጥቅምና ፍላጎት ለመጠበቅ ወደኋላ የማይል፣ የልማት ራዕይ የሰነቀና ውጤት ተኮር የሆነ፣ የሕዝብን ትርታ የሚያዳምጥና የሚረዳ፣ የሕዝብ አመኔታ ያለው በመሆኑ ላነገበው የልማት ራዕይ ሁሉንም ዜጋ ለማስተባበር ችሎታ ያለው አመራር መኖር ማለት ለሥልጡን ባህሪም የሚገዛ መሆኑን አሌ ማለት አይቻልም። በመሆኑም ቀጣዩ ትውልድ ከግጭትና ከምክንያተ-ቢስ አተካራ የተገላገለ እንዲሆንና ዕውቀት የዘለቀው፣ ጠርዝ ረገጣን የሚጠየፍ፣ በምክንያት የሚከራከርና የፈጠራ ችሎታውም የዳበረ አምራችና ተግባቢ ብሎም ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ለይ የሚገኝ ሕብረተሰብ መፍጠር ያስችላል። ለዚህም ነው አንዳንድ አገራት ከዚህ የተለየ ተዓምር ተፈጥሮላቸው ሳይሆን ሕብረተሰባቸው ተከባብሮና ተስማምቶ፣ ልዩነትን በሰከነ መንገድ መፍታት በመቻሉ ግጭቶችን አስወግዶ፣ አንድነቱን ጠብቆ፣ ጠረዝ ረገጣን አስወግዶ፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተንከባካቢ ተቋማትን አጠናክሮ፣ በዲፕሎማሲው መስክም ተሳትፎውንና ተሰሚነቱን አጎልብቶ በዕውቀት ዳብሮ፣ በኑሮው በልጽጎ፣ አገሩንና ዜጋውን አስከብሮ፣ የተፈጥሮና አካባቢያዊ ኃብቶቹን ጠብቆና የወድፊት ትውልድንም ተንከባክቦ መኖር የቻለው ለሥልጡን ባህሪ የሚገዛ አመራርና ሕብረተሰብ ያለው በመሆኑ ነው። 

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here