spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየስርዓቱ ጠባቂዎች (ጋቸነ ስርና እና የሰላም ሠራዊት )

የስርዓቱ ጠባቂዎች (ጋቸነ ስርና እና የሰላም ሠራዊት )

አብዮት ጠባቂ _ Oromia

እስያኤል ዘ ኢትኤል
ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ላለፊት ስድስት አመታቶች በመጠኑና በይዘቱ ከፍተኛ የሆነ ያለመረጋጋት ውስጥ የገባችበት ወቅት ነው፡፡ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት አልቻሉም፤ላባቸውን አፍሰው ያፈራቱን ሀብት በጠራራ ፀሃይ ተዘርፈዋል ሲከፋም ወድሞባቸዋል፡፡ በአንዳንድ አከባቢዎችም ዜጎች የዘር ግንዳቸው ተቆጥሮ እርጉዝ፣ህጻናት፣ ወጣቶች፣ እናቶችና አባቶች ተገድለዋል፤በህይወት ከተረፉም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ለውጥ መጣ በሚል ከዳር እስከ ዳር በተለያዩ ሁኔታዎች ሀገሪቷ ስትናጥ ቆይታለች፤ አሁንም እየተናወጠች ቀጥላለች፡፡ የለውጥ ሀይል ነኝ፤ እኛ ኢህአዴግ ውስጥ የነበርን ቢሆንም እኛ እንለያለን ያሉት የብልጽግና ፖርቲ የተባለ አቋቁመው ህዝቡን ለመከራ፤ ሀገሪቷን ደግሞ መቆሚያ የሌለው ለሚመስል ትርምስ ውስጥ እንድንገባ እድርገው ይህው ድፍን ስድስት አመታቶች ሞሉን፤በየቦታው ደም መፋሰስ፣ረሃብ፣ጦርነት፣ ኢኮኖሚ ድቀት፣የህዝብ ተስፋ መቁረጥ እና ከሚኖሩበት ቦታ በሰላም ወጥቶ መግባቱ ብርቅ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

የሀገሪቷን የህግ የበላይነት ያስከብራል የተባለው መንግስት እራሱን መከላከል የማይችል ደካማ፤ በየቦታው መሳሪያ የታጠቁ አካላት የመንግስትን መዋቅር የሚቆጣጠሩበትና የራሳቸውን አስተዳደር የሚዘረጉበት ሁኔታ የተፈጠረ ሲሆን በተለያዩ የሀገሪቷን ሉዓላዊ ግዛቶች ውስጥ ጎረቤት ሀገራት በጉልበት ዘልቀው በመግባት የሀገሪቷን ሉዓላዊነት ተደፍሮ፣ ዳር ድንበሯ ያለጠባቂና ከልካይ በጎረቤት ሀገራት ተወሮ ተይዟል፡፡ ከእነዚህም ሀገራት ውስጥ ሱዳን፣ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ የሀገሪቷን ግዛት ጥሰው በመግባት ወደራሳቸው የመቀላቀልና የራሳቸውን አስተዳደር እስከመዘርጋት ደርሰዋል፡፡ በዚህም የሀገርቷ ክብር ተዋርዷል፣ ሉአላዊነቷ ተደፍሯል፡፡ በተለይም ባለፊት ስድስት ዓመታት ያለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ብቻ በመመስረት ሀገርቷን ተገማች ሀገር እንዳትሆንና እንደጠባጫሪ ሀገር ተቆጥራለች፡፡ የለውጡ ሀይል ነኝ የሚለው መንግስት ከመጣ ወዲህ በኢህአዴግ ጊዜ የሚሰራባቸው የነበሩ የተለያዩ የሀገሪቷ ፖሊሲዎችን ወደ ጎን ተትተው ጠቅላዩ እራሳቸው ፖሊሲም፣ ህግም ሆነው አሉ፡፡

በተለይም በትግራይ የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በክፍለ ዘመኑ ከተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ እጅግ ዘግናኝና ያልሰለጠነ ጦርነት የተከሄደበት፤ የብዙ ንጽሀን ዜጎች ህይወት የቀጠፈ፣ የጎረቤት ሀገር ጦር የተሳተፈበት፣ ከፍተኛ የጦር ወንጀል የተሰራበት፣ በየትኛውም በኩል ያሉ ወንጀል የሰሩ ሃይሎች ተጠያቂ ያልሆኑበት አውዳሚ ጦርነት ነበር፡፡ በዚህም ጦርነት ምክንያት ማዕከላዊ መንግስቱ(ፌደራል መንግስቱ) የተዳከመበትና እራሱን በዋና ከተማዋ ላይ ገድቦ የተቀመጠበት ጊዜ ነው የተፈጠረው፡፡

