spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኦሮሞ ጥያቄ ምንድን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ ምን ይፈልጋል? 

የኦሮሞ ጥያቄ ምንድን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ ምን ይፈልጋል? 

የኦሮሞ ጥያቄ ምንድን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ ምን ይፈልጋል? 

አሰፋ አበበ

) የኦሮሞ  ዋና ዋና ጥያቄዎች

በኦሮሞ ጥያቄ ላይ ማለትም የኦሮሞ ሕዝብ በፖለቲካው ረገድ ምን ይፈልጋል? በሚለው ጉዳይ ላይ ኦሮሞን እንወክላለን ወይም ለኦሮሞ ቁመናል በሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከልም ሆነ ለኦሮሞ እንቆረቆራለን በሚሉ ምሁራንና ኤሊቶች መካከል መግባባት የለም:: ይህ ጽሑፍ በኦሮሞ ጥያቄ ላይ በኦሮሞዎች መካካልና ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያኖች መካከል ውይይት ለመጫር በማሰብ የቀረበ ነው::

በኦሮሞ ጥያቄ ላይ መግባባት አለመኖር ኦሮሞዎች ተከፋፍለው እንድጋጩና አንዲዋጉ ምክንያት ሆኗል:: ይህ በኦሮሞ ጥያቄ ላይ ተለያይቶ  መጋጨት እ. አ. አ. ከ1992 ጀምሮ ተባብሶ ቀጥሏል:: በአሁኑ ጊዜ ይህ ልዩነት በዋነኛነት ኦሮሞን አንወክላለን በሚሉ አራት የፖለቲካ ድርጅቶች ይንጸባረቃል:: እርሱም 1) የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ክንፍ፤2) የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንጉሬስ፥ 3) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፥ እና 4) የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ናቸው:: የእነዝህ ድርጅቶችን  የትግል ስልት ትተን ክፍፍሉን ስናይ ግን የኦሮሚያ ነጻነትን የሚደግፉና የማይደግፉ ብለን ለሁለት ክፍለን ማየት እንችላለን::

የኦሮሞን በፖለቲካ መከፋፈልና አለመግባባት ለመቀነስ የኦሮሞን ጥያቄ አንደገና መርምሮ በመተንተን ማጥራትና በጠራው የኦሮሞ ጥያቄና ፍላጎት ዙሪያ ሕዝቡን ማሰለፍ ያስፈልጋል:: ለዝህም በተለያዩ ጊዜያት የኦሮሞ ጥያቄዎች ናቸው ተብለው የተነሱትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንስተን ጥያቄዎቹ ሊፈቱ የሚችሉበትን ሁኔታዎችን መመልከት ያስፈልጋል:: 

እነርሱም:

 1. የኦሮሞ የነጻነት ጥያቄ የኦሮሞ ነጻነት ትግል አባት ከሆኑት ውስጥ  አንዱ አቶ ኤሌሞ ቂልጡ ነው:: እርሳቸው ለነጻነት ትግል ወጥተው እ.አ.አ. በ1974 የመጀመሪያውን ጥይት ስተኩሱ “ይህ የኦሮሞ ነጻነት ድምጽ ነው” ብለው አንደተኮሱ ይነገራል:: “የኦሮሞ ነጻነት” ማለት ምን ማለት ነው? ኦሮሞዎች የምኖሩበትን አከባቢ(ኦሮሚያን) ከኢትዮጵያ ግዛት ነጥለው የራሳቸው ነጻ አገር መመስረት አለባቸው ማለት ነው ወይስ ከማንኛውም የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጭቆና ነጻ ወጥተው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሰላምና በአንድነት ይኖራሉ ማለት ነው? በዝህ ጉዳይ ላይ በኦሮሞዎች መካከል መግባባት የለም:: በመሆኑም በዝህ ምክንያት ቀደም ሲል በኦሕዴድና በኦነግ መካከል አሁን ደግሞ በብልጽግና ፓርቲና ኦነግ-ኦነሠ መካከል ግጭት ይታያል::

