spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትበሙስና የተነከረው የአዲስ አበባ የመሬት ጉዳይ

በሙስና የተነከረው የአዲስ አበባ የመሬት ጉዳይ

ENA

 ከልዑል ማቴዎስ 

ሙስና የሃገራችን የሥራ አካል መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። ምንም እንኳን የተለያዩ መንግሥታት ሙስናን ሲያወግዙና ከስሩ መንግለው ለመጣል ቃል ቢገቡም፤ ሙሥና እየጠነከረ፤ እየሰፋና፤ የሚያሳፍር የሌብነት ድርጊት መሆኑ ቀርቶ የሚኮራበት “ቢዝነስ” እንደሆነ ተደርጎ እየተወደሰ ነው።  

የብልፅግና ፓርቲ፤ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)  ስለሙስና አምርረው ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሰምተናል። ከዚህም አልፈው፤ ከፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተጨማሪ፤ እሳቸውን ያካተተ “ልዩ” ኮሚቴ አዋቅረው በሙስና ላይ “ዘመቻ” መጀመሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። የሙስና ዘመቻው በልዩ ኮሚቴው የተዋቀረ ሰሞን፤ በሙሥና ተጠርጠረው ስለተያዙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሰማን በኋላ፤ ሁሉም ነገር የወኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።  

በተለይ አሁን ከአዲስ አበባ የመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤ በመሬት አስተዳደር ውስጥ ባሉ ሹመኞች ስላለው ከፍተኛ ሙስና የሚሰሙ የሚዘገንኑ ነገሮች፤ የአደባባይ ሚስጥር ሆነው ሳለ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ልዩ ኮሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን መምረጡ ለእንደ እኔ ዓይነት ተበዳይ ግራ የሚያጋባ ነው።  

የመሬት ጉዳይ በትክክልና በተገቢ ሁኔታ የማይስተናገድ በመሆኑ፤ ሃገር እየተጎዳች፤ ወደ ሃገራችን መጥተን መስራት ለምንፈልገውም ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው። ከዛሬ 16 ዓመት ገደማ በፊት፤ በአጋሮ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሼ በገዛሁት የግል ይዞታ በሆነ መሬት ላይ ግንባታ ለማድረግ ፈቃድ ስጠይቅ ጉቦ በመጠየቄ፤ ጉቦውን ላለመክፈል በመወሰን፤ ተመልሼ ወደ ስደት ሃገሬ ለመሄድ ተገድጃለሁ። ያፕሮጀክት ቢሳካ ኖሮ፤ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል በፈጠረ ነበር። ያ ቦታ ዛሬም ድረስ አረም ይነገሰብት ቦታ ሆኖ ቀጥሏል። በእንደዚህ ዓይነት “አገር ገዳይ” ባለሥልጣናት ዛሬ ተባብሶ የቀጠለው ሙስና ብዙዎችን እያማረረ ከመሆኑም አልፎ፤ ወደ ሃገራችን ተመልሰን፤ ለሃገራችን ግንባታ አስተዋጽኦ እንዳናደርግ ከፍተኛ ማነቆ ሆኗል።  

በሃገር ተስፋ አይቆረጥም በሚል ስሜት፤ ከጥቂት ወራት በፊት፤ ወደ ሃገሬ ተመልሼ መዋእለ ነዋዬን ለማፍሰስና ፤ ለጥቂት የሃገሬ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር በማሰብ፤ የህንፃ ግንባታ ለማድረግ፤ የመሬት ይዞታ በሊዝ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ፤ ለጉቦ የተጠየቅኩት የገንዘብ መጠን፤ የልብ ትርታዬን ሊያስቆም የሚችል የገንዘብ መጠን ነበር። ጉቦ የጠየቀኝን ሹም “ይህንንን ለአለቆችህ እነግራለሁ” ስለው “በምፀት ፈገግታ” “ንገራቸው፤ እነሱ ጨምረው ያስከፍሉሃል” ሲለኝ የተሰማኝ ልብ ሰባሪ ስሜት ነበር። ወይ ሃገሬ! መቼ ነው ኢትዮጵያ ከሙሥና የምትፀዳው? እኔ የምኮንነው ጉቦ ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን ሰጭውንም ጭምር ነው። ሰጭ ከሌለ ተቀባይ አይኖርም።ባለመስጠት የምናጣው ነገር ሊኖር ይችላል፤ ግን ይህንን የሃገር ካንሰር የሆነውን በሽታ እየቀነስን እንሄዳለን የሚል ተስፋ አለኝ። 