መንግስት የህዝብንና የራሱን አመራሮች ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ቢኖርበትም አቅሙ ስለተዳከመ በተለያዩ አከባቢዎች ከመደበኛው ፀጥታ መዋቅር ውጭ መንግስት በሃይል ገፍቶ ይመጡብኛል ብሎ የሚያስባቸውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህውሃት)ና የትግራይ መከላከያ ሃይልን(TDF)፣የአማራ ፋኑ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ተደራጅተው በትጥቅ ትግል መንግስትን እንቀይራለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ይከላከሉልኛል ብሎ የሚያስባቸውን በየቦታው በመመልመል ስልጠና በመስጠት የስርዓቱ ዘብ ጠባቂ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

የፎቶ ምንጭ፡ የምስራቅ ሸዋ ኮሙኒኬሽን

የመጀመሪያው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተደራጀውና በብዛት እየተደራጀ ያለው በኦሮሚኛ መጠሪያ ስሙ ጋቸነ ሲርና(Gaachana Sirnaa) ማለትም አብዮት ጠባቂ(ስርአቱን ጠባቂ) ማለት ሲሆን በክልሉ ባለው ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር ምክንያት መንግስት ስልጣኔን ይቀሙኛል የሚላቸውን ሃይላት ይከላከሉልኛል ብሎ ያደራጀው ነው፡፡ በተለይም በክልሉ የተደራጅቶ የሚንቀሳንቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ሠራዊት በመንግስት እምነት ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነትና ድጋፍ ስላለው እሱን ለመከላከልና በህዝቡ መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና እንዲጋጭላቸውን የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘምና ለማደላደል ይረዳናል ብለው በማሰብና ሀገሪቷ ላይ ባለው የብሔር ፖለቲካ ምክንያት ከሌሎች ብሔሮች ሊቃጣ የሚችለው ጥቃት ለማስቀረት የታፍራ ፖሊሲ (deterrence policy) ለመተግበር ያሰበ ነው፡፡

ብልፅግና በመላው ኦሮሚያ የጋቸነ ስርና እና የመንግሥት ሠራተኛውን ጨምሮ በሰፊው እያሰለጠነ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሀይላት ብልጽግና የራሱን ጊዜያዊ ሥርዓት ለማስጠበቅ የሚጠቀምባቸዉ ከማህበረሰቡ የተወጣጡ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸዉ:: የብልፅግና ውድቀት ግልፅ ከመሆኑም በላይ እየሄደበት ያለው ቁልቁለት አወዳደቁን ክፉ ያደርገዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን(መንግስት ሸኔ በማለት የሚጠራው) ፍለጋ በሚል ህዝቡን መግደል፣ ማሠር፣ ማሠቃየት ሳያንስ ጫካ ለጫካ ሲያዞርና ሲያንከራትት  የሚውለው እነዚህን የስርዓቱ ዘብ ጠባቂዎች ነው፡፡

ብዛት ያላቸው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ደጋፊዎችና አባላት እንደሚያስረዱት መንግስት የነጻነት ሠራዊቱን ስም ለማጠልሸትና በህዝብ እንዲጠላ ለማድረግ የነጻነት ሠራዊቱን ስም  ለውጥ በማድረግ ሲሆን በዚህም አዲስ ስም በማውጣት፤ ይህውም “ሸኔ” በማለት ከህዝቡ እንዲነጠል በተለያዩ ጊዜቶችና ቦታዎች ላይ በንጹሃን ላይ ጥቃት በመፈጸም የነፃነት ሠራዊቱ እንደፈጸመው በሚዲያዎቹ በማስነገር የነፃነት ሠራዊቱ በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና እንዲጠላ ለማድረግ ታስቦ ነው ይላሉ፡፡ አንድ የድርጅቱ ደጋፊ እንዳሉትም፡- 