የኦሮሞ ነጻነት ትግል አባት የሆኑትና የኦነግን የመጀመሪያውን ፕሮግራም ከጻፉት ሶስት ሰዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዲማ ነገዎ ኦክቶበቤር 21/2023 በ“ቢርጅ ሚዲያ” ላይ ቀርበው እንደገለጹት የመገንጠል ወይም ነጻ የኦሮሚያ ሪፓብሊክ ምስረታ የሚባለው ነገር በመጀመሪያው የ1973ቱ (እ. አ. አ.) የኦነግ ፕሮራም ውስጥ የለም ብለዋል:: ይህ ሀሳብ በ1976 በችኮላ በተጻፈውና እስከ አሁን ባልተሻሻለው የኦነግ ፕሮግራም ውስጥ የገባ ነው፤ ይህም መታረም ያለበት ስህተት ነው ብለዋል::

ዶ/ር ዲማ ነገዎ ከሌላው የኦሮሞ ነጻነት ትግል አባትና የ1973ቱን የኦነግ ፕሮግራም ከጻፉት ሶስት ሰዎች አንዱ ከሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ ጋር ሆነው የኦሮሞ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈታ ይችላል ብሎ የሚያምን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የተባለ ድርጅት ማቋቋማቸው ይታወሳል፥፥

የ2023 የኦነግ-ኦነሠ የፖለቲካል ማኒፈስቶም ኦነግ-ኦነሠ ለኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ  የመወሰን መብት መከበር፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከፖለቲካ መገለል፤ ከኢኮኖም ብዝበዛና ከማህበራዊና ባሕላዊ መገለል ነጻ መውጣት እንታገላለን ይላል አንጂ ስለመገንጠል ወይም ስለነጻ ኦሮሚያ ወይም ስለ ኦሮሚያ ሪፓብሊክ ምስረታ አያነሳም::

ታዲያ በየንግግሩና ጽሁፉ የሚነሳው የነጻ ኦሮሚያ ምስረታ ጉዳይ ምንጩ ምንድነው? የ1976ቱ የኦነግ ፕሮግራም? ይህ ፕሮግራም ለግማሽ ምዕተ አመት ለምን አልተሻሻለም?

 1. የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በኦነግ-ኦነሠ በመጀመሪያ ደረጃነት የሚጠየቀውና የመታገያ አጀንዳ የሆነው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 29 የተከበረ ነው:: የጭቅጭቅ ምክንያት እየሆነ ያለው የራስን ዕድል የመወሰን ውይይትና ሪፌሬንደሙ ኦሮሚያ በማን ቁጥጥር ሥር እያለች መሆን አለበት– በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ሥር ወይስ በኦነግ-ኦነሠ ቁጥጥር ሥር የሚለውና አካሄዱ/ ፕሮስጀሩ ነው::
 2. የአፋን ኦሮሞ ጥያቄ በ2014-2018 የቄሮ ንቅናቄ ወቅት ጎልተው ከተሰሙ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግስት የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት የሚል ነበር:: የዝህ ጥያቄ ገፊ ምክንያትም በፌዴራል  መንግስት ተቋማት ውስጥ የሥራ ዕድል የማግኘት ጉዳይ ነው:: በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 5 መሰረት የፌዴራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው::  ስለዝህ ጥያቄውን ለመመለስ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል:: ሆኖን ግን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕገ መንግስት መሻሻል ረገድ ስሰሩ አይታይም:: የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም የኦሮሚኛ ቋንቋ አገልግሎት በክልሉና በጎረበት ክልሎች እንዲዳብር በቂ ሥራ እየሰራ አይደለም::

