spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአደዋ ምእራፎችና የኢትዮጵያውያን የዋህነት።

የአደዋ ምእራፎችና የኢትዮጵያውያን የዋህነት።

የዳግማዊ አጼ ምንሊክ ሃውልት
የዳግማዊ አጼ ምንሊክ ሃውልት

ከሚኒሊካዊው

ኢትዮጵያውያን ታላቅ መሆን ያልቻልንው 1ኛ በየጊዜው በመታለላችን፣ 2ኛ የዋህ በመሆናችን፣ 3ኛ ጦርነትን ፊት ለፊትና በምድር ብቻ አድርገን በማሰባችን ነው። ይህ ጽሑፍ ላለፉት 150 አመታት ኢትዮጵያውያን በነዚህ ቱባ ችግሮች ስንጠለፍ መኖራችንን የሚያብራራ ነው። መፍትሄውም እነዚሁ ቱባ ችግሮች ውስጥ ነው ያለው። አደዋ ከ128 አመታት በፊት ተደርጎ እንደተጠናቀቀ መቁጠር ስህተት ነው። በአንጻሩ የካቲት 23 ቀን 18888 ዐ/ምም የተደረገው ጦርነት ትልቁና 1ኛው የአደዋ ጦርነት ምእራፍ እንጂ ሙሉ ክፍሉ እንዳልሆነ የዚህ ጽሑፍ አቋም ነው። አሁንም የአደዋ ጦርነት ምእራፍ ላይ መሆናችንን ጽሑፉ ይዳስሳል። 

የቅኝ ግዛት መጀማመሪያው ላይ እንግሊዝ በናፒየር ጦር እየተመራች ኢትዮጵያን ልትወጋ መጥታ ነበር። ነገር ግን እንግሊዝ የቴዎድሮስን ጦር መውጋትና ከኢትዮጵያ ጋር መዋጋት አንድ እንዳልሆነ አሳምራ በማወቋ ኢትዮጵያን በቀጥታ ለመቆጣጠር አልደፈረችም። ቴዎድሮስ የተሸነፈው ሌሎች ሊያግዙት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነበር። እንዲያውም በዝብዝ በሚል የሚታወቀው ካሳ ምርጫ ወይም አጼ ዮሀንስ መንገድ ለሰጠበትና ላመላከተበት ብዙ መሳሪያዎችን ከእንግሊዝ ተሰጥቶት ነበር። እንግሊዝና ፈረንሳይ ቀስ በቀስ እግራቸውን ማስገባት ቢፈልጉም በቀጥታ ከኢትዮጵያውያን ጋር ጦርነት መክፈት ግን ውርደት እንደሚያስከትል ሳይገባቸው አልቀረም። ለዚህም ነው ከአጼ ዮሀንስ እና ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ድርድሮችን ሲያደርጉ የነበረው። የሂወት ስምምነት፣ ሶማሊያን አስመልክቶ የተደረገ ስምምነት፣ ጅቡቲን አስመልክቶ የተደረገ ስምምነት እና ወደቦች ጋር የነበሩ ስምምነቶች የዚህ አካላት ናቸው። 

ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት እንደሚሉት የኢትዮጵያውያን ትልቁ ችግር ማለቂያ የሌለው መታለላችን ነው። እንግሊዝ ከአጼ ዮሀንስ ጋር ባደረገችው ድርድር ከረን፣ ቦጎስ እና ምጽዋን ለኢትዮጵያ እንድትመልስ እና በምትኩ ኢትዮጵያ ደግሞ ግብጽን ወክለው ሲዋጉ በመሀዲስቶች የተያዙባትን ምርኮኞች እንድታስለቅቅላቸው ተስማሙ። ኢትዮጵያ በየዋህነት ውሉን ቀድማ ፈጸመች። እንግሊዝ ግን ከረንና ቦጎስን አስረክባ ምጽዋን ለኢጣልያ ስጦታ አቀረበች። መታለል 1 ይህ ነው። እንግሊዝ ምጽዋን ለኢጣልያ መስጠቷ ራሷ ኢትዮጵያን በቀጥታ መውረር ስለማትፈልግ ነው የሚለውን መደምደሚያ የሚያጠናክርልን ነጥብም ይሆናል። 

ኢጣልያ በበኩሏ ኢትዮጵያን በጦርነት ከማንበርከኬ በፊት የማታለል ስራ ልስራ ብላ ነበር የወሰነችው። ከንጉስ ሚኒሊክ ጋር ስምምነት በመፈጸም ለስለላ የሚያገለግላት ቦታ እንዲሰጣት አደረገች። ከአጼ ዮሀንስም ጋር ወዳጅ መስላ ስትቀርብ ጀግናው አሉላ ዶጋሊ ላይ ድባቅ መታት። አጼ ዮሀንስ ሳትታዘዝ ኢጣልያን ወግተሀል ብለው አሉላ ላይ ቅጣት በየኑበት። የኢጣልያንን ወዳጅነት ላለማጣት መሆኑ ነው። እየተንኳተተ ኤርትራን የያዘው ኢጣልያ ወዳጅ ተደርጎ በአጼው መቆጠሩ መታለል ነው ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል?

