spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትፋኖ፟ ከጦር አርበኝነት ባሻገር - መሠረታዊ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ፈተና

ፋኖ፟ ከጦር አርበኝነት ባሻገር – መሠረታዊ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ፈተና

ምናባዊ የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ውይይቶች

ፋኖ፟

ተስፋዬ ደምመላሽ

አማራው በሚያደርገው የህልውና ትግል ፋኖ፟ነት መዋቅር ቀያሪ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ የሚችለው እንዴት ነው? ለዚህ መሠረታዊና ወቅታዊ ጥያቄ እዚህ አጥጋቢ መልስ መስጠቱ አዳጋች ቢሆንም ጥያቄውን በግልጽና ደርዝ ባለው መልክ መቅረጹ ራሱ የመልስ ፍለጋው ጥረት ዋና አካልና መነሻ ነው።

ዛሬ የአማራው ሕዝብ ራስና አገር አድን ትግል በፋኖ፟ ኃይሎች ግንባር ቀደምትነት እየተጧጧፈ አገራዊ ስፋትና ጥልቀት የመያዝ አፋፍ ላይ በደረሰበት ወቅት ጥያቄው አግባብ ያለው መሆኑ ተረጋገጧል። ‘አራሽ ቀዳሽ ተኳሹ’ ፋኖ፟ ‘ነጋሽ’ መሆንም ግድ ይለኛል በሚልበት ወቅት ጉዳዩ ይበልጥ ብርቱ ሆኗል። 

ሆኖም፣ የአርበኞቹ ንቅናቄ ከለት ተለት እያደገ ከአካባባዊ ተከላካይነትና ከተኩስ ጦርነት ከፍ ወዳለ የመንግሥት ሥልጣን ቁጥጥር ደረጃ እየተሸጋገረ ሲመጣ፣ ወታደራዊም ፖለቲካዊም አንድነቱ ተመዛዝኖ መበርታቱን የማይፈልጉ፣ አቅጣጫውን ከማደናገር ወይም ከማለስለስ ወደኋላ የማይሉ፣ የውስጥም የውጭም ወገኖች ጠፍተው አያውቁም። 

ዛሬም አሉ፤ ለምሳሌ የወያኔንም የአብይንም ዘረኛ አገዛዝ በጠምዛዥ ‘አማካሪነት’ም በተቃውሞ ቦታ ያዥነትም ያገለገለው አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬም በዘመነ ፋኖ፟ በጣልቃ ገብነት አለ፣ እጁን አልሰበሰበም።     

ከአገዛዙም ከምዕራባዊ ኃይሎችም ጋር ንክኪ ያላቸው፣ የፖለቲካና የሐሳብ ተጽዕኖ ማሳረፍ የለመዱ፣ አማራንና ኢትዮጵያን ደጋፊ መሰል ወገኖች በልዩ ልዩ ዓይነት ሥራዎች ተሰማርተው ይታያሉ። የአገር ውስጥም ውጭም ጥረቶቻቸው ‘ጋዜጠኝነትን’፣ ‘ለስብእና መብቶች ተሟጋችነትን’፣ በምዕራቡ ‘ዲፕሎማሲያዊ’ እንቅስቃሴ ማድረግን፣ ለፋኖ፟ ተፎካካሪ ‘ድጋፍ ሰጪነትን’ እና የትግል ‘ፍኖተ ካርታ አርቃቂነትን’ ያጠቃልላሉ።

የፋኖ፟ ጦረኝነት ጥበብ ከነዚህ የተባዙና የተንዛዙ እንቅስቃሴዎች ራስን በማላቀቅ ባልተወሳሰበ ኃቀኛ አገር በቀል የንቅናቄ ዘዴ የህልውና ትግሉን (አያይዞም የሥርዓተ መንግሥት ለውጡን) አላማ በሙሉ ልብና ቆራጥነት መከተል ነው። በአማራና በኢትዮጵያ ስም የሚደረጉ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ጥረቶች ግን፣ በዕቅድም ሆነ በተጨባጭ ትግሉ አቅጣጫውን እንዳይከተል የማድረግ፣ ትኩረቱን የማስቀነስ ወይም የማስቀየርና ቆራጭ ስለቱን የማደንዘዝ አዝማሚያ ያላቸው ናቸው።       

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ለግማሽ መእተ ዓመት እየተንከባለለ፣ እየተደራረበና እየተባባሰ የመጣው አገራዊ መንግሥትም ተቃውሞ አሰናካይ ውጥረት እንግዲህ ለፋኖ፟ ንቅናቄ የደቀነው ትልቅ ተግዳር አለ። ይኸውም የአማራን፣ ብሎም የኢትዮጵያን ህልውና ለዘለቄታው የሚያረጋግጡ መሠረታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ለውጦችን በውይይትና ምክክር አዳብሮ ሥራ ላይ ማዋል ነው።

ላለፉት አስርተ ዓመታት ለውጡን በቅንነት እንደ አላማ ያነገቡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን (በተለይ ምሁራን) የጎሣ አገዛዝ መዋቅሩን በመቃወም ያደረጓቸው ክርክሮችና እንቅስቃሴዎች በአይነታቸው ወይም የሃሳብ ጥራታቸው፣ በሒሰታዊ ይዘታቸው እና ተጨባጭ ተጽዕኗቸው አገሪቱ የገጠማትን ወስብስብ ውጥረት የሚመጥኑ ነበር ማለት አዳጋች ነው። 

ዛሬም በአማራው ሕዝባዊ ኃይሎች (ፋኖ፟ አርበኞች) ንቅናቄና በዙሪያው ለተሰባሰቡ ተግሉን ደጋፊና መሠረታዊ ለውጥ ፈላጊ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ባህላዊ ማኅበረሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ መንፈሳዊ መሪዎች፣ምሁራን፣ ስቪክ ማኅበራትና የሚዲያ ወገኖች ውጥረቱ ከባድ ፈተና ደቅኗል፤ የመዋቅር ቅየራውን ትግል ኃቀኝነት በጽኑ አንድነት የማረጋገጥ ፈተና፣ ከዘላቂ አቅጣጫውና መንገዱ ዝንፍ ያለማለት ፈተና። 

ከዚህ ግምት ተነስቼ፣ ለአገርና ሕዝብ በሚበጅ መልክ የፖለቲካ ኃልዮና አሠራር ባህላችንን ከሥር መሠረቱ ገምግመን ለመለወጥ በመጠኑም ቢሆን ትረዳ ይሆናል በሚል ተስፋ ነው ይችን ባለሦስት ክፍል ምናብ ወለድ የአገር ወዳድ ጓደኛሞች ጭውውቶች የያዝች ጽሑፍ ያቀረብኩት። 

በተወሰነ ‘ተውኔት’ መልክ እኔ (ቸሩ መርምሬ) እና አንድ የረጅም ጊዜ ባልንጀራዬ (አበራ ጎበዜ) የምናደርጋቸው ወጎች ሦስት የተዛመዱ ነባርም ወቅታዊም ርዕሰ ነገሮች ላይ ያተኩራሉ። እነዚህ ለመዋቅር ቅየራው ንቅናቄ ወሳኝ ግብአት ሊሆኑ ይችላሉ እምላቸው ርዕሶች (1) የፋኖ፟ ሕዝባዊ ትግል ድንቅ ልዩነት (2) ነፃ ሕዝብ ወካይ ሕይወታዊ የፖለቲካ ቅርጽ እና (3) መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ናቸው።

ነፃ ውይይቶች

ክፍል አንድ

የፋኖ፟ ሕዝባዊ ንቅናቄ ድንቅ ልዩነት

(ቸሩ መርምሬ እና አበራ ጎበዜ)

አበራ  የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ፟) ተገዶ የገባበትን ተደናቂ የህልውና ተጋድሎ በድል አገባዶ አዲስ አበባ ሳይገባ በምን ሒሳብ ነው ስሜት የማይስቡ የመዋቅር ለውጥ ፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ጉዳዮችን እንወያይባቸው የምትለኝ?

