spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeነፃ አስተያየትመልካም አስተዳደርና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት   

መልካም አስተዳደርና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት   

በእስያኤል ዘ ኢትኤል  
መጋቢት 14 /2016 ዓ.ም ካንሰስ ከተማ፣አሜሪካ 

ኢትዮጵያ ከ3000 አመታት በላይ ያለፈ የስርዓት መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ስትሆን በተለያዩ  ዘመናት ነገስታትና መንግስታት እየተፈራረቁባት ሲያስተዳደሯት፤ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን  በመገንባት ህዝባቸውን በሚችሉትና በተቻለ አቅም፣ በተረዱት ልክና ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንዲሁም  ህዝቤ ያስፈልገዋል ብለው ያመኑበትን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡  

እንደ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ “መንግስት እና የህዝብ አስተዳደር” በሚለው መጽሐፋቸው  የመንግስት ዋና ተግባርዎች ካሏቸው ውስጥ ሰላም ማስጠበቅ፣ እውቀት እና መሰረተልማት  ማሟላት፣ ለአንድ ሀገር ትልቁ የእድገት መሰረት መሆኑንና እዚህም ከፍተኛው የመንግስት ስራዎችና  ሃላፊነቶች ናቸው በማለት ያብራራሉ፡፡ መንግስታት ለህዝባችን ይጠቅማል ብለው የሚያስቡትን  አስተዳደር አይነትና ሰርዓተ-መንግስት በመምረጥ ህዝባቸው በብልጽግናና በሰላም እንዲኖር የማድረግ  ሀላፊነታቸውን ተጠቅመው ህዝባቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ 

ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ለመፍጠር ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚ  ሊባል የሚችለው መልካም አስተዳደር እንደሆነ የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ  ምሁራን ምልከታ መሰረት በመንግስትና ህዝብ መካከል በመተማመንና በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ  ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው የመንግስት ስርዓቱ አስተማማኝ የመልካም አስተዳደር ሁኔታን መገንባት  ሲችል ብቻ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር የሚገለፅባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ የተባበሩት  መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የህግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊነት፣ አሳታፊነትነና  ግልጽነት ዋነኛዎቹ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች መሆናቸውን ያትታል፡፡ ኮሚሽኑ በማያያዝም  ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የሚገለፁበት መልካም አስተዳደር በማንኛውም አገር ውስጥ ዘላቂ  የኢኮኖሚ እድገትንና አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑንም ይጠቁማል፡ ፡ መልካም አስተዳደር በሰፈነበት አገር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠ በመሆኑ የዜጎች ቅሬታ  በእጅጉ ይቀንሳል፤ የዚህ ዓይነቱ አስተዳደር የዜጎችን ሁለንተናዊ አገራዊ ተሳታፊነትና ባለቤትነት  የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሚወጠኑ የመንግስት የልማትም ሆነ ሌሎች አገራዊ ፋይዳ ያላቸው  ፖሊሲዎች ህዝባዊ መሰረትን ይጎናፀፋሉ፤ ይህም ዜጎች ለአገር የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ በአንድም  ይሁን በሌላ መልኩ ጉዳት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  እንዲሳኩ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ የማይሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡  

ዜጎች ከመንግስት የሚጠብቋቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን በሚፈልጉት ጥራት፣ ፍጥነትና ብቃት  ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ የሚፈጠረው ጠንካራ መልካም አስተዳደር በሰፈነበት ስርዓት ውስጥ  ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ በህዝብና በመንግስት መካከል ጠንካራ መተማመንን እንዲኖር  ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ሰላምና መረጋጋጥ እንዲጠናከር፣ እድገትና ብልጽግና እውን እንዲሆን፣  በተጋገዝና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነትን ለማምጣት መልካም አስተዳደር ሁነኛው  መንገድ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ስንል በህዝብ ተቀባይነት ያለው አስተዳደርና ተቋም ማለት  ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ሙሉ በሙሉ እውን ከማድረግ አኳያ ከላይ የተጠቀሱት የመልካም  አስተዳደር መገለጫዎችን በተናጠል ማየት ያዳግታል፡፡ እያንዳንዱ የመልካም አስተዳደር መገለጫ  በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እርስ በእርሱ የተቆራኘ በመሆኑ አንዱን ከሌላው ነጥሎ ማየት አግባብ  አይሆንም፡፡  

እላይ በጥቂቱ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ዜጎች ከመንግስታቸው የሚጠብቁትን መሰረታዊ አገልግሎት  በአግባቡ ማግኘት ካልቻሉ በመንግስታቸው ላይ ያላቸው እምነት ይሸረሸራል፤ መንግስታቸው  የሚወጥናቸውን የልማትም ይሁን ሌሎች ፖሊሲዎች ለማስፈጸም የሚኖራቸው ተነሳሽነት በእጅጉ  ይቀንሳል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነም አገርን ሰላምና  መረጋጋት በማሳጣት ቀውስ ውስጥ ሊከት እንደሚችል በተለያዩ ምሁራን የቀረቡ ጥናቶች በተጨባጭ  አረጋግጠዋል፡፡ 

በአገራችን በተለይም አዲስ ወይም ዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት ከተመሰረተበት ካለፉት አስርት  ዓመታቶች ወዲህ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በስፋት እየታዩ ስለመሆናቸው  የብዙዎቻችን ትዝብት ነው፡፡ ከንጉሳዊ አስተዳደር መውደቅ በኋላ የተተካው የደርግ መንግስት  ተከትሉ የመጣው አስተዳደር የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያላደረገና አዲስ ልምምድ ያመጣ ሲሆን  በተለይም የፖርቲ ፖለቲካ እየተዋወቀበት የመጣበት ሲሆን የመንግስት መንበሩን የተቆጣጠሩ  አካላት መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን በተለይም የተቋማትን ግልጽነትና ገለልተኝነት በማሳጣት  ለእኛ ብለው ላቋቋሙት ፖርቲ ጥቅም መገልገያ ሲያደርጉት እስካሁን ቆይተዋል፡፡ 

