spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeመጣጥፍ‘አንቱ በእናት’  (ሓዳስ ኤርትራ)

‘አንቱ በእናት’  (ሓዳስ ኤርትራ)

ሓዳስ ኤርትራ

ይኼ ጽሑፍ ‘አንቱ በእናት’ በአሥመራ የዛሬ ዓመት ስትመረቅ የነበረው መንፈስ ውጤት ነው። ያኔ ከደራሲው አንዴም  ሁለቴም ተገናኝተን ስናወራ፡ ሰዎች መጽሓፍትን አንብበው ሲያበቁ ሂስ ስለማይጽፉ፡ የሚፈለገው ውጤት አይገኝም የሚል  መንፈስ ያዘለ ሀሳብ ስለወረወረልኝ፡ ግዴለም እኔ እሞክራለሁ ብዬው ነበር። ይኼው ጊዜው ነጐደ። ከጀመርኩት ብዙ ጊዜ  ቢሆነውም፡ ዛሬ ነገ ስል አቈየሁት። ጊዜው ደረሰና ቃሌን ለማክበር ይኸው ክፍል አንድን በማስቀደም ላንባቢዎች  እያቀረብኩት ነው።  

መልካም ንባብ!  

ክፍል አንድ – ‘አንቱ በእናት’በአሥመራ  
“እንኳን እግዚአብሄር አተረፋችሁ!”  

ሰረበ እስቲፋኖስ – አሥመራ  

እስከ አፍጢሙ ድረስ ሞልቷል። የሞላው ኩሬም፡ ወንዝም፡ ጅረትም፡ ባሕርም አይደለም። አዳራሽ ነው። ሰዉ ፈሳሽ ሆኖ  ፈሶ ደጃፍ ድረስ ሞልቷል። አስቀድሞ የመጣውም የዘገየውም፡ መቀመጫ ፍለጋ ዓይኑን ያንከራትታል። ተስፋ የለም- ሁሉም  ተይዟል። ታዳሚዎቹ አዳራሹ ውስጥ ጥግጥጉን ግድግዳና ጠረጴዛዎችን ተደግፈው በመቆም ዝግጅቱን በጥሞና  ይከታተላሉ። 

ዕለቱ ዓርብ 03/03/2023 ነበር። የግብዣ ወረቀቱ፡ መርኃ ግብሩ ከሰዓት በኋላ አስራ አንድ ተኩል ላይ እንደሚጀመር  ያሳያል። ቦታው ደግሞ አሥመራ እምብርት ላይ በሚገኘው እምባሶይራ ሆቴል ነው። 

ለዚያ ፍሰት ዋነኛ ምክንያት የሆነው፡ ከወደ አዲስ አበባ የመጣ እንግዳም ቤተኛም የሆነ ሰው ነው። ይህን ሰው ባንድ ወቅት  ባላሰበበት መንገድ ህይወት እያንከባለለች ወደ ኤርትራ አምጥታው ነበር፤ ያቺ ሁሉንም እንደፈለገች በፈለገችው መንገድ  የምትለዋውጥ ህይወት። አምጥታም ምን ያላደረገችው ነገር አለ! መጀመርያ ወታደር ሆኖ ወደዚህ እንዲኮበልል አደረገችው።  ከወታደርነትም የከባድ መሣርያ አስተኳሽነትን መረጠችለት። ደግሞም ወሰድ አደረገችና ዙፋን ለምትባል የትግራይ ሴት  አፍቃሪም ባልም እንዲሆን ፈረደች። አስቀድማ ዝናሽ ከምትባል የወለጋ ልጅና የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር  የመጀመሪያውን የፍቅር ጣዕም እንዲቀምስ አድርጋው ነበር። እስከዚህ ድረስ ዕጣ ፈንታው ስሟ ‘ዘ’ በሚለው የፊደል  ቤተሰብ ከሚጀምር ሴት ጋር የተጣበቀ አስመስላው ነበር። ሲሰለቻት ደግሞ አፍዓበት ወስዳ በጥይት እንዲቆላ ፈረደችበትና  ምርኮኛ አደረገችው። ቀጥላም የምርኮኝነትና የትምህርት ዘመኑን እስኪጨርስ ጠብቃ፡ የኤርትራ ነፃነት ታጋይ እንድትሆን  አምሮኛል ብላ አብኩታ፡ ጋግራ ተጋዳላይ አደረገችው። ከዛም ምን ዓይነት ታጋይ ይሁን ብላ አሰበችበትና የፖለቲካና  የአካደሚ አስተማሪ እንዲሆን ወሰነችበት። ብቸኝነቱ አሳዝኗት እንደሁ፡ ምን አድርጌ ብጠፈጥፈው ይሻላል ብላ አሰላሰለችና  ለሶስተኛ ጊዜ አፍቃሪም ተፈቃሪም አድርጋው ቁጭ! ህይወት እንዳማራት ስለሆነች፡ ፈልጋ አፈላልጋ የሷ

ሞክሼ ከሆነች  ታጋይ ጋር ነው ያቆራኘችው – ከህይወት ተስፋይ ጋር። እናም ‘ዘ’ በሚል የሚጀምረው የሴት ስም፡ ዕጣ ፈንታው  እንዳልነበረ ዕቅጩን ነገረችው።  

ባንድ ወቅት፡ ሁለቱም የፍቅር አጋሮች የለየላቸው  
ባላንጣዎች ነበሩ – እሱ መቃብሯን ሲቆፍርላት  
እሷም ሞቱን ትመኝለት ነበር። የህይወት ሚስጢር  
የማይደረስበት ስለሆነ ግን በስተመጨረሻ  
የድራማው ትዕይንት ከመቼው ተቀይሮ አንዱ  
የሌላው ተገን፡ ጋሻ መከታ ሆነው እንዲገኙ  
ወሰነች። በውሳኔዋም ጸናች። እናም አሽታ አሽታ  
ሁለቱንም የአራት ልጆች ወላጆች አድርጋቸዋለች።  
ኧረ ጭራሽ አያቶች ሆነውም አርፈውታል። አንዱ  
ያንዱን ህይወት ለመቅጠፍ የነበራቸው ሩጫ  
መለኪያ አልነበረውም። ግን የህይወት አክሮባት  
አይታወቅምና አገለባብጣ ባንጻሩ ተፋቅረው አራት  
ህይወቶችን ወደ ሰው ዝርያ እንዲጨምሩ ፍርዷን  
አስተላልፋለች። የተጨመሩትም እየጨመሩ ነው!
እንግዳው ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደር በመሆን
ባስተኳሽነት የኤርትራ የነፃነት ታጋዮችን ገድሏል፡  አስገድሏልም። ድሮ የሰውን ህይወት የሚቀጥፍ አረር ኤርትራውያኑ ላይ ያርከፈክፍባቸው እንዳልነበር አሁን ግን ህይወት  የሚያለመልም ትልቅ ስጦታ ሊያበረክትላቸው ነው ሲበር ከአዲስ አበባ ብቅ ያለው። መምጣቱን ልዩ የሚያደርገውና ደስ  የሚለው ነገር ደግሞ እንግዳው ሌላ እንግዳ ይዞ ብቅ ማለቱ ነው። የእንግዳዪቱ የጥምቀት ስም ‘አንቱ በእናት’ ይባላል። 

የተወለደችበት ዓመት 2013 (እ.ኢ.አ) ሲሆን ቦታውም አዲስ አበባ ነበር። የአዋላጅዋ ስም ጆቴ (ማሞ አፈታ) ሲሆን ክብደቷ  370 ገጽ ይሆናል። አሁን ግን እንድትጸነስ ምክንያት ወደሆነውና ዘሯ ወደተዘራበት የትውልድ ቀዬዋ መጥታለች። ልክ እንደ  አዲስ አበባው እዚህም ‘Happy birthday’ ሊዘፈንላት ነው። የልደት በዓሏን ለማክበር በተዘጋጀው አዳራሽ ውስጥ በክብር  

ቦታዋ ተሰይማለች። የመተዋወቂያው ጊዜ ደርሶ ሁሉም ተጋባዥ ቤተሰብ እንደ ህጻንነቷ ‘ለኔ፡ ለኔ’ በማለት እየተቀባበለና  እሽሩሩ እያለ እጉያው እየሸጎጣት ነው። እሷም ቤተሰቦቿን በማግኘቷ ፈንድቃለች፡ ፈንጥዛለች። ራሱ ፍንድቅድቅ  ፍንጥዝጥዝ ሆናለች! ገና ከአዲስ አበባ ስትነሳ፡ ጆቴ አሥመራ ድረስ ወስዶ ከቤተሰቦቿ ሊያስተዋውቃት እንደሆነ ሲነግራት  ያን ያክል ቤተሰብ እንደነበራት ግንዛቤ ነበራት ማለት ይከብዳል። የትውልድ ቀኗ ምሽት ላይ ያየችው የፈሰሰው ቤተሰብ ግን  አንደበቷን አስሮ ዝም እንዳሰኛት መገመት ይቻላል።  