ንጉስ ሚኒሊክም ንጉሰነገስት ሆነው ሲቀቡ መንገስ የነበረበት የዮሀንስ ዘር ነው እንጂ ሚኒሊክ አይደለም ብላ ኢጣልያ ራስ መንገሻን ወዳጅ አደረገች። አጼ ሚኒሊክን በጎን እውቅና የምሰጠው ለእርስዎ ነው እያለች ለማታለል ትሞክር ነበር። አጼ ሚኒሊክ ግን ጮሌ ነበሩና ወይ መንገሻን ወይ እኔን ምረጪ ብለው ኢጣልያን ከራስ መንገሻ ጋር አጣልተው መንገሻን በጎን ወዳጅ አደረጉት። 

ቀጣዩ የማታለል ድርጊት ውጫሌ ላይ የተደረገው ነበር። እስከመረብ ወንዝ ድረስ ቀድማ የተቆጣጠረችው ኢጣልያ ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ውጫሌ ላይ ባደረገችው ስምምነት ሆነ ብላ የኢጣልያንኛ ትርጉሙን አበላሸች። አንቀጽ 3 እስከመረብ ወንዝ ድረስ ያለውን ቦታ ይዛ እንድትቆይና ከወንዙ እንዳትሻገር የሚያትት መሆኑ ለኢትዮጵያ ጉዳት ቢሆንም አጼ ሚኒሊክ ግን ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። በነገሱበት አመት ሁሉንም ሕዝብ አስተባብረው ምድረ ባህር ወይም ኤርትራን ከኢጣልያ ማስለቀቅ የሚያስችል አቅም አልነበራቸውምና ስምምነቱን ፈጽመዋል። ክፉ ቀን የተባለው ረሀብ ደግሞ ችግሩን አባሰው። አንቀጽ 17 ግን ግልጽ ማጭበርበር የተፈጸመበት ነበር። የአማርኛና የኢጣልያንኛ ትርጉሙ በተጋጨ ጊዜ በጋራ ማሻሻያ እንደሚደረግ ቢስማሙም ኢጣልያ ሆነ ብላ ያበላሸችው ስለሆነ እምቢኝ አለች። መታለል ሁለት እንበለው። 

ከ5 አመታት በኋላ ጦርነት ግድ ሆነ። አምባላጌ ላይ ኢጣልያ ተሸነፈች። ከአምባላጌ ቀጥሎ መቀሌ የሰፈረው የኢጣልያ ጦር ለመስማማት ፈቃደኛ ነኝ እያለ ሲያዘናጋ ቆይቶ ጠንካራ ምሽግ ሰራ። ባለ3 ዘርፍ ምሽግ ነበር። የመጀመሪያው በሹል ጠርሙስ የታጠረ፣ 2ኛው በሹል ሽቦ የታጠረ፣ እና 3ኛው ደግሞ በጠንካራ የድንጋይ ግንብ የተገነባ ነበር። ድርድርን እንደማሸነፊያ ተጠቅሞ ምሽጉን ማጠናከሩ ነው። ሶስተኛው መታለል ይሉታል ይሄ ነው። 

በመጀመሪያው ዙር ምክርን አልሰማ ብለው በጀግንነት የተዋጉት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ እልቂት ደረሰባቸው። ምሽጉ ድረስ ቀርቦ መዋጋት እልቂት ስለሚያደርስ ምንጩ ይያዝ ያሉት ወታደር ምክራቸው ባለመሰማቱ በጀግንነት ተዋግተውና የሚገድሉትን ፈጅተው ተገደሉ። 

ከዚህ ለጥቆ ምንጩ ተይዞና በመትረየስ እና መድፍ ታጥሮ ይጠበቅ ጀመረ። ኢጣልያ በውሀ ጥም ተሸነፈ። ነገር ግን ጦርነቱን አሸነፈ። አሸናፊ የሆነውም በማታለል ነበር። ከእንግዲህ ላይዋጋ ቃል ገብቶ፣ ስንቁም መሳሪያውም በኢትዮጵያውያን አጋስሶች ተጭኖለት ተሸኘ። የአጋስሶቹን ኪራይ ቢከፍልም የአጓጓዦቹን ክፍያ ግን አልከፈለም ነበር። ይህም ሌላው ማታለል ነው። ብልኋ እቴጌ ሲሆን ሲሆን ይማረክ፣ ካልሆነ ደግሞ መሳሪያውን አስረክቦ ይሂድ ብለው ነበር። ምክራቸው ባለመሰማቱ ኢጣልያ በግንባር የተሸነፈውን በድርድር ድል አደረገ። 

