spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeነፃ አስተያየትመነኩሴ ዓለምን ታፈቀረ ጭድ እሳት ዳር ከተከመረ!

መነኩሴ ዓለምን ታፈቀረ ጭድ እሳት ዳር ከተከመረ!

መነኩሴ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የቤተክርስትያን ታሪክ እንደሚያስተምረው በክርስትና ዓለም ምንኩስናን የጀመረው እንጦስ የተባለ መነኩሴ ነው፡፡ እንጦስ ምንኩስናን የጀመረው ዓለምን ንቆ ሐብቱን ጥርግ አርጎ ለድሀ መጽውቶና አካላዊ ስሜቱን ሙልጭ አርጎ አስወግዶ ገዳም ውስጥ በመግባት ነው፡፡ የእኔን እያት ጨምሮ የድሮዎች የኢትዮጵያ መነኩሴዎችም ይከተሉት የነበረው ይኸንኑ የምንኩስና ሥርዓት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ምንኩስና የሚታወቀው “መነኮሰ ሞተ!” በሚለው ጥልቅ አባባል ነው፡፡ የመነኮሰ ሰው መሞቱ የሚታወቀው ሰውን ከመለኮት ነጥለው ከሳጥናኤል ጉያ የሚከቱትን ስስትን፣ ስግብግብነትን፣ የፍህተ ወት ሥጋ ፍላጎትን፣ ርሃብን፣ ጥማትን፣ ቅናትን፣ ፍርሀትን፣ አድርባይነትን፣ ቅጥፈትን፣ ውሸትን፣ አጭበርባሪነትን ወዘተርፈ ካልታዩበት ብቻ ነው፡፡ መነኩሴ ለዚህ “መንኩሰ ሞተ” ለሚለው ብቃት የሚደርሰው ደሞ በወር መቶ ሺ ብር ደመወዝ እየተከፈለው ጳጳስ ወይም ፓትርያሪክ ሲሆን ሳይሆን አካሉን በርሃብና በፀሎት አድቅቆ ባህታዊ ወይም ብቸኛ ሆኖ ገዳም ውስጥ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ መነኩሴ ከገዳም መውጣት ያለበት አንድም መለኮት በህልሙም ሆነ በቁሙ ለሕዝብ መነገር ያለበት የምስራች ወይም ማስጠንቀቂያ ሲነግረው አለዚያም  ሕዝብን፣ አገርና ቤተከርስትያንን የሚበድልና የሚያጠፋ ክፉ ዘመን ሲመጣ ያንን ክፉ ኃይል በፅናት ለመቋቋም ነው፡፡ በሰላም ጊዜ በጾምና በፀሎት አካሉን አድቅቆም ሳጥናኤል ስለሚፈታተነው እንኳን ሰዎች እርቃናቸውን ጥለው በሚሄዱባቸው እንደ ኒው ዮርክ ታሉ ከተሞች ተንፈላሶ መኖር ሊገባው ገዳም ወፍ ድር ብላ ስትበር ወይም አውሬ ሲመጣበት እንኳ ወደ ጎን ወይም ቀና ብሎ ማየትም ክልክል ነው፡፡