ህጻኗን ከቤተሰቦቿ ለማስተዋወቅ የተጠራው መርሀ ግብር በዝክረ-ሰማዕታት ከተጀመረ በኋላ፡ የመድረኩ መሪ (ኤፍሬም  ሃብተጽዮን) አዳራሹ ከዚያ ምሽት በፊት አንግሊዘኛን ጨምሮ የተለያዩ በኤርትራ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት የተመረቁበት  እንደሆነ አስታውሶ፡ በዚያ ምሽት ደግሞ በተራው በአማርኛ የተጻፈች መጽሓፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያስመርቅ ስለሆነ የተለየ  ክስተት እንደሚያደርገው ገለጸ። የኤርትራ አብዮት (ህዝባዊ ግንባር) ለምርኮኞች ያሳየው የሰባዊነት አያያዝ የመርሆው አካል  እንደነበረና በዛው እምነት መሠረት ተማርከው የነበሩ ሰዎች ‘ንዝገበረልካ ወይ ግበረሉ ወይ ንገረሉ’ (ለባለ ውለታህ፡  አንድም ውለታውን መልስለት፡ አሊያም ንገርለት’) በሚል ግንዛቤ ውለታቸውን እንደፈጸሙና ማሞም አንዱን ብቻ ሳይሆን  ሁለቱንም አከናውኗቸዋል ይልና “ታግሎለታልም ያይን ምስክርነቱን የያዘው  መጽሓፉን አበርክቶልናልም” ብሎ ለጸሓፊው ሥራ እውቅና ሰጥቶ ነበር። ቀጥሎ  መጽሓፏን አስመልከተው ሶስት ሰዎች ሀሳባቸውን እንደሚያቀርቡ ካስተዋወቀ  በኋላ፡ መድረኩን ለአቅራቢዎቹ ለቀቀ።  የመጀመሪያው አቅራቢ (ሚካኤል ፀጋይ) መድረኩን ከተረከበ በኋላ፡ የሆነ  መጽሓፍ በይዘቱና በቅርጹ እንደሚገመገም አስታውሶ፡ ‘አንቱ በእናት’ን ያየበት  መንገድ ደግሞ በዛው መልኩ ነበር። ኪነ-ጥበባዊ ሚካኤል የመጽሓፏ አርእስት  የይዘቷ መዳረሻ ምን እንደሆነ ፍንጭ በማይሰጥ መንገድ ስለቀረበ (ፍንጭ ከሰጠ  የንባብ አምሮት ስለሚቀንስ)፡ ጆቴ የወሰደው ምርጫ በአወንታ እንደሚገመገም  አከለበት። ቀጥሎም፡ “የአንድ ታጋይ የግል ታሪክ ካንድ ህዝብ ታሪክ ጋር  ሚዛኑን በጠበቀና በተጓዳኝ በሚታመን መልክ ከቀረበ፡ አስተማሪና አዝናኝ  ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ ወይ ለጋራ ታሪክ ማጣቀሻ ሊሆን እንደሚችል ያሳየች  መጽሓፍ” እንደሆነችም አስገነዘበ። 

በማስከተልም እየተጻፈ ካለው የጋራ ታሪክ እያንዳንዱ ባለ ታሪክ ግለሰብ ታሪኩን በተጓዳኝ ጽፎ ወይንም አስጽፎ ቢሆን ኖሮ የሚያሰኝ የተቀደሰ ቅናት ታሳድራለች ይልና አያይዞም የመጽሓፏ ይዘት ከዚህ ቀደም ስለ ኤርትራ ህዝብ  ያልተጻፈ ታሪክ እንደሆነ ሲገልጽ ታሪኩ “የኤርትራ ታጋዮች አስተምረውና  በተግባር አርአያ ሆነው እነዛን እሳት ይዘው በመምጣት ጠላት የነበሩትን [ሰዎች] ወደ ጓዶችና ታጋዮች የመቀየር ታሪክ ነው”  ብሏል። ጆቴ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ የሰዎች አመለካከቶች፡ ከነበሩባቸው ተጨባጭ እውነታዎች አንጻር እያወዳደረ  ስላቀረባቸው የሚደነቅ እንደሆነም አክሏል። እንዲሁም ‘አንቱ በእናት’ ለኤርትራ ህዝብ፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ፡ ለኤርትራ  ታጋዮችና ለኢትዮጵያ ወታደሮች የሚገባቸውን ክብር ስለሰጠች የመጽሓፏ ጥሩ ጎን እንደሆነ አብራርቷል። በተጨማሪ  መጽሓፏ ፍቅርና ፍትሃዊ ዓላማ፡ ቅኝ ግዛት የፈጠረውን የዘር ፖለቲካ፡ ጥላቻንና ቅራኔን ሲያሸንፉ አሳይታለች ብሏል።  መጽሓፏ ለኤርትራ ህዝብ ትግል እና ታጋይ ህዝቧን የሚገባቸውን ክብርም ሰጥታለች ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ለዚህም  ማስረጃው በጆቴ ምስክርነት አማካኝነት ባሁኑ ወቅት ስለ ኤርትራ ታሪክ በማሳነስና በማንኳሰስ እየተጻፉ ላሉት መጽሓፍት  ምላሽ የሚሆን ሀቀኛ ታሪክ የያዘች መጽሓፍ በመሆን ኤርትራ ውስጥ የነበረው የምርኮኞች አያያዝ ለኢትዮጵያውያን  አንባቢዎች ሀቀኛ ምስል ለማቅረብ የቻለች መጽሓፍ ናት ሲልም መስክሯል። 

የግለሰቦች አስተዋጽኦ የማይናቅ ቢሆንም፡ መጽሓፏ፡ ጆቴ ተሰማርቶበት የነበረውን የመምህርነት፡ የትርጉም ሥራና ‘የንቃ’ መጽሔት አዘጋጅነትን የመሳሰሉ ነገሮች የብቻው በሚመስል መንገድ ስላቀረበች፡ ያን በመርህ ደረጃ ለጋራ ሥራ ትልቅ ቦታ  ይሰጠው የነበረውን የቡድን አሠራርን በሚገባ ያንጸባረቀችው ስለማትመስል ቅር እንደሚያሰኝም አልሸሸገም ሚካኤል።  ሌላው ሚካኤል እንደ ድክመት የገለጸው የመጽሓፏ ገጽታ፡ ለጆቴ ከገላዬ በተጨማሪ ሌሎች ሴቶች ፍቅራቸውን ሲገልጹለት  የሚታዩበት ክፍል ነው። በዚህም አንባቢ፡ ሴት ታጋዮች ለፍቅር ብቻ የሚንሰፈሰፉ ሰዎች አድርጎ ሊቀርጻቸው እንደሚችልና  ላሳዩት ተጋድሎ፡ መስዋዕትነት (እስከ ያለ ልጅ መቅረት) የመሳሰሉ እውነታዎች ጭምር ቦታ ቢሰጠው ኖሮ ያማረ ይሆን  ነበር ሲል ስሜቱን አጋርቷል። በተጨማሪም፡ መጽሓፏ የሚበዙት ክስተቶች የተፈጸሙበትን ዕለትና ዓመተ ምህረት  ስለማትገልጽ፡ ለዋቢነት መስጠት የነበረባትን ጥቅም አሳንሶታል ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል።  

ጆቴ ስለተከተለው የአጻጻፍ ቅርጽ ሲገልጽ፡ ‘አንቱ በእናት’ በአጻጻፍ መልክ ያለማጋነን ከ’ኦሮማይ’ (በዓሉ ግርማ)፡ ‘የኑረነቢ  ማህደር’ (ተስፋዬ ገብረአብ) እና ‘ሰመመን’ እንዲሁም ‘ግርዶሽ’ (ሲሳይ ንጉሡ) የምትወዳደር ሆና እንዳገኛትና ጆቴ  የተጠቀመበት የሶስተኛ አካል ተራኪ (third person narrator)፡ እሱ ስላልነበረበት ቦታና ፍጻሜ እንዲተርክ ስላስቻለው፡  ጥሩ ምርጫ እንደነበረም ገልጿል። ሌላው ተመስጦ የፈጠረለት ደግሞ ጆቴ ልክ እንደነ ማክሲም ጎርኪ የመሳሰሉ ጸሓፊዎች  የተገኙ ክስተቶችን በመውሰድ በተጓዳኝ ሌላ ሀሳብ ለማስተላለፍ በመቻሉ አወንታዊ ጎኗ እንደሆነ መስክሯል። አያይዞም  የምዕራፎቹ የገጽ ብዛት አለመመጣጠን ከድክመቷ ውስጥ እንደነበርም አብራርቷል። በስተመጨረሻም፡ ጆቴ ግለ-ታሪኩን  ለመተረክ የልብወለድ ነገሮች እዚህም እዚያም ማካተቱ እንደ ምርጫ መወሰድ የሚቻል ቢሆንም፡ ኤርትራውያን የታሪክ  መጽሓፍ በመጻፍ በኩል የሚቀረን ነገር ስላለ፡ ሀቀኛ ታሪኮችን ልብወለድ ቀመስ ሳናደርግ ብንጽፋቸው የተሻለ አማራጭ  ይሆናል በማለት ስሜቱን በመግለጽ ደመደመ።  

ቀጥሎ መድረኩን የተረከበው ስነ-ጥበባዊ መለስ ንጉሠ ነበር። መለስ መጽሓፏን ካነበባት በኋላ ጆቴና ገላዬ፡ መጀመሪያ ሰው  ሆነው ከቤታቸው ወጥተው ኋላ ላይ ግን ታሪክ ሆነው ወደ ቤታቸው የተመለሱ ሰዎች ናቸው የሚያሰኝ ስሜት  እንደፈጠረበት ገልጾ፡ ያ ትልቅ የሆነው የነሱ ታሪክ በመጽሓፍ መልክ እንደሰነዱት ያስታውስና “መጽሓፉ ሐወልት ነው።  እናም ዛሬ ይህንን ሐወልት እያስመረቅን እንገኛለን። ለነዚህ ጥንዶች ይሄ ቀን በርግጥም ትንሳኤ ነው” ሲል ተመስጦውን  አጋርቷል። ትንሳኤ የሚለው ቃል አንዲት ‘ትንሳኤ’ በመባል የተሰየመች ግጥም (የገጣሚውን ስም ለማስታወስ አልቻለም)  እንደምታስታውሰው ገልጾ ግጥሟን ለነጆቴ ክብር ሲል እንደሚከተለው አነበነባት። 

