spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ከንቲባ

የአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ከንቲባ

በእስያኤል ዘ ኢትኤል
መጋቢት 2016 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 24/2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጥግ እንዲሁም ከምዕራብ እስከምስራቅ ዳርቻ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ በማግኘት በህዝብ ከረዥም ጊዜ በኋላ ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው መሪ ሆኑ፡፡ በተለይም ህዝብ ሊሰማ የሚፈልገውን ንግግሮች በማድረግና የህዝቡን ለውጥ መፈለግን በመጠቀም እኔ አሻጋሪችሁ ነኝ አሻግራችኋለው በማለት ህዝብ ከእሳቸው ብዙ እንዲጠብቅ ሆኖ ነበር፡፡ 

ትንሽ ሳይቆይ ግን በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ግድያዎች፣ አፈናዎች፣ቁሳዊ ውድመትና የህግ የበላይነት ጠፋ፤ በዚህም መንግስታቸው ችግሮችን ከመፍታትና የህግ የበላይነት እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮ እውቅና በመንፈግ መፍትሄ መስጠት ተሳናቸው፡፡ በዚህም ከብዙ ቦታዎች ሰዎች በገፍ መፈናቀልና መገደል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲፈጸም ሀይ የሚል አካል አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ታጣቂ ቡድኖች ሰዎችን ከሚገሉበትና ከሚያፈናቅሉበት ቦታ አድማሳቸውን በማስፋት እየተስፋፉ ብዛት ያላቸውን ቀበሌዎችን ወደመቆጣጠርና ማስተዳደር ከፍ እያሉ ሄዱ፡፡ በተለይም በኦሮሚያ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(OLA) ብሎ የሚጠራው ቡድን አብዛኛውን የኦሮሚያ የሚገኙ ቀበሌዎችን መቆጣጠርና ማስተዳደር ቻለ፡፡ 

በተመሳሳይ በህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፌደራል መንግስቱ ቁጥጥር ውጭ እየሆነ መጣ፡፡ በሌሎች የሀገሪቷ ክፍልም መንግስት እንደፈለገው መቆጣጠርና ማስተዳደር እየተሳነው መጣ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል እየሄዱ የሚያደርጉት የስራ ጉብኚትና  የህዝብ ውይይት በቀላሉ ማድረግ የማይቻሉ እየሆኑ መጡ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጭነት እየተባለ በተለያዩ ቦታዎች የፖርክና የመዝናኛ ቦታዎች ግንባታ መገንባት ጀመሩ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የሆነ ወጭ ተመድቦላቸው እየተሰሩ ፕሮጀክቶች ከሚያስፈልጋቸው የኢንፍራስትራክቸር ግንባታ ይልቅ፣ ሰላም መተኪያና ተወዳዳሪ የሌለው ነገር ሆኖ ሳለ በጠቅላዩ አስተሳሰብ በእኔ ጊዜ የተገነቡ ለማለት ብቻና ካድሬዎቹን ለማስጎብኚት እንዲሁም ፕሮፓጋንዳ ስራቸውን ለመስራት ተጠቀሙበት፤ እየተጠቀሙበትም ይገኛል፡፡

 መሰረታዊ የሆነውን ነገር የዘነጉት ጠቅላዩ ሰዎች ደህንነታቸው ሳይጠበቅ የትም ቦታ ሄደው መዝናናት የሚባል ነገር እንደማይታሰብ ከግምት ውስጥ አላስገቡትም ወይም ህዝቡ ምን ያመጣል የራሳችሁ ጉዳይ ብለው ይመስላል፡፡ እንደአብርሃም ማስሎን ንድፈ ሀሳብ ከሆነ የሰው ልጅ በመጀመሪያ መሟላት ያለበት መሰረታዊ ፍላጎት(ምግብ፣መጠጥ፣መጠለያ..) ሲሆን የመጀመሪያው ፍላጎት ሳይሟላ ወደ ቀጣዩ ፍላጎት አይሄድም፣ በሀገራችን ላይ እነዚህ ነገሮች ተሟልተዋል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው፤ ቢሆንም እየራበንም መዝናናት እንችላለን ተብሎ ይታሰብ፤ ቀጣዩ ፍላጎት የደህንነት ፍላጎት ነው፡፡በሀገሪቷ ባለው ነባራዊ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ የስጋት ችግር አለባቸው ከሚባሉ የአለም ሀገራት ውስጥ አንዷ ሆናለች፡፡ ስለሆነም እነዚህ የተገነቡ መዝናኛ ቦታዎች የተሰሩት ለአብዛኛው የሀገሪቷ ህዝብ አይደሉም ማለት ነው፡፡ የሚዝናኑት ጎብኚዎች ከውጭ ይመጣሉ ተብሎ ቢታሰብ የደህንነት ዋስትና በሌለበት ሀገርና የሀገራት ኢንባሲዎች የጉዞ ማስጠንቀቂ በሚሰጡበት ሀገር ማን መጥቶ ሊዝናናበት ይሆን፤ለማንኛውም ፕሮጀክቶቹ ምን አልባት ጊዜና ሁኔታን ከግምት ያላስገቡ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን አይጠቅሙ ማለት አይደለም፣ ሰላምና ደህንነት ሲረጋገጥ ያስፈልጉን ይሆናል፡፡ 