“እኛ ለኦሮሞና በኦሮምያ ዉስጥ ለሚኖሩት ጭቁን ህዝቦች ነፃነት እንጂ የሚንታገለዉ በኦሮምያ ለዘመናት በሰላም የኖሩትን ንፁሃን ለመግደል አይደለም። እንደሱ ቢሆንማ ኦነግ በወለጋ ዉስጥ ላለፉት 40 አመታት ሲንቀሳቀስ ነበር። ለምን ታዲያ ያኔ የዚህ አይነት ተመሳሳይ ድርጊት አልፈፀመም። ይህ መንግስት እኛን ለማጥላላትና አሸባሪ ለማሰኘት ባለፉት አመታት በወሎና በከረዩ አባገዳዎች ላይ የተፈፀሙትን የጅምላ ጭፍጨፋዎች ጨምሮ በእኛ እንዳመኻኘ፤ ሁሉንም አሁንም ለራሱ ርካሽ ፖለትካ ሲባል እራሱ በኦነግ ስም አሰልጥኖ ያሰማራቸዉ “ጋቸነ ስርና” ወይም አብዮት ጠባቂ የተባሉ ነፍሰ ጓደዮች የፈፀሙት ወንጀል ነዉ” በማለት ያስረዳሉ፡፡ በርግጥ እንዳሉት መንግስት ኮሬ ነጌኛ በሚል ያቋቋመው አፋኝና ገዳይ ቡድን የከረኞ አባገዳዎችንና ሌሎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተወቀሰበትን ግድያዎች እንደፈጸመ ሮይተር በምርመራ ሪፖርቱ አስነብቧል፡፡ በአጠቃላይ ጋቸነ ስርና የስርዓቱ ጠባቂ ሆኖ መንግስት ድንገት ወታደሩ ቢከዳው ወይም ቢዳከምበት ከእነዚህ ሃይላት መሳሪያ በማስታጠቅ( አንዳንዶቹ ታጥቀዋል) መንግስት ጠላቴ በሚለው ሃይል ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ በማድረግ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድንገባ የሚያደርግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ልክ እንደ ሩዋንዳው ኢንተርሃሙይ የዘር ጭፍጨፋ እንዲያደርግ ቢታዘዝ ሙሉ አቅም ያለው ጥፋት ሃይል ነው፡፡ 

አብዮት ጠባቂ

በተመሳሳይ በመዲናዋ አዲስ አበባ በተመሳሳይ የተቋቋመው የሰላም ሠራዊት የተባለ ህዝባዊ አደረጃጀት ሲሆን ልክ እንደ ጋቸነ ሲርና( Gaachana sirnaa) የስርዓቱ ጠባቂ እንዲሆንላቸው ያቋቋሙት ነው፡፡ ይህ የሰላም ሠራዊት በትግራዩ ጦርነት ጊዜ መንግስት ያሰጉኛል የሚላቸውን “ፀጉረ ልውጦች” ወይም የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በየሰፈሩ ቤት ለቤት በመሄድ፣ መንገድ ላይ በማቆም ብዙ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን እየጦቆሙ በማሲያዝና አለፍ ሲልም ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩ ናቸው፡፡

እንደ አዲስ አበባ አስተዳደር የሰላም ሠራዊቱ አባላት ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ሥጋቶችን በትግል በማክሸፍ ለአዲስ አበባ ሰላም ማስጠበቅ ነው፡፡ እንደ እነሱ ገለጻ “የሠው ልጅ እንስሳት፣አዕወፋት እንዲሁም በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ሰላምን ይሻሉ። ነገን ተስፋ የሚያደርግ፣ለሕይወቱ ቀጣይነት የሚያስበው የሰው ልጅ ደግሞ ሰላምን በጣም ከሚፈልጉ እንስሳት መካከል አንዱ ነው። የሆነው ሆኖ ሰላምን የሚወዱ፣የሚፈልጉ እና ለሰላም የሚተጉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ደግሞ ከሰላም ሳይሆን ከሁከት እና ብጥብጥ ትርፍ ለማግኘት የሚያስቡ የፀረ ሰላም ኃይሎችም ከሰው መካከል አይጠፉም። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የሁለቱም ጎራ ተፋላሚዎች በዚህ ዓለም ላይ ሲታገሉ ይታያሉ። ለዚህም ነው በተለያዩ ዓለማት የሠላም አስከባሪ ኃይል እየተባለ የሚደራጀው፤ ሰላም የሚነሳ ኃይል ስላለ ነው የሰላም ኃይል የሚቋቋመው። በአገራችንም የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሕብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት የማድረግ ተልዕኮውን ለማሣካት ከፈጠራቸው አደረጃጀቶች መካከል የሠላም ሠራዊት አንዱ ነው።” በማለት ማብሪሪያ ይሰጣሉ፡፡ 