ያቺ ወረተኛዋ ዓለም ወረቷን ጨርሳ  
ለኔ ያላት እምነት ቢጎድልም ቢሳሳ  
ሰገነት ስፍራዬን ለሌላ ብትሰጠው  
አሽቀንጥራ ጥላኝ ከአፈር ከትብያው  
ይህ ምንም ነው የተራ ነገር ነው  
ድሮም ትንሳኤኮ ከሞት በኋላ ነው  

ቀጥሎም መለስ ‘አንቱ በእናት’ ለየት ያለች የታሪክ መጽሓፍ እንደሆነች ገልጾ ማንኛውም መጽሓፍ ትረካ ይዞ ወደ ኣንባቢ  የሚቀርብ ቢሆንም ሁሉም ትረካ መጽሓፍ ሊሆን ስለማይችል አተራረኩ የተለየ መሆን እንደሚያስፈልገው አብራራ። ‘አንቱ  በእናት’ን ልዩ የሚያደርጋት በኤርትራና ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአንዲት ሴት ታጋይና ሌላ ምርኮኛ የነበረ ታጋይ የታዬ  የፍቅር ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ዋነኛው መልእክቱ ጦርነት የሚተወው ጠባሳና የምርኮኞች አያያዝ ምን ይመስል እንደነበረ  የዓይን ምስክርነት የምትሰጥ መሆኗ እንደሆነ ገለጸ። ታሪኩን ከባድ የሚያደርገውም ነገር ቢኖር ያ ከቅኝ ገዢዎች ግፍ ጋር  ተያይዞ የሚመጣው የዘር ፖለቲካ በኤርትራውያን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ስሜት በቦታው እያለ፡ እነዚህ ባላንጣ የነበሩ  ጥንዶች የመሠረቱት ትዳር ጥያቄ የሚጭር ሆኖ መገኘቱ እንደነበረ አስረድቷል። በግንባሩ (ህዝባዊ ግንባር) የነበረው የንቃተ  ህሊና ደረጃ በሁሉም ታጋዮች ውስጥ እኩል እንዲንጸባረቅ መጠበቅ ተግባራዊ ስላልሆነ በጆቴና ገላዬ የነበረውን ግንኙነት  በአሉታ እንዲታይ አድርጎታል ብሏል። እነዚህ በትግል ውስጥ ሆኖው ሌላ ተጋድሎ የፈጠሩ ጥንዶች፡ ተመኩሮዋቸው  ላለፉበት ህይወት የተለየ እንዳደረገውም አክሏል። ጆቴም ትግሉንና ትንግርቶቹን በፍቅር እያጣጣምን እንድናነበው አድርጓል  ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዛም መለስ የመጽሓፏን ይዘት ባጭሩ በመግለጽ የፈጠረችለትን ተመስጦ በየመሀሉ እያስገባ  ንግግሩን ቀጠለ። የሁለቱ ጥንዶች የህይወት ጉዞ፡ የፔንዱራ ብልቃጥ ከሚባለው የግሪክ ተረት ጋር እንደሚመሳሰል  አስታውሶ በተረቱ መሠረት መከራ ሲያልቅ ተስፋ ይለመልምና እፎይታና ፍቅር ይነግሳሉ። ስለዚህም እነዚህ ጥንዶች ባገኙት  የፖለቲካ ንቃት (ትምህርት) የመጣውን የኤርትራና የኢትዮጵያ ተስፋ ሊወክሉ ይችላሉ አለ። ከዛም ባለፈ የአፍሪካ ሰላምና  ፍቅርም ሊወክሉ ይችላሉ ሲልም ግምቱን ሰጥቷል። የሰው ልጅ የተደረገለትን ይረሳል። እንደነ በዛብህ ጴጥሮስ የመሳሰሉ  የተደረገላቸውን ረስተው ዳግመኛ ስህተት የፈጸሙ እንዳሉ ሁሉ፡ ባንጻሩ ጆቴም እንደ ሌሎቹ ቅን ሰዎች በግንባሩ  የተደረገለትን መልካም እንክብካቤ በሀቀኛ መልኩ አቅርቦታል ሲል አስተያየቱን ሰጠ።  

ቀጥሎ ተመስጦውን ያቀረበ ኪነ-ጥበባዊ ምስጉን ዘርአይ (ወዲ ፈራዳይ) ነበር። ምስጉን፡ ጆቴ በመጽሓፏ መግቢያ ስለ  ኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን አመለካከት ያሰፈረውን ሀሳብ እንደመንደርያ በመጠቀም ነበር ሀሳቡን የጀመረው። በመቀጠልም  ኤርትራውያን በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መጽሓፏን ካነበቡዋት በኋላ የደራሲው ጽሑፍ ገማጋሚዎቹ በዕለቱ ካቀረቡት  ጭማቂ ባሻገር ሰፋ ያሉ እመርታዎችን የያዘ እንደሆነ መገምገማቸው አይቀርም ካለ በኋላ የመጽሓፏ ቁምነገር ደግሞ እዛ ላይ  እንደሆነ አስምሮበታል። ደራሲው የተጠቀመበት የአተራረክ ስልት ግን ባንድ የአጻጻፍ ዝርያ ብቻ የሚወሰን አይደለም  ሲልም ሀሳቡን አጋርቷል። በመቀጠልም ማሞ፡ ከምናውቃቸው የድሮ ጸሓፊዎች በተለይም ባሁኑ ወቅት ኤርትራንና  ኢትዮጵያን አስመልክተው በመጻፍ ካሉት ጸሓፊዎች በይዘትና በቅርጽ የተለየ ደራሲ እንደሆነም መስክሯል። ‘አንቱ  በእናት’ን፡ በኢትዮጵያውያን ጸሓፊዎች ከተጻፉት እንደነ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’፡ ‘አርአያ’፡ ‘እንደወጣች ቀረች’፡ ‘ኦሮማይ’ ጋር  እያነፃጸረ እንዳነበባት በመግለጽ ከነዚህና መሰል ጸሓፊዎች ማሞ የተለየ ጸሓፊ ነው ሲል ገልጾታል። በመሆኑም መጽሓፏ  ከኦሮማይ ብቻ በትንሹ የምትመሳሰል ሆና እንዳገኛትም አክሏል። ይሁንና በይዘትና በዓላማ ሁለቱም መጽሓፎች  እንደማይገናኙና በዓሉ ግርማ ከስሟ ጀምሮ ፍፁም ኤርትራዊ ያልሆነች በ‘ፊያሜታ’ የምትታወቅ ሴት ለፍቅረኛዋ ስትል  ኤርትራዊነቷን እንደምትክድ አድርጎ ሊስላት ሲሞክር ማሞ ግን ያፈቀራትንና ያፈቀረችው ሴት ታጋይ ከፍቅር አንጻር ሲታይ  እንደባለቤቱ፡ ከዜግነት አንጻር ሲታይ ግን ፍፁም ኤርትራዊ አድርጎ እንዳቀረባት በንጽጽር አሳይቷል ምስጉን።  

ጆቴ በየመሀሉ የሚያቀርባቸው ረጃጅም ደብዳቤዎች የአንባቢን ትዕግስት የሚፈታተኑ ቢሆኑም፡ ደራሲው ግን ያለፈውን  የህይወቱ ክፋይ ለማሳየት የወሰደው ምርጫ ብልህ መሆኑን እንደሚያሳይም አክሎ ገልጿል። የተጠቀመበት የምልሰት  መንገድ ደግሞ አንባቢ ከጆቴ ሳይለይ እንዲጓዝ እንደረዳውም አብራራ። ቀጥሎም ምስጉን፡ ጆቴ በመጽሓፏ ውስጥ ኤርትራ  ውስጥ በተደረገው ውጊያ ያለቁ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በቡልዶዘር አንዱ ባንዱ ላይ ተነባብረው ያለምንም መጨቃጨቅ  ጉድጓድ ውስጥ በጅምላ ሲቀበሩ በማየቱ፡ ለምን ይሆን ወገኖቼ ከአስከሬኖቹ የማይማሩት ብሎ የጻፈውን ግሩም ጽሑፍ  ጠቀሰ። እናም ከጆቴ ጋር እያወሩ ሳለ በጭውውታቸው መሀል ምስጉን ያንን ጥቅስ በማስታወስ ጆቴን በኤርትራና  በኤርትራውያን ቅናት ያድርብሀል ወይ ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ጆቴ ሀገሩ እንደ ኤርትራ እርስ በርስ የሚዋደዱ ህዝቦች ቢኖሯት ምኞቱ እንደሆነ እንደገለጸለትም ለአድማጮች አጋርቷል። አያይዞም ጆቴና ገላዬ ከብዙ ፈተና በኋላ በተለይም ገላዬ  የከፈለችው መስዋዕትነት አልፎ እስካሁን አብረው እንደሚኖሩ ከገለጸ በኋላ በመጽሓፏ አቀራረብ መሠረት አስቀድመው  ጆቴን አፍቅረው የነበሩ ሴቶች ከገላዬ በመልክ የሚበልጡ መስለው እንደሚታዩት፡ ይሁንና ከውስጥ ውበት አንጻር ሲታይ  ግን ፈጽመው ከሷ እንደማይወዳደሩና፡ የገላዬ ስብዕና ብቻ ሳይሆን የታገለችለት ዓላማና የታገለችላት ኤርትራም ከሁሉም  የበለጡ ናቸው ይልና፡ ገላዬና ኤርትራ የጆቴን ልብ ሰለቡት ሲል አስተያየቱን አጋርቷል። 

