spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየወልቃይት ጉዳይና ኢትዮጵያዊነት   

የወልቃይት ጉዳይና ኢትዮጵያዊነት   

Ethiopia _ Wolkait _ Tegede

ከጸሀይ

እልቂት በአማራ ሕዝብ ላይ 

ካለፉት 50 አመታት ወዲህ ጎልቶ የሚታየው፤ ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት የሚፈርጀው የጎሳ-ብሔረተኝነትን ያቀነቀነ ርእዮተ-አለም የፖለቲካ ሥልጣን ላይ መውጫ እርካብ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ጎሰኝነት፤ በመጀመሪያዎቹ 17  አመቶች በከረረ ቅራኔና በጭካኔ ላይ በተመሠረተው የደርግ መንግሥት ውስጥ ሠርጎ በመግባትና ከዚያ ወዲህ በሚቆጠሩት 33 አመታት ደግሞ በቀጥታ የፖለቲካ ሥልጣንን በእጁ በማስገባት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እጣ ፈንታ እየወሰነ ይገኛል። 

የጎሳ-ብሔረተኞቹ ለትግል የተጠቀሙባቸው ስልቶች፤ አንደኛ ራሳቸውንም ሆነ ባእዳንን “የሚያሳምኑና” የቅኝ ገዥና ተገዥነት ባህሪያትን የሚያሟሉ አዳዲስ የሀሰት ትርክቶችን በመፍጠር በጋራ መሥርተንና ጠብቀን ያኖርናትንን አገራችንን ኢትዮጵያን በቅኝ-ገዥነት መወንጀል፣ ሁለተኛ እነዚህንም ትርክቶች ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያን ሲወርሩ ከተጠቀሙባቸው የመከፋፈል ፕሮፓጋንዳዎች ጋር በማመሳሰል፤ የኢትዮጵያዊያንን የአብሮነትና የነጻነት ታሪክ በማጠልሸት የውጭ አባሪና የትግል አጋዥ ማመቻቸት ናቸው። በወያኔ ኢህአደግ መሪነትና በኦነግ አባርነት፤ በውጭ ኃያላን ተባርኮ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊቱን አዙሮበት የወደቀውን የደርግ ሥርአት የተካው የመጀመሪያው የብሔር ነጻ አውጭ መንግሥት ሳይውል ሳያድር፤ በኢትዮጵያዊነቱ የጸናውን ወይም ለጎሳ-ብሔረተኝነት ባእድነት የሚሰማውን ሁሉ፤ ወይ በአድርባይነት ወይም በጠላትነት በመፈረጅ መከራውን አሳይቶታል።  

አስተሳሰቡ በፈጠራቸው የህሊና አጥሮችም ሆነ በከለላቸው የመሬት ድንበሮች የተነሳ መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መሄጃ ማጣት፣ መራብና መሞት የበርካታ ኢትዮጵያዊያን እጣ ፈንታ ቢሆንም፤ “በቅኝ-ገዥነት” ለተፈረጀችው ኢትዮጵያ ዋና ተጠያቂ ሆኖ በጠላትነት በመጠቆም ለከፋ አፈናና የተናጠልም ሆነ የጅምላ ግድያን ለሚያካትት መከራ ልዩ ኢላማ የሆነው፤ “ኢትዮጵያ… ኢትዮጵያ” የሚለው የአማራ ሕዝብ መሆኑን በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚኖር ሁሉ ያውቀዋል። 

ከ2018 (እኤአ) ጀምሮ “ከዚህ ጥፋ” እየተባለ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተደገፉ የተለያዩ ታጣቂዎችና በኦሮሞ ነጻ  አውጭ ሠራዊት እርስት ጉልቱን መነጠቅና፣ ሀብት ንብረቱን መዘረፍ ብቻ ሳይሆን፤ ሰው ለመባል የሚያስችል ባህሪ  ያለው ፍጥረት ይፈጽመዋል የማይባል አረመኔያዊ ጭካኔ የታየበት ጭፍጨፋ እየተፈጸመበት ነው። ጭፍጨፋው በቤንሻንጉል ክልልና በሌሎችም ቦታዎች ተከስቷል። አማራን የማጥፋት ዘመቻው በዚህ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በርካታ  የተለያዩ ዘርፎች አሉት፤ አልፎም አማራ በሰላማዊ መንገድ ተበደልሁ ብሎ መጮህና ተቃውሞ ማሰማትም የተከለከለ  ሕዝብ ነው። ጸጥ ለጥ ብሎ መገደልና መሳደዱን እንዲቀበል ነው የሚጠበቅበት። የአማራን ሕዝብ ጩኸት ሊያሰማ  የሞከረ ጋዜጠኛ፣ ምሁር፣ የፓርላማ አባል፣ ማንኛውም ንቁ ዜጋ፤ አማራም ባይሆን እንደ ታዲዎስ ታንቱ የሰብአዊነትና  የኢትዮጵያዊነት ህሊናው የሚያስገድደው ሁሉ፤ ድምጹን፣ መብቱንና ነጻነቱን ተገፍፎ በህሊና እስረኝነት ይማቅቃል።   