አብዮት ጠባቂ  _ 2

የሰላም ሠራዊቱ የከተማው አስተዳደር ስጋትና ችግር ሊገጥመኝ ነው ብሎ ሲያስብ በከተማው ውስጥ በሚገኙት 11 ክፍለ ከተሞች ውስጥ በቀንና በማታ ያሰማራል፣ መረጃ እንዲያሰባስቡ ያደርጋል፣ ለመረጃ ተቋማት በየሰፈሩና በየቤቱ  ፀረ-መንግስት አቋም ያላቸውን ሰዎች በመጦቆም ማሲያዝና ከመንግስት የሚሰጣቸውን ትዛዞች ያስፈጽማሉ፡፡ ለዚህም ተግባራቸው መንግስት አበል፣ ዘይትና ሌሎች ድጋፎች ሲኖሩ ይሰጣቸዋል ወይም ቅድሚ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡

በየጊዜው ስልጠና በማዘጋጀትና በማሰልጠን መንግስት በደንብ ታማኝና አገልጋይ እንዲሆኑና የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር በመንግስት ላይ የተለዩ ሀሳቦችና ተቋውሞዎች እንዳይነሱ ለማፈን ለሚያደርገው አስተዋጽኦ በዘላቂነት የመንግስት ስልጣን ለማስቀጠል በርትተው ይሰራሉ፡፡ እንደአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አህዝ ከሆነ የሰላም ሠራዊቱ ብዛት ከአራት መቶ ሺ በላይ ሲሆን መንግስት ባለስልጣናት በፈሩ ቁጥር ቀን ከለሊት ጥበቃ ውለው ያድራሉ፡፡

ከዚህ እንደምንረዳው የብልጽግና መንግስት ምን ያህል ስጋት ያለበት እንደሆነና ባለው የፀጥታ መዋቅር ተማምኖ መተኛት የማይችልና አሁን እያደረገ ያለው ልክ የደርግን የመጨረሻ ጊዜ በሚያስታውስ መልኩ ህዝብን ወደ ማስታጠቅ የተኬደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህም ህዝቡ በእነዚህ የስርዓቱ ጠባቂዎች ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰትና ግድያ እየደረሰበት ይገኛል፡፡ መንግስት እነዚህን ህገ ወጥ አደረጃጀቶችን በማፍረስና ችግሮችን በሃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ለእርቅና ለድርድር በሩን ክፍት በማድረግ በሀገሪቷ ላይ ሰላም እንደሰፍን ቢሰራ፤ የተበደሉትን ለመካስ እውነተኛ በሆነ የሽግግር ጊዜ ፍትህ  መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የሀገሪቷን ችግር ከጠብመንጃ አፍ ለማግኘት መሞከሩ ያስከፈለንን ዋጋ ባለፊት ስድስት አመታት በተግባር ስላየነው፤ ለሰላም የምንሰጠውን ቦታ ከፍ በማድረግ፤ ጊዜዊ ጥቅማችንና የፖለቲካ ስልጣናችን ሳይሆን ነገ ልጆቻችን የሚረከቧት ነጻነትና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር ማስረከቡ ላይ ማቶከሩ የተሻለ ይሆናል፡፡ ላለፋት ስድስት አመታት ስንጋደል ከርመናል በዚህም ከሚባለው በላይ ተዳክመናል፣ ኢኮኖሚያችን ደቋል፣ በፍጥነት እያደገ ካለሀገር በፍጥነት እየፈረሰ ወዳለ  ሀገርነት ተሸጋግረናል፡፡ ስለዚህም ቆም ብሎ ማሰብና ለእርቅና ለሰላም በራችንን መክፈት ይኖርብና፤ይገባልም፡፡

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here