አያይዞም ‘ህይወት ቀጭኗ’ በሚል አርእስት ጆቴ ለገላዬ ከጻፈላት ረጅም ግጥም ቀንጨብ አድርጎ አነበነበ። በመጨረሻም  እንዲህ ሲል ንግግሩን ዘጋ፡ “ደራሲው እውነተኛ ምስክርነቱን አቅርቧል። ህዝባዊ ግንባር፡ ምርኮኞች የነበራቸውን አስተሳሰብ  አጥቦ፡ አስተያየታቸውን ለውጦ፡ ከጎኑ እንዲሰለፉ ለማድረግ ያስቻለውን ሰባዊነትና መርህን የተከተለ ስነ-ሀሳባዊ አቋሙን  ልብ በሚነካ ስነ-ጽሑፋዊ አቀራረብ ከትቦታል። ማሞ የዛ በእምነት የተሰለፈለት ህዝባዊ ግንባር አባል ሆኖ፡ አንዲት ታጋይን  አፍቅሮ አግብቷል። [ሁለቱም] የነዚህ ያሳለፉት የጦርነትና የግጭት ምዕራፍ ለዘልአለሙ በመዝጋት በአብሮነትና በመተባበር  መኖር የሚገባቸው ኤርትራና ኢትዮጵያ ዜጎች የሆኑ አራት ልጆችን አፍርተዋል። “አንቱ በእናት” ያለፈውን መራራና ጣፋጭ  ህይወት የምትተርክ፡ ለህዝቦች ሰላምና መተባበር ጥሪዋን የምታቀርብ ብርቅዬ መጽሓፍ ናት” ሲል መጽሓፏን አድንቋል።  

ቀጥሎ መድረኩን የተረከበው የአብዮት ጥበቃ (ሓለዋ ሰውራ) አባል የነበረው መንግስተአብ አርአያ (አምሓራይ) ነበር።  መንግስተአብ መጽሓፏን አስመልክቶ ሳይሆን የአብዮት ጥበቃ አባላት ማህበርን ወክሎ ንግግር እንዲያደርግ ስለተጋበዘ ትንሽ  ነገር ለማለት እንደመጣ አስታውሶ፡ ማሞ በአንድ የኢትዮጵያ ሜድያ ቀርቦ፡ ኤርትራውያን ታሪካቸውን በሚገባ አያውቁትም  ብሎ እንደነበር በማስታወስ፡ እንኳንስ ሰፊው የኤርትራ ህዝብ፡ በትግሉ ሜዳም ጭምር ስለ ምርኮኞች አያያዝ የነበረው  ግንዛቤ የአሳሪና ታሳሪ፡ የጠባቂና ተጠባቂ ታሪክ ተደርጎ ይወሰድ ነበር ብሏል። ይሁንና ባጠቃላይ በተለያዩ መስኮች  ተሰማርተው የነበሩ የግንባር አባላትም ይሁኑ በተለይም የአብዮት ጥበቃ አባላት የሰውን አስተሳሰብ በመቀየር ሥራ ላይ  ነበር ይንቀሳቀሱ የነበሩት ሲልም መስክሯል። እስካሁን ድረስ በአብዮት ጥበቃ ዙርያ ይሠሩ የነበሩት ሥራዎች ለህዝብ  የቀረቡበት መልክ አነስተኛ እንደሆነና ለወደፊት ሁሉንም ሥራዎች የሚያጠቃልል ሥራ ከተሠራ አጠቃላይ ስእል ሊሰጥ  ይችላል ሲልም አስገንዝቧል። በማያያዝም የአብዮቱ ጥበቃ የነበሩት አባላት ልንጽፈው የሚገባን ነገር አልጻፍንም ይልና  የማሞ ጅማሮ ጥሩ እንደሆነ ሀሳቡን አካፍሏል። ‘አንቱ በእናት’ ለማጣቀሻነት እንደምታገለግልም ታሳቢ በማድረግ፡ ለበለጠ  ጥቅም ወደ ኤርትራዊ ቋንቋ መተርጎም እንዳለባትም አስታውሷል። በመጨረሻም በማህበሩ ስም ማሞን እንኳን ደስ አለህ  በማለት ንግግሩን ቋጨ።  

በመጨረሻም፡ የ‘አንቱ በእናት’ ጸሓፊ የሆነው ጆቴ በደማቅ የተጋባዥ እንግዶች ጭብጨባ ታጅቦ ነበር መድረኩን  የተረከበው። ፊቱ ላይ ደማቅ ፈገግታ እየተንጸባረቀ፡ “በየናይ ቋንቋ ከምዝጅምር ጠፊኡኒ’ሎ” (በየትኛው ቋንቋ እንደምጀምር  ግራ ገብቶኛል) በማለት ንግግሩን በትግርኛ ሲጀምር ተጋባዡ ትግርኛ አይችልም የሚል ግምት ስለነበረው ይሆናል እየሳቀ  ጭብጨባውን ለገሰለት። ቀጥሎም በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ መጀመር ሳይሻል አይቀርም ምክንያቱም ሰው ሲወለድ መጀመሪያ  የእናቱን ቋንቋ ነው የሚችለው አለና የሱም የእናት ቋንቋ ኦሮምኛ በመሆኑ “አካም ጀርቱ” ሲል በኦሮምኛ ከዚያም  ከትምህርትና ከአከባቢው እንዳገኘው በገለጸው አማርኛ “ደህና ናችሁ? እንደምን አላችሁ? እንኳን ዓይን ለዓይን አገናኘን”  ሲል ሰላምታውን አቀረበ። ሶስተኛ ቋንቋው ደግሞ ከትግል ሜዳ የተማረው ትግርኛ እንደሆነ ገልጾ በተለያዩ የትግል  መንገዶች አልፌያለሁ ብሎ እንደሚያምን ከገለጸ በኋላ ምንና ምን እንደሆኑ ሲገልጻቸው፣ አርነት ማምጣት፡ ቋንቋ መማርና  በተማረው ቋንቋ መጽሓፍትን መተርጐም፡ ከሱ ጋራ ለተማረኩት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ከትግርኛ ወደሚገባቸው ቋንቋ  በመተርጐም ማስተማር ግድ ይል ስለነበር፡ ራሱን አስተምሮ ሌሎቹን ለማስተማር እንደቻለ በማብራራት ገለጻውን በትግርኛ  ቀጠለበት።  

አያይዞም “የኤርትራ ህዝብ ለነፃነቱ ሲል የተዋደቀ፡ ልጆቹን የገበረ፡ በጣም ደግ ህብረተሰብ፡ ጨዋ ህብረተሰብ ነው። ይሄ  ቃል ዝም ብሎ በተባለ ወይንም በወሬ ሳይሆን ውስጥ ውስጡን ዋኝቼ በረሀብ ጊዜ ከህዝቡ ጋር እየተራብኩ ደም  ሲያስፈልግም በጥይት ባልዋጋም በልማታዊ ሥራ ሞደሻ እጅን ሲያቆስል፡ አካፋ እጅን ሲልጥ ደም እየተቀባበልን አንድ ላይ  ደማችን በመደባለቅ ሰርተናል፡ ደም ከፍለናል” ሲል ያኔ ለነበረው እጅና ጓንት በመሆን የተሠራውን ሥራ አጽንዖት  ሰጥቶታል። ቀጥሎም በልማት ሥራ እያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ምርኮኞች በደርግ የአውሮፕላን ድብደባ ተመትተው  እንደተገደሉም መስክሯል። “ስለዚህ” አለ ጆቴ “ይሄ ህብረተሰብ ምን ዓይነት ህብረተሰብ እንደሆነ፡ ከሱ ጋር አብረን ደክመን፡ ከሱ ጋር ወጥተን፡ ከሱ ጋር አብረን ተርበን፡ ከሱ ጋራ ሠርተን፡ የምንመስክረው እንጂ፡ በወሬ አይደለም፡ ሰምተህ  የሚወራ አይደለም፡ በተግባር አይተን የምንሰጠው ምስክርነት ነው” ሲል አሰመረበት።  

በመቀጠልም “እንኳን ደስ አላችሁ። ይሄ አስቀድሞ በጓዶቻችን ሲገለጽ የነበረው የናንተ ፍሬ ነው” ካለ በኋላ “የኤርትራ  ህዝብ ያታገለና የታገለ ህዝብ ነው። ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ ማለት ነፃነታችሁን ተቀዳጅታችኋል። ግን ነፃነታችሁን ለብቻችሁ  አይደለም ያገኛችሁት። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አድናችሁ፡ አስተምራችሁ፡ ላለቀሱ እናቶች የደረሳችሁ  [ልጆቻቸውን ያስረከባችሁ]፡ በእውነቱ ንጹህ ህዝብ ናችሁ” ሲል ለህዝቡ ትግልና ደግነት ያለውን ከበሬታ ገለጸ። ከዛም እሱ  ራሱ የዚሁ የኤርትራ ህዝብ ትግልና ደግነት ውጤት እንደሆነ፡ የኤርትራ ታጋዮች በጦር ሜዳ እየተዋደቁና እየተሰዉ እያለ  እሱን (ማሞ) የማረከው ታጋይ ካጠገቡ የተሰዉ ጓዶቹን እያየ ስሜቱን ውጦ፡ እሱን (ማሞ) ማርኮ በህይወት እንዲቆይ  ማድረጉን ሊገልጸው ከሚችለው በላይ እንደሚሆንበት ስሜት ውስጥ ገብቶ መስክሯል።  

