spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየፋኖ መንግስት መመስረት አስፈላጊነት

የፋኖ መንግስት መመስረት አስፈላጊነት

የፋኖ መንግስት _

ደሳለኝ ቢራራ
መጋቢት 2016

በኢትዮጵያ ታሪክ የተለመደ፡ በጦርነቶች ወቅት የሚታወቅ የህዝብ ስነልቦና እና የፖለቲካ አቋም አለ። ህዝቡ ሳይነጋገር ከሚግባባባቸው አቋሞች ውስጥ አንዱ መሪ ለመሆን ከሚታገል ቡድን ይልቅ ወደ ትግል የገባን መሪ ደጀን መሆን ነው። ሁለቱ አካላት ልዩነታቸው ግልጽ ነው ብቻ ሳይሆን እየተዋጉ ያሉ ናቸው። ጦርነት ከሚያደርጉት አካላት ውስጥ ቢያንስ አንዱ የሀገር መሪ ወይንም መንግስት የሆነው አካል ሲሆን ሌላው ተዋጊ አካል ደግሞ ነባሩን አፍርሶ አዲስ መንግስት ለመመስረትና አዲስ መሪ ለመሆን የሚዋጋው ነው። 

በተለያዩ ወቅቶች በተደረጉ ጦርነቶች እንደተስተዋለው ድምጽ አልባው ብዙሀን የሚያሳየው ዝንባሌ  የመንግስት መዋቅርን ይዞ ወደ ጦርነቱ የሚዘምተውን የተጠናከረ አካል መደገፍና መንበረ-ስልጣኑን ማጽናት ነው። ይህ በበርካታ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎችና የማህበራዊ ህይዎት ልምዶች ተጽዕኖ የተነሳ ህዝቡ በውዴታ ግዴታ የሚገባበት ምርጫ ሊሆን ይችላል። ንጉስ በዙፋኑ ሲመጡበት ስለሚኖረው ቁጣ እና ስለሚፈጀው ህዝብ የሚተረቱ ብዙ አባባሎችም አሉ። 

አሁን ያለው ማህበረሰብ ከዚህ የመንግስት ደጀን ስለመሆን ከሚተጋ ባህልና እሳቤ የተቀዳ ከመሆኑ ባሻገር፡ የራሱ የሆነ ደግሞ ንቃተ-ህሊና እና በአዘቦት ኑሮው የሚጋፈጠው በመንግስት የሚደርስበት ግፍና ስቃይ አለ። በመንግስት የሚደርስበትን በደል ማወቁ ደግሞ ብቻውን በቂ ምክንያት ሁኖ ላያስነሳው ይችላል። በዚህን ጊዜ ህዝባዊ ዝምታ መንገሱ አይቀርም። ምክንያቱም መንግስትን ወግቶ መጣልም እንግዳ የሆነ ስምሪት ነው፤ እንደተለመደው የመንግስት ደጋፊ መሆንም የማይቻል ነገር ይሆናል። በዚህ ዝምታ ላይ ያለ ህዝብ ምንም ያህል የከፋው-ብሶተኛ ቢሆንና ለለውጥ አብዮት የታመቀ ቢሆን እንኳ የተግባር ተጽእኖ መፍጠር አለመቻሉ ገለልተኛ አቋም የያዘ ሊያስመስለው ይችላል። ነባር የባህልና ታሪክ መሰረቶቹን አውቆ፡ ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚመሩትን እሳቤዎችና ልምዶች ተገንዝቦ፡ ተስማሚ አሰላለፍ የሚፈጥርለት አታጋይ ይፈልጋል። የፋኖ እዞችም ሆነ እስክንድር አሁን ባላቸው ቁመና እንደዚህ አይደሉም።  ሁለቱም ኃይሎች የህዝብ ተቃውሞ እንደሌለባቸው እሙን ነው። ስለራሱ ህልውና ሊታደጉት ጦርነት ገብተው እየተሰው ያሉ ልጆቹን ስለመቃወም ከቶም ሊታሰብ አይችልም። “ሁሉም አማራ ዘማች ለምን አልሆነም?” ስለሚል ጥያቄ እንጅ! 