ቀጣዩ የአደዋ ጦርነት ነው። የአደዋ ድል ለኢትዮጵያ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ትልቅ ቦታ የሚይዘው የኢጣልያ መታለል ነበር። የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ እንደሚባለው ሆነና ኢጣልያ ሰላዬ ናቸው ያለቻቸው እነአውአሎም አታለሏትና በተሳሳተ ጊዜና ቦታ ጦርነቱን ጀመረች። ያ ሁሉ ጦር በ8 ሰአታት ውስጥ እምሽክ ብሎ ተጠናቀቀ። አደዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአለም ጭቁን ሕዝብ ብርሀን ሆነ። 

ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የተሸወድንው የአደዋ ጦርነት የመጨረሻው መስሎን ነበር። ኢጣልያ በአደዋ ጦርነት አንገቷን ደፍታ ብቻ አልተቀመጠችም። አንገቷን እንደደፋች ሴራ ታውጠነጥን ነበር። ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ መስላ የአዲስ አበባ ስምምነትን ፈጸመች፤ ኤምባሲ ከፈተች፤ በአጼ ሀይለስላሴ ተጎበኘች፤ ሌሎች የወዳጅነት ስምምነቶችን ፈጸመች። ወዳጅ መስሎ መቅረቧን 5ኛው ማታለያ ብለን እንቁጠረው። እንዲህ  እያታለለች እስከወልወል ግጭት ድረስም ሙሉ ዝግጅት ስታደርግ ቆየች። 

ኢጣልያ ከአደዋ ጦርነት ተምራ ነበር ከ40 አመት በኋላ የቀረበችው። ኢትዮጵያን ፊት ለፊት በምድር ጦርነት ተዋግቶ ማሸነፍ እንደማይቻል አምና አውሮፕላን እና የመርዝ ጋዝ መጠቀም ግድ መሆኑን ወስና ነበር። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን የአደዋ ጦርነት የመጨረሻው መሆኑን አምነን እና በኢጣልያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተታለን በውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ስንታመስ ቆይተን ለጦርነት ምንም ዝግጅት አላደረግንም ነበር ማለት ይቻላል። በተቃራኒው የሰገሌ ጦርነት የተባለ እጅግ አውዳሚ ጦርነት አድርገን ሕዝባችንን ጨረስን።

ኢጣልያ ወልወልን አሳባ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ ጦርነት ጀመረች። አውሮፓውያንም ኢጣልያ የመሳሪያ ችግር እንደሌለባት እያወቁ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ሁለቱም ላይ የመሳሪያ ማእቀብ ጥለናል አሉ። በዚህም ምንም እንኳን ምእራባውያኑ እውቅና ባይሰጡት 2ኛው የአለም ጦርነት ተጀመረ። ኢጣልያ ከአደዋ ጦርነት ብዙ ትምህርት ወስዳ ነበር። የኢትዮጵያ ጥንካሬ አንድነቷ መሆኑን በማመኗ አንድነቷን የሚበጣጥሱ መረቦችን ስትጠልፍ ቆይታ ነበር። በዚህም አማራ፣ ኦርቶዶክስ፣ ታሪክ የተባሉትን በሙሉ ማፍረስ እንዳለባት ወሰነች። ብዙ ባንዳዎችንም ተጠቀመች። በባንዳዎች ምክንያት ያለቁት ጀግኖችን ቁጥር ፈጣሪ ይቁጠረው። በምድር መዋጋት የለመደው የኢትዮጵያ ገበሬ ከሰማይ የሚዘንብበትን የመርዝ ጋዝ መቋቋም አልቻለም። ብዙ ሰው ካለቀ በኋላ ኢትዮፕያውያን የጦርነት ዘዴያችንን ቀየርን። ይኸውም ፊት ለፊት ከመዋጋት ይልቅ በሽምቅ መዋጋት ብቸኛ አማራጭ መሆኑን አርበኞች አመኑ። የውስጥ አርበኞችንም ተጠቅመው ውጊያቸውን አጧጧፉ። ኢጣልያ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ቢችልም ኢትዮጵያ እጅ ሳትሰጥ ለአምስት አመታት ያህል ተዋጋች። በመጨረሻም ኢጣልያ ሽንፈቷን ተከናንባ ኢትዮጵያን ለቃ ወጣች። 

በምትኩ እንግሊዝ ሞግዚት ካልሆንኩ ብላ አሻፈረኝ አለች። አጼ ሀይለስላሴ በጥበብ የእንግሊዝን ጌታ አሜሪካን አባብለው እንግሊዝን ጠራርገው አስወጡ። 

ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ስትከፍት የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካን ነበር የተጠቀመችው። አማራ እና ኦርቶዶክስን ከመፍጀቷም ባሻገር የኢትዮጵያን ታሪክ ስትመርዝ ቆይታ ነበር። ኦስትሪያዊው ሮማን ፕሮቼስካ ፍንትው ባለ መልኩ ኢትዮጵያን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል አስቀምጦ ነበር። ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንዲከፋፈሉ ማድረግ ውጥኑ ነበር። 

ይህ ውጥን እየተጠናከረ ሄደ። ምእራባውያን ኢትዮጵያን አልቻሏትም። በ2ኛው የአለም ጦርነት ኢትዮጵያ በሰማይም በምድርም ጦር ቢወርድባትም ተቋቁማ ቅኝ ሳትገዛ ቀርታለች። በዚህ ሳታበቃ ቅኝ ተገዢዎች ነጻ እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ ቀጥላለች። የገለልተኞች ማኅበር (nonaligned movement) በሚልም ከሁለቱም ርእዮተ አለሞች ሳትወግን ሚዛን አስጠባቂ ሆናለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ አፍሪካ እንዳትበዘበዝ የሚያደርጋትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዋለደች። 

ይህን ምእራባውያን በጸጋ የሚቀበሉት ሊሆን አልቻለም። ከጦርነቶች አብዛኛው የሚከሰተው በሀብት (resource) መቀራመት መሆኑ ግልጽ ነው። አፍሪካውያን በባርነት የተጋዙት አሜሪካ ያለውን ሀብት የሚያለማ የሰው ሀብት በመታጣቱ ነበር። ኢንደስትሪዎች እንደአሸን ሲፈሉና የሰው ሀብት ፍላጎት ሲቃለል አፍሪካ ለጥሬ እቃዋ ተፈለገች። በዚህም ቅኝ ግዛት ተጀመረ። አፍሪካውያን እምቢኝ ብለው ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ ደግሞ ከቅኝ ግዛትም የከፋ አዲስ አገዛዝ ተፈጠረ። እስካሁን ድረስ አብዛኛው የፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ለፈረንሳይ ገንዘብ ይከፍላሉ። አፍሪካውያን ምእራባውያንን በሚያገለግሉ ሰዎች እየተመሩ ዜጋቸውን ሳይሆን ምእራባውያንን ያገለግላሉ። 

ኢትዮጵያ ባላት ተጽእኖ ፈጣሪነት ለራሷ አለመገዛቷ ሳያንሳት ሌሎች አፍሪካውያንም እንዳይገዙ እና እንዳይበዘበዙ ታደርጋለች በሚል ጥርስ ተነከሰባት። በዚህም የአደዋ ጦርነት የተቋጨ ቢመስልም መልኩን ቀይሮ እንደቀጠለ ነው። በመጀመሪያው የአደዋ ጦርነት ኢጣልያ ፊት ለፊት በመሬት ገጥማ ስትሸነፍ የጦርነት ስልቷን ከመሬት ወደሰማይ ቀየረች፤ በመርዝ ጋዝም ደበደበች፤ የኢትዮጵያ አንድነት ላይም ጥቃት ፈጸመች። ይህ ባለመሳካቱ ምእራባውያን ዘዴያቸውን ዳግም ከለሱት። በመሬትም ሆነ በሰማይ ከውጪ በማጥቃት ኢትዮጵያን ቀርቶ ሌሎች አፍሪካውያንንም መቆጣጠር እንደማይቻል አለም በተግባር ስላወቀ ቅኝ ግዛት የተባለውን ነገር እርግፍ አድርጎ ተወ። በምትኩ ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ ማጥቃት የሚል ስልት ተከተለ። አሁንም ያለንው ይኸው ደረጃ ላይ ነው። አፍሪካውያን ነጻ በወጡ በጥቂት አመታት ወታደሮች ቤተመንግሥትን እየጣሱ ስልጣንን በሀይል ተቆጣጠሩ። ሀገራቸው የምእራባውያን ገባር እንድትሆንም አደረጉ። የአፍሪካ ባለውለታዎች በየተራ በራሳቸው ሰዎች ተገደሉ። ኢትዮጵያም የዚህ ገፈት ቀማሽ ሆነች። በጦር ሜዳ ድል የነሳችውን ቅኝ ግዛት በራሷ ዜጎች እንድትጋተው ሲደረግ ቆየ፣ ላለፉት 50 አመታት። ኢጣልያ ቁጥር አንድ ጠላቶቿ ያደረገችው አማራ፣ ኦርቶዶክስ እና የኢትዮጵያን ታሪክ በጥቅሉ የኢትዮጵያን አንድነት ነበር ብለናል። በደርግ ዘመን መንግሥት ሀይማኖትን ለማጥፋት፣ አማራን በተዘዋዋሪ ለማድከም፣ የኢትዮጵያ ታሪክን ለመደምሰስ ቀን ከሌት ሰራ። ደርጉ በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ነበርና ብዙ ሀገር ወዳዶች የነበራቸው ምርጫ ወይ ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት አለበለዚያም ጦር ማንሳት ነበር። ምእራባውያኑ ሁለቱንም ተጠቀሙበት። ደርግም የኢትዮጵያን የልብ ትርታ ማቋረጥ ላይ ነበር ሲሠራ የነበረው፤ ተዋጊዎቹም መዳረሻቸውን ሳያውቁ የተጠለፉት ሀገርን በሚበታትኑ አዝማቾች ነበር። የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ የሚባል መላ ቅጥ የሌለው ጥያቄ አብዝቶ የተቀነቀነውም በደርግ ዘመን ነበር። በ1954 ዐ/ም ሁሉም ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዲማር ኢትዮጵያ ፖሊሲ የቀረጸች ቢሆንም አብዛኛው ሕዝብ ግን የዳበረ የጽሑፍ ቋንቋ አልነበረውም። ለኢትዮጵያ ውድቀቶች በሙሉ ንጉሰነገስቶቹን፣ አማራን እና ኦርቶዶክስን ሰበብ አደረጉ። የሕዝቡ ማኅበራዊ ድር (social fabric) የነበረውን አንድነት በጣጥሰው ኢትዮጵያ ታሪኳን፣ ሥርዐተ መንግሥቷን፣ ባህሏን፣ አኗኗሯን፣ ቋንቋዋን፣ በጥቅሉ እሴቶቿን በሙሉ እንድትጥል ቀን ከሌት ተሠራ። ይህ ሁሉ የሆነው በምእራባውያን ሴራ፣ ሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው እና ባለማወቅ በተታለሉ ብዙሀን ነበር። ደርግ ስልጣን የያዘው ንጉሰነገስቱ ባልበደሉት በደል በዳይ እንደሆኑ ተደርጎ ለሕዝብ ተዘርቶ ጠባቂ አልባ ሆነው በመቅረታቸው እንጂ በጦርነት አይደለም። ሚኒስትሮች ሳይቀር ራሳቸው ናቸው እጅ የሰጡት። በዚህም ደርግ ሕዝቡን እና ባለስልጣናትን አታሎ ስልጣኑን በእጁ ካስገባ በኋላ የኢትዮጵያ አሌኝታ የተባሉትን በሙሉ ረሸነ። የኢትዮጵያም ታሪክ ከሀ እንዲጀምር ተደረገ። 