“እኔ ማን እንደማረከኝ አላውቅም። ያ ‘እለፍ፡ ጠመንጃህን ጣል’ ያለኝ [ታጋይ] እኮ ምናልባት በህይወት አይኖርም ይሆናል።  አሁን ተሰውቶ ይሆናል። ስሙን አላውቀውም። እኔ ግን ከፊታችሁ ቆሜ እናገራለሁ። ይ ሀቅ ነው። ስለዚህ እኔ የልጃችሁ  ምትክ ነኝ” ብሎ ሲል ደማቅ ጭብጨባ ጐረፈለት። “ጀግኖች በደማቸው ያቆሙን፡ ዳግመኛ የተፈጠርን፡ በኤርትራና  በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የተፈጠርን ፍጡሮች ነን” ሲልም አከለበት። ያንን መልካም ሥራና ታሪክ ለሠሩት የኤርትራ  ህዝብና ግንባሩ የሚገባቸውን ክብርና እውቅና በመስጠት ንግግሩን ቀጠለ – ጆቴ።  

አያይዞም በEBS TV ቀርቦ እንኳንስ እሩቅ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ፡ የኤርትራ ህዝብም ሳይቀር ታጋይ ልጆቹ ምርኮኞቹን  ይይዙበት የነበረውን መልካም ታሪክ እንደማያውቅ፡ ከዛም ባለፈ ራሳቸው ታጋዮቹ የማረኩት ምርኮኛ ወደሚመለከተው  አካል ካስተላለፉ በኋላ ምርኮኛው በምን ሁኔታ እንዳለ አያውቁም ነበር ምክንያቱም የነሱ ተልእኮ መዋጋት ስለነበር ነው  ብሏል። ስለ ምርኮኞች የተጣራ መረጃ የነበረው የአብዮት ጥበቃ (ሓለዋ ሰውራ) ክፍል እንደነበር፡ አባላቱ የነሱ አርአያ  እንደነበሩና ከነሱ ጋር አብረው ደምና ላብ በመቀላቀል ይሠሩ እንደነበሩ መስክሯል። ከነፃነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ  ከመመለሱ በፊት እንደ ማንኛውም ሰው ኤርትራዊ ዜግነቱን በመጠቀም በሬፍረንደም ድምጹን እንደሰጠም ገልጿል።  በማስከተልም በመጽሓፏ ዙርያ ያለውን ሀቅ በይፋ ለመግለጽ የፈለገበት ምክንያትም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ  ህዝብ ስለ እውነታው ማወቅ አለበት ከሚል እምነት የሚመነጭ እንደሆነም አብራርቷል።  

ከምርኮው በኋላ፡ በምርኮኞቹ አእምሮ ተቀርጸው ከሚቀሩትና ልብ ውስጥ ሰምጠው ከገቡት ክስተቶች መካከል አንኳር  አንኳር የሆኑትን አንድ ሁለት እያለ ለተጋባዡ ማቅረብ ጀመረ። የመጀመሪያ ትውስታውን ሲተርክ ተማርከው እያሉ፡  የኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላኖች ሲያንዣብቡ በመታየታቸው ታጋዮቹ ከራሳቸው በላይ ለምርኮኞቹ ህይወት ቅድሚያ  በመስጠት መሬት ላይ እንዲተኙ አዘው እነሱ ግን ቦታ ስላልያዙ እነማሞን ለመጠበቅ ቆመው እንደቀሩ ባዩ ጊዜ በጣም  እንዳስደመማቸው እየተገረመ ተረከ።  

አውሮፕላኖቹ ከሄዱ በኋላ፡ አንድ ኃላፊ የሆነ ታጋይ በመምጣት ‘እንኳን እግዚአብሄር አተረፋችሁ!’ ብሎ ሲላቸው  ሁለተኛው ግርምት የፈጠረባቸው ፍጻሜ ነበር። እነማሞም ይህን የሚያክል መልካም ነገር ከ‘ወንበዴ’ አፍ ይወጣል የሚል  ግምት ስላልነበራቸው “ሽፍታ ወንበዴ ‘እንኳን አተረፋችሁ’ ይላል እንዴ?” ብለው ከመጠን በላይ እንደተገረሙ ሲተርክ  ተጋባዡ በሳቅ አጀበው።  

ከዛም ትንሽ ሄደው ከአውሮፕላን ቅኝት የሚጋርዳቸው ሸንተረር ላይ ከደረሱ በኋላ ቁስለኞች እየወጡ እንዲታከሙ ሲደረግ፡  ሶስተኛው ግርምታቸው ተፈጸመ። የሆነው እንዲህ ነበር። ማሞ እግሩን እየታከመ ሳለ፡ ገና ከነጠመንጃው ያለ ስለመሰለው  ጠመንጃውን በዓይኑ ማፈላለግ ይጀምራል። ሀኪሟ፡ “ምን እየፈለግክ ነው ወንድሜ?” ብላ ስትጠይቀው “ውይ፡ ጠመንጃዬን  አስደግፌ እየታከምኩ ስለመሰለኝ ነውኮ” ብሎ ሀቁን አፍረጥርጦ ይነግራታል። የሀኪሟ መልስ ያልተጠበቀ ነበር። “ውይ  ጠመንጃማ ምናባቱ ያረግልሃል! ከጠመንጃማ ተገላግለሃል እኮ! ምናባቱ ያረግልሃል! ሂድ ወደ ጓደኞችህ” እንዳለችው  እየተገረመ ምስክርነቱን ሰጠ። እሱ የጠበቀው መልስ ግን “አሁንም ጠመንጃ ትላለህ፡ አንተ ግማታም!” የሚል እንደነበር  ሲገልጽ ተጋባዡ በጭብጨባ አጅቦ አዳራሹን በሳቅ አጥለቀለቀው።  

አራተኛው ግርምት ደግሞ ከች አለ። እነዛ ከነማሞ አንጻር በመሆን አስቀድመው ሲታኮሱ የነበሩት ታጋዮች ከነአቧራቸው  ደረሱና “እንኳን አተረፋችሁ ወንድሞቻችን! እንኳን አተረፋችሁ! እናንተኮ የጭቁኑ የኢትዮጵያዊ ገበሬ ልጆች፡ የወዛደር ልጆች ናችሁ። እንደኛ ጭቁኖች እንጂ ምንም የምታውቁት ነገር የለም። ሆን ብላችሁ እኛን ለማጥፋት አልመጣችሁም።  በመንግስታችሁ ተገዳችሁ ነው የመጣችሁት። እኛ ደግሞ ለነፃነታችን ነው የምንዋጋው እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማጥፋት፡  እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ለመግደል አይደለም ዓላማችን። የሆነ ሆኖ፡ ካሁን በኋላ ሞት ቀርቷል። ካሁን በኋላ በህመም  ካልሞታችሁ በስተቀር በጥይት [መሞት] አብቅቷል፡ ሞት የለም። አይዟችሁ፡ እንዳትረበሹ” ብለዋቸው ወደየሥራቸው  ሄዱ።  

ትረካው ዝም ብሎ እንደ ጅረት ይፈሳል። ማሞም ተጋባዡም በትረካው እንደተገረሙ ነው። እስከ ደጅ ድረስ የፈሰሰው  ታዳሚ መጽሓፏ የያዘቻቸውን አስጎምጂ ክስተቶች በዓይነ-ህሊናው እየዳሰሰ ይቀጥላል።  

ከዛም በመቀጠል ጆቴ፡ ታጋዮቹ ትልቅ ጎላ ድስት እሳት ላይ በመጣድ ገንፎ አዘጋጅተው በቅቤ ምትክ የሰሊጥ ዘይት  አድርገው በማቅረብ “ብሉ እንግዲህ የኛ ጮማም የኛ ቅቤም ይኼው ነው” ብለው እንዲበሉ ሲጋብዟቸው ለምርኮኞቹ  አምስተኛው ግርምት እንደነበር አወጋ።  

እነዚህን የመሳሰሉ ደጋግ የምርኮኞች አያያዝ፡ ወንበዴ፡ ሽፍታና አውሬ ከሚባሉ ታጋዮች ሲቸሩ ማየት እንደ ተአምር  እንዲቆጥሯቸው ከገፋፏቸው ምክንያቶች አንዱ፡ ምርኮኞቹ ራሳቸው በኤርትራውያን ላይ ሲፈጸም የነበረውን ግፍ  አስቀድመው ለመመስከር በመቻላቸው እንደነበር በ’አንቱ በእናት’ ላይ አስፍሮታል። እዛ ላይ አንዳንድ ጨካኝ የኢትዮጵያ  ወታደሮች የተማረኩ የኤርትራ ታጋዮችን ይተፉባቸውና በሰደፍ ይመቷቸው እንደነበረ ጆቴ ያወሳል። እነዚህ ወታደሮች፡  ከሞት ራሳቸውን ለማዳን በየዋሻውና ጫካው ተደብቀው ያገኟቸውን ህጻናትም ሳይቀር ‘የእባብ ልጅ እባብ ነው’ በሚል  አስተሳሰብ ይገድሏቸው እንደነበረም ጆቴ ይመሰክራል። ስለዚህ የተማረኩት የኢትዮጵያ ወታደሮች፡ በታጋዮቹ  የተደረገላቸው ሰባዊና ፍቅራዊ አያያዝ ትንግርት ቢሆንባቸው የሚያስገርም አይሆንም።  