ነገሮች እየገፊ የሰላሙ ጉዳይ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት በመሄድ በተለያዩ አከባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ግጭቶችና በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የጦርነት ቀጠና በማድረግ በሚሊዩን ለሚቆጠሩ ህዝቦች ሞት ምክንያት ሆነ፤ ከጦርነት ያመለጡ ዜጎች ደግሞ በርሃብ አለንጋ ተገረፊ፡፡ በዚህም ሀገሪቷን አካልዳማ ሆነች፤ ንጽሃን በዘር ግንዳቸው ተሳደዱ እንዲሁም ከሰውነት በወጣ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ ሀገሪቷ ከለውጥ ወደ ማቆሚያ ወደ ሌለው ነውጥ ወስጥ ገባች፡፡

ጠቅላዩ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ህዝብን ማወያየትና መጎብኘት አቆሙ ከአዲስ አበባ ከወጡም በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ብቻ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጠቅላዩ የአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ከንቲባ በመሆን በአይነቱ አዲስ የሆነ ስልጣን አይነት ባለቤት ሆኑ፡፡ በየእለቱ ወይም በየቀኑ ጠቅላዩ ከንቲባ ትልቁ ስራቸው የአዲስ አበባ ውበትና ጽዳት፣ የወንዝ ዳር ፖርኮች፣ የመቶ ድሃ ቤት አፍርሶ ለአምስቱ ቤት ሰርቶ መስጠት፣ በከተማዋ የሚገኙ በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና በከተማዋ የሚካሄዱ ስብሰባዎችን መገኘትና መክፈት፣ የውይይት መድረኮችን በቤተ-መንግስታቸው ማዘጋጀት፣ የየክልሉን ባለስልጣናትና ካድሬዎች እንዲሁም ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍል የተወጣጡትን ሰዎች እየጠሩ ማወያየት ብቻ ሆነ ስራቸው፡፡

  በተለያዩ ጊዜ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ቦሌ መንገድ ያለውን አበባይን ቆረጡቡኝ፣ አዲስ የሰራውት መንገድ ላይ ሽንት ሸኑብኝ፣ ዛፍ ቆረጡብኝ…ወዘተ እያሉ የከተማዋን ጠቅላይ ከንቲባ  ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛል፡፡ ጠቅላዩ ከንቲባ ያለ እሳቸው እውቅና በከተማዋ አንዳችም የሆነ ነገር ማድረግም ሆነ ማሰብ እንደማይቻል ከንግግራቸውና ከተግባራቸው ማየት ይቻላል፡፡ ስልጣናቸው ልክ እንደ ማዕከላዊ አፍርካ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ 2018 በፊት የሀገራቸውን 10 ፐርሰንት ብቻ የሚያስተዳድር ሰው ነበሩ፤ ዋና ከተማዋንና  አከባቢዎን፤ 90 ፐርሰንት የሚሆነው የሀገሪቷ ክፍል በአማጽያን እጅ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጠቅላዩ ከንቲባ ዋና ከተማዋን ፣ ሸገር ከተማንና በቅርብ እርቀት ያሉ አከባቢዎችን በሙሉና በከፍል የሚያስተዳድሩ ሆኑ፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ግን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊቶች( መንግስት ሸኔ እያለ የሚጠራው) ከመዲናዋ የሚወጡ ሰዎችን በመጥለፍና በመግደል በቅርብ እርቀት ይንቀሳቀሳሉ፣ ዜጎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ወይም ከከተማዋ ወጥተው መግባት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ በዚህ ከቀጠለ ጠቅላዩ ከንቲባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በዋናነት በማስተዳደር ከተማዋ በሁለት ከንቲቦች የምትተዳደር ሊያደርጓት ይችላሉ፡፡ 

ጠቅላዩ ከንቲባ በተደጋጋሚ በሚሰጡት ማብራሪና ገለጻዎች ስለሀገሪቷ ጉዳዩች ከሚያወሩት ይልቅ ስለአዲስ አበባ የሚያወሩትና ያላቸው መረጃ የተሻለ ይመስላል፡፡ ለሚነሳባቸው የልማት ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ የሚሰጡት በአዲስ አበባ እየተሰሩ ስላሉ ፕሮጀክቶች እንጂ በጋንቤላ፣በትግራይ፣ በአፋራና በኦሮሚያ ስለተሰሩ ስራዎች አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ ተሰብሳቢዎችና የውጭ ሀገር እንግዶች የሚያሳዩት አዲስ አበባ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉትን ፕሮጀክቶች ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ክብር ጠቅላዩ ከንቲባ የሚያስተዳድሩትን የአዲስ አበባ ከተማ እንደመሆኑና ላለፊት 6 አመታት ሰራው የሚልቱን ስራዎች ያለው እዚህች ከተማ ላይ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ሌላው የሀገሪቷ ክፍሎች ከቁጥጥራቸው ውጭ በመሆኑ ስልጣንና ሀላፊነታቸው አዲስ አበባ ላይ ብቻ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ እንደ እኔ እምነት ጠቅላዩ ከንቲባ ለስልጣናቸው ካላቸው ፍቅር አኳያ ልክ እንደማዕከላዊ አፍርካ ሪፐብሊክ የራሻውን ቅጥረኛ ወታደር ዋግነር ቡድን ቀጥረው ግዛታቸውን 90 ፐርሰንቱን እንዳስመለሱ ሁሉ የማስመለስ ስራ አይሰሩም ብይ ባላምንም ሌላው የሀገሪቷ ክፍል ግን ላልታወቀ ግዜ ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሆነ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ በዚህም አዲስ አበቤ በሁለቱም ከንቲባዎች ፍዳውን መብላቱንና ከቀየው መነሳቱን የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here