spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአዲስ አበቤን አስቀይሞ የፀና ስልጣን የለም!

የአዲስ አበቤን አስቀይሞ የፀና ስልጣን የለም!

Ethiopian News _ Addis Ababa
የፎቶ መግለጫ፦ ከፍትህ መጽሄት የሶስተኛ ዓመት ቁጥር 137፣ ሰኔ 2013 ዓ.ም የፊት ገጽ (ከቨር ፔጅ) የተሰወሰደ ነው፡፡  

በዚህ ጊዜ ስለ አዲስ አበባ መጻፍ መቼም ንዴትን እና ቁጭትን በህዝቡ ላይ መጨመር መስሎ ይታየኛል፡፡ በአንጻሩ አለመጻፍ ደግሞ ከአፍራሾቹ ጋር የተባበርኩኝ ያህል ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ስሜቴን ለመግልጽ፣ እንዲሁም የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ይህችን ጽሁፍ ጀባ ልበል፡፡

አዲስ አበባ እንኳን እንደኔ ተወልዶ ላደገባት ይቅርና ለመጤው በተለይም አሁን ላይ ታሪኳን ለማጥፋት ለሚራወጡት ሳይቀር ሲሳያቸው፣ እንጀራቸው፣ ደምቀው መታያቸው፣ እንደ መጤ የማይቆጡሩባት፣ ሰርተው የሚለወጡባት፣ ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ የሚበቁባት ከተማ ነች፡፡ ምን ዋጋ አለው እነዚህ በልቶ ካጆች፣ ያጎረሰች እጇን ነክሰው ታሪክ አልባ ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው እያፈራረሷት ነው፡፡

‘አዱ ገነት’ ይሏታል ያራዳ ልጆች፣ ምክንያቱም ገንዘብ ከፍሎ መብላት ለማይችለው አብልታ፣ ደግሞ በትንሽ ብር አፉን አብሶ እንዲውል አድርጋ፣ እንደ አቅሙ ሁሉም ማደሪያም ሆነ መዋያ የማታሳጣ ድንቅ ከተማ ነች፡፡ የትኛውንም የክፍለ ሃገር ሰው ብትጠይቁ “አዲስ አበባ ጾም አይታደርም” ይላችኋል፡፡ እውነት ነው እንኳን ሰርቶ ቀርቶ ለምኖ ጾም የማይታደርባት ከተማ ናት፡፡ ታዲያ አዱ ገነት መባል ሲያንስባት ነው፡፡

እምዬ ምኒልክ ከቆረቆሯት በኋላ፣ ባንክ አቁመው ህዝቡ ገንዘብ እንዲቆጥብ ሲያስተምሩ፣ ሆቴል ከፍተው እንዲዝናና ሲያደርጉ፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ተክለው የተራራቀን በቀጭኑ ሽቦ ሲያገናኙ፣ ሲኒማ ቤት ሰርተው ህዝብ የስልጣኔው ተካፋይ ሲያደርጉ፣ ባቡር የሳምንታት እና የወር መንገደን በቀን አሳጥረው ዘመድ ከወዳጁ እንዲገናኝ አደረጉ፣ መኪና አስመጥተው ዓለም የደረሰበትን ስልጣኔ ህዝባቸው እንዲካፈል አደረጉ፡፡ ዘመናዊነትን፣ ከዓለም ጋር መቀራረብን ለህዝባቸው አስተምረው አለፉ፡፡ አጼ ምንይልክ ያቆሟትን ከተማ ዘምን የሰጣቸው ቅሎች ታሪኳን ለማጥፋት ይባትላሉ፡፡ መስሏቸው እንጂ ታሪኩን ከቦታው ቢያነሱትም ከልባችን ፈጽሞ አያጠፉትም፡፡

ብልጽግና = ጸረ ታሪክ

ባለፉት አምስት ዓመታት ስልጣን ላይ ያለው የብልጽግና አገዛዝ ከወያኔ የተማረውን ታሪክን፣ እምነትን እና ባህልን የማጥፋት አቅድ ከምንግዜውም በላይ እያፋጠነው ነው፡፡ ምናልባት እነዚህን አካላት የሚያዛቸው አንዳች መንፈስ እያሯሯጣቸው ይሆን ???  ምናልባት ደግሞ ያላቸው ጊዜ አጭር ስለሆነ ይሆእናል ያለእረፍት ከተማዋን የሚያተራምሷት ? ለማንኛውም በዚህ ከልክ ባለፈ ድርጊታቸው የህዝብ ጩኸት ከፍ ሲል በአፋቸው “ኧረ እአ ታሪኩን በሚመጥን ሁኔታ ለመስራት ነው” ፣ “ለትውልድ የሚሻገር ስራ እየሰራን ነው”  ወይም “ እኛ የሃገር ቅርስን እንጠብቃለን እንጂ አናፈርስም” … ወዘተ ይላሉ፡፡ ተግባራቸው ግን ቀን እየጠበቁ አንድ በአንድ ማፍረስ፣ በሌላ የተጣረሰ ስራ ይመጥዐሉ፡፡ (አንበሳን በፒኮክ መቀየር ፣ ታሪክን በተረት መበረዝ…)  

