spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeአበይት ዜናኢትዮጵያን የማዳን ጥሪ

ኢትዮጵያን የማዳን ጥሪ

ከልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት

የአድዋ ድል ቀን፤ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችና እህቶች፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ በጨለማ ጉዞ ከመደናበር ወይም በደስታና በኩራት ከመጓዝ መምረጥ ባለባት ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ የምናቀላፋበት ወይም የሀገራችንን ጉዳት ለሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች እድል የምንሰጥበት መሆን የለበትም፡፡ ከሶስት ሺህ አመታት በላይ ያልተለየንን የአምላክ ፀጋና ረድኤት የምናባክንበት ሰአት መሆንም የለበትም፡፡ 

የኢትዮጵያ እጣፈንታ አሁን በእጃችን ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦችና የዘውድ ምክርቤቱ በአንድ አላማ እጅ ለእጅ ተሳስረው ለመስራት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡

እኛ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፤ ዛሬ ፀሎታችንን የምናጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም ቸሩ አምላክ ረድቶን በ1888 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጀግኖች፤ በዳግማዊ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ መሪነት፤ የጣልያንን ጦር ድል ያደረጉበትን ቀን እያከበርን ስለሆነ ነው፡፡ ታላቁ የአድዋ ድል፤ ለኢትዮጵያውያን የነፃነት ጮራ ያንጸባረቀና ክብራቸውንም ለአለም ህዝብ ያበሰረ በመሆኑ፤ የዘውድ ምክርቤቱ እስካሁን ድረስ፤ ይህንን የአንድነታችን ምልክት የሆነውን ቀን፤ ምን ጊዜም ከአእምሮአችን እንዳይጠፋ ሲታገል ቆይቷል፡፡ በዛሬው ፀሎታችንም በ1933 ዓ.ም የኢትዮጵያ አርበኞች የጣልያንን ሁለተኛ የግፍ ወረራ ድል የተቀዳጁበትን ወቅት እንድናስታውስ የዘውድ ምክርቤቱ ይጠይቃል፡፡ 

በተጨማሪም፤ የዛሬው ፀሎታችን፤ በወቅቱ የሀገራችንን ህልውና ከባድ አዳጋ ላይ በመጣል ላይ ያለውን ጦርነትና ግጭት፤ ቸሩ አምላካችን መፍትሄ እንዲሰጥልን የምንማጸንበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት፤ የህዝባችንን ህይዎትና ኑሮ በማጥፋትና በማጓደል ላይ ይገኛል፡፡ የአለምም ህዝብ በሚገባ የተገነዘበው አይመስልም፤ ወይም አውቆ በግዴለሽነት የተወው ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ብልጽግናና መብት ትጠብቅ በነበረችበት ጊዜ፤ የአምላክ ረድኤትና ፀጋ አለተለያትም ነበር፡፡ አሁን ግን፤ ሀገራችን ከባድ ችግር ላይ ለመውደቅ እየተንገዳገደች ትገኛለች፡፡ 

የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት፤ ላለፉት 50 አመታት የገጠሙትን ከባድ ፈተናዎች ተቋቁሞ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በመንቀሳቀስና በመጠናከር ላይ ይገኛል፡፡ የደርግ መንግስት፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በግፍ ከመግደሉም በላይ፤ በ1966 ዓ.ም ያቀዱትን ዲሞክራሲያዊና ፍጹም ነፃነት እንደዚሁም ለሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል የመሆን መብት ማምጣት ይችል የነበረውን የህገመንግስት ረቂቅ ማጨናጎፉን ብዙዎቻችን የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፤ እነዚያ በአድዋና በጎንደር ግዙፍ ድሎችን ያቀናጁን ታላላቅ ንጉሰነገስታት ዛሬ በህይዎት ባይኖሩም፤ በመንፈስ ከእኛ ጋር ናቸው፡፡ ከአእምሮአችንም አልጠፉም፡፡ የሚያበረታታውና የሚያነሳሳው ቋሚ ስራቸውም፤ ከእኛ አእምሮ በፍጹም አልተሰወረም፡፡ ስለሆነም አልሞቱም፡፡ የሰሎሞናዊው ዘውድም ለኢትዮጵያዊያኖች ብልጽግናና ደህንነት ጠንክሮ ለመስትራትም ሆነ ክብርና ኩራት ለሀገራችን አጎናጽፎ ለአለም ህዝቦች የምስራች ጮራ ለማንጸባረቅ ዝግጁ ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የደረሱብንን የተወሳሰቡ ችግሮችንና መሰናክሎችን ማስወገዱ በእኛ እጅ ነው ስንል፤ ወደ መከራ፤ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የከተቱንን በውስጣችን ያሉ ልዩነቶች ለማስወገድ፤ መነጋገርና አንተም ተው አንተም ተው ተባብለን፤ በመካከላችን ውስጥ መተማመን ለመፍጠር መጣር እንደሚኖርብን በማሰብ ነው፡፡

ነገርግን አንድ እውነት ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ከገባንበት ወጥመድና ዝቅጠት ለመውጣት የሚረዳን፤ በሐምሌ 30 ቀን 1966 ዓ.ም የተነደፈውን ሆኖም ግን በስራ ላይ ለመዋል እድል ያላገኘውን ህገመንግስት አሁን ተቀብለን፤ የዲሞክራሲ አሰራርና የህግ የበላይነት በሀገሪቱ እንዲሰፍኑ ስንጥር ነው፡፡

ዘውዱ፤ በኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት አማካኝነት፤ ህገመንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትና በውጊያ ላይ ላሉት ሃይሎች የጋራ ድልድይ ሆኖ ለማነጋገርና ለማስማማት ያለውን ዝግጁነት ያስታውቃል፡፡ በ1966 ዓ.ም በተነደፈው ህገመንግስት መሰረት፤ የኢትዮጵያ ዘውድ፤ በፓርላማ ምርጫ ሂደትና በመንግስት የእለት ስራ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ ሆኖም ግን፤ ህገመንግስቱን ማስከበርና የኢትዮጵያዊያኖችን ህጋዊ መብትና ነፃነት ማስጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ ስለሆነም፤ በወቅቱ በውጊያ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ሃይሎች ሁሉ፤ ዘውዱ የሰላም ማውረድ አላማ እንዳለውና ይህንንም እርቅ ለማምጣት ዝግጁ መሆኑን እንዲረዱ እናሳስባለን፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያዊያኖች፤ በልዩነቶቻችን ላይ ለመነጋገርና ለመስማማት እንችል ዘንድ፤ አምላካችንን እየተማጸን፤ ታላቋን ኢትዮጵያንና በውስጧ ያሉትን ብርቅና ውብ ብሄረሰቦች እንዲበለጽጉና እንዲያብቡ የምንችለውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ዛሬ ነገ ሳንል እንዘጋጅ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ የጊዜውን ወሳኝነት ተረድቶ እንዲነሳና በሀገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነትና አሰራር እንዲኖር፤ በህዝቦች መካከል እኩልነት እንዲንሰራራና ለሁሉም ዜጋ ክፍት የሆነ የእድገት እድል እንዲመጣ ለመታገል ይዘጋጅ፡፡ አምላክም ይህን ተማጽኖአችንን እንዲሰማልንና እንዲያሳካልን እንፀልይ፡፡ የስራችንንም ፍሬ ለመላው አለም እንድናሳይ ይርዳን፡፡

ይህ ወቅት፤ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ ክብርና ፀጋ አምላክ መልሶን፤ ለእኛም ሆነ ለአለም ህዝብ የምናሳይበት ይሁን፡፡ ኢትዮጵያን እንደገና የተከበረችና የተቀደሰች ሀገር እንድናደርጋት አምላክ ይርዳን፡፡ አሜን

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here