ቸሩ  አይ፣ ጉዳዮቹን እንዳሉ ከመኖር አለመኖር ትግሉ አካተው የተለዩ አድርጌ ስለማላያቸው ነው፤ ሆኖም ወደነሱ ከመሄዳችንችን በፊት የስካሁኑን የፋኖ፟ አርበኞች ንቅናቄ ይዞታ እንዴት ታየዋለህ? እስቲ አስቀድመን፣ በጽንሰሃሳብም ትንሽ ገባ ብለን እንነጋገርበት።

አበራ  ጥሩ፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፋኖ፟ ተቃውሞ ብዙ አድናቆት ያተረፈው አመት እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አማራን ጨፍጫፊ አረመኔያዊ የኦሮሙማ ጦር ሠራዊት ላይ እየተቀዳጃቸው ባሉ ግሩም ወረራ ቀልባሽ የደፈጣ ውጊያ ድሎች ነው።

ቸሩ  አድናቆቱን ትጋራለህ?

አበራ  እንዴታ! ግን ይበልጥ የሚያስደንቀኝ የአማራው ሕዝባዊ ኃይል ድሎቹን እየተጎናጸፈ ያለበት ልዩ፣  እውንም እምቅም የውጊያ ዘዴ ነው።

ቸሩ  የሕዝባዊ ኃይሉ ብቻ የሆነ ዘዴ?! የደፈጣ ውጊያ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜና ኢትዮጵያን ባመሳቃለው የአብዮት ዘመንም በአገራችን የተለመደ አልነበር እንዴ? የፋኖ፟ አርበኝነት ባህል በዛሬዎቹ አማራ ታጋዮች የተፈጠረ አዲስ የውጊያ ስልት ነው እያልክ አደለም! 

አበራ  ፈጽሞ እንዲያ እያልኩ አደለም። ዘዴው ታጋዮቹ ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት አኩሪ የጦረኝነት ቅርስ መሆኑን በደንብ እረዳለሁ። 

ሆኖም፣ ጥሪቱ ዛሬ የሚቃኝበት የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አውድ ከቀድሞ ሁኔታው የተለየ መሆኑን አንዘነጋም። የዛሬዎቹ ፋኖ፟ አርበኞች ቅርሱን ዱሮ እንደነበረ ወይም ዝምብሎ በታሪክ እንደተሰጠ የሚወሰዱት አንዳልሆነ ላስገነዝብህ ፈልጌ ነው። 

ቸሩ  ታዲያ የዘመናችን ፋኖ፟ነት አገራዊም ፖለቲካዊም ሁኔታ ምንድነው ልዩነቱ?

አበራ  መሠረታዊ ልዩነቱ አማራው የገጠመው ድርብርብ የህልውና ፈተና (እንደ ፋኖ፟ ታጋይ፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም እንደ አስኳል የኢትዮጵያ አካል) አያት ቅድመ አያቶቹ ከተቋቋሟቸውና ከተወ፟ጧቸው ብርቱ ችግሮች ሁሉ ይበልጥ ውስብስብና ፈታኝ መሆኑ ነው።

ቸሩ  ውስብስብ እንዴት?

አበራ  በቀድሞዎቹ ነገሥታት ሥርዓት ውስጥ በሕዝብ የተድገፈ፣ ራሱን አስታጣቂና አሰልጣኝ የፈቃደኛ ዜጎች ፋኖ፟ነት ሚና ከመንግሥት ዕውቅናን ያገኘና የአገር ጠባቂ ጦርን መጓደል የሚያሟላ ረዳት ወይም ተጨማሪ ሕዝባዊ ኃይል መሆን ነበር። 

በመሠረቱ የፖለቲካ ሥልጣን ከመያዝ ዕቅድ ወይም የአገዛዝ መዋቅር ከመለወጥ አላማ ጋር ግንኙነት አልነበረውም፤ ያን አይነት አላማ መከተል አላስፈለገውም። የዛሬው ፋኖ፟ አርበኝነት ግን…

ቸሩ  …ላቋርጥህና፣ ዛሬ ፋኖ፟ነት ከረዳት ብሔራዊ ጦር ወደ ዋና ሕዝባዊ-አገራዊ ኃይል ከፍ ብሎ፣ ይበልጥ ሰልጥኖ፣ ታጥቆና ተደራጅቶ እንዲወጣ አስገዳጅም አስቻይም ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ልትለኝ ነው?

አበራ  ትክክል! ያሰብኩትን ገና ገልጬ ሳልጨርስ ቀድመህ የተረዳኸው ይመስላል! ‘አዕምሮዬን አነበብከው’ እንደሚሉት አሜሪካውያን።

ቸሩ  የለም፣ ጨርሼ ተረድቼህ ሳይሆን የምስማማበት ክርክርህ ምክንያታዊ ፈለግ ወይም አቅጣጫና መዳረሻ በጨረፍታም ቢሆን ቀድሞ ስለተገለጸልኝ ስሜቴ ተቀስቅሶ ነው ተቻኩዬ ያቋረጥኩህ፤ በል ሃሳብህን ጨርስ።

አበራ  መልካም። የዘመኑ ፋኖ፟ የትግል ስልት ከዱሮው የሚለይበትን ይዞታ ለመረዳት የመጀመሪያው እርምጃ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የገጠማትን በታሪኳ አይታው የማታውቅ ሁለገብ መንግሥታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ልማታዊ ቀውስ በሚገባ መገንዘብ ነው። 

የዘመናዊው ፋኖ፟ ጦር ስምሪት ዳራ ይህ የደናቁርት ዘረኛ ‘ሊህቃን’ ፋሽስታዊ ሕዝበኝነት የወለደው በነውጥ የተዋጠ ሁኔታ ነው። 

ቸሩ  እርግጥ! ለማንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የማይበጀው ዘርፈ ብዙ ውጥረት ለአሁኑ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ተልዕኮና ዘዴ አንድምታ አለው፣ ማለትም ከቀድሞው የፋኖ፟ ጦር ዘማችነትና ስምሪት ተለይቶ ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው። 

መላ፟ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ዘርፎች ከተዋጡበት ቀውስ ለመውጣት የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የፋኖ፟ ታጋዮች (ለዘላቂ የአማራም የኢትዮጵያም ደህንነት ሲሉ) ከጦር አርበኝንት ዘልቀው በፖለቲካ ንቅናቄ ማገዝ ግድ ይላቸዋል። 

ይህ በተለይ በጎሣ ጉረኖዎች ተከልለው የፈላጭ ቆራጭና ተለጣፊ ፖለቲካ ‘ምርኮኛ’ የሆኑ የኢትዮጵያ ብዝሃን ነገዳዊ ማኅበረሰቦችን ይመለከታል። 

ማኅበረሰቦቹ ከስሮ ክፍለ ሀገራትንም አገርንም አክሳሪ ከሆነ ለከትየለሽ፣ አዕምሮቢስ የማንነት ፖለቲካ ተላቀው በአንድነት ተገቢ አካባባዊም ባህላዊም ቅርጻቸውን መልሰው እንዲይዙ የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ፋኖ፟ዎች እጅ ላይ ወድቋል…  

አበራ  …አዎ፣ ፈልገውትም ይሁን በተጨባጭ ታሪካዊ አጋጣሚ። የአማራን፣ በጠቅላላም የኢትዮጵያን ህልውና ለዘለቄታው ከማረጋገጥ አኳያ ችላ ሊሉት ወይም ሊያመልጡት የሚችሉ ኃላፊነት አደለም። 