የመልካም አስተዳደር የአንድ ሀገር ቀጣይነት ያለውና አውንታዊ ሰላም የሚያመጣና የሚያጸና  ሲሆን እነዚህም የህዝብ ተቋማት ለእነዚህ ፖርቲ ጥቅም በምናውልበት ወቅት ህዝቦች የመልካም  አስተዳደር እጦት ይገጥማቸዋል፤ተቋማቱ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ህዝብን የመጮቀኝ መሳሪያ  ይሆኑሉ፡፡በዚህም ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ምስቅልቅል ውስጥ ትገባለች፣ውድመት ይከሰታል፣ ሀገር  ሰላም ታጣለች፣ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ እልቂት ይከሰታል፡፡ እነዚህ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር  ከሚጠቀሙባቸው ተቋማት ውስጥ መካከል የሀገር መከላከያ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣  የፖሊስ ሰራዊትና ከፀጥታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት ሲሆኑ እነዚህን ተቋማት የህዝብ  ተቋም ባለማድረግና ላልተፈለገ አላማ እንዲውሉ በማድረግ የሀገሪቷን ሰላምና መረጋጋት በማወክ  ዜጎች ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ እላይ መንግስታቶች በተቀያየሩ ቁጥር  ከሚጠቀሙባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ ስለሆነው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም አንዱና  ዋነኛው ሲሆን ስለዚህ ተቋም ታሪካዊ ዳራ፣ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና  ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ 

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አጭር የኋላ ታሪክ 

በአፄ ሀይለሥላሴ ዘመን 

የመረጃና ደህንነት ስራ በኢትዮጲያ የተጀመረው በአፄ ሐይለስላሴ ዘመን ከ1937-1955ዓ.ም ባለው  ጊዜ ውስጥ መሆኑን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር  “የፀጥታ ጠቅላይ መምሪያ” በሚል ተቋቁሞ የአገርና የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮ ተሰቶት  ይሰራ ነበር (ከዚህ በፊት በአፄ ሚኒሊክ ዘመን የመጀመሪያው መጠሪያውን እንደሆነ የሚገለጽለት  “የሚስጥር ዘበኛ” በሚል ተቋቁሞ የተለያዩ የደህንነት ስራዎችን ሲሰራ እንደነበረ መዛግብት ያሳያሰሉ)፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ የአርበኞችን ተቃውሞ መከላከል፣ጣልያኖች በዘረጉት የክልሎች የከፋፍለህ  ግዛ በተፈጠሩ የክልላዊ አስተዳደሮች ሊነሱ የሚችሉ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠርና ከጣልያን ወረራ  በኋላ የነበረውን አለመረጋጋት መቆጣጠር ዋነኛው ተግባሩ ነበር፡፡

በተጨማሪም የፀጥታው ጠቅላይ መምርያ በወቅቱ በነበሩ የስጋት ትኩረቶችን መሰረት አድርጎ  በመዋቅሩ የእስልምና ክፍል፣ የኮሚኒስት ክፍል፣ የአየር መቆጣጠር ክፍል ፣የአረብ ክፍል እና  የምስራቃውያን ክፍል የሚባሉ አካሎች ነበሩት፡፡ 

በ1953 ዓ.ም. በነበረው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ ግን ተቋሙ አወቃቀሩን በሁለት  በመክፈል በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ድርጅት፤ እና በንጉሱ ፅ/ቤት ስር  የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ልዩ ካቢኔ በሚል እንደገና ተዋቅሯል፡፡ የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ድርጅት ተልዕኮ  የስለላና ፀረ-ስለላ ስራ ሲሆን የንጉሰነገስቱ ልዩ ካቢኔ ተልዕኮዎች ደግሞ የካቢኔ አባላቱን፤ የሰራዊት  ሀላፊዎችን መከታተል፣ በህዝቡና በሰራዊቱ የሚነሱ ተቃውሞዎችን መሰለልና መከታተል እና  የውጪ ስለላ መስራት ናቸው፡፡ 

የዚህ ተቋም በዋናነት በተለያዩ የመንግስት ተቋም ውስጥ በመሆን ለበዓድ ሀገራትና ስርዓቱን  የሚቃወሙትን ለመልቀምና ጥቃት እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንዲሁም ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ  ዜጎችን የመከታተል በተለይም ካውንተር ኢንተጀለንሲ ወይም ሀገሪቷን ለመሰለልና ጉዳት ለማድረስ  የሚመጡትን ጠላቶች ጉዳት እንዳያደርሱ መከላከልና ማክሸፍ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በተለይም  ይሄ ተቋም በንጉሱ ላይ ሊቃጡ ወይም በዘውዳዊ ሰርዓት ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም ጥቃት  ወይም ተቋሙሞ ማክሸፍ አንዱና ዋና ተግባሩ ነው፤ በሌላ አገላለጽ ዘውዳዊ ስርዓቱን መጠበቅ  ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡

በአጠቃላይ በንጉሱ ዘመን የተጀመረው የደህንነት ሥራ የአገርንና የሕዝብን ፍላጎት ያማከለ ሳይሆን  በይበልጥ ለንጉሱ ዘብ በመቆም ስልጣናቸውን ለማራዘም ያለመ ነበር በንጉሱ ስርአት ግዜ የሕዝብ  ግንኙነት ስራ በደህንነት ተቋሙ ውስጥ በመዋቅር ተካቶ ለመተግበሩ ምንም መረጃ አያሳይም፡፡በዚህ  ተቋሙ አሰራሩና ተግባሩ ለህዝብ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሌለው በተወሰኑ አካላት ብቻ የሚዘወር  ነበር ለማለት የሚቻል ነው፡፡ በዚህም ዜጎች ለተቋሙ የነበራቸው አመለካከት እየተቀየረና ፍረሃት  እያሳደረባቸው መጥቶ ነበር፡፡ 

በደርግ መንግስት ዘመን  

ደርግ በ1966 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም የነበረውን የንጉሱን ዘመን የመረጃና የደህንነት  ተቋም በማፍረስ የራሱን በደርግ ፅ/ቤት የመረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ በሚል አቋቋመ፡፡ የዚህ  ተቋም ተልእኮ በወቅቱ የነበረውን የሶማሊያ ሁኔታ መከታተልና ፀረ-አብዮተኞችና የኢምፔርያሊስቶች  ቅጥረኛ የሚባሉ ሀይሎችን መከታተል አብይ ተግባሩ ነበር፡፡ 

ከ1972 ዓ.ም. በኋላ የደህንነት ተቋሙ ለመጀመርያ ግዜ የአገርና የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር  በሚል በአዋጅ እንደገና ተቋቋመ፡፡ መስሪያ ቤቱ የደህንነትና የመረጃ ስራዎችን አጣምሮ በመስራት  ተቋማዊ መልክ መያዝ የጀመረበት ግዜ ሲሆን ተቋሙ በወቅቱ የነበረው አደረጃጀት፡- የውስጥ ደህንነት  ድርጅት፤የውጪ አገሮች ጥናትና ምርምር ድርጅት፤ የኢኮኖሚ ደህንነት ድርጅት፤ የኢምግሬሽንና  የይለፍ ጉዳይ ድርጅት፤ የስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር፤ የወታደራዊ ደህንነት (በሰራዊቱ አመፅ  እንዳይነሳ የሚከታተል)፤ ልዩ ጥበቃና እስትራተጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት (ማሰልጠኛ) የሚባሉ የነበሩ 

ሲሆን የተቋሙ ተልዕኮም በወቅቱ የነበረውን የፀረ-ደርግ ተቃውሞ ትግል መከታተል ነበር፡፡ ከ1980-1983ዓ.ም የኢህዴሪ መመስረትን ተከትሎ ተቋሙ ሰፊ ስልጣን ተሰጥቶት የአገር ውስጥ  ጉዳይ ሚኒስቴር በሚል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደረጎ፤ ቀድሞ ከነበሩት ክፍሎች በተጨማሪ  የፖሊስ ሰራዊት፤ወታደራዊ ኮሚሳርያት፤ወህኒቤቶች አስተዳደር እንዲካተቱ ተደርጎ እስከ 1983ዓ.ም  መጨረሻ ዘለቀ፡፡ በዚህ በአዲሱ መዋቅር የነበረው ተልዕኮም በጎረቤት ሃገራትን ጨምሮ በውጪ  ሃገራት የስለላ ስራ መስራትና፤ በውስጥ ከህዝቡም ሆነ ከሰራዊቱ ሊነሳ የሚችል ተቃውሞና አመፅ  በማፈን የስርዓቱን ህልውና መጠበቅ ነበር፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በደርግ ዘመን የነበረው  የደህንነትና የመረጃ ስራ የፖለቲካ አቋም ይዞ ደርግን በስልጣን ላይ ለማቆየት ብቻ ሲሰራ እንደ ነበረ  መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  

በአጠቃላይ ልክ እንደ ቀድሞ የደህንነት ተቋም ስርዓቱን መጠበቅና ማስጠበቅ የደርግም ዘመን  የደህንነትና የመረጃ ተቋም ዋና ተልዕኮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ግዜ ይህ ተቋም ስርዓቱን  ለመጠበቅ የብዙሀን ህይወት እንዲያልፍ፣ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት እንዲደርስ ምክንያ ሆኗል፡፡ በተለይም መንግስት ይቃወማሉ ተብለው የሚታሰቡትን ድርጅቶችና ግለሰቦችን እየተከታተሉ ግድያና  ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ነበር፡፡ በዚህም ህዝብ ለተቋሙ ያለው እምነት  የተሸረሸረ ሲሆን ተቋሙን ፀረ-ህዝብ ተቋም አድርጎ በማሰብ የህዝቡ ፍርሃት ከፍተኛ እየሆነ  መጣ፡፡ ተቋሙ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ስላላሰፈነ የመንግስትን ስልጣን የያዙ ጥቂት ግለሰቦችና  ቡድኖች የሀገርን ጥቅም ማስከበር ትተው ለግልና ለቡድን ጥቅማቸው በማዋል ሀገሪቷ ሰላም አጥታ በብጥብጥና የብዙሀንን ህይወት ያጠፋና በሀገሪቷ ውስጥ የሰላም እጦት እንዲኖር ሆኗል፡፡ በዚህም  ዜጎች ለተቋሙ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ 