American Peac Corps, evangelican missionaries፣ እና ተመሳሳይ በሆኑ ዘዴዎች ኢትዮጵያን ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ ማጥቃት የተጀመረው በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ነው። ለእድገት ይሆናል የተባለው ትምህርትም ለኢትዮጵያ ውድቀት ነው የሆነው። የወቅቱ ተማሪዎች ያነበቡትን ሳያላምጡ የሚውጡ ሆነው መንግሥት አልባ ሀገር እንድትኖረን አድርገው ራሳቸውም በለጋ እድሜያቸው ተቀጠፉ።

ከደርግ ቀጥሎ ህውሀት መንግሥትን ተቆጣጠረ። ህውሀትን የሚዘውሩት ሰዎች በከፊል ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም ከኢጣልያ እና እንግሊዝ ዘር ቅልቅል ያለባቸው ነበሩ። ከደርግ ቀጥሎ ኢሃዲግ ሳይሆን ህውሀት ነው የመራው። ሌሎቹ ስም ብቻ ነበሩ። ልክ እንግሊዝ በእጅ አዙር ትገዛ እንደነበረው ማለት ነው። ብዙ ሰው ግን የሚሳሳተው ህውሀትን ብሔር ተኮር ቢሆንም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ድርጅት በመቁጠር ነው። ህውሀት በዘር ለዚያውም በከፊል ካልሆነ በቀር በግብር ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት አልነበረምም አይደለምም። እድሜውን ሙሉ ሲሠራ የነበረው ለምእራባውያን ነው። ኢትዮጵያ ያላትን በሙሉ እንድታጣ አደረገ። ወታደሯን በተነ፤ ኤርትራን ካልተገነጠልሽ ብሎ በጫና ገነጠለ፤ ምጽዋንም አሰብንም ውሰጂልኝ አለ፤ የተሻሩትን የቅኝ ዘመን ግዛት ውሎች እየጠቀሰ መሬቷን ለሱዳን ሰጠ፤ ሀገሪቷን በዘር ከፋፍሎ ሕዝቡ ሁሉ አማራ ላይ እንዲነሳ አደረገ፤ የፕሮቴስታንት እምነት ሀገሩን እንዲያጥለቀልቀው በማድረግና ኦርቶዶክስ እንድትዳከም በማድረግ ኦርቶዶክስ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈጸመ፤ ጳጳስ፣ ተቃዋሚ፣ ዝነኛ የተባሉትን በሙሉ አሳደደ፣ ገደለ፤ ሕዝብን በተለይም አማራን ጨፈጨፈ፣ አፈናቀለ፤ የኢትዮጵያ ባህል በምእራባውያን ባህል እንዲዋጥ አደረገ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ አመት እና የቅኝ ግዛት ታሪክ አደረገ፤ ቅርስና ታሪክ እንዲወድም አደረገ፤ በአጭሩ የኢትዮጵያ እሴቶችን በሙሉ እየገዘገዘ፣ እየገዘገዘ ማጥፋትን ሥራዬ ብሎ ያዘው። 