በተለይ በፖለቲክው ዘርፍ የፋኖ፟ ኃይሎች አጣዳፊ ተጠሪነት ቀውሱን ቀልብሶ፣ የዘር አገዛዙን ልጥፍጥፍ ድርጅቶች፣ በተለይ በድኑን በአዴንን አካቶ መክላት ነው። 

እነዚህ ተልካሻ፣ በቁማቸው ሙታን የሆኑ የአገዛዙ አሻንጉሊት አካላት ከጽንሳቸው የሰለሉና ከተለጣፊነት ያለፈ ተቋማዊ ሕይወት የሌላቸውን ‘ምክር ቤት’ እና ‘የፍተሕ ተቋም’ ተብዬዎች በዋናነት ያካትታሉ። 

የጦር ሜዳ ድል አድራጊነትን የሚከተል የፋኖ፟ ኃይሎች ዘላቂ ኃላፊነት ደግሞ ሰማዩም ምድሩም በሙሉ የኔ የብቻዬ ነው የሚለውን ቀውሰኛ የኦሮሙማ አገዛዝ ከሥሩ መንግሎ፣ በዘረኝነት ሙጃ የተዋጠውን የአገሪቱ ፖለቲካ ምህዳር ጎልጉሎ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚበጅ ፍትሐዊ የመንግሥት ሥርዓት ግንባታ ማመቻቸትና ማዳበር ነው። 

የፋኖ፟ ኃይሎች ይህን ገንቢ ኃላፊነትም በመሠረቱ እንደተቀበሉ እረዳለሁ። 

ቸሩ  ግንዛቤህን እጋራለሁ። ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ የታየህን የፋኖ፟ ደፈጣ ውጊያ ስልት ድንቅ ልዩነት፣ አግባብነቱን ጨምረህ፣ እንዴት ትገልጸዋለህ? እስቲ ይህን በመጠኑ እናውጋበት። 

አበራ  መልካም! በነገራችን ላይ፣ ልዩነቱን የማደንቀው ኢትዮጵያ ተወጥራ የተያዘችባቸውን ውስብሰብ የህልውና ፈተናዎች በፖለቲካ አስተሳሰብና ስልት ከመግጠም አኳያም ካለው አግባብነት ተነስቼ ነው። 

የአማራ ሕዝባዊ ኃይሎች የትግል ስልት ከደፈጣ ውጊያ ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ከጦር አርበኝነት ባሻገር በሌሎች የትግል ዘርፎችም ሥራ ላይ ሊውል የሚችልበት ይዞታ አለው፣ ወይም ሊኖረው ይችላል።

ቸሩ  ግን የስካሁኑን የአማራ ፋኖ፟ ራስና አገር አድን ንቅናቄን ልዩ ቅርጽ እንዴት ታየዋለህ? አንዳንድ የፋኖ፟ ደጋፊዎች ንቅናቄው ከጦር ኃይል አወቃቀር ያለፈ ድርጅታዊ መልክና ይዞታ ወይም ፖለቲካዊ ቁመና ይጎለዋል ይላሉ። 

በዚህ ጉድለት ምክንያት የአማራው ተጋድሎ አቅጣጫውን አሳሳች፣ አኪያሄዱንም አስተጓጓይ ለሆነ በምዕራቡ ለሚደገፍ አጨናጋፊ “ድርድር” የተጋለጠ ነው እያሉ ሲጨነቁ ይደመጣሉ። 

አበራ  ጭንቀታቸው ይገባኛል። ስጋቱ ያለ ነው፣ በተለይ ትግሉ እየተራዘመ ከሄደ። ባለፈው ሰሞን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ከፋኖ፟ዎች ጋር ንግግር ለመክፈት እየሞከረ እንድሆነ ተዘግቧል።

ከተማሪው ንቅናቄ ጊዜ ጀምሮና በአብዮቱ ዘመን ቀጥሎ እስከዛሬ ድረስ አማሮች በታጋይነትም በአመራርም ተሳትፈው ብዙ ዋጋ የከፈሉባቸው የለውጥ ዕቅዶችና ጥረቶች በሆኑ ያልሆኑ የውስጥም የውጭም ወገኖች ከጽንሳቸው ተጨናግፈዋል፤ የተረፉትም በሂደት ተሰናክለዋል።

በስሌትና ዕቅድም ይሁን በውጤት፣ አማራን እና ኢትዮጵያን የለውጥ ትግል ባለቤት ከማድረግ ይልቅ  ኢላማ አድርገዋል። ለዚህ ተጠያቂዎች ሕወሓትና ኦነግ/ሚኤሶን ብቻ ሳይሆኑ ኢሕአፓም ነው።

ቸሩ  የዛሬው፣ ወደ አዲስ አበባ “እየመጣን ነው”፣ መዳረሻችን “አራት ኪሎ” ነው የሚለው ጮክ ያለ ችኩል መፈክር ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰቦችንና ስብስቦችን በተቀናቃኝ የፋኖ፟ ድጋፍ ሰጪነት ማነሳሳቱ ያለፈውን አስከፊ ታሪክ የመድገም አደጋ አለው። 

ሰሞኑን የጎጃም ፋኖ፟ መሪ ዘመነ ካሴ በአሻራ ሚዲያ እንዳለው፣ “የስልጣን ጥም” ለማርካትም ሆነ ሌላ ጥቅም ለማግኘት “ብር በኩንታል ጭነው” በፋኖ፟ዎች “መስዋእትነት…ላይ የሚቆምሩ አሉ”። 

እንዳልከው ስጋቱ እውን ነው። የአማራ/ኢትዮጵያ ሕዝብ የሚይዘውን የመሠረታዊ ለውጥ ትግል አቅጣጫ እንዳይከተል የማድረግን አስከፊ ታሪክ ዛሬም መልሶ ላለመድገም የፋኖ ኃይሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ብሎም የሚያስፈልገውን ሁሉ እርምጃ በቆራጥነት መውሰድ ግድ ሊላቸው ይገባል። 

አበራ  ትክክል! ግን ወደ አነሳኸው የፋኖ ንቅናቄ ቅርጽ ጉዳይ እንመለስና፣ ብዙውን ጊዜ ቅርጽንና ንቅናቄን ወይም ድርጊታዊ ይዘትን አዋህደን አናይም። ስለ ቅርጽ ስናስብ ባንዴ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው እንቅስቃሴዎችን የሚያቀናብር፣ ራሱን የቻለ የኃይል ጠገግ ወይም ተዋረድ (ደርጅታዊ/ተቋማዊ ሕንጸት) ነው። ድርጊትንና ቀራጭ መዋቅርን ሁለታዊ አድርጎ የማየት ዝንባሌ አለን።

ቸሩ  ይህ አተያይ የተሳሳት አደለም! የፋኖ፟ ደፈጣ ውጊያ ዘዴ ላይ ነጥብህ ምንድነው?

አበራ  አይ፣ አመለካከቱ አካቶ ስህተት አደለም። ጽንሰሃሳባዊ ፍሬ ነገሩ እንቅስቃሴ በጦር አርበኝነት ብቻ የማይወሰኑ የፋኖ፟ እሴቶች፣ ገቢሮች፣ ድርጊቶችና ክንውኖች ገላጭ ብቻ ሳይሆን ለአማራ ሕዝባዊ ኃይሎቹ ትግል አደራጅ መርህና ቅርጽ ፈጣሪ መሆኑንም ወይም ሊሆን መቻሉን መረዳታችን ነው።

ቸሩ  እንዴ፣ ተው ኢንጂ! እንቅስቃሴ ባንዴ ገቢርም ቅርጽም ሊሆን ይችላል? 