በኢፌዴሪ መንግስት ጊዜ 

የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ የሽግግሩ መንግስት የነበረውን የደርግ የመረጃ ተቋም አደረጃጀት  በአዋጅ እንዲፈርስ ካደረገ በኋላ ከአደረጃጀቱ የፖሊስ ሰራዊት፣ ማእከላዊ ምርመራና ወህኒቤት  ከተቋሙ እንዲወጣና ወታደራዊ ኮሚሳርያትና ወታደራዊ ደህንነት ክፍሉ እንዲፈርስ ተደርጎ በነበረው  የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚል ስያሜ ቀጥሏል፡፡ ተቋሙ በሽግግሩ አመታት (ከ1983- 1987ዓ.ም) የስርዓት ለውጡን ተከትለው የመጡ የፀጥታ ችግሮችን ለማስወገድና በሃገሪቱ ሰላምና  መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ተልዕኮው ነበር ፡፡ 

በመቀጠልም በ1987 ዓ.ም. ተቋሙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ስያሜውም የኢሚግሬሽንና  የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በሚል በአዋጅ ቁ6/1987 እንደገና የተቋቋመ ሲሆን ተልዕኮም፡- 

• በአገር ውስጥና በውጪ የአገርና የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ስራ መስራት፤ 

• የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ፖሊሲ ማዘጋጀትና ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ፤በአገር ነፃነትና  ኢኮኖሚ የሚጠነሰሱ ሴራዎችን መከታተል፤ማጣራትና ለሚመለከተው ማሳወቅ፤እና 

• ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር የኢሚግሬሽንና የስደተኞች አገልግሎቶችን መስጠት የሚሉ  ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ 

የዓለምን የማያቋርጥና ፈጣን የኢኮኖሚ፣የፖለቲካና ማህበራዊ ለውጥ ከግምተ በማስገባት አገራችን  ከለውጡ ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና ስጋቶችን ለመቋቋም  እንዲሁም ለመከላከል ጠንካራ የደህንነትና የመረጃ ተቋም ለመፍጠር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የብሄራዊ መረጃና  ደህንነት አግልግሎት በ2005 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 804/2005 እንደገና ተቋቁሟል፡፡ ይህም የሀገሪቱን  የሰላም፣ የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርአት ግንባታ ይደግፋል ተብሎ ታምኖበት  ነበር፡፡ 

ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠዉን ስልጣንና ተግባር የመረጃና ደህንነት ተልዕኮዎችን መፈፀም ሲሆን  በመረጃ ረገድ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በህገወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚደረጉ  እንቅስቃሴዎችን የመከታታል እንዲሁም በየአካባቢዉ የሚነሱ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው  የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መረጃ በማሰባሰብና ጥልቅ ትንታኔ በማድረግ ለመንግስት የስራ  ሀላፊዎች የውሳኔ ሓሳብ ማቅረብ ነው፡፡

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም አይነት ሴራዎችና  ስጋቶችን በተለይም ደግሞ ከሽብርተኘነት፣ ከአክራሪነትና፣ ፅንፈኝነትጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ሊከሰቱ  የሚችሉ የተለያዩ የስጋት አዝማሚያዎችን አስቀድሞ በመገመት የመከላከል ስራዎችንም ይሰራል፡፡ በአጠቃላይ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሀገሪቱና በዜጎቿ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም  ስጋቶች የማጥናት፤ጉዳት ሳያደርሱ ቀድሞ የመከላከል ስራዎችን ያከናዉናል፡፡ በደህንነት መስክም  ለቁልፍ ተቋማትና ባለስልጣናት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ከአቬሽን ደህንነት ባለፈም ለግዙፍ መሰረተ  ልማት ዝርጋታዎችም ተገቢዉን ፍተሻና ጥበቃ ማድረግ የተቋሙ የደህንነት ስራዎች ናቸው፡፡ በሌላ  በኩል ለመረጃና ደህንነት የሚያገለግሉ ማንኛቸውም አይነት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይም ደረጃ  የማውጣትና የጥራት ስራዎችን ከመስራት ባሻገር ፍቃድ የመስጠት ስራዎችንም ያከናዉናል፡፡  

ተቋሙ በዋነኝነት የህዝቦችንና የሀገሪቱን የደህንነትና የፀጥታ አደጋዎች አስቀድሞ የማየትና  የመተንተን መንግስት አደጋዎችን አስቀድሞ እንዲከላካልና መልካም አጋጣሚዎች ካሉ በአግባቡ  ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ሊዉሉ የሚችሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራዎችን እንዲሰራ ያደርጋል፡፡  ከዚህ አንፃር የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ በተሰጠዉ ስልጣንና ተግባር በሀገሪቱ ላይ  ሊቃጡ የሚችሉ የዉጭ ወረራዎች እንዲቀለበሱ ከማድረግ ባለፈ በተለይም ደግሞ ከሽብርተኝነትና  ፅንፈኝነት ጋር በተያያዘ የሽብር ቡድኖች በህዝብና በሀገር ላይ ሊፈፅሙ የሚችሉትን ጥቃትና አደጋ  አስቀድሞ ከመከላከል ረገድ ዉጤታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ 

የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊጎዱ የሚችሉ አደጋዎችንም ከመከላከል አንፃርም ጉልህ  ሚና ተጫውቷል፡፡ ቁልፍ የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናትን የደህንነት አደጋ እንዳያጋጥማቸዉ  በማድረግ በኩልም ተቋሙ ተልኮዉን በብቃት ፈፅሟል፡፡ ሀገሪቱ የአፍሪካ መዲና አንዲሁም የዓለም  አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችና ጉባኤዎች  በሰላም እንዲጠናቀቁ የደህንነት ስራዎች በተቋሙ ተከናውነዋል፡፡ 