“ጥይት ስንጠብቅ ገንፎ መጣልን። ስድብ ስናስብ ‘እንኳን አተረፋችሁ! መጣልን’ ሲልም በዛ በጣም አጭር የምርኮ ጊዜ  የተፈጸሙ ተስፋ መቁረጥን አስወግደው ህይወት የሚያለመልሙ የታጋዮቹ ደጋግ ተግባሮችን ደስ በሚል አገላለጽ  አጠቃለላቸው። ከዛም ወደ ብሌቓት ተወስደው እያለ አንድ ቀን ሽንት ሸንተው እንደተመለሱ፡ ወዲያውኑ ተሰለፉ የሚል  አጣዳፊ ትእዛዝ ሲሰጣቸው በቃ የቁርጥ ቀኗ ደረሰች ልንገደል ነው ብለው እንዳሰቡ አስታውሶ፡ በሰልፍ ተጉዘው አንድ ሜዳ  ላይ ከደረሱ በኋላ ግን ከውጭ የመጡ ነጭ ሰዎች በመኪና እንደመጡና ካሜራዎቻቸውን በማዋደድ እንደቀረጿቸው፡  ክስተቱ ግንባሩ ምርኮኞች እንዳሉትና እንደሚያኖርም ለዓለም ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማሳወቅ እንደረዳም አስገነዘበ።  ቀጥሎም ፖለቲካዊ ትምህርትና ስለ ኤርትራ ታሪክ እየተማሩ ንቃተ-ህሊናቸውን ለማጎልበት እንደቻሉ፡ በግንባሩ ኃላፊና  ተራ የሚባል ነገር ሳይኖር ሁሉም አብረው እንደሚሠሩና እነሱም አብረው በልማት ሥራ ላይ ይሳተፉ እንደነበር ገለጸ።  ንቃተ-ህሊናቸው እየጎለበተ ከሄደ በኋላ ምርኮኞቹ፡ ኤርትራውያን እንደኛ ሰዎች አይደሉም እንዴ። ለነፃነታቸው ነው  እየታገሉ ያሉት ብለው ማሰብ እንደጀመሩና በአብዮት ጥበቃ ክፍል ከነበሩ ታጋዮች ጋር የነበረው መተሳሰብና መከባበር  እየዳበረ እንደመጣም መሰከረ።  

በመጨረሻም በ1981 እስከ 5000 የሚሆኑ ምርኮኞች ከተለያዩ ቦታዎች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ተደርገው እንደነ ዓሊሰይድ  ዓብደላና ግርማ አስመሮም የመሳሰሉ የግንባሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በመምጣት መግለጫ ከሰጡ በኋላ ከዛ ቀን ጀምሮ ሁሉም  ነፃ እንደሆኑ እንዳበሰሯቸው ገለጸ። የዛን ጊዜ ነፃ የወጣው ምርኮኛው ብቻ ሳይሆን እነሱን ሲጠብቁ የኖሩት ታጋዮችም  አብረው ነፃ የወጡበት ቀን እንደነበረ ያወሳና ምክንያቱን ሲገልጽም ሰውን የመሰለ ፍጡር መጠበቅ ከባድ ሥራ ስለነበረ ነው  ብሏል። ይህንን አስመልክቶ ጆቴ በመጽሓፉ ዙፋን የከረን ፍቅረኛው፡ ሃብረንገቓ እያለ የላከችለት ‘ፍቅር እስከ መቃብር’  በሚባለው መጽሓፍ ፊታውራሪ መሸሻ ልጃቸው ሰብለወንጌል ከተጠየፉት በዛብህ ጋር ፍቅር መጀመሯን ባወቁ ጊዜ የቤት  እስረኛ እንድትሆን ፈርደውባት እንደነበር ይተርካል። ችግሩ ግን እሳቸውም ማንንም ስላላመኑ እሷን ለመጠበቅ ሲሉ ከስዋ  ጋራ እስረኛ መሆናቸው ነበር – አሳሪና ታሳሪ አብረው ሲታሰሩ ያለው ጆቴ። ገጽ 414 ላይ ሀዲስ አለማየሁ እንዲሁ  ያስነብቡናል፡ “ሰብለ ወንጌል ከታሰረችበት ባስረኛው ቀን እስክትፈታ ድረስ አባትዋም እግራቸው በግር ብረት ውስጥ  አይግባ እንጅ እንደስዋ እስረኛ ሆነው ሰነበቱ”።  

ጆቴ፡ በዛች የደስታ ቀን ስላጋጠሙ ሁለት ክስተቶች ለተጋባዦች አጋርቷል። አንደኛው፡ አንድ ምርኮኛ (ያኔ ከነጆቴ ጋር  ለኤርትራ ነፃነት ለመዋጋት የወሰነና ባሁኑ ሰዓት የኤርትራን ነፃነት ለማየት በቅቶ ናቕፋ ላይ ምግብ ቤት ከፍቶ በመተዳደር ላይ የሚገኝ ታጋይ)፡ በግንባሩ ኃላፊዎች የተሰጠው መግለጫ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ብድግ ብሎ እንደሮጠና ማንም  ቁም ብሎ የሚያስቆመው ሲያጣ ነፃ መሆኑን እንዳረጋገጠም ሲገልጽ ሁለተኛው ደግሞ፡ በራሱ በጆቴ ላይ የደረሰ ክስተት  ነበር። ሁሉም በመዝናናትና ጭፈራ ላይ እያሉ አንድ ታጋይ ትጥቁንና ጠመንጃው ሲወረውርለት እንደደነገጠና ከምርኮ በኋላ  ለመጀመሪያ ጊዜ ያነገበው የታጋዮች ጠበንጃ እንደነበረም ተርኳል። ክስተቱ ጆቴ ምን ያክል በታጋዮቹ ታምኖና ተቀባይነት  አግኝቶ እንደነበር የሚያሳይ ነበር።  

ከዛም ንቃተ-ህሊናው ከፍ እያለ ከሄደ በኋላ ጆቴ ታጋዮች እንደኛ ሰዎች ናቸው። ከዚህ ሄደን ከደርግ ጋር ልንወጋቸው  ነውን? ይኼኛው የበደልነውን ህዝብ በደማችን መካስ አለብን በሚል ስሜት ተገፋፍቶ ታጋይ ሆኖ ለኤርትራ ነፃነት  ለመዋጋት እንደወሰነ ገለጸ። ምን ማለቱ እንደሆነ ሲያብራራም፡ ከረን ላይ እያለ የከባድ መሣሪያ አስተኳሽ እንደነበረ ከገለጸ  በኋላ “በእውነቱ ምን ያክል ሰው እንዳስገደልኩ አላውቅም። ሁሌም የሚታየኝ ተማሪዎች ተሰብስበው ወይም በትምህርት  ቤት እየተማሩ፡ ይኼ ብረት፡ ቁምቡላ ሄዶ ወድቆ ስንት ተማሪዎች እንደገደለ አላውቅም. . . ለታጋዮች ብለህ የወረወርከው  ቁምብላ ትምህርት ቤት ላይ ሊያርፍ ይችላል። እህል በማጨድ ላይ ያሉ ሰዎች፡ የሚኮተኩቱ፡ በማህበር እየጠጣ የነበረ፡  በተሰበሰበ ህዝብ ላይ ሊያርፍ ይችላል። አንድ ቦምብ ስንት ሰው ነው የሚገድለው? ስለዚህ ስንት ኤርትራውያን እንደገደልኩ  አላውቅም። ፈጣሪ ነው የሚያውቀው. . . ለዚህ ሁሉ በደል ነው ህዝባዊ ግንባር ይቅርታ ያደረገው።” ካለ በኋላ ንቃተ ህሊናው ስላደገ ከነበሩት ምርጫዎች መካከል (ውጪ መሄድ፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች መቀላልቀል) ከጓዶቹ ጋራ  ወደ ግንባሩ ለመቀላቀል እንደወሰነ በንጽህና ምስክርነቱ ሰጠ።  

አዳራሹ ጸጥ ረጭ እንዳለ ነው። በስተመጨረሻም ነፃነት ከሆነ በኋላ እንደማንኛውም ኤርትራዊ በሬፍረንደም ጊዜ ለነፃነት  ድምጹን ሰጥቶ እናቱን ለመርዳት ብሎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳመራ ሲገልጽ ደማቅ ጭብጨባ ተዥጎደጎደለት።  

ስለሱና ስለ ገላዬ ግንኙነት ሲገልጽም ፍቅር እንደ አሞራ ቦታ ሳይመርጥ ነው የሚያርፈውና የሱ ፍቅር በሷ፡ የሷ በሱ ላይ  አርፎ ለትዳር እንደበቁ ገለጸና ሌሎች ሴቶች ቢኖሩም የሰው ልጅ ምንጊዜም የሰው ልጅ ነው የሚል አቋም የነበራት ገላዬ  እንዳሸነፈች ወደ ባለቤቱ እያየ አስረዳ። ከዛም የሱና የገላዬ የፍቅር ጉዞ ውጣ ውረድ የበዛበት እንደነበር፡ ገላዬ እሱን  ማፍቀሯ ሊቀበሉት ያልቻሉ ታጋዮች እንደነበሩም ላንባቢዎች ገለጸ።  