ለአብነት ጥቂቶቹን ላንሳ፣ ሰንጋ ተራ የሚገኘውን የሎምባርዲያን ካፌ በቅርስነት ቢመዘገብም እነ ምን-ግዴ ድምጥማጡን ለማጥፋት ቀን አላባከኑም፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ በመንገድ ማስፋት ሰብብ ሌላኛውን ቅርስ የራስ አበበ ወልደአረጋይ ት/ቤት እንዲፈርስ ተደረገ፡፡ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ የሚያደርሰውን ባቡር መነሻ ላጋር (ለገሃር) አፈረሱት እንዳይባል ይሄን የሃገር ቅርስ ለባእድ አሳልፈው ሸጡት፤ ባለበት ለታሪክ ቢቀመጥ፣ ትውልዱ እየሄደ ቢጎበኘው፣ ሃገርም ከዚህ ብትጠቀም ምን ነበረበት ? ፋሽስት ጣሊያን ‘መርካቶ ኢንዲጂኖ’ ብላ የሃገሬ ሰው እንዲገበያይ ለከተሜው የተወችለትን በአፍሪካ ሰፊውን የመሬት ገበያ መርካቶንም ቀስ በቀስ ከነበረው የንግድ ጠባዩ እየቀየሩት እየሸራረፏት ነው፡፡ 

ከአራት ኪሎ ቀበና ያሉት የመንዱን ዳርና ዳር ይዘው የተሰሩ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቤቶችም በመንገድ ማስፋት ስም እየፈረሱ፣ ቦታዎቹ ለባለሃብት እየተቸበቸቡ ነው፡፡ በሸገር ወንዝ ልማት ስም የስንቱ ቤት ፈረሰ፣ ስንቱ ታሪክ ጠፋ? ፍል ውሃ (አምባሳደር) ፣ ፊት በር ፣ ዶሮ ማነቂያ… አዲስ አበባ ውስጥ ያልፈረሱት አካባቢዎች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ 

ሰሞኑ ደግሞ የስንቶቹ መቀጣጠሪና የተዳር መሰረት የሆነችው፣ ለብዙዎች ጊዜ ማሳለፊያ፣ ለአንዳንዶች ደግሞ የእንጀራ ገመዳችው፣ ለሃብታሞች ማጌጫቸው፣ ለድሆች ቁራሽ ማግኛቸው… በእግር ለማዝገም ቢሉ አረፍ ብለው የሆድ የሆድን ከወዳጆ ለማውጋት የምትመቸው፣ ከክበብ እስከ ክለብ ሁሉ በእጇ ሁሉ በደጇ የሆነችው፣ የሰፈሮች አድባር ፒያሳን እነሆ ያለ ርህራሄ ወደ አፈርነት እየቀያየሯት ነው፡፡ በፋሽስቱ ጣሊያን የአምስት አመት ወረራ ወቅት የውስጥ አርበኞች የተገረፉበት፣ ከነጻነት በኋላ ከያኒያን ሀገራዊ ትእይንቶችን ያሳዩበትን ለህዝብ ጀባ ያሉበት የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደጃፉ ድረስ አርሰውታል፡፡ የሃገራችን የመጀመሪያው ሃኪም እንደሆኑ የሚነገርላቸ የሃኪም ወርቅነህ ቤት ወድሟል፡፡አያሌ ሙዚቃ ቤት፣ ታንጎ ሙዚቃ ቤት፣ ዶሮ ማነቂያ (ከስጋ ቤቶች እስከ አትክልት ቤት፤ ከቁርስ ቤት እስከ ሬስቶራንት፣ ከጠጅ ቤት እስከ የመጠጥ ግሮሰሪና የምስት መዝናኛ፣ ለዘመናት ከነበሩ ኬክ ቤቶች እስከ ዘመናዊ ካፊቴሪያ…) ያለ ርህራሄ ፈርሰዋል፡፡ ለዚያውም ለሶስት ወር ጌ ተሰጥቷቸው እና ለአድዋ  00 ፕሮጀክት ምርቃት ሲባል አድሱ ተብለው በአስር ቀናት እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡

ወደ ታች  ደግሞ አንበሳ ፋርማሲን እና የሰይጣን ቤትን አይሆኑ አድርገውታል፡፡ ወይ በትክክል አልሰሩ ወይ አልፈረሱ እነዲሁ ተገስጠዋል፡፡ ምናልባት ዙሪያቸው ፈርሶ  እስኪያልቅ ቀናቸውን እየተጠባበቁ ይሆናል፡፡ አራዳ ህንጻ ላይ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚውን ማማተር የለ ፤ አሊያም ደጃች ውቤ ሄዶ ከጓደኞች ጋር ሻይ ቡና ማለት አይታሰብም፡፡ ደጃች ዉቤን ካፈረሱት ከርመዋል፡፡ ቀጥዐዩ ደግሞ ጣሊያን ሰፈር፣ ሰባራ ባቡር ነው፡፡ እግዚኦ ጭካኔ !!!