ነገር ግን ልክ እንደ ደርግ ሁሉ በኢፌዴሪ መንግስትም በተመሳሳይ ለስርዓቱ ጠንቅና አደጋ ናቸው  የተባሉ በሙሉ ዘወትር ግድያ በሚፈጸምባቸውና ሕይወት እንደዋዛ የሆነበት ሀገር በመሆንና  መንግስታዊ ሽብር በከፋ ሁኔታ ነገሰ፣ እንዲሁም ለብዙ ሰዎች ሞትና መሰደድ ምክያት ሆነ፡፡  ንጽሀን ከፍርድ በፊት በፀራራ ፀሀይ ተገደሉ፣ አካል ጉዳተኛና ለከፍተኛ ስነ-ልቦና ቀውስ ተጋለጡ፡፡ ተቋሙ ከዚህ ቀደም የነበረውን ስም ከማደስና ታማኝነቱን ከማስመለስ ይልቅ የአንድ ፖርትና  የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ማስፈጸሚ ተቋም በመሆኑ ምክንያት ዜጎች በከፍተኛ ፍርሃት እንዲዋጡ  አድርጎል፡፡

መንግስት ተቋሙን ለህዝብ ተጠያቂና ታአማኒ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፣ በመንግስት ኦዲት  መስራቤት እራሱ ኦዲት የማይደረግ እንደፈለገው የሚሆን ተቋም በመሆን በተለያዩ ጊዜ መንግስትን  ይቃወማሉ ወይም መንግስትን ለመጣል አሲረዋል በማለት በህዝቦች ላይ ፍርሃትን በማሳደር  ተቋሙ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈራና ተጠያቂነት የሌለበት እንዲሆን ሆኗል፡፡ በዚህም በሀገሪቷ ላይ  አሉታዊ ሰላምን ማምጣት የተቻለ ቢሆንም አውንታዊ ሰላም ግን እንዳይኖር አድርጓል፡፡ በዚህም  በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች ላይ የደህንነት ተቋሙ በዜጎች ላይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት እስከሞት ጉዳት  ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ በዚህም እጅግ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ታፍነው ጠፍተዋል ወይም  ተገድለዋል፡፡ ህዝቡም ተቋሙን ሲያስብ ለፍርሃትና ከግድያ ጋር በማገናኝት የእራሱ እንዳልሆነ  ሲያየው ቆይቷል፡፡ 

በብልጽግና ዘመን (ከመጋቢት 2010 ዓ.ም በኋላ) 

ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የፀጥታ ተቋማትን ለማሻሻል ቃል በመግባት  በተለይም በኢህአዴግ ጊዜ ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጸምበት የነበረ ተቋም ነበር ያሉትን የብሔራዊ  መረጃና ደህንነት ተቋም ያሉበትን ድክመቶች አስቀርቶ ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርአቱን  በተከተለ መልኩ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሳይጋፋ ከዚህ በታች ያሉትን ዕራይና  ተልኮች በተለይም የተቋማዊ ራዕይውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞችን ለመከላከል፣  ለመጠበቅና ለማሳደግ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመረጃና ደኅንነት ተቋም መሆን እንዳለበት  በመግለጽ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ከማንኛውም ስጋት ለመከላከል፣ ለመጠበቅና  ለማሳካት የሚያስችሉ፡-

 • መረጃዎች መሰብሰብ፣መተንተንና ለሚመለከታቸው የመንግስት አመራሮችና ተቋማት ማቅረብ፤  • የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የውጭ ሀገር መሪዎችና ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ደኅንነት  መጠበቅና ማስጠበቅ፤ 

 • በሀገራችንና ህዝቦቿ ጥቅምና ክብር ላይ የሚቃጣ የስነልቦና ጦርነት መከላከልና መቀልበስ  የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት ነው፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱትን አላማዎች በብቃት እንዲያሳካና ተቋሙ በየትኛውም ደረጃ መደበኛና ልዩ  ተልዕኮውን በተጠያቂነት እንደሚሰራ በ2011 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ላይ ተገልጻል፡ ፡ በዚህ የዶ/ር አብይ መንግስት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ብዙ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡በተለይም  የተሻሻለው አዋጁ ከየካቲት 2010 ዓ.ም. በፊት አንዳንድ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ተቋሙ  በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ማስፈጸም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ሲገባቸዉ  ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸዉ በአስተሳሰብና በአመለካከት ልዩነታቸዉ ኢሰብአዊ ድርጊቶች  ደርሶባቸዋል በሚል በህብረተሰቡ ለተቋሙ መልካም አመለካከት አልነበረውም፡፡ በህዝብ ዘንድ  ያለው ተቀባይነትም በአገልጋይና ተገልጋይ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ከመሆን ይልቅ በጥርጣሬና  በስጋት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ 

በተለይም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ባለመሆኑ ምክንያት በሽብርተኝነትና ፅነፈኝነት ሽፋን  ዜጎችን ሲያስር፡ ሲያንገላታና ሲመረምር ነበር በሚል በህብረተሰቡ ዘንድ የሚወደድ፡ የሚከበርና  የሚታመን ተቋም መሆን ሲገባዉ የሚፈራ ሆኗል፡፡ ከዚሁ በመነሳት ተቋሙ ልክ እንደቀድሞ  ሁሉ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ሚስጢራዊነትን ተገን በማድረግ በመገናኛ  ብዙሃን በኩል ይፋ ሊሆኑ የሚገባቸዉ መረጃዎች አለመገለፃቸዉ የተቋሙን የግልፀኝነት ጉዳይ  ጥያቄ ዉስጥ አስገብቶት ቆይቷል፡፡ 