ወልቃይት ጎንደሬዋ 

የአማራን ዘር የማጥፋት ዘመቻው ዛሬ በሰፊው ይካሄድ እንጅ የተጀመረው ከ50 አመት በፊት ነው፤ ከሚታወቁት ጉልህ  ዘመቻዎች መሀል በጭካኔው ጉልህ የሆነውን የወልቃይት ታሪክ ይናገራል። የወልቃይትን ጎንደሬነትና አማራነት በጽሁፍ  የተደገፉ የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ1። በሕይወት ያሉና እድሜያቸው ከሃምሳ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም ሊመሰክሩ  ይችላሉ። የሕወሓት መስራቾችም ሆኑ ቀደምት የአካባቢው መሪዎች ተፈጥሮአዊ ድንበሩን ጠንቅቀው ያውቃሉ።  

ሕወሓት ገና ከደርግ ጋር መዋጋትን ሲያቅድ ጀምሮ፣ ጎን ለጎን ያካሄደው “ወልቃይትን ከነባር ኗሪዎቿ ማጽዳት” ነበር። በዚህ እቅድ መሠረትም ለ17 አመታት ያህል፤ ቃል በቃል የዘር ማጽዳት የሚባል ተግባር እንዳካሄደ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ተመራማሪዎች የከፈቷቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮችና ከሞት አምልጠው ዛሬ በሕይወት ያሉት ወልቃይቴዎች  

ይመሰክራሉ2 3። ማእከላዊ ሥልጣኑን በእጁ ያስገባውና መላዋን ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው፣ ፈላጭ ቆራጩ ሕወሓት  ምን ጎድሎበት ነበር ነባሩን ሕዝብ ማጽዳት ያስፈለገው ቢባል፤ መልሱ አንደኛ አገሪቷን በክልል ከሸነሸነ በኋላ ተከዜን  ተሻግሮ ከአማራ ክልል መሬት ቆርጦ በመውሰድ የትግራይን ክልል የማስፋትና ታላቋን ትግራይ የመፍጠር ቅዠት  ስለነበረው ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ ለአለማት ለታላቋ ትግራይ የዳቦ ቅርጫትና የሱዳን መውጫ በር ስለሚያስፈልገው  ነበር። ወልቃይት ለምም ወደ ሱዳን መውጫ በርም በመሆኗ ሁለቱንም የሕወሓትን ፍላጎቶች ታሟላለችና፤ በወልቃይት  አማራ ላይ የተፈጸመው እልቂት ከወያኔ “የነጻነት ትግል” መጀመሪያ ቀን ጀምሮ የታቀደ መሆኑ ግልጽ ነው።  

ወያኔ ሕወሓት በእቅዱ መሠረት በጭፍጨፋና በማፈናቀል ነባር ኗሪዎቹ ላይ የዘር ጽዳት ከፈጸመ በኋላ፤ የወያኔ ታጋይ  የሚባሉትንና ቤተሰቦቻቸውን በብዛት በማስፈር ምርታማ የሆነውን ለም መሬት እንዲከፋፈሉ አደረገ። ከዚያ ቀጥሎ  ወያኔ ወልቃይትን “ምእራብ ትግራይ” ብሎ በመሰየምና ሌሎችንም የአማራ ግዛቶች፤ ጠለምትንና ራያን በማካተት አዲስ  ካርታ ሳለ። ስለካርታው የመሬቱን ባለቤቶች፣ ተጎጅዎችን፣ ማንም አላማከራቸውም፣ የተፈጸመባቸው ታላቅ ዝርፊያም  እውቅና አላገኘም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ የተረፉት ነባር ኗሪዎች በመሣሪያም ሆነ፣ በሕጋዊ መንገድ ማንነታቸውንና ህልውናቸውን ለማስከበር የማያቋርጥ ትግል ሲያደርጉ ኖረዋል። ብዙ ሽህዎቹም ሕይወታቸውን ገብረዋል። ከ30  አመታት ኋላ በ2021-2022(እኤአ) በወያኔና በመንግሥት መካከል የተደረገው ጦርነት፤ ለአማራ ወልቃይትን የማስመለስ  እድል ፈጥሮለታል። ሕገ-መንግሥቱ ወልቃይትን የትግራይ ክፍል አድርጎ አያያትም። ባጠቃላይ ሕገ-መንግሥቱ  በክልሎች መሀል ስላለ የውስጥ ድንበር አይናገርም። 