በመሆኑም የፋኖ ትግል የቱንም ያህል አሳማኝ ምክንያት አንግቦ ለህዝብ ህልውና እና ጥቅም ሲል የሚደረግ ተጋድሎ መሆኑን ህዝቡ ቢያውቅም፤  ተዋጊ መሆን ያለበት ህዝብ ተመልካች ሁኖ ሊቆይ ይችላል። ተመልካችነት ደግሞ በተዘዋዋሪ ፋሽስታዊ ስምሪት ላይ ያለውን አገዛዝ እንደመደገፍ ይቆጠራል። ማለትም ስልጣን ላይ ያለው አካል ምንም እንዃ ገዳይ-አረመኔ መንግስት ቢሆንም በህዝቡ ነባር የፖለቲካ ተግባቦት እና ልምምድ ላይ ለውጥ ባለመደረጉ የሚያስጠብቅለት አንጻራዊ አለ ማለት ነው።   ወይንም ብዙሀኑ ህዝብ በጦርነቱ የማይሳተፍ መሆኑ ጥቅም የሚኖረው ስልጣን ይዞ እየተዋጋ ላለው አካል ነው። ይህ የሆነው ህዝቡ የመንግስት ደጋፊ ስለሆነ አይደለም! ይህንን ማህበራዊ ባህርይ መረዳት መቻል የፋኖውን ትግል አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ያስችለዋል።  የተጽዕኖ አድማሱንና የአቅም ልኩንም ከፍ አድርጎ መገመት አለበት።  የትግሉን መልክና ባህሪ ለህዝብ የሚያስረዳበት መንገድና ስልቶችም ማደግ አለባቸው። 

አሁን ፋኖ ያለበትን አቋም ስንገመግም በሞራልና ስነምግባር፥ በስነስርአት አፈጻጸሙ፥ በስምሪትና መስተጋብሩ እንዲሁም በህዝብ ባገኘው ተቀባይነትና ታማኝነቱ ከመንግስታት ሰራዊት ሁሉ በበለጠና በላቀ ደረጃ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ በተግባር አሳይቷል። ይህንን ሁሉ መልካም ባህሪያት እና ድሎች ተላብሶ፤ የህዝብ ድጋፍና ተቀባይነት አግኝቶም ግን በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ የአገዛዙን ስርአት መገርሰስ ቀላል አይሆንለትም። ምክንያቱም ውጊያ እያደረገ ያለው እራሱን አማጺ ቡድን አድርጎ ነው። የመንግስትነት ባህሪዎችና ስነስርአቶችን በላቀ የሞራል ከፍታ መፈጸም የሚችል ጠንካራ ወታደራዊ አደረጃጀት እና ግዙፍ ህዝባዊ መሰረትና ድጋፍ ያለው ቡድን አማጺ ሳይሆን መንግስት ሁኖ ነው መዋጋት የሚገባው። እንኳንስ የራሱን ህዝብ ደጀን አድርጎ እየተዋጋ ያለ ጠንካራ አደረጃጀት ይቅርና በውጭ ሀገር የሚኖር ስደተኛ መንግስት አቋቁመው፡ ታግለውና አታግለው ድል ለመቀዳጀት የበቁ እጅግ በርካታ ትግሎችም እንዳሉ ትምህርት መወሰድ አለበት። 

