spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትበኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ የብሄርነት ዕሳቤዎችና ሊጋሯቸው የሚችሉ ጉዳዮች

በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ የብሄርነት ዕሳቤዎችና ሊጋሯቸው የሚችሉ ጉዳዮች

የብሄርነት ዕሳቤዎችና
ከአልጃዚራ ገጽ ላይ የተገኘ

ያሬድ ወልደ ማርያም

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኢትዮጵያን ታሪክ አሁናዊ ሁኔታና የወደፊት ቢሆኖች በሚመለከት ሁለት ተፎካካሪ ዕሳቤዎችን ስንታዘብ ቆይተናል።  አንደኛው ኢትዮጵያን እርስ በርስ መልካም ግኑኝነትና ሁሉም ተጠቃሚ የሆኑበት ልውውጦች ያሏቸው ማኅበረሰቦችን ያቀፈች ጥንታዊ አንድነቷን የጠበቀችና ነጻ ሀገር አድርጎ ይመለከታታል።  ይሄኛው ዕሳቤ የጋራ ባህርያትን ከዘውግ ልዩነቶች፣ ሀገርን ከዘውግ እና ዘውጋዊ ያልሆነ ፖለቲካን ያስቀድማል።  ሁለተኛው ዕሳቤ ኢትዮጵያን በቅድመ ዘመናዊ እና ዘመናዊ ታሪኳ የተለያዩ ሕዝቦች በወረራ በጭቆናና በብዝበዛ የተያዙባት ኤምፓየር እንደሆነች ይገልጻታል።  የዘውግ ማህበረሰቦችን ወጥ ባህልና እንዳላቸውና ከሌሎች የተለዩ እንደሆኑ አድርጎ ያያቸዋል።  ዘውገኝነትንም ከሀገራዊነት በማስቀደም ዘውጋዊ ፌዴራሊዝምን ወይም የዘውጎችን መገንጠል ያራምዳል።

ሁለቱም አመለካከቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በሚመለከት የተወሰኑ እውነታዎችን ቢያንጸባርቁም ታሪካዊና ማኅበረ ፖለቲካዊ ክስተቶችን እያማረጡ በመጠቀም ስለሀገሪቱ ዕጣ ፋንታ የሚለያዩ ራዕዮችን ያቀርባሉ።  አሁን አገሪቱ የምትተዳደርበት በብሄር ፌዴራሊዝም ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግስት ከሁለተኛው ዕሳቤ ጋር የተያያዘ ነው።  የእዚህ ዕሳቤ አራማጆች የህገ መንግስቱን መሠረታዊ መርሆዎች ሲደግፉ የመጀመሪያውን ዕሳቤ የሚቀበሉት ደግሞ ህገ መንግስቱ ሰፊ ማስተካከያ እንዲደረግበት ወይም ጭራሹኑ እንዲወገድ ይሻሉ።  እነዚህ የሚለያዩ አስተሳሰቦች አሁን ለምናየው አለመረጋጋት ግጭቶችና የሀገሪቱን ቀጣይነት በሚመለከት ላሉ ስጋቶች አሰተዋጽኦ አድርገዋል።  በሁለቱ ዕሳቤዎች አራማጆች መካከል መግባባትና መቻቻል እምብዛም አይታይም።  ነገር ግን የሀገሪቱን ማኅበረሰቦች ፍላጎቶችና ሕልውና ለማረጋገጥ ሁለቱም ትርክቶችና እና ምኞቶች የጊዜው የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ አካል እንደሆኑ መቀበልና የሚጋሩትን ጉዳዮች ማፈላለግ ግዴታዎች ናቸው።