አበራ  አዎ፣ ይችላል። ቅርጽ የግድ ከተግባር ጋር የማይወራረስ ነፃ (ውጨኛ) የሆነ መልክ አለው ማለት አንችልም፤ ሁለቱ ሊመጋገቡ ወይም ሊወራረሱ ይችላሉ። አንዱ የሌላው ህላዌ ጎን ወይም ውስጣዊ አካል ሊሆን ይችላል። ይህ ነገር ሌላ ጊዜ በሁለተኛው ክፍል ጭውውታችን ጠጋና ገባ ብለን ለምናየው መሠረታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ዕቅድ አንድምታ አለው። 

ላሁን ግን የፋኖ፟ ትግል ፖለቲካዊ ቅርጽ ይይዛል ስንል ቅርጹ ተመዛዝኖ ተንቀሳቃሽ ይሆናል (በፋኖ፟ ሥርዓት ለዋጭ ንቅናቄ መንፈስ ይታነጻል) እንጂ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይሎቹ ጋር ሕይወታዊ ትስስር የሌለው አንድ ወጥ አምባገነናዊ የፖለቲካ ውቅር ኃይሎቹ ላይ ይጫናል ማለታችን አደለም።  

ቸሩ  በጽንሰሃሳብ ደረጃ ክርክርህ ገባኝ፣ ግን በተጨባጭ የአማራ ሕዝባዊ ኃይሎችን ትግል ዘዴ ለይተህ የምትገልጸው እንዴት ነው? ዘዴው ድንቅ ነው የምትልበትን ምክንያትም እስቲ አክለህ ንገረኝ።

አበራ  እሺ፤ በታሪካዊም ወቅታዊም አውዱ የፋኖ፟ ጦረኝነት መሠረታዊ ዝንባሌ በተንዛዛ፣ ሰብአዊነት በሌለው፣ አምባገነናዊ የአስተዳደር ሰንሰለት የታጀለ አደለም። 

የውትድርና ሙያን፣ ኑሮንና ሥራን ነጥሎ በማጉላት የተለየ ዋጋ አይሰጥም። ማዕከላዊ እሴቱ ሕዝባዊ አርበኝነት የሆነ፣ በአማራው ማኅበረሰብ ውስጥ በተለያዩ የመተዳደሪያ ዘርፎች የተሰማሩ አገር አፍቃሪ ፈቃደኛ ዜጎች ያዳበሩት ተወዳጅ፣ ትውልድ ተሻጋሪ የነፍጠኝነት ባህል ነው።

ዛሬ የፋኖ፟ ኃይሎች ከያቶቻቸውና ቅደመ አያቶቻቸው የወረሱትን ሕዝባዊ የጦረኝነት ባህል ሥራ ላይ የሚያውሉበት ዘዴ አስደናቂነት የተለያዩ መገለጫዎች አሉት። 

መጀመሪያ ነገር፣ አርበኞቹ በአማራነታቸው ላይ ያነጣጠረ የማያባራ የዘረኛ አገዛዞች ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ አፈና፣ ወረራና  ጭፍጨፋ አንገሽግሿቸው፣ ትዕግሥታቸው ተሟጦባቸው፣ ውለው አድረውም ቢሆን ማንነታቸውን ይበልጥ ወድፊት አምጥተውና አማክለው ለህልውና ተጋድሎ ቆርጠው መነሳታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ታሪካዊ ሥር መሠረታቸውን ሳይለቁ አርበኝነታቸውን ከዘመኑ ሁኔታዎችና ጋር በአስተውሎ የማጣጣም ችሎታቸውም ጭምር ነው… 

ቸሩ  …ይቅርታ አብርቾ፣ የትግሉን ዘዴ ድንቅነት መገለጫዎች መጠቆም ከመቀጠልህ በፊት፣ ብዙውን ጊዜ እዚህ ግባ የማይባል አደናጋሪ “የአማራ ብሔርተኝነት” ጉዳይ ስለሚነሳ እሱን ባንዳፍታ አጣርተን ብናልፍ ምን ይመስልሃል?

አበራ  በደስታ፣ ምንድነው የሚምታታው ነገር?

ቸሩ  አማራው ከወያኔና ኦነጋውያን በጎሣ ማንነቴ ተለይቼ “ታላቅ አገር” ልሁን ባይነት ጋር የሚመሳሰል የነገዳዊ “ብሔርተኝነት” ርዕዮትም ሆነ ዕቅድ የለውም፤ ኖሮትም አያውቅም። 

አማራው ከተቃጣበት ጥፋት ራሱን ላማዳን የትጥቅ ተጋድሎ ሲያደርግም ታሪካዊ አገራዊነቱን የዘውግ ማንነቱ ዋና፟ አካል አድርጎ በውስጡ ይዟል። የማኅበረሰቡ ነገዳዊ ልዩነት ወይም ማንነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ብሔርተኝነቱ በገለጻ አገራዊ (ኢትዮጵያዊ) እንጂ ጎሠኛ አለመሆኑ ላይ ብዙውን ጊዜ ብዥታ አለ።      

ማለትም፣ ለአማራው ኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ምርጫ ወይም አጀንዳ ሳይሆን የነገዳዊ ህልውናው ዋና አካል ነው። ለዚህ ነው ፋኖ፟ አገራዊነቱን የመኖር አለመኖር ትግሉ መዳረሻ ብቻ ሳይሆን መነሻም መንደርደሪያም ያደረገው። የትግሉ መዝሙር ሳይቀር ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ ነው።

እዚህ ላይ የምትለው አለህ?

አበራ  አይ፣ ምንም ያህል የለኝም። ግንዛቤዬ እንዳንተው የፋኖ፟ አርበኞች ከኢትዮጵያዊነት የተለየና የወጣ ወይም የወረደ “አማራ ብሔርተኝነት” የላቸውም የሚል ነው። እርግጥ አማራው እንዳልከው የሚለይበት የራሱ ተክለነገድነት እንዳለው አይካድም፤ የራሱ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ማንነት ባለቤት ነው። 

ሆኖም ግን አማራነትንና ኢትዮጵያዊነትን በቅደም ተከትል የምንይዛቸው ሁለታዊ ክፍሎች ወይም መደቦች አድርጌ አላያቸውም። ፈጽመው የተለያዩ የህልውና ወይም የማንነት ፈርጆች አደሉም። ምንነታቸው/ልዩነታቸው አንጻራዊ እንጅ ፈርጃዊ አደለም፤ ሊሆንም አይችልም።  

ይህ ነጥብ ትንሽ ረቀቅ ያለ ስለሆነ ቀላል ግልጽነት ቢጎለውና በአንዳንዶች ዘንድ፣ አማሮችንም ጨምሮ፣ ብዥታ ቢጋብዝ አያስደንቅም።   

ቸሩ  መልካም፤ በል እንግዲህ ወዳቋረጥነው ጉዳይ እንመለስ።

አበራ  ጥሩ፤ ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት የፋኖ፟ ሽምቅ ውጊያ ዘዴ ድንቅነት መገለጫ ላይ አንድ ሌላ ዋና ማሳያ ልጨምር። ማሳያው አርበኞቹ ትግሉን ከሚያካሂዱበት ምጣኔ ኃይል ጋር የተያያዘ ነው። 

ቸሩ  “ምጣኔ ኃይል”? 