ይህን የፋኖ መንግስት ምስረታ ምክረሀሳብ ሳቀርብ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው። አንደኛ) ፋኖ ከአገዛዙ ጋር እያደረገ ያለው ትግል ከአማራ ህዝብ ህልውና ጋር በቀጥታ የተገናኘ ስለሆነ ትግሉን ከማሸነፍ ውጭ ምርጫ የለውም። ትግሉን ቢያቆም ህዝቡ ለዘር መጥፋት ይዳረጋል። በተለያዩ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የተደረገው ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ የአገዛዙን ባህሪ ፍንትው አድርጎ ያሳዬ ተሞክሮ ነው።  ሁለተኛ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወይም ሙሉ በሙሉ የአገዛዙን መዋቅር መስበር መቻልና መንግስት እንዲፈርስ ማድረግ ብቻውን ስኬት ወይም ድል አይደለም። ፋኖ በያዘው የውጊያ ስልት ገዥውን መንግስት ሙሉ በሙሉ ስራ እንዳይሰራ በማድረግና መዋቅሩን መስበር መቻል ስርአቱን ማሸነፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። መንግስትና መስተዳድር ዘርግቶ አገልግሎትና ወጥነት ያለው አመራር መስጠት ካልቻለ ግን የሀገር መፍረስ (state failure) እንጅ ድል ተደርጎ አይወሰድም።

ስለዚህ ፋኖ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ሙሉ የመንግስት መዋቅርና ካቢኔ ያለው መስተዳድርም መሆን አለበት። በሚቋቋመው መስተዳድር ውስጥ የክልል፥ የዞንና የወረዳ አወቃቀሮች መሟላት አለባቸው። እነዚህን መስተዳድራዊ መዋቅሮች የሚመሩ ሹማምንትና የስራ ኃላፊዎች በአሁኑ ሰአት የጦርነት ዘመቻውን እየመሩ እንዳሉ ታስቦ ነው ድልደላ እና ምድባ መሰራት ያለበት። ማለትም ከፋኖዎቹ ውስጥ ለሁሉም ኃላፊነቶች የሚመጥኑት ሰዎች ተመርጠው መሰየም አለባቸው። ይህን ትግል ሲመሩ የመስተዳድሩ ሚናቸውን ያገናዘበ እንደሆነ እያወቁ ያዋጋሉ፡ ዘመቻውን ይመራሉ ማለት ነው። አጠቃላይ ዘመቻውን እየመራ ያለው የክልል ፕሬዝደንቱ ቢሆን የጸጥታና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ደግሞ የውጊያው አዛዥ ሊሆን ይችላል። ሌላው የጤና፥  የግብርና፥ የትምህርት፥ የቱሪዝም፥ ወዘተ ቢሮዎች ኃላፊዎች በያሉበት የመንግስት ካቢኔ፡  ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ሙሉ መዋቅራቸውን የሚያሟላ የስራ ኃላፊ መመደብ አለበት። ይህ ሁሉ መሪ ዘመቻው ላይ መሆኑ አይዘነጋም። የክልሉ ፕሬዝደንት በጦርነት ዘመቻ ላይ እንደመሆኑ መሪነቱን በየዕለቱ ይወጣል። አጠቃላይ መስተዳድሩን ህዝቡን እና ጦርነቱን ያዝዛል፤ ይመራል። ለህዝቡም  ለካቢኔውም ትእዛዝ ያስተላልፋል። በዚህ መልኩ እያንዳንዱ ተዋጊ ፋኖ ግንዛቤ መያዝ ያለበትም የፋኖ መንግስት ሙሉ አቅሙን እና መዋቅሩን ይዞ ወደ ጦርነት የገባ መሆኑን ነው። እንጅ ገና ከጦርነት በኋላ ምናልባት አሸናፊ ከሆኑ ስልጣን ሊይዙ እንደሚችሉ በማስረዳት አይደለም። እየተዋጉ ያሉት ተገቢነት ያለው የስልጣን ባለቤት መንግስት ዘመቻውን አጠናቆ ወደ መደበኛ ስራው እንዲመለስ ነው። 