ቀጥሎም ‘አንቱ በእናት’ን ለምንና እንዴት እንደጻፋት ሲያስረዳ፡ ወደ ኢትዮጵያ ቢሄድም ልቡ ሁሌም እዚህ እንዳለ፡  በኢትዮጵያ የነበረውን ህይወት መልመድ እንዳቃተው፡ የታጋዮች ባህል ለምደህ ሌላ መልመድ እንደሚከብድ ምክንያቱም  በትግል ሜዳው ስስት፡ ሌብነት፡ ውሸት፡ ጉቦ፡ ገንዘብ የሚባሉ ነገሮች ይነካኩዋቸው እንዳልነበሩ አከለ። ስለዚህ ያ ሁሉ  ያለፈው ታሪክ እንዴት ይገለጽ የሚል ጥያቄ እንደመጣበትና ይኼ ታሪክ እኔ ካልጻፍኩት ማን ይጽፈዋል ብሎ ከራሱ ጋር  ተነጋግሮ እንደጀመረው ገለጸ። እናም ትግራይ ውስጥ ሥራ ላይ እያለ ጊዜውን በማጣበብ ከሌሊቱ 9 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12  ሰዓት በእጁ እየጻፈ፡ እዛው የመንገድ ግንባታ ድርጅታቸው ውስጥ የምትሠራ ሰው በከምፕዩተር እየጻፈችለት እንደቀጠለና  ከዛም በኋላ በልጆቹ እገዛ መጽሓፏ ለዚህ ደረጃ መብቃቷን ገለጸ። ከህትመቷ በኋላ ምሁራኑን ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ  ክፍሎች እያመሰገኑት እንዳሉና ስለ ኤርትራ ታሪክ የነበራቸውን ብዥታ እንዳጸዳላቸው እንደሚመሰክሩ ገለጸ። ስለዚህ  መጽሓፏን ወደ አንባቢዎች በማድረስ በኩል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪውን አቀረበ። አዲስ አበባ ላይ በመጽሓፏ  የመመረቂያ ቀን የኢትዮጵያ ምሁራን፡ ማሞ አፈታ ኤርትራንና ኢትዮጵያን የምታገናኝ ሀገር፡ ድልድይ፡ አስረክቦናል በማለት  እንደመሰከሩም ለተጋባዡ አጋርቷል። በመጽሓፏ የሱ ሚና እንደ መሣሪያነት የገባ እንጂ ዋናው ቁምነገሩ ኤርትራና ኢትዮጵያ  እንዴት በሰላም ይኖራሉ የሚል ነው ብሏል። የዚች ዓይነት መጽሓፍ ስታዘጋጅ ተግዳሮት እንደሚያጋጥሙና መስዋእትነት  እንደሚጠይቅም አስምሮበታል።  

ቀጥሎም በመጽሓፏ ዙርያ ለተባበሩት ሰዎች አመሰገነ – መጀመሪያ ውድ ባለቤቱን በማስቀደም። በስተመጨረሻም ለባለቤቱ  ክብር የጻፈውን ‘ህይወት ቀጭኗ’ የሚል ረጅም ግጥም አነበነበ። ግጥሙ ከሞላ ጎደል ሁለቱም ስላሳለፉት ህይወት የሚተርክ  ስለሆነ ተራኪ ስነ-ግጥም (narrative poetry) ከሚባለው ምድብ ይደለደላል። ጸሓፊዎች ነገሮችን ሲገልጹ ከራሳቸው ብቻ  

ሳይሆን ከሌሎች ነገሮችም እያወዳደሩና እያመሳሰሉ ያቀርቧቸዋል። እነዚህ መንገዶች ‘ተምሳሌት/ልክ መሆን’ (metaphor) እና ‘ንጽጽር/መመሳሰል’ (simile) በመባል ይታወቃሉ። የመጀመሪያው፡ አንዱ ነገር እንዳለ ሌላኛው ነገር ነው ተብሎ  ይገለጻል። ለምሳሌ ‘ራሄል ቆቅ ናት’ ካለ ራሄልና ቆቅ አንድና አንድ ናቸው የሚል ምስል ይፈጥራል። ሁለተኛው (simile) ግን ‘እንደ’ በማለት መመሳሰላቸውን ያሳያል። ለምሳሌ ‘ራሄል እንደ ቆቅ ናት’ ካለ ሁለቱም ይመሳሰላሉ እንጂ አንድና አንድ አይደሉም ማለት ነው። እነዚህ መንገዶች ሁለት የማይገናኙ ነገሮችን በማወዳደር፡ ያ የሚነፃፀረው ነገር የሌላውን ማንነት  ስለሚወስድ ወይንም ስለሚመሳሰል ባንባቢ ላይ የተለየ ስእለ-አእምሮ ይፈጥራል። 

ጆቴ በመጀመሪያው ስንኝ ‘የኔ ወርቅ/የኔ ሆድ/የኔ ማር/የኔ እመቤት ልበላት’ እያለ ባለቤቱን ከተለያዩ ነገሮች ጋር እያወዳደረ  የሆነ ስእል ለማሳየት ሞኩሯል። በዚሁ ስንኝ መሠረት ህይወት ባለቤቱ ወርቅ ናት። አንገትና ጆሮ ላይ የምትንጠልጠል  ሐብል፡ ጣት ላይ የምትሰካ ቀለበት፡ ክንድ ላይ የምትዥረገግ አምባር። ማርም ነች የምትቀመስ፡ የምትላስ፡ የምትጣፍጥ።  ደግሞም ሰው ሰራሽ ማርመለይድ (ማርማላት) ሳትሆን በተፈጥሮ ከሚገኙ አበቦች የተሠራች ተፈጥሮአዊ ጣፋጭነት። ከዛም  ባለፈ ሆድም ናት። ቻይ፡ ታጋሽ፡ ሁሉንም ውጣ የምታስቀር፡ በነገ ተስፋ የምትኖር ሸጋ ናት። እመቤትም ናት፡ ጆቴ  የሚሰግድላትና የሚያከብራት። እሱ ከታች ሆኖ አንጋጦ የሚያይ አገልጋይ፡ እሷ ደግሞ ከላይ ከዙፋኗ ሆና የምታዘው  ንግሥት። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው በግጥሙ የገለጻት።  

ሞትና መከራ ተዘርተው በሚበቅሉበት አከባቢ፡ አይዞህ፡ ሁሉም ነገር ያልፋል የሚልና መጠጊያ የሚሆን ወገን ማግኘት  ምነኛ መታደል ነው። ምህላውን የሰማው ፈጣሪ ገላዬን ላከለት።  

ከመስዋዕት ሜዳ ከሞት ከመከራ  
ከጥይት ከአረር ከጦር ሜዳ አዝመራ  
ህይወት ቀጭኗ ‘አጆኻ’ አለቺኝ  
መጀመሪያ እንደ ጓድ እቅፍ አረገችኝ  
ዓይኔን ከፈተችው ድፍረትም ሰጠችኝ . . . ብሎ ይገልጻታል ጆቴ።  

አንድ ጽሑፍ የራሱ የሆነ ስሜት ወይንም መንፈስ አለው። ይህንን ስሜት ወይንም መንፈስ የጥበብ ሰዎች ‘ቃና’ (tone) ሲሉ  ይገልጹታል። ጽሑፉ የቀረበበት መንፈስ ደስተኛ፡ የላላ፡ የጠበቀ፡ ተጫዋች፡ ሀዘንተኛ፡ አዝናኝ፡ ኮስታራ፡ ፈታ ያለ፡  አብጠልጣይ፡ የሚያሳንስ፡ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ወዘተ ቃና ያዘለ ሊሆን ይችላል። ጆቴ በላይኛው ስንኝ ጥይትንና አረርን  የጦር ሜዳ አዝመራ ሲል ይገልጻቸዋል። ሁለቱም ህይወትን የሚቀጥፉ ሰው ሰራሽና ሰው በላ ብረት ሲሆኑ ባንድ በኩል  እህል፡ ዛፎች፡ ፍራፍሬዎች እንደማፍራት የሰው ልጅ በምትካቸው እነሱን እያፈራ እንደነበር ሲገልጽ፡ በሌላ በኩል ደግሞ  አውዳሚ ባህሪያቸውን በለበጣ አነጋገር የሚተች ይመስል ያሳንሰዋል። በስነ-ጽሑፍ ዓለም ይሄንኑ ዓይነት ቃና  condescending ይሉታል። እናም ጆቴ ያ ገላዬ ህይወቱን ካስጣለችው ተራራ የሚያክል የመከራ ህይወት ቀላል በማስመሰል  ክብደቱን ሲቀልድበት እናያለን።  

ከኤርትራ ነፃነት በኋላም ቢሆን ገላዬ የጀመረችውን እስከ ወዲያኛው ለማድረስ ጨርቄን ማቄን ሳትል ተከትላው ብቻ  ሳይሆን እየመራችው በትዳር ጦር ግንባር ረጂም ከሆነው የእናትነት ትግል ጋር ግብግብ ለመግጠም ወደፊት ገሰገሰች –  ለዳግመኛ ትግል። ለዛም ጆቴ ‘የትዳር መሪዬ ብርሃን መብራቴ’ ሲል ያሞካሻታል በግጥሙ። የአፍላ ዕድሜ ፍቅረኛ ከመሆን  ባሻገር የትዳር ጉራንጉር እንዴት እንደሚኬድ እጁን ይዛ በብርሃኗ እየመራች አሳይታዋለች። አልተደናበረም። አልፈራም።  አንቺ ብርሃን ነሽ። ብርሃንም አንቺ ነው በማለት እሷና ብርሃን አንድም ሁለትም እንደሆኑ መስክሮላታል። እናም አከለበትና፡  

በዚህ ረጅም ርቀት በዚህ የኑሮ ሩጫ  
ህይወት ቀጭኗ ነች ሻምፒዮን ባለ ዋንጫ  

በማለት ለዚህች ከብረት የጠነከረ መንፈስ ያላትና ባንዴ ፍቅረኛም፡ እህትም፡ ባለቤትም መሆን የቻለችን አርአያ ሴት  የሚገባትን ክብር በመስጠት ፍቅሩን ገልጾላታል። ሻምፒዮኗ፡ በርግጥም ነበረች ህይወት ቀጭኗ! እንደሷ ዓይነት ችግር  የማይበግራት እንደ አለት የጠነከረች ባለቤት የማይመኝ ወንድ ይኖራልን?  