አበራ  አዎ፣ ምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚ) እንዲሉ። ማለትም፣ የፋኖ ጦረኞች የህልውና ትግላቸውን በም፟ጡን ግብአቶችና ጥረቶች “ምርታማ” የሚያደርጉበት ቅርጽ፣ ንቅናቄያቸውን ከመሠረታዊ አላማቸውና ተለዋዋጭ የትግል ሁኔታዎች ጋር በማመጣጠን ከፍ ዝቅ፣ ሰፋ ጠበብ የሚያደረጉበት ተለማጭ የሆነ ቁጥብ የኃይል አጠቃቀምና አስተዳደር ይዞታ። 

ቸሩ  ጦረኞቹ እስካፍንጫው የታጠቀ ጠላት ላይ ማየ፟ል የቻሉት፣ ባልተጠበቀ ውጤታማነትና ቀልጣፋነት የዘረኛ አገዛዙን ወረራ ለመቋቋም፣ ብሎም ለመቀልበስ የበቁት ‘ትልቅ ዉጤት በአነስተኛ ጥረት’  የሚል አመርቂ የትግል መርህ፣ ወይም እንዳልከው ምጣኔ ኃይል ተከትለው ይመስላል። 

አበራ  ለዚህም ነው በጦር ሜዳ ባስገኛቸው ተጨባጭ ውጤቶች ብቻ ሳይሆን በዘላቂ ዘዴኛነቱ የአማራ ፋኖ፟ን ንቅናቄ የማደንቀው። 

ቸሩ  ግንኮ ንቅናቄው ምንም ያህል የትግል ስልት ምርጫ አልነበረውም። ይበልጥ የወታደር ብዛትና የከባድ ጦር መሣሪያ አቅም እንዲሁም የላቀ የትጥቅ፣ ስንቅና መጓጓዣ አቅርቦት ያለውን ግዙፍ የመንግሥት ኃይል ለመቋቋም በዓለም ዙሪያ የተፈተነን የሽምቅ ውጊያ ስልት መጠቀም ግድ ብሎታል።  

ከጅምሩ የኦሮሙማ አገዛዝ ጦር ኃይልና የፋኖ፟ ወታደራዊ አቅም ተመዛዝኝ ስላልነበሩ ፋኖ፟ ኃይሎች አገዛዙን ፊት ለፊት ከመፋለም ይልቅ በየቦታውና በየጊዜው በሚደረጉ እጥር ምጥን ባሉ ድንገተኛ እንቅስቃሴዎች፣ መብረቃዊ ጥቃቶችና ስኬታማ ተልዕኮዎች የጠላትን አቅም ማመንመን፣ ራሳችውንም በሂደት ማጎልበት አስፈልጓቸዋል። 

አበራ  እርግጥ! ጠላትን በመጨረሻ ዝረራ ማሸንፍ የሚችሉትም ቀድመው በዚህ የተለመደ የደፈጣ አመታት ዘዴ አለሳልሰውና አዳክመው እንደሆነ የአማራ ሕዝባዊ ኃይሎች ጠንቅቀው አውቀዋል። 

ሆኖም፣ የምጣኔ ኃይላቸው ድንቅነት ከደፈጣ ዉጊያ ስኬቶች ባሻገር መዋቅራዊ ለውጥ አስቻይ እምቅ አቅምና አግባብነት ያለው መሆኑም ነው። 

ፋኖ፟ ጦረኞች በሂደት ወደ መደበኛ፣ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሲለወጡም ይኸው ወድፊት እውን ሊሆን የሚችል ዘዴኛ አቅም አጠቃቀማቸው ከለውጡ ጋር ተመዛዝኖና ዳብሮ አግባብነቱ ሊቀጥል ይችላል፤ ይገባልም።   

ቁጥብ ኃይል አጠቃቀምና አስተዳደራቸው በጦር ሜዳ የሚወሰን ሳይሆን በተለያዩ የሰላም ትግል አውዶች፣ ዘርፎችና እርከኖችም ቦታ ያለው ወይም ሊኖረው የሚችል ነው። እነዚህ ከተኩስ ጦርነት ባሻገር የፖለቲካና ሐሳብ ንቅናቄዎችን በዋናነት ያካትታሉ።

ቸሩ  መሠረታዊ የፖለቲካ ሥራና አስተሳሰብ ለውጥ ጉዳዮችን በመጪ ሁለት ተከታታይ የጭውውታችን ክፍሎች በተራ ስለምንሄድባቸው የያዝነውን ንግግር በጦር ዉጊያው ዘርፍ ላይ ወስነን ብንቋጨው ምን የመስልሃል?

አበራ  ጥሩ ሐሳብ!

ቸሩ  እንግዲያውስ በድንቅ ምጣኔ ኃይል የተቃኘው የአማራ ፋኖ፟ ሕዝባዊ ኃይሎች ጦረኝነት ላይ ቅድም ጠቆም ያደረከውን ትንሽ አብራራው።

አበራ  መልካም፤ የአማራ ፋኖ፟ ጦር ኃይል አያያዝና አጠቃቅም ቁምነገር በትክክለኛና ተገቢ ራስን የማዳን ዓላማ፣ በዘላቂ ስልታዊ ተዕግሥትና የሕዝብ ደጋፍ፣ እንዲሁም የትግል ሁኔታዎችን ለራስ ጥቅም በማዋል ደም አፋሳሽ፣ ንብረትና ከተማ አውዳሚ ጦር ውጊያን ቢያንስ በመቀንስ፣ ሲቻልም ጨርሶ አላስፈላጊ በማድረግ የጠላትን ጉልበት አዳክመው፣ ቅስምና ሞራሉንም ሰብረው ለማሸነፍ ይጥራሉ። 

የወራሪው ኦሮሙማ አገዛዝ ኃይሎችን ከቦታ ወደ ቦታ ዘውውሮች የፋኖ፟ ተዋጊዎች በቀዳሚ ቀልጣፋ የቆረጣ መላዎችና እንቅስቃሴዎች ደጋግመው የሚያጨናገፉት በዚህ አኪያሄድ እንደሆነ እንረዳለን።

ቸሩ  ትክክል፤ የጦር ሜዳ ቅልጥፍናቸውም የዘመን አመጣሽ ፖለትካ ማንፌስቶ ወይም ድርጅታዊ አመክንዮና አሠራር ውጤት ሳይሆን በዋና፟ነት ፋኖ፟ ተዋጊዎች ከአያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት አኩሪ አገር በቀል የሥልጡን ሕዝብ ጦረኝነት ቅርስ ነው።

አበራ  ልክ ነህ፤ ትግሉ ዘመናዊ ይዘትና ገጽታዎች ቢኖሩትም በመሠረቱ አገር በቀል ፍሬ ነው። እዚህ ላይ ያስቀመጥነውን ዋና ነጥብ ለማጉላት፣ የስካሁኑ የአማራ ሕዝባዊ ተዋጊዎች የጦር ሜዳ ስኬት በግል ወይም ቡድነኛ ጦረኞች አድራጊ ፈጣሪነት ብቻ የተገኘ ሳይሆን የመላ አማራ ተዋጊዎችን ስኬታማ እንቅስቃሴዎች ሕይወታዊ ቅርጽ፣ ቅንብርና ድባብ እየሰጠ ያለ ምጣኔ ኃይል ውጤት መሆኑንም እንገነዘባለን።

ግንዛቤያችንን ይበልጥ ግልጽና ጥብቅ ለማድረግ፣ በህልውና ተጋድሏቸው እንኳን ስብዕናን የማያጓድሉ ቁጥብ የጦር ኃይል ተጠቃሚ የአማራ ፋኖ፟ አርበኞችን ባንድ በኩል፣ ሲበዛ ኃይል አባካኝ፣ ንጹሓን ላይ  እልቂት ፈጻሚና ንብረታቸውንም ዘራፊና አውዳሚ የሆነን ቡከን የአገዛዙ ሠራዊት በሌላ በኩል፣ ማነፃፀር ብቻ ይበቃል። ሌላ ብዙ ማለት አያስፈልግም።

ቸሩ  የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም ይገርማል፣ ነገሮች የተገላቢጦ ሆነዋል። 