ተቋሙ ከላይ ከተጠቀሱትን ችግሮች ተላቆ ሕገ መንግስታዊ ወደ ሆነው አሰራር ለመግባት ከ2010  ዓ.ም ጀምሮ በሚከተለው ሪፎርም የማንም የፖለቲካ ወገን ደጋፊ ሳይሆን ተጠያቂነትን ባማከለ  መልኩ የህዝቡን፣የመንግስትን፣ የሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ፣ የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡን  ደህንነት ለማረጋገጥ የሃገር ኩራት ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ 

ተቋሙ ልክ እንደቀድሞ ሁሉ ዜጎችን ከመንግስት ወይም ከገዥው ፖርቲ የአስተሳሰብ ልዩነት አላችሁ  በማለት በተለያዩ ጊዜቶች ንጽሐንን በሀሳባቸው ምክንያት በመጥለፊ፣ በማፈን፣ በመሰወር፣አካላዊ  ጉዳት በማድረስና በግድያ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ከሌሎቹ ጊዜቶች በባሰበት ሁኔታን ሰዎችን በዘር  ሀረጋቸው በመለየት ማሳደድ፣ማፈንና ማሰር ወስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡ በዚህም ማህበረሰቡ ለውጥ  መጥቷል ብሎ እንዳያስብና በሃገራችን የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ መልካም አስተዳደር 

እንዳይሰፍን እና ሁሉ አቀፍ መሻሻሎች እውን እንዳይሆኑና መልካም አስተዳደር ከማስፈን እና ተያያዥ የልማት አጀንዳዎች ላይ ንቁ፣ ሞጋችና ጫና በመፍጠር ተሳትፎ የሚያደርግ እና የዜግነት  ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ ማህበረሰብ እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት ልክ እንደቀድሞቹ ሁሉ  አስተጓጉሎታል፡፡ 

ይህ ችግር ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ባህል እንዳያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍንና ህዝብ  ባለው ሁኔታ እንዳይረካ በማድረግ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር  አድርጓታል፤ ይህ ዓይነት ሁኔታ በመፈጠሩ ምክንያ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮችን አስከትሏል፡ ፡ በተለይም አውንታዊ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ትግል እጅግ አስቸጋሪና እውን እንዳይሆን  ያደረገው ሲሆን በዚህ ምክንያት ዜጎች እራሳቸውን ለመከላከልና ለመጠበቅ የተለያዩ ኢመደበኛ  አደረጃጀቶችን እንዲፈጥሩና ያሉትንም እንዲደግፍ ሲያደርጋቸው የሚታይ ሲሆን ዜጎችን በሀገራቸው  ጉዳይ ተስፋ ቢስ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ለአሉታዊ ሰላም ግንባታ(የህግ የበላይነት  መከበር) ደንቃፋ ሆኗል እየሆነም ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭትና  ብጥብጥ እንዲነግስ ሆኗል፣ እየሆነም ይገኛል፡፡ 

መደምደሚያ  

ኢትዮጵያ የእረጅም አመታት ያስቆጠረ የስርዓት መንግስት ልምምድ ያላት ሀገር ስትሆን በዚያው  ልክ በተለያዩ ዘመናት ነገስታትና መንግስታት እየተፈራረቁባት የተለያዩ የአስተዳደር ዘይቤዎችንና  ተቋማትን በማቋቋም ህዝባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት  ለመፍጠር ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚ ሊባል የሚችልው መልካም አስተዳደር  እንደሆነ የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ምሁራን ምልከታ መሰረት በመንግስትና  ህዝብ መካከል በመተማመንና በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው የመንግስት  ስርዓቱ አስተማማኝ የመልካም አስተዳደር ሁኔታን መገንባት ሲችል ብቻ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር  የሚገለፅባቸው ሁኔታዎች መካከል ደግሞ በመንግሥት አሠራር ላይ ግልጸኝነትና የተጠያቂነትን  መርህ መሰረት ያደረገ አሰራር ሲኖር ነው፡፡ 

መልካም አስተዳደር በሰፈነበት አገር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠ በመሆኑ የዜጎች ቅሬታ  በእጅጉ ይቀንሳል፤ የዚህ ዓይነቱ አስተዳደር የዜጎችን ሁለንተናዊ አገራዊ ተሳታፊነትና ባለቤትነት  የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሚወጠኑ የመንግስት የልማትም ሆነ ሌሎች አገራዊ ፋይዳ ያላቸው  ፖሊሲዎች ህዝባዊ መሰረትን ይጎናፀፋሉ፤ ይህም ዜጎች ለአገር የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ በአንድም  ይሁን በሌላ መልኩ ጉዳት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  እንዲሳኩ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ የማይሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ 

በአገራችን በተለይ አዲስ ዓይነት የፖለቲካ ስርዓት ከተመሰረተበት ካለፉት 60 ዓመታት ወዲህ  በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዎ ለውጦች በስፋት እየታዩ ስለመሆናቸው የብዙዎቻችን  ትዝብት ነው፡፡ከንጉሳዊ አስተዳደር መውደቅ በኋላ የተተካው የደርግ መንግስት ተከትሉ የመጣው  አስተዳደር የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያላደረገና አዲስ ልምምድ ያመጣ ሲሆን በተለይም ፖርቲ  ፖለቲካ እየተዋወቀ የመጣበት ሲሆን የመንግስት መንበሩን የተቆጣጠሩ አካላት መልካም አስተዳደር  እንዳይሰፍን በተለይም የተቋማትን ገለልተኝነት በማሳጣት ለእኛ ብለው ላቋቋሙት ፖርቲ ጥቅም  መገልገያ ሲያደርጉት እስካሁን ቆይተዋል፡፡ 