አፋን ኦሮሞን የፌዴራል መንግስት የሥራ ቋንቋ የማድረግ ሙከራ ካልተሳካ ኦሮሞዎችና ሌሎች አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ዜጎች እንዳይጎዱ ሌላ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዘኛን የፌዴራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ በሕገ መንግስቱ ረቂቅ ውይይት ወቅት የተነሳ ጉዳይ ነበር:: በመሆኑም ቢያንስ እንግሊዘኛን የፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ የሥራ  ቋንቋ ማድረግ ይቻላል::

 1. በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ መብት/ ጥያቄ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል መሆን አለበት ወይስ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 እንደተቀመጠው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለው ሁኖ በከተማው የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም መጠበቅ አለበት የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ነው:: በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ላለፉት 29 ዓመታት ዝርዝር ሕግ ባለመውጣቱ ውዝግቡ ለተራዘመ ጊዜ እንዲካሄድ  ሆኗል:: በመሆኑም ዝርዝር ሕጉን ቶሎ ማውጣትና ጉዳዩን መቋጭት ያስፈልጋል:: የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ድንበር መካለሉ ግን ጥሩ አርምጃ ነው::
 2. የኦሮሞ የነፃነት ትግል አባቶች ቃል አተረጓጎም የኦሮሞ ነጻነት፥ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት መብት፥ ኦሮሚያ አገር ነች: በራስ ሃብት ላይ የማዘዝ መብት: የኦሮሚያ ድንበሮች: የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባሉ ቃላቶችና ሐረጎች አተረጓጎምና አፈጻጸም ላይ መወያየትና የጋራ መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል::
 3. የኦሮሞ አንድነት/ ኦሮሙማ ጉዳይ ኦሮሞ ማን ነው? አንድ ሰው ምን አይነት ባሕልና አስተሳሰብ ስኖረው ነው ኦሮሞ የሚባለው? የኦሮሚያ ነጻነትን መደገፍና አለመደገፍ የአንድን ሰው ኦሮሞነት (ኦሮሙማ) ደረጃ ይወስናልን? በዝህ ላይ መወያየትና የጋራ መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል:: ኦሮሙማ ምን እንደሆነ ለሌች ማስረዳት በእነርሱ ላይ ምንም ዓይነት ጎጂ ተጽዕኖ እንደለለው መግለጽ ያስፈልጋል:: የኦሮሞ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለይቶ አውቆ መሥራት፤ ለኦሮሙማ ድጋፍ የሚያስገኙ ተግባራትን ማከናወንና ያሉትን ውዥንብሮች ማጥራት ያስፈልጋል::
 4. የዲሞክራሲ ጥያቄ ጉዳይ የዴሞክራሲ መስፈን የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ ይችላል ወይስ አይችልም? ኢትዮጵያ ኢምፓዬር ናት፤ ኢምፓዬር ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አገር መሆን ስለማይችል መበተን አለበት የሚለው አባባል ምን ያክል ትክክል ነው? በዝህ ጉዳይ ላይ መወያየትና የጋራ መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል::

) የኦሮሞ የወደፊት የትግል አቅጣጫ 

ሰላማዊ ትግል ወይስ የትጥቅ ትግል– ለኦሮሞ የቱ ይሻላል? ኦነግ አላማውን በትጥቅ ትግል ለማሳካት ለ50 ዓመታት ታግሏል:: ካነሳቸው ጥያቄዎች አንዳንዶቹ የተመለሱ ቢሆንም አንዳንዶቹ ነጻ ኦሮሚያን የመመስረት ጥያቄን ጨምሮ አልተመለሱም:: ስለዝህ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ የትጥቅ ትግሉ መቀጠል አለበት ወይስ በሰላማዊ  መንገድ መታገል ይሻላል ወይስ ጥያቄዎቹን እንደገና መመርመር ያስፈልጋል? የሌሎች አገሮች/ ድርጅቶች ተሞክሮ ምን ያስተምረናል? ለምሳሌ:

 1. ከናይጄሪያ ገንጥሎ የባይፍራ ሪፑብሊክ ለመመስረት እ.አ.አ. ከ1967-1970  የተደረገው ጦርነት ዓላማውን አላሳካም:: 
 2. የኮሎምቢያ ማዕከላዊ መንግስትን በኃይል ለማስወገድ እ.አ.አ. ከ1964-2016 በFARC የተደረገው ጦርነት ዓላማውን አላሳካም:: 
 3. ከስሪ ላንካ ገንጥሎ ለታሚሎች አገር ለመመስረት እ አ.አ. ከ1972-2009 በታሚል ታይግር የተደረገው ጦርነት ዓላማውን አላሳካም::
 4. ሰሜን አይርላንድን ከእንግልዝ ለመገንጠል እ.አ.አ. ከ1969-2010 በ IRA/Sinn Fein የተደረገው ጦርነት ዓላማውን አላሳካም::
 5. የፖሊሳሪዎ ግንባር ሳራዊ ሪፑብሊክን ለመመስረት እ.አ.አ. ከ1973 እስከ አሁን  ያደረገው ጦርነት ዓላማውን አላሳካም::
 6. አዛኒያ የተባለ የጥቁሮች ብቻ አገር በደቡብ አፍሪካ ለመመስረት እ.አ.አ. በ1959 ከANC የተገነጠለው Pan Africanist Congress (PAC) ሙከራ አልተሳካም::
 7. ከካሜሩን ገንጥሎ አምባዞኒያ የተባለ ለእንግሊዘኛ ተናጋሪ ካሜሩናዉያን አገር ለመመስረት እ.አ.አ. ከ2017 ጀምሮ በአምባዞኒያ አማጽዎች የተካሄድው አመጽ ዓላማውን አላሳካም::
 8. የኤርትሪያ የነጻነት ትግል በሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ጎራዎች መካከል ያለውን ክፍፍል ተጠቅሞ ሶሻሊስት የነበረውን የኢትዮጵያ መንግስት ለማዳከም ከምዕራባውያን በተደረገለት ዕርዳታ እ.አ.አ.  በ1991 ዓላማውን ቢያሳካም ኤርትሪያ ለዜጎችዋ  የተመቸች አገር መሆን አልቻለችም::
 9. ደቡብ ሱዳን በደቡቡ ጥቁር ክርስቲያንና በሰሜኑ የዐረብ ዝሪያ ያለው ሙስሊም መካከል ባለው ግጭት ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም አርዳታ አግኝታ እ.አ.አ.  በ2021 ከሱዳን ብትገነጠልም ለዜጎችዋ  የተመቸች አገር መሆን አልቻለችም::
 10.  የስኮትላንድ ብሔራዊ ፓርቲ ስኮትላንድ ከእንግልዝ ተገንጥሎ ነጻ አገር እንድሆን ያቀረበው ጥያቄ እ.አ.አ.  በመስከረም 2014 በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ ውድቅ ተደርጓል::   
 11. ኪዩቤክ ከካናዳ ተገንጥላ ነጻ አገር እንድትሆን የቀረበው ጥያቄ እ.አ.አ. በ1995 በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ ውድቅ ተደርጓል::
 12. ካታሎኒያ ከስፔን ተገንጥላ ነጻ አገር እንድትሆን የቀረበው ጥያቄ  እ.አ.አ. በጥቅምት 2017 በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ በአብዘኛው ቢደገፍም ስፔን ሕዝበ ውሳኔው ሕገ መንግስታዊ አይደለም ብላ ውድቅ አድርጋለች::
 13. ሶማሊላንድ እ.አ.አ.  በ1991 ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ያወጀች ቢሆንም እውቅና ስላላገኘች እስከ አሁን ነጻ አገር መሆን አልቻለችም::