ህውሀትም ሆነ ኤርትራ ሲደገፉ የነበረው በውጪ ሀይሎች ነው። ህውሀት ስልጣን ከያዘ በኋላም ምእራባውያን ቀኝ እጁ ነበሩ። የአማራ እልቂት፣ መፈናቀል፣ መጨቆን ለምእራባውያን ምንተዳቸውም አልነበረም። በተቃራኒው ጨቋኙን እና ገዳዩን ህውሀት ሲደግፉት ኖሩ። ምክንያቱም የአደዋ ቀጣይ ጦርነት ላይ ስለነበሩ ነው። ኢትዮጵያ ተበታትና ካልፈረሰች የአሜሪካ ጥቅም እንደማይከበር በፖሊሲ ጭምር ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ ነው የኖሩት። ይህን ደግሞ እንደቀድሞው በቀጥታ ጦር ልኮ በመውረር ለማሳካት የዘመኑ የፖለቲካ ሥርዐት የማይፈቅደው እንደሆነ ተረድተውታል። ፍላጎታቸውን ማሳኪያ ብቸኛ መንገድ ውስጥ ለውስጥ በማሴር፣ በማታለል፣ ትግልን በመጥለፍ፣ ትርክትን በመፍጠር፣ ሚዲያዎችን በመጠቀም ነው። ይህ ጦርነት ለብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን ግልጽ አልነበረም። አማራውም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንዲል የተሠራው በህውሀት ነው። የኢትዮጵያ ፓርቲ ነኝ ሲል የነበረው ኢህዴን ስሙን ቀይሮ ብአዲን ነኝ ብሎ እንዲመጣ ተደረገ። መአህድ ድራሹ እንዲጠፋ ተደርጎ ቅሪቱ መኢአድ ሆነ። አማራው ብቻውን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ሲያቀነቅን ሌሎቹ ግን ኢትዮጵያን የሚያስታውሷት የአማራውን ድጋፍ ሲፈልጉ ብቻ ነበር። አብዛኞቹ ብሔሮች ተታለው እጃቸውን በሀገራቸው ላይ አነሱ። የሀገራቸው ጥንካሬ አንድነቷ፣ ታሪኳ፣ ሀብቷ፣ ቅርሷ ወ.ዘ.ተ ሆኖ ሳለ ሁሉንም ረግመው በራሳቸው እጅ እንዲጠፋ አደረጉ። 

ይህ ሁሉ የሆነው ምእራባውያኑ በባሮን ፕሮቼስካ፣ Abisinia: The barrel of the Powder, በሚሉ ሰነዶች እና በአሜሪካ ፖሊሲ ውስጥ ኢትዮጵያን መከፋፈል እና ማፍረስ የሚለው በይፋ እየተሠራበት ነው። ፊት ለፊት የሚነገረንን እንኳን መተንተን አለመቻላችን የሚገርም ነው። 

ህውሀት ኢትዮጵያን እንዲገድል የተመደበ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያን ከሞላ ጎደል ገድሎ ካጠናቀቀ በኋላ ቀባሪ ያስፈልጋታል ብለው ምእራባውያኑ አምነዋል። ቀብሩም የሚፈጸመው በራሳቸው በኢትዮጵያውያን መሆን እንዳለበት አምነዋል። ለዚህም ብልጽግናን ተጠቀሙበት። ብልጽግና ቀብር አስፈጻሚ እንጂ ገዳይ ነው ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ የሞተች የመሰለችው ህውሀት በዘር፣ በሀይማኖት፣ በትርክት ብትንትኗን አውጥቶ፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ሸብቦ፣ አንዱን አጥቂ ሌላውን ተጠቂ አድርጎ የአንድነት መሠረቶቿን በሙሉ ሲንደው ነበር። ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቦርቡራ ተቦርቡራ ራሷን መጠበቅ የማትችልበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ የሚፈልገውን ጳጳስ ሾሞ ሲያስተዳድራት ነበር። ህውሀት ሥራውን ሁሉ የሠራው ቀስ በቀስ ቢሆንም ፍጥነቱ ግን ቀላል የሚባል አልነበረም። በአንድ ጊዜ ያላደረገበት ምክንያት ደግሞ እድሜው እንዳያጥር ነው። 