በተለይም የፀጥታ ተቋማትን ለግለሰቦችና ቡድኖች ጥቅም ሲያውሏቸው ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት  ውስጥ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አንዱና ዋነኛው ነው፡ የመረጃና ደህንነት ስራ በኢትዮጲያ  የተጀመረው በአፄ ሐይለስላሴ ዘመን ከ1937-1955ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን መረጃዎች  የሚያሳዩ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር “የፀጥታ ጠቅላይ መምሪያ” በሚል  ተቋቁሞ የአገርና የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮ ተሰቶት ይሰራ እንደነበርና ከሚያከናውናቸው  የተለያዩ ስራዎች ውስጥ ለንጉሱ ዘውድ ችግር ይፈጥራሉ የተባሉትን ሲያስርና ሲያሰድድ የነበረ እና ከዚያም ቀጥሎ በመጣው ደርግ ዘመንም የፕሬዝዳንቱንና ፖርቲያቸውን ፍላጎትና ጥቅም  ለማስጠበቅ በብዙ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡በተመሳሳይ በኢፌዴሪ መንግስትም ከዚህ  ቀደም የነበረውን ልምምድ በመቀጠል ዜጎችን ባላቸውን ፖለቲካዊ አቋም ምክንያት በማሳደድ፣  በመግደል፣በማሰር፣በመሰወርና የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡በዚህም ማህበረሰቡ  ተቋሙን በመፍራትና ለደህንነቱ የስጋት ምንጭ ሆኖበታል፡፡ ባለንበት በብልጽግና ዘመንም ከዚህ  ቀደም የነበረውን ባህሉን በመቀጠል ዜጎችን በሀሳባቸው፣በመጡበት ማህበረሰብ ዘር ግንድ፣ አቋም  በማሳደድ፣በመግደል፣በማፈንና በመሰወር ዜጎች ለተቋሙ ያላቸውን አመለካከት ወደባሰ ጥላቻና  ፍራቻ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ በዚህም ተቋሙ ለአውንታዊ ሰላም የሚያበረክተውን አስተዋጾ  በአግባቡ እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡ በሃገራችን የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ መልካም አስተዳደር  እንዲሰፍን እና ሁሉ አቀፍ መሻሻሎች እውን እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ የዜጎች ተሳትፎ እንዳይፈጠር  በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈጠሩ እያደረጉ ቆይተዋል፤እያደረገም ይገኛል፡፡ 

ምክረ ሀሳብ 

ተቋማት ልምድና ተቋማዊ ቁመና በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት አደጉ የሚባሉ አገሮች፣ የብሔራዊ  መረጃና ደኅንነት አግልግሎት ተቋማት ራሳቸውን ችለው ከፖለቲካ ሥርዓት ገለልተኛ በሆነ መልኩ  ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ የደኅንነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት  የፖለቲካ ቁንጮውን በሚዘውሩ መሪዎች ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ አሁኑ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ 

ከዚሁ ጋርም የአገሪቱ መሪዎች አገሪቱ ያላትን እጅግ አነስተኛ ሀብት እንደዚሁም ከተለያዩ አካላት  የሚገኘውን የልማት ድጋፍና ብድር ለታለመላቸው ስራዎች በተገቢው መንገድ ማዋል ሲጠበቅባቸው  ለእነዚህ ተቋማት ያለተጠያቂነት በመስጠት የእራሳቸውን የስልጣን መንበር ለማስጠበቅ ይረዳል  ብለው በማሰብ ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሳሉ፡፡ በዚህም ተቋሙን እንደ ግል ንብረታቸው በመጠቀም  የግለሰብና የቡድን ፍላጎታቸውን ማስፈጸሚያ ያደርጉታል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ዓላማ በማዋላቸው  የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያደርገው ጥረትም ከዚህ አኳያ ሊነሳ የሚገባው ተግባር  ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ይህም የአገሪቱ የልማት አጋሮች የሚሰጡትን ድጋፍ የበለጠ  አጠናክረው እንዲቀጥሉበት የማያደርጋቸው በመሆኑ በሀገሪቶ ላይ ሊመጣ የሚገባው ልማትና  እድገት በሚፈለገው ደረጃ ሳይመጣ ይቀራል፡፡ ለጋሾች ደካማ መልካም አስተዳደር በተንሰራፋበት  አገር ውስጥ ለውጥ ማምጣት አይታሰብም ብለው ስለሚያምኑ ድጋፋቸው ዝቅተኛ ይሆናል፤በዚህም  ዜጎች በድህነትና በመልካም አስተዳደር ችግር የሚሰቃዩ ሲሆን ለሀገሪቷ ሰላምና ደህንነት የስጋት  ምንጭ ይሆናል፡፡ በእነዚህ ተቋማት ላይ ለውጥ ማምጣት ማለት ከፍተኛ እመርታዎች ህዝብ  በመንግስት ላይ ያለውን እምነት አጠናክሮ፤ ከፍተኛ የማደግና የመለወጥ መንፈስንም ይፈጥራል፡፡  እንደ እኔ እምነት የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች ተፈጻሚ ቢደረጉ በትንሹም ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብይ አስባለሁ፡፡ ከእነዚህ ምክረ ሀሳቦች ውስጥም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- በባለሙያ ደረጃ፡  

• የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞችን ተቋማዊ ባህል የተመሰረተባቸው  መርሆዎች፣ መሰረታዊ እሴቶችና ሙያዊ ፍልስፍናዎች የሚከተሉት እንዲሆኑ ማድረግ፤በዚህም  ሰራተኞቹ ሀቀኝነት መርህን ተግባራዊ በማድረግ የላቀ የሞራል ልእልና ባለቤት፣ ቅን፣ ቀጥተኛና  ሃቀኛ፣ ቃላቸውን የሚያከብሩና በስራቸው እምነት የሚጣልባቸው እንዲሁም ለተበላሸ ስነምግባር  ከሚያጋልጡ አመለካከቶች፣ ተግባሮች፣ ተፅእኖዎችና አዝማሚያዎች ነፃ በመሆን ተልእኮቸውን  የሚፈጽሙ፣ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን በመጠቀም ተልእኮኣቸውን  ለማሳካት የሚተጉ፣ ለሁኔታዎች፣ ክስተቶች፣ ሃሳቦችና የተለያዩ አዝማሚያዎች ፈጣን ምላሽ  ለመስጠት የሚያስችል የአካልና የመንፈስ ጥምረት በመፍጠር በፍፁም ተነሳሽነት የሚሰሩ መሆን  አለባቸው፣ እንዲሁም በተሟላ የሙያና እውቀት ልህቀት ላይ በመገኘት ተልእኮአቸውን በብቃትና  ቅልጥፍና ለመፈፀም የሚተጉ፣ የሰራ አፈፃፀማቸውንም በመገምገም ለመማር፣ ልምድ ለመቅሰምና  ራሳቸውን በማሻሻል ለላቀ ውጤት የሚያዘጋጁ፡፡ መረጃ የማግኘት አቅማቸውን በቀጣይነት ለማሳደግ  የኢንፎርሜሽን ምንጮቻቸውን፣ የድርጊያ ዘዴዎችና አሰራሮቻቸውን ምስጢራዊነት የሚጠብቁ፣  እንዲሁም ስራቸውን በመደጋገፍና በመተባበር የሚሰሩ፣ በጋራ ውጤት የሚያምኑ ፣ ብዝሃነትንና  አካታችነትን ዋነኛ የተልእኮ አፈፃፀም መሳርያዎቻቸውን አድርገው የሚጠቀሙ ባለሙያዎች መሆን  ይጠበቅባቸዋል፡፡እነዚህ እሴቶች ከተላበሱ የትኛውም ስርዓት ቢሄድ ቢመጣ በተቋሙ ላይ አውንታዊ  ተጽኖ ማምጣት ይችላሉ፡፡ 

በተቋም ደረጃ፡  

 • ተቋሙን በመርህ ደረጃ ህዝብ የሚቆጣጠረኝና የበላይ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲኖረው  መስራት 

 • የአመራር ምደባ በብቃትና ችሎታ (ሜሪት) ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርግ ስርዓት  እንዲዘረጋና ብቃታቸው ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ለማድረግም ቀጣይነት ያላቸው የማብቂያ እርምጃዎች  እንዲወሰዱ ማድረግ፣ 

 • በሁሉም ደረጃ በሚደረግ የአመራር ምደባ ላይ ግልጸኝነትና ስርዓት ባለው መንገድ ማድረግ  ወይም መዘርጋት፣  

 • የምክር ቤቶች፣ የማህበራትና የሚዲያው አመራሮችና አባላት ጥፋት በተቋሙ ውስጥ ሲፈጸም  እንዲናገሩና በድፍረት በመታገላቸው የሚደርስባቸውን ጫናና ሌላ በደል በተመለከተ ጥበቃ  የሚደረግበት ህጋዊ ስርዓት መዘርጋት፣ 

 • የተጠያቂነትና ግልጸኝነት አስራሮችን መዘርጋት 

በማህበራሰብ ደረጃ  

• ለማህበረሰቡ ስለተቋሙ አሰራርና ሁኔታ በአግባቡ እንዲያውቅ ማድረግ  • ለረዥም ጊዜ የተፈጠረውን ፍርሃት ከውስጡ እንዲያወጣ ተቋሙን ወደ ህዝብ የማቅረብና  ህዝቡ እንደእራሱ ተቋም እንዲያየው ማድረግ፡፡ 

• በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች የተቋሙን አገልግሎት እንዲቀላቀልና እንዲወደው የግንዛቤ  መፍጠር ስራ መስራት  

በመንግስት ደረጃ  

• የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚመለከቷቸውን የብዙሃንና ሙያ ማህበራትንም ሆነ ሌሎች  ሊሳተፉ የሚገባቸውን አካላት በሚያከናውኗቸው ስራዎች ሁሉ (በዕቅድና ግምገማ፣ መመሪያዎችን  በማውጣት) ማሳተፋቸው የየተቋማቱ የአፈጻጸም መገምገሚያና መለኪያ መስፈርት ሆኖ እንዲቀመጥ  ማድረግ፡፡ 

• የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የህዝብ ተሳትፎ ሲፈለግ የህዝብ ተሳትፎ የሚደረግባቸውን  ጉዳዮችና ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚፈለጉ አካላትን መሰረት ያደረጉ የተሳትፎ መንገዶችን መዘርጋትና  እንደአግባብነታቸው የተለያዩ የተሳትፎ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፡፡ 

 • ሁሉም የመንግስት የሚዲያ አካላት የህዝብን ድምጽ የሚያሰሙበትና ከህብረተሰብ ጋር  የተያያዘ ጉዳዮችን የሚታይበት የአየር ሰዓት እንዲመድቡ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋት፡፡  

• መንግስት ተቋሙ ገለልተኛ እንዲሆንና ተጠሪነቱ ከስራ አስፈጻሚ ይልቅ ለህዝብ ተወካዬች  ምክር ቤት የሙሆንበትን አሰራር መፍጠር ፡፡  

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here