በአጭሩ የነጻነት ወይም አገር የመሆን ጥያቄን የሚያቀነቅኑ ድርጅቶች ለሪፌሬንዴም የሚያስፈልገውን ሂዴት፥ የአብዘኛውን ድምጽ ሰጪ ሕዝብ ፍላጎት፥ በጉልበት ያለፍላጎቴ ይዞኛል የሚባለው አገር ምላሽና የዓለም መንግሥታት ምላሽን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል:: በጦርነት ማሳካት የሚፈለገው ዓላማ የመሳክት ዕድልና ሙከራው የሚያስከፍለው ዋጋ በደንብ መመዘን አለበት::

የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸውንና አሰራራቸውን የማሻሻል ችግር እንዳለባቸው ግልጽ ነው:: ሌላው ቀርቶ የጎደሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎቻቸውን እንኳ አሟልተው ሥራቸውን በብቃት መሥራት አልቻሉም:: ስለተዘጉ ቢሮዎቻቸው ደጋግመው ከመናገር አልፈው በአይ.ቲ. ወይም ሌላ ዘመናዊ መንገድ ተጠቅመው አባላት ማፍራትና ማደራጀት አልቻሉም:: የኦሮሞ ምሁራንም  ከቀላዋጭ ፖለቲካነትና ባሉበት ከመርገጥ አልፈው ለኦሮሞ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ/ የሚያመጣ አዳዲስ ሀሳብ ማመንጨት አልቻሉም:: የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች አሰራሪም፥ የኦሮሞ ምሁራን አስተሳሰብም፥ የኦሮሞ ሕዝብ ችግርም አዙሪት ውስጥ ገብተዋል:: አዳዲስ አስተሳሰብ፥ አዳዲስ ስትራቴጅና አዳዲስ ታክቲክ ሥራ ላይ በማዋል አዙሪቱን መስበር ያስፈልጋል:: የኦሮሞ ሕዝብ ችግርና መፍትሔው እንደገና መታየት አለበት (Oromos will have to go back to the drawing board).

በኦሮሚያ ያለውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከልና በኦነግ-ኦነሠና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተለያዩ የእርቅ/ የሰላም ምክክሮች ተካሂደዋል:: ሆኖም ግን ውጤታማ ልሆኑ አልቻሉም:: የሩቁን ትተን የቅርቡን እ.አ.አ. 2023 በኦነግ-ኦነሠና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በታንዛኒያ የተካሄዱትን ሁለት ዙር የሰላም ምክክሮች/ ደርድሮች የከሸፉበትን ምክንያቶችን በአጭሩ እንመልከት::

) የዛንዝባሩና የዳሬ ሰላሙ የእርቅ/የሰላም ውይይቶች ለምን ከሸፉ? የእርቅ የወደፊት ዕድልስ?

ማንኛውም ድርድር ስደረግ ተደራዳሪዎችን የሚያስማሙ ጉዳዮች አውቆ በእነርሱ ላይ (Zone of Possible Agreement/ ZOPA) የበለጠ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል:: ተደራዳሪዎቹ በድርድሩ ወቅት መቀበል የሚችሉትን አነስተኛውን የስምምነት ሃሳብ (Best Alternative To a Negotiated Agreement /BATNA) ለይተው በሰጥቶ መቀበል መሪህ ስምምነት ላይ ለመድረስ በቅንነት መስራት ይገባቸዋል:: አለመታደል ሆኖ በሁለቱም ዙር የታንዛኒያ ድርድሮች ይህንን ዝግጁነትና ቅንነት አላየንም:: 

የታንዛኒያው ድርድር የከሸፈበት ዋናው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው::