ብልጽግና ስልጣን ሲይዝ ስልጣን ሊይዝበት የሚችልበት ብቸኛ አቅም ሕዝበኝነት ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጣውን እና የሚፈልገውን ያውቃል። የተነጠቀውን አንድነት መመለስ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እጅግ ብዙ መሆኑን ብልጽግና ያውቃል። የዚያን ያህል ባይሆኑም እንኳን የበላይ ሆነው ቀጣይ ጨቋኝ መሆን የሚፈልጉ እንደኦሮሙማ ያሉ አስተሳሰቦችን የሚከተሉም እንዳሉ ያውቃል። ቻናል በቀየረ ቁጥር የሚናገረውንም እየቀየረ ብልጽግና የቀብር ሥነሥርዐት መፈጸሙን ተያያዘው። ስልጣኑን ግን ያጠናከረው ሕዝብን አታሎ ነበር። መታለል የማይሰለቸው ሕዝብ። 

ባለፉት 128 አመታት ኢትዮጵያውያን የዋህነቱን አብዝተንው ስንታለል ኖረናል። ጦርነት ሁልጊዜ ፊት ለፊት በግንባር የሚገጠም አይደለም። በመሬትም፣ በሰማይም፣ ከውጪም፣ ከጓዳም እያለ መልኩን የሚቀያይር ነው። ኢትዮጵያውያን ግን የዋሆች በመሆናችን ጦርነትን ፊት ለፊት እና በመሬት ብቻ ነው የምናስበው። ይህን ያስተዋሉ ጥቂቶችን ደግሞ አብረን እየረገምን፣ ስልጣን ፈላጊዎች እያልን፣ conspiracy theory እያልን፣ ጠባቦች ዘረኞች እያልን፣ ጠላቶቻችን ሰርቀው እኛ ወዳጆቻችንን ሌባ እያልን ያለጠባቂ ቆይተን ነበር። አሁን ግን ከ50 አመታት በኋላ የነቃን ይመስላል። 

ይህ የመጨረሻው የአደዋ ጦርነት ክፍልን ማሸነፍ የምንችለው በሚከተሉት መንገዶች ነው። 

1ኛ የዋህነቱን ስንቀንስ፤
2ኛ መታለሉን ስናቆም፤
3ኛ ድርድር የሚባል ነገርን አንቀበለውም ስንል፤
4ኛ ሁሉን ነገር በይፋ ሳይሆን በውስጥም ሥራ መሥራት ስንችል፤ 
5ኛ ልክ እንደአጼ ሚኒሊክ የአደዋ ድል ሁሉ ጠላቶቻችንን ማታለል ስንችል፤ 
6ኛ የስልጣን ሽኩቻን መግታት የሚያስችል መንገድ መከተል ስንችል፤
7ኛ ይሉኝታን ትተን ጨከን ብለን የጠላቶቻችንን መጠቀሚያዎች እግር በእግር እየተከታተልን ማጥፋት ከቀጠልን፤
8ኛ ከድል መልስ ከአደዋ ጦርነት በኋላ በተሠሩት ሴራዎች የፈረሱብንን ተቋማት፣ ያጣናቸውን እሴቶች በሙሉ መመለስ ቁጥር አንድ ሥራችን ሲሆን ነው።

ድርድር በየትኛውም ጦርነት አይቀሬ ነው በሚል የሚያላዝኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሄ ታሪክንም እውነታውንም መካድ ነው። የእጅ መስጠት ስምምነትን በሙሉ ድርድር እያሉ መጥራት አሳፋሪ ነው። ለምሳሌ፣ ህውሀትና ብልጽግና ያደረጉት የፕሪቶሪያ ድርድር ተብዬ አማራውን ቢጎዳውም ድርድር ነበር ለማለት ግን አይቻልም። ድርድር እኮ ሰጥቶ መቀበል ማለት ነው። መሸነፉ የተረጋገጠ አካል እጄን ልስጥ ሲል ድርድር ብሎ መጥራት የድርድርን ትርጉም ማዛባት ነው። ህውሀት ሊያበቃለት ሲል ነው ተሯሩጦ አማላጅ ልኮ እጅ የሰጠው። 

የ1ኛው የአለም ጦርነት፣ 2ኛው የአለም ጦርነት የመሳሰሉትንም እንይ። የቨርሴልስ ስምምነት የሚባለው አሸናፊዎቹ ተሸናፊዎቹ በግድ እንዲፈርሙ ያደረጉት ስምምነት እንጂ ድርድር አልነበረም። ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ ጃፓን በናጋሳኪ ላይ ከደረሰው የኒኩሌር ቦምብ ጥቃት በኋላ እጇን ሰጥታ ሳለ ከእጅ መስጠቱ በኋላ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ፈጽማለች። በስምምነቱም ጃፓን ያለአሜሪካ ፈቃድ ከተወሰነ ወታደር ቁጥር በላይ እንዳይኖራት፣ የመሳሪያዎቿ አይነቶች እንዲገደቡ ተስማምታ ነው የፈረመችው። ታዲያ በምትኩ ምን አግኝታ ነው ድርድር አደረገች ሊባል የሚችለው? 