ይህ የመኩስና ሥርዓት ይህ አድግ የሚባለው ሰይጣናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ እስከወደቀባት ድረስ ሲተገበር የነበረ ነው፡፡ እስከዚህ እርጉም ዘመን ድረስ የበቃ ሰው የሚመነኩሰው በጾምና በፀሎት ለዓመታት ተፈትኖ በመጨረሻም መቃብር ተቆፍሮ እስከ አንገቱ ድረስ አፈር ተመልሶበትና ተቀበሮ ቃለ መሐላ ከፈጠመ በኋላ ነበር፡፡ ሳጥናኤል ይህ አድግን ተላከውና አባ ገረመድህንን ፓትርያሪክ ካረገ ጊዜ ጀምሮ ግን ምንኩስና እንደ እንጦስ ሐብትን መጽውቶ ወደ ገዳም የሚገባበት ሳይሆን ከችጋር ወደ ባለሐብትነነት፣ ካድሬነትና ሌሎችም ዓለማዊ ስሜቶችን የማርኪያ ድልድይ ሆነና አረፈው፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ አባ በርገር ያለው ወሮበላ ሁሉ እየመነኮሰና እየቆመሰ ቀዳሽ ቄስ ነኝ፣ የነፍስ አባት ነኝ፣ ጳጳስ ነኝ፣ ፓትርያሪክ ነኝ ማለት እንደቀጠለ የምናየው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን አሁን ካለችበት ፈተና እጅግ የበለጡ ፈተናዎች በታሪኳ ደርሰውባታል፡፡ ያን ሁሉ ፈተና አልፋ ከሁለተ ሺህ ዘመናት በላይ ጸንታ የኖረችው  በመለኮት ፈቃድ፣ መነኮሰ ሞተን ይተገብሩ በነበሩ መነኩሳትና ባህታውያንና በጽኑ አማኝ ሕዝቧ መስዋእትነት ነው፡፡ ዛሬም የደረሰባትን ፈተና የምታልፈው እነዚህ ጠባቂዎቿ ምሰሶዎች በሥፍራው ሲገኙና ቀጥ በለው ሲቆሙ ነው፡፡ ከየትኛውም ዓለም በበለጠ መጽሐፍ ቅዱስን በግብር ያውሉት የነበሩት የቅድመ አያቶቻችን መለኮት ዛሬም እነዚያ ብፁአን ከተቀበሩበት ምድር ከኢትዮጵያ ጋር ነው፡፡ ሕዝቡም አገሩና ቤተክርስቲያኒቱ እንዳይጠፉ ከመቼም ጊዜ በበለጠ መስዋእትነት እየከፈለ ነው፡፡ ትልቁ ክፍተት ያለው መነኩሴ ነን እያሉ በቤተ ክርስትያኗ ተሰግስገው እንደ መዥገር ከተጣቁት ካህናትና አባቶች ነን ብለው በመንበሯ ላይ ዝርፍጥ ካሉት ጳጳሳትና ፓትሪያሪኮች ዘንድ ነው፡፡ 

በውስጧ የተሰገሰጉት መነኩሳትም ሆነ አባት ነን ብለው ተመበሯ የተጎለቱትን ጳጳሳትና ካህናት ሕዝብን ተሕዝብ ለሚያናክሱና ቤተከርስትያኗ ተሚያጠፉ ሳጥናኤል ለላካቸው ወሮ በላ ገዥዎች እንዲሰግዱ ያደረጋቸው ደሞ ዓለምን ሙዝዝ እስቲሉ መውደዳቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዓለምን ሙዝዝ እስቲል ያፈቀረ ላፈቀራት ዓለም ሲል የማይሰብራቸው አስርቱ ቃላት እንደማይኖሩ የታወቀ ነው፡፡ ከዓለም የራቀ ወይም ዓለምን የተጠየፈ ደሞ ከመለኮት በቀር የሚፈራው አንዳችም ኃይል እንደሌለ በእነ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል የታየ ነው፡፡ መነኩሳት ከመመንኮሳቸው በፊት በብዙ ፈተናዎች የሚመዘኑትም ለእንደዚህ ዓይነቱ ቀውጢ ዘመን ለማዘጋጀት ነው፡፡ የግራኝ ወረራ፣ የአድዋውንም ሆነ የአምስቱ ዘመንን ፈተና ቤተክርስትያኗ የተሻገረቸው እንደ ጧፍ በነደዱ የቤተክርስትያን አባቶችና ፅኑ አማኝ ሕዝብ ነው፡፡ 

ዓለም እንደሚታወቀው መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ እሴት ኢትዮጵያን በአለት ላይ የገነባ ፀጋ ነው፡፡ ይኸንን ፀጋ እየተመገቡ በሰላም ጊዜ በነፍስ አባትነት፣ በሽምግልና፣ በመምህርነትና በፈላስፋነት የሚያገለግሉ፤ ሰላምን የሚነሳ ሰይጣን የላከው ወራሪ ሲመጣም ጦር ሜዳ ሄደው መሳሪያ አንስተው እስከ መዋጋት የሚደርሱ የሃይማኖት አባቶች ቁጥር እልቆ መሳፍርት እንዳልነበረው ታሪክ የመዘገበው ነው፡፡

እነዚህ የኢትዮጵያ መነኮሳት ዓለም ስትበቃቸው የሚመንኩሱት፣ የምንኩስና ኑሯቸው የሚመሩት፣ ለእምነታቸው፣ ለእውነትና ለፍትህ ሲሉ የሚሰውትም በመጻሕፍተ መነኩሳት ህግጋት በመመራት ነው፡፡ 

መጻሕፍተ መነኮሳት የመነኮሳትን ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ ታሪክ፣ ተጋድሎና ተመከራም የሚያገኙትን ትሩፋት የሚያስተምር ተአዋልድ መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ የአዋልድ መጻሕፍት ትርጉም የመጻሕፍት ልጆች ማለት ሲሆን ወላጆችም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፡፡ 

ተብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን የተወለዱት መጻሕፍተ መነኮሳትም ሶስት ናቸው፡፡

ልጅ አንድ፡- ማር ይስሐቅ ስለመነኮሳት ቃል ኪዳን፣ ግብር፣ጾምና ተጋድሎ ያስትምራል፡፡

ልጅ ሁለት፡- ፊልክስዩስ ስለ መነኮሳት የገዳም ታሪክና ተጋድሎ ያስረዳል

ልጅ ሶስት፡- አረጋዊ መንፈሳዊ መነኮሳት መከራን ተቀብለው ስለሚያገኙት ፀጋ ወይ ትሩፋት ያስተምራል፡፡

አረጋዊ መንፈሳዊ ሥርዓተ ብሕትውናን ጳውሎስ፤ ሥርዓተ ምንኩስናን ደሞ እንጦስ ሐብቱን ሁሉ ለድሀ ሰጥቶ ገዳም በመግባት እንደ ጀመረው ያስተምራል፡፡ [1]    ይኸን በመከተል ኢትዮጵያውያን ዓለም ስትበቃቸው መንኩሰው ወደ ገዳማት እየተመሙ ለሰው ልጅ ባቻ ሳይሆን ለእንሰሳትና ለሳሩ ቅጠሉ ሁሉ ሲጸልዩ ኖረዋል፡፡ ፊልክስዩን እንደዚሁ “የዋህ ሁን ለክፉ ግን የዋህ አትሁን” [2] ሲል ያስተምራል፡፡ ይኸንን መልዕክት ተከትለው መነኮሳት በእንቁላል ቀቃይ ባንዳዎች እየተመራ ሕዝብ የፈጀውን ፋሽሽት መሳሪያ ታጥቀው እንደተዋጉ ይታወቃል፡፡ የበቁ መነኮሳት  በደብረ ሊባኖስና በሌሎች ገዳማትም እንደተረሸኑ አፍ ቢኖራቸው ስጋቸውን የበሉት ሜዳዎችና ተራሮች እንደዚሁም ደማቸውን የጠጡት ወንዞች እንደሚመስክሩ ይታመናል፡፡ 

መነኮሳት ዓለምን ንቀው እንዴት መኖር እንዳለባቸው ማር ይስሐቅ ሲያስተምርም “ለሰውነትህ እረፍትን ኅድዓትን ታገኝ ዘንድ ዘወትር መጽሐፍትን መመልከት ውደድ፤ ከንዑሳን ሕጣውእ ተከልከል” ይላል፡፡ ንዑሳን ሕጣውእንም “ማየት፣ መስማት፣ ያለመጠን መብላትና መጠጣት ናቸው” ይላል፡፡[3]  ማር ይስሐቅ ማስተማሩን ሲቀጥልም “የእንጨት ብዛት እሳቱን እንደሚያበዛው የምግብ ብዛትም ዝሙትን ያበዛል፡፡ በልቼ ጠጥቼ፤ አይቼ ሰምቼ፣ ንጽሕናየን ጠብቄ ከሴት ርቄ መኖር ይቻላል አትበል ይላል፡፡ [4]ማር ይስሐቅ መነኮሳትን ስለገንዘብ ማሳደድ ሲያስጠነቅቅም “ድሀ ትሆን ዘንድ ውደድ፣ ተርታ ልብስ መልበስን ውደድ ይላል፡፡ [5]

እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት መነኮሳትን መንፈሳዊ ሕግጋት በመከተል እህት የሚባሉት እንደ ኮፕቲክ ያሉ ቤተክርትያናት ለጳጳሳትም ሆነ ለሌሎች መነኩሳት ደመወዝ አይከፍሉም፤ ለእለት ጉርሳቸው በቀር መነኩሳት ገንዘብም አይጠይቁም፡፡ በቤተክርስትያን አገልግሎቶች ረገድም መነኩሳት በጎደለ ይሞላሉ እንጅ በቋሚነት ቄስ ሆነው ደሞዝ እየተከፈላቸው የቅዳሴ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ እኛም ስናድግ የመነኩሴ ቀዳሽ ወይም ደብር አለቃ አይተን አናውቅም፡፡ ከእህት ቤተክርስትያናት በተለዬ  መንገድ ከለማኝ አስራትና በበሽታ ከሚሰቃይ ምእመናን ስለት እየተሰበሰበ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የወር ደሞዝ የሚከፈላቸው የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ጳጳሳትና ፓትሪያሪክ ናቸው፡፡ ጵጵስናና ፓትርያሪክነት ደሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ እሴዎች ሳይሆኑ የተዋህዶ ቤተክርስትያንን በአለት ላይ የመሰረቱቱን ሊቃውንት እጨጌዎችን ያጠፉ  መጤ የግሪክ ቅርሶች ናቸው፡፡ እነዚህ በመጤ ጵጵስናና ፓትቲያሪክ ማእረግ ካባቸውን የደረቡና እንደ አክሊል ቆባቸውን የደፉ መነኩሴዎች  ዓለምን ሙዝዝ እስተሚሉ ከወደዱ ደሞ ይህች ከንቱ ዓለም በነዳቻቸው መንገድ ሁሉ እንደሚነጉዱና ስገዱልኛ ላላቸው የሰይጣን መልእክተኛ ገዥ ወይም ጣኦት ሁሉ እንደሚያጎበድዱ በቅዱሱ መጽሐፍም ሆነ በልጆቹ በአዋልእድ መጻሕፍት የተመዘገበ ነው፡፡  

ስለዚህ ሕዝብ ሆይ! ዓለምን ከንፈሩ እስቲወድቅ የወደደ መነኩሴም ሆነ ሌላ ካህን ቤተክርስትያንን ያድናል ብሎ መጠበቅ የበሬ ፍሬ ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ መሆን ነው፡፡ ዓለምን ያፈቀረ መነኩሴና እሳት ዳር የተከመረ ጭድ አንድ ነው፡፡ ዓለምን ያፈቀረ መነኩሴ ዓለምን ባዬና በተጠጋ ቁጥር  የሥጋም ሆነ የመንፈስ አምሮት ጭርር አርጎ የሚያቃጥለው ከእሳት ዳር የተከመረ ጪድም ነፋስ ሽው ባለ ቁጥር ጠሽ ጠሽ አርጎ እሳት የሚያነደው ብናኝ ነው፡፡ መነኩሴን ከዓለም የመለየትም ሆነ ጭድን ከእሳት የማራቁ ኃላፊነትም በእግዚአብሔር የሚያምን የሕዝብ ነው፡፡ እንደሚታዬው ጳጳስ ወይም ፓትርያሪክ ነኝ እያለ ካባ የደረበው ሁሉ እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ለእመነቱ፣ ለቤተክርስትያኑ፣ ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለሕዝብና ለአገር ለመሰዋት የተዘጋጀ ሳይሆን በዓለም ፍቅር ተጠልፎ እንደ አባ ገረ መድህንና ብዙዎቻችን እንደ ስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ ውፍረት፣ የልብ በሽታ፤ ነቀርሳና ሌሎችም በሽታዎች ሲው ብሎ በሁለተኛው ዓለም መቃጠል ነው፡፡

እሳት ጭድን የሚጨብጠው በሙቀት አማሎ ነው፡፡ ዓለም የመነኩሴን ልብና ፍቅር የምትገዛው ወርቅ፣ ገንዘብና ምቹ አልጋ እያሳየች ነው፡፡ ቤተክርስትያኗን ከመጥፋት የማዳን አንደኛው የትግል ዘርፍ መነኩሴን ከዓለም ፍቅር ማላቀቅ ነው፡፡ መነኩሴን ከዓለም ፍቅር የማላቀቁ ዘዴም ቅዱሱ መጽሕፍና መጻሕፍተ መነኮሳት በሚያዝዙትን መሰረት መነኩሳትን ተወርቅና፣ ተገንዘብና ምቹ አልጋ አርቆ በብዙ ችግሮች መፈተን ነው፡፡ ፈታናውን አልፎ በእምነቱ የጸና በምንኩስናው እንዲቀጥል ያልጸና ቆቡን ታጥቦ እንደሚሰጣ ልብስ ተአጥር ሰቅሎ ተቤተክርስትያኗ እንዲርቅ ማድረግ ነው፡፡  አመሰግናለሁ፡፡

ዋቢ፡-መጻሕፍተ መነኮሳት 1928 ዓ.ም ብርሃንና ሰላም እትም

  1. አረጋዊ መንፈሳዊ፡ መቅድም ገጽ 3
  2.  2. ፊልክስዩስ ገጽ 252-253 
  3. ማር ይስሐቅ ገጽ 10 
  4. ማር ይስሐቅ ገጽ 57
  5. ማር ይስሐቅ ገጽ 14

ይቆይን! 

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here