በአንድ በኩል፣ ሕግ አስከብራለሁ ባዩ አገዛዝ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ አሸባሪነትን በሚያዋስን ለከት የለሽ ሥርዓተ አልበኝነት የንጹሓንን ሕይወት፣ ንብረትና ምርት ሆን ብሎ ያጠፋል፣ ብዙውን ጊዜ የማያወድመውን ነገር እንድተራ ወንበዴ አይን ባወጣ ውንጀለኛነት ይዘርፋል። 

በሌላ በኩል፣ አገዛዙን እየተቋቋሙት ያሉ “ሽፍታ”፣ “ጽንፈኛ” የሚላቸው አማራ ፋኖ፟ አማፅያን እቁጥጥራቸው ሥር ባሉ ወረዳዎችና አካባቢዎች ደምብና ጸጥታ እያስከበሩ ነው። የአማራ፣ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ እየሆኑ ነው።

አበራ  የአብይ አገዛዝን አጉልቶ የሚለየው ኃይል አባካኝ አጥፊነት በጦርነት ከሚያደርሰው ወንጀለኛ ውድመትና ኪሳራ ዘልቆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል፣ እሴቶችና አርማ፣ መንፈሳዊ ተቋማትና ገቢሮች፣ እንዲሁም የልማትና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በሚያሳርፈው አሉታዊ ተጽዕኖም ይገለጻል። 

በወራዳ ድርጊቶቹ በአፍሪካና ዓለም ዙሪያ ተከብራ የኖረች አገራችንን ያዋረደው አገዛዝ በቅርቡ በኦፊሴል አገርና መንግሥት ካልሆነው ሶማሊላንድን ጋር የተፈራረመው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ጎጂ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ የወደብ ተጠቃሚነት “ውል” እንዳሳየው፣ በቅንነት በቅጡ ያልታሰቡና ያልተመከረባቸው ጠብ ጫሪ እርምጃዎች መውሰድ ልማዱ ነው።

ቸሩ  የዚህ በመሠረቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተጣላ፣ የራሱንም “ኦሮሟዊ” ጥቅም ከአፍንጫው ጫፍ አርቆ ማየት የማይችል ገዢ ቡድን ኃይል አጠቃቀም ልማድ ፍልቀቱ ምንድነው? መነሻውን በሚገባ መረዳቱ የማርከሻው እውቂያ ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ይመስለኛል፤ ካልተሳሳትኩ።

አበራ  አይ፣ ልክ ነህ። የኦሮሙማው አገዛዝ ወንጀለኛ ኃይል አጠቃቀምም ሆነ አባካኝነት ከግለሰብ “መሪዎቹ” ቀውሰኛ ባሕሪያትና ደናቁርት ድርጊቶች (በተለይ ከአዕምሮ ብክንክኑ አብይ አሕመድ) በቀጥታ የሚፈልቅ መሆኑን መረዳት አዳጋች አይሆን ይሆናል።  

ግን የመንግሥት ችሎታዎችና ፀጋዎች አብካኝነት ዘወርዋራ መዋቅራዊ ምንጮች ለብዙዎች በተመሳሳይ መጠን ጎልተውና ቀለው አይታዩም። ሆኖም፣ ምንጮቹ ገዢ ግለሰቦችና ቡድኖች አድራጊ ፈጣሪነት ላይ ወሳኝ (ቀራጭ) ተጽዕኖ አላቸው።

ከአገር ውስጥም ውጭም የብዙዎችን ትኩረት ለመቆጣጠር ከመሞከር የማይቦዝነው፣ ዲስኩር አያልቅበት አብይ በዋሾ ጮሌነትና ሥርዓተቢስነት ያለውን ቢል፣ ያደርገውን ቢያደርግ፣ ውሎ አድሮ ወይኔዎች የፈጠሩት አገር ከፋፋይ አገዛዝ መዋቅር ፍጡር መሆኑ አይካድም። በመሠረቱ ዘረኛ ሥርዓቱን ጠባቂና አስቀጣይ ነው።  

ቸሩ  ገባኝ፣ ግን የመንግሥት ኃይልና ፀጋዎችን አላግባብ ተጠቃሚነትና አባካኝነት ሥርዓታዊ ምንጮች ባጭሩ እንዴት ትገልጻቸዋለህ?

አበራ  ጉዳዩ ወሰብሰብ ያለ ነው፤ ብዙ ሳልል ሁለት የተዛመዱ ዋና መገለጫዎች ልጠቁም። አንደኛው፣ የአገዛዙ ‘መሠረተ ድንጋይ’ የሆነ ከኢትዮጵያዊነት ተለይቶ፣ ርቆና ተጣርሶ የተከለለ ጠባብ፣ ደሴታዊ የጎሣ ማንነት ሕንጸትን ይመለከታል። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ሳይኖረው፣ አገዛዙ የአገሪቱን አካባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖማዊና መንግስታዊ ጉዳዮችን በማናለብኝነት ጨፍላቂ መሆኑ ነው። 

ሆን ተብሎ በጠባብ ወገንተኛ-ጎሠኛ ፖለቲካ ዕቅድና ሥራ የተጠመደው የ“ኦሮሚያ” ፓርቲ የኢትዮጵያን ሐቀኝነት (እውን አንድነት) የጠበቀ ለውጥና ልማት የሚያራምድ ሳይሆን ከአገሪቱ ህልውና ጋር ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ ያለው ነው። ፓርቲው ኢትዮጵያን አፍርሼ “የኩሽ ኤምፓየር” አቋቁማለሁ ባይ ነው። 

የአብይ አገዛዝ ለጥቂት አመታት አገር አቀፍ ተጽዕኖ የነበረው ቢሆንም ከወያኔ ጅምሩ አገራዊ መንግሥት ሆኖ አያውቅም። ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፣ ግን ኢትዮጵያ መንግሥት አልነበረም፤ አደለምም።

ቸሩ  ለስሙ ‘የኢትዮጵያ መንግሥት’ ቢባልም በአወቃቀሩ፣ ባሕሪውና መንፈሱ ራሱን ከብሔራዊ ሕይወታችንና ሥልጣኔያችን የለየ፣ ያራቀና ያቃረነ መሆኑን እረዳለሁ፣ ግን ይህ ይዞታው ከኃይል አባካኝነቱ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው?   

አበራ  ወደ አገዛዙ ኃይል አጠቃቀም ብኩንነት እየመጣሁ ነበር። የአብይ ወራሪ አገዛዝ በተፈጥሮው የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ በቀና ሞራላዊ፣ ምሁራዊና ፖለቲካዊ አመራር አግባብቶ የሕዝቡን ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል ቁመናም ሆነ አቅም ወይም ፍላጎት ፈጽሞ የሌለው በመሆኑ…

ቸሩ  …እንዲያ በመሆኑ ግዙፍ የሕጋዊነትና የሕዝብ ተቀባይነት ኪሳራ ስለደረሰበት እራሱን በስልጣን ላይ ለማቆየትም ሆነ የ“ታላቋ ኦሮሚያ”ን ምኞታዊ ሃሳብ ለመግፋት ስግብግብና ከመጠን በላይ አፋኝ፣ ጨቋኝ፣ አጥፊና ጨፍጫፊ ኃይል መጠቀም ተገዷል እያልክ መሰለኝ።

አበራ  አዎ፣ በተለይ አማራን የምዝበራ፣ የውድመትና የጭፍጨፋ ኢላማ ያደረገ ፋሽስታዊ የመንግሥት ጦር ኃይል። እንኳን ሐሳቤን ጨረስክልኝ። ነጥቡን ካንተ አልቄ ልገልጸው አልችልም ነበር!