በመቀጠል ጦርነት እየተደረገ ያለው በሁለት መንግስታት መካከል መሆኑን ለህዝብ ማስገንዘብ ነው። ህዝቡ ትእዛዝ የሚሰጠው መሪ ይፈልጋል። የመንግስትነት መልክ ከሌለው አካል ግን ትእዛዝ አይቀበልም። ከተበታተነ የፋኖ ጎሪላ ይልቅ የጎረቤት ሀገር ፕሬዝደንት ዘመቻ ቢጠሩት ለአመነበት አላማ ሆ ብሎ ህዝቡ ይነሳል። መዋቅራዊ መሰረት ያለው ኃላፊነት እና ስልጣንን ነው ህዝቡ የሚቀበለው። ከዚያ በኋላ በሁለት መንግስታት መካከል የሚደረገውን ጦርነት በተለያዩ መስፈርቶች ህዝቡ በራሱ ሚዛን ይመዝነዋል። በፍትሀዊነቱ፥ በተነሳበት አላማ፥ በሚያሳያቸው ባህርያቱና ቃል በሚገባቸው ውጤቶች በነጻነት ያመዛዝነዋል። ካመዛዘነ በኋላም ነው ሙሉው ህዝብ የፋኖውን መንግስት መሪዎች ጥሪ እና ትእዛዝ ተቀብሎ የሚፈጽመው። 

የፋኖ መንግስት መመስረት የህዝቡን አንድነትና ሙሉ ትብብር እንዲያገኝ የሚያስችልበት ምክንያቶች አሉ። አሁን የፋኖ ተጋድሎ እየቀጠለ ባለበት ፍጥነትና ሂደት ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ጦርነት ውስጥ የሚቆይ ከመሰለው “በዘመነ መሳፍንት ተከስቶ የነበረው መፈረካከስና የጎበዝ አለቆች በየጎጡ ቆራጭ ፈላጭ ሁነው ይነሳሉ” የሚል ተጨባጭ ስጋት አለ። የፋኖ መንግስት መኖሩ ከታወቀ ግን ምንም እንኳ ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ቢችልም፡ የመንግስትነት እሳቤው የህዝብን ስጋት ይከላከላል። 

በተጨማሪም የፋኖ መንግስት መመስረት በርካታ ተጓዳኝ ችግሮችን ይቀርፋል። ስልጣን እያደቡ ያሉ በውጭም በውስጥም ያሉ የድል አጥቢያ ጀግኖችን ወደየሙያቸው እንዲበተኑና ሰርተው እንዲበሉ ያደርጋል። ፋኖውን ወታደር ብቻ አድርገው የሚመለከቱ፡ ፋኖ አገዛዙን ከገለበጠ በኋላ የሚመሰረተው መንግስት ባለስልጣን ለመሆን ተዘጋጅተው የተቀመጡ ቀላል እንዳልሆኑ ይታወቃል።  ብዙዎቹ በውጭ ድጋፍ ሰበብ ፋኖውን የሚከፋፍሉ እና የሚያቃርኑ ስለነበሩ ሁሉንም አርፈው እንዲቀመጡ ያደርጋል። እዚህ ላይ ላሰምርበት የፈለኩት ጉዳይ እነዚህን አካላት ስለማግለል አይደለም። መሸከም በሚችሉት ኃላፊነት ልክ ሚና ቢሰጣቸው ሁሉም ኃይሎች ጠቃሚ እንደሚሆኑ አምናለሁ። ሳጋውን ወጋግራ የማድረግን አሰራር ነው የማልቀበለው። መሬት ላይ ያለው ፋኖ መንግስት ከመሰረተ በኋላ ለተፈለገው መዋቅር የሚፈልገውን ሰው ከየትም ቦታ መርጦ ሊሾመው ይችላል። የመረጠውንና የፈለገውን ሰው አጭቶና መልምሎ የመሾም ወይም የመሻር ስልጣን ግን የፋኖ ብቻ ነው። ይህም ስልጣን እንዲተገበር የፋኖ አሰራር በመንግስት ቅርጽ መሆን ይጠበቅበታል። አሰራሩ ሁሉ በመንግስት መልክ ሲሆን ተግባቦቱ ቀጥተኛ ግልጽና የበለጠ ታማኝ ይሆናል። ለመደገፍም አመች ነው። ከውጭ መንግስታትና ተቋማት ጋርም ግንኙነትና ትብብር ለማድረግ አመች ይሆንለታል። 

[የሜጀር ጀነራል ውባንተ አባተ መታሰቢያ]

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here