spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ/የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻት ቀንዲል እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ/የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻት ቀንዲል እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው!!

‹‹ኢትዮጵያ በሁሉ መስክ የምታኮራን አገር ነች፤ በዐድዋ ጦር ግንባር ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ካበሰረችልን ነጻነት ባሻገር- ‹ጥቁር ሕዝብ ትልቅ አእምሮአዊ ጥበብ ለሚጠይቅ ሥራ የሚያበቃ የአእምሮ ልሕቀትና ስፋት የለውም፤› የሚለውን እኩይ፤ ዘረኛ አሳሰተሳብ በመሻር በተግባር ያሳየች አገር ናት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የዚህ አኩሪ ታሪክ አካል፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ዓርማ፣ ብሔራዊ ኩራት ምንጫችን ነው!!››

(የኮንጎ ጠቅላይ ሚ/ር፤ ፓትሪስ ሉሙምባ እና የዓለም ሰላም ሰላም የኖቤል ተሸላሚና የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ) 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ዳኛቸው ተሾመ 

ባለፉት ሳምንታት በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ፤ ‹‹በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የጉዞና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ማዕቀቦችን ማድረግ በብልጽግና መንግሥት ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና፣ ፖለቲካዊ ግፊት እንዲደርስበት ማድረግ ይኖርብናል፤›› በሚል ሐሳቡን በሚደግፉና በሚቃወሙ መካከል የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ ሰንብተዋል፡፡

በመሠረቱ በበኩሌ፤ ከሰላማዊ ትግል አንጻር መሳሪያ አንስቶ ከመፋለም በመለስ ያሉትን ሁሉንም ዓይነት የትግል ዓይነቶች ደጋፊ ነኝ፡፡ ስለሆነም በሰላማዊ ትግል ለጊዜው በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ እያራመደ ያለውን የውስጥም ይሁን የውጭ ግንኙነቶችን ከቅርብ ሆኖ በመመርመር በማይስማሙባቸው ነጥቦች ላይ፤ ለሀገርና ለሕዝብ አይበጁም ብለው በሚያምኑበት የውስጥም አሠራር ይሁን የውጭ ስምምነቶች ላይ ሁሉ ቅሬታን አለገደብ ለሕዝብ በማሰማት አስፈላጊም ሆኖ ከተገኘ ቅሬታንና አለመስማማትን ለማሳየት ሕዝብን ለተቃውሞ ለሰልፍ እንዲወጣ፤ ወይንም የቅሬታና የአለመስማማት ምልክት የሆኑትን የሥራ ማቆም አድማን መጥራት፣ የርሃብ አድማን ማድረግና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡

ከላማዊ ትግል አንፃር በአጭሩ ይህን ካልኩ ዘንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በተመለከተ ከሰሞኑን በዚህ የበይነ-መረብ የውይይት መድረክ ላይ እየተንሸራሸረ ካለው ሐሳብ አንፃር ስለ አየር መንገዳችን ጥቂት ነገር ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ 

ታሪክ እንደሚነግረን አየር መንገዱ፤ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ ከመሆኑ ባሻገርም በዋነኝነት የአፍሪካ/የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻት ኩራትና ቀንዲል ነው!! ይህ መከራከሪያዬን ፈር ለማስያዝ ያህል አንድ ሁለት ታሪካዊ ሐቆችና ላጣቅስ እስቲ፤ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛና ዲፕሎማት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በተባበሩት መንግሥታት በኮንጎ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር አስተርጓሚ ሆነው ወደ ኮንጎ ዘምተው ነበር፡፡ በዛም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል የአፍሪካና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኑን ያረጋገጠ አንድ ክስተትን በአንድ ወቅት እንዲህ ጽፈው አካፍለውን ነበር፡፡ ከታሪኩ አንድ ሰበዝ ልምዘዝ እስቲ፤

… ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ ይኖሩባት የነበረችውን ከተማ ስታንሌይቪልን ለመጎብኘት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላን እንዲያውሳቸው ጠየቁ፡፡ ጉብኝታቸውም እንዲሳካ የኢትዮጵያ ጦር መምሪያ እንዲተባበር ትዕዛዝ ደረሰው፡፡ በተባለው ቀን ሉሙምባ ስታንሌይቪል ሲደርሱ ኮሎኔል ወልደ ዮሐንስ ሸታ ኤርፖርት ሄደው ተቀበሉዋቸው፡፡

ሉሙምባም የአውሮፕላኑን አብራሪ ለማመስገን ጥሩልኝ ብለው እኔ ሄጄ ጠራኋቸው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሉሙምባን ያመጣው ዲሲ ሦስት አውሮፕላን ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ከመደበቻቸው ከሦስቱ አንዱ ነበር፡፡ የአውሮፕላኑ አብራሪም አብሮ አደጌ የመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት የእግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው መቶ አለቃ ፋንታ በላይ ነበር፡፡ በኋላም ሜጄር ጄኔራል ማዕረግ ላይ ደርሶ በ1981ዱ መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ ደርግ በግፍ የገደለው መኰንን ነው፡፡

ሉሙምባ ጥቁሮች/ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችን ቢያዩ የተሳሳትኩ መስሏቸው ነበር፡፡ እሳቸው የሚጠብቁት የፈረንጅ አብራሪ ነበር፡፡ የእኛ አየር ኃይል አፍሪካን ያኮራ እንደመሆኑ መጠን አብራሪው መቶ አለቃ፣ ምክትል አብራሪው አምሳ አለቃ፣ ቴክኒሺያኑ አሥር አለቃ መሆናቸውን ለሉሙምባ ሳስረዳቸው ተደንቀው የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ጄኔራል ሉንዱላን ጠርተው፤

‹‹አየህ ኢትዮጵያ በሁሉ መስክ የምታኮራን አገር ነች፤ በዐድዋ ጦር ግንባር ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ካበሰረችልን ነጻነት ባሻገር- ጥቁር ሕዝብ ትልቅ አእምሮና ጥበብ ለሚጠይቅ ሥራ የሚያበቃ የአእምሮ ልሕቀትና ስፋት የለውም የሚለውን እኩይ፤ ዘረኛ አሳሰተሳብ በመሻር በተግባር ያሳየች ናት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም  የዚህ ታሪክ አካል፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ዓርማ፣ ብሔራዊ ኩራት ምንጫችን ነው!!›› በማለት አስረዱዋቸው፡፡ ኮሎኔል ወልደ ዮሐንስ ሽታን አመስግነው ሁላችንንም እራት ጋበዙን፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም፤ የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ የራሳቸውንና የሕዝባቸውን የነጻነት ትግል በተረኩበት ‹‹Long Walk to Freedom›› በተባለ መጽሐፋቸው ውስጥ ይህንኑ የሉሙምባን ምስክርነት የሚያረጋግጥ የታሪክ ሐቅን ጽፈውልናል፡፡

ማንዴላ ለፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠና በ1954 ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት- የተሳፈሩበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችና ረዳቶቻቸው በሙሉ ጥቁር/ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በማየታቸው የፈጠረባቸውን ደስታ፣ ኩራት ከመግለጽም ባሻገር፤ ‹‹የጥቁር አእምሮ ላቅ ያለ ጥበብና እውቀት ለሚጠይቅ ሥራ አይበቃም የሚለውን ዘረኛ አሳተሳሰብ በመሻር- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትና ነጻነት     ትእምርት/ሲምቦል መሆኑን ማስመስከሩን አረጋግጠውልናል፡፡

ስለሆነም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዋልታና ማገር ከመሆኑ ባሻገርም የአፍሪካ/የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻት ቀንዲል እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው!!

ሰላም ለአገራችን፤ ሰላም ለአፍሪካ!!

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – English page

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here