“አሸናፊ ነን” ባዮቹ፤ ወልቃይትን እራሳቸው ለራሳቸው ያበረከቷት “የድል መሽሞንሞኛ” አድርገው ስለሚቆጥሯት  ከ“ይገባኛል” ባይነት መውጣት አይፈልጉም። በወልቃይት ነባር ሕዝብ ላይ ምን አይነት የጭካኔና የግፍ እልቂት  ፈጽመው፣ ምንስ አሻጥር ሠርተው እጃቸው ውስጥ እንዳስገቧት እንዳይነገርም በርትተው መከላከል ይቀጥላሉ።  አሜሪካኖቹም ይሄን የወልቃይትን “የድል መሽሞንሞኛ” መደረግ ባርከው እውቅና እየሰጡ ይመስላል። 

በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት ማይክ ሀመር፤ በ7 ማርች ተጀምሮ እስከ 13 ማርች አዲስ-አበባ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት አስተናጋጅነት በተካሄደው በብልጽግና መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈጸመውን “የፕሪቶርያ” ድርድርን በተመለከተ የተደረገ ስልታዊ ግምገማ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ያስተላለፏቸው መልእክቶች ምን ያህል ለኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከተጨነቀ ወዳጅነት የመነጩ ይሆኑ? መልእክተኛው ተፈናቃዮች ወደቦታቸው ይመለሱ በማለት ስለአንደኛው ወገን ብቻ የተጨነቁ የሚያስመስል አስተያየት ከመሰንዘር ባሻገር፤ የጉዳዩን ክብደት ተገንዝበው የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ ለማነጋገር ምን ያህል ፍላጎት አሳይተዋል?  

በብልጽግና መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተካረረው ግጭት የጫረው የእርስ-በርስ ጦርነት፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ተሻግሮ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል። የአማራ ክልል የጦር ሜዳ ተደርጎ፣ ሕዝቡ የተፈጸመበት እልቂት፣ ስደትና የሀብት ውድመት የብዙ አስርተ-አመታት የፈተና ጊዜ ተሸካሚ አድርጎት እንዳለፈ በብዛት ተነግሯል። ዛሬ ደግሞ ከዚያ ለመውጣት ዳዴ ማለት ሲጀምር፤ በአገሪቱ መከላከያ ኃይል ወረራ ተፈጽሞበት በሕልውና ትግል ላይ ይገኛል። በጦርነቱ የተጎዱት ሁሉም አካሎች በፕሪቶሪያው ድርድር ተካፋይ አለመሆናቸው ስህተትነቱን በመገንዘብ አዲስ ሁኔታ መፍጠር የወዳጅነት ተግባር በተባለ ነበር። የኢትዮጵያ ሰላም መደፍረስ ጥቅማቸውን እንዳይጎዳ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች፤ የወልቃይት ጉዳይ ከሕወሓት ጥቅም አኳያ እንዲፈታ እውቅና መስጠት፤ መጨረሻ ለሌለው ከትውልድ ትውልድ ለሚተላለፍ ግጭት መንገድ ከመክፈት የተለየ ሆኖ ሊታይ  አይችልም።  

ኢትዮጵያዊነት እንደ መፍትሔ 

የወልቃይት ጉዳይ መነሻውም፣ አካሄዱም ሆነ ያለበት ሁኔታ፣ የተጓዝነው ጉዞ የደረሰበትን የገደል አፋፍ ያመለክታል። ገደል ላለመግባት ከወሰንን፤ መፍትሔዎች አናጣም። ነገር ግን፤ ሲሆን ሁላችንም፣ ሳይሆን ደግሞ ብዙዎችችን ገደል አለመግባትን አጥብቀን መፈለግ ይኖርብናል።  