ይቺ ከተባረከ ማህጸን የወጣች የተባረከች ሴት፡ ጆቴን በበረሀው ውስጥ የሰውነትን ልክ አሳይታው ሀሩሩም ብርዱም፡  ጠጣሩም ለስላሳውም፡ አቀበቱም ሜዳውም፡ ወረቱም ጓደኝነቱም ካንተ ጋራ ይጣፍጣል ብላ ምንም ሳይበግራት አለኝታው  እንደሆነች አስመስክራለች። ጆቴ እሷን ይመጥናሉ ባላቸው ቃላት ስብእናዋን ለመግለጽ ብዙ ጥሯል። ከማር፡ ከወርቅ፡  ከሆድ ወዘተ እያመሳሰለም ስእለ-አእምሮ ሲፈጥር ተመልክተናል። እኔም ጆቴን ብሆን ኖሮ በተራዬ እንዲህ በማለት  አደንቃት ነበር። 

ማርማ ተቀምሶ ‘ሚጨረሰው  
ወርቅስ ቢሆን በጸሐይ ‘ሚደበዝዘው  
ሆድም በተራው ሲራብ ‘ሚፈታው  
ማን አርጎት  
መንትያሽን – እኩያሽን!  
ተዝቆ ‘ማያልቀውን  
ተጋልጦ ‘ማይደበዝዘውን  
አምሮት ‘ማይበግረውን  
ፈልጌ አስፈልጌ እኩያሽን አጣሁ  
‘ሚመጥንሽ ከሆነ አቻምየለሽ ብዬሻለሁ…  
ገላዬ!  

ያቺ የፍቅር ምሽት፡ ‘የአንቱ በእናት’ ምሽት፡ በጣም የምታስቀና ምሽት ነበረች። ሌሎቹ ቀናት በጣም ቀንተውባት  እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል። ያቺ የፍቅር ምሽት፡ የይቅርታም ምሽት ነበረች። ጆቴ ተጋባዦቹን ልጆቻችሁን፡ ወንድምና  እህቶቻችሁን ገድዬ የመጣሁ ነኝ። ያስተኮስኩት ተተኳሽ ስንቶቹን ንጹሀን ጎድቶ እንደሚሆን እርግጠኛ አይደለሁም  እያላቸው ነው። እነሱ ግን በፍቅርና በይቅርታ መንፈስ ያጨበጭቡለታል። ፍቅራቸውም አዳራሹን ሞልቶ እንደ ብዛታቸው  ወደ ደጅ ፈሷል። ከ’ሓዳስ ኤርትራ’ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ስለዚህ እውነታ መስክሯል። “ኤርትራውያን በዚህ  መልክ ነው እንዴ የሚመለከቱኝ? ይኼን ያክል ነው እንዴ የሚያከብሩኝ?” ብሎ እንደተገረመ ተናግሯል (መጋቢት 21፡  2023)።  

እናም በዚያችው ምሽት፡ አዳራሹ ውስጥ ፍቅር ስትዳበስ፡ ስትሸተት፡ ስትታይ፡ ስትሰማ፡ ስትቀመስ ታየች። ማሞ እዛው  መድረክ ቆሞ በፍቅር ተከቦ ሲያወራ፡ ፍቅር እንደ ዝናሽ የሱዳን ሽቶ እየሸተተችው አሊያም እየሸተታት የነበረ ይመስል  ነበር። ፍቅር በለሰለሱ እጆቿ እየዳበሰችው እንደነበረችም ያስታውቅ ነበር። እምባሶይራ ሆቴል ውስጥ የዘነበው የፍቅር ዶፍ፡  የጆቴን ልብሶችንና ጫማን ብቻ ሳይሆን፡ መላ አካላቱንም በማራስ ፈሷል።  

ማሞ በኤርትራ ቆይታው ላይ፡ ድሮ የኢትዮጵያ ወታደርና የኤርትራ ታጋይ በነበረ ጊዜያት ያውቃቸው የነበሩትን ቦታዎች  እንዲጎበኝ አዘጋጆቹ ሁሉንም ነገር አመቻችተውለት ነበር። ሰዎች ህጻናትን ሲያዩ እየተቀባበሉ ማቀፍና መሳም በኤርትራዊና  ኢትዮጵያዊ ባህል በጣም የተለመደም ቅቡልም ባህል ነው። የኤርትራ ህዝብ ማሞን እንደ ህጻን በፍቅር አባብሎታል፡  አቅፎታል፡ ተቀባብሎለታል። “እንኳን እግዜብሔር አተረፋችሁ!” የምትለዋ የዚያኔዋ ሐረግ፡ ማሞን ለዚህ አብቅታዋለች።  ዓራርብ፡ ናቕፋ፡ አፍዓበት፡ ከረን በየተራ እንዲደርሳቸው ‘ለኔ’፡ ‘ለኔ’ እያሉ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ተቀባበሉለት –  በሄሊኮፕተር። ያቺ ያኔ ሞት በሽበሽ ሆኖ ወደነበረበት አፍዓበት ጎትታ በመውሰድ ‘ተወጣው እንግዲህ!’ ብላ መጨረሻውን  ሳታይ ጥላው የፈረጠጠችው ሄሊኮፕተር፡ ዛሬ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ፡ የወጣትነት ዘመኑን ያሳለፈባቸውን ቦታዎች  ለማስጎብኘት አዝላዋለች – ልክ እንደ እናት! አዝላም በቀስታ ያለመንገጫገጭ መሬት ላይ አስቀምጣዋለች። አስቀምጣውም  እንደበፊቱ አልፈረጠጠችም። የፈለገውን ቦታ እስከፈለገበት ጊዜ እስኪጎበኝ ድረስ ጸጥ ብላ በትዕግስት ጠብቃዋለች።  ህይወትና ትንግርቷ! ለሞትም በሄሊኮፕተር፡ ለሽርሽርም በሄሊኮፕተር! ጆቴ በሄሊኮፕተሯ ውስጥ ሆኖ ስለዚሁ የህይወት  ግጥምጥሞሽ ሳያሰላስል ቀርቶ ይሆን? ይሄ ህልም አይሉት ቅዠት ነገር (surrealism) ከነዚህ በጣም ረጅም ዓመታት በኋላ  በውን ይደርሳል ብሎ ማን ሊገምት ይችላል? በተለይም ማሞ ፈጽሞ ሊገምተው አይችልም።  

“እንኳን እግዜብሔር አተረፋችሁ!” የምትለዋ ሐረግ፡ ተራ ሐረግ እንዳልሆነች፡ ከነዛ በሞት አፋፍ ላይ ይገኙ ከነበሩና የነዛ  ደጋግ ታጋዮች ርህራሄ የተቸሩት ምርኮኞች በላይ ሊገባው የሚችል ፍጡር ሊገኝ አይችልም። ለነዛ በፍርሃት ሳቢያ  በየሴኮንዱ እየሞቱ የነበሩት ፍጡራን (የመገደያ ጊዜያቸውን እየቆጠሩ ስለነበሩ)፡ ይቺ ሐረግ የመጨረሻዋ እንጥፍጣፊ  ተስፋቸው ነበረች። ያቺን ቃል በሰሙ ጊዜ ከሞት የመመለስ ያክል ጣፋጭ እንደነበረች ከነሱ በላይ ሊመስክር የሚዳዳው  አይኖርም። ሐረጓ ጆቴንና ጓዶኞቹን ከሞት ያስነሳች፡ ዳግመኛ ልደታቸውን ለማክበር፡ ወልደው ለመሳም፡ ስመውም  ለመዳር፡ ድረውም አያቶች ለመሆን ያበቃች ነፍስ ዘራሽ፡ ህይወት አዳሽ ነበረች። ያቺ ሐረግ ለኤርትራውያንና  ለኢትዮጵያውያን አንዲት እንቡጥ ህጻን አምጥታልናለች። ህጻኗን እሽሩሩ እያልን ከጠበቅናትና እንደመማሪያ ከወሰድናት፡ የእውነት ቡቃያ ናትና፡ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክቶች ሲመጡ እንደማጣቀሻ እየተጠቀምን ለወደፊት ጉዟችን የመንደርደሪያ  ነጥባችን ትሆናለች። 

አሁን ጆቴ ተንፈስ ብሏል። ህጻኗን ከቤተሰቦቿ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቿም አስረክቦ ሄዷል። ህጻኗን መንከባከብ  የኛ ድርሻ ይሆናል።  

ጆቴ ከላይ በተጠቀሰው ጋዜጣ (ሓዳስ ኤርትራ) ባደረገው ጭውውት ላይ “ስለ ታሪካችን የምትተርክ እስከሆነች ድረስ  በማሰራጨቷና በማስተዋወቋ በኩል ሁሉም ሰው ሊጥርላት ይገባል” ብሏል። ይኸው እኔም የበኩሌን እየተወጣሁ ነው።  እግዚሄር ከፈቀደም በሚቀጥሉት መጣጥፎቼ፡ ደራሲው በመረጣቸው የአጻጻፍ መንገዶች (የትረካ ሂደት – plot  development፡ የቃላት አመራረጥ – word choice፡ ዘይቤዎች – style፡ መንጽረ-ታሪክ – point of view፡ ቊም ነገር –  theme/s ወዘተ) ተንተርሼ የማወጋችሁ ነገር ይኖራል። የነገ ሰው ይበለን።  

ዋቢ ጽሑፍ 

ሓዳስ ኤርትራ (ሰሉስ 21 መጋቢት 2023)

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here