 1. የሽግግር መንግስት ይመስረት ጥያቄ የኦነግ-ኦነሠ ተወካይ አቶ ቀጀላ ሲራጅ ኖቬምበር 23, 2023 እንደገለጹት የዳሬ ሰላሙ የእርቅ ድርድር የከሸፈው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ብሎ ኦነግ-ኦነሠ ያቀረበውን ሀሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት አልቀበልም በማለቱ ነው ብሏል::
 2. የሥልጣን ክፍፍል/ ሥልጣን የመያዝ ጥያቄ  የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒከሽን ኖቬምቤር 21, 2023 ባወጣው መግለጫ ኦነግ-ኦነሠ “መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ” ከሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርደር ነጥብ ማምጣት አልቻለም” ብሏል:: የሚሰጠውን ሥልጣን ተቀብሎ ወደ መንግሥት ለመካተትም ኦነግ-ኦነሠ ፈቃደኝነትን አላሳየም ስልም ከሷል::
 3. የትጥቅ መፍታት ጥያቄ የየራሳቸው የጦር ኃይል ያላቸው ሁለት መንግስታት አንድ አገር ማስተዳደር ስለማይችሉ a monopoly on violence እና Disarmament, Demobilization, and Reintegration (DDR) መርሆችን  ተከትሎ ትጥቅ መፍታት የግድ ይሆናል::
 4. የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ መቼና እንዴት?- የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ  የሕገ-መንግስቱን መርሆች ተከትሎ እንዲፈጸም ማድረግ ያስፈልጋል::
 5. የኦሮሞ ጥያቄአይሸራረፍምመፈክር ጉዳይ የኦሮሞ ጥያቄዎች በአግባቡ ቢለዩ፤ ቢሻሻሉ፤ የጊዜ ሰሌዳ ቢኖራቸው ማለትም በአጭር፤ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ቢከፋፈሉ ጥሩ ነው:: ጥያቄአችን አይሸራረፍም በማለት አንድ ቦታ ተቸክሎ መቅረትና ለውደፊት ድርድር ይሆናሉ ተብለው የተነሱትን ጥራቄዎች (horse trading price) በሙሉ ካላገኘን ማለት አያስከድም::
 6. የፉከራና የመናናቅ ጉዳይ በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው መካከል መናናቅና መፈራራት መኖሩ ይታወቃል፤ መተባበሩ ቢቀር መናናቁና መፈራራቱ መቅረት አለበት:: ተከባብሮ አብሮ መስራት መለመድ አለበት:;

አሁን ባለበት ሁኔታ የኦሮሚያን ችግር ሊፈታ የሚችል የሰላም ስምምነት በኦነግ-ኦነሠ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል  በአጭር ጊዜ ሊደረግ ይችላል ብሎ መጠበቅ አይቻልም:: የኦነግ-ኦነሠ መሪ መሮ ድሪባ አፕሪል 13,2024 የኦሮሞ አርበኞችና ሰማዕታት ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት “በታንዛኒያው ድርድር ለብዙ ጉዳይ መቋጫ ማድረግ ይቻል ነበር:: ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት መገዳደል ይብቃ ወደ መሃል መንገድ መጥተን ጉዳያችንን በዕርቅ እንቋጭ የሚል ፍላጎት ያለው ሳይሆን እንደ ዘንዶ ሰው መዋጥ የሚፈልግ በሆኑ ይህ ሳይሆን ቀርቷል:: ኦሮሞ ቁርጡን ማወቅ ይገባዋል፥ እጅ ስጡና ግቡ ካልተባለ በቀር ከዝህ መንግሥት ጋር ዕርቅ የማድረግ ተስፋ የለም:: በመሆኑም መጪው መስዋዕትነት ካለፈው የከበደ ይሆናል” ብለዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም በበኩላቸው  አፕሪል 20, 2024 በማዕክላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ከተማ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አመለካከት አለ:: አንደኛው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፤ ትበታተናለች የሚል ሲሆን እኛ ደግሞ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች የአፍሪካ የነጻነት፤ የኢኮኖሚ፤ የሰላም: የአንድነት ምሳሌ ትሆናለች እንላለን:: እነዝህ ሁለት ሃሳቦች በቀላሉ አይታረቁም” ብለዋል:: በተጨማሪም “በጫካና በአንዳንድ ስፍራ የሚትገኙ ኢትዮጵያውያን ከላካችሁ ኃይል ኢትዮጵያ ትበልጣለች፥ ከሚከፍላችሁ ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጣለች:: ለኢትዮጵያ አንድነት ለኢትዮጵያ ሰላም፥ ለኢትዮጵያ ብልጽግና በጋራ እንዲንቆምና ከከፋፋይ፥ ከሰፈርተኝነት፥ ከመንደር እሳቤ ነጻ ወጥታችሁ ወደ ኢትዮጵያዊነት ከእኛ ጋር እንዲታድጉ በጉራጌ ሕዝብ ስም ዛሬ ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ” በማለት ጫካ ያሉት አማፂዎች የራሳቸው ዓላማ የሌላቸው የውጭ ኃይል ተላላኪዎችና ተከፋዮች: ወደ ኢትዮጵያዊነት ደረጃ ያላደጉ መንደርተኞች ናቸው ስሉ ከሰዋቸዋል:: ጥሪው ኑና ከእኛ ካደግነው ጋር ተቀላቀሉ የሚል እንጂ ተመካክረን፤ ተደራድረን፥ በሰጥቶ መቀበል መሪህ አብረን እንስራ የማለት አይመስልም:: በመሆኑም በድርድርና በእርቅ ጉዳይን የመጨረስ ዕድል ጠባብ ይመስላል::