ከ50 አመታት በፊት የጋራ የሚመስል አንድ ሕልም ይዘን ተነስተን ነበር- አገራችንን ወደፊት ለማስሄድና ሕዝባችንን ለማገዝ፣ ጉድለታችንን በጋራ አስተካክለን፤ የምናፍርበትን አስወግደን የምንኮራበትን አጉልተን፣ በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ እኩልነት አረጋግጠን፣ በነጻ ዜግነት ላይ የተመሠረተ አገራዊ አንድነትንና ሉአላዊነትን ልናሰፍን የተነሳን ይመስል ነበር። ከአያት ቅድመ-አያቶቻችን የወረስነውን፤ ነጻነታችንን በውጭ ጣልቃገብነት አለማስደፈርን አብረን እየጠብቀን፤ ከዘመናችን የአለም ትውልድ ጋር ደግሞ አለም-አቀፋዊነትን አብረን ለማራመድ የተነሳን ይመስል ነበር። ለሰብአዊ መብትና ለፍትህ አብሮ መቆም ብቻ ሳይሆን አብረን ለሞመት የተነሳሳን ይመስል ነበር። የሁላችንንም ፍላጎት የሚያስተናግድ ኢትዮጵያዊነት፣ ወይም ኢትዮጵያዊ-ብሔረተኝነት ለማቀንቀን የተነሳን ይመስል ነበር። 

በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተወለደ ግለሰብ፤ ሰብአብዊ መብቱና ነጻነቱ፣ እንዲሁም ዜጋዊ መብትና ግዴታው በሕግ ፊት በእኩልነት መታየቱ፣ መከበሩና ደህንነቱ መረጋገጡ ነው የኢትዮጵያዊነት መሠረቱ። ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በላይ ከተስፋፋው ረሃብ፣ መፈናቀል፣ ስደትና እልቂት ለመትረፍ፤ ከአፋኝ ጨቋኞች መዳፍ ሥር ወጥተን በሰላምና በነጻነት፣ በመተማመንና በመተጋገዝ ላይ በተመሠረተ እኩልነት መኖር ነው አማራጫችን። ይህ አማራጭ በአለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተፈተነና የተሻለ መፍትሔ ሆኖ የሚታይ ነው፤ ኢትዮጵያውያንም እድሉ በእጃቸን ነው። የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብቱ የአገሩን መሪዎች እስከመምረጥና በመሪነትም እስከ መመረጥ ድረስ መሆኑ እውቅና አግኝቶና ሙሉ መብቱና ነጻነቱ ተረጋግጦ በሕግ እስካልተከበረ ድረስ፤ ከትውልድ ትውልድ በሚሸጋገር ግጭት ውስጥና በጊዜያዊ ድል-አድራጊዎች ጭቆና ሥር ከመዳሸቅ የሚያድነው አማራጭ እንደማይኖር ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። የአገር መሪ፤ ለአገርና ለሕዝብ ታማኝነቱ የታወቀ፣ ለሕግ ተገዥነቱ የተረጋገጠ፣ እውቀቱና ብቃቱ የተሟላ እንጅ፤ በጎሳው/በብሔሩ፣ በእምነቱ፣ በዘር-ግንዱ ወይ በጾታው የተመረጠ መሆን አይገባውም። ማንኛውም ዜጋ ነጻ የሆነ የመራጭነት፣ ያስመራጭነትም ሆነ የተመራጭነት መብቱ በተግባር እንዲተረጎም መሟላት ያለባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አሉ።  

ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትን እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች ቢኖሩም፤ ባለፉት ሃምሳ አመቶች በተካሄደው ከፋፋይ ፖለቲካ የተደረገበት ተጽእኖ ምን አይነት ሥነ-ልቦናዊ ስብራት እንዳደረሰበት የሚያሳይ በጥናት የተደገፈ መረጃ መኖር አለመኖሩን ግን መመርመር ያሻል። ሆኖም ግን በደርግ ጊዜ በድብስብስ ተጀምሮ፤ ካለፉት 35  አመታት ወዲህ ግን በገሀድ፤ በከፋፋዩ የጎሳ ብሔርተኝነት ርዮተ-አለም ኢላማ በተደረገው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን የተናጠልም ሆነ የጅምላ አፈናና ግድያ የሚቃወም፤ አገር-አቅፍ የሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አለመታየቱ ከላይ የተጠቀሰውን ሥነ-ልቦናዊ ስብራት የሚያመለክት ይሆን ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።   

1አቻምየለህ ታምሩ (2012)። የወልቃይት ጉዳይ- የወልቃይት፣ ጠለምት እና ሁመራ የወሰንና የመልክዓ – ምድር ታሪክ መርምር ውጤት  (ከ323 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም.)

2 https://borkena.com/2022/04/05/wolkait-mass-grave-researchers-say-tplf-had-killed and-tortured-about-59000-people/ 

3 ወረራና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ (የጥናት ቡድን)

___

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here