የነዋሪዎችዋን ደኅንነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ዕውቀትን መሰረት ያደረገ፣ ሁለንተናዊ፣ አቃፊ እና አክባሪ የሆኑ የሀገሩን ታሪክና ማህበረ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ አረዳድ እና የወደፊት ራዕይ እጅግ አስፈላጊ ናቸው።  እንደዚህ ያለ ዕይታ ባንድ በኩል የሀገሩን ዘውጋዊ ማኅበረሰቦች ብዝኀነትና ልዩነቶች እና ብዙዎቹም ስላስተናገዱት ታሪካዊ መገለል ዕውቅና ይሰጣል።  በሌላ በኩል የሀገሩ ማኅበረሰቦች የነበራቸውን የረዥም ጊዜ ግኑኝነት፣ የጋብቻና የንግድ ትስስር፣ የባህል ልውውጥ፣ የጋራ ባህርዮችና ከአውሮፓውያን አገዛዝ ነጻነትን ጨምሮ የሚጋሩትን ብሄራዊ ተሞክሮ ያቅፋል። ታሪካዊ በደሎችንም ለማረም በሁሉም ማኅበረሰቦች አባላት የተከፈለውን ብዙ መስዋዕትነትና የተደረጉ ለውጦችን ይቀበላል።  እነዚኽ ለውጦች በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አገዛዝ ወቅት አገሩን የማዘመን ሂደት፣ የደርጉን የመሬት አወጅ እና በኢህአዴግ ጊዜ ለቋንቋዎች መብት፣ ለማንነትና ለአስተዳደራዊ ፌዴራሊዝም የተሰጠውንም ዕውቅና ያካትታሉ።  ዛሬ ያለችውን ትልቅ፣ ኅብረ ዘውጋዊ፣ የተሳሰረችና በማኅበረሰቦች መካከል ስምምነት የሚታይባት ሀገርንም ማድነቅ ይገባል።  እንዲህ ያለ ግንዛቤ በሀገሪቱ የተስፋፋውን ሙስና፣ አለመቻቻል፣ ግጭቶችና የዘር ማጽዳት እንዲሁም የዘር ማጥፋት ያስከተለውን በመንግስት ውስጥና ከመንግስት ውጭ ባሉ አካላት ዘንድ የሚታየውን የጠንካራ ብሄረተኛነት አመክንዮ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። 

ስለዚህ የጊዜውን የፖለቲካና የደህንነት ሁኔታዎችን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችና የህገ መንግስቱን ዘውጋዊ መሠረት የፌዴራል አወቃቀርና የምርጫ ስርዓት በሚመለከት የሚታሰቡ ለውጦች ከላይ የተገለጹትን የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የሚለያዩና የጋራ ተሞክሮዎችንና ባህርያትን ማገናዘብ ይኖርባቸዋል።  ለምሳሌ ለሃገሪቱ የሚበጀው የዘውግ ወይስ የአካባቢ ፌዴራሊዝም ስለመሆኑ በልሂቃንና በህዝቡ ዘንድ ትልቅ የልዩነት ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን።  ይህ አጣብቂኝ ታሪካዊ ተለምዶን፣ የአካባቢ ቋንቋን፣ አስተዳደራዊ አመቺነትን፣ የማህበረሰቦችን መቀራረብ፣ የወሁዳንን መብትና ሬፈረንደምን ጨምሮ የማህበረሰቦችን ምርጫ የሚያስተናግድ የፌዴራል ስርዓት ላይ በመወያየትና በመወሰን ሊፈታ ይችላል።  በእዚህ ሂደት የሚመረጠው የዘውግም ሆነ የአካባቢ ፌዴራሊዝም የግልና የቡድን መብቶችን፣ የዘውግ ማንነትንና ብሄራዊ ትስስርን ባንድ ላይ ማስተናገድ ይኖርበታል። ይኽም በዋነኛነት የቡድን ፍላጎትና ማንነት ማስጠበቂያ መሳርያ የሆኑትን የዘውግ ብሄረተኝነትንና ፖለቲካን ሳቢነትና አስፈላጊነት ሊቀንሳቸው ይችላል።  ይልቁን ኅብረ ባህላዊነት እንዲሁም የሕግ የበላይነትን፣ ሙስናን የሚቆጣጠር መልካም አስተዳደርን፣ ሰብዓዊ መብቶችን፣ የማኅበረሰቦችን ወንድማማችነትን፣ ነፃነትንና ዴሞክራሲን ያማከለ የፖለቲካ ስርዓት ዘላቂ የህዝብ ደህንነትና አብሮነት መሰረት ይሆናሉ። 

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News 


ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here