ያጠፋሁትን ገንዘብ አጥፍቼ፤ አሁንም ጉቦ ላለመስጠት በመወሰን፤ የምፈልገውን ነገር ሳላደርግ ወደ ስደት ሃገሬ ተመልሻለሁ። ብዙ የማውቃቸው ሰዎች፤ “ጉቦ ካልሰጠህ መሥራት አትችልም” የሚለውን ነገር እንደ መርህ ይዘውታል። ይህንን መቼም ነጋ ጠባ “ሙስናን እንዋጋለን” የሚሉን ባለሥልጣኖች ሳያውቁት ይቀራሉ ለማለት አልችልም። ይህ ሁሉ አቤቱታ እያለ፤ ጉዳይ ለማስፈፀም፤ ከቀበሌ ተላላኪ እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣን ገንዘብ ካልሰጠነው ሥራ አይሰራልንም እያለ ሕዝብ በህዝብ መገናኛ አውታሮች ሁሉ እየተናገረ፤ የፌደራል ሥነ ምግባርና ሙስና ክሚሽን የተባለው ተቋም ምን እየሰራ ነው ብሎ የሚጠይቅ እንዴት ይጠፋል?  

አንዳንድ የማውቃቸው አሜሪካውያን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመስራት ከፍተኛ ገንዘባቸውን አባክነው፤ በማያቋርጥ የጉቦ ቢሮክራሲ ተማረው፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ላለመሄድ መወሰናቸውን ሲነግሩኝ፤ እጅግ እሸማቀቃለሁ። አንዳንዶቹ ያባከኑት ገንዘብ እንዲመለስ በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ክስ ለመመስረት እያቅማሙ መሆናቸውን ነግረውኛል። ይህ ለሃገር ምን ያክል ውርደት እነደሆነ ምን ያህሎቻችን እንደሚገባን አላውቅም። በጣም የሚገርመው ጉቦ ጠያቂዎቹ የሚጠይቁት ከፍተኛ ገንዘብ በዝቷል ሲባሉ፤ “ይህ ከላይ እስከታች የምንከፋፈለው ነው” የሚሉት ድፍረት የተሞላበት አባባል አላቸው። ይህ አለም ያወቀው፤ ፀሃይ የሞቀው በሽታ መንግሥት እያውቀው መፍትሔ ያላበጀለት በሽታ መሆኑ፤ “ሙስናን እንዋጋለን” “ሌብነትን እንዋጋለን” የሚባለው ከመፈክር ያላለፈ መሆኑን ይነግረኛል።  

ይህ የሃገር ጥፋት እንዲቀጥል፤ የሕዝብ መገናኛ አውታሮችም ጥፋት አለበት። መገናኛ አውታሮች ምን እየሰሩ ነው? የሕዝቡን ምሬት ያውቃሉ፤ ግን መሬት ላይ ወርደው የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ በመስራት፤ ሙሰኞችን ለማጋለጥ ታታሪ ሆነው አለመስራታቸው ችግሩን አባብሶታል ብዬ አምናለሁ። ችግሩ የሁላችንም ነው፤ ካልተባበርን፤ ጣት በመጠቆም ብቻ ልንወጣው አንችልም። ስለዚህ፤ ይህንን አገር ገዳይ የሙስና በሽታ፤ በተለይ በመሬት አስተዳደር፤ እንዲሁም በሌሎች መስሪያ ቤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ፤ ችግሩ በአስቸኳይ እየተቀረፈ እንዲሄድ ሊደረግ ይገባዋል። ጋዜጠኞችም ሥራችሁን በመስራት፤ የመፍትሔው አካል እንድትሆኑ በትህትና እጠይቃለሁ።  

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here