መቼም ፒያሳን እንኳን በኔ እድሜ ያለ ይቅርና፣ አባቶቻችን ሲያውቋት ሲኖሩባት እስካሁን ሲሳሱላት የነበረች የአራዶቹ ሰፈር፣ በዘመን አመጣሾቹ ግባተ መሬቷ እየተፈጸመ ይገኛሉ፡፡ ፒያሳን ስትፈርስ እንደማየት ልብ የሚሰብር ነገር ምን አለ? በዚህ የማያዝን መቼም… 

ከመዝናኛ ስፍራ እስከ መስሪያ ቦታ፣ ከካፌ እስከ መሸታ ቤት፣ ከዘመናዊ ገበያ እስከ ሱቅ በደረቴ፣ ከቱጃር እስከ ደሃ አሰባጥራ ያቆየችውን ፒያሳን፣ ታሪክ የማያውቁና የማይወዱ አፈራረሷት፡፡ ለእነሱ ብልጭልጭ ነገር ብርቃቸው ነው፡፡ አሮጌ ታሪካዊ ቤት ከሚኖር ይልቅ ዘመናዊ ህንጻ መስራት ትልቅ ነገር ነው፡፡ የታሪክ አተያያቸው የተንሸዋረረ፣ በተረት የተሞላ ስለሆነ ቆመው የነበሩት የአዲስ አበባ ዘመናት ያስቆጠሩ ታሪካዊ ቤቶችና ቅርሶች ስሜት አይሰጧቸውም፡፡ እንዲያውም ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ስለቆረቆሯት የሚበሳጩ እና የእሳቸውን አሻራ ለማጥፋት የሚውተረተሩ ይመስለኛል፡፡  

መፍትሄው ምንድነው? 

እየሆነ ባለው ነገር የህዝቡን ቁጣ እና ስሜት ለመረዳት መቼም ነብይ መሆን አይጠበቅም፡፡ በቀላሉ ማህበራዊ ሚዲያውን አይቶ ድምዳሜ መስጠት ይቻላል፡፡ መሬት ላይ ያለው ነገርስ ከዚህ የከፋ ለመሆኑ አስረጂ አያስፈልግም፡፡ ለማንኛውም መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ አዲስ አበቤውን አስቀይሞ ሰላም አገኛለሁ ማለት ካለፈው አገዛዝ አለመማር ነው፡፡ በቀጣይ ምርጫ የአዲስ አበባ ነዋሪም ይሁን መላው ኢትዮጵያዊ (ይሄ ታሪክ የማጥፋት ሂደት የሚያንገበግበው) ይሄን ጸረ ታሪክ፣ ጸረ ህዝብ የሆነን አገዛዝ በምርጫ ካርዱ የመቅጣት ትልቅ አደራ አለበት፡፡    

ህዝቡን በኑሮ ውድነት እያማረሩ፣ እንዳይገባ እንዳይወጣ እያደረጉ ፣ በፖለቲካው ባይተዋር እንዲሆን እየሰሩ፣ካደገበት ቀዬ ያለበቂ ካሳ እና ክፍያ እያፈናቀሉ እና እምነቱን፣ ታሪኩን፣ ትውፊቱን፣ ባህሉን እንዳያከብር እያስቸነቁ፣ በሚወደው እና በሚያከብረው (ቀይ መስመሩ) እየመጡበት የሚጸና መንግስት አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ደግመው ያስቡበት ፤ አይሆንም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ሲወድድ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በአንጻሩ ሲጠላም ምን ማድረግ እንደሚችል ራቅ ሲል ከፋሽስት ጣሊያን ከቀረብ ሲል ደግሞ ከወያኔ መማር ይቻላል፡፡ አሊያም ህዝቡን እንደፈለግኩት እያደርግኩኝ በባዶ ዲስኩርና በብልጭልጭ እያታለልኩኝ እዘልቃለሁ ማለት ጉም እንደ መጨበጥ ይቆጠራል፡፡

የቁጭቴን መጣጥፍ በዚህ የአሌክስ አብርሃም ጽሁፍ ላጠቃልል፡፡ “…ምንድነው ለጠላ ቤቱም ለጠጅ ቤቱም ትዝታ እያሉ ማለቃቀስ?” የሚሉ ሰዎች የተወለዱበት መንደር ላለ ቋጥኝና ዛፍ፣ ለምንጭና ለሞተች ላማቸው [ከብታቸው] ሳይቀር በትዝታ አይናቸውን ጨፍነው እየተንሰፈሰፉ የሚዘፍኑ ሁነው ታገኟቸዋላችሁ!” 

ሰላም ለሃገራችን 

___በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News

ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here