ግን ያልከው ላይ ጥቂት ልጨምር። ዘረኛ አገዛዙ፣ በወያኔ ትግሬም በኦነጋዊ ኦሮሞም ቅርጹ፣ ሥልጣን የጨበጠው በበጎ፣ ልባዊ የአገር ፍቅር፣ ባለቤትነትና ኃላፊነት ስሜት ሳይሆን በክፉ የኢትዮጵያ አንድነት ጥላቻና ደመኛነት ነው። ይህ የጠላትነት ስነልቦናው ደግሞ አገዛዙን ለመንግሥት ኃይል አባካኝነት፣ የንጹሐንን ሕይወትና ንብረት አጥፊነት የሚገፋፋና የሚያበረታታ ነው። 

ይህ ነው በሚባል መርህ ወይም ርዕዮት የማይመራው ሙልጭልጩ የአብይ ፋሺስታዊ አገዛዝ ያባከነው ግልብ የጦር ጉልበቱንና የፖለቲካ አቅሙን፣ እንዲሁም ከጅምሩ የነበረውን ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና ማኅበራዊ መዋለ ንዋይ ብቻ ሳይሆን የሃሳቦችን ኃይል ጭምር ነው። ምርታማ ምጣኔ ኃይል እንደሌለው ሁሉ ፍሬያማ ምጣኔ ሐሳብም የለውም። 

ቸሩ  ምን ማለትህ ነው፣ “ምጣኔ ሐሳብ”?

አበራ   የአገዛዙ የተቃረነ መዋቅራዊ አመክንዮ ጠባብ ግን ተስፋፊና ወራሪ ጎሠኝነትን ያማከለ ነው ይህ ደግሞ እንደ “አንድነት”፣ “ፍትሕ”፣ “ዲሞክራሲ”፣ “የሕግ የበላይነት” እና “ልማት” ያሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተፈላጊ ሃሳቦችን በሰፊ አገራዊ አገባብ የመቀበል፣ ተጨባጭ ትርጉም የመስጠትና በሚገባ ተፈጻሚ የማድረግ አቅምም ሆነ ፍላጎት የሚሰጥ አደራጅ መርህ አደለም። ዘረኛ አመክንዮው ለሐሳብና መርህ ተገዥ ከመሆን ጋር አብሮ አይሄድም፤ ሃሳቦችን መልሶ በሚገባ ማስተዳደር የሚያስችልም አደለም። 

ሆኖም፣ ሃሳቦቹ በአገዛዙ ውስጥና ዙሪያ የተትረፈረፈና የናረ ሕይወትየለሽ የአስመስሎ ዝውውር አልተጓደለባቸውም። የጽንሰሃሳባዊ ፍሬ ነገራቸው ወይም ተግባራዊ ፍቻቸው ስርጭት ሳይሆን የቃል በቃል (መጠሪያ ስሞቻቸው) ብቻ ዝውውር! 

ቸሩ  ልክ ነህ፤ ሃሳቦች የተባሉት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዙን ለታይታ ከማቆንጀት የማያልፉ፣ ደረጃቸው በጣም የወረደ፣ መናኛ ርዕዮታዊም ተቋማዊም ጌጣጌጦች ናቸው። ለምሳሌ፣ “የተከበረው ምክር ቤት” የአብይ ፋሽስታዊ አገዛዝ ማጌጫ ውዳቂ አካል ነው። 

በል ኢንግዲህ አንደኛውን የውይይታችን ክፍል እናገባደው።

አበራ  መልካም፤ ለመዝጊያ ያህል እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅህ። የፋኖ፟ ንቅናቄን የጦር ሜዳ ስኬቶችና ዘዴ አድናቆቴን፣ ስለትግሉ የወደፊት ክንውኖች ያለኝን ተስፋም እንደምትጋራ እረዳለሁ። ግን ስጋቶች አሉህ፣ ወይም እርግጠኛ ያልሆንክባቸው ነገሮች?

ቸሩ  አይ፣ ሌሊት እንቅልፍ የሚነሳ ጭንቀት የለኝም፤ ግን የፋኖ ንቅናቄ ቀጣይ፣ አገር አቀፍ ምዕራፍ  ያልተለመደና እምብዛም ያልተረጋገጠ መሆኑ ያሳስበኛል።

ችግሩ ቀጣዩ የፋኖ፟ ተጋድሎ ንቅናቄ አቅጣጫ ወይም ደረጃ ግልጽ ያለመሆን አደለም። አንዳንድ ነገሮች  ሂደትን ቀድመው ከጅምሩ በይፋ ግልጽ ላይደረጉ እንደሚይችሉ ይገባኛል። ይልቅስ የፋኖ ስምሪት አዲስ የለውጥ ዕቅድ ስኬታማ አፈጻጸም ነገር ነው ትንሽ ጥርጥር ላይ የጣለኝ።

አበራ  አዲስ የለውጥ ዕቅድ? 

ቸሩ  አዎ፤ ለፈኖ፟ አዲስ የሆነ ዕቅድ። የዛሬው ፋኖ፟ በጦር ሜዳ የተሰማራው ከቅድመ አያቶቹ የወረሰውን የአርበኝነት ባህል ተከትሎ በአገሩ መሬት በመንቀሳቀሰ ቢሆንም የሚያካሂደው ሥርዓታዊ ለውጥን ያቀደ ራስና አገር አድን ትግል ቀድሞ በአማራው ተደርጎም ታይቶም አይታወቅም። 

ለዚህ ነገዳዊም ኢትዮጵያዊም ለሆነ የአገዛዝ መዋቅር ቀያሪ የህልውና ንቅናቄ የአማራው እንግዳነት የማያስተማምን (ያልተቀየሰ መሬት ላይ የሚካሄድ) መሆኑ ያሳስበኛል።

አበራ  አሳሳቢነቱ ያለ፟ ነው። በተጨማሪ የስካሁኑ የፋኖ፟ ኃይሎች ወታደራዊ ቁመና እና ንቅናቄ ፖለቲካዊ-ድርጂታዊ አስኳል ወይም ስልታዊ አመራር ሰጪ ስቪል ክፍል በግልጽ የሚታይበት አለመሆኑ (አካቶ የለውም ባይባልም) ለስጋትህ አስተዋጽዎ ይኖረው ይሆናል።

ቸሩ  እርግጥ አለው። ከዚህ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ትንሽ ጥርጣሬ ያሳረፈብኝ ሌላም ነገር አለ።

አበራ  ምንድነው እሱ?

ቸሩ  በተኩስ ውጊያ እንከን የማይወጣላቸው የፋኖ፟ ኃይሎች የጦር ሜዳ አርበኝነታቸውን የሚመጥንና ወደ መደበኛ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትነት የሚያሸጋግር ሥነ ሥርዓታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አሠራርና አመራር ካላዳበሩ፣ መሠረታዊ የለውጥ ዕቅዳቸውን ለሚያዛቡ የውስጥም የውጭም ጣልቃ ገብ ወገኖች ያጋልጣሉ።

ሰርስረውም ሰርገውም የሚገቡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወገኖች፣ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ መድረኮች የመጠቀም ዕድሎች ምንጊዜም የማይጓደሉባቸው የተለመዱ አማካሪ ፖለቲከኞችን፣ ተከራካሪዎችን፣ ተቀናቃኝ የዳያስፖራ ተዋናኞችንና ባለሚዲያ አጋሮቻቸውን ያካትታሉ። 

አንዳንዶቹ በይፋ የአማራ ፋኖ፟ን ትግል ደጋፊ ሆነው ቢቀርቡም፣ ምዕራቡ የሚሸልማቸውና አብልጦ የሚያቀርባቸው፣ “ዲፕሎማሲያዊ” በሮቹንም የሚከፍትላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች ናቸው። እነዚህ ወገኖችች የፋኖ፟ ኃይሎችን ትግል ከጀርባ አጓታች መዕራባዊ ጣልቃ ገብነትን (“ንግግር” እና “ድርድር” በመግፋት) አመቻቺ የሆኑ ግለሰቦችና ስብስቦች ናቸው። 