ጦርነት በድርድር ሊፈታ የሚችለው ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው። 1ኛው ሁለቱ ወገኖች ያላቸው አቅም ተመጣጣኝ ሆኖ አሸናፊ ሲጠፋ እና 2ኛ ሁለቱ ወገኖች ያላቸው አለመግባባት ሊታረቅ የሚችል ሲሆን ነው። አሁን በአማራው ላይ የተከፈተው የህልውና ጥቃት ነው። ይሄ ደግሞ በምንም ሊታረቅ የማይችል አለመግባባት ነው። አማራው ህልውናውን ንግግር ውስጥ አስገባው ማለት አለቀለት ማለት ሲሆን ብልጽግና ደግሞ ኢትዮጵያን ሊቀብር የሚችለው አማራውን እና ሌሎቹን ደግሞ በተራቸው ማጥፋት ሲችል ነው። እነዚህ ሁለቱ ፍላጎቶች ሊጣጣሙ የሚችሉ አይደሉም። በአቅም ደረጃም ብናይ ብልጽግና የመሳሪያ፣ የገንዘብ፣ የሎጂስቲክስ፣ የሚዲያ የበላይነት ቢኖረውም ጦር ሜዳም ላይ ሆነ በዲፕሎማሲው ተበልጦ ነው ያለው። ንጹሀንን ከመጨፍጨፍ ባለፈ ፋኖን መቋቋም እንዳልቻለ በይፋ አምኗል። 

በተቃራኒው ድርድር ዳግም መታለያ ነው የሚሆነው። ድርድር የሚሰራው ተደራዳሪዎቹ ወገኖች በድርድሩ ላይ የሚስማሙትን ለመተግበር የጸኑ ሲሆኑ ብቻ ነው። ብልጽግና እና ህውሀትን የመሰሉ ድርጅቶች ደግሞ ድርድርን ጊዜ መግዣ፣ አስብቶ ማረጃ፣ አድፍጦ ማጥቂያ ነው የሚያደርጉት። ልክ እንደመቀሌው ጦርነት ምሽጋቸውን ነው የሚያጠናክሩበት፤ ለአደዋ ጦርነት ነው የሚዘጋጁበት። ስለሆነም ድርድር የሚባል ነገር እንደማይታሰብ ፋኖ በአንድ አቋም ውሳኔ ማሳለፍ አለበት።

ሌሎቹንም እርምጃዎች አንድ በአንድ ሊሠራባቸው ይገባል። ምእራባውያኑ ስልታቸውን ቀይረው መምጣታቸውም ስለማይቀር ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚቃጣበትን ግልጽና ህቡእ ሴራ መቋቋሚያ ስልቶችን በየጊዜው መቀየስ አለበት። 

ያን ጊዜ አደዋ ሙሉ ይሆናል። ያን ጊዜ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በውስጣዊ ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ያለችውንም አፍሪካ ማንቃት ይችላል። ያን ጊዜ አፍሪካ ከመበዝበዝ ወደመሰልጠን እንድትጓዝ ማድረግ ይቻላል። በጥቅሉ አለም አዲስ ርእዮተ አለም እንድታስተናግድ ማድረግ ይችላል። አማራ እና ኦርቶዶክስ የእስራኤልን ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያን ታላቅነት መመለስን ግባቸው አድርገው ሊሠሩ ይገባል። የማንንም ሳይከጅሉ የራሳቸው የነበሩትን በሙሉ የራሳቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል። 

የአደዋ ጦርነት የመጨረሻው ክፍል በድል እንደሚጠናቀቅ ተስፋ አለን።

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

Ethiopia 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. ከጅምሩ “ምኒሊካዊው” ነኝ ብለህ ራስህን አጋለጥክ። የዋህ አንሁን እያልክ ተንኮል ብጤ ዘራህ። ድሮም ችግሩ ያለው እንዳንተ ዓይነቱ ጋ ነው። “አማራ እና ኦርቶዶክስ የእስራኤልን ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያን ታላቅነት መመለስን ግባቸው አድርገው ሊሠሩ ይገባል። የማንንም ሳይከጅሉ የራሳቸው የነበሩትን በሙሉ የራሳቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል” ብለህ ደመደምከው? እንዲያው ትንሽ እንኳን አታፍርም? እንዳንተ ዓይነቱን፦ ትምክህተኛ ጠባብ ዘረኛ ነፍጠኛ ትእቢተኛ የሚሏችሁ አለምክንያት አይደለም። አማራን እያሰደብክ ነው፤ አለአቅምህ እየተንጠራራህ አማራን ለሚጠሉ ዱላ እያቀበልክ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here