) ማጠቃለያ

ኦሮሞዎችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ልዩነታቸውን በሰላማዊና በምክክር ቢፈቱ ለእነርሱም ለአገርም ይበጃል:: የእርስ በእርስ ግድያ፥ ውንጀላ፥ ስም መጠፋፋት ለማንም አይጥቅምም:: በታጠቁ ኃይሎች ፍትጊያ ሰላማዊው ዜጋ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንድወድቅ፤ ሥራ አንዳይሰራ መተጓጓልና ወጣቱ አመጸኛ እንድሆን መደረግ የለበትም:: ምሁሩ ሀሳቡን እንዳይገልጽ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቁ መሪ እንዳይኖራቸው፤ ክልሎች በሕግ የተሰጣቸውን ሥራ ትተው የቃል ትዕዛዝ ፈጻሚ አሽከሮች (cundhura): እንድሆኑ ማድረግ: ፖለቲካው እንዲሽመደመድና  የተለየ ሀሳብ ያለውን መግፋት ለአገሩ አይበጅም:: ነገሮች ካልተሻሻሉ ሕዝቡ ያለው አማራጭ ያው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለመደው “ወይ ገብር ወይ ሸፍት” የሚለው ሁለት ምርጫ ብቻ ይሆናል::አሁን ካለው አድርግ አታድርግ ፖለቲካ ተላቀን ኢትዮጵያ በውይይትና በዴሞክራሲ ለሁሉም ዜጋ እንዲትሆን አድርገን ካልቀረጽን ሥቃዩ የሁሉም ዜጋ ይሆናል:: የኦሮሚያ ፕረዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አፕሪል 7, 2024 በፌስ ቡካቸው አንዳሉት ከመጨራረስ ይልቅ ጉዳያችንን በንግግር ብንጨርስ ይሻላል::

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና የኦሮሞ ምሁራን የኦሮሞ/ የኦሮሚያ ችግር በሰላም እንዲፈታ በትጋት መስራት ይኖርባቸዋል:: የኦሮሞ ችግር መፈታት ግማሹን የኢትዮጵያ ችግር መፍታት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለችግሩ መፈታት አስተዋጾ ማድረግ ይጠበቅበታል:: አለዝያ ግን የኦሮሞ ችግር ለሌላውም ተርፎ ሥቃዩ የጋራችን ይሆናል::

========================መጨረሻ ========================

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here