አበራ  እነዚህ ወገኖች አማራ ፋኖ፟ የሚከተለውን ግልጽ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ዕቅድ ፊት ለፊት ባይቃወሙም፣ በእጅ አዙር ዕቅዱን የማለስለስ፣ ቆራጭ ስለቱን የማዶልዶም፣ ብሎም አቅጣጫውን የማስቀየር ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። 

ቸሩ  ትክክል! አንዳንድ ተገዳዳሪ የዳያስፖራ ሚዲያና ምሁራን ወገኖች የተወሰኑ አካባባዊ ወይም ጠቅላይ ግዛታዊ ፋኖ፟ዎችን ለይተው የገንዘብና የውከላ ድጋፍ በመስጠት የአማራ ሕዝባዊ ኃይሎቹ ላይ አደገኛ ከፋፋይ ተጽዕኖ ያሳርፋሉ ወይም ሊያሳርፉ ይሞክራሉ።    

አበራ  የአማራ ፋኖ፟ መዋቅረ መንግሥት ቅየራ ዕቅድ ለመሳካቱ እንቅፋት የሚሆኑበትን ነገሮች ከወዲሁ ተገንዝቦ በሥርዓታዊ ዘዴ ባጭር መቅጨት ወይም ፍሬቢስ ማድረግ ይኖርበታል። የፋኖ፟ ኃይሎች በትብብር ይህን ግዴታ መወጣት እንደሚችሉ አልጠራጠርም። 

ቸሩ  እሺ፤ በመጨረሻ፣ እኔ ከጠቆምኳቸው፣ ከሞላ ጎደል የምትጋራቸው መለስተኛ አሳሳቢ ሁኔታዎች ሌላ የሚያሰጉህ ነገሮች ካሉ እነሱን በልና አንደኛውን የጭውውታችን ክፍል እንዝጋ። እዚህ ልንወያይባቸው ጊዜ ስለሌለን ጠቅስናቸው ብቻ እንለፍ።

አበራ  መልካም፤ በጣም አስጊ ባይሆኑም አጠያያቂ ወይም ግልጽ ያልሆኑ የምላቸውን ሁለት ጉዳዮች ላንሳ። አንደኛው፣ በስክንድር ነጋ የሚመራውን የአማራ ሕዝባዊ ግንባር (አሕግ) የሚመለከቱ ድርጅት ነክ ጥያቄዎች የሚያስነሳ ነው። 

ማለትም፣ አሕግ ከፋኖ፟ ሕዝባዊ ኃይሎች ጋር ሕይወታዊ (የአመራርም ሆነ የአሠራር) ትስስር አለው ወይስ ግንባር ቀደም ሳይሆን በረዳትነት የተወሰነ ድርጅት ነው? በፋኖ ኃይሎች ውስጥም ሆነ ዙሪያ ወይም በዳያስፖራ ‘ዲፕሎማሲ’ ጎኑ ዋና ሥራው ምንድነው? ከእስክንድር የግል ታዋቂነት ባሻገር ድርጅቱ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ ምን ያህልና እንዴት ይሆን?  

ሁለተኛው ጉዳይ…

ቸሩ  …ሁለተኛውን ጉዳይ ከመጥቀስህ በፊት ያነሳኸውን ጥያቄ ለማጠናከር…በጎጃም የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ፟) መሪ ዘመነ ካሴ ባለፈው ሰሞን በሰጠው አንድ የሚዲያ ገልጻ ላይ ንግግር ካደረገላቸው የእንጂባራ ፋኖ፟ ታጋዮች መካከል አንዱ ‘ሕዝባዊ ኃይሉ ከሕዝባዊ ግንባሩ ጋር ያለው ልዩነት ወይም አንድነት እያደናገረን ስለሆነ መግለጫ ቢሰ፟ጠን’ ብሎ ሲጠይቅ አዳምጫለሁ። 

ማለትም፣ ጉዳዩ እኛ እንደ ውጭ የትግሉ ደጋፊዎች ከሩቁ የምናስበው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሞት የሽረት ትግል እያደረጉ ያሉ የፋኖ፟ አርበኞች ራሳቸው በግልጽ መገንዘብ የሚፈልጉት ነገር ይመስላል። 

ሰሞኑን በጎንደር የፋኖ፟ እዝ ምሥረታ እንቅስቃሴ መሬት ላይ ያሉ የሻለቃ፣ የብርጌድና የክፍለ ጦር መሪዎችን ያላክተተ፣ በሕዝባዊ ግንባሩ ሰዎች ወይም ተወካዮች ነን ባዮች ጣልቃ ገብነት የተደረገ ሙከራ እንደነበር ተዘግቧል። ይህ ውዝግብም የግንባሩን ያልተረጋገጠ፣ አጠያያቂ ሚና ያመላክታል።

በል፣ ሁለተኛ ጉዳይ ያልከውን ጠቁምና እንጨርስ። 

አበራ  እሺ፤ አመሰግናለሁ ለአጠናካሪ መረጃዎቹ። ሁለተኛው፣ በአዕምሮዬ ብቅ ጥልቅ እያለ የሚያሳስበኝ ነገር የስካሁኑ የፋኖ፟ ኃይሎች ጠቅላላ የጦር ውጊያ ይዞታ ወይም አኪያሄድና ለሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ዕቅዳቸው ያለው አንድምታ ነው።

የፋኖ፟ ኃይሎች ከተሞችን ያዝ ለቀቅ የማድረጉ ወይም እከተሞች ገባ ወጣ የማለስቱ ውጊያ ዘዴ አንዳንድ ትያቄዎች ያስነሳል፥ 

እስከመቼ ይሆን ዘዴው አስፈላጊ ሆኖ የሚቀጥለው? 

ፋኖ፟ በውጊያ የያዛቸውን ከተሞች ለቆ ሲወጣ ሕዝቡን ለአገዛዙ ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና የንብረት ውድመት ላለማጋለጥ ምን መከላከያ አለ ወይም ሕዝቡ (በፋኖ እርዳታ) ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? 

ሰፋና ጠለቅ ካለ ስልት አኳያ፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚደረጉ ታክቲካዊ ውጊያዎችና የሚገኙ ድሎች በየጊዜው እየተጠራቀሙ፣ እየተገነባቡ፣ እየተጠናከሩና እያየሉ በመሄድ ወደ አማራ ጠ/ግዛቶች ዋና፟ ከተሞች፣ ከዚያም ወደ ሌሎች ክፍለ ሀገራትና አዲስ አበባ የሚዛመቱበትን አቅጣጫ ማስያዝ ምን ያህል ታሳቢ ሆኗል? ወይስ በሆነ ምክንያት ችላ ተብሏል? 

ጨረስኩ።

ቸሩ  ከጥያቄዎችህ አቀራረብ እንደምረዳው፣ ጉዳዮች እንዳወሳሰናቸው የፋኖ፟ ኃይሎችን ወደ ‘አራት ኪሎ’ የትግል ጉዞ ሊያቀላጥፉ ወይም ሊያጓትቱ ይችላሉ። ያ ብቻም አደለም፤ ጥያቄዎቹ እንዳመላለሳቸው የፋኖ፟ን የሥርዓት ለውጥ ዕቅድ ተፈጻሚነት የማመቻቸት ወይም የማስተጓጎል ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል እንዲሉ።

የመጀመሪያ ጭውውታችንን እዚህ ላይ አገባደድን። ሌላ ቀን በፋኖ፟ ንቅናቄ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በምናደርገው ሁለተኛ ክፍል ውይይታችን እስክንገናኝ ድረስ ደህና ቆየኝ አበራ።

አበራ  ደህና ሰንብት፣ ቸሩ።

ይቀጥላል…        

__

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡
t.me/